Administrator

Administrator

ከኃላፊዎች ውጭ ሞባይል ይዞ መግባት አይፈቀድም


     በአዲስ አበባ የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤትና ቂሊንጦ የቀጠሮ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች በድብቅ የሚገቡ ሞባይል ስልኮች መበራከታቸውን ምንጮች ገለፁ፡፡
ወደ ሁለቱም ማረሚያ ቤቶች ሞባይል ይዞ መግባት የሚፈቀድላቸው ለአመራሮቹ ብቻ ቢሆንም በርካታ ታራሚዎች ግን ሞባይል አስገብተው እንደሚጠቀሙ የገለፁት ምንጮች፤ አንድ ሞባይል ስልክ ለማስገባት እስከ 20 ሺ ብር እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡ ሞባይሎቹን ቻርጅ የሚያደርጉላቸው ደግሞ ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለአንድ የሞባይል ቻርጅ ማድረጊያ 150 ብር እንደሚያስከፍሉ የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ አንድ የመቶ ብር ካርድም እስከ 500 ብር እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የማረሚያ ቤቱ ጥቂት ፖሊሶች ለአንድ ደቂቃ 30 ብር እያስከፈሉ ታራሚዎችን ያስደውሉ ነበር ያሉት ምንጮች አሁን ሞባይል የገባላቸው ታራሚዎችም ለአንድ ደቂቃ 20 ብር እያስከፈሉ እንደሚያስደውሉ ታውቋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገረመው አያሌው ስለ ጉዳዩ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ ስለ ጉዳዩ በጭምጭምታ ከመስማት በቀር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ ከኃላፊዎች ውጪ ታራሚዎችም ሆኑ ሰራተኞች ወደ ማረሚያ ቤት ስልክ ይዘው እንደማይገቡ ገልፀዋል፡፡

 የሞ ፋውንዴሽን መስራች ትውልደ ሱዳናዊው ቢሊየነር ሞ ኢብራሂም፤ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በፈቃደኝነት ስልጣናቸውን የሚለቅቁ ከሆነ፣ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የመሰረተባቸውን ክስ እንዲያቋርጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ለሳምንታት በዘለቀውና አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ በሚጠይቀው ተቃውሞ ዙሪያ ከቢቢሲ ጋር ውይይት ያደረጉት ሞ ኢብራሂም፤ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ፈቃደኛ ሆነው ስልጣናቸውን በመልቀቅ አገሪቱንና ህዝቧን ከእልቂትና ከጥፋት ለመታደግ ከቻሉ በዳርፉር የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል በአለማቀፉ ፍርድ ቤት የተመሰረተባቸው ክስ ሊቋረጥላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሱዳናውያን አልበሽር ስልጣን እንዲለቅቁ በመጠየቅ በአደባባይ ተቃውሞ ማድረግ ከጀመሩ ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ መንግስት ያሰራቸው ተቃዋሚዎች ቁጥር ከ800 በላይ መድረሱ ተነግሯል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን አልበሽርን ሲቃወሙ የሰነበቱ ሲሆን ባለፈው ረቡዕ ደግሞ አልበሽርን የሚደግፉ ሱዳናውያን በካርቱም የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ አግባብነት የሌለው ተቃውሞ ስልጣናቸውን እንደማያስለቅቃቸው በይፋ ሲያስታውቁ የሰነበቱት ፕሬዚዳንቱም በስፍራው በመገኘት ለደጋፊዎቻቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳና ኖርዌይ ባለፈው ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ፤ የአልበሽር መንግስት የተቃዋሚዎችን መብቶች እንዳይጥስ ጥሪያቸውን ማቅረባቸው የተዘገበ ሲሆን፣ መንግስት ተቃዋሚዎችን በገፍ ማሰሩንና መግደሉን የማያቋርጥ ከሆነ ማዕቀብ ሊጥሉበት እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

 ናይጀሪያ በ2018 ብቻ ከነዳጅ ዝርፊያ 2.8 ቢ. ዶላር አጥታለች

    ናይጀሪያን ከኢኮኖሚያዊ ቀውስና ከአለመረጋጋት ለማውጣት አልቻሉም በሚል ትችት የሚሰነዘርባቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ቡሃሪ፣ ናይጀሪያን ላለመረጋጋት የዳረጓት ሟቹ የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ናቸው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ናይጀሪያ የሽብርተኞች መናኸሪያ የሆነቺው በጋዳፊና በአጋሮቻቸው ሴራ ምክንያት ነው ያሉት ቡሃሪ፤ ከሊቢያ ሰርገው የገቡ የጋዳፊ ግብረ አበሮች አገሬን እያመሷት ይገኛሉ ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ናይጀሪያን በሽብር እያተራመሷት የሚገኙት የራሷ ዜጎች የሆኑ የቦኮ ሃራም አሸባሪዎችና ታጣቂዎች መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ ቡሃሪ ግን የአገሬ ገበሬዎች በታሪካቸው ከአርጩሜ በላይ ታጥቀው አያውቁም፤ ኤኬ አርባ ሰባት ታጥቀው ናይጀሪያን የሚያምሷትና አለመረጋጋት ውስጥ የዘፈቋት ሰርጎ ገብ የጋዳፊ ቅጥረኞች ናቸው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ጋዳፊ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ናይጀሪያውያንን ብቻ ሳይሆን የማሊ፣ የቡርኪናፋሶ፣ የኒጀርና የቻድ ዜጎችን እየመለመሉ ጦርነት ሲያስተምሩ ኖረዋል ያሉት ቡሃሪ፤ የጋዳፊን ሞት ተከትሎ ከአገራቸው የፈረጠጡት እነዚህ ሰልጣኞች ወደ ናይጀሪያና ወደ ሌሎች አገራት ዘልቀው በመግባት የሽብር ጥቃቶችን ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ናይጀሪያ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ዝርፊያ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምዕራብ አፍሪካና የሳህል ቀጠና ቢሮ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ የነዳጅ ሃብት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ የተፈጸመ ሲሆን የባህር ላይ ዝርፊያም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

 አጠቃላይ የሃብት መጠኑ 810 ቢሊዮን ዶላር ያህል የደረሰው ታዋቂው የአሜሪካ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ኩባንያ አማዞን፤ በአለማችን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ቁጥር አንድ ኩባንያ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በአማዞን ኩባንያ ውስጥ የ16 በመቶ ድርሻ ያላቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው ጄፍ ቤዞስ አጠቃላይ የሃብት መጠን 135 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና የወቅቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር መሆናቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
የሃብት መጠኑን በአመቱ በ10 በመቶ ያህል ከፍ ያደረገውንና በአፕል ተይዞ የነበረውን የአንደኛነት ደረጃ የተረከበውን አማዞን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ማይክሮሶፍት ነው ያለው ዘገባው፤ የኩባንያው አጠቃላይ የሃብት መጠን 790 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንም አመልክቷል፡፡
ጎግል አልፋቤት በ750 ቢሊዮን ዶላር የሶስተኛነትን ደረጃን ሲይዝ፣ አጠቃላይ የሃብት መጠኑ 1.1 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ቀዳሚው የአለማችን ኩባንያ ሆኖ አለምን አጀብ ሲያሰኝ የነበረው አፕል በበኩሉ፣ በ2018 የሃብት መጠኑ 35 በመቶ ያህል ቀንሶ 710 ቢሊዮን ዶላር በመድረሱ የ4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ተነግሯል።

 የኦባማ ነጠላ ዜማ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፏል


    በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2018 ከፍተኛ የሙዚቃ አልበም ሽያጭ ያስመዘገቡ የአለማችን ምርጥ ድምጻውያን ዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ካናዳዊው ራፐር ኤሚኔም በአመቱ 755 ሺህ 27 አልበሞችን በመሸጥ የአንደኛ ደረጃን መያዙ ተነግሯል፡፡
በዝአንግል የተባለው ድረገጽ ባወጣው አለማቀፍ የሙዚቃ አልበሞች ሽያጭ ደረጃ መሪነቱን የያዘው የ46 አመቱ ራፐር ኤሚኔም፤ በተለይም በቅርቡ ያወጣው ካሚካዚ የተሰኘ አስረኛው አልበሙ 373 ሺህ 67 ኮፒ እንደተሸጠለት አመልክቷል፡፡ ድረገጹ ባወጣው መረጃ እንዳለው፤ በአመቱ የአልበም ሽያጭ የሁለተኛ ደረጃን የያዘው ቢቲኤስ የተባለው የሙዚቃ ቡድን ሲሆን፣ 603 ሺህ 307 አልበሞች ተሸጦለታል፡፡
በሌላ በኩል፤የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የለቀቁት ዋን ላስት ታይም የተሰኘ ነጠላ ዜማ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማትረፉንና በቢልቦርድ የአርኤንድ ቢ ሙዚቃ የደረጃ ሰንጠረዥ 22ኛ ደረጃን መያዙን ፎርብስ ዘግቧል፡፡
ኦባማ ከክርስቶፈር ጃክሰንና ቢቢ ዊናንስ ከተባሉ ድምጻውያን ጋር በጋራ የሰሩትና እንደገና በአዲስ መልክ ተሰርቶ በቅርቡ የወጣው ይህ ነጠላ ዜማ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ 9 ሺህ ጊዜ ያህል ዳውንሎድ የተደረገ ሲሆን፣ በድረገጽ አማካይነትም ከ307 ሺህ ጊዜ በላይ በቀጥታ መታየቱ ተነግሯል፡፡

  በቻይና የመኪኖች ሽያጭ በ20 አመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀንሷል

    ታዋቂው የጀርመን የመኪና አምራች ኩባንያ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ 2.31 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ ከአለማችን ኩባንያዎች ቀዳሚነትን መያዙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት በመኪና ሽያጭ ቀዳሚው የአለማችን ኩባንያ ሆኖ የዘለቀው የጀርመኑ መርሴድስ ቤንዝ፤ በአመቱ ከፍተኛ የሽያጭ ክብረወሰን ማስመዝገቡን የጠቆመው ዘገባ፣ በቻይና ብቻ ሽያጩ በ11 በመቶ ማደጉን አመልክቷል፡፡
ቢኤምደብሊው፣ አውዲና መርሴድስ ቤንዝ እጅግ ዘመናዊ የቅንጦት መኪኖችን በብዛት በመሸጥ ለአስርት አመታት ተፎካካሪ ሆነው መዝለቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአመቱ 245 ሺህ 240 መኪኖችን የሸጠው የአሜሪካው ቴስላም ከኩባንያዎቹ ተርታ እየተሰለፈ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በአለማችን ትልቁ የመኪኖች ገበያ እንደሆነች በሚነገርላት ቻይና የመኪኖች ሽያጭ ከሃያ አመታት በኋላ በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ የ6 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ በቻይና ገበያ በአመቱ 22.7 ሚሊዮን መኪኖች ብቻ መሸጣቸውን ገልጧል፡፡
ለቻይና የመኪና ሽያጭ ቅናሽ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በአለማችን የመኪና አምራች ኩባንያዎች ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ ይገኝበታል ያለው ዘገባው፤ ፎርድ፣ ቮልስዋገን፣ ጃጓርና ላንድሮቨርን ጨምሮ ታላላቅ የውጭ አገራት የመኪና አምራች ኩባንያዎች በቻይና ገበያ ያስመዘገቡት የአመቱ ሽያጭ መቀነስ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡

በቻይና የመኪኖች ሽያጭ በ20 አመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀንሷል

    ታዋቂው የጀርመን የመኪና አምራች ኩባንያ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ 2.31 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ ከአለማችን ኩባንያዎች ቀዳሚነትን መያዙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት በመኪና ሽያጭ ቀዳሚው የአለማችን ኩባንያ ሆኖ የዘለቀው የጀርመኑ መርሴድስ ቤንዝ፤ በአመቱ ከፍተኛ የሽያጭ ክብረወሰን ማስመዝገቡን የጠቆመው ዘገባ፣ በቻይና ብቻ ሽያጩ በ11 በመቶ ማደጉን አመልክቷል፡፡
ቢኤምደብሊው፣ አውዲና መርሴድስ ቤንዝ እጅግ ዘመናዊ የቅንጦት መኪኖችን በብዛት በመሸጥ ለአስርት አመታት ተፎካካሪ ሆነው መዝለቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአመቱ 245 ሺህ 240 መኪኖችን የሸጠው የአሜሪካው ቴስላም ከኩባንያዎቹ ተርታ እየተሰለፈ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በአለማችን ትልቁ የመኪኖች ገበያ እንደሆነች በሚነገርላት ቻይና የመኪኖች ሽያጭ ከሃያ አመታት በኋላ በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ የ6 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ በቻይና ገበያ በአመቱ 22.7 ሚሊዮን መኪኖች ብቻ መሸጣቸውን ገልጧል፡፡
ለቻይና የመኪና ሽያጭ ቅናሽ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በአለማችን የመኪና አምራች ኩባንያዎች ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ ይገኝበታል ያለው ዘገባው፤ ፎርድ፣ ቮልስዋገን፣ ጃጓርና ላንድሮቨርን ጨምሮ ታላላቅ የውጭ አገራት የመኪና አምራች ኩባንያዎች በቻይና ገበያ ያስመዘገቡት የአመቱ ሽያጭ መቀነስ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡

Saturday, 12 January 2019 14:20

የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያለ ህፃን እያለቀሰ ያስቸግራል፡፡ ቢያባብሉት፣ እሹሩሩ ቢሉት አሻፈረኝ አለ፡፡ በማባበል እምቢ ሲል ማስፈራራት ጀመሩ፡፡
“እንግዲህ ዝም ካላልክ ለአያ ጅቦ ልንሰጥህ ነው” አለች እናት፡፡
“ዋ በመስኮት ነው የምወረውርህ!” አለው አባት፡፡
ይህንን ሲሉ ለካ አያ ጅቦ ደጅ ሆኖ ያዳምጥ ኖሯል፡፡ ይጠብቃል … ይጠብቃል … ይጠብቃል… ልጁ አልተወረወረም፡፡ አሁንም ያዳምጣል፡፡ ተስፋ ሳይቆርጥ መጠበቁን ቀጠለ፡፡ ምንም ዝር ያለ ነገር የለም፡፡
የልጁ ለቅሶ ግን ቀጥሏል፡፡
አሁንም እናቱ፤
“ዋ! ለአያ ጅቦ ነው አስረክቤህ የምመጣው!!”
አባትም ዳግም፣
“ዛሬ ነግሬሃለሁ ለአያ ጅቦ ነው የምጥልህ” አለው፡፡
ልጁ ማልቀሱን ቀስ በቀስ አቆመ፡፡ አያ ጅቦ ምራቁን እያዝረበረበ፣ ቆበሩን እየደፈቀ ቀረ፡፡ በመካያውም አንድያውን ጥሎ ለመሄድ፤ “ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ ቄሱም ዝም፣ ዳዊቱም ዝም፤ ሆነ!
***
አንድ የሀገራችን ዕውቅ ገጣሚ፤ የደርግ ሥርዓት አብቅቶ የኢህአዴግ ሥርዓት ሲጀምር፤
“ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ከምሮ እየናደ፣ ንዶ እየከመረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ ማለቂያው ጀመረ” ብሎ ፅፎ ነበር፡፡
ዕውነትም የማያልቅ ዘመን የለም፡፡ አዲስ ሁሉ ያረጃል፡፡ የማይለወጥ አንዳችም ሥርዓት የለም። የአዲሱ አሸናፊነትም አይቀሬ ነው፡፡ አጠራጣሪው በየትኛው መንገድ ይለወጣል? የሚለው እንጂ ለውጥ መቼም ቢሆን መቼ መምጣቱ የማይቀር ሂደት ነው፡፡ ፈረንጆቹ፤
Everything changes
Except the law of change የሚሉት የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡
“ከቶም ከለውጥ ህግ በስተቀር የማይለወጥ ነገር የለም” እንደማለት ነው፡፡ እነሆ ለውጥ መምጣቱ ግድ ከሆነ ለለውጥ ዝግጁ መሆን ዋናውና አስፈላጊው ጉዳይ ነው፡፡ የሀገራችን ሰው አንድ ለውጥ ባገኘ ቁጥር በዚያው ተወስኖና ያንን ፍፃሜ - ነገር አድርጎ ማሰብ ይቀናዋል፡፡ ሆኖም መሰረታዊ ችግሩ የጊዜ - ቀመር አለማበጀት (Time - plan አለመኖር) ነው፡፡ መልካም የጊዜ ግምት ማጣትን የመሰለ ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት የለም፡፡ “ጊዜ የስልጣን እጅ ነው” ይለናል፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን። ጊዜ የሚታዘዘው ሰው ብቻ ነው - ዕውነተኛ ባለስልጣን! ለሁሉም፤ ትክክለኛ ምክር ሰሚ መሆን ታላቅነት ነው፡-
“ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ …
ምንኛ ታድሏል የሰነፍ አዕምሮ
 እንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና!
አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
ይሉናል ገጣሚ ከበደ ሚካኤል፡፡ ካልተደማመጥን ወንዝ አንሻገርም፡፡ ካልተጋገዝን አገር አትንቀሳቀስም፡፡ አሉታዊ ገፅታዎቻችንን ብቻ እየነቀስን በማጉላት ለውጥ የሚመጣ የሚመስለን በርካቶች ነን፡፡ ሀገራችን ለሶስት ሺህ ዘመን ያጠራቀመችው በቂ አሉታዊ ነገሮች አሏት፡፡ እነዚህን በማጉላት ምንም አናተርፍም፡፡ ይኸውም ልዩ ዕውቀት እየመሳሰለን የምንደገግ ብዙ ነን፡፡ ስለ ሰው ክፉ ክፉውን በመናገር፣ ዘራፍ ማለት የአሸናፊነት ስሜት መፍጠሩ ዕውነት ነው፡፡ ሆኖም በትክክለኛ መፍትሄ ካልታገዘ ጎጂ ባህል ይሆናል፡፡ ለመፍትሄ ያልተዘጋጀ ህብረተሰብ፣ የአፍራሽነት ሥነ-አዕምሮ ይዞ የሚጓዝ ስለሆነ ከለውጥ ይልቅ ወግ-አጥባቂነትን ያዘወትራል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለው ማህበረሰብ ከጅምሩም ተራኪ (Story-teller) ህብረተ-ሰብ ነው፡፡ ከተግባራዊነት ይልቅ አፍአዊነት ይቀናዋል፡፡ አፍአዊነቱም በጥናት ላይ አለመመስረቱ ደግሞ ነገረ - ዓለማችንን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ነው የወሬ አገር ሆነን የቀረነው፡፡
ያለምነውንና የተመኘነውን ዲሞክራሲ እስከምናገኝ ብዙ ዳክረናል፡፡ ብዙ ፈግተናል፡፡ ልጃቸውን ይወረውሩልኛል ብሎ በር በሩን ሲያይ እንዳመሸው አያ ጅቦ፤ በመጨረሻው ዘጋግተው እንደሚተኙ እንዘነጋለን፡፡ እንደ ህፃኑ ልጅ የሚያስቸግረውንም የኢትዮጵያ ህዝብ አባብለው እንደሚያስተኙት ግልፅ እየሆነ ሲመጣ፤ የእኛ ትርፍ “ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” ማለት ብቻ ከሆነ አደጋ ላይ ነን፡፡ ዲሞክራሲ ከራሳችን የሚፈልቅ እንጂ ማንም የሚሰጠን ምፅዋት ወይም ዳረጎት አይደለም!

የደንብ ልብስ በመልበስና የጦር መሳሪያ በመያዝ ዘረፋ የሚያካሂዱ የፖሊስ አባላት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በከተማችን አዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች የደንብ ልብስ የለበሱና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሆኑ ፖሊሶች፣ ግለሰቦችን በጦር መሳሪያ በማስፈራራትና በማስገደድ ዘረፋ እያካሄዱ መሆኑን ከፖሊስ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ዘራፊዎቹ በተለያዩ ቀናትና በተለያዩ ስፍራዎች በመዘዋወር “ዶላር እንመነዝርላችኋለን”፣ በማለትና መንዛሪዎቹን በጦር መሳሪያ በማስገደድ፣ የያዙትን ዶላርና ሞባይል ስልክ ይዘው ይሰወራሉ ተብሏል፡፡
ከፖሊስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 6፡30 አምስት የፌደራል የወንጀል መከላከል ፀጥታ ህግ ማስበር ዳይሬክቶሬት ቲም አዛዥ የሆኑና ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ልዩ ቦታው ሳሪስ አቦ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ አንድ ግለሰብን “ዶላር እንመንዝርልህ” በማለት ይዘውት ከገቡ በኋላ ለመመንዘር የያዘውን 160ሺ ብር በጦር መሳሪያ አስፈራርተው በመቀማት ላዳ ታክሲ ይዘው ከተሰወሩ በኋላ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት የሆኑ 5 ፖሊሶች ከአንዲት ወጣት “ዶላር እንመንዝርልሽ” በማለት 310 ሺ ብር እና ግምታቸው 16ሺ ብር የሆኑ ሁለት ሞባይሎችን በመሳሪያ አስፈራርተው በመቀማት ከተሰወሩ በኋላ በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በአራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ራስ መኮንን አካባቢ በሚገኘው ኦይል ሊቢያ ነዳጅ ማደያ ውስጥ የማደያው ሰራተኛ የሆነውን ግለሰብ በስለት በመውጋትና እጅና እግሩን በገመድ በማሰር፣ ይዞት የነበረውን ከ55 ሺ ብር በላይ ዘርፈዋል የተባሉ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጃንሜዳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አባላት  አራት ተጠርጣሪዎችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
በፖሊስ አባላት የሚፈፀመው ዘረፋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱን ያመለከተው የፖሊስ መረጃ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው 22 አዲሱ ሰፈር አካባቢ በሚገኘው ሳንቶያዝ የመጠጥ ማከፋፈያ በተባለው ስፍራ ተጠርጣሪዎች የፖሊስ ታርጋ የለጠፈ አንድ ጋቢና ፒካፕ በመያዝ ወደ መጠጥ ማከፋፈያው መደብር ገብተው “ዶላር መንዝርልን” ብለው ከጠየቁ በኋላ ዶላር እንደማይመነዝር ሲነገራቸው “የፖሊስ አባላት ነን” በማለትና መታወቂያቸውን በማሳየት የድርጅቱን ባለቤት በካቴና አስረው፣ ካዝናውን እንዲከፍት ካደረጉት በኋላ በውስጡ የሚገኘውን 540ሺ ብር እና ግምቱ 50ሺ ብር የሚያወጣ ሞባይሉን በመውሰድ፣ “ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዘንህ እንሄዳለን” በማለት መኪና ውስጥ አስገብተውት፣ ወደ ሰዋራ ስፍራ ከወሰዱት በኋላ ከመኪናው አውርደው ጥለውት ተሰውረዋል፡፡
እነዚሁ ተከሳሾች በድጋሚ ቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው መብራት ኃይል በሚባል ቦታ ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡20 አንድ ግለሰብ ሊፍት እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ ከገቡ በኋላ በመሳሪያ በማስፈራራት በሻርፕ አፍነው፣ ከመኪና ካስወረዱት በኋላ 28ሺ ብር፣ ላፕቶፕና መኪናውን ይዘው ተሰውረው ከአዳማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሊያዙ እንደቻሉ ፖሊስ ጠቁሟል፡፡

የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ “አዴፓ” እና አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን ከሁለቱ ፓርቲዎች ስራ አስፈፃሚ አባላት የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች በስራ አስፈፃሚ ደረጃ የመከሩ ሲሆን በአዴፓ በኩል የፓርቲው ሊቀ መንበርና ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም በአብን በኩል ሊቀመንበሩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ስብሰባውን መርተዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ የአዴፓ አስራ አንዱም የስራ አስፈፃሚ አባላት የተገኙ ሲሆን በተመሳሳይ የአብን ዘጠኙም ስራ አስፈፃሚዎች መገኘታቸው ታውቋል፡፡ ውይይቱ በዋናነት አሁን ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ ታሳቢ ያደረገ ነው የተባለ ሲሆን በፀጥታ፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በልማትና በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት የጋራ ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ ከሁለቱ ፓርቲዎች ስራ አስፈፃሚዎች የተመረጡት የጋራ ኮሚቴው አባላት ወደፊት ዝርዝር መግለጫ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡