Administrator

Administrator

30 ኢትዮጵያውያን ከየመን ጅቡቲ ገብተዋል
    በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የተፈፀመው ጥቃት  በማን እንደተፈፀመ እየተጣራ እንደሆነና  ከየመን ወደ አገራቸው ለመመለስ በኤምባሲው በኩል ከተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 30 ዜጎች  ጅቡቲ መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በየመን መዲና ሰንአ የሚገኘው  የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ጥቃቱ በማን እንደተፈፀመ እየተጣራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ተወልደ፤ በተፈፀመው ጥቃት በኤምባሲው ሰራተኞች ላይ ምንም የደረሰ  ጉዳት የለም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በየመን የሚገኙ ዜጎች ተመዝግበው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ባደረገው ጥሪ መሰረት፤ ከተመዘገቡት ውስጥ 12 ሴቶች፣ 11 ህፃናት እና 7 ወንዶች የተካተቱበት አንድ ቡድን ጅቡቲ መድረሱን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡
የመን ውስጥ በስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ የአየር ጥቃት ተደብድበው ህይወታቸው አልፏል በሚል የተሰራጩ ዘገባዎችን በተመለከተ አቶ ሙሉጌታ በሰጡት ምላሽ፤ “በኛ በኩል ባደረግነው ማጣራት በዚህ ሁኔታ የሞተ ሰው የለም” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የየመኑ የሁቲ አማፂ ቡድን ከኢራን የሚያገኘውን የወታደራዊ ቁሳቁስ ድጋፍ በቀይ ባህር በኩል በማሻገርና ለአማፂያኑ የወታደራዊ ስልጠና ቦታዎችን በአገሯ ላይ በማመቻቸት በተደጋጋሚ ስሟ የሚነሳው ኤርትራ፤ ሰሞኑን ተመሳሳይ ውንጀላ በሳኡዲ የመገናኛ ብዙሀን ተደርጎብኛል በሚል በሰጠችው ምላሽ፤ ውንጀላው መሰረተቢስ እንደሆነ ገልፆ የወሬው ምንጭም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ናቸው ስትል አጣጥላለች፡፡
አብዛኛውን የየመን ክፍሎች በመቆጣጠር የአገሪቱን መሪ ከስልጣን ያስወገደው የሁቲ አማፂያን ቡድን፤ ከኢራን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚነገር ሲሆን የሚያገኘውንም ድጋፍ በማስተላለፍና ለወታደራዊ ስልጠና ቦታ በመስጠት ኤርትራ በተደጋጋሚ ስሟ እንደሚነሳ አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ የሚዲያ የምርምር ተቋም ከጥቂት አመታት በፊት “ኢራን በቀይ ባህር የእንቅስቃሴ አድማሷን እያሰፋች ነው” በሚል ርዕስ  ባወጣው መረጃ፤  ኢራን ለሁቲዎች የምታደርገው የወታደራዊ ቁሳቁሶች ድጋፍ በኤርትራ በኩል እንደሚያልፍ ጠቁሞ ኢራን ሁቲዎችን የምታሰለጥንበት ካምፕ ኤርትራ ውስጥ ከየጊንዳዕ ከተማ በስተምስራቅ ደንጎሎ የሚባል ቦታ እንደሚገኝ አስታውቆ ነበር፡፡ ሰሞኑን የሳኡዲ የመገናኛ ብዙሀን፤ ሁቲዎች ከኢራን ለሚያገኙት ድጋፍ ኤርትራ ትብብር ታደርጋለች ሲሉ ዘግበዋል፡፡
“ዘገባው ከሙያዊ ስነምግባር ያፈነገጠ ነው” በማለት ባለአስር ነጥብ መግለጫ ያወጣው የኤርትራ መንግስት፤ ዜናውን መሰረተ ቢስ ሲል ያጣጣለ ሲሆን የመረጃው ምንጮችም የአፍሪካ ቀንድ አገራት እንደሆኑ ገልጿል፡፡ “ሻባይት” የተባለው የኤርትራ መንግስት ድረገፅ በበኩሉ፤ የዚህ መረጃ ምንጮች አንዳንድ የስለላ ተቋማትና የኢትዮጵያው ህወሓት ነው ብሏል፡፡
የኤርትራ መንግስት ባወጣው ባለአስር ነጥብ አቋም ውስጥ፤ የየመን ጉዳይ የራሷ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ የትኛውንም የውጭ ሀይል በመደገፍ ኤርትራ እንደማትሰለፍ አስታውቋል፡፡
የሳኡዲ መንግሥት በበኩሉ፤ የሁቲ አማፅያን እንቅስቃሴ ለአገሬ ስጋት ናቸው በሚል  በየመን ወታደራዊ ድብደባ እየፈፀመ እንደምገኝ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስትም የሳኡዲን አቋም እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

  • ‹‹የሥነ ምግብ ጥናቱ የትኛውንም ሃይማኖት በተለየ የሚመለከት አይደለም›› /አስተባባሪው/
  • ‹‹ሥጋወደሙን ከምግብ መቁጠር ሃይማኖታዊ ነጻነትንና ሥርዓትን የሚፃረር ነው›› /ምእመናን/

   ከውልደታቸው እስከ ስድስት ወራት ዕድሜአቸው ድረስ ያሉ የአገሪቱ ሕፃናት፣ ከእናቶቻቸው ጡት ወተት ውጭ ተጨማሪ ነገር ስለመውሰዳቸው የዳሰሳ ጥናት ለማካሔድ በሚል ለመረጃ ሰብሳቢዎች የተሰጠው ሥልጠና፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሕፃናት ከሚፈጸመው ሥርዐተ ቊርባን አኳያ የሥነ ምግብ ባለሞያዎችን ማከራከሩ ተገለጸ፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ዲፓርትመንት ባለፈው የካቲት ወር፣ የሕፃናት ጥቃቅን ንጥረ ምግብ(micro nutrients) እና ተያያዥ የጤና ችግሮችን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሚሰበሰቡ መረጃዎች ለሦስት ሳምንት የዘለቀ ሥልጠና በሰጠበት ወቅት፣ ‹‹አንድ ሕፃን እስከ ስድስት ወር ዕድሜው ድረስ ሥጋወደሙን ወይም ቁርባን ከተቀበለ  የእናቱን ጡት ወተት ብቻ እንደተመገበ (exclusive breast feeding) አንቆጥረውም፤ እንደ ተጨማሪ ምግብ ነው የምናየው፤›› በሚል በጥናቱ አስተባባሪ የተነሣው ሐሳብ ብዙዎቹን አጥኚዎች ክፉኛ እንዳከራከረ የሥልጠናው ተሳታፊዎች ይናገራሉ፡፡
አንድ ሕፃን ከልደቱ እስከ ስድስት ወር ድረስ መመገብ ያለበት በበቂ ንጥረ ነገሮች የበለጸገውንና በተስማሚነቱ መተኪያ የሌለውን የእናት ጡት ብቻ እንደኾነ በሕክምና ሳይንሱ ይመከራል፤ ይህም ተጨማሪ ምግብና ፈሳሽ ለመውሰድ የሕፃኑ ጨጓራና አንጀት ዝግጁ ባለመኾኑና ለጤና እክልም እንዳይጋለጥ በሚል እንደኾነ የሚያስረዱት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ተከታይ ባለሞያዎቹ፣ በሥርዓተ እምነታቸው ዕድሜ እና ጾታ ሳይለይ የአምላክ አማናዊ ሥጋ እና አማናዊ ደም እንደኾነ አምነው የሚቀበሉት ቅዱስ ቊርባን፤ ‹‹ተጨማሪ›› በሚል በሚሰበሰበው መረጃ ለማካተት መታሰቡንና ከሥነ ምግብ አንጻር መታየቱን በጥብቅ እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡
በሕክምናው ስድስት ወራት ያልሞላቸው ሕፃናት ሲታመሙ ሽሮፕ ወይም ክኒን እንዲሟሟ ተደርጎ ለተወሰነ ጊዜ መድኃኒት እንደሚሰጣቸውና ይህም ለመዋዕለ ዘመናቸው የተወሰነውን የእናት ጡት ወተት ብቻ የመመገብ ሥርዓት ያፈርሰው እንደኾነ ለአስተባባሪው ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ባለሞያዎቹ፣ ‹‹በሐኪም ትእዛዝ ከኾነ ችግር የለውም፤ ሥርዐተ ምግቡን አያፈርሰውም ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ ቁርባን ከወሰደ ግን ያፈርሰዋል›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ይህም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚታመንበት የሥርዐተ አመጋገቡ መግለጫ እንደኾነ ተነግሮናል የሚሉት ባለሞያዎቹ፣ ከሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ አካላት ለማረጋገጥ ሲጠይቁ ግን ‹‹በዚኽ ጉዳይ መልስ መስጠት አልፈልግም›› እንደተባሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሕፃናት ጤና አጠባበቅ ከአህጉሩ በቀዳሚነት ለምትጠቀስበት ስኬቷ፣ በሥርዓተ ሃይማኖቱ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሕፃናት የሚፈጸመው ቊርባን ዕንቅፋት ይኾናል ብለው እንደማያምኑ ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡ በእምነቱ የተቀደሰ ትውፊት ከስድስት ወራት በፊት ያሉ ሕፃናትንም ቢኾን ማቁረብ ለመንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ዕድገታቸው የመጨነቅ የጥሩ እናትነት ምልክት መኾኑን የሚያስረዱት ባለሞያዎቹ፣ በብዙ ሚልዮን የሚገመቱት ክርስቲያን ሕፃናት እስከ ስድስት ወራቸው ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ የማይመገቡበት አንዱ ምክንያት ‹‹ስለሚቆርቡ ነው›› የሚል ድምዳሜ በዳሰሳ ጥናቱ እንደ አንድ ነጥብ ቢቀመጥ ለአገር የሚያሰጠው ገጽታ ከወዲኹ መጤን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሥርዓተ ቊርባን፣ ሕፃናት በተወለዱ ከ40 እና ከ80 ቀናቸው ጀምሮ የሚቀበሉትና ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን አንድነት የሚያረጋግጡበት የእምነታቸው አክሊልና ፍጻሜ ነው ያሉት ባለሞያዎቹ፣ ከስድስት ወራት በፊት ያሉ ሕፃናትን አመጋገብ ያፈርሳል የሚለው የጥናቱ ውጤት በሒደት የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት መርሐ ግብር አካል ተደርጎ ሊሠራበት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡ ይህም የሃይማኖት ነጻነትን የሚጋፋ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ የምእመናኑን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያጠፋና የሚደመስስ፣ እንዲኹም ለባዕድ አስተሳሰብም አሳልፎ የሚሰጥ በመኾኑ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረውና በጽኑ እንደሚያወግዙት ገልጸዋል፡፡
‹‹መረጃውን ለእናንተ ከነገሯችኹ ሰዎች በላይ ለምንሠራው ሥራ ሓላፊነት ይሰማናል›› ያሉት በኢንስቲትዩቱ የሥነ ምግብ ዲፓርትመንት የሥልጠናው አስተባባሪ ለአዲስ አድማስ በስልክ እንደተናገሩት፣ ጥናቱ የተወሰነ ሃይማኖትን የሚመለከት አይደለም፤ ዓላማውም ምን ያኽል ሕፃናት እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ብቻ ወስደዋል የሚለውን ለማወቅ ብቻ በመኾኑ ከሃይማኖት ጋራ የሚያያዝ ትንታኔ የሚሰጠበት አይደለም፡፡
‹‹ለሕፃኑ ከውልደቱ ጀምሮ እስከ ስድስት ወሩ ድረስ ከእናት ጡት ውጭ የተሰጠው ማንኛውም ነገር አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ‹‹በሃይማኖት ሥርዓትም ቢኾን›› በመረጃ ሰብሳቢዎቹ መጠየቅ እንዳለበት በሥልጠናው ላይ በአጽንዖት መነገሩን የሚጠቁሙት አስተባባሪው፤ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ለሕፃናት ከሚፈጸመው ቁርባን አንጻር ከአንድ ተሳታፊ ጥያቄ መነሣቱን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹በሃይማኖት ሥርዓትም ቢኾን ብለን ጥያቄ ስንጠይቅ ኦርቶዶክስ ሊኾን ይችላል፤ ሙስሊም ሊኾን ይችላል፤ ባዕድ አምልኮ የሚከተል ሊኾን ይችላል፤ እኛ እርሱ አይደለም የሚያሳስበን፤ በሃይማኖታዊ ሥርዓትኮ ሥጋወደሙ ብቻ አይደለም፤ ልጆች ሲታመሙ ጠበልም ምንም በተከታታይ አብዝቶ ይሰጣል፤ ይህም ኾኖ ወላጆች የእናት ጡት ብቻ ነው የመገብነው ይላሉ፤ ጤና አዳም ውኃ ውስጥ አድርገው ይሰጡና ምንም አልሰጠንም ይላሉ፡፡ በዚኽ ኹኔታ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው ሕፃናት ይኖራሉ፤ ከኦርቶዶክስ እምነት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ነገሩ ተገቢው ግምት ስለማይሰጠው በየትኛውም ሃይማኖት የሰጣችኹት ነገር አለ ወይ? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ጥያቄው እንዲኽ ያሉ ነገሮችን ለማስተካከል ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱ የሕፃናት ሕመምና ሞት መጠንን ማሻሻል ብትችልም የሚፈለገውን ያኽል መሔድ አልተቻለም፡፡ ስለዚኽ በሃይማኖታዊ ሥርዓትስ የሰጣችኹት ነገር የለም ወይ? ምን? የሚል ጥያቄ በመጠይቁ ተካትቷል፤›› ሲሉ አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡  

ከኦባማ ቀጥሎ በአሜሪካ ከፍተኛው ደመወዝ ተከፋይ ነበሩ
ከ2ሺ በላይ የተሳኩ ቀዶ ህክምናዎችን አከናውነዋል
ወንድሞቻቸው፡- ፕሮቶን፣ ኒውትሮን፣ ዲዩትሮን፣ ኤሌክትሮን እና ፖሲትሮን ይባላሉ

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ኤሌክትሮን ክበበው፤ ለ33ኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የ2015 “የዓመቱ የዓለማችን ልዩ ስም” ውድድር ላይ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት በቀዳሚነት እየመሩ እንደሆነ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ዘንድሮም የተለያዩ አገራት ዜጎችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ 64 ግለሰቦች ያልተለመዱ ስሞች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ኤልክትሮን ክበበው፤ በ1ሺህ 132 ድምጽ፣ በ89.6 በመቶ ውጤት በቀዳሚነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በኢሜልና በተለያዩ መንገዶች ከቀረቡለት በርካታ ለየት ያሉ ስሞች 64 ያህሉን በመምረጥ፣ ለአንድ ሳምንት ያህል በድረ ገጽ አማካይነት ድምጽ እንዲሰጥባቸው የሚያደርገው የውድድር ኮሚቴው፤ የመጨረሻውን ውጤት ከጥቂት ቀናት በኋላ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
የሰማይ እንሽላሊት፣  ጣፋጭ ቡና፣ ዳላስ፣ ቶክዮ፣ ቴኒስ እና የመሳሰሉ የአገር፣ የቦታ፣ የእቃ፣ የሰብል ወዘተ መጠሪያዎችን የያዙ የተለያዩ አገራት ዜጎች በዘንድሮው ውድድር እንደተሳተፉ አወዳዳሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው ውድድር ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት በመምራት ላይ ለሚገኙት የ47 አመቱ ዶ/ር ኤሌክትሮን ይህን ስም ያወጡላቸው፣ ኤሌክትሪካል ኢንጂነር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አባታቸው አቶ ክበበው ነበሩ፡፡
ልጆቻቸው የእሳቸውን ፈለግ ተከትለው በሳይንሱ ዘርፍ ላይሰማሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረባቸው አቶ ክበበው፤ በልጆቻቸው ልቦና ውስጥ ገና በለጋ እድሜያቸው የሳይንስን ስሜት ለማስረጽ በማሰብ ነው፣ ባልተለመደ ሁኔታ ለልጆቻቸው ከኤሌክትሪሲቲ ጋር የተያያዙ ስሞችን ያወጡት፡፡
አቶ ክበበው፤ ለአምስቱ ልጆቻቸው ፕሮቶን፣ ኒውትሮን፣ ዲዩትሮን፣ ኤሌክትሮን እና ፖሲትሮን የሚሉ ስሞችን አውጥተዋል፡፡ ዶ/ር ኤሌክትሮን በስማቸው ብቻ አይደለም የሚለዩት፡፡ ከስማቸው በላይ ብዙዎችን ያስገረመው፣ በህክምና ሙያቸው የአሜሪካ መንግስት የሚከፍላቸው ዳጎስ ያለ ደመወዝ ነው ይላል ድረ-ገጹ፡፡
ከአራት አመታት በፊት “ዊኪኦርግቻርትስ” የተባለ ተቋም “የአመቱ የአሜሪካ መንግስት 1000 ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋዮች” በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ፣ ዶ/ር ኤሌክትሮንን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቀጥሎ ከፍተኛ ደመወዝ የሚያገኙ የመንግስት ሰራተኛ በማለት በሁለተኛነት አስቀምጧቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የተማሩት ዶ/ር ኤሌክትሮን ክበበው፤ በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከሚገኘው ዪኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ በህክምና የተመረቁ ሲሆን የአሜሪካን ቦርድ ኦፍ ሰርጀሪን የቀዶ ህክምና ሰርተፊኬትም አግኝተዋል፡፡
ላለፉት 20 አመታት በሳንፍራንሲስኮ በኢንዶክሪንና ታይሮይድ ካንሰር ዘርፍ የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ዶክተሩ፤ በአሜሪካ ብሄራዊ የካንሰር ኢንስቲትዩት፣ የካንሰር ምርምር ማዕከል የኢንዶክራይን ኦንኮሎጂ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሲሆኑ የካንሰር ጄኔቲክስ ክፍሉንም በበላይነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶክተሩ በእስካሁኑ የሙያ ዘመናቸው ከሁለት ሺህ በላይ የተሳኩ ቀዶ ህክምናዎችን ያከናወኑ ሲሆን ከ150 በላይ የጥናት ጽሁፎችንና መጽሃፍትን ለህትመት እንዳበቁ “ብሬኪንግጎቭ” የተሰኘ ድረገፅ አመልክቷል፡፡

የአፍሪካ ሀገራትን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ተጨባጭ እውነታ በጥናት እየፈተሸ ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው “አፍሪካ ክራድል” ድረገፅ፤ ሰሞኑን 10 ተፅዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ አገራትን ይፋ ያደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ተብላለች፡፡ የሀገራቱ የተፅዕኖ ፈጣሪነት ደረጃ የተሠጠው በጦር ሃይል፣ በዲፕሎማሲ እና በአለማቀፍ ደረጃ ባላቸው እውቅና ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ የተሠጣት ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ብቸኛ የ “ቡድን 20 እና የ “BRICS” አባል ሀገር እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ቀዳሚ የንግድ ሸሪክ መሆኗ ለደረጃው አብቅቷታል ተብሏል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ስም ሲነሳ የማንዴላ የአፓርታይድ ተጋድሎ አብሮ እንደሚነሣ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ዛሬ በሀገሪቱ ለተገነባው ዲሞክራሲያዊ ስርአት የማንዴላና ተከታዮቻቸው የእነታቦ ኢምቤኪ አስተዋጽኦ የጐላ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
በተፅዕኖ ፈጣሪነት ሁለተኛ ደረጃ የተሠጣት ኢትዮጵያ፤ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሟ 44 ጊዜ ያህል መጠቀሱን፣ በታሪክ፣ ቅኝ ባለመገዛት፣ በጦር ሃይል፣ በፖለቲካና ዲፕሎማሲ ወደር የለሽ ታሪክና ተሞክሮ እንዳላት በማውሳት በዚህ ረገድ ከአፍሪካ አገራት የሚስተካከላት እንደሌለ ሪፖርቱ ጠቁሟል። አገሪቱ በአድዋ ጦርነት የተቀዳጀችውን ድል ተከትሎ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን የባንዲራ ቀለማት በተለያየ ቅርፅና ይዘት ለመጠቀም እንደተገደዱ፣ የቡና የትውልድ አገር እንዲሁም፣ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን፣ የራሷ የቀን አቆጣጠርና ፊደላት እንዳላትም የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ነዳጅ ሳይኖራት ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት ኢኮኖሚዋን በከፍተኛ መጠን እያሳደገው መሆኑን፣ በጦር ሃይልም ቢሆን ጠንካራ ሃይል ከገነቡ የአፍሪካ ሀገሮች ተጠቃሽ እንደሆነች አመልክቷል፡፡
ሀገሪቱ ለወደፊቱ በአለም ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብለው ተስፋ ከሚጣልባቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እንደምትሆንም ሪፖርቱ ተንብይዋል።
ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ግብፅ በ3ኛ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተብላለች፡፡ በርካታ የተማሩ ሰዎች አሏት የተባለችው ኬንያ 4ኛ ደረጃ ሲሰጣት፣ የአለማቀፍ ኩባንያዎች መቀመጫ የተባለችው ሞሮኮ 5ኛ፣ ቀዳሚ የኢኮኖሚና የሃይል ባለቤት የተባለችው ናይጄሪያ 6ኛ፣ ውጤታማ የኢኮኖሚ ገበያ ስርአት ባለቤት እንደሆነች የተነገረላት ኡጋንዳ 7ኛ፣ዜጎቿ ከእርስ በእርስ ግጭት ወጥተው በፍቅር ይኖሩባታል የተባለችው ሩዋንዳ 8ኛ፣ ህዝቧ ፈሪሃ አምላክ ነው የተባለችው ዚምባቡዌ 9ኛ ሲሆኑ በመጨረሻም የተረጋጋ የኢኮኖሚ ባለቤት የተባለችው አልጄሪያ 10ኛ ደረጃ ተሰጥቷል፡፡
 በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪነት፡፡      

Saturday, 28 March 2015 10:17

የፍቅር ጥግ

አንዳንዴ ለዓይን የተሰወረውን ልብ ያየዋል፡፡
ኤች ጃክሰን ብራውን ጄአር.
ፍቅር ማለት ራስን ያለ ዋስትና መስጠት ነው፡፡
አኔ ካምቤል
አበባ ያለ ፀሐይ ብርሃን አያብብም፤ ሰው ያለ ፍቅር አይኖርም፡፡
ማክስ ሙለር
የፍቅር የመጀመሪያ ተግባሩ ማድመጥ ነው፡፡
ፓውል ቲሊች
ፍቅር፣ ዕድሜ፣ ገደብና ሞት አያውቅም፡፡
ጆን ግላስዎርዚ
የሌላው ሰው ደስታ የናንተ ደስታ ሲሆን ያኔ ፍቅር ይባላል፡፡
ላና ዴል ራይ
ማፍቀር ያለባችሁ ብቸኛ ስትሆኑ አይደለም፤ ዝግጁ ስትሆኑ ነው፡፡
ያልታወቀ ሰው
ለዘላለም እንዲዘልቅ የምትሹትን ነገር አታጣድፉት፡፡
ያልታወቀ ሰው
10 የማፍቀሪያ መንገዶች፡- ማድመጥ፣ መናገር፣ መስጠት፣ መፀለይ፣ መመለስ፣ መጋራት፣ መደሰት፣ ማመን፣ ይቅር ማለት፣ ቃል መግባት፡፡
ዊል ስሚዝ
በዓይኖቻችሁ ሳይሆን በልባችሁ አፍቅሩ፡፡
ያልታወቀ ሰው
ፍቅር አደገኛ የአዕምሮ በሽታ ነው፡፡
ፕሌቶ
ፍቅር ፍፁም እንዲሆን መጠበቅ የለብንም፤ እውነተኛ መሆን ብቻ ነው ያለበት፡፡
ያልታወቀ ሰው
በፍቅር መውደቅ፤ ደካማ አማልክት ያለው ሃይማኖት መፍጠር ነው፡፡
ጆርጅ ሉይስ ቦርግሰ
ለዓለም አንድ ሰው ብትሆኑም፣ ለአንድ ሰው ግን ዓለም ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡
ያልታወቀ ሰው

Saturday, 28 March 2015 10:05

የሲኒማ ጥግ

ሴት ተዋናዮች ስለሙያቸው)
በተዋናይነቴ እጅግ አስደሳቹ የትወና ክፍል ዳይሬክተሩን ማስደሰት ነው፡፡ ሁሌም ዳይሬክተሬን ማስደሰት እፈልጋለሁ፡፡
ጆን አን ቼን
ጠንክሬ መስራቴና ግሩም ሥልጠና ማግኘቴ ከአንዳንድ ተፎካካሪዎቼ የተሻልኩ ተዋናይት እንድሆን አስችሎኛል፡፡
ፓላ ኔግሪ
እንደሌላ ሰው የምዘፍን ከሆነ ጨርሶ መዝፈን አያስፈልገኝም፡፡
ቢሊ ሆሊዴይ
ሰዎች ሁለት ነገሮችን ፈጽሞ አይረሱም፡- የመጀመሪያ ፍቅራቸውንና ቀሽም ፊልም ለመመልከት የከፈሉትን ገንዘብ፡፡
አሚት ካላንትሪ
ተዋናይት መሆን አልፈልግም ነበር፡፡ የጥርስ ሃኪም መሆን ነበር ፍላጐቴ፤ ነገር ግን ህይወት የሚያመጣላችሁን አታውቁትም፡፡
ሶፍያ ቬርጋራ
ተዋናይት የምትተውነው ሴትን ብቻ ነው። እኔ ተዋናይ ነኝ፤ ምንም ነገር ልተውን እችላለሁ፡፡
ውፒ ጐልድበርግ (ሴት ተዋናይት)
በዘጠኝ ዓመት ዕድሜዬ ባልጀምር ኖሮ ተዋናይት እሆን ነበር ብዬ አላስብም፡፡
ክሪስቲን ስቴዋርት
ስጀምር ተዋናይት የመሆን ወይም ትወና የመማር ፍላጐት አልነበረኝም፡፡ ዝነኛ መሆን ብቻ ነበር የምፈልገው፡፡
ካታሪን ሄፕበርን
አምስት ዓመት ሲሆነኝ ይመስለኛል ተዋናይት ለመሆን መፈለግ የጀመርኩት፡፡
ማርሊን ሞንሮ
በተዋናይትነት ስኬታማ ለመሆን ሰብፅና በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡
ማ ዌስት
እስከ 45 ዓመቴ ድረስ ፍቅር የያዛት ሴት ሆኜ መጫወት እችላለሁ፡፡ ከ55 ዓመቴ በኋላ አያት ሆኜ እተውናለሁ፡፡ በሁለቱ መካከል ያሉት 10 ዓመታት ግን ለሴት ተዋናይ አስቸጋሪ ነው፡፡
ኢንግሪድ በርግማን
ዝነኛ ተዋናይት መሆን የትልቅነት ስሜት ሊፈጥርባችሁ ይችላል፡፡ ግን እመኑኝ…ቅዠት ነው፡፡
ጁሊቴ ቢኖቼ

   ናይጀሪያ በዛሬው ዕለት የምታከናውነውን ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ከቦኮ ሃራም ጥቃትና ከውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ለመከላከል እንዲሁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  በሚል ካለፈው ረቡዕ ምሽት ጀምሮ ሁሉንም የባህርና የየብስ ድንበሮቿን መዝጋቷን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የናይጀሪያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፓትሪክ አባ ሞሮ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የሌሎች አገር ዜጎች ድንበር አቋርጠው በመግባት በአገሪቱ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት እንዳቀዱ የሚያመለክቱ መረጃዎች በመገኘታቸው፣ ምርጫውን ከውጭ ጣልቃ ገብነቶች ለመከላከል ሲባል ድንበሮቹ ተዘግተዋል፡፡
ቦኮ ሃራም በተባለው የአገሪቱ ጽንፈኛ ቡድን ላለፉት ስድስት አመታት ሲፈጸሙ የቆዩ ጥቃቶችን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ናይጀሪያውያን፣ በዛሬው ምርጫ ድምጽ መስጠት እንደማይችሉም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ባለፉት ስድስት ሳምንታት የአገሪቱ ሃይሎች በአሸባሪው የቦኮሃራም ቡድን ቁጥጥር ስር የነበሩ የድንበር አካባቢዎችን መልሰው መያዝ ቢችሉም፣ በተለይ በሰሜን ምስራቃዊ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰርጎ ገቦች ድንበር ጥሰው ገብተው ምርጫውን ያደናቅፋሉ በሚል ስጋት መንግስት ሁሉንም የአገሪቱ ድንበሮች ለመዝጋት መወሰኑን ዘገባው ገልጧል፡፡
ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ሲባል፣ ሁሉም የአገሪቱ ድንበሮች እስከ ዛሬ እኩለ ሌሊት ድረስ ዝግ ሆነው እንደሚቆዩና ቦኮ ሃራም በሚንቀሳቀስባቸው ቦርኖ፣ ዮቢና አዳማዋ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደተጣለም ተዘግቧል፡፡
የቦኮ ሃራምን ጥቃት የመቋቋም ቁርጠኝነትና ብቃት ያንሳቸዋል በሚል በስፋት ሲተቹ የቆዩት ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ በጸጥታ ስጋት ለሳምንታት ተራዝሞ  ዛሬ በሚካሄደው ምርጫ ከተቀናቃኛቸው የቀድሞው የጦር መሪ ሙሃማዱ ቡሃሪ ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ ጦራቸው በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ስር የሚገኙ የአገሪቱ ግዛቶችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ውስጥ እንደሚያደርግ ባለፈው ሳምንት ቢናገሩም፤ ቦኮ ሃራም እስከ 11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 500 ህጻናትን ዳማሳክ ከተባለችው የአገሪቱ ከተማ አፍኖ መውሰዱን ቢቢሲ ባለፈው ማክሰኞ ዘግቧል፡፡

በሽታው እስካሁን ከ10 ሺ በላይ ሰዎችን ገድሏል

    ከአንድ አመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰውና ከ10ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት እንደዳረገ የተነገረለት የኢቦላ ወረርሽኝ እስከ መጪው ነሐሴ ወር ድረስ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የተመድ የኢቦላ ምላሽ ግብረ ሃይል ሃላፊ ኢስማኤል ኦውልድ ቼክን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በጊኒ የተከሰተውንና ወደ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት የተስፋፋውን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ፣ በመጀመሪያዎቹ የወረርሽኙ ወራት በተመድ የተሰሩት ስራዎች ያልተቀናጁና በእውቀት ላይ ያልተመሰረቱ ነበሩ፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች በሂደት እየተሻሻሉ መጥተዋል ያሉት ሃላፊው፤ ባለፈው አንድ አመት ኢቦላን ለመግታት በተደረገው እንቅስቃሴ ልምድ ቀስመናል፤ ወረርሽኙን እስከ መጪው ነሐሴ ወር ሙሉ ለሙሉ መግታት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
የኢቦላ ቫይረስ ዳግም በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ለመከላከልና አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ሲባል፣ ራሱን የቻለ አለማቀፍ የኢቦላ ፈጣን ምላሽ ቡድን ለማቋቋም የሚያስችል ዕቅድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መውጣቱንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ድንበር የለሹ የሃኪሞች ቡድን በበኩሉ፤እስካለፈው ጥር ወር ድረስ በምዕራብ አፍሪካ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም፣ ከዚያ በኋላ አልቀነሰም፤ ወረርሽኙ ገና ሙሉ ለሙሉ አልተገታም ብሏል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው፣እስከያዝነው ሳምንት መጨረሻ ድረስ፣4ሺ 296 ላይቤሪያውያን፣ 3ሺ 742 ሴራሊዮናውያን፣ 2ሺ 261 ጊኒያውያን፣ 8 ናይጀሪያውያን፣ ስድስት ማሊያውያንና አንድ አሜሪካዊ በኢቦላ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል፡፡

በዓለማችን በግዙፍነቱ አቻ እንደማይገኝለት የተነገረውና ሃይብሪድ ኤር ቪሄክልስ በተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ ዲዛይን የተደረገው “ኤርላንደር 10” የተሰኘ አዲስ አይነት አውሮፕላን ከስድስት ወራት በኋላ ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ በእንግሊዝ ሰማይ ላይ የሙከራ በረራ እንደሚያደርግ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በአሜሪካ የጦር ሃይል ለወታደራዊ አሰሳ ስራ እንዲውል ታስቦ የተሰራው ይህ አውሮፕላን፤ርዝማኔው ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ እንደሚበልጥ የጠቆመው ዘገባው፣ 302 ጫማ ቁመት እንዳለው፣ዲዛይኑም ከተለመደው ወጣ ያለና የአውሮፕላንና የሄሊኮፕተር ቅልቅል እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ኩባንያው የአውሮፕላኑን ፕሮጀክት ከጀመረ ቆየት ቢልም፣ በበጀት እጥረት ምክንያት ሥራው  ሲጓተት መቆየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ በመጨረሻም ከእንግሊዝ መንግስት ባገኘው የ5.1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስራውን ከዳር ማድረሱን አስታውቋል፡፡
አውሮፕላኑ 10 ቶን ክብደት የመጫን አቅም ያለው ሲሆን አጠቃላይ አሰራሩ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው ተብሏል፡፡ ነዳጅ ቆጣቢነቱ፣ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የመብረር ብቃቱና በአካባቢ ብክለት እምብዛም አለመታማቱም ተመስክሮለታል፡፡
ኤርላንደር 10 ለመነሳትና ለማረፍ ሰፊ ማኮብኮቢያና የተመቻቸ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የሚፈልግ አለመሆኑና በቀላሉ መንቀሳቀስ በሚችልበት መልኩ መሰራቱ ደግሞ፣ ከወታደራዊ አሰሳ ባለፈ በአደጋ ጊዜ የፈጥኖ ደራሽ ስራን ለማከናወን ተመራጭ አድርጎታል ብሏል ዘገባው፡፡

Saturday, 28 March 2015 09:14

የግጥም ጥግ

የተነሳህ ለት

የዛፍ ባላጋራ
ከምትተናነቅ
ከመቶ ቅርንጫፍ
ከሺህ ቅጠል ጋራ
እንደጡንቻ ሁሉ
ስልት በማፈርጠም
ወርደህ ከግንዱ ጋር
አንድ ለአንድ ግጠም፡፡

ሠም እና ሠም

አበባው አብቦ ንቡ ገብቶልህ
እንግዲህ ጎበሌ ማር ካላበላህ
“እንኳንስ ማርና አላየሁም ሰፈፍ”
እያልህ በመራራ ዜማ ከመንሰፍሰፍ
ያ! የቀፎው አውራ ማሩን የደበቀው
ንብ ሆኖ ሲመጣ ጭስ ሆነህ ጠብቀው፡፡
(“የአመድ ልጅ እሳት” የግጥም መድበል፤
መጋቢት 2007)