Administrator

Administrator

Saturday, 30 August 2014 10:57

የጸሐፍት ጥግ

ጉድጓድ ውስጥ ስትሆን መቆፈርህን አቁም፡፡
       ዴኒስ ሂሌይ (እንግሊዛዊ የፖለቲካ መሪ)
በርቀት ያለ ውሃ በአቅራቢያ የተነሳ እሳትን አያጠፉም፡፡
ሃን ፌይ (ቻይናዊ ፈላስፋ)
ካልተሰበረ አትጠግነው፡፡
 ቤርት ላንስ (አሜሪካዊ ባለሥልጣን)
ከምናውቀው የበለጠ ብልህ ነን፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን
(አሜሪካዊ ገጣሚና ወግ ፀሐፊ)
ቡትቶ ለብሰህ ተደራድረህ ሃር ልትለብስ ትችላለህ፡፡
የአይሁዶች አባባል
ታዳጊ የቀርከሃ ዛፎች በቀላሉ ይጎብጣሉ፡፡
የቬትናሞች አባባል
ጎረቤትህን እባብ ከነደፈው አንተም አደጋ ላይ ነህ፡፡
የአፍሪካዊያን (ስዋሂሊ) አባባል
እውነተኛ ወርቅ እሳት አይፈራም፡፡
የቻይናዊያን አባባል
ሚስት የሌለው ወንድ ልጓም እንደሌለው ፈረስ ነው፡፡
የቬትናሞች አባባል
ኮረዳ ወላጆቿን ለማስደሰት ስታገባ፣ ባሏ የሞተባት ራሷን ለማስደሰት ታገባለች፡፡
የቻይናዊያን አባባል
ልብ ውስጥ የተፃፈ ደብዳቤ ፊት ላይ ይነበባል፡፡
የአፍሪካዊያን (ስዋሂሊ) አባባል

ሜሪ ጄን ዋግል ትባላለች፡፡ አሜሪካዊት ናት፡፡ በሙያዋ የከተማ ፕላን አውጪ (Urban planner) ብትሆንም በ2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ላለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ የስኬታማ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ታሪክ የሚዘክር መፅሃፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡ በመጪው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁት የ64 ስኬታማ ሴቶችን ታሪክ የያዙ መፅሀፍት ለንባብ የሚበቁ ሲሆን መፃሕፍቱ  ታዳጊ ሴቶች ላይ አተኩረው ለሚሰሩ የስልጠና ማዕከላትና ት/ቤቶች በነፃ ይሰራጫል ተብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ “ተምሳፀለት  የተሰኘው መፅሃፍ ጠንሳሽና አዘጋጅ ከሆነችው ሜሪ - ጄን ዋግል ጋር በመፅሃፉ ዙሪያ ያደረገው ቃለምልልስ እንዲህ ቀርቧል፡፡

          የስኬታማ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን አጭር የህይወት ታሪክ የሚዘግብ መፅሀፍ ማዘጋጀትሽን ሰምቻለሁ፡፡ መፅሃፉን ለማዘጋጀት ምን አነሳሳሽ? እስቲ ስለመፅሃፉ ጠቅለል አድርገሽ ንገሪኝ…
ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ አመጣጤም ከትውልድ ሃገሬ ውጪ ያሉኝን ልምዶች ለማካበት ነበር፡፡ በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ጥምረት ፕሬዚዳንት ከሆኑት ወ/ሮ ሳባ ገ/መድህን ጋር የሃገሪቱ ሴቶች ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ መፅሃፎችን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን እንዳሰብኩት ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በወ/ሮ መአዛ አሸናፊ የተፃፈው የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን የሚተርክ መፅሃፍ ብቻ ነው ላገኝ የቻልኩት፡፡ ከዚህ ቀደም በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ የታላላቅ ሴቶችን ታሪክ አግኝቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ስኬታማ ሴቶች የሚዘክር መፅሃፍ ግን ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተደራጀ መፅሃፍ ማዘጋጀት ቢቻል፣ የሃገሪቱ ታዳጊ ወጣት ሴቶች የቀደሙትን ሴቶች ታሪክና ልምድ እንዲሁም ጥንካሬ በሚገባ ተረድተው እንዲያድጉ ማድረግ ይቻላል በሚል መፅሃፉን ለማዘጋጀት ወሰንኩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወ/ሮ ሳባን ሳማክራት በጣም ተደሰተች፡፡ መፅሃፉ ጠቃሚ ነው ቀጥይበት አለችኝ፡፡
በዚህ መልኩ ስለውጤታማ ሴቶች መረጃዎች ማሰባሰብ ጀመርኩ፡፡ አብዛኞቹ ታሪኮች በጋዜጣና በመፅሄቶች ተበታትነው የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ ያልተሟሉ ናቸው፡፡ የተወሰኑ የአዲስ አበባ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን መርጠን መረጃዎችን በመፈለግ እንዲረዱን ጠየቅን፡፡ እነሱም ትብብራቸውን አልነፈጉንም፡፡ የታሪኩ ባለቤቶችና ቤተሰቦቻቸውን አፈላልጎ በማግኘት፣ ቃለመጠይቆችን ማድረግ፣ በእነሱ ዙሪያ የተፃፉትን ዘገባዎች ማሰባሰብና ሌሎችንም የስራው ሂደቶች አብረን ተወጥተናል፡፡ ሁሉም ሲያገለግሉ የነበረው በበጎ ፈቃደኝነት ነበር፡፡
በዝግጅቱ ወቅት ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ባለታሪኮች ራሳቸው ቃለ መጠይቃቸውን በራሳቸው ቋንቋ አርመው እንዲመልሱልን አድርገናል፡፡ ከ300 በላይ ሴቶች ነበሩ የተመረጡት፤  ከዚያ ውስጥ ነው ወደ 64 የሚሆኑት ተመርጠው በመፅሃፉ የተካተቱት፤ ነገር ግን የሁሉም ታሪክ ለታዳጊ ሴቶች የሚያጋራው የራሱ ነገር አለው፡፡ ለዚህ ሲባል በድረገፃችን ላይ የሁሉንም ሴቶች ታሪክ አስፍረናል፡፡
ፎቶግራፎችን በተመለከተም ታዋቂዋ ፎቶግራፍ አይዳ ሙሉነህ እንድታነሳ አድርገናል፡፡ ለሁለት አመት ገደማ የእነዚህን ባለታሪኮች ፎቶግራፍ ስታሰባስብና በስራ ላይ እያሉ ስታነሳ ቆይታለች፡፡ ፎቶግራፎቹ አለማቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ጥራት ያላቸው ናቸው፡፡ የታተመውም በአሜሪካን ሃገር ሎሳንጀለስ በሚገኘው ፀሃይ ፕሬስ ማተሚያ ቤት ነው፡፡
በመፅሃፉ የተካተቱት ባለታሪኮች እንዴት ነው የተመረጡት?
በመፅሃፉ የተካተቱ ባለታሪኮችን ስንመርጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገናል፡፡ ሴቶቹ ከተለያዩ የስራ ዘርፎች የተመረጡ ናቸው፡፡ ገበሬ ከሆኑት ጀምሮ የህዝብ መሪ እስከሆኑት ሴቶች ድረስ በጥልቀት ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ የመጀመሪያዋ አውሮፕላን አብራሪ ሴት፣ የኮንስትራክሽን ክሬን ባለሙያ፣ አርቲስት፣ ሃኪም አምባሳደር… የመሳሰሉት በመፅሀፉ ተካተዋል፡፡ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለመምረጥ ተችሏል፣ ከኪነ- ጥበብ፣ ከማህበራዊ እንቅስቃሴዎች፣ ከህዝብና የመንግስት ሰራተኞች፣ ከመገናኛ ብዙሃን፣ በቢዝነስ ስኬታማ ከሆኑት፣ ከህክምና ሌሎችም የተመረጡ ናቸው፡፡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ እንዲሆኑም ጥረት ተደርጓል፡፡ 64 ሴቶችን ብቻ ስንመርጥ በሃገሪቱ ስኬታማ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለታችን አይደለም፡፡ የግዴታ መምረጥ ስላለብንና ማሳያ ይሆናሉ ብለን ስላሰብን እንጂ፡፡ የ300ዎቹን ሴቶች ታሪክ በሙሉ በመፅሃፉ ባናካትትም ድረገፃችን ላይ ታሪካቸው እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ለወደፊት ታሪካቸው  በሌላ መፅሃፍ ታትሞ ሊወጣ ይችል ይሆናል፡፡ የ64 ሴቶች ታሪክ የያዘው ይህ አዲስ መፅሀፍ ግን የአዲስ ዓመት ስጦታ ይሆናል፡፡
የመፅሃፉ ፋይዳ ምንድን ነው? የትኛውን የህብረተሰብ ክፍልስ ያለመ ነው?
መጀመሪያ መፅሀፉ ታሳቢ የሚያደርገው ታዳጊ ሴቶችን ነው፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ለወደፊት የህይወት አቅጣጫቸውን ለመወሰንና በጥንካሬ ለመጓዝ ባለታሪኮቹ ምሳሌ ይሆኗቸዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚታሰበው ሴቶች ትምህርት ተማሩም አልተማሩም የሆነ እድሜ ላይ ሲደርሱ ባል ማግባት እንዳለባቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወይ የቤት እመቤት ይሆናሉ አሊያም ባሎቻቸውን በስራ የማገዝ ኃላፊነት ይሸከማሉ፡፡ ትልቅ ደረጃ ስለመድረስ አይታሰባቸውም፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሴቶች የህይወት ተሞክሮ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ለታዳጊዎች በሚገባ ያስተምራል፡፡ ማድረግ የሚፈልጉትን ለማድረግ ምንም የሚሳናቸው ነገር እንደሌለ የባለታሪኮቹ ታሪክ ለታዳጊዎቹ ያሳያል፡፡
በመፅሀፉ ዝግጅት ወቅት ፈታኝ የነበሩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
አንዱ ትልቁ ፈተና የነበረው ሴቶቹን ማግኘት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ታሪካቸውን ለመናገር አይደፍሩም፤ እንደውም የአንዷን ሴት ታሪክ ለማግኘት 3 ጊዜ ያህል መመላለስ ግድ ሆኖብን ነበር፡፡ የኢንተርኔት፣ የስልክ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ሴቶቹን እንደልብ ማግኘት አንችልም ነበር፡፡ ታሪኮቹን ማረምም የራሱን ሰፊ ጊዜ ወስዷል፡፡ በመፅሃፉ ዝግጅት ላይ የተሳተፉትን ሰዎች ጊዜ ከተገቢው በላይ የተሻማ መፅሀፍ ነው፡፡ የተሰባሰቡትን መረጃዎች በፅሁፍ፣ በፎቶግራፍ፣ በዲዛይን ማቀናበር በራሱ አስቸጋሪና ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ ነገር ግን በበጎ ፈቃደኝነት የተሳተፉ ተማሪዎችን ጨምሮ የፎቶግራፍ እና ዲዛይን ስራውን የከወኑት ባለሙያዎች ለስራቸው ታማኝ በመሆናቸው ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡
መፅሃፉን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ  መተርጎም በራሱ ከባድ ነበር፡፡ የትርጉም ስራውን የሰራው ኢዮብ ካሣ እና የፊደል ለቀማ (Proof readeing) የሰሩት ሰዎች እጅግ የሚደንቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመስራቴ ኩራት ይሰማኛል፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው ማን ነው?
በአብዛኛው የመፅሃፉ ዝግጅት የተሰራው በበጎ ፍቃደኞች እገዛ ነው፡፡ መፅሃፉ ለንባብ ሲበቃ ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎችና ለመሳሰሉት የትምህርት ተቋማት በነጻ ነው የሚሰራጨው፡፡ በመፅሃፉ ዝግጅት ወቅት 13 ያህል ተቋማት ትብብር አድርገውልናል፤ ድጋፋቸውንም ቸረውናል፡፡ የስዊድን መንግስት፣ ኮካኮላ ኩባንያ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ፣ የእንግሊዝ አለማቀፍ የልማት ተቋም (DFIO)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የፈረንሳይ ኤምባሲ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ አይፓስ ኢትዮጵያ፣ ዴቪዲና ሉሲ አለማቀፍ ፋውንዴሽን፣ ፓዌ ኢትዮጵያ፣ አይርሽ ኤይድ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገውልናል፡፡ መፅሀፉ ታዳጊ ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች ለሚያሰለጥኑ የትምህርት ተቋማት በነፃ እንዲበረከት የእነዚህ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
መፅሀፉ መቼ ነው አንባቢያን እጅ የሚደርሰው?
የመጀመሪያው የመፅሃፉ ህትመት ለሽያጭ አይቀርብም፡፡ እንዳልኩህ በነፃ ነው የሚታደለው፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ጥምረት የእንግሊዝኛና የአማርኛ ትርጉም መፅሃፉን ይፋ ሲያደርግ ምናልባት ለሽያጭ ሊቀርብ ይችላል፡፡ የዚህ መፅሃፍ ምረቃ የሚካሄደው መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ የምረቃ ቦታውም በብሄራዊ ሙዚየም ይሆናል፡፡ የፎቶግራፍ ባለሙያዋ አይዳ ሙሉነህ ያነሳቻቸው ፎቶዎችም በኤግዚቢሽን መልክ ይቀርባሉ፡፡ በሌሎች ሃገሮች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ ሰርተሽ ታውቂያለሽ?
አይ! በሌላ ሃገር እንዲህ አይነት ስራ ላይ ተሳትፌ አላውቅም፡፡ በሙያዬ የከተማ ፕላን አውጭ ነኝ፡፡ በአሜሪካ በቤቶች ልማት ላይ  ሰርቻለሁ፡፡ በመፅሃፍ ዝግጅት ደረጃ የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የነበረሽን ቆይታ እንዴት ትገልጭዋለሽ?
ኢትዮጵያን በጣም ወድጃታለሁ፡፡ አስደናቂና ውብ ሃገር ነች፡፡ ባህሉ ጥልቅ ነው፣ በቤተሰብና በሃይማኖት ዙሪያ ማዕከል ያደረገ ትስስሮሽና ባህል አላችሁ፡፡ ሰው አሜሪካ በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት የተሻለች ናት ሲል እሰማለሁ፤ እኔ ግን እዚህም የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳለ በሚገባ አይቻለሁ፡፡ የሃገሬውን ምግቦችም ወድጃቸዋለሁ፤ ሽሮ ወጥ በጣም ነው የምወደው፡፡ ማኪያቶው ደግሞ የትም ሃገር የማይገኝ ልዩ ጣዕም ያለው ነው፡፡
ቀጣይ እቅድሽ ምንድን ነው?
መፅሀፉ ከተመረቀ በኋላ ወደ አሜሪካ እመለሳለሁ፡፡ መኖሪያ ቤቴ ሎስ አንጀለስ ነው፡፡ በሎስ አንጀለስ መደበኛ ስራዬን እቀጥላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሰራሁትን ፕሮጀክት እዚያም ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡
ስለቤተሰብሽ ሁኔታ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?
አግብቼ ሶስት ልጆች ወልጄ ፈትቻለሁ፡፡ ሶስት ቆንጆ ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ ሁሉም በተለያየ ቦታ ነው የሚኖሩት፡፡ አንዷ ህንድ፣ ሌላዋ ሎስአንጀለስ፣ አንዷ ደግሞ ኒውዮርክ ነው የምትኖረው፡፡ አያትም ሆኛለሁ፤ በህንድ ሁለት የልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ ለ5 ዓመት በህንድ ኖሬያለሁ፣ ይሄ ደግሞ የተለያዩ ባህሎችን ለማወቅ አግዞኛል፡፡ ወደ ትምህርት ሁኔታ ስመጣ በከተማ ፕላን ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ በመንግስት አስተዳደር ወስጃለሁ፡፡  በተማርኩባቸው የሙያ መስኮች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎችም ሃገሬን አገልግያለሁ፤ በማገልገል ላይም እገኛለሁ፡፡

(Baaxo’gini baaxot yaagiteeh, baaxo abaara) -
የአፋር ተረት

የሚከተለውን የፃፉልን እጓለ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ነው፡፡
በግሪክ ሜቶሎጂ የሚገኝ አንድ ትልቅ ተረት አለ፡፡
(ይህም ስለ ፕሮሚሴቭስ የሚነገረው ነው፡፡ ትልቅ ምሥጢር በውስጡ ደብቆአል፡፡ ፕሮሚሴቭስ በሚል አርእስት የቀድሞውን ተረት መሠረት በማድረግ ኤስሂሎስ የሚባለው ትራጀዲን የፈጠረ ባለቅኔ፣ አንድ ትሪሎጂ - ማለት ሦስት ድራማዎች ጽፎአል፡፡ እሱን በመከተል ሸሊ ባይረን ጌቴ ጽፈዋል፡፡ የፕሮሚሴቭስ መንፈስ በአውሮፓ የመንፈስ ታሪክ ውስጥ መካከለኛውን መሥመር የያዘ ነው፡፡ አሁን የጠቀስናቸው ሰዎች በአውሮፓ የሥነ ጽሑፍ ጠፈር ላይ በጣም ጐልተው የሚታዩ ከዋክብት ናቸው፡፡)
የፕሮሚሴቭስ ተረት እንደሚቀጥለው ነው፡፡ ፕሮሚሴቭስ በከፊል አምላክ፣ በከፊል ሰው የሆነ ሕላዌ ነበር፡፡ በከፊል አምላክ እንደመሆኑ ዐሥራ ሁለቱ የግሪክ አማልክት በኦሉምቦስ ተራራ ሆነው ስለሰውና ስለዓለም አስተዳደር ሲመክሩ ይሰማ ነበር፡፡ በከፊል ሰው እንደመሆኑ የሰው ሥቃይና መከራ በጣም ያሳዝነው፣ ይጸጽተው ነበር፡፡ ሰው ቤት ንብረት ሳይኖረው በበረሃ፣ በጫካ፣ በዱር፣ በገደል፣ በዋሻ፣ በቁር፣ በሀሩር እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር፡፡ ይህ መሆኑ አማልክት መክረው ዘክረው ለሰው የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ብርሃንን የሰጡት እንደሆን ከዕለታት ባንድ ቀን ሰጭነታቸውን ክዶ በነሱ ላይ በመነሳት የሚያምፅ መሆኑን በመረዳት ብርሃንን ከሰዎች ደብቀው ከማይደርሱበት ቦታ በመሠወራቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች በጭለማና የርሱ ተከታይ በሆኑት ችግሮች ሥር ሲሰቃዩ ይኖራሉ፡፡
ይህ የሰዎች መራራ ዕድል ወገናቸው በሚሆን በፕሮሚሴቭስ ላይ ርህራሄ አሳድሮበት ብርሃንን አማልክት አርቀው ከደበቁበት ሰርቆ ለሰዎች ወስዶ ሰጠ፡፡ ያንጊዜ ማናቸውም ነገር ግልጽ ሆኖ ታያቸው፡፡ በብርሃን ምክንያት ጥበብና ማናቸውም የዕውቀት ስልት ስለተገለጸላቸው ራሳቸውን ከገዛ ራሳቸው በተገኘው ዘዴ ለማስተዳደር ጀመሩ፡፡
ፕሮሚሴቭስን ግን ለሰዎች ብርሃንን ሰጥቶ በጐ በመሥራቱ አማልክት ቀንተው በብርቱ ስቃይ ይቀጣ ዘንድ አዳኝ ከማይደርስበት ገደል ላይ ከቋጥኝ ድንጋይ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ አሞራ ለዘለዓለም እንዲበተብተው ፈረዱበት፡፡
***
ከፕሮሚሴቭስ ዕጣ -ፈንታ ይሰውረን፡፡ ይህ ፕሮሚሴቭስ የሰውን ዕድል ለማሻሻል የሚታገሉት የዕውቀት ሰዎች፣ የመምህራንና የሊቃውንት ምሳሌ ነው፡፡ እሱ ብርሃንን አማልክት ከደበቁበት ቦታ ወስዶ ለሰው እንዳበረከተ ፣ የዕውቀት ሰዎችም ዕውቀት በመለኮታዊ ምሥጢርነት ከሰው ተደብቃ ስትኖር ሳለ በብዙ ትግል አግኝተው፣ ከገዛ ራሳቸው አሥርፀው የወገኖቻቸውን ዕድል ለማሻሻል ያበረክታሉ፡፡ ዋጋቸውም ሌላ ሳይሆን ስቃይ መከራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሶክራቲስ በመርዝ ተገድሎአል፡፡ ጆርዳኖ ብሩኖ የጧፍ ቀሚስ ተጐናጽፎ በእሳት ተቃጥሎአል፡፡
እነዚህ ሰዎች እንደ ጧፍ መብራት ማለት ናቸው፡፡ ራሳቸው ነደው ተቃጥለው ያልቃሉ፡፡ ለሌሎች ግን ብርሃን ይሰጣሉ፡፡ የፕሮሜሴቭስ ምሳሌ አንድ ትልቅ ሕግ ጉልህ አድርጐ ያሳያል፡፡ ይህም “ዕውቀት በሥቃይ የሚገኝ ነው” (Learn through suffering) የሚል ነው፡፡  
ልጆቻችንን ይህን ለሌሎች ስንል መታገል፣ መሰዋት፣ ማድረግ እንደምን እናስተምር? ብርሃን የሚያመጡ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዕውቀትን ለሀገር ለማጎናፀፍ የሚጥሩ መምህራን ያሹናል፡፡ የዕውቀት ብርሃን ለመጪው ትውልድ ታትሮ ለማለፍ ፣ ልብና ልቡና ይፈልጋል፡፡ አረፍ ብሎ ወዴት እያመራን ነው ብሎ መጠየቅን ግድ ይላል፡፡ ዕውቀት ከትምህርት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከኑሮአችን፣ ከልምዳችን፣ ከትግላችን እንጂ፡፡ ይህ ወረድ ብሎ አፈሩን መዳሰስን፣ ህዝቡን ማግኘትን፣ የልብ ትርታውን ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ምን ጎደለው? ስለዚህ ጉዳይ ግንዛቤ አለ ወይ? በምን ዓይነት መንገድ የጎደለውን ዕውቀት ለማሟላት እችላለሁ? ማለትን ይጠይቃል፡፡ መንገዱን ካገኙ በኋላም፤ ጧት ማታ ሳይታክቱ መታተርን ይጠይቃል፡፡ ይህን ከልብ ካደረግን አገር መውደድ ገብቶናል፡፡ ያንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ብቻ አገርን ከገባችበት ማጥ አያወጣትም፡፡ “ኦሆ በሀሊ፣ ያርጓጅ አናጓጅ፣ በደመቀበት ቦታ ሁሉ የሚያጨበጭብ አንድም የተለየ ነገር ለማስገኘት አይችልም” ይላሉ ዶክተር እጓለ፡፡ ሉቃስን በመጥቀስም እንዲህ ይሉናል፡- “ውሰብአ አቴናሰ ወእለ ይነግድ ኲሎሙ ህየ በእደ ትካዘ አልቦሙ ዘእንበለ ዳእሙ ለአፅምኦ ወነቢብ ዘሐዲስ”፡፡ አቴናውያን አዲስ ነገር ከመስማት ወይም ከመናገር በስተቀር ሌላ ምኞት አልነበራቸውም፡፡ ባለው ላይ ቆሞ አዲስ ነገር ለማግኘት የሚጣጣር ሰው ሁል ጊዜ ወደፊት ይሄዳል - ማለት ነው፡፡
እንደ አቴናውያን፤ በአለው ላይ ቆመን አዲስ ነገር ለማግኘት የምንጣጣር ከሆነ ወደፊት እንሄዳለን፡፡ ትምህርትንና ዕውቀትን መሰረቱ ያደረገ ትውልድ ከፈጠርን የራሱን ጥያቄ፣ የራሱን ነገ ራሱ ይወልዳል፡፡ የሚኖርበት ቤት ሲጠበው ቤቱን ራሱ አስፋፍቶ ይሰራዋል፡፡ ሁሉን እኛ እናድርግልህ ካልነው - ሁሉን ቀላቢ እንሁንለት ካልን፤ ዞሮ ዞሮ ተቀላቢ ትውልድ ነው የምናፈራው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት - Spoon – Feeding mentality ይጠቀልለዋል - የአጉሩሱኝ አስተሳሰብ እንደማለት ነው፡፡
ለወጣቱ የመንግሥቱ ለማን ግጥም “መርፌ - ትሰራለህን” ማንበብና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ የአባት ነው በየትኛውም አቅጣጫ! ወጣቱ በሥነ ምግባር ረገድ፣ የሰውን ፀባይና ችሎታ በሚመረምር መልኩ አዕምሮው መታነፅ አለበት፡፡ ዕውቀትን መሰረት ሳያደርግ ለትግል ብቻ ብናዘጋጀው የፕሮፖጋንዳ ወይም የአጀንዳ ማስተላለፊያ አሸንዳ ቱቦ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በታሪክም የታየ ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮው የእያንዳንዱ መብትና ተግባር የሚጠበቅበት፣ “ሰው በንፁህ ተምኔቱ መሰረት በሰላም ተደስቶ የሚገኝበትን ሕግ” ይዞ መጓዝ እንዳለበት ሊረዳ ይገባል፡፡ ህይወት እንደ ጂኦሜትሪ ትምህርት በቀጥታ መሥመር የተሞላና የተለካ አይደለም፡፡ ቀላል ሂሳብም አይደለም፡፡ እንዴት እንደሚገነባ፣ ከራሱ ህይወት ተነስቶ እንዴት ለማደግ እንደሚችል፣ ትምህርትን ባሰላሰለ መልኩ ማጤን እንጂ “ሳይገሉ ጎፈሬ፣ ሳያረጋግጡ ወሬ” መሆን የለበትም፡፡ እስከዛሬ አጭር ተመልካች፣ አጭር ተጓዥ ሳናደርገው (Myopic) አልቀረንም፡፡ አጭር ግቦች አጭር ያደርጉናል!
አንድ ደራሲ እንደሚለው፤ “… የውጪ ጉዳዮችን ካገር ውስጥ ኃይሎች አሰላለፍ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከጥበብ ሽግግርና ከውጪ ርዳታ፣ የቋንቋ መዘበራረቅና ጉራማይሌነትን ከባህላዊ ድቀት፣ የሐሳብ ነፃነትን ከጋዜጣ፣ ራዲዮና አጠቃላይ ውይይት ምህዳር መጥበብ ጋር…” የሚያነፃፅር ወጣትም ሆነ አዋቂ ያስፈልገናል፡፡
ወጣቱ አገሩን ያውቅ ዘንድ ጥልቅ አስተሳሰብ፣ ረዥም ርዕይና በግብረገብ የታነፀ ድፍረትና መስዋዕትነት ያስፈልገዋል፡፡ መጪውን አዲስ ዓመት እንዲህ እናስብ! የሀገራዊነት፣ የወገን አሳቢነት፣ የኢ-ራስ - ወዳድነት፣ የሁሉን - አውድም አስተሳሰብ አለመያዝ፣ ሁሉን - ረጋሚ ያለመሆን አመለካከት፣ ኢፅንፋዊነት ወዘተ እንደመርህም፣ እንደኑሮም ሊሰርፁበት ይገባል፡፡ አለበለዚያ አፋሮች እንደሚሉት “አገሩን የማያውቅ ሰው፣ መሬትን እየረገጠ መሬትን ይረግማል” ይሆናል፡፡                 



  • በ514 የዳስ እና የዛፍ ጥላዎች ትምህርት እየተሰጠ ነው
  • ከ20ሺህ በላይ ስራ አጥና መሬት አልባ ወጣቶች አሉ
  • ከግማሽ በላይ ህዝብ የትራኮማ ተጠቂ ነው

           ከኢህዴን/ብአዴን ዋና ዋና የጦር ማዘዣዎችና መንቀሳቀሻ አካባቢዎች መካከል አንዱ የነበረው የዋግኽምራ ዞን፤ በኢኮኖሚ እድገት ወደኋላ መቅረቱንና ድህነት አለመቃለሉን በመጥቀስ ከአስር አመታት በፊት ለቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ቅሬታ አቅርቦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ሰሞኑን በድጋሚ ለፌደራልና ለክልል ባለስልጣናት ምሬቱን ገለጸ፡፡
ባለፈው ቅዳሜ በሰቆጣ ከተማ በተደረገ ውይይት ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ዞኑ በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አስር ዞኖች ጋር ሲነጻጸር፤ በድህነት፣ በጤና ጉድለትና በትምህርት ችግሮች ቀዳሚ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ጥራት ላይ  መጠነ ሰፊ ችግር እንዳለና በዞኑ በ514 ዳሶችና የዛፍ ጥላዎች ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ እና ከዛም በላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች በአካባቢው ባለመኖራቸው 32 ሺ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውንም አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ከተሰሩት ሶስት ሆስፒታሎች አንዱ ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ ከሃያ ዘጠኝ የጤና ጣቢያዎች አስሩ ከደረጃ በታች በመሆናቸው እንደተዘጉ፤ ከተገነቡት 125  ጤና ኬላዎች  አስሩ ከደረጃ በታች ሆነው ሥራ እንዳቆሙ፣ 6 የግል ጤና ተቋማት ቢኖሩም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንደማይሰጡ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ከወሊድ ጋር በተያያዘ በሚከሰት  የእናቶች ሞት ዞኑ ከክልሉ በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ  ለትራኮማ በሽታ የተጋለጠና በቤተሰብ አንድ ሰው ለዓይነ ስውርነት የተጋለጠ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡  
የዋግኽምራ ህዝብ ያደረገው የትግል ተጋድሎ ታሪክ የማይረሳ ቢሆንም፣ ከሌሎች ዞኖች ጋር ሲነፃፀር የልማት ተጠቃሚነቱ አነስተኛ ነው  ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፤ ወደ ትግራይ ክልል ብንካለል ለውጥ እናገኝ ነበር፤ ምክንያቱም አላማጣና ራያና ቆቦ መንገድ ሲሰራ ለእኛም ይሰራልን ነበር ብለዋል፡፡
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ለቀረቡት ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ በዞኑ የሚታዩ ችግሮች ተደራራቢ ከመሆናቸው አንፃር ችግሮቹን ከመሰረቱ መቅረፍ አዳጋች መሆኑን ገልፀው፣ ዞኑን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መሰረት የሚጥሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎች ያነሷቸው ችግሮች መኖራቸውን አምነው፣ ይሄም ሆኖ ግን በትምህርት፣ በጤናና በምግብ ልማት ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ለውጥ እየታየ መሆኑንና የልማት ስታራቴጂውን ከግምት ማስገባት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡ አካባቢው የቱሪስት መስህቦች ያሉት ቢሆንም በድህነት ምክንያት ዝቅ ያለና የተረሳ ዞን መሆኑን ያወሱት የአካባቢው ተወላጅና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሣ ተ/ብርሃን፤ “ከአካባቢው ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ አንጻር ህዝቡ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያደርገው ተጋድሎ ተጠቃሽ ነው፣ በትጥቅ ትግሉ ሁላችንም በእግራችን ስንማስን እናውቀዋለን፤ በዞኑ የሚሰሩና የሚኖሩ ህዝቦችን ጥረት አደንቃለሁ” ብለዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገድሉ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ከ5 አመታት በፊት በክልሉ ከሚኖረው 20 ሚ. ህዝብ 2.5 ሚ የሚሆነው የምግብ ዋስትና ያላረጋገጠ እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በችግሩ ውስጥ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ዋግኽምራ ዞንም በርከት ያለ ህዝብ በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር ተረጂ እንደሚሆንና ዞኑ ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር የሚታይበት በመሆኑ ሁልጊዜም አጀንዳ ሆኖ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ 128 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሰቆጣ ላሊበላ  መንገድ በ2007 ዓ.ም. ለመስራት መታቀዱን ጠቁመው፣ በዞኑ ያሉትን መጠነ ሰፊ ችግሮች ለመፍታት የአካባቢውን ተፈጥሮዊ አቀማመጥ ባገናዘበ መንገድ ህብረተሰቡና መንግስት በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የስራ አጡን ቁጥር ከመቀነስ አኳያም የተደራጁ ስራ አጦችን በንብ፣ በማር እና በአሳ ምርት በማሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስገንዝበዋል፡፡
የእንስሳትና የአሣ ልማት ምርት፣ የቱሪዝም፣ የብረታ ብረትና ማዕድን መስኮች ላይ ትኩረት አድርጐ መስራት ለዞኑ የተፋጠነ ልማት ለማምጣት ተመራጭ አካሄድ እንደሆነም አቶ ገድሉ  ተናግረዋል፡፡

እንግሊዝን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ጫት ራሱን የቻለ አደንዛዥ ዕጽ ነው በማለት እንዳይገባ መታገዱን  ተከትሎ ወደ አውሮፓ ይላክ የነበረው ምርት ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ፣ አገሪቱ ለአለማቀፍ ገበያ ከምታቀርበው የጫት ምርት አብዛኛውን የምትሸፍነው አወዳይ ከተማ የኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ መውደቋን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡ለኢትዮጵያ ጫት በሯን በመዝጋት የመጨረሻዋ የአውሮፓ አገር የሆነችው እንግሊዝ፣ ባለፈው ሰኔ ወር ጫትን ህገወጥ ዕጽ በማለት እንዳይገባ መከልከሏን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህም በሺዎች በሚቆጠሩ የአወዳይ ጫት አምራች ገበሬዎች፣ ነጋዴዎችና ላኪዎች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ማድረሱን  ጠቁሟል፡፡
በአወዳይ አካባቢ በጫት ልማትና ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ነጋዴዎችን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ አብዛኛው የአካባቢው ህዝብ የገቢ ምንጭ ከጫት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ክልከላውን ተከትሎ የተከሰተው የገበያ መቀዛቀዝ በአካባቢው እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡
እንግሊዝ ጫትን ከመከልከሏ በፊት፣ በወር ከሶስት ቶን በላይ ጫት ወደዚያው ይልክ እንደነበር ያስታወሰው ሙስጠፋ የተባለ በጫት ኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማራ ነጋዴ፣ ከክልከላው በኋላ ግን ምርቱን የሚያቀርበው ለአገር ውስጥ ገበያ ብቻ በመሆኑ ገቢው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘጋቢ ተናግሯል፡፡ በኬንያም ተመሳሳይ የገበያ ችግር እንደተፈጠረ ተጠቁሟል፡፡
በአወዳይ አካባቢ የሚኖሩ ለውጭ ገበያ የሚላክ ጫት ደላሎች፣ በአንድ ኪሎ ጫት እስከ 30 ዶላር ገቢ ያገኙ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ገቢው ወደ 5 ዶላር ማሽቆልቆሉን አመልክቷል፡፡
በጫት ንግድ ዘርፍ የተሰማራ አንድ ሌላ የአካባቢው ነጋዴም፣ አንዳንድ አርሶ አደሮች የገቢውን መላቅ በማየት ሌሎች የእህል አይነቶችን ማምረት ትተው ወደ ጫት እርሻ ጠቅልለው መግባታቸውን በማስታወስ፣ ችግሩ በርካታ የአካባቢውን አርሶ አደሮች እንደሚጎዳ ጠቁሟል፡፡
አገሪቱ በአሁኑ ሰዓት የጫት ምርቷን የምትልከው ሶማሊያና የመንን ለመሳሰሉ አገራት መሆኑን የጠቀሰው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ፤ እ.ኤ.አ በ2012/13 ጫት በአገሪቱ የኤክስፖርት ምርት ደረጃ የአራተኛነትን ቦታ ይዞ እንደነበርና  270 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘም አስታውሷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአለማችን የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ፈታኝ የነበረውን የበጀት አመት ክብረ ወሰን ባስመዘገበ ስኬት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ከትናንት በስቲያ በፌስቡክ ድረገጹ ላይ ባስነበበው መረጃ እንዳለው፣ አመታዊ ገቢውን አምና ከነበረበት 21 በመቶ በማሳደግ፣ በአመቱ 46 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ ተሳፋሪዎችን የማመላለስ አቅሙን በ17 በመቶ ከፍ ማድረጉንና ከተሳፋሪዎች የሚያገኘውን ገቢ በ16 በመቶ ማሳደጉንም አስታውቋል፡፡
እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ የሚነገርለትን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ጨምሮ፣ 13 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 9 አዳዲስ መዳረሻዎች በረራ መጀመሩንም ተናግሯል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት 41 ባቡሮችን ለመስራት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት የፈጸመውና ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ስራውን በማከናወን ላይ የሚገኘው ‘ቻይና ሲ ኤን አር ቻንግቹን ሬልዌይ ቪሄክልስ’ የተባለው የቻይና ባቡር አምራች ኩባንያ የመጀመሪያውን ባቡር ሰርቶ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ሊዩ ጋንግ፣ ባቡሩ በሰዓት 70 ኪሎሜትሮች የመጓዝ አቅም እንዳለው፣ ነጭና አረንጓዴ ቀለም እንዳለው እንዲሁም ለተሳፋሪዎች ምቹ በሆነና የጸሃይ ብርሃንን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ዲዛይን መደረጉን ለቻይናው የዜና ወኪል ዥንዋ ተናግረዋል፡፡“በመጪው መስከረም ወር 50 ኢትዮጵያውያን የባቡር አሽከርካሪዎችንና የጥገና ሰራተኞችን ወደ ኩባንያችን በማስመጣት አስፈላጊውን ስልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው” ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ ኩባንያው ሁሉንም ባቡሮች በታሰበው የጥራት ደረጃ ሰርቶ ለማጠናቀቅና በተቀመጠው ጊዜ ለማስረከብ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡የመገጣጠም ስራው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀው የመጀመሪያው ባቡር፣ በቻይና የሰሜን ምስራቅ ግዛት ጂሊን ውስጥ በምትገኘውና የኩባንያው መቀመጫ በሆነችው ቻንግቹን ከተማ ባለፈው ማክሰኞ የተሳካ የሙከራ ጉዞ እንዳደረገ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የባቡር ስራውን ለኩባንያው የሰጠው ባለፈው ግንቦት ወር መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኩባንያው እስከ መጪው ጥር ወር ሁሉንም ባቡሮች አጠናቆ ለማስረከብ ተዋውሎ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡
የከተማ ባቡር ትራንስፖርት በአፍሪካ አህጉር በጅማሬ ላይ ያለ ዘርፍ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር በሌሎች አገራት እምብዛም አለመስፋፋቱንና ይህም ለቻይና የባቡር አምራች ኩባንያዎች ከፍተኛ የገበያ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ አመልክቷል፡፡
በአህጉሪቱ ቀላል የከተማ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተዘረጋባቸው አገራት አልጀሪያ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ እንደሆኑ የጠቀሰው ዘገባው፤ የምድር ውስጥ የባቡር መስመር ያለባቸው የአፍሪካ ከተሞች ደግሞ ካይሮና አልጀርስ ብቻ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

       በአለማቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የባንክ ክፍያ ስርዓቶችን በመዘርጋት የሚታወቀው ቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ የተባለ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ‘ስማርትቪስታ’ የተሰኘ ዘመናዊ የባንክ ክፍያ ስርዓት ሊዘረጋ መሆኑን ባንክስ ቢዝነስ ሪቪው ድረ-ገጽ ትናንት ዘገበ፡፡የ “ስማርትቪስታ” የተባለውን የክፍያ ስርዓት የመዘርጋት ሃላፊነቱን በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ባንኮች በጋራ ከመሰረቱት የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረት የተረከበውና ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ የሆነው ቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ፣ በአገሪቱ ሊዘረጋው ያቀደው የክፍያ ስርዓት ዘመናዊና ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ ተመራጭ እንዳደረገው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረት አዲሱን የክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት ያቀደው፣ ሁሉንም የአገሪቱ ባንኮች በአንድ የገንዘብ ዝውውር ማዕከል አማካይነት ለማስተሳሰርና ደንበኞች የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን በኤቲኤም፣ በፖይንት ኦፍ ሴል ዲቫይስ፣ በሞባይልና በኢንተርኔት አማካይነት እንዲያገኙ ለማስቻል በማሰብ እንደሆነ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ኩባንያው በቀጣይም “ስማርትቪስታ” በተሰኘው ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት አማካይነት የአገሪቱ ባንኮች ቪዛ ካርድንና ማስተር ካርድን በመሳሰሉ የመክፈያ ካርድ አሰራሮች አለማቀፍ ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉበትን አሰራር እንደሚዘረጋ ተነግሯል፡፡
የቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ዳሪል በርግ፣ መሰል ፕሮጀክቶችን በመላው አለም በስኬታማ መንገድ በማከናወን የካበተ ልምድ ያለው ኩባንያው፣ በኢትዮጵያም የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ጠንካራና የተሻሻለ የክፍያ መሰረተ ልማት እንደሚዘረጋ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡  የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ በበኩላቸው፣ ጥምረቱ በባንኮች ውስጥ የሚከናወነውን የክፍያ አሰራር ሂደት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ በበለጠ ሁኔታ የተቀላጠፈ፣ ግልጽነት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ የማድረግ ዓላማ ይዞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
“በአገሪቱ ዘመናዊ የባንክ ክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት የያዝነውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በዘርፉ በአለማቀፍ ደረጃ የሚሰሩ ኩባንያዎችንና የክፍያ ስርዓቶችን የመገምገም ስራ በስፋት ከተከናወነ በኋላ፣ ወቅታዊውንና የወደፊቱን ዘርፈ-ብዙ ፍላጎታችንን የሚያሟላው “ስማርትቪስታ” በመሆኑ ልንመርጠው ችለናል” ብለዋል አቶ ብዙነህ፡ቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ በአሁኑ ወቅት በ45 የተለያዩ የአለም አገራት ለሚገኙ 126 ደንበኞቹ በዘርፉ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረትም እ.ኤ.አ በ2011 በብሄራዊ ባንክና በአገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ባንኮች ያቋቋሙትና ለፋይናንስ ተቋማት ብሄራዊ የክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ አክስዮን ማህበር መሆኑን አስታውቋል፡፡



          ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በህግ ሙያ የተመረቀችውና በአሜሪካ በአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋችነት በመስራት ላይ የምትገኘው፣ ማየትና መስማት የተሳናት ትውልደ ኢትዮጵያዊት የህግ ጠበቃ ሃቤን ግርማ፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ መድልኦ ይፈጽማል ስትል ስክሪፕድ የተባለውን ታዋቂ የአሜሪካ የድረገጽ ኩባንያ መክሰሷ ተዘገበ፡፡ ቢዝነስ ኢንሳይደር ድረገጽ ባለፈው ሳምንት እንደዘገበው፤ ዲጂታል መረጃዎችን ለአንባብያን በስፋት በማቅረብ የሚታወቀው ስክሪፕድ የተባለው ኩባንያ፣ የሚከተለው አሰራር ማየት የተሳናቸው አንባቢዎችን ፍላጎት ያላሟላና መድልኦ የሚፈጥር ነው በማለት ነው ሃቤን በኩባንያው ላይ ክስ የመሰረተችው፡፡ የ26 አመቷ ጠበቃ ሃቤን ግርማ፤ ‘ናሽናል ፌደሬሽን ኦፍ ዘ ብላይንድ’ እና ‘ብላይንድ ቬርሞንት ማዘር ሄዲ ቪነስ’ የተባሉትን የአሜሪካ የአይነስውራን መብቶች ተሟጋች ተቋማት በመወከል በስክሪፕድ ላይ በመሰረተችው ክስ፣ ኩባንያው የድረገጽ አገልግሎቶቹ ሆን ብሎ ለአይነስውራን አንባብያን ተደራሽ እንዳይሆኑ በማድረግ፣ የአገሪቱን የአካል ጉዳተኞች ህግ በሚጥስ መልኩ ያልተገባ ድርጊት ፈጽሟል ብላለች፡፡

ስክሪፕድ ከ40 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠናከራቸውን መረጃዎች በድረገጹና በአፕሊኪሽኖቹ አማካይነት ለደንበኞቹ 8 ነጥብ 99 የአሜሪካ ዶላር ወርሃዊ ክፍያ በማስከፈል የሚያሰራጭ ሲሆን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ደንበኞቹን ስራዎች በድረገጽ አማካይነት ታትመው ለንባብ እንዲበቁ በማድረግ፣ በአለማቀፍ ዙሪያ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ኩባንያ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡ስትወለድ ጀምሮ ማየትና መስማት የተሳናት ሃቤን፤ ትምህርቷን የተከታተለችው በአሜሪካ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከሊዊስ ኤንድ ክላርክ ኮሌጅ ተቀብላለች፡፡ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም በህግ የሁለተኛ ዲግሪ ይዛለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም በበርክሌይ የአካል ጉዳተኝነት መብት ተሟጋች ጠበቃ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡የቢዝነስ ኢንሳይደር ድረገጽ ‘የ2013 እጅግ አስደማሚ 20 ምርጥ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች’ በሚል ባለፈው አመት ከመረጣቸው ተጠቃሽ ተማሪዎች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሃቤን ግርማ አንዷ እንደነበረች ዘገባው አስታውሷል፡፡

Saturday, 30 August 2014 10:30

ጋዛ - ከእንባ ወደ እልልታ…

           ለሰባት ሳምንታት የማያባራ የሮኬት ድብደባ ሲወርድባት የዘለቀች፣ 490 ያህል ጨቅላዎቿን ጨምሮ 2 ሺህ 142 ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች፣ አይሆኑ ሆና የፈራረሰችው ጋዛ፤ ከከረመባት መከራና ስቃይ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይ አለች፡፡ ባለፈው ማክሰኞ አመሻሽ ላይ፣ ተረኛውን ሮኬት በፍርሃት እየተርበተበቱ የሚጠብቁት የጋዛ ሰዎች፤ ያልጠበቁትን ከወደ ካይሮ ሲደገስ የሰነበተ አንዳች በጎ ነገር አደመጡ፡፡ የፍልስጤሙ ፕሬዚደንት ማሃሙድ አባስ ከወደ ዌስት ባንክ ይፋ ያደረጉት መረጃ፣ እርግጥም ጧት ማታ በሮኬት ድብደባ አሳር መከራዋን ስታይ ለነበረችው የፈራረሰችው ጋዛ ትልቅ የምስራች ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ እስራኤል በፍልስጤም የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት በጄ ብላ መቀበሏን ማብሰራቸውን፣ ሃማስም የድል ብስራት ዜናውን ለጋዛ ነዋሪዎች በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ማድረሱን ተከትሎ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በጋዛ ጎዳናዎችና በአደባባዮች ወጥተው ደስታቸውን ገለጹ፡፡ ጣቶቻቸውን ከፍ አድርገው በማውጣት የ v ምልክት አሳይተዋል - “ድል ለፍልስጤም ሆነ!” ለማለት፡፡ የሃማሱ ምክትል መሪ ሞሱአ አቡ ማርዙክም ቢሆኑ፣ እስራኤል የቀረበላትን የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳብ መቀበሏ፣ ለሃማስ ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቃል አቀባይ ኦፊር ጌንዴልማን በበኩላቸው፤ አገሪቱ በጋዛ ስታደርገው የነበረው ወታደራዊ ዘመቻ በድል መጠናቀቁን ነው የሚናገሩት፡፡

ሃማስ ከዚህ ቀደም በግብጽ ቀርቦለት አሻፈረኝ ያለውን የሰላም ሃሳብ ነው መልሶ የተቀበለው ይላሉ ቃል አቀባዩ፡፡ በግጭቱ 69 ያህል ዜጎቿን ያጣችው እስራኤል የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ማርክ ሬጌቭ በበኩላቸው፣ ሃማስ ባለፈው ሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ የቀረበለትን የሰላም ስምምነት ሃሳብ በወቅቱ ቢቀበል ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ደም መፋሰስ ባልኖረ ነበር በማለት ተጠያቂነቱን ወደ ሃማስ አድርገዋል፡፡ ስምምነቱን እውን ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ ለቆዩት ለግብጽ፣ ለኳታርና ለአሜሪካ ምስጋና ይግባቸውና፣ አሁን ደም አፋሳሹ የሁለቱ አገራት ግጭት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ጋብ ብሎ የሚቆይበት ሁነኛ የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱ ሃይሎች መካከል እንዲደረስ አስችለዋል፡፡ የአልጀዚራው ዘጋቢ አንድሪው ሲሞንስ ከጋዛ በላከው ዘገባ እንዳለው፣ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰው ስምምነት፣ እስራኤል የዘጋቻቸውን የጋዛ መግቢያዎች በአፋጣኝ እንድትከፍትና በሂደትም በጋዛ ሰርጥ አካባቢ የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ እንድታነሳ የሚያደርግ ነው፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ተጀምሮ የተቋረጠው ውይይትም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚቀጥል ዘግቧል፡፡ሃማስ በቀጣይ በጋዛ ውስጥ የአየር ማረፊያና የባህር ወደብ ማቋቋም ይገባኛል፣ ፍልስጤማውያን እስረኞችም መፈታት ይኖርባቸዋል እያለ ሲሆን እስራኤልም የጋዛን ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ማስፈታት እፈልጋለሁ እያለች ነው፡፡ እንዲህ እና እንዲያ ያሉ ከግራና ቀኝ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ይካሄዳል በተባለው ቀጣይ ውይይት እልባት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡

ስምምነቱ ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያዋስነው 9 ማይል የሚረዝመው የራፋህ ድንበር እንዲከፈት፣ የጋዛ ድንበሮች በፍልስጤም ሃይሎች ቁጥጥር ውስጥ እንዲሆኑና የመልሶ ግንባታ ስራውን የመምራት ሃላፊነቱንም የፍልስጤም መንግስት እንዲወስድ የሚያደርግ ሲሆን፣ እስራኤልም በጋዛ ውስጥ ያላትን የደህንነት እንቅስቃሴ አሁን ካለበት 300 ሜትር ክልል ወደ 100 ሜትር እንድትቀንስ፣ ከአየርና ከምድር የምትሰነዝረውን ወታደራዊ ጥቃት እንድታቆም የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰው ይህ ስምምነት እንደሚለው፣ የፍልስጤም መንግስት የጋዛን ድንበር ከሃማስ ሃይሎች ተረክቦ የመቆጣጠር ሃላፊነቱን ይወስዳል፤ እስራአልም ከጋዛ ድንበር በሶስት ማይል ርቀት ገድባው የነበረውን የአሳ ማስገር ስራ ወደ ስድስት ማይል ማስፋት ይጠበቅባታል፡፡ ስምምነቱ በጋዛ ሰማይ ላይ የሰላም አየር መንፈስ ለመጀመሩ ማሳያ ነው ቢባልም ታዲያ፣ የማህበረሰብ መሪዎች ግን፣ ህዝቡ ወደቤቱ እንዳይመለስ እየመከሩ ነው ተብሏል፡፡ ጋዛ አሁንም ገና ከስጋት አልወጣችም የሚል አመለካከትም በብዙዎች ዘንድ ይንጸባረቃል፡፡