Administrator

Administrator

          ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም እ.ኤ.አ በ2013 በአለም ዙሪያ በሚገኙ 95 አገራት በሰራው ጥናት፣ ባለፈው አመት ከአፍሪካ አህጉር አነስተኛ ሙስና የተሰራባት አገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ማስታወቁን የኬንያው ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አልጀዚራ በበኩሉ ትናንት ባወጣው ዘገባ፣ በኢትዮጵያ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ቅንጦት ነው ብሏል፡፡
የአገራትን ዜጎች አስተያየትና ሌሎች መስፈርቶችን በመጠቀም ባወጣቸው የሙስና መለኪያዎች በ6 በመቶ ነጥብ ያገኘችው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት አነስተኛ ሙስና ያለባት አገር እንደሆነች የገለጸው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፣ ዴንማርክ፣ ፊላንድ፣ ጃፓንና አውስትራሊያም በተመሳሳይ ሁኔታ 1 በመቶ ነጥብ ይዘው በአለማችን አነስተኛ ሙስና ያለባቸው አገሮች መሆናቸውን በጥናቱ ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
በሙስና መለኪያዎች 84 በመቶ ውጤት ያገኘችው ሴራሊዮን በአለማችን ከፍተኛ ሙስና የሚፈጸምባት አገር እንደሆነች የገለጸው ተቋሙ፣ ላይቤሪያ፣ የመንና ኬንያ እንደሚከተሏት አስታውቋል፡፡
ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አነስተኛ ሙስና ያለባት አገር ሩዋንዳ መሆኗን የገለጸው ተቋሙ፣ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት መካከልም ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ሱዳን በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘው እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
አልጀዚራ በበኩሉ ትናንት ለንባብ ባበቃው ዘገባው በኢትዮጵያ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ቅንጦት እንደሆነ ገልጾ፣ ምንም እንኳን 52 በመቶ የአገሪቱ ህዝብ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የተሟላለት ቢሆንም፣ የውሃ መስመር ቤታቸው ድረስ የተዘረጋላቸው የአገሪቱ ዜጎች 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ አስረድቷል፡፡በአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ከሚኖሩት ዜጎች የንጹህ የመጠጥ ውሃ ቧንቧ መስመር የተዘረጋላቸው አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑም ገልጧል፡፡የአገሪቱ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ቢሆንም፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሁንም ድረስ በበቂ ሁኔታ አለመሟላቱንና ከፍተና ስራ መስራት እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

        ላለፉት ዓመታት የቅጂና ተዛማች መብቶች ጥሰት በፈጠረው ስጋት ተቀዛቅዞ የከረመው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘንድሮ የተነቃቃ ይመስላል፡
ታዋቂ ድምፃውያን ለአዲሱ አመት አዳዲስ ነጠላ ዜማቸውንና አልበማቸውን አበርክተዋል፡፡ ይሄም ለሰሞኑ የአውዳመት ድባብ ተጨማሪ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ፣ የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”፣ የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው” የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”፣ የቤተልሔም ዳኛቸው “ሰው በአገሩ” እና የተስፋፅዮን ገ/መስቀል “ጀመረኒ” እንዲሁም የቴዎድሮ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማም ለአዲስ ዓመት ከተበረከቱ የሙዚቃ ስራዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡
“ሙዚቃ እንደ በረዶ በቀዘቀዘበት ዘመን ደፍረውና መስዋዕትነት ከፍለው አዲስ ነገር ይዘው ስለመጡ አድናቆት ይገባቸዋል” ብለዋል በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስራ ኃላፊ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሙዚቃ ባለሙያ፡፡
በዚህ አመት ለአድማጭ ይበቃሉ ከተባሉት የሙዚቃ አልበሞች መካከል፣ የኤፍሬም ታምሩ አልበም የሚጠቀስ ሊሆን፣ የድምፃዊው ወላጅ እናት በሳምንቱ መጀመሪያ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት አልበሙ ሳይለቀቅ ቀርቷል፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ”
ከሁለት ሳምንት በፊት ገበያ ላይ የዋለው አብነት አጎናፍር “አስታራቂ” አልበም 14 ዘፈኖች የተካተቱበት ሲሆን ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሀይሉና አቤል ጳውሎስ አቀናብረውታል፡፡  ድምፃዊው ሶስተኛ ስራው በሆነው በዚህ አልበም አገራዊ፣ ማህበራዊ እና የፍቅር ጉዳዮችን የዳሰሳ ሲሆን ከአድማጮች በተገኘ አስተያየት፣ ከአብነት ስራዎች ውስጥ ስለአገር የዘፈናቸው “አያውቁንም”፣ “ለማን ብዬ”፣ “አስታራቂ” እና “የኔ ውዳሴ” የተሰኙት ይበልጥ ተወደዋል፡፡ በAB ሙዚቃና ፊልም ፕሮዳክሽን የታተመው “አስታራቂ” አልበም፤ በአርዲ ኢንተርቴይመንት እየተከፋፈለ ሲሆን የአዲሱ ዓመት አንዱ ገጸ በረከት ነው፡፡ አብነት ከአማርኛ ሙዚቃ በተጨማሪ ሱዳንኛ እንደሚጫወት የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ “አያሌሌ” የተሰኘ የጉራጊኛ ዘፈን አካትቷል፡፡ ድምፃዊው በአብዛኛው ዘፈኖቹ ላይ በግጥምና በዜማ ድርሰት ተሳትፏል፡፡
የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”
ለአዲሱ ዓመት በገፀ-በረከትነት ከቀረቡት አልበሞች ውስጥ የታምራት ደስታ አራተኛ ስራ የሆነው “ከዛ ሰፈር” አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለአድማጭ ጆሮ የደረሰው ይሄው አልበም፤ 14 ዘፈኖችን አካትቷል፡፡ ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ሚካኤል መለሰና ኪሩቤል ተስፋዬ በቅንብር የተሳተፉበት ይሄ ስራ፤ በግጥም እና ዜማ ጌትሽ ማሞ አማኑኤል ይልማ፣ መሰለ ጌታሁንና ኢዩኤል ብርሃኔን አሳትፏል፡፡ በናሆም ሪከርድስ አሳታሚና አከፋፋይነት ገበያ ላይ የዋለው የታምራት አልበም፤ በስፋት እየተደመጠ ሲሆን በተለይም “ሊጀማምረኝ ነው” “አዲስ አበባ”፣ “ማማዬ” እና የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “ከዚያ ሰፈር” የተሰኙ ዘፈኖች የበለጠ እየተሰሙ እንደሚገኙ ከአድማጮች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡
የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ”
ከበደሌ ጋር አመቱን ሙሉ በሚዘልቅና “ወደ ፍቅር ጉዞ” በተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት ከአድናቂዎቹ ጋር ለመገናኘት የጀመረው ስራ የተሰናከለበት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ ከሁለት ሳምንታት በፊት የለቀቀው “ሰባ ደረጃ” የተሰኘ  ነጠላ ዜማው በስፋት እየተደመጠ ሲሆን ማህበራዊ ድረ - ገፆችን በተለይም ፌስ ቡክን ተቆጣሮጥት ሰንብቷል፡፡ የቴዲ “ሰባ ደረጃ” ፒያሳ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ ሰራተኛ ሰፈር፣ አራት ኪሎን፣ ታሪካዊ ክስተቶችንና አለባበሶችን ከፍቅር ጋር እያሰናሰለ ያነሳሳል፡፡ የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማ ሙሉ አልበምን የመወከል ያህል ተቀባይነት አግኝቶ በየምሽት ቤቱ፣ በየሆቴሉና በየሬስቶራንቱ በስፋት እየተደመጠ ያለ የአዲስ አመት የበዓል ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”
“ቆሪብኪለኩ” (ቆረብኩልሽ) በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ በተለይም “ንኢባባ” በተሰኘው ዘፈኑ የሚታወቀው ወጣቱ የትግርይኛ ዘፋኝ ሰለሞን ሃይለም ከሳምንታት በፊት “ውህበቶ” የተሰኘ አልበም ለአድማጭ አቅርቧል፡፡ አልበሙ 12 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን፣ ስለ ሃገር፣ ስለ ፍቅር ስለማህበራዊ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡ ሙሉ ግጥምና ዜማው በራሱ በድምፃዊው የተሰራ ሲሆን፣ በቅንብሩ አብዛኛውን ዘፈኖች ተወልደ ገ/መድህን ሲሰራ፣ ሁለት ዘፈኖችን ዮናስ መሃሪ እና ደነቀው ኪሮስ፣ አንዱን ዘፈን ዘመን አለምሰገድ አቀናብረውታል፡፡ በስፋት እየተደመጠም ይገኛል፡፡
የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው”
ድምፃዊና ጋዜጠኛ ዮሴፍ ገብሬም አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ “መቼ ነው” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበሙን ከ10 ቀናት በፊት በገበያ ላይ አውሏል፡፡ ለዝግጅት 6 አመታትን የፈጀው ይሄው አልበም፤ በአገር፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ላይ የሚያተኩር ሲሆን 7 አቀናባሪዎችና የተለያዩ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተሳትፈውበታል፡፡ “መቼ ነው” የተሰኘው የአልበሙ መጠሪያ፣ “ክፉ አይንካብኝ” ሲል ስለ አገር የዘፈነው፣ “ፍቅር ነው ያገናኘኝ” እንዲሁም ስለአንድነትና መተባበር (በጉራጊኛ) የዘፈናቸው ይበልጥ ተወዳጅ እንደሆኑለት ከአድማጮች ያገኘነው አስተያየት ይጠቁማል፡፡ አልበሙ በተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተደመጠ ይገኛል፡፡  
የቤተልሔም “ሰው በአገሩ”
በ1996 ዓ.ም ለአድማጭ ባቀረበችው “ቅዳሜ ገበያ” የተሰኘ ባህላዊ ዜማዋ የምትታወቀው ድምፃዊት ቤተልሔም ዳኛቸው፣ ሰሞኑን “ሰው በአገሩ” የተሰኘ አዲስ አልበሟን ለአድማጭ አቅርባለች፡፡
ነዋሪነቷ በስዊዘርላንድ የሆነው ድምፃዊት ቤተልሔም ያቀረበችው አዲስ አልበም፤ 13 ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪና የድምፃዊቷ ባለቤት ዳዊት ጥላሁን ባቀናበረው በዚህ አልበም ውስጥ ራሱ ዳዊትና ቤተልሔም ጥላሁን በዜማና ግጥም ደራሲነት ተሳትፈዋል፡፡
የተስፋፅዮን “ጀመረኒ”
በባህላዊ የማሲንቆ አጨዋወቱ አድናቆት የተቸረው ድምጻዊ ተስፋፅዮን ገ/መስቀል ከሰሞኑ “ጀመረኒ” የተሰኘውንና ራሱን በማሲንቆ ያጀበበትን የትግርኛ ሙዚቃዎች ለአድማጭ አብቅቷል፡፡ ከዚህ ቀደም “ቆልዑ ገዛና” የተሰኘ አልበም አውጥቶ ተቀባይነትን ያገኘው ድምፃዊው፤ በ“ጀመረኒ” አልበሙ የሰርግን ጨምሮ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 13 ሙዚቃዎችን አካትቷል፡፡ አልበሙን ዳአማት መልቲ ሚዲያ አሳትሞ እያከፋፈለው ሲሆን፣ ለአዲሱ ዓመት በተለይ በትግርኛ ዘፈን አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
“አራዳ” ቪሲዲ ኮሌክሽን
በመስፍን ታምሬ ፕሮዲዩሰርነት የታተመውና 14 እውቅ ድምፃዊያን የተሳተፉበት “አራዳ” ባህላዊ እና ዘመናዊ ዘፈኖች በምስል (በቪዲዮ) የቀረቡበት ነው፡፡ የዚህ ቪሲዲ አዘጋጅ “ኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን” ሲሆን “ፒያሳ ዘ አራዳ ኢንተርቴይመንት” አሳትሞ ከትናንት ጀምሮ እያከፋፈለው ይገኛል፡፡ በ“አራዳ” ኮሌክሽን ቪሲዲ ላይ ሸዋንዳኝ ሃይሉ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ እመቤት ነጋሱሲ (ሰንዳበል)፣ ጃኪ ጎሲ፣ የኦሮምኛ ዘፋኙ አበበ ከፍኔና  ቤተልሄም ዳኛቸውን ጨምሮ 14 ያህል ታዋቂ ድምፃዊያን ተሳትፈውበታል፡፡
“አራዳ” ብቸኛው ለአዲስ ዓመት የተዘጋጀ ቪሲዲ እንደሆነ ታውቋል፡፡

“How Successful People Think” በሚል ርዕስ በዶ/ር ጆን ማክስዌል ተፅፎ፣ በአባተ መንግስቱ የተተረጎመው “የአሸናፊነት መንገዶች” የተሰኘ መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት ለአንባቢያን ደርሷል፡፡ መፅሀፉ እንዴት ወደ አሸናፊነትና ስኬት እንደሚደረስና የመድረሻ መንገዱን የሚያመለክቱ ቁልፍ ነጥቦች የተነሱበት ሲሆን በተለይም በትኩረት ስለማሰብ፣ የፈጠራ አስተሳሰብን ስለመግራትና ስልታዊ አስተሳሰብን ስለመቃኘት በስፋት ይተነትናል፡፡ በ11 ርዕስ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገው መፅሀፉ፤ በ168 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ46 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ በተያያዘ ዜና በዮሐንስ በላይ የተደረሰው “ሃመልማል” የተሰኘ ልብወለድ መፅሀፍ አንባቢያን እጅ ደርሷል፡፡ መቼቱን ደሴና ኮምበልቻ ላይ ያደረገው ድርሰቱ፤ አዝናኝ የፍቅርና የህይወት ታሪክን ነው ተብሏል፡፡ 57 ገፆች ያሉት የዮሐንስ በላይ መፅሀፍ፤ በ25 ብር ገበያ ላይ ውሏል፡፡

የባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድህን ሥራዎችን የሚቃኘውና “ምሥጢረኛው ባለቅኔ” በሚል ርዕስ በደራሲ ሚካኤል ሽፈራው ተዘጋጅቶ በ1996 ዓ.ም ለአንባቢያን ቀርቦ የነበረው መጽሐፍ፤ በ10ኛ ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ታተመ፡፡ ደራሲው ለመጽሐፉ ሰፊ የአርትኦት ሥራ ማከናወናቸውንና አዳዲስ መረጃዎችን ማካተታቸውን በመግቢያው ላይ አመልክተዋል፡፡ 365 ገፆች ያሉት መጽሐፉ፤ በ80 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ዓለም አቀፍ የሰላም አምባሳደር በሆነው ወጣት መኮንን ሞገሴ የተዘጋጀው “ከልካይ የሌለው ስጥ” የተሰኘ መፅሀፍ የፊታችን ሰኞ በብሄራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡ መፅሀፉ በዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የስነ-ልቦና ዝቅጠት ላይ ያተኩራል የተባለ ሲሆን ፀሐፊው በስድስት ወራት የመስክ ቆይታው በአዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ ዲላ፣ ሐገረ-ማርያም፣ ያቤሎ፣ ኢትዮጵያ ሞያሌ፣ ኬኒያ ሞያሌ እና ኬንያ ጋንቦ ድረስ በመሄድ በጎዳና ተዳዳሪነት፣ በተሸካሚነት እንዲሁም በአስተናጋጅነት እየሰራ የታዘባቸውን የከተበበት እንደሆነ ታውቋል፡፡ በእሁል ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን አስተባባሪነት የሚመረቀው መፅሀፉ፤ የደራሲው ሁለተኛ ስራ ሲሆን ከዚህ ቀደም “የአስተናጋጁ ገፆች ቅፅ 1” የተሰኘ መፅሀፍ ለንባብ ማብቃቱ ታውቋል፡፡

በሰአሊና ደራሲ ገዛኸኝ ዲኖ የተፃፈው “በቃ እንሂድ” የተሰኘ ልብወለድ መፅሀፍ የፊታችን ማክሰኞ በሩሲያ የሳይንስና የባህል አዳራሽ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ይመረቃል፡፡ 460 ገፅ ያለውና መቼቱን ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ላይ ያደረገው መፅሃፉ፤ በአንድ ሰዓሊ ህይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ እለት ደራሲያንና ሌሎች እንግዶች የሚገኙ ሲሆን በመፅሀፉ ዙሪያ ውይይት ይካሄዳልም ተብሏል፡ መፅሐፉ በ70 ብር ከ85 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡ የመፅሃፉ፤ ደራሲ ሰዓሊ ገዛኸኝ ዲኖ ለ19 ዓመታት በፈረንሳይ አገር እንደኖረ ታውቋል፡፡

  •  ከትኬት ሽያጭ ቢያንስ 5 ሚሊዮን ብር እንደተገኘ ተገምቷል *
  • “ኮንሰርት” የሚወዱ “የእጅ አመለኞች” አስቸግረው ነበር

ከወራት በፊት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው “ሬጌ ዳንሶል ኢን ኢትዮጵያ ቁጥር 1” የሙዚቃ ኮንሰርት የተሰረዘው ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ጋር በመገጣጠሙ እንደነበር አዘጋጁ “አውሮራ ኤቨንት ኦርጋናይዘርስ” መግለጹ ይታወሳል፡፡ የኮንሰርቱ ተጋባዥ ከያኒ ጃማይካዊው ቢዚ ሲግናል ለሸገር ሬዲዮ በሰጠው ቃለምልልስ ደግሞ፤ “ኮንሰርቱ የተሰረዘው በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱ መዘግየቶች ነው” ብሎ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲሉ፣ ኮንሰርቱ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ የምሽቱ ድባብ ከምሽቱ 2፡00 ላይ የተጀመረው የሙዚቃ ኮንሰርቱ፤ በአገራችን የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኞችና በዲጄ እየተሟሟቀ የዘለቀ ሲሆን ራስ ጃኒ፣ ሲዲኒ ሳልመን፣ ጃሉድ አወል፣ ሃይሌ ሩትስ እና ጆኒ ራጋ ማራኪ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

በየመሃሉ በዲጄ ባባ ትንፋሽ እያገኙ መድረኩን ያደመቁት ኢትዮጵያዊ ድምፃዊያን፤ በታዳሚው ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝተዋል፡፡ መድረኩ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅቷል፤ የላይትና የድምፁ ቅንብር እንከን የለሽ ነበር፡፡ ኮንሰርቱ ተጀምሮ እስከሚያልቅ አንድም የድምፅ መቆራረጥና መረበሽ አላጋጠመም፡፡ ድምፃዊያኑ ለኮንሰርቱ በቂ ዝግጅት ለማድረጋቸው በመድረክ ያሳዩት ጥንካሬና ብቃት ምስክር ነው፡፡ ራስ ጃኒ የምሽቱ ምርጥ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጃሉድ “የገጠር ልጅ ነኝ”፣ “አሻበል ያሆ”፣ የእርግብ አሞራ እና ሌሎችንም ስራዎቹን በጥሩ ሁኔታ በመጫወት ታዳሚውን የማረከ ሲሆን ሃይሌ ሩትስ በበኩሉ፤ “ባዶ ነበር”፣ “እርጅና መጣና” በተሰኙ ታዋቂ ዘፈኖቹ ተመልካቹን አዝናንቷል፡፡ ጆኒ ራጋም አነቃቂ ምሽት ለመፍጠር ችሏል፡፡ ጆኒ ራጋና ሃይሌ ሩትስ በጋራ ተቀናጅተው ያቀረቡት ሥራም ልዩ አድናቆት የተቸረው ነበር፡፡ በየመሃሉ ዲጄ ባባ መድረኩን በሙዚቃ እያደመቀ፣ አርቲስቶቹም ትንፋሽ እየሰበሰቡ፣ ታዳሚውም ልቡ እስኪወልቅ እየጨፈረና እየዘለለ ጊዜው ወደ አምስት ሰዓት ነጐደ፡፡

የዕለቱ “ሰርፕራይዝ” መድረኩን በጥሩ ሁኔታ በመምራት የተሳካለት ጋዜጠኛ አንዷለም ተስፋዬ፤ በኮንሰርቱ መጀመሪያ ላይ “ሰርፕራይዝ” እንዳለ በመግለጽ የታዳሚውን ልብ አንጠልጥሎት ነበር፡፡ እናም የመድረኩ መብራት ደብዝዞ፤አይን የማያጨልም ድባብ ተፈጠረ፡፡ ሰፋፊ ኮፍያ ያደረጉ ሰዎች ደንገዝገዝ ባለው ድባብ ውስጥ እየሮጡ ወደ መድረኩ በመግባት ቦታ ቦታቸውን ያዙ፡፡ ታዳሚው ለ“ሰርፕራይዙ” ጓጉቶ ነበር፡፡ የመድረኩ መብራት ፏ ብሎ በራ፡፡ “ሰርፕራይዟ” ዘፋኝ፤ ነጭ ብልጭልጭ ቲ-ሸርትና ነጭ ቁምጣ ለብሳ ብቅ አለች፡፡ ጭብጨባና ፉጨቱ ቀለጠ፡፡ ድምጻዊት ቤቲ ጂ. “ከአንተ አይበልጥም” የሚለው ዘፈኗን በዳንስ ቡድኗ ታጅባ፣ አብራ እየተውረገረገች አስነካችው፡፡ እየዘፈነችና እየጨፈረች ታዳሚውን አስጨፈረችው፡፡ ሁለተኛ ዘፈኗም ቀጠለ፡፡ በጣም ግሩም አቀራረብ ነበር ያሳየችው፡፡ ሥራዋን ጨርሳ ከመድረክ ስትወርድም በህዝቡ አድናቆትና ሆታ ተሸኝታለች፡፡ የታዳሚውን ልብ የነካ ስራ “እኔ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ሆኜ እንኳን አላወቅሁም፤ በጣም የተገረምኩበትና የተደነቅሁበት ጉዳይ ነው” ይላል፤የ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘርስ” ዋና ስራ አስኪያጅ ሸዊት ቢተው፡፡ ቤቲ ጂ.፣ ጃሉድ አወል፣ ሃይሌ ሩትስ እና አንድ ፊቱ አዲስ የሆነ አርቲስት ወደ መድረክ ወጡና ማንም ያልጠበቀውን ዘፈን መዝፈን ጀመሩ፡ “ነገን ላያት እጓጓለሁ” በማለት፡፡

ይሄን ጊዜ ታዳሚው መጮህ፣ ማልቀስና ማፏጨት ያዘ፡፡ በድንገተኛው ዘፈን አዳራሹ ተደበላለቀ፡፡ ከአመት በፊት በድንገት ህይወቱ ያለፈውን የሬጌውን አቀንቃኝ ድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ለመዘከር ታስቦ የቀረበው ሙዚቃ የመላ ታዳሚውን ልብ የነካ ነበር፡፡ በመሃል “ወይኔ እዮቤ ውውው…” በማለት ጩኸቷን ያቀለጠችው አንዲት ወጣት ታዳሚ፤እንባዋ በጉንጯ እየወረደ ደረቷን መድቃት ጀመረች፡፡ ጓደኞቿ ተረጋጊ እያሉ ቢያፅናኗትም አልቻለችም፡፡ “እዮቤን በጣም ነው የማደንቀው፤ አሟሟቱም በጣም ያሳዝናል” እያለች ማልቀሷን ቀጠለች፡፡ የብዙሃኑ ታዳሚ ጩኸት፤ ፉጨትና ዝላይማ በቃላት ለመግለጽ አዳጋች ነው፡፡ “ነገን ላያት እጓጓለሁ” ቀጠለ፡፡ አርቲስቶቹ በጣም ያምሩ ነበር፤የሙያ አጋራቸውን የዘከሩበት መንገድም አንጀት ይበላል፡፡ “ይህንን ሃሳብ ያፈለቁት ዝግጅቱን ከእኛ ጋር በአጋርነት የሰሩት የሲግማ ኢንተርቴይንመንት የስራ ባልደረባ ብሩክ እና የአውሮራ ማኔጅመንት አባል ዳዊት ናቸው” ይላል ሸዊት፡፡

ያረፈደው የክብር እንግዳ እኩለ ሌሊት አለፈ፡፡ የእለቱ የክብር እንግዳ ብቅ አላለም፡፡ ዲጄ ባባ የመሸጋገሪያውን ሙዚቃ እያጫወተ 7፡45 ሆነ፡፡ የመድረኩ አጋፋሪ አንዷለም ተስፋዬ ብቅ አለ፡፡ “አሁን በጉጉት የምትጠብቁት እንቁ ድምፃዊ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ ይመጣል” ሲል አዳራሹ በጩኸት ተሞላ፡፡ ከስንት ጥበቃ እና ጉጉት በኋላ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ ሲመጣ አዳራሹ ይበልጥ ተናጋ፡፡ ዳልቻ ኮት በነጭ ሸሚዝና ጠቆር ባለ ግራጫ ሱሪ ያደረገው ቢዚ ሲግናል፤ ነጭ ፍሬም ያለው ጥቁር መነፅር ፊቱ ላይ ሰክቶ ለታዳሚው ሰላምታ ሰጠ፡፡ የእሱን ዘፈን ለመስማት ዝግጁ መሆን አለመሆናችንን ጠየቀ፤ “Are you feeling good?” (በጥሩ ስሜት ውስጥ ናችሁ እንደማለት) ታዳሚው በፉጨት እና በጭብጨባ ምላሽ ሰጠ፡፡ በዚህ ምሽት ከዚህ ውብ ህዝብ ጋር በመገናኘቱ የተሰማውን ደስታ አርቲስቱ ገለፀ፡፡ በግምት በ20ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ቢዚ ሲግናል፤ እንደብዙዎቹ የሬጌ ሙዚቀኞች ፀጉሩ ድሬድ አይደለም፡፡

ምንም እንኳ በዘፋኝነት ይበልጥ የታወቀው “One more night” የተሰኘውን የፊል ኮሊንሰን ቀደምት ስራ ሪሚክስ አድርጎ ከተጫወተ በኋላ ቢሆንም በርካታ የራሱን ስራዎችም አበርክቷል፡፡ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ የመጣው ታዳሚው በጭፈራ ጉልበቱን ከጨረሰ በኋላ ነበር፡፡ በየመሃሉ “ቢዩቲፉል ሌዲስ” እያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በማድነቅ ማቀንቀኑን ቀጠለ፡፡ አጠገቤ የነበሩ በቡድን የታደሙ ሰዎች “በቃ ያቺን ዋን ሞር ናይት ይዝፈናትና እንሂድ” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡ እርሱ ግን አውቆም ይሁን ሳያውቅ ዘፈኗን ወደ መጨረሻ ላይ አደረጋት፡፡ ሲግናል እስከ ሌሊቱ 9፡41 ድረስ መድረክ ላይ ነበር፡፡ ታዳሚው ግን ከቢዚ ሲግናል ይልቅ በኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ይበልጥ መደሰቱን ታዝቤአለሁ፡፡ የኮንሰርቱ አንዳንድ እንከኖች በምሽቱ ድራፍትና ሃሺሽ እኩል ሲጠጡ አመሹ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሀሺሽ በየደቂቃውና በየቅርብ ርቀቱ ይጨሳል፤ እንደጉድ ይጦዛል፡፡ ለሽታው ባዕድ የሆነ ያጥወለውለዋል፡፡ ያስመለሳቸውም ነበሩ፡፡ አጠገቤ የነበረ አንድ ታዋቂ አርቲስት፣ ሃሺሽ ከሚያጨስ አንድ ወጣት ጋር አንገት ለአንገት ሲተናነቅ አይቻለሁ- “ሌላ ቦታ ሄደህ አጭስ” በሚል፡፡ በርካታ ኪስ አውላቂዎችም (ሌቦች) አሰላለፋቸውን አሳምረው ነበር፡፡

ቦርሳዎች፣ ሞባይል ስልኮች፣ የኪስ ቦርሳዎችና ሌሎች ንብረቶች ለመንታፊዎች ሲሳይ ሆነው አምሽተዋል፡፡ አንድ የውጭ ዜጋ “ዋሌቴን ተሰርቄአለሁ፤ ውስጡ ፓስፖርት አለው፤ እባካችሁ እዚሁ እንዳልቀር ፓስፖርቱን እንኳን መልሱልኝ” የሚል መልዕክት በመድረክ አጋፋሪው አስነግሯል፡፡ ባለረጃጅም ተረከዝ ጫማዎችን የተጫሙ ሴቶች እግራቸውን ሲደክማቸው ጫማቸውንና ቦርሳቸውን መሬት ቁጭ አድርገው ሲጨፍሩ የሌባ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አንዲት ወጣት “ሌላው ቢቀር ጫማዬን እንኳን ባገኝ---” በማለት እንባዋ እንደጎርፍ እየፈሰሰ፣በታዳሚው ስር በመሽሎክሎክ ጫማዋን ስትፈልግ አስተውያለሁ፡፡ የ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘርስ” ዋና ሥራ አስኪያጅ ሸዊት ቢተው ስለስርቆቱ ጠይቀነው ሲመልስ፤ “የእኛ ኮንሰርት የመጀመሪያ ከማይመስልባቸውና ከሚለይባቸው ጉዳዮች መካከል በምሽቱ ከካራማራ ፖሊስ ጋር በመተባበር አዳራሽ ውስጥ ሆነው የሰው ንብረት የሰረቁ ሌቦችን ይዘን ሞባይል፣ ቦርሳ፣ ፓስፖርትና ሌሎች ንብረቶችን ለባለቤቶቹ ማስመለሳችን ነው” ብሏል፡፡ ከተሰረቁት እቃዎች አብዛኞቹ ለባለቤቶቹ እንደተመለሱና አንድ ሁለት ሰዎች ብቻ እቃቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ሸዊት ተናግሯል፡፡ ኮንሰርቱን ከ10 እስከ 12ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደታደሙት ከዚህም ውስጥ 2ሺህ ያህሉ በተጋባዥነት እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከትኬት ገቢም ቢያንስ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደተገኘ ተገምቷል፡፡

ክሪስ ፕሩቲ ስለ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ የፃፈችውን መፅሀፍ፣ ውብሸት ስጦታው (ክፉንድላ) ወደ አማርኛ በመመለስ “ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ” በሚል ርዕስ አሳትሞ ሰሞኑን ለገበያ አውሏል፡፡ መፅሀፉ ስለኢትዮጵያዊያን ስም አወጣጥ፣ የጣይቱ 5ኛ ባል ስለሆኑት የሸዋው ንጉስ አፄ ምኒልክ፣ ስለጣይቱ የእቴጌነት ማዕረግ፣ ከጣልያን ጋር ስለተደረጉት የአምባላጌ፣ የመቀሌና የዓድዋ ጦርነቶችና በርካታ ተያያዥ ታሪኮች ተካተውበታል፡፡ በ18 ምዕራፍ ተከፋፍሎ በ459 ገፅ የተመጠነው መፅሀፉ፤ በ80 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ደራሲያን፣ ሃያሲያንና ጋዜጠኞች በተገኙበት በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ተመርቋል፡፡

እናት ልጃቸው ያለቅጥ ማምሸቱ አስግቷቸዋል፡፡ ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ የ26 ዓመት ልጃቸው መጠጥ አይቀምስም፣ ብዙ ጓደኞችም የሉትም፡፡ ሁሌም በጊዜ ወደቤቱ የመግባት ዓመል ነበረው፤ዛሬ ግን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡ (የዛሬ 2 ዓመት ገደማ ነው) እናት ወገባቸውን በነጠላቸው አስረው እያቃሰቱ፣ ወደ አራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ በመሄድ፣ ልጃቸው እንደጠፋባቸውና የሞባይል ስልኩም እንደማይሰራ እንባ በጉንጫቸው እየፈሰሰ ለፖሊስ ተናገሩ፡፡ ስሙንና መልኩንም በደንብ አብራሩ፡፡
ፖሊስ ይሄኔ የልጁ ማንነት ገባው፡፡ ወጣቱ የመኪና አደጋ ደርሶበት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ገብቶ፣ ሃኪሞች አስቸኳይ የሲቲስካን ምርመራ እንዲያደርግና ውጤቱን ፖሊሶች ይዘው እንዲመጡ አዘው ነበር፡፡ ፖሊሶችም አደጋው የደረሰበትን ወጣት፣ ወደ “ውዳሴ ዲያግኖስቲክ የምርመራ ማዕከል” በመውሰድ ምርመራው በነፃ እንዲያገኝ አደረጉ
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአራዳ ክ/ከተማ ትራፊክ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊ ስለውዳሴ ዲያግኖስቲክ በሰጡት አስተያየት፤ “ምንም እንኳን ወጣቱ በደረሰበት ከባድ የመኪና አደጋ ከሞት ባይተርፍም ማዕከሉ ግን አስቸኳይ ምላሽ ሰጥቶት ነበር፤ ከእኛ ጋር በመተባበር በሚሰሩት ስራ ከፍተኛ አድናቆት አለን” ብለዋል፡፡
እንደዚህ መሰል አደጋዎች፣ አሊያም በተፈጥሮ በህመም ምክንያት በሃኪም የሲቲስካን ምርመራ ሲታዘዝ ዋጋው ከሌሎች ምርመራዎች ስለሚወደድ ብዙ ሰዎች እድሉን ሳያገኙ ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን የሰዎች ችግር ለመቅረፍ የሚሰራው “ውዳሴ ዲያግኖስቲክ የምርመራ ማዕከል”፤ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መርህ፤ ከ500 በላይ ለሆኑ ሰዎች ነፃ የሲቲስካን ምርመራ እንደሚያደርግ የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሃይሉ አስታወቁ፡፡ ማዕከሉ በ2001 ዓ.ም ተቋቁሞ 65 ያህል ሰራተኞችን እንደሚያስተዳድር የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት መርህ ከ5ሺህ በላይ ለሆኑ የሲቲስካን ምርመራ ፈላጊዎችና በራሳቸው ለመመርመር አቅም ለሌላቸው ሰዎች አገልግሎቱን እንደሰጠ አብራርተዋል፡፡
“አንድ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ከሚያገኘው ነገር ላይ አቅም የሌላቸውን መርዳትና ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት” ያሉት አቶ ዳዊት፤ በየአመቱ በጳጉሜ ወር በዘመቻ መልክ ነፃ የምርመራ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ የማዕከሉ የማርኬቲንግ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሰብለ ኃይሉ እንደገለፁት፤ ከአራዳ ክ/ከተማ ትራፊክ ፅ/ቤት ጋር በመተባበር የመኪና አደጋ ደርሶባቸው የሲቲስካን ምርመራ ለሚስፈልጋቸው ሰዎች፣ በየትኛውም ሰዓትና ቀን ነፃ የምርመራ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ “ዓመቱን ሙሉ ቢያንስ ከ4-5 ሰው በየቀኑ በተለያየ ምክንያት ምርመራው አስፈልጎት ሲመጣ ነፃ ምርመራ ያገኛል” ያሉት ወ/ሮ ሰብለ፤ ጳጉሜ ላይ በዘመቻ መልክ ለብዙ ሰዎች አገልግሎቱን የምንሰጠው ሌላውም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ምሳሌ ለመሆን ነው ብለዋል፡፡
“ምንም እንኳ ለትርፍ የተቋቋምን ብንሆንም መልካም ስራ ኪሳራ የለውም” ያሉት ወ/ሮ ሰብለ፤ ሰውን ማትረፍ መቻል በራሱ ትርፍ ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ባለፈው ዓመት ጳጉሜ ለ500 ሰዎች ነፃ ምርመራ ለማድረግ ጥሪ አቅርቦ፣ 950 ሰዎች መመዝገባቸውንና ሁሉም ነፃ ምርመራውን እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቃለክርስቶስ ሃይሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም፤ ማንኛውም የአገልግሎቱ ፈላጊ የሚመለከተው የመንግስት አካል በግሉ ለመርመር እንደማይችል ጠቅሶ ደብዳቤ ከፃፈለትና ሃኪም ምርመራው ያስፈልገዋል ብሎ ከመሰከረ፣ 500 ቢባልም የመጣው ሁሉ መመርመሩ አይቀርም ብለዋል፡፡
“ውዳሴ ዲያግኖስቲክ” በዚህ የበጎ አድራጎትና ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት እንቅስቃሴው እንደሚቀጥል የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ማዕከሉ በሚገኝበት አራዳ ክ/ከተማ  ነዋሪ ለሆኑ ታካሚዎች 20 በመቶ የክፍያ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ከዚህም በተጨማሪ ለክ/ከተማው ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት ይሰጣልም ተብሏል፡፡
ለነፃ ምርመራ ጳጉሜን ለምን መረጣችሁ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ዳዊት ሲመልሱ፤ “ጳጉሜ አሮጌው አመት አልቆ ወደ አዲስ አመት መሸጋገሪያ እንደመሆኑ መጠን፣ ሰዎች ነፃ ምርመራ አግኝተው በተስፋና በደስታ አዲሱን ዓመት እንዲቀበሉ የበኩላችንን ለማድረግ አስበን ነው” ብለዋል፡፡

ቀይ ስጋ፣ ስብና ጨው የበዛባቸው ምግቦች አይበረታቱም  

በሳምንት ከ10 ፖርሽን (1 ፖርሽን ለአንድ ሰው የሚበቃ ምግብ መጠን ነው) በላይ ቲማቲሞችን የሚመገቡ ወንዶች በዘር ፍሬ ዕጢዎች ካንሰር (Prostate Cancer) የመያዝ አደጋን 20 በመቶ እንደሚቀንሱ በእንግሊዝ የተደረገ ጥናት ጠቆመ፡፡
የብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ቡድን 20ሺህ የሚደርሱ ዕድሜያቸው ከ50-69 ዓመት የሆኑ የእንግሊዝ ወንዶችን የአመጋገብና የአኗኗር ዘዬ ያጠና ሲሆን, በየሳምንቱ ከ10 ፖርሽን በላይ ቲማቲሞችን (የተቆረጡ ቲማቲሞች፣ የቲማቲም ጭማቂ፣ በቲማቲም ሱጎ የተጋገረ ባቄላ) የተመገቡ ወንዶች በዘር ፍሬ እጢ ካንሰር የመጠቃት ዕድላቸው 18 በመቶ መቀነሱን ተመልክቷል፡፡
“የጥናት ውጤታችን ቲማቲም የዘር ፍሬ እጢ ካንሰርን በመከላከል ረገድ ጠቃሚ እንደሆነ ይጠቁማል” ያሉት ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት ተወካይ ቫኔላ ኢር፤ ግኝታችንን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናቶች መካሄድ አለባቸው ብለዋል፡፡
“ወንዶች በርካታ የተለየዩ ዓይነቶች አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን መመገብ፣ ጤናማ የሰውነት ክብደታቸውን መጠበቅና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው” ሲሉ መክረዋል ቫኔላ፡፡
ተመራማሪዎቹ የዘር ፍሬ እጢዎች ካንሰርን የሚከላከሉ ሌሎች ሁለት የምግብ ዓይነቶችንም መርምረዋል፡፡ ዳቦና ፓስታ በመሳሰሉት ከዱቄት የሚዘጋጁ ምግቦች ውስጥ የሚገኘው ሴሊኒየም የተባለ ንጥረ ነገር እንዲሁም ወተትና ቺዝ በመሳሰሉት የወተት ውጤቶች ውስጥ የሚገኘው ካልሲየም በፕሮስቴት ካንሰር የመጠቃት አደጋን እንደሚቀንሱ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ቲማቲምንና ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት የምግብ ንጥረ ነገሮች በቅጡ የሚጠቀሙ ወንዶች ለበሽታው የመጋለጥ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው ብለዋል አጥኚዎቹ፡፡
በጥናቱ ላይ አስተያየት የሰጡት ዶ/ር አያይን ፍሬም በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ አደጋን ለመቀነስ ይችሉ ዘንድ ወንዶች የትኞቹን የተወሰኑ ምግቦች መብላት እንዳለባቸው ተጨባጭ ጥቆማ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ማስረጃ አልተገኘም ብለዋል፡፡
ወንዶች እንደ ቲማቲማ ባለ አንድ የምግብ ዓይነት ላይ ብቻ መተማመን የለባቸውም የሚሉት ዶ/ር ፍሬም፤ “ጤናማ፣ በዛ ያሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያካተተ የተመጣጠነ ምግብ ከመደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ጋር ይበልጥ የተሻለ አማራጭ ነው” በማለት አስረድተዋል - ዶ/ር ፍሬም፡፡
የዩኬ ካንሰር ምርምር ተቋም ተወካይ ቶም ስታንስፌልድ በበኩላቸው፤ “ላይኮፒኒ በተባሉ ንጥረነገሮች የበለፀጉ እንደቲማቲም ያሉ ወይም ሴሌኒየም የያዙ ምግቦች የፕሮቴስት ካንሰር አደጋን ከመቀነስ ጋር ሊያያዙ ይችላሉ፤ ነገር ግን ይሄ ነገር አልተረጋገጠም፤ የአሁኑ ጥናት በምግብና በፕሮስቴት ካንሰር መካከል ግንኙነት ይኑር አይኑር ሊያረጋግጥ አይችልም” ብለዋል፡፡
ነገር ግን ሁሉም ወንዶች የፍራፍሬና አትክልት ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግን እንዲያዘወትሩ እናበረታታለን ያሉት ቶም ስታንስፌልድ፤ ቀይና በፋብሪካ የተቀነባበረ ስጋ እንዲሁም ስብና ጨው የበዛባቸው ምግቦችን በእጅጉ መቀነስ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የዘር ፍሬ እጢዎች ካንሰር በመላው ዓለም በወንዶች ላይ በስፋት የተሰራጨ ሁለተኛው የካንሰር ዓይነት ሲሆን በእንግሊዝ በየዓመቱ 10ሺ ገደማ ወንዶች በበሽታው ይሞታሉ፡፡