Administrator

Administrator

Monday, 07 April 2014 15:17

ለማይስቅ ውሻ ነጭ ጥርስ

ለማይገላመጥ ዶሮ ቀይ ዐይን ይሰጠዋል!
(የሚጬነ ከናስ አቻ ቦታ እሜስ ዴሬቄነ ኩቶስ አይፌ ዞኡዋ እሜስ)
የወላይታ ተረት

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ደቃቃ ጥንቸል፤ እህል ውሃ ፍለጋ በጫካ ውስጥ ስትዘዋወር፤ አንድ ዝንጀሮ ታገኛታለች፡፡ ጥንቸሏ ግዙፍ ስላልሆነች በየቅጠላ ቅጠሉ ውስጥ እየተሹለከለከች መሄድ እንደምትችል ዝንጀሮ ያውቃል፡፡ ሆኖም አንድ ምክር ሊመክራት ፈልጓል፡፡
“እመት ጥንቸል! የረዥም ጊዜ ወዳጅነታችንን መሰረት በማድረግ ምክር ልለግስሽ እፈልጋለሁ” አላት፡፡
ጥንቸልም፤
“ምን ዓይነት ምክር? ስትል ጠየቀችው”
ዝንጀሮም፤
“ይህን ጫካ አትመኝው፡፡ ሰሞኑን አዳኞች መጥተው ለአውሬ ማጥመጃ የሚሆን ትላልቅ ጉድጓድ ሲቆፍሩ እኔ ዛፍ ላይ ሆኜ አይቻቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ጫካው እንደድሮው ሰላም መስሎሽ ወዲህ ወዲያ አትበይ”
ጥንቸልም፤
“አመሰግናለሁ፡፡ የወጥመዱን የሰሩት ለእኔ አይመስለኝም፡፡ እንደ አንበሳ፣ እንደነብር፣ እንደዝሆን ላሉት እንጂ እንደኔ ቀጫጫ ለሆነ ፍጡር አይደለም፡፡ ባጋጣሚ ጉድጓድ ውስጥ ብወድቅም መውጫ ብልሃት አላጣም!” ትለዋለች፡፡
ዝንጀሮም፤
“እንግዲህ የወንድምነቴን መክሬሻለሁ፡፡ ብታውቂ እወቂበት” አላትና ሄደ፡፡
ጥንቸል እየተዘዋወረች ቅጠል መበጠሷን ትቀጥላለች፡፡ ጥቂት እንደሄደች ዝንጀሮ እንደፈራው አንድ በቅጠል የተሸፈነ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ሳታስበው ትወድቃለች፡፡ ጉድጓዱ በጣም ጥልቀት ያለው በመሆኑ በጭራሽ በቀላሉ ልትወጣ የምትችልበት አይደለም፡፡ ስለዚህ አላፊ-አግዳሚውን እንዲያወጣት ለመለመን ተገደደች፡፡
“እባካችሁ አውጡኝ፡፡ እባካችሁ እርዱኝ!” እያለች መጮህ ጀመረች፡፡ ተኩላ ድምጿን ይሰማና ወደ ጉድጓዱ አፍ ይሄዳል፡፡ አጎንብሶም ወደ ጥንቸሏ ያይ ጀመር፡፡
ጥንቸልም
“አያ ተኩላ! እባክህ ዘወር በል፡፡ ይሄ ጉድጓድ ለሁለታችን አይበቃንም፡፡ አንተ ያለህበት ቦታ እንደበረሀ የሚያቃጥል አየር ነው ያለው፡፡ እዚህ ግን በጣም ነፋሻና ቅዝቅዝ ያለ አየር ነው ያለው፡፡ ለእኔ በጣም ተስማምቶኛል፡፡ ሆኖም ወደዚህ ለመውረድ ብትችልም እንኳን ቦታው አይበቃንም” አለችው፡፡ ተኩላ፤ የጥንቸሏ ንግግር በጣም አጓጓውና፤ “ልውረድስ ብል በምኔ እወርዳለሁ?” ሲል ጠየቃት፡፡
ጥንቸልም
“እዚያ ጉድጓድ አፍ አጠገብ አንድ በገመድ የታሰረ ባሊ አለልህ፡፡ ባሊው ውስጥ ገብተህ በገመዱ ተንሸራተህ መውረድ ትችላለች” አለችው፡፡
ዕውነትም አንድ ባሊ አጠገቡ እንዳለ አየ፡፡ ባሊው ወደታች ሲወርድ ጉድጓዱ ውስጥ ያለው ገመድ ጫፍ ወደላይ የሚወጣ ነው፡፡ እንደ ፑሊ የሚሰራ ገመድ ነው፡፡ ጉድጓድ ውስጥ ያለውን ጫፍ ጥንቸሏ ይዛለች፡፡
አያ ተኩላ ባሊው ውስጥ ገብቶ ቁልቁል ተምዘግዝጎ ሲወርድ ጥንቸል የገመዱን ጫፍ ይዛ ወደ ላይ መጣች፡፡
እሱ እየወረደ፣ እሷ እየወጣች መንገድ ላይ ሲተላለፉ፤ ከት ብላ እየሳቀች፤
“አየህ አያ ተኩላ፤ ህይወት ማለት እንደዚህ ናት፡፡ አንዱ ሲወርድ አንዱ ይወጣል!“ አለችው፡፡
ተኩላ መሬት ሲደርስ ጥንቸሏ ጉድጓዱ አፋፍ ወጣች!
*   *   *
አንዳንድ ሰዎች አንድ ችግር ውስጥ ሲገቡ ሌላውን እዚያ ውስጥ ነክረው እራሳቸውን ማዳን ይችሉበታል፡፡ ተታልለው እዚያ ችግር ውስጥ የሚገቡት ሞኞች የሚሳሳቱት በአልጠግብ ባይነታቸውና እጉድጓዱ ውስጥ እንኳ ያለው ነገር እንዳያመልጠኝ ብለው ሲስገበገቡ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት በርካታ ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ቀርተዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁለቱም ለሀገርና ለህዝብ አይጠቅሙም፡፡ አደጋን ከሩቅ አይተው የሚያስጠነቅቁ እንደ ዝንጀሮው ያሉ አስተዋዮች ቢኖሩም እህ ብሎ የሚያዳምጣቸው ሰው አያገኙም፡፡ ባንዱ እግር ሌላው እየገባ፣ ህይወት ትቀጥላለች፡፡
ማይ ግሪንፊልድ የተባለ ፀሐፊ፤
“ታሪክ ራሱን ይደግማል፤ ይላል ታሪከኛ ሁሉ
እኔን ያሳሰበኝ ግና፣
ታሪክ በደገመ ቁጥር፣ ዋጋው ይብስ መቀጠሉ” ይላል፡፡ የሚያስከፍለን ዋጋ እየባሰ የሚመጣው እኛ ከታሪክ ለመማር ባለመቻላችን ነው፡፡ የቀደመው የሰራውን ስህተት የኋለኛው ይደግመዋል - ያውም በዚያኛው እየሳቀ፣ እየተሳለቀ! “በእገሌ ጊዜ የተበደላችሁ እጃችሁን አውጡ!” እያለ፡፡ ከንቲባዎች ተቀያረዋል፡፡ አስተዳዳሪዎች ተቀያይረዋል፡፡ ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል ወዘተ… ማንም ከማንም አይማርም፡፡ ሁሌ እኔ ከወደቀው የተሻልኩ ነኝ የሚለውን ለማረጋገጥ የቀደመውን እየረገሙ መቀጠል ነው!! በዚህ ዓይነት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እመሰርታለሁ ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ከተነሳው ሹም መውሰድ ያለብንን ደግ ነገር ካላወቅን ከዜሮ እንደ መጀመር የከበደ ነው ጉዟችን፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመኖች ለንደንን በቦምብ በደበደቡ ጊዜ ሦስት ዓይነት ህዝቦች ተፈጥረው ነበር ይባላል፡፡ 1) የተገደሉ 2) ለጥቂት የተሳቱና 3) በርቀት የተሳቱ፡፡ የተገደሉት ሟቾች ናቸውና ስለአደጋው ወሬ አይነዙም፡፡ ለጥቂት የተሳቱት በሰቀቀንና ስቃዩን በማስታወስ የሚኖሩ ሆኑ፡፡ በሩቅ የተሳቱት ግን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹን ለመዷቸውና ልበ ሙሉ ሰዎች ሆኑ፤ ይለናል ፀሐፊው ማልኮልም ግላድዌል፡፡ ችግርን መልመድ ደፋርና ልበ - ሙሉ ያደርጋል ነው ነገሩ! ከዚህ ተነስቶ ለአገርና ህዝብ መቆርቆር መቻል መታደል ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደሞ ማየት፣ በትክክለኛው ቦታ መገኘትና የሚሰሩትን በቅጡ ማወቅ ግዴታ ነው፡፡ ችግርን ለምዶ መተኛት ግን ሌላ ችግር ነው! ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ እያሉ አግባብነት ያለው ተግባር የማይፈፅሙ አያሌ ናቸው፡፡ የተማሩትና የሰለጠኑበት ሌላ የሚሰሩት ሌላ፤ የሆኑም አያሌ ናቸው! ስለግንባታ እያወሩ የማይገነቡ ከአፈረሰ አንድ ናቸው፡፡ መንገድ ሰርቶ በቅጡ ሳንሄድበትና ሳናጣጥመው ከፈረሰ ወይ ሰሪው በቅጡ አላበጀውም፣ ወይ ሂያጆቹ መሄድ አይችሉም፣ አሊያም ሆነ ብለው የሚያጠፉ አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በቅጡ ራስን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ “የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ”ንም ልብ ማለት መልካም ነው፡፡ ሁሉን በውል በውሉ ካላስቀመጥንና ታማኝነትን ብቻ መለኪያ እናድርግ ካልን የተወዛገበ አካሄድ ውስጥ እንሰረነቃለን፡፡ እመጫት እንደ በዛው ፅሁፍ ከዋናው ማረሚያው ይበረክታል፡፡ ከተቃወምንም ዕድሉን ባግባቡ እንጠቀም፡፡ እንዳያማህ ጥራውንም እንተው! በእጃችን ያለውን በወጉ መጠቀም ያስፈልጋል በሁሉም ወገን፡፡ አለበለዚያ “ለማይስቅ ውሻ ነጭ ጥርስ፣ ለማይገላምጥ ዶሮ፣ ቀይ ዐይን ይሰጠዋል” የሚለው የወላይተኛ ተረት ይመጣል፡፡ “ቆሎ ለዘር፤ እንዶድ ለድግር አይሆንም” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡    

በአምስተረዳም አንድ ሰው ከሞተና የሚቀብረው ወዳጅ ዘመድ ከሌለው አንድ ገጣሚ ግጥም ይፅፍለትና በቀብር ሥነ-ሥርአቱ ላይ ያነብለታል፡፡
ቦሊቪያ ውስጥ የሚገኘው ትልቁ ወህኒ ቤት ምኑም እስር ቤት አይመስልም ነው የሚባለው፡፡ እስር ቤቱ ራሱን የቻለ ህብረተሰብ የፈጠረ ሲሆን ግቢው ውስጥ ጥበቃዎች የሉም፡፡ ወህኒ ቤቱን የሚጠብቁት ራሳቸው እስረኞቹ ሲሆኑ የራሳቸውን መሪዎች ይመርጣሉ፤ የራሳቸውን ህጎችም ያወጣሉ፡፡ እዚያው ተቀጥረው በመስራት ከሚያገኙት ክፍያም ለእስር ክፍላቸው ኪራይ ይከፍላሉ፡፡ ከቤተሰባቸው ጋር መኖርም ይፈቀድላቸዋል፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ፡፡
እ.ኤ.አ ከ1939 እስከ 1989 ባሉት ዓመታት ከስፔን የተለያዩ ሆስፒታሎች 300ሺ ገደማ አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ህፃናት ተሰርቀዋል፡፡ ህፃናቱ የተሰረቁት ደግሞ በውጭ ሰዎች ሳይሆን ህገወጥ የህፃናት ዝውውር መረብ በዘረጉ የህክምና ተቋማት ሃኪሞች፣ ነርሶች፣ ቄሶችና መነኮሳት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲጠይቁም እንደ ሞቱ ይነገራቸው ነበር፡፡
የጃፓኗ ኦኪናዋ ደሴት በምድራችን እጅግ ጤናማ ሥፍራ በሚል ትታወቃለች፡፡ በዚህች ደሴት ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ከ450 በላይ ሰዎች ይኖራሉ፡፡
የአውሮፓ ፓርላማ ዋና ተርጓሚ የሆነው አዮአኒስ አይኮኖም 32 ቋንቋዎችን አቀላጥፎ እንደሚናገር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

       ኖህ ዌብስተር የመጀመሪያውን መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት 36 ዓመት ፈጅቶበታል፡
ዳን ብራውን “ዘ ዳ ቪንቺ ኮድ” የተባለውን መፅሃፉን ከመፃፉ በፊት የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝና የዘፈን ግጥም ደራሲ ነበር፡፡ ሁለተኛው የሙዚቃ አልበሙ “ኤንጅልስ ኤንድ ዴሞንስ” በሚል ስያሜ ነበር የወጣውስ፡፡
ሲድኒ ሼልደን 50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እስኪገባ ድረስ ረዥም ልብወለዶችን መፃፍ አልጀመረም ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት “I Dream of Jeannie” እና “The Patty Duke Show” የመሳሰሉ ተወዳጅ የቴሌቭዥን ድራማዎችን ነበር የሚፅፈው፡፡ ቬልይን “The Bachelor and the Bobby Soxer” በተባለች የፊልም ጽሑፉ ኦስካር አሸንፏል- “ምርጥ ኦሪጅናል የፊልም ጽሑፍ” በሚል ዘርፍ፡፡
የ “ሃሪ ፖተር” ደራሲ ጄ.ኬ.ሮውሊንግ መጀመሪያ ላይ ሥራዋን የሚያሳትምላት አጥታ መከራዋን በልታለች፡፡ ብዙዎች ውድቅ እያደረጉባት ተስፋ ከቆረጠች በኋላ ብሉምስበሪ ፕሬስ ሊያሳትምላት ተስማማ፡፡ እሱም ቢሆን ግን አይሸጥ ይሆናል በሚል ፍራቻ 500 ቅጂዎችን ብቻ ነበር ያሳተመላት፡፡ ሴት ፀሐፊ መሆኗ እንዳይታወቅ ሙሉ ስሟን እንዳትጠቀም አድርጓታል፡፡ አሁን ደራሲዋ ቢሊዮነር መሆኗ ይታወቃል፡፡
የታዋቂዋ ደራሲ ዳንኤላ ስቲል ህይወት በአንዳንድ መልኩ የፈጠራ ሥራዎቿን ይመስላል ይባላል፡፡ ደራሲዋ አምስት ጊዜ ጋብቻ የመሰረተች ሲሆን ሳን ፍራንሲስኮ ክሮኒክል እንደዘገበው፤ ሁለተኛ ባሏ ከእሷ ጋር እያለ አስገድዶ በመድፈር የተፈረደበት የባንክ ዘራፊ ነበር፡፡ ሦስተኛ ባሏ ደግሞ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛና ቤት ሰርሳሪ ነበር ተብሏል፡፡



        በአዲስ ጉዳይ መጽሔትና በድረ-ገፆች ላይ የተለያዩ መጣጥፎችንና ግጥሞችን በመፃፍ የሚታወቀው አሌክስ አብርሃም ፤“ዶ/ር አሸብርና ሌሎችም ታሪኮች” በሚል ያዘጋጀው የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ባለፈው ሳምንት ለገበያ ቀረበ፡፡ ሃያ አምስት አጫጭር ልቦለዶችንና ታሪኮችን የያዘው መድበሉ፤237 ገፆች ያሉት ሲሆን በሊትማን መጽሐፍት አከፋፋይነት በ50.65 ብር እየተሸጠ ነው፡፡  
በሌላ በኩል በብርያን ትሬሲ ተፅፎ በእስክንድርያ ስዩም የተተረጎመው “መቶ የቢዝነስና የአመራር ህጎች” የተሰኘ የንግድ ክህሎት መፅሀፍ እየተሸጠ ነው፡፡ በስምንት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ142 ገፆች የተቀነበበው  መፅሀፉ፤በህይወትና በስኬት ህግጋት፣ በመሪነት፣ በገንዘብና በሽያጭ ህጎች እንዲሁም በንግድ ሥራ ህጎችና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን የተሳካ የንግድ ስራን ለመጀመር፣ ለመምራትና ለማሳደግ የሚረዳ መፅሐፍ ነው ተብሏል፡፡ የእንግሊዝኛው መፅሃፍ በብዙ ሚሊዮን ቅጂዎች እንደተሸጠና የብዙዎችን የቢዝነስና የአመራር ህይወት እንደቀየረ ተጠቁሟል፡፡ ወደ አማርኛ የተተረጎመው መፅሀፉ   በ35.45 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በየሺወርቅ ወልዴ የተፃፈው እና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው “የጠፋው ቤተሰብ” የተሰኘ ልብ ወለድ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሀፉ በውስጡ ሌሎች አጫጭር ታሪኮችና ግጥሞች የተካተቱበት ሲሆን ለደራሲዋ ሁለተኛ ስራዋ እንደሆነም ታውቋል፡፡  “የጠፋው ቤተሰብና ሌሎችም” መፅሐፍ 122 ገፆች ያሉት ሲሆን በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል። ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “አትሮኖስ” የተሰኘ የግጥም መፅሀፍ ለንባብ አብቅታለች፡፡ በሌላ በኩል በገጣሚ ውድነህ ግርማ (የአስቴር ልጅ) የተፃፈው “ሽበቴን ለቅማችሁ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ከ120 በላይ አጫጭር ግጥሞችን የያዘው መጽሐፉ፤በ65 ገፆች የተቀነበበ  ሲሆን በ30 ብር ይሸጣል፡፡ ግጥሞቹ በፍቅር፣ በማህበራዊ ኑሮ፣ በታሪክና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናሉ፡፡ ወጣቱ ገጣሚ የግጥም መድበሉ የበኩር ስራው እንደሆነ ጠቅሶ ወደፊት ሊያሳትም ያዘጋጃቸው የልብወለድ ስራዎች እንዳሉትም ገልጿል፡፡

አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ሥራዎች ከኤሎሄ አርት ፕሬስ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት “ስንቅ” መፅሔት ዛሬ ከቀኑ በ10 ሰዓት በኦካናዳ ሬስቶራንት እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ በኪነጥበብ ላይ አተኩሮ በየአሥራ አምስት ቀኑ እየታተመ የሚወጣው መጽሔቱ፤ባለፈው ቅዳሜ የመጀመሪያ ዕትሙን ለንባብ እንዳበቃ ታውቋል፡፡ “ስንቅ” መፅሔት ከወቅታዊ ጉዳዮች ባሻገር ሙዚቃ፣ ግጥሞች፣ ወጎች እና ሌሎች የኪነጥበብ ስራዎችን ያስተናግዳል፡፡  

    ከለርስ ኦፍ ዘ ናይል ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ባለፈው ሰኞ በብሄራዊ ቲያትር ለሁለተኛ ጊዜ የተከፈተ ሲሆን በዘንድሮ ፌስቲቫል ‹‹ሌንሶች ለአፍሪካ ህዳሴ›› በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 15- 22 የፊልም ስክሪኒግ እና ወርክሾፖች እንደሚካሄዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ብሉ ናይል የፊልምና ቴሌቭዥን አካዳሚ ከኢትዮጵያ የፊልም ሰሪዎች ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ፌስቲቫል  የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት መሪ ቃልን በማስተጋባት ሲኒማ ህብረተሰቡን በማነጽ፣በማዝናናት፣አፍሪካውያንን በማቀራረብ፣አፍሪካዊ ባህልን በማዳበር እንዲሁም ለትውልድ በማስተላለፍና ዴሞክራሲያዊ ባህልን በማጎልበት ለአፍሪካ ህዳሴ አስተዋፅኦ  እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡
በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ በጣሊያን ካልቸር ኢንስቲትዩት እና በብሄራዊ ሙዚየም በሚደረጉ የተለያዩ ዝግጅቶች 48 የውጪና የሀገር ውስጥ ፊልሞች ለውድድር እንደሚቀርቡ የታወቀ ሲሆን ከ22 አገራት  የተውጣጡ ከ28 በላይ የፊልም ባለሞያዎች ይሳተፉበታል፡፡ ፌስቲቫሉ የፊታችን ማክሰኞ በብሄራዊ ቲያትር በሚካሄድ የመዝጊያ ፕሮግራም ይጠናቀቃል፡፡
ባለፈው ዓመት ‹‹የአፍሪካ ሲኒማ ዘመናዊ ስፍራ›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የመጀመሪያው የፊልም ፌስቲቫል፤ ከ28 አገራት የተውጣጡ ከ40 በላይ ታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች መሳተፋቸው የሚታወስ ሲሆን 56 ምርጥ የአፍሪካ ፊልሞች ተስተናግደውበታል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአሜሪካ የንግድ ምክርቤት አካል ከሆነው አለማቀፍ የግል ንግድ ተቋማት ማዕከል (CIPE) ጋር በመተባበር ያቋቋመውና በአፍሪካ ቀንድ በአይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት የንግድ ስራ ስልጠና አካዳሚ ባለፈው ማክሰኞ ተመርቆ ተከፈተ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን በአካዳሚው የምረቃ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ የንግድ ስራ የልህቀት ማዕከል በመሆን እንዲያገለግል ታስቦ በአዲስ አበባ የተገነባው የዚህ የንግድ ስራ ስልጠና አካዳሚ መከፈት፣ በአገሪቱ የግል ዘርፍ ላይ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው፡፡
በአገሪቱ ያለው የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ ከተለምዷዊ አስተሳሰቦችና አሰራሮች መላቀቅና በዘመናዊ የንግድ ስራ ንድፈ ሃሳቦችና አሰራሮች መመራት እንደሚኖርበት የገለጹት ወ/ሮ ሙሉ፣ አካዳሚው ለንግዱ ማህበረሰብ አባላትና ለሚመለከታቸው ድርጅቶች ሰራተኞች ተገቢውን ስልጠና በመስጠት፣ የግሉን ዘርፍ አቅም በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የስልጠና ማዕከሉ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትንና  የአባል ድርጅቶችን የአመራርና የአስተዳደር ክህሎት የማጠናከርና ተቋማዊ አቅምን የመገንባት አላማ ያለው ነው፡፡ በንግዱ ዘርፍ በተሰማሩ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት፣ ትብብርና፣ ጥምረት ለማሳደግም ይሰራል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ከፍተኛ የህግ ባለሙያው ፕሮፌሰር ሞሃመድ ሃቢብ በበኩላቸው፣ መሰል አለማቀፍ ትብብር መፍጠር፣ ወቅቱን የጠበቀ የንግድ ስራ እውቀትን በማሰራጨት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ አካዳሚው መቋቋሙ በአገሪቱ ያለውን የግሉን ዘርፍ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃና እድገቱን እንደሚያፋጥን  ተናግረዋል፡፡
የልህቀት ማዕከሉ መገንባቱና ተገቢውን ስልጠና መስጠቱ፣ የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ ልማትና እድገት ላይ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና እንዲጫወት የሚያስችል መነሳሳት እንደሚፈጥርም አክለው ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በተከናወነው የአካዳሚው የምረቃ ስነስርዓት ላይ የመንግስት ተወካዮች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የአለማቀፍ የልማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ከ60 አመታት በላይ የአገሪቱን የንግድ ማህበረሰብ ማገዝ የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ተነግሯል፡፡

      በኢትዮጵያ የቴሌኮም ፕሮጀክቶች ላይ ላለፉት 12 ዓSqƒ ሲሰራ የቆየው ዜድቲኢ፣ አሁን በመካሄድ ላይ በሚገኘው የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት 50 በመቶ ድርሻ መውሰዱ የሚታወቅ ሲሆን፤  በኤሌክትሪክ ሃይል ስርጭት፣ በትምህርት አቅርቦትና በከተማ አስተዳደር ዙሪያ ሶስት የቴክኖሎጂ ውጤቶቸን ለኢትዮጲያ ገበያ አስተዋወቀ፡፡
ፓወር ግሪድ፣ ኢለርኒንግ እና ስማርት ሲቲ በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የተሣለጠ የከተማ አኗኗር ለመፍጠር የሚያስችሉና በከተማ አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ የሚባሉትን መሰረታዊ መረጃዎች በማጠናቀር አመራራርን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው፡፡
የኢትዮጲያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ለሀገር ውስጥ ገበያ የተዋወቁት የቴክኖሎጂ ውጤቶች በፍጥነት እያደገች ባለችው ቻይና እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተተግብረው ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ዜድቲኢ ገልፆ፤ በአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አምራችነት ቀዳሚ ስፍራ ለማግኘት አስችለውኛል ብሏል፡፡
ስማርት ሲቲ የተሰኘው ቴክኖሎጂ የ2013 የአለም አቀፍ የሞባይል ቴክኖሎጂ የሽልማት አሸናፊ እንደሆነና በቤጂንግ ከተማ ተተግብሮ የአለም አቀፍን የፈጠራ ተሸላሚ ለመሆን እንደበቃ ኩባንያው ገልጿል፡፡  ኢለርኒግና ፓወር ግሪድ የተባሉት ቴክኖሎጂዎችም ከቻይና በተጨማሪ በሞሪሺየስ፣ ፓፓዋ ኒው ጊኒ፣ በአሜሪካ፣ በቬንዙዌላ እና በኬኒያ ተሞክረው ውጤታማ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
በፍጥነት እያደጉ ባሉባት የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተተግብረው ውጤታማ እንደሚሆኑ ዜድቲኢ ጠቅሶ፤ የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት በ2020 ወደ 120 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅና ከዚህም ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ በከተማ ይኖራል ተብሎ እንደሚገመት ገልጿል።

Monday, 31 March 2014 11:07

የጥንቱ አገረሸ

ሁሉን የሚችል ዳስ አንጣሎ፤ ገትሮ
ደልድሎ፤ አሳምሮ
ሊጡ ተቦካና እንጀራው ተጋግሮ
ለብሶ ተከምሮ፤
ጠጁ ተጣለና በጠላ ጉሮሮ
ሊወርድ ተደርድሮ፤
ወጡ በያይነቱ ባዋቂ ተሠርቶ፤
ቁርጡ ተሰናድቶ፤
ሰው ሁሉ ለመብላት፤ ለመጠጣት ጓጉቶ፤
ሲጠብቅ ሰንብቶ፤
አዝማሪው ለዘፈን ቆሞ ተዘጋጅቶ፤
ማሲንቆው ተቀኝቶ፤

ጨዋታ ፈረሰ!
ዳቦ ተቆረሰ!
ሙሽራው ጠፋና ሠርጉ ተበላሸ፤
የተጠራው ሸሸ፤
ጊዜ ከዳውና በጊዜው ላመሸ፤
ዳሱ ተረበሸ፤
የጥንቱ አገረሸ፡፡
(ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም
“ዛሬም እንጉርጉሮ” የተሰኘ የግጥም መድበል የተወሰደ)