Administrator

Administrator

 ከ400 በላይ ኢንዱስትሪዎች ምርት አቁመዋል ተብሏል

              በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ከ446 በላይ ኢንዱስትሪዎች በገጠሟቸው የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ምርት አቁመው መዘጋታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኢንዱስትሪዎቹ መዘጋት በዋናነት የተጠቀሱት ምክንያቶች፡- የጥሬ እቃና የፋይናንስ እጥረት፣ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ችግርና የተቀናጀ የመንግስት ድጋፍ እጦት ናቸው ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ የምርት ግብአት ከውጭ አስመጥተው ማምረት ያልቻሉ 26 የኤሌክትሮኒክስና የማሽነሪ ፋብሪካዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ መዘጋታቸው ታውቋል፡፡
 ከማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካዎች ውስጥ ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙት የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ምርመራና ልማት ማዕከል እንደገለጸው፤ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ የፓወር ኬብል፣ ትራንስፎርመር፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ኬብል፣ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ፍሪጅና ሞባይል የመሳሰሉትን ምርቶች የሚያመርቱ 26 የማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ ተዘግተዋል።
ከውጭ ምንዛሬ እጥረት በተጨማሪ የሃይል መቆራረጥ፣ የፋይናስ አቅም እጥረትና የመሥሪያ ቦታ ችግር  ለፋብሪካዎቹ ተግዳሮት እንደሆነባቸው የጠቆመው ማዕከሉ፤ በዚህም ሳቢያ በማምረት ላይ የሚገኙም ፋብሪካዎች ቢሆኑ ባለፉት 9 ወራት ሲያመርቱ የነበረው ከ20 በመቶ በታች  አቅማቸውን በመጠቀም እንደሆነ አመልክቷል፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ተያያዥ ተግዳሮቶች የውሃና መጠጥ ማምረቻ ኢንዱስትሪውም ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አልቀረም፡፡ በቅርቡ 20  የሚደርሱ የታሸገ ውሃ አምራች ኩባንያዎች ተግዳሮቱን መቋቋም አቅቷቸው መዘጋታቸው አይዘነጋም።

Saturday, 07 May 2022 15:08

ወይኔ

ከፀጉርሽ ዘለላ ከዓይኖችሽ ሽፋሽፍት
ከፈገግታሽ ላሕይ ከዚያ መቃ ደረት
ከአለንጋ ጣቶችሽ ከሎጋው ቁመትሽ
በዓይኖቼ ቆንጥሬ፤
ለከርሞ አዝመራ
እዘራው ይመስል ከልቤ ሸሸግኹት
ፍቅርሽን ቋጥሬ፡፡
ደጅ አዳሪ ልቤን
ያላደበ ቀልቤን
በተስፋ ሣባብል፤
ከአጥሬ ነቅዬ ሳበጅልሽ አልጋ፣
መደብ ስደለድል፣
እኔ የሰኔ ሟች ቀልደኛ ገበሬ
ከደጄ ላይ ሞፈር ከቁናዬም ዘሬ
ከሠራ አካላትሽ “ለዘር” የቋጠርሁት
ተሰወረ ከእጄ ከጉያዬ አጣኹት፡፡
ከዓይኔ ላይ የቀረሽ፣
ልቤ ላይ የቀረሽ፣
የተኛሽ ካንጀቴ
ያልዘራሁሽ ወይኔ፣
ያልቀጠርኩሽ ወይኔ፣
አንቺ ሆይ ስስቴ
ከሰው አፀድ በቅለሽ፣
ለሰው ማጀት ደርሰሽ፣
ከሰው ቤት ተጠምቀሸ
ከሰው አቁማዳ ከሰው ዋንጫ ተሾምሽ፡፡
ባልጤሰበት ገንቦ፣ባልታጠነ ዋንጫ
የስርቆት ወይን ጠምቆ መሆን መዛበቻ
ዘርን ለወፍ ሰጥቶ ፀፀት መሠንበቻ፡፡

      ሰሜን ኮርያ በፕሬስ ነጻነት ጭቆና አቻ አልተገኘላትም

             ባለፉት 5 አመታት ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የአለም ህዝብ የፕሬስ ነጻነት ጭቆና እንደተባባሰበትና በመላው አለም 455 ጋዜጠኞች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ የተባለው የፕሬስ ነጻነት ተሟጋች ተቋም በበኩሉ፤ በ28 የአለማችን አገራት የፕሬስ ነጻነት እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱንና ከአለማችን አገራት መካከል በፕሬስ ነጻነት ጭቆና ሰሜን ኮርያን የሚፎካከራት እንዳልተገኘ ከሰሞኑ ባወጣው የ2022 የፈረንጆች አመት አለማቀፍ የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በዘንድሮው የፕሬስ ነጻነት ሪፖርቱ ካካተታቸው 180 የአለማችን አገራት መካከል ሰሜን ኮርያ  180ኛ ደረጃን መያዟ የተነገረ ሲሆን፣ ኤርትራ 179ኛ፣ ኢራን 178ኛ፣ ቱርኬሚኒስታን 177ኛ፣ ማይንማር 176ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
አውሮፓዊቷ ኖርዌይ የፕሬስ ነጻነት በእጅጉ ያበበባት የአመቱ ቁጥር አንድ የአለማችን አገር ናት ያለው ሪፖርቱ፤ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ኢስቶኒያና ፊንላንድን እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ሰጥቷቸዋል፡፡
ተቋሙ በጋዜጠኞችና በነጻ ሚዲያ ተቋማት ላይ የሚደርሱ ዘርፈ ብዙ ጥቃትና ጉዳቶችን በመገምገም ባወጣው የዘንድሮው ሪፖርቱ፤ የፕሬስ ነጻነት እጅግ አስከፊ በሆነ ደረጃ ላይ የሚገኝባቸው ብሎ የጠቀሳቸው አገራት 28 ሲሆኑ ይህን ይህል ብዛት ያላቸው አገራት በዚህ ምድብ ውስጥ ሲካተቱ ይህ የመጀመሪያው መሆኑም ተነግሯል፡፡
ቁጥጥር የማይደረግበትና አለማቀፍ ተደራሽነት ያለው የድረገጽ ሚዲያ ለሃሰተኛ መረጃዎች ስርጭትና ፕሮፓጋንዳ መስፋፋት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ መንግስታት በሚዲያ ላይ የሚያደርጉት አፈናም ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክቷል፡፡አገራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ከመቼውም በተለየ ፍጥነት እንደምታበለጽግና ለማንም እንደማትተኛ ባሳለፍነው  ሳምንት በአደባባይ የዛቱት የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን፣ ባለፈው ረቡዕ በ4 ወራት ጊዜ ውስጥ 14ኛውን ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፋቸው ተነግሯል፡፡
ሰሜን ኮርያ ከመዲናዋ ፒንግያንግ አቅራቢያ ከሚገኘው ሱናን የተባለ አካባቢ ወደ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻዋ ያስወነጨፈችው በሰዓት 13 ሺህ 119 ኪሎ ሜትር ፍጥነት የመጓዝ አቅም ያለው ባለስቲክ ሚሳኤል፣ በፈረንጆች አመት 2022 አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ያስወነጨፈችው 14ኛው ሚሳኤል መሆኑን የዘገበው ሮይተርስ፤ ደቡብ ኮርያ በበኩሏ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀረውን የአዲሱ ፕሬዚዳንቷ ዩን ሱክ ዮል በአለ ሲመት ለማሳመር ተፍ ተፍ በምትልበት ወቅት የተፈጸመውን ይህን የሚሳኤል ሙከራ #ውጥረትን አባባሽ; ስትል በፍጥነት እንዳወገዘችው አስነብቧል፡፡
የደቡብ ኮርያ መንግስት ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ሰሜን ኮርያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያዥጎደጎደችው ያለው የሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊት ለኮርያ ባህረ ሰላጤ ብቻ ሳይሆን ለአለማቀፉ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ስጋት ነው ሲል እንዳወገዘው የጠቆመው ዘገባው፣ አገሪቱ ከሰሜን ለሚቃጣባት ማንኛውም ጥቃት የከፋ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ማስታወቁንም አመልክቷል፡፡
የጃፓን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ማካቶ ኦኒኪ በበኩላቸው፤ ከምድር በ780 ኪሎ ሜትር ያህል ከፍታ 500 ኪሎ ሜትሮችን ያህል ያቆራረጠውን ይህን የሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊት #በትዕግስት ሊታይ የማይገባው ጸብ አጫሪ ትንኮሳ; ሲሉ ያወገዙት ሲሆን፣ ሰሜን ኮርያ ባለፈው ወር ህዋሶንግ የተባለውን በግዙፍነቱ አቻ የማይገኝለት አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ማስወንጨፏንም ዘገባው አስታውሷል፡፡  ባለፉት 3 ወራት አፕሊኬሽኖች 37 ቢሊዮን ጊዜ ዳውሎድ ተደርገዋል አለማቀፉ የአፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ 8.6 ቢሊዮን ደርሷል

             አሜሪካ፣ ሁሉም የአውሮፓ ህብረት አገራትና የህብረቱ አባላት ያልሆኑ ሌሎች 32 የአለማችን አገራት የተካተቱበት አንድ የ60 አገራት ቡድን፤ ነጻ፣ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የኢንተርኔት አገልግሎት በአለማቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ባለፈው ሳምንት የጋራ ስምምነት መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡
አገራቱ መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎትን ከማፈን ይልቅ ሃሳብን በነጻነት ለማንሸራሸርና ለዲሞክራሲ ግንባታ የሚውል ገንቢ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን አምነው ለዘርፉ ልማት ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ሲሉ የፈጸሙት ነው በተባለው በዚህ ስምምነት፣ አገልግሎቱን ማግኘት ላልቻሉ በመላ አለም የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አለማቀፍና ነጻ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማከናወን መስማማታቸውን ነው ቢዝነስ ስታንዳርድ የዘገበው፡፡
ስምምነቱን ከፈጸሙት ሌሎች አገራት መካከል አልባኒያ፣ ካናዳ፣ አርጀንቲና፣ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ታይዋን፣ ዩክሬንና ኡራጓይ እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለመዘርጋት የተስማሙት 60 አገራት ቢሆኑም፣ በቀጣይ ሳምንታት ሌሎች ተጨማሪ አገራት የቡድኑ አባል የሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ቻይና፣ ህንድና ሩስያ በስምምነቱ ውስጥ እንዳልተካተቱም አመልክቷል፡፡
በሌላ ተያያዥ ዜና ደግሞ፤ በፈረንጆች አመት 2022 የመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ብቻ ከአፕል ስቶርና ጎግል ፕሌይ የተለያዩ አፕሊኬሽኖች 37 ቢሊዮን ጊዜ ዳውሎድ እንደተደረጉና አጠቃላዩ አለማቀፍ የአፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ መጠን 8.6 ቢሊዮን መድረሱ ተዘግቧል፡፡
ሴንሰር ታወር የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ እንዳለው፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ብዛት ያላቸው አፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ የተደረጉት ከጎግል ፕሌይ ሲሆን ከድረገጹ 28.3 ቢሊዮን ጊዜ ዳውንሎድ ተደርጓል፡፡ ቲክቶክ የተባለው የቪዲዮ ማጋሪያ አፕልኬሽን በብዛት ዳውንሎድ በመደረግ ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን፣ አፕሌኬሽኑ ይፋ ከተደረገበት 2018 መጀመሪያ አንስቶ በድምሩ ከ3.5 ቢሊዮን ጊዜ በላይ ዳውንሎድ መደረጉ ተነግሯል፡፡
ከቲክ ቶክ በመቀጠል በብዛት ዳውንሎድ በመደረግ የሚከተሉት አፕሊኬሽኖች ኢንስታግራም፣ ፌስቡክ፣ ዋትሳፕና ቴሌግራም መሆናቸውም ተቋሙ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡


ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ብቻ በሜዲትራኒያን ባህር እና በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት በጉዞ ላይ የነበሩ ከ3 ሺህ 535 በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ለሞትና ለመጥፋት መዳረጋቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ እንዳለው፤ በአመቱ የተመዘገበው የሞቱና የጠፉ ስደተኞች ቁጥር በ2020 ከነበረበት በእጥፍ ያህል የጨመረ ሲሆን፣ ከመረጃ አያያዝ ጉድለት ጋር በተያያዘ ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ በእጅጉ ሊጨምር እንደሚችልም አስታውቋል፡፡ በፈረንጆች አመት 2022 ያለፉት ወራት ብቻ 478 ስደተኞች ለሞትና ለመጥፋት መዳረጋቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ለአደጋ በመጋለጥ ረገድ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የአፍሪካ አገራት ስደተኞች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ ሪፖርቱ በየብስ ላይ ጉዞ የሞቱትንና የጠፉትን ስደተኞች እንደማያጠቃልልም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
አገራት ስደተኞችን ላለመቀበል የሚያደርጉት የበዛ የድንበር ላይ ክልከላና ጥበቃ የስደተኞችን ለአደጋ የመጋለጥ እድል በእጅጉ እንደጨመረው የጠቆመው ኮሚሽኑ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞች በአስቸጋሪ የባህር ላይ ጉዞ የሚያጋጥማቸውን ዘርፈ ብዙ አደጋ ለመቀነስ ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

   ጦርነቱ 3ሺህ 153 ንጹሃን ዩክሬናውያንን ለሞት ዳርጓል ተብሏል

               ከሩስያ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ከ70 ቀናት በላይ ያስቆጠረችው ዩክሬን፤ ከጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከአለማቀፉ ህብረተሰብ በጥሬ ገንዘብ ብቻ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ማግኘቷ ተነግሯል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሻምያልን ጠቅሶ ቢዝነስ ስታንዳርድ እንደዘገበው፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለዩክሬን ያሳየው ድጋፍ ትልቅ ትርጉም ያለውና ምስጋና የሚቸረው ነው፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የተሟላ የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገሪቱ ሌሎች አዳዲስ የድጋፍ አገልግሎት ፕሮግራሞችን ለመጀመር ማቀዷንም ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ለድህረ ግጭት የመልሶ ግንባታ ስራዎች የሚውል ገንዘብ የማሰባሰቢያ መድረክ መፍጠሩን እንደገለጹ የጠቆመው ዘገባው፣ ዩክሬን ባለፈው ሳምንት ብቻ ከአለም ባንክ የ500 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቷንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ለሞት የተዳረጉት ንጹሃን ዩክሬናውያን ቁጥር 3ሺህ 153 መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ በዩክሬን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለሞት ከተዳረጉት 3ሺህ 315 ሰዎች መካከል 722 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ 154 ያህሉ ደግሞ ህጻናትና ልጃገረዶች ናቸው፡፡
በአገሪቱ በጦርነቱ ሳቢያ ለሞት ከተዳረጉት ዜጎች በተጨማሪ 3 ሺህ 316 ንጹሃን ዜጎች ለመቁሰል አደጋ መጋለጣቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 324 ሴቶች፣ 349 ያህሉ ደግሞ ልጃገረዶችና ህጻናት መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉንም የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል፡፡

  ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ቄስ ምዕመናኑን ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ሲያስተምሩ፤
“ምዕመናን ሆይ!
ዓለም ሰፊ ነው። መልክ ረጋፊ ነው። ዛሬ ያለን ሀብት፣ ንብረት፣ ነገ ከእኛ ጋር የለም። እኛ ዛሬ አለን እንላለን እንጂ ነገ ከነገ ወዲያ ሁላችንም የለንም። ወደ ማይቀረው ቤታችን እንሄዳለን። ስለዚህ ያንን ቤታችንን ዛሬ እንስራው። ዛሬ እናመቻቸው፡፡ ስለሆነም ጠግበን ስንበላ፣ የተራቡትን እናስብ። ለመዝናናት ስንጠጣ የተጠሙትን እናስታውስ። ከልኩ በላይ ስንለብስና ስናጌጥ የተራቆቱትን፣ እርቃናቸውን በብርድ የሚፈደፈዱትን፣ የተራቆቱትን “እንደምን አድረው ይሆን?” እንበል። “ታምሜ ጠይቃችሁኛልን? ታርዤ አልብሳችሁኛልን? ተቸግሬ ደጉማችሁኛልን?; እያለ ይጠይቃችኋል። ስለዚህ ስጡ። ዛሬ የሰጣችሁትን ነገ በሰማይ ቤታችሁ ታገኙታላችሁ። የዚህ ዓለም ሀብት ንብረት አላፊ ጠፊ ነው። ኗሪው ደግ ስራ ነው።
“ባለፀጋ ነን”፤ “ብልፅግና አለን”፤ “ባለ ጊዜ ነን” ብላችሁ አትታበዩ። አትደገጉ። “ከእኔ በላይ ማን አለና?” እያላችሁ፣ ሰው ጤፉ አትሁኑ። ዓለም አላፊ፣ መልክ ረጋፊ  ነውና አሁን በእጃችሁ ያለ አዱኛ፣ በእጃችሁ ያለ ፀጋ፣ በእጃችሁ ያላችሁ የጦር ሀይል፣ የእኛ ነው ያላችሁት ቤት ንብረት ሁሉ፣ ነገ የእናንተ አይደለም፡፡ በእጃችሁም የሚቆይ አይደለም። ስለዚህ ምን ያህል አጋሰስ ጫንኩ? ምን ያህል ፈረስ ለጎምኩ? ምን ያህል እህል በጎተራ ሞላሁ? እያላችሁ አትጨነቁ። ይልቁንም በስነ-ምግባር የታነፁ ልጆችን አሳድጉ። በግብረ ገብነት መንፈሱን የሞላ ብልህና አስተዋይ ትውልድ ፍጠሩ! የሰማይ ቤታችሁን ማነፅ ዛሬ ጀምሩ!
በመጨረሻም የዛሬ ትምህርቴን የማሳርገው በአንዲት አጭርና ጠንካራ መልዕክት ነው። እነሆ፡-
“ስጡ፣ ታገኛላችሁ!
አንኳኩ፤ይከፈትላችኋል!
ሁለት ያለው፣አንዱን፣ አንድ ለሌለው ይስጥ!”
አሉና ቄሱ አቡነ-ዘበሰማያት ብለው አበቁ። በቤተ-ክርስቲያን አካባቢ የተገኘውን የበዓል ቡራኬም፣ ሰምበቴም፣ ከምዕመናኑ ጋር ተቋድሰው ከደጀ- ሰላሙ ወደ ቤታቸው ሄዱ።
የቅስና ልብሳቸውን ቀይረው ወደ ግብዣ መሄድ ነበረባቸውና ወደ ቁም ሰንዱቃቸው ሲሄዱ፣ የልብሶቻቸው ቁጥር በግማሽ ቀንሶ ያገኙታል፡፡ በድንጋጤ ባለቤታቸውን ጠርተው፤
“አንቺ ልብሴን ሁሉ ምን በላው?” ሲሉ ጠየቋት፡፡
ሚስታቸውም፤ “ለተቸገረ ሰጠሁት” አለቻቸው።
“እንዴት? ለምን? ለኔ ሳትነግሪኝ?” አሉ በንዴት።
ሚስቲቱም፤
“ቅድም በተስኪያን ነገሩን እኮ! “ሁለት ያለው፣ አንዱን፣ አንድ ለሌለው ይስጥ” አላሉም?”
ቄሱ በብስጭት፤ “ታድያ #ይስጥ; አልኩ እንጂ #ልስጥ” አልኩ? ወጣኝ?!” አሉ፤ይባላል።
***
መንግስታዊ መመሪያዎቻችን፣ የምንደነግጋቸውም ህጎች ሁሉ፣ በእኛም ላይ መስራት እንዳለባቸው አንርሳ! በእኛ ባይደርሱ በልጆቻችን ላይ ተፈጻሚ ናቸው። “ህግን የሚሰራት ሰው፤ የሚያፈርሳት እራሱ ነው” ይላሉ እንግሊዞች - #a law-maker is a law breaker; እንዲል መጽሐፉ። ስንፅፈውና ስንደነግገው ቀላል፤ እንተግብርህ ስንለው ግን እጅግ አዳጋች፤ አያሌ ጉዳይ አለ። በቴሌቪዥን መስኮት  ከረቫት አስረን፤ ሽክ ብለን የተናገርነውን ሁሉ መሬት ለማውረድ ብዙ ጣጣ አለበት! ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ለማውረድ ይቸግራልና! ለዛውም ለመስቀልም ሳንቸኩል፣ ለማውረድም ሳንቸኩል ከሆነ ነው! ለማንኛውም፣ “ወዳጄ ልቤ ሆይ! የእኔ መከራ ያንተ መከራ አይደለምን?” የማለት ወኔው ቢኖረን መልካም ነው!
ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን በአፄ ቴዎድሮስ አንደበት፤
“ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታውሰው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ”
ይላል። ያልሞከርነውን እናስብ። ገና ብዙ ይቀረናል። ስለ ዴሞክራሲ ለፈፍን እንጂ ስራ አልሰራንም። ስለ ፍትህ አወራን እንጂ ገና ፍርድ ቤቱን አላፀዳንም፤ አላስተካከልንም። ዳኞች መደብን እንጂ ዳኝነታቸውን አላየንም፡፡ አሁንም ከእነ ሸረሪት ድሩ አለ። ስለዚህ ገና ነን! “በጊዜያዊ ድል አንኩራራ!” ይላል መፅሐፈ ድል ዘሱማሌ ወኤርትራ። የንብረት ክፍፍል፣ የሀብት እኩልነት አለመቀራረብ፣ በተለይ ከፓርክ መስፋፋት አንፃር እንየው ስንል፣ ዛሬም አባይን በጭልፋ ነው! የኑሮ ውድነትን ስናስብም “ኑሮ ውድነት ድሮ ቀረ!” እያልን እንድንናፍቅ ገፍቶናል። አንድ ገጣሚ እንዳለው፤ “ዱሮ፣ ዱሮ ቀረ!”
በአንድ ወቅት በሃይለ ስላሴ ዘመን አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፤ “የእኛ ችግር - ችግር ምን እንደሆነ አለማወቃችን ነው” ብለው ነበር። በቀድሞው ጊዜ የነበረ አንድ የጋምቤላ ተወካይ ደግሞ፤ “ችግር አለ፤ ግን ችግሩን ለመናገርም ችግር አለ” ብሏል። ለአገራችን፤ ችግር፤ “የአስራ ሶስት ወር ፀጋ” ነው! እንደ ዝናብና ፀሀይ ያልተለየን በረከተ- ሰማይ- ወምድር!
አንድ ስለ ኤችአይቪ የተዘፈነ መዝሙራችን፣ ብዙዎች “ማለባበስ ይቅር” በሚለው የሚያውቁት፣ “የማንፈልገውን፣ በራሳችን፣ ደርሶ
 ሌላው ላይ እንዲደርስ፤ አናርገው ጨርሶ” ይላል።
እኛ በጎረቤቶቻችን ላይ፣ ጎረቤቶቻችንም በእኛ ላይ እንዳይደረግ የምንሻው፤ ተንኮል፣ ሴራ፣ ዲፕሎማሲያዊ አሻጥር በርካታ ነው። ከስዊስ ካናል መከፈት እስከ ዐባይ ድልድይ መገንባት፤ ዘመናት አልፈዋል። ተጠቃሾቹ ሁለቱ ይሁኑ እንጂ መንግስታት ተለዋውጠዋል። አስተሳሰብ ፈርሶ ተገንብቷል። ወድቆም ተነስቷል። አንዳንድ አገሮች ልክ እንደኛ አገር- እንደ አፈ ታሪኳ ፊኒክስ ናቸው። አፈር ልሰው ሞተው ይነሳሉ! ትንሳኤ አላቸው! ዳግማይ ትንሳኤን ያለነገር አልወደድነውም! ወደፊት የሚራመድ ለአገር አሳቢ ሰው፤ መሪ መፈክሩ - ትንሣኤ - ዳግማይ ትንሣኤ ይሁን ብለናል። ጥናቱን ይስጠን! ጥናቱንም፤ ፅናቱንም ቢሆን፡-
“ሁለት ያለው፤
አንዱን፤
አንድ ለሌለው ይስጥ!!” አሜን።
መንግስት “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” የሚለውን ተረት ልብ ይበል። የእግር መንገዶች ወይ ወደ አውራው ጎዳና፤ ወይ ወደ ጫካ ማምራታቸው አይቀሬ ነውና! ቀላል የሚመስሉ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ውስብስብ የአገር ጉዳይ ሊያመሩ እንደሚችሉ ታሪክ አሳይቶናል። በቤንዚን መወደድ የአውቶቡሶች ስራ ማቆም፤ የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ፤ የሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ፤ የክፍለ ጦሮች ጥያቄ ማንሳት ለ1966ቱ አብዮት ያደረጉትን ያየ፣ ልምድ ሊወስድ ይገባዋል። “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” ይላል አበሻ። ታዋቂው ደራሲ ሔሚንግ ዌይም፤ “coming events cast their shadows” ይለናል። “ለከርሞ የሚቆስል እግር፤ ዛሬ ማሳከክ ይጀምራል” ይላሉ የተረት ጠበብት። ቸር ወሬ ያሰማን!     


 • በከልል አደረጃጀት ላይ የተለየ ሃሳብ ይዘን መጥተናል
   • መሬት የህዝብና የዜጐች ነው ብለን እናምናለን
   • የተለየ የቋንቋ ፖሊሲ ቀርፀናል

                አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በምስረታ ላይ ነው - “የኢትዮጵያ ዜጐች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት” ይሰኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠና አለማየሁ አንበሴ፣ ከፓርቲው የምስረታ አስተባባሪ ኢ/ር እንግዳወርቅ ማሞ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ አዲሱን ፓርቲ እንተዋወቀው፡፡

             እስቲ በምስረታ ሂደት ላይ ስለሚገኘው ፓርቲያችሁ ጥቂት ይነገሩን?
አሁን ፓርቲያችንን እንደ አዲስ የምንመሰርተው ቢሆንም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ግን የነበረ ፓርቲ ነው፡፡ በወቅቱ በነበረው መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች እውቅና ነፍጎን የቆየን ሲሆን አሁን የተሻለ ነገር መጥቷል ብለን ነው እንቅስቃሴ የጀመርነው፡፡ ፓርቲያችን በውስጡ ትልቅ ፅንሰ ሃሳብ ያለው፣ ሀገራዊነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በህዝብ ፍፁም የስልጣን ባለቤትነት የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ ስያሜውም “የኢትዮጵያ ዜጐች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት” የሚል ነው። መርሁ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ ብቻ የሚመሰረት ፖለቲካን ማራመድ ነው፡፡
የፓርቲው የምስረታ ሂደት ምን ላይ ደርሷል?
ከምርጫ ቦርድ የመመስረቻ ሂደቱን የምናሳልጥበት የድጋፍ ደብዳቤ ካገኘን በኋላ፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል፡፡ በፀረ ሽብር ህጉ “ሽብርተኛ” ተብለው በተፈረጁ ድርጅቶች ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸውን ዜጐች በሙሉ በፓርቲያችን ውስጥ በአባልነት የማሰባሰብ ስራ እያከናወንን ነው። አሁን ወደ ማጠቃለሉ እየሄድን ሲሆን ቀጣይ ተግባራችን ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ይሆናል፡፡
መቼ ለማካሄድ አቅዳችኋል?
በቅርቡ ጉባኤውን እናካሄዳለን፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ጉባኤውን ያካሄደበትን አራዳሽ እንዲፈቅድልን ጠይቀናል፡፡ እኛ ብልፅግናን አዳራሽ ስንጠይቅ፣ ብዙዎች ግር ሊላቸው ይችላል፡፡ በኛ ግንዛቤ ግን የብልፅግና ጉባኤ የተደረገበት አዳራሽ የህዝብ ንብረት ነው፡፡ ለብልፅግና ብቻ የሚያገለግልበት ምክንያት የለም፡፡ እኛም የመጠቀም መብቱ አለን፡፡ በዚህ መሰረት ነው የአዳራሽ ጥያቄውን ያቀረብነው ድንገት የማይሳካ ከሆነ ብለን ደግሞ ሆቴል ዲ አፍሪክንም ጠይቀናል፡፡
ፓርቲያችሁ የሚመራበት ርእዮተ ዓለም ምንድን ነው?
ለበራሊዝም ነው፡፡ ሊበራሊዝም ስንል ከሌሎች ለየት የሚያደርገን፣ በሀገራዊ እሳቤዎች የተቃኘ መሆኑ ነው፡፡ መሬት የህዝብና የዜጐች መሆን አለበት ብለን አናምናለን፡፡ በዚያው ልክ በተመረጡ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ መንግሥት ጣልቃ መግባት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡  ወደፊት ይፋ የምናደርገው ለየት ያለ የቋንቋ ፖሊሲ አዘጋጅተናል፡፡ በክልል አደረጃጀት ላይ የተለየ ሃሳብ ነው ይዘን የመጣነው፣ ፕሮግራማችንን ለህዝብ ይፋ ስናደርግ የሚገለፅ ይሆናል፡፡
ፓርቲያችሁ ሊያሳካቸው የሚሻቸው ግንቦች ምንድን ናቸው?
አንደኛ፤ ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ማፅናት ላይ እንሰራለን፡፡ አንዳች መልካም ግብ ላይ ለመድረስም እንተጋለን፡፡ ስልጣን በጉልበት ሳይሆን በህዝብ ይሁንታ ብቻ የሚገኝበት ሀገር ለመፍጠር እንሻለን፡፡ ለዚህም ያለንን እውቀት ሁሉ ተጠቅመን እንታገላለን፡፡ ሀገሪቱ በትክክል የዜጐች መብት የሚረጋገጥባት እንድትሆን እንተጋለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት የነገሰባት፣ ኢትዮጵያ እንደትመሰረትም አበክረን እንታገላለን፡፡ የአገሪቱን ሉአላዊ ድንበር እናስከብራለን፡፡ እኛ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ከማንም ጋር አንደራደርም፡፡
በዋናነት በየትኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ነው የምትንቀሳቀሱት?
በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች አባላት አሉን፤ ስለዚህም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች -  በመላው ኢትዮጵያ እንንቀሳቀሳለን ማለት ነው፡፡ በጉባኤያችን ላይ ከ1500 በላይ አባላት ይሳተፋሉ፡፡


 በክልሉ የተፈፀመው የንፁሃን ግድያ በዓለምቀፍ ገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል

                 መንግስት በኦሮሚያ ክልል “ኦነግ ሸኔ” በሚል የሚጠራውን ታጣቂ  አማፂ ቡድን ለመደምሰስ በጀመረው  ወታደራዊ ዘመቻ በርካታ ንጹሃን  መገደላቸውን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ያመለከተው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፤ የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በዓለም አቀፍ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
መንግስት በክልሉ “ኦነግ ሸኔ”ን  ለማጥፋት  በሚል እያካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ፤ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከ278 በላይ ንፁሃን ሰዎች ተገድለዋል ብሏል -ፓርቲው  በመግለጫው፡፡
በቅርቡ የፌደራል መንግስቱና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፤ታጣቂውን አማጺ ቡደን ከክልሉ ለማጥፋት የመጨረሻውን   ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚያካሂዱ በጋራ መግለፃቸውን ኦፌኮ ጠቅሷል፡፡
በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች  “ዓሳውን ለመያዝ ባህሩን ማድረቅ” በሚል መርህ የሚመራው ወታደራዊ ዘመቻ እየተካሄደ ነው ያለው ፓርቲው፤ “በዚህም ንፁሃንን መግደል፣ቤታቸውን ማቃጠል፣ንብረታቸውን መዝረፍና ማውደም፣ ዜጎችን ለእስርና ለስቃይ መዳረግ አንዳንዴም ልጆቻቸው ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ወላጆችን መግደል …የተለመደ  እየሆነ መጥቷል”  ብሏል፡፡ በተለይም በአራቱ የወለጋ ዞኖች፣በምዕራብ ሸዋ፣በሰሜን ሸዋና ምስራቅ ሸዋ፣በምዕራብ አርሲ፣በምስራቅ ጉጂ በኦሮሚያ ልዩ የቦረና ዞኖች፣ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ዞን እንዲሁም በቤኒሻንጉል- ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞንና  አካባቢዎቹ  ወታደራዊ ዘመቻው መካሄዱን ፓርቲው አመልክቷል- በመግለጫው፡፡
 በቅርቡ  ደግሞ የመንግስት ሃይሎች  ከወታደራዊ ዘመቻው ጋር በተገናኘ የድሮንና ሄሊኮፕተር ጥቃቶችን ፈፅመዋል ሲል የወነጀለው ኦፌኮ፤ የጥቃት እርምጃው ለበርካታ ንጹሃን ሞት፣  ለመኖሪያ ቤቶችና ንብረት ውድመት፣  ከሞት ለተረፉት  መፈናቀል መዳረጉን ከጥቃቱ ሰለባዎች መረዳት ይቻላል” ብሏል፡፡
“ይህም የሸኔን ቡድን ጠራርጎ ለማጥፋት” በሚል ሰበብ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን የጥቃት መጠን ፍንትው አድርጎ ያሳያል  ብሏል -ፓርቲው በመግለጫው፡፡
ኦፌኮ፤በኦሮሚያ ክልል ለተፈፀመው የንጹሃን ዜጎች  ግድያ ከመንግስት በተጨማሪ “ፅንፈኛ ያለውን “የፋኖ ቡድን” ተጠያቂ አድርጓል፡፡
“ይህ ቡድን ለኦሮምያ ክልልም ሆነ ለአጎራባች ክልሎች የሰላም ስጋት እየሆነ ነው፡፡ ሆኖም ክልላዊ መንግስቱ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤  የፌደራሉ መንግስት ፈጣንና  ህጋዊ መፍትሄ እንዲሰጥ እንጠይቃለን” ብሏል በመግለጫው፡፡፡
ፓርቲው በመጨረሻ ባወጣው ባለ7 ነጥቦች የአቋም መግለጫ፤ የፌደራል መንግስቱ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የገባውን ጦርነት በማቆም፣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የጠየቀ ሲሆን መንግስት በአፋጣኝ የተኩስ አቁም በማድረግ ወደ ድርድር እንዲገባ  ኦፌኮ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በማሳረጊያው፤ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ የንፁሃን ዜጎች ግድያን በዓለማቀፍ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
የፌደራል መንግስት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በጥምረት በጀመሩት ታጣቂውን አማፂ ቡድን የማፅዳት ወታደራዊ ዘመቻ ድል መመዝገቡ በመንግስት የተገለፀ ሲሆን ለንፁሃን ላይ ጥቃት መድረሱን በተመለከተ ግን እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡


Page 4 of 603