Administrator

Administrator

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2010 ባወጣውና ተግባራዊ እያደረገው ባለው የ2025 ራዕይ፣ በ15 አመታት ውስጥ አሳካቸዋለሁ ብሎ ያስቀመጣቸውን ግቦቹን በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ ለማሳካት መቻሉን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ አበባ የተጀመረውን የአለማቀፉ የሲቪልአቪየሽን ተቋም 4ኛው አለማቀፍ የአቪየሽን ዘርፍ ስልጠና ሲምፖዚየም ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፣አየር መንገዱ አግባብነት ያለው ዕቅድ ማውጣቱና ትክክለኛውን የማስፈጸም ስልት መጠቀሙ በ15 አመታት ውስጥ አሳካቸዋለሁ ያላቸውን ግቦች በ5 አመታት ጊዜ ውስጥ ለማሳካት አስችሎታል ብለዋል። አየር መንገዱ ባለፉት ሰባት አመታት እጅግ ፈጣን እድገት ማስመዝገቡን የጠቆሙት አቶ ተወልደ፤ የአፍሪካ ቀዳሚው አየር መንገድ የመሆን ራዕዩን ካስቀመጠው ጊዜ በአስር አመት ያህል ቀደም ብሎ ለማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

 ከግብጽ መዲና ካይሮ በስተደቡብ በሚገኘው ዳሹር የተባለ አካባቢ በተደረገ ቁፋሮ፣ ከ3ሺህ 700 አመት በላይ ዕድሜ እንዳለውና የመጀመሪያው የጥንታዊ ግብጻውያን የልሙጥ ፒራሚድ ግንባታ ሙከራ ሳይሆን እንደማይቀር የተነገረለት አዲስ ፒራሚድ መገኘቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ዳሹር በተባለውና ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ የነበሩ ጥንታውያን ግብጾች መካነ መቃብር መገኛ መሆኑ በሚነገርለት በዚህ አካባቢ የተገኘው አዲሱ ፒራሚድ፤ ኮሪደሩን ጨምሮ የተወሰነ አካሉ በቁፋሮ መለየቱን የአገሪቱ የጥንታዊ ቅርሶች ተቋም ሃላፊ ማህሙድ አፊፊ ባለፈው ሰኞ ማስታወቃቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
አዲሱ ፒራሚድ በጥሩ ይዞታ ላይ እንደሚገኝ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የግብጽ የአርኪዎሎጂ ተመራማሪዎች በግኝቱ ላይ ተጨማሪ ጥናቶችንና የቁፋሮ ስራዎችን ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡ በፒራሚዱ አካል ላይ ተጽፈው የተገኙ ጥንታዊ ጽሁፎች ይዘት በተመራማሪዎች በጥልቀት እንደሚጠናና፣ ጥናቱ ፒራሚዱን ማን አሰራው እና በየትኛው ስርወ መንግስት ወቅት ተሰራ የሚሉትን የመሳሰሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስችላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አስረድቷል፡፡

 በ2015 ከአለማችን አራት ወንዶች አንዱ በየዕለቱ ያጨስ ነበር

        ሲጋራ በማጨስ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝና በአለማችን በየአመቱ ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 10 በመቶ ያህሉ የሚከሰቱት ሲጋራ በማጨስ ሳቢያ መሆኑን አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
በ195 የአለማችን አገራት ላይ የተሰራውን ሰፊ ጥናት መሰረት ያደረገውንና ዘ ላሰንት በተባለው ሜዲካል ጆርናል ላይ ታትሞ የወጣውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፤ በ2015 ብቻ አንድ ቢሊዮን ያህል ያህል ሰዎች በየዕለቱ ሲያጨሱ እንደነበርና በአመቱ ከአለማችን አራት ወንዶች አንዱ በየዕለቱ ሲጋራ የሚያጨስ (የዘወትር አጫሽ) መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሲጋራ ማጨስ ያለ ወቅቱ ለሚከሰቱ ሞቶችና ለአካል ጉዳተኝነት ምክንያት በመሆን ሁለተኛውን ደረጃ እንደሚይዝ የጠቆመው ጥናቱ፤ በ2015 አመት ብቻ በአለማቀፍ ደረጃ ከትምባሆ ጋር በተያያዘ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ6.4 ሚሊዮን በላይ እንደሆኑ አክሎ ገልጧል፡፡
የትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ገበያቸውን በተለይም ወደ አላደጉ አገራት ለማስፋት እየሰሩ ከመገኘታቸው ጋር በተያያዘ በማጨስ ሳቢያ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ጥናቱ፤ መንግስታት የትምባሆ ቁጥጥር ህግን ማጥበቅ እንደሚገባቸውም መክሯል፡፡

 በበርካታ ፊልሞቹ ተደናቂነትን ያተረፈውና ወደ ፖለቲካው አለም መግባቱን ተከትሎ ከፊልሙ ተሰናበተ ተብሎ ሲነገርለት የነበረው የቀድሞው የካሊፎርኒያ ገዢ አርኖልድ ሽዋዚንገር፣ በቀጣዩ “ተርሚኔተር” ፊልም ዳግም ወደፊልሙ ጎራ ሊቀላቀል እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ታዋቂው የሆሊውድ ዳይሬክተር ጄምስ ካሜሮን ቀጣዩን “ተርሚኔተር” ፊልም ከአዲስ ኩባንያ ጋር በመስራት ለእይታ ለማብቃት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የዘገበው ስካይ ኒውስ፤ ሽዋዚንገርም
በዚህ ፊ ልም ላ ይ በ መተወን ዳግም ከ አድናቂዎቹ ጋር እንደሚገናኝ ማብሰሩን ገልጧል፡፡ ሽዋዚንገር
“ዘ ተርሚኔተር” በሚለው ተወዳጅ ፊልም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወነው እ.ኤ.አ በ1984 እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

አይሲስ በሊቢያ አግቷቸው የነበሩ 28 ኤርትራውያን ተለቀቁ

    የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሆኑ 1 ሚሊዮን ያህል ስደተኞች በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት በማሰብ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው የስደት ጉዞ ላይ እንደሚገኙ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ባለፉት 3 ወራት ብቻ 590 ያህል አፍሪካውያን ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ሰጥመው መሞታቸውን የጠቆሙት በሊቢያ የእንግሊዝ ኤምባሲ የቀድሞ ሃላፊ  ጆ ዎከር ከዚንስ፣ 1 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያን ስደተኞች ለሞት በሚያጋልጠው በዚህ አስቸጋሪ ጉዞ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016፣ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ጣሊያን የገቡ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር 181 ሺህ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ በዚሁ የስደት መስመር ጣሊያን የገቡ አፍሪካውያን ስደተኞች 22 ሺህ ያህል እንደሚደርሱም  አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ አሸባሪው ቡድን አይሲስ በሊቢያ ሲርጥ ውስጥ አግቷቸው የነበሩና ቡድኑ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ አካባቢውን ለቅቆ ከሄደ በኋላ የትሪፖሊ መንግስት ከሽብር ቡድኑ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል በሚል አስሯቸው የቆዩ 28 ኤርትራውያንና ሰባት ናይጀሪያውያን ስደተኞች መለቀቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከእስር ከተለቀቁት ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ወደ አውሮፓ ለመግባት በስደት ጉዞ ላይ የነበሩ ሴቶች እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ የአይሲስ ታጣቂዎች ሴቶቹን በማገት ለወሲብ ሲጠቀሙባቸው እንደነበርም ገልጧል፡፡
ስደተኞቹ ባለፈው ረቡዕ ከእስር መለቀቃቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የተቀበላቸው ሲሆን  የህከምና ምርመራ ተደርጎላቸው ወደ መጠለያ እንዲገቡ መደረጉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

 በወጣቱ ደራሲ ሙሉጌታ አለባቸው የተጻፈው “መሐረቤን ያያችሁ” የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ መጽሐፍ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በሞዛይክ ሆቴል በተከናወነ ልዩ ፕሮግራም ተመርቆ በገበያ ላይ ውሏል፡፡
የስነ-ጽሁፍ ቤተሰቦች በተገኙበት ስነ-ስርዓት የተመረቀውና ማሕበራዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሀሳቦችን የሚዳስሰው “መሐረቤን ያያችሁ”፣ መቼቱን በ1980ዎቹ መጨረሻ የኢትዮጵያ ማሕበራዊ ሕይወት ላይ አድርጎ፣ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያነሳ ሲሆን በአዳዲስ የትረካ ቅርጾች የተዋቀረ ነው፡፡
የደራሲ አዳም ረታን “ሕጽናዊነት” የተባለ ልዩ የአጻጻፍ ስልት መጠቀሙን በመጽሃፉ መግቢያ ላይ የጠቆመው ደራሲው፤ በ215 ገጾች የቀረቡት አስራ ሁለት አጫጭር ትረካዎች እርስ በእርስ በቀጫጭን የትረካ መስመር እንደሚገናኙም ገልጧል፡፡
በሕጽናዊነት የአጻጻፍ ስልት ዙሪያ ጥልቅ ትንታኔዎችን ሲያቀርብ የቆየው ደራሲው፤ “ይሄን ስልት መጠቀሜ ሕጽናዊነትን የማስቀጠል ደፋር ሙከራዬ ነው” ሲል አብራርቷል፡፡
ደራሲ አዳም ረታ በመጽሃፉ የጀርባ ሽፋን ላይ በሰጠው አስተያየት፤ “የሙሉጌታ አለባቸው ቋንቋ ውብ ነው፡፡ ይሕ መጽሐፍ ሊናቅ የማይችል የአንድ ወጣት የስነጽሑፍ ጀብደኛ ዘራፍ ነው” ብሏል፡፡
በአዲስ አድማስና በሌሎች ጋዜጦችና የህትመት ውጤቶች ላይ ለረጅም ጊዜያት አጫጭር ልቦለዶችን፣ ስነጽሁፋዊ ትንተናዎችን፣ መጣጥፎችንና የትርጉም ስራዎችን ለንባብ በማብቃት የሚታወቀው ሙሉጌታ አለባቸው፤ መጽሃፉ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመጽሃፍት ቤቶችና በአዟሪዎች እየተሸጠ እንደሚገኝም በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጧል፡፡

 በደራሲ መላኩ ደምሰው ተፅፎ በአቦወርቅ ሀብቴ የተዘጋጀውና በአቡ ፊልም ፕሮዳክሽንና በአሰፋ ገረመው ፕሮዲዩስ የተደረገው “ፈልጌ አስፈልጌ” የተሰኘ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ ድራማ ፊልም ዛሬና ነገ በሁሉም የግልና የመንግሥት ሲኒማ ቤቶች እንደሚመረቅ ተገለፀ፡፡ ፊልሙ በዋናነት አንድ አደራ የተሰጠው ወጣት አደራውን ለመወጣት የሚያደርገውን ውጣ ውረድና ፈልጎ አስፈልጎ የሚያገኘውን አደራውን የመጠበቅ መንገድ እንደሚያሳይ የፊልሙ ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰር አቶ የአቦወርቅ ሀብቴ ተናግረዋል፡፡ ሐሙስ ረፋድ ላይ በአዜማን ሆቴል ፊልሙን አስመልክተው ደራሲውና ፕሮዲውሰሩ በሰጡት መግለጫ፤ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 18 ወራትና 900 ሺህ መፍጀቱን ጠቁመው፤ የ1 ሰዓት 23 ደቂቃ ርዝመት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ በፊልሙ ላይ ተዘራ ለማ፣ ዝናህብዙ
ፀጋዬ፣ ፍ ፁም ፀ ጋዬ፣ ያ የህይራድ ማ ሞ፣ ኢ የሩሳሌም ደረጀ፣ ዳንኤል አበበ፣ ሀረግ መኳንንት፣ አማን ታዬ፣ መላኩ ደምሰውና ሌሎችም ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ በወቅቱ የአገራችን ፊልም ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ሙያዊ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

  ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ነገ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ
ቤተ - መፃሕፍትና ቤተ - መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ፣ “ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ” እና “የብርሃን ፍቅር” በተሰኙ
የገፃሚ ደበበ ሰይፉ የግጥም መድበሎች ላይ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት ደራሲ
ዳንኤል ወርቁ እንደሆኑ የገለፀው ሚዩዚክ ሜይ ዴይ፤ ፍላጎት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ጋብዟል፡፡

  69ኛው የግጥም በጃዝ ምሽት የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በራስ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ በዕለቱ ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን፣ ደራሲና ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ዲስኩር የሚያቀርቡ ሲሆን አለማየሁ ታደሰ፣ አስቴር በዳኔ፣ ሽመልስ አበራና እታፈራሁ መብራቱ አጭር ተውኔት እንደሚያቀርቡ የፕሮግራሙ አዘጋጆች በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

 በወሩ መጨረሻ ባሉት ቅዳሜና እሁድ የሚካሄደው ትራኮን የመፅሀፍት አውደ ርዕይና የሂስ ጉባኤ፤ ዛሬና ነገ ጥቁር አንበሳ ፊት ለፊት በሚገኘው ትራኮን ታወር ይካሄዳል፡፡ ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ለሂስ የሚቀርበው መፅሀፍ የዶ/ር ምህረት ከበደ የመጀመሪያ ስራ የሆነው “የተቆለፈበት ቁልፍ” ሲሆን ለዚህ መፅሐፍ የውይይት መነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በ“ፍቅር እስከ መቃብር” መፅሐፍ ላይ ለየት ያለ ትንታኔን “እውነትና ገሀድ” በተሰኘው መፅሀፋቸው ያስነበቡትና የስነ መለኮት ሊቁ ዶ/ር ዘካሪያ አምደ ብርሃን እንደሚሆኑ የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ በፍቅሩ
ዳኛቸው ገልፀዋል፡፡
    እነሆ መፅሀፍት መደብር፣ ሊትማን ቡክስና ክብሩ መፅሐፍት መደብር በመተባበር “ሀሳብን በሀሳብ መፈተን” በሚል መሪ ቃል በሚያዘጋጁት በዚህ አውደ ርዕይና የሂስ ጉባኤ፣ የመፅሀፍ እቁብን ጨምሮ ከ25 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ የተደረገባቸውን መፅሐፍት መግዛትና በውይይቱ ላይ መሳተፍ የእውቀት አድማስን ማስፋት ነው ሲሉ አዘጋጆቹ ጋብዘዋል፡፡

Page 8 of 335