Administrator

Administrator

  ኢትዮጵያ ባለመረጋጋት ከአፍሪካ 10ኛ ደረጃ፤ ፊንላንድ በመረጋጋት ከአለም 1ኛ ደረጃ ይዘዋል ተብሏል

      ፈንድ ፎር ፒስ የተባለውና ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው የጥናት ተቋም በቅርቡ ይፋ ባደረገው የ2017 የዓለማችን አገራት ያለመረጋጋት ደረጃ ሪፖርት መሰረት፣ ደቡብ ሱዳን ከአለማችን መረጋጋት የራቃትና የመፈራረስ ከፍተኛ ዕድል ያላት ቀዳሚዋ አገር ሆናለች፡፡
አስራ ሁለት ያህል ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁልፍ አመልካቾችን መሰረት አድርጎ የአለማችንን አገራት የመፈራረስ ዕድል ተጋላጭነት ደረጃ የሚያስቀምጠው ተቋሙ፣ በ2017 ሪፖርቱ ካካተታቸው 178 የአለማችን አገራት ደቡብ ሱዳንን እጅግ በከፋ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ሲል በቀዳሚነት አስቀምጧታል፡፡ ባለመረጋጋት ከደቡብ ሱዳን ቀጥሎ በቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት የአፍሪካ አገራት ሶማሊያ፣ መካከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ ናይጀሪያ፣ ዚምባቡዌ እና ኢትዮጵያ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ገልጧል፡፡
በተቋሙ ሪፖርት መሰረት፤ እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም በመረጋጋት ከአለማችን አገራት የአንደኛ ደረጃን የያዘቺው ፊላንድ ስትሆን፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዴንማርክና አየርላንድ ይከተላሉ፡፡
ከፍተኛ ያለመረጋጋት ችግር ካለባቸው የአለማችን አገራት መካከል ሶማሊያ፣ መካከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ የመንና ሶርያ እንደሚጠቀሱ የገለጸው ሪፖርቱ፣ ከአምናው ደረጃቸው አንጻር የመረጋጋት ሁኔታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ካሽቆለቆለባቸው የአለማችን አገራት መካከል ሜክሲኮ፣ ኢትዮጵያና ቱርክ እንደሚገኙበትና ኢትዮጵያ ባለመረጋጋትና ለመፈራረስ ተጋላጭ በመሆን ከአፍሪካ አገራት 10ኛ ደረጃ መያዟንም አመልክቷል፡፡
ተቋሙ አመታዊ ሪፖርቱን ማውጣት ከጀመረ 13 አመታት ያህል ቢሆነውም፣ ከአጠናን ስልቱ፣ ከሚዛናዊነቱና ሊገመቱ የሚችሉ ሁነቶችን ወይም ክስተቶችን ቀድሞ ከመተንበይ አቅሙ ጋር በተያያዘ በስፋት እንደሚተች ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

  አለማቀፍ የሆቴሎች ኔት ወርክ የተሰኘው ተቋም፤እንግዶች የሰጧቸውን የግብረ መልስ አስተያየት መነሻ በማድረግ፣ ሒልተን አዲስ ሆቴልን “የኢትዮጵያ የአመቱ ምርጥ ሆቴል” ሲል ሽልማት አበርክቶለታል፡፡
በመላው ዓለም በአለማቀፍ ሆቴሎች የሚጠቀሙ ደንበኞች በሚሰጡት የአገልግሎት እርካታ አስተያየት፤ ከኢትዮጵያ ሒልተን ሆቴል ጥሩ መስተንግዶ እንዳለው መመስከራቸውን ተከትሎ የእውቅና ሽልማት እንደተበረከተለት፣ የሆቴሉ የማርኬቲንግና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሃበን ክልሞን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ ለሽልማቱ ሆቴሉ ያለው አለማቀፍ እውቅና አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ኀላፊዋ አልሸሸጉም፡፡  
ባለፈው ዓመት በተደረገው የኢትዮጵያ ሆቴሎች የደረጃ ምዘና፣ሒልተን አዲስ ባለ 3 ኮከብ ደረጃ ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡

  በደራሲና ጋዜጠኛ መልሰው በሪሁን የተሰናዳው ‹‹እኔ የሌለው እኔ›› የተሰኘ መፅሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ መፅሀፉ ‹‹ክብ ታሪኮች››፣ ‹‹አበቃቀል›› እና ‹‹መብተክተክ›› በሚሉ ሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን እነዚህ ሶስት ሀሳቦች በአንድም በሌላም መንገድ የሚገናኙና የሚሰናሰሉ በመሆናቸው ‹‹Tripod of life›› የሚለው ሃረግ እንደሚገልፃቸው ደራሲው በመግቢያው አስፍሯል፡፡
ሶስቱም ክፍሎች በሶስቱ ክብ ሀሳቦች የተሳሰሩ ፍልስፍናዊ ሀሳቦች ያሉበት፤ በመብተክተክ ሀሳቦችን የሚፈትሹ ናቸው ተብሏል፡፡ በመፅሀፉ ‹‹የኔ ፊርማ በታችም መስመር በላይም መስመር አለው››፣ ‹‹የፊት ቅርፅ እና እሳቤ››፣ ‹‹የማፍቀር አርኪ ገፅታ››፣ ‹‹የአባቴ ሱሪዎች›› የተሰኙና ሌሎችንም ወጎች አካትቷል፡፡ ደራሲው መልሰው በሪሁን በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ቴሌቪዥን በጋዜጠኝነት እያገለገለ ይገኛል፡፡

 በደራሲ አበበ ዓለማየሁ የተፃፈውና በኩባና በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መካከል ያለውን የግንኙነት ደረጃ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተዋውቃል የተባለው ‹‹የማይረሳ ውለታ›› መፅሀፍ ዛሬ ጠዋት ከ2፡30 ጀምሮ በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
   መፅሀፉ በዋናነት በወራሪው የሶማሌ ጦር አገር ስትወረር አገራችንን ለመደገፍ የመጡትን የኩባ ወታደሮችና የከፈሉትን መስዋዕትነት እየዳሰሰ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ኩባ ሄደው በመማር አገራቸውን እንዴት እያገለገሉ እንዳሉና የሁለቱ አገራት መንግስታት ህዝቦች ያላቸውን የጠበቀ የወዳጅነት ግንኙነት ያሳያል ተብሏል፡፡ አንድ የስነ ፅሁፍ ባለሙያም በመፅሀፉ ዙሪያ ዳሰሳ ያቀርባል ተብሏል፡፡ መፅሀፉ በ232 ገፆች ተቀንብቦ፣ በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው አቶ አበበ አለማየሁ ካሳ ኩባ ሄደው እንዲማሩ እድል ካገኙት የዘመኑ ተማሪዎች አንዱ እንደነበሩ
በመፅሀፉ ጀርባ ባሰፈሩት ማስታወሻ ገልፀዋል፡፡

    የሚከተለውን የፃፉልን እጓለ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡
“የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ነው፡፡
በግሪክ ሜቶሎጂ የሚገኝ አንድ ትልቅ ተረት አለ፡፡
(ይህም ስለ ፕሮሚሴቭስ የሚነገረው ነው፡፡ ትልቅ ምሥጢር በውስጡ ደብቆአል፡፡ ፕሮሚሴቭስ በሚል አርእስት የቀድሞውን ተረት መሠረት በማድረግ፣ ኤስሂሎስ የሚባለው ትራጀዲን የፈጠረ ባለቅኔ፣ አንድ ትሪሎጂ - ማለት ሦስት ድራማዎች ጽፎአል፡፡ እሱን በመከተል ሸሊ ባይረን ጌቴ ጽፈዋል። የፕሮሚሴቭስ መንፈስ በአውሮፓ የመንፈስ ታሪክ ውስጥ መካከለኛውን መሥመር የያዘ ነው፡፡ አሁን የጠቀስናቸው ሰዎች በአውሮፓ የሥነ ጽሑፍ ጠፈር ላይ በጣም ጐልተው የሚታዩ ከዋክብት ናቸው፡፡)
የፕሮሚሴቭስ ተረት እንደሚቀጥለው ነው፡፡ ፕሮሚሴቭስ በከፊል አምላክ፣ በከፊል ሰው የሆነ ሕላዌ ነበር፡፡
በከፊል አምላክ እንደመሆኑ ዐሥራ ሁለቱ የግሪክ አማልክት በኦሉምቦስ ተራራ ሆነው ስለ ሰውና ስለ ዓለም አስተዳደር ሲመክሩ ይሰማ ነበር፡፡ በከፊል ሰው እንደመሆኑ የሰው ሥቃይና መከራ በጣም ያሳዝነው፣ ይጸጽተው ነበር፡፡ ሰው ቤት ንብረት ሳይኖረው በበረሃ፣ በጫካ፣ በዱር፣ በገደል፣ በዋሻ፣ በቁር፣ በሀሩር እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር፡፡ ይህ መሆኑ አማልክት መክረው ዘክረው፣ ለሰው የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ብርሃንን የሰጡት እንደሆን ከዕለታት ባንድ ቀን ሰጭነታቸውን ክዶ፣ በነሱ ላይ በመነሳት የሚያምፅ መሆኑን በመረዳት፣ ብርሃንን ከሰዎች ደብቀው ከማይደርሱበት ቦታ በመሠወራቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች በጭለማና የርሱ ተከታይ በሆኑት ችግሮች ሥር ሲሰቃዩ ይኖራሉ፡፡
ይህ የሰዎች መራራ ዕድል ወገናቸው በሚሆን በፕሮሚሴቭስ ላይ ርህራሄ አሳድሮበት ብርሃንን አማልክት አርቀው ከደበቁበት ሰርቆ ለሰዎች ወስዶ ሰጠ፡፡ ያንጊዜ ማናቸውም ነገር ግልጽ ሆኖ ታያቸው፡፡ በብርሃን ምክንያት ጥበብና ማናቸውም የዕውቀት ስልት ስለተገለጸላቸው፣ ራሳቸውን ከገዛ ራሳቸው በተገኘው ዘዴ ለማስተዳደር ጀመሩ፡፡
ፕሮሚሴቭስን ግን ለሰዎች ብርሃንን ሰጥቶ፣ በጐ በመሥራቱ አማልክት ቀንተው፣ በብርቱ ስቃይ ይቀጣ ዘንድ አዳኝ ከማይደርስበት ገደል ላይ ከቋጥኝ ድንጋይ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ፣ አሞራ ለዘለዓለም እንዲበተብተው ፈረዱበት፡፡
*   *   *
ከፕሮሚሴቭስ ዕጣ -ፈንታ ይሰውረን፡፡ ይህ ፕሮሚሴቭስ የሰውን ዕድል ለማሻሻል የሚታገሉት የዕውቀት ሰዎች፣ የመምህራንና የሊቃውንት ምሳሌ ነው፡፡ እሱ ብርሃንን አማልክት ከደበቁበት ቦታ ወስዶ ለሰው እንዳበረከተ፣ የዕውቀት ሰዎችም ዕውቀት በመለኮታዊ ምሥጢርነት ከሰው ተደብቃ ስትኖር ሳለ በብዙ ትግል አግኝተው፣ ከገዛ ራሳቸው አሥርፀው የወገኖቻቸውን ዕድል ለማሻሻል ያበረክታሉ፡፡ ዋጋቸውም ሌላ ሳይሆን ስቃይ መከራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሶክራቲስ በመርዝ ተገድሎአል፡፡ ጆርዳኖ ብሩኖ የጧፍ ቀሚስ ተጐናጽፎ በእሳት ተቃጥሎአል፡፡
እነዚህ ሰዎች እንደ ጧፍ መብራት ማለት ናቸው፡፡ ራሳቸው ነደው ተቃጥለው ያልቃሉ። ለሌሎች ግን ብርሃን ይሰጣሉ፡፡ የፕሮሜሴቭስ ምሳሌ አንድ ትልቅ ሕግ ጉልህ አድርጐ ያሳያል። ይህም “ዕውቀት በሥቃይ የሚገኝ ነው” (Learn through suffering) የሚል ነው፡፡  
ልጆቻችንን ይህን ለሌሎች ስንል መታገል፣ መሰዋት፣ ማድረግ እንደምን እናስተምር? ብርሃን የሚያመጡ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡
ዕውቀትን ለሀገር ለማጎናፀፍ የሚጥሩ መምህራን ያሹናል፡፡ የዕውቀት ብርሃን ለመጪው ትውልድ ታትሮ ለማለፍ ፣ ልብና ልቡና ይፈልጋል፡፡ አረፍ ብሎ ወዴት እያመራን ነው ብሎ መጠየቅን ግድ ይላል፡፡ ዕውቀት ከትምህርት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከኑሮአችን፣ ከልምዳችን፣ ከትግላችን እንጂ። ይህ ወረድ ብሎ አፈሩን መዳሰስን፣ ህዝቡን ማግኘትን፣ የልብ ትርታውን ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ምን ጎደለው? ስለዚህ ጉዳይ ግንዛቤ አለ ወይ? በምን ዓይነት መንገድ የጎደለውን ዕውቀት ለማሟላት እችላለሁ? ማለትን ይጠይቃል፡፡ መንገዱን ካገኙ በኋላም፤ ጧት ማታ ሳይታክቱ መታተርን ይጠይቃል። ይህን ከልብ ካደረግን አገር መውደድ ገብቶናል፡፡ ያንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ብቻ አገርን ከገባችበት ማጥ አያወጣትም፡፡ “ኦሆ በሀሊ፣ ያርጓጅ አናጓጅ፣ በደመቀበት ቦታ ሁሉ የሚያጨበጭብ አንድም የተለየ ነገር ለማስገኘት አይችልም” ይላሉ ዶክተር እጓለ፡፡ ሉቃስን በመጥቀስም እንዲህ ይሉናል። “ውሰብአ አቴናሰ ወእለ ይነግድ ኲሎሙ ህየ በእደ ትካዘ አልቦሙ ዘእንበለ ዳእሙ ለአፅምኦ ወነቢብ ዘሐዲስ”። አቴናውያን አዲስ ነገር ከመስማት ወይም ከመናገር በስተቀር ሌላ ምኞት አልነበራቸውም። ባለው ላይ ቆሞ አዲስ ነገር ለማግኘት የሚጣጣር ሰው ሁል ጊዜ ወደፊት ይሄዳል - ማለት ነው፡፡
እንደ አቴናውያን፤ በአለው ላይ ቆመን አዲስ ነገር ለማግኘት የምንጣጣር ከሆነ ወደፊት እንሄዳለን። ትምህርትንና ዕውቀትን መሰረቱ ያደረገ ትውልድ ከፈጠርን የራሱን ጥያቄ፣ የራሱን ነገ ራሱ ይወልዳል። የሚኖርበት ቤት ሲጠበው ቤቱን ራሱ አስፋፍቶ ይሰራዋል፡፡ ሁሉን እኛ እናድርግልህ ካልነው - ሁሉን ቀላቢ እንሁንለት ካልን፤ ዞሮ ዞሮ ተቀላቢ ትውልድ ነው የምናፈራው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት - Spoon – Feeding mentality ይጠቀልለዋል - የአጉሩሱኝ አስተሳሰብ እንደማለት ነው፡፡
ለወጣቱ የመንግሥቱ ለማን ግጥም “መርፌ - ትሰራለህን” ማንበብና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ የአባት ነው፡፡
በየትኛውም አቅጣጫ! ወጣቱ በሥነ ምግባር ረገድ፣ የሰውን ፀባይና ችሎታ በሚመረምር መልኩ አዕምሮው መታነፅ አለበት፡፡ ዕውቀትን መሰረት ሳያደርግ ለትግል ብቻ ብናዘጋጀው የፕሮፖጋንዳ ወይም የአጀንዳ ማስተላለፊያ አሸንዳ ቱቦ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በታሪክም የታየ ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮው የእያንዳንዱ መብትና ተግባር የሚጠበቅበት፣ “ሰው በንፁህ ተምኔቱ መሰረት በሰላም ተደስቶ የሚገኝበትን ሕግ” ይዞ መጓዝ እንዳለበት ሊረዳ ይገባል፡፡ ህይወት እንደ ጂኦሜትሪ ትምህርት በቀጥታ መሥመር የተሞላና የተለካ አይደለም፡፡ ቀላል ሂሳብም አይደለም፡፡ እንዴት እንደሚገነባ፣ ከራሱ ህይወት ተነስቶ እንዴት ለማደግ እንደሚችል፣ ትምህርትን ባሰላሰለ መልኩ ማጤን እንጂ “ሳይገሉ ጎፈሬ፣ ሳያረጋግጡ ወሬ” መሆን የለበትም፡፡ እስከ ዛሬ አጭር ተመልካች፣ አጭር ተጓዥ ሳናደርገው (Myopic) አልቀረንም፡፡ አጭር ግቦች አጭር ያደርጉናል!
አንድ ደራሲ እንደሚለው፤ “… የውጪ ጉዳዮችን ካገር ውስጥ ኃይሎች አሰላለፍ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከጥበብ ሽግግርና ከውጪ ርዳታ፣ የቋንቋ መዘበራረቅና ጉራማይሌነትን ከባህላዊ ድቀት፣ የሐሳብ ነፃነትን ከጋዜጣ፣ ራዲዮና አጠቃላይ ውይይት ምህዳር መጥበብ ጋር…” የሚያነፃፅር ወጣትም ሆነ አዋቂ ያስፈልገናል፡፡
ወጣቱ አገሩን ያውቅ ዘንድ ጥልቅ አስተሳሰብ፣ ረዥም ርዕይና በግብረገብ የታነፀ ድፍረትና መስዋዕትነት ያስፈልገዋል፡፡ መጪውን አዲስ ዓመት እንዲህ እናስብ! የሀገራዊነት፣ የወገን አሳቢነት፣ የኢ-ራስ - ወዳድነት፣ የሁሉን - አውድም አስተሳሰብ አለመያዝ፣ ሁሉን - ረጋሚ ያለመሆን አመለካከት፣ ኢ-ፅንፋዊነት ወዘተ እንደ መርህም፣ እንደ ኑሮም ሊሰርፁበት ይገባል፡፡ አለበለዚያ አፋሮች እንደሚሉት፤ “አገሩን የማያውቅ ሰው፣ መሬትን እየረገጠ መሬትን ይረግማል” ይሆናል፡፡   

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲንጋፖር የቀጥታ በረራ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ። አየር መንገዱ ባለፈው ረቡዕ ማታ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በሚገኘው ቢሮው በሰጠው መግለጫ፤ የቀጥታ በረራው በሳምንት አምስት ቀናትና በጣም ፈጣን በሆነ ሰዓት ከሲንጋፖር ወደ 53 የአፍሪካ አገራትና ከአፍሪካ አገራት ወደ ሲንጋፖር መብር የሚያስችል መሆኑን የአየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል፡፡ ሲንጋፖር በአሁኑ ሰዓት በጣም ያደገች፣ 5 ሚ. ህዝብ ያላትና የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከፍተኛ ከሆኑ የዓለም አገራት በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ በመሆኗ የቀጥታ በረራ አገልግሎቱ በኢኮኖሚው እድገትም ሆነ የቱሪስትን ፍሰት ከመጨመር አኳያ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብሏል - ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡   
ሲንጋፖር አየር መንገድ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የስታር አሊያንስ አባል በመሆኑ ሁለቱ አየር መንገዶች በመተባበር ትልቅ ስራ መስራት እንደሚችሉም አቶ ተወልደ ተናግረዋል። ሲንጋፖርን ጨምሮ አብዛኞቹ የእስያ አገሮች ወደ አፍሪካ ቀጥታ በረራ እንደሌላቸው የገለፁት ኃላፊው፤ ከጆሀንስበርግና ከኬፕታውን ወደ ሲንጋፖር የሚበር አንድ አየር መንገድ እንዳለና አፍሪካንና ሲንጋፖርን የሚያገናኝ ይሄኛው ሁለተኛው መስመር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ሲንጋፖር ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ እንደሌላት ተጠቅሶ፣ የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምን ይመስላል በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሥራ አስፈጻሚው፤ ”ሲንጋፖር እዚህ ኤምባሲ የላትም፤ የሲንጋፖር የኢትዮጵያ አምባሳደርም የሚቀመጠው ሲንጋፖር ነው፤ ምንም እንኳን ኤምባሲ እዚህ ባይኖራቸውም ሁለቱ አገሮች ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው፤ የቀጥታ በረራው ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ መዳረሻዎች ከ95 በላይ የደረሱ ሲሆን ባለፈው ሰሞን ወደ ቼንዶ፣ መጋቢት መገባደጃ ላይ ቪክቶሪያ ፎልስ፣ ማዳጋስካር አንታናናሪቮ፣ እንዲሁም ኖርዌይ የቀጥታ በረራ ከፍቷል፡፡
ከሚያዝያ እስከ ግንቦት ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ አምስት አዳዲስ የቀጥታ በረራ መስመሮችን መክፈቱንም አቶ ተወልደ ገ/ማርያም ገልፀዋል፡፡


  አባቱ ቦብ ማርሊ ሲሞት 2 ዓመቱ የነበረው የመጨረሻው ልጅ ዲሚያን ጁኒየር ጎንግ ማርሊ፤ ማክሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በግዮን ሆቴል ኮንሰርት እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡
አዘጋጆቹ ባለፈው ረቡዕ በራማዳ አዲስ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ዲሚያን 20 የሬጌ ሙዚቃ አባላትን ይዞ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ እዚህ ካሉት አርቲስት ዘለቀ ገሠሠና አርቲስት ጆኒ ራጋ ጋር ብላክ ኖት ሂፕ ሃፕን በማካተት፣ “ዋን ላቭ” የተሰኘ የዓመቱን ትልቅ ኮንሰርት እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
በበርካታ የዓለም አገራት (ፓሪስ፣ ለንደን፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሼልስ …) እየዞረ ኮንሰርት በማቅረብ ላይ የሚገኘው ዲሚያን፤ በ1976 (እ.ኤ.አ) ‹‹ሚስ ዎርልድ›› ከነበረችው አሜሪካዊት ሲንዲ ብረክስፓር የተወለደ ብቸኛው የቦብ ማርሊ ልጅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአገራችን ኮንሰርት ማካሄድ የተለመደው ቅዳሜና እሁድ ነው ያሉት አዘጋጆቹ፤ የዚህኛው ኮንሰርት ማክሰኞ መሆን ያልተለመደ ስለሆነ ቢራ ፋብሪካዎች ስፖንሰር ለማድረግ ፈቃደኞች አልሆኑም ብለዋል፡፡ የኮንሰርቱ መግቢያ ዋጋ 400 ብር፣ ቪአይፒ 600 ብር ሲሆን ቀድመው ለሚገዙ ውሱን ቲኬቶች በ350 ብር እንደሚሸጡ ተነግሯል፡፡
ዲሚያን፣ በሚመጣው ረቡዕ በኬንያ ኮንሰርት አቅርቦ በዚያው ወደ ሲሼልና ደቡብ አፍሪካ እንደሚሄድ ጠቅሰው፣ አዲስ አበባ የሚገባው ሰኞ ማታ እንደሆነ፣ በማግስቱ ማክሰኞ ኮንሰርቱን አቅርቦ፣ ‹‹አገሬ ናት›› የሚላትን ኢትዮጵያን እንደሚያይ፣ ረቡዕ ወደ ላሊበላ እንደሚጓዝ፣ ከተቻለም ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ለማየት እንደሚሞክር፣ ከዚያ መልስ ወደ ገርጂ መሄጃ ኢምፔሪያል አደባባይ የሚገኘውን የአባቱን የቦብ ማርሊን ሀውልት እንደሚጎበኝና ዓርብ በ20 የአውሮፓ አገሮች ኮንሰርት ለማቅረብ ወደ ለንደን እንደሚጓዝ ገልጸዋል፡፡   

   “በዘመኔ” የተሰኘውና የተለያዩ የሰርግ ዘፈኖችን ያካተተው አዲሱ የድምጻዊ ሃይልዬ ታደሰ አልበም፤ ከትናንት በስቲያ ምሽት በሳፋሪ አዲስ ሆቴል በተከናወነ ስነ-ስርዓት በይፋ ተመርቋል፡፡
ለድምጻዊው አራተኛ ስራው በሆነው በዚህ የሙዚቃ አልበም ውስጥ 9 የሰርግ ዘፈኖች የተካተቱ ሲሆን፣ ሞገስ ተካ፣ ቴዲ አፍሮ እና አሌክስ ይለፍ በዜማ ደራሲነት ሲሳተፉበት፤ በግጥም ደግሞ ሞገስ ተካ፣ መሰለ ጌታሁን፣ ይልማ ገብረ አብ እና ቴዲ አፍሮ ተሳትፈውበታል፡፡
ድምጻዊ ሃይልዬ ታደሰ በ1991 ዓ.ም ካወጣውና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ካተረፈው “አንቺን ይዞ” ከተሰኘው የመጀመሪያ አልበሙ በተጨማሪ፣ “ሁሌ ሁሌ” እና “ፍቅር” የተሰኙ የሙዚቃ አልበሞቹን ለአድማጭ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
የድምጻዊው አድናቂዎች፣ ታዋቂ ድምጻውያንና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በተከናወነው የአልበሙ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ድምጻዊውና ሌሎች ታዋቂ ድምጻውያን ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን ሌሎች ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችም ተከናውነዋል፡፡

 በ2016/17 የውድድር ዘመን የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች  ሲገባደዱ  ቼልሲ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ    ፤ ጁቬንትስ በጣሊያን ሴሪ ኤ ፤ ባየር ሙኒክ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ፤ ሪያል ማድሪድ በስፔን ላሊጋ እንዲሁም ሞናኮ በፈረንሳይ ሊግ 1 ሻምፒዮንነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከ5ቱ ታላላቅ ሊጎች ባሻገር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ  በዩሮፓ ሊግ ማንችስተር ዩናይትድ ከአያክስ ተፋልመዋል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ 2ለ0 በማሸነፍ ለመጀመርያ ጊዜ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ያሸነፈ ሲሆን እንዲሁም በሊጉ አምስተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቁ በቀጣይ የውድድር ዘመን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን አሳክቷል፡፡ በሌላ በኩል ከሳምንት በኋላ በ62ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ  የስፔኑ ላሊጋ ሻምፒዮን  ሪያል ማድሪድ ከጣሊያኑ ሴሪ ኤ አሸናፊ ጁቬንትስ  ይፋጠጣሉ፡፡
በቅርቡ ይፋ ባደረገው  ሪፖርት The CIES Football Observatory የተባለ የእግር ኳስ ጥናት አድራጊ ተቋም በ5ቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች እንደተለመደው የኃይል ሚዛኑ ከታላላቅና ውጤታማ ክለቦች ሊወጣ አልቻለም፡፡ በተለይ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከ1993 እኤአ ወዲህ በአዲስ አሰራር መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየሊጎቹ የገቢ ሁኔታዎች በከፍተኛ ደረጃ ያደጉ ቢሆንም፤ በትልልቅ እና ትንንሽ ክለቦች መካከል ያለው የሃይል ሚዛን ሊጠብብ ግን አልቻለም፡፡  
በሲአይኢኤስ ሪፖርት መሰረት  ከ1993 እኤአ ወዲህ በነበሩት  25 የውድድር ዘመናት በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች  ሻምፒዮን የሆኑ ክለቦች በዝርዝር ሲጠቀሱ የጥቂት ክለቦች የበላይነት ቀጥሏል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 6 ፤ በጣሊያን ሴሪ ኤ 5፤ በስፔን ላሊጋ 5፤ በጀርመን 6 እንዲሁም በፈረንሳ ሊግ 1 10 የተለያዩ ክለቦች የሻምፒዮናነት ክብሩን ባለፉት 25 የውድድር ዘመናት ማሳካታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በሻምፒዮናነት የጨረሰው  ቼልሲ ሲሆን፤  ባለፉት 25 የውድድር ዘመናት በአጠቃላይ የሻምፒዮናነት ክብሩን ለማግኘት የበቁት 6 ክለቦች ናቸው፡፡ ማንችስተር ዩናትድ 13 ጊዜ፤ ቼልሲ 5 ጊዜ፤ አርሰናል 3 ጊዜ፤ ማችስተር ሲቲ 2 ጊዜ እንዲሁም ሌስተር ሲቲ እና ብላክበርን ሮቨርስ እኩል አንድ ጊዜ የሊጉን የሻምፒዮናነት ክብር ተጎናፅፈዋል፡፡
በጣሊያን ሴሪ  ኤ ለስድስተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን የስኩዴቶውን ክብር ለመቀዳጀት ከጫፍ ላይ የደረሰው ጁቬንትስ ሲሆን፤ ባለፉት 25 የውድድር ዘመናት የስኩዴቶውን ክብር  ለመጎናፀፍ የበቁት አምስት ክለቦች ናቸው፡፡ ለ11 ጊዜያት የስኩዴቶውን ክብር በመቀዳጀት ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበው ጁቬንትስ ሲሆን ከ2012 ጀምሮ እስከ 2017 ለስድስት ተከታታይ ጊዜያት ሻምፒዮን መሆኑ ክብረወሰን ሆኖ የሚመዘገብ ነው፡፡  ለ6 ጊዜያት የሴሪኤውን የስኩዴቶ ክብር በመጎናፀፍ ኤሲ ሚላን ሲከተል፤ ኢንተርሚላን ለአምስት ጊዜ ፤ ላዚዮ እና ሮማ እኩል አንድ ጊዜ የስኩዴቶውን ክብር ተጎናፅፈዋል፡፡
በስፔን ላሊጋ ከ2012 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሪያል ማድሪድ ሲሆን 25 የውድድር ዘመናት 5 ክለቦች የሻምፒዮናነት ክብሩን አግኝተዋል፡፡ ባርሴሎና  በድምሩ ለ12 ጊዜያት የስፔን ሻምፒዮን በመሆን ቀዳሚ ሲሆን  ሪያል ማድሪድ ለ7 8 ጊዜያት ሻምፒዮን በመሆን በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ አትሌቲኮ ማሪድ እና ቫሌንሽያ እያንዳንዳቸው እኩል ሁለቴ እንዲሁም ዲፖርቲቮ አንዴ ዋንጫውን አንስተዋል፡፡
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የዘንድሮ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ባየር ሙኒክ ሲሆን፤ ባለፉት 25 የውድድር ዘመናት 6 የተለያዩ ክለቦች የሻምፒዮናነት ክብሩን አግኝተዋል፡፡ 16 የቡንደስሊጋ የሻፒዮንነት ክብሮችን በመሰብሰብ ግንባር ቀደም የሆነው ባየር ሙኒክ ሲሆን፤ ቦርስያ ዶርትመንድ  3 ጊዜ፤ ዌርደር ብሬመን ሁለት ጊዜ እንዲሁም ካይዘስላውተርን ፤ ስቱትጋርት እና ዎልፍስበርግ እኩል አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን ችለዋል፡፡
በፈረንሳይ ሊግ 1  ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሞናኮ ሲሆን ባለፉት 25 የውድድር ዘመናት 10 የተለየዩ ክለቦች ሻምፒዮኖች ሆነዋል፡፡  ኦሎምፒክ ሊዮን ለ7 ጊዜያት፤ ፒኤስጂ ለ4 ጊዜያት፤ ሞናኮ ለ3 ጊዜ፤ ናንትስ እና ቦርዶ እያንዳንዳቸው እኩል 2 እንዲሁም ኦክዜር፤ ሌንስ፤ ማሴይ፤ ሊል እና ሞንትፕሌየር እኩ 1 ሻምፒዮን ሊሆኑ ችለዋል፡፡
በሌላ በኩል በ2016/ 17 የውድድር ዘመን The CIES Football Observatory በሰራው ሪፖርት በተጨዋቾች ስብስብ የዋጋ ግምት ደረጃ ውዱ ክለብ የነበረው የእንግሊዙ ማንችስተር ዩናይትድ በ626 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ በ553 እና ማንችስተር ሲቲ በ533 ሚሊዮን ፓውንድ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ባርሴሎና በ423፤ ቼልሲ በ419፤ ፒኤስጂ በ397፤ ጁቬንትስ በ345፤ አርሰናል 332፤ ባየር ሙኒክ በ312 እንዲሁም ሊቨርፑል በ310 ሚሊዮን ፓውንድ የተጨዋቾች ስብስብ የዋጋ ተመናቸው እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
በውድድር ዘመኑ በ5ቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች  የእግር ኳስ ገበያው እስከ 25 ቢሊዮን ዩሮ የተንቀሳቀስበት ሲሆን በየሊጎቹ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ድምር ገቢ ከ15 ቢሊዮን ዩሮ በላይ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ  718 ፤ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ 316፤ በስፔን ላሊጋ 264፤ በጣሊያን ሴሪኤ 133 እንዲሁም በፈረንሳይ ሊግ 35 ሚሊዮን ዩሮ ተንቀሳቃሽ ትርፍ ይጠበቃል፡፡
የአምስቱ ሊጎች የተጨዋቾች ደሞዝ ወጭ  ከ7.4 ቢሊዮን ዩሮ በላይ የነበረ ሲሆን በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ እስከ 4.2 ቢሊዮን ዩሮ ወጥቷል፡፡  በትራንስፈርማርከት  በዝርዝር በሰፈረው መረጃ መሰረት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ላይ የተወዳደሩ 20 ክለቦች የነበሩት 521 ተጨዋቾች የዋጋ ተመናቸው 4.91 ቢሊዮን ዩሮ ፤ በስፔን  ላሊጋ የተወዳደሩ 20 ክለቦች  484 ተጨዋቾች የዋጋ ተመናቸው 3.65 ቢሊዮን ዩሮ ፤ በጣሊያን ሴሪ ኤ የተወዳደሩ 20 ክለቦች  529 ተጨዋቾች የዋጋ ተመናቸው 2.88 ቢሊዮን ዩሮ  ፤ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የተወዳደሩ 18 ክለቦች  506 ተጨዋቾች የዋጋ ተመናቸው 2.63 ቢሊዮን ዩሮ እንዲሁም በፈረንሳይ ሊግ 1  የተወዳደሩ 20 ክለቦች  553 ተጨዋቾች የዋጋ ተመናቸው 1.73 ቢሊዮን ዩሮ ነበር፡፡

   የአውሮፓ የቅርብ አመታት የሽብር መዝገብ፣ ከፓሪስ እስከ ማንችስተር

      አሁንም አውሮፓ ተሸበረች…
ባለፈው ሰኞ ምሽት በእንግሊዟ ማንችስተር ከተማ ሙዚቃን ሊያጣጥሙና መንፈሳቸውን ዘና ሊያደርጉ ከየአቅጣጫው የተሰባሰቡ የሙዚቃ አፍቃሪያን፣ በአንድ አዳራሽ ውስጥ ታድመው ነበር፡፡ በርካታ ወጣቶችና ህጻናት የታደሙበት የአሜሪካዊቷ አሪያና ግራንዴ የሙዚቃ ኮንሰርት ሞቅ ደመቅ ብሎ ወደ መገባደጃው ተቃርቧል፡፡
የሆነች ቅጽበት ላይ ግን…
አዳራሹን ያናወጠና ከሙዚቃው ድምጽ በላይ ጎልቶ ያስተጋባ፣ ያልተጠበቀ ፍንዳታ ድምጽ ተሰማ፡፡ ለሙዚቃ የታደሙት ተመልካቾች በድንገተኛው ፍንዳታ ተደናግጠው ነፍሳቸውን ለማዳን በየአቅጣጫው ተራወጡ፡፡ ጭንቅ ሆነ፡፡ ሁሉም ራሱን ለማዳን የቻለውን ሁሉ ማድረግ ያዘ፡፡
ከአይሲስ ጋር ግንኙነት እንዳለው በተነገረለት አጥፍቶ ጠፊ የተፈጸመውና የሽብር ቡድኑም ሃላፊነቱን እንደሚወስድ በይፋ ባስታወቀበት የማንችስተሩ የሽብር ጥቃት፤ 22 ያህል ሰዎችን ሲገድል፣ ሌሎች 59 ሰዎችን አቆሰለ፡፡ እንግሊዝ ብቻ ሳትሆን መላ አውሮፓ በድንጋጤ ክው አለች፡፡
የማንችስተሩ የሽብር ጥቃት እ.ኤ.አ ከ2015 ወዲህ በምዕራብ አውሮፓ አገራት የተፈጸመ 13ኛው ጥቃት ሲሆን፣ በእነዚሁ ጥቃቶች ከ300 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት እንደተዳረጉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ለአብዛኛዎቹ የሽብር ጥቃቶች ሃላፊነቱን የወሰደውም አሸባሪው ቡድን አይሲስ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ሽብር ከወትሮ በተለየ አምና እና ዘንድሮ አውሮፓን ደጋግሞ ሰለባው አድርጓታል፡፡ አህጉሪቱ ሽብርንና ሽብርተኞችን ለመዋጋት የቻለቺውን ያህል ታጥቃ ብትነሳም፣ ችላ መመከት እንዳቃታት ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሽብር ጥቃቶች ከፈረንሳይ እስከ ቤልጂየም፣ ከእንግሊዝ እስከ  ጀርመን በየአቅጣጫው መፈጸማቸውንና የከፋ ጥፋት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል፡፡
አምና እና ዘንድሮ ብቻ በአህጉሪቱ ከተፈጸሙት ዋና ዋና የሽብር ጥቃቶች መካከልም የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት አንድን ፖሊስ ለሞት የዳረገ ሲሆን፣ አሸባሪው ቡድን አይሲስ ለሽብር ጥቃቱ ሃላፊነቱን ወስዷል፡፡
በሚያዝያ መጀመሪያ በስቶክሆልም የተፈጸመው የሽብር ጥቃትም አምስት ሰዎችን ለሞት፣ ከ15 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለመቁሰል አደጋ ዳርጓል፡፡ ትልቅ መኪና ይዞ ጥቃቱን የፈጸመው ራክማት አኪሎቭ የተባለ ኡዝቤክስታናዊ ሲሆን፣ ግለሰቡ የአይሲስ አባል እንደነበረም ተናግሯል፡፡
በመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ ካሊድ ማሱድ የተባለ ግለሰብ፣ በታዋቂው የለንደኑ ዌስትሚኒስቴር ድልድይ አቅራቢያ በከፈተው የተኩስ ጥቃት አራት ሰዎችን ገድሎ፣ ሌሎች ከ40 በላይ የሚሆኑትንም አቁስሏል፡፡ በስተመጨረሻም ሊያመልጥ ሲሞክር ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ተገድሏል፡፡ አይሲስም እንደ ልማዱ ሽብሩን የፈጸምኩት እኔ ነኝ ሲል በኩራት አውጇል፡፡
ያለፈው አመት 2016 ሃምሌ ወር ለጀርመን የተደራራቢ የሽብር ጥቃትና የሃዘን ወር ነበር፡፡ በዚያው ወር በበርሊን ሆስፒታል ውስጥና በኡዝበርግ ባቡር ላይ የተፈጸሙትን የሽብር ጥቃቶች ጨምሮ በአንድ ሳምንት ብቻ አምስት የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡
በመጋቢት ወር 2016 መጨረሻም በቤልጂየም መዲና ብራስልስ እጅግ አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ በብራስልስ አውሮፕላን ማረፊያ እና በባቡር ጣቢያ አካባቢ የተፈጸሙት ሁለት የሽብር ጥቃቶች በድምሩ 32 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት ሲዳርጉ ከ300 በላይ የሚሆኑትንም ለመቁሰል አደጋ ዳርገዋል፡፡
በፈረንጆች አመት 2015 የመጀመሪያ ሳምንት በቻርሊ ሄቢዶ መጽሄት ዝግጅት ክፍል ቢሮ ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት 17 ዜጎቿን ያጣቺው ፈረንሳይ፣ ከወራት በኋላም 130 ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሌላ የሽብር ጥቃት አስተናግዳለች፡፡