Administrator

Administrator

“ኦፕራ ከኔ ጋር ልትፎካከር? አታደርገውም! የምታደርገው ከሆነ ግን፣ ግጥም አድርጌ ነው የማሸንፋት!” - ዶናልድ ትራምፕ

    በቅርቡ በተካሄደው የጎልደን ግሎብ ሽልማት ስነስርዓት ላይ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር ማድረጓን ተከትሎ፣ በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዲሞክራቶችን በመወከል ከትራምፕ ጋር ትፎካከራለች ተብሎ በስፋት ሲነገርላት የሰነበተቺው ታዋቂዋ የቶክ ሾው አቅራቢ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ በፕሬዚዳንትነት የመወዳደር ፍላጎት እንደሌላት በይፋ ማስታወቋን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ብዙዎች ለፕሬዚዳንትነት እንደምትወዳደር ሲዘግቡ ሰንብተዋል፤ እኔ ግን የምችለውንና የማልችለውን ነገር ጠንቅቄ የማውቅ ሰው ነኝ! የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት የለኝም ስትል፣ ኢንስታይል ከተባለው መጽሄት ጋር ከሰሞኑ ባደረገቺው ቃለ መጠይቅ ኦፕራ አቋሟን መግለጧን  ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኦፕራ በ2020 በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደምትሳተፍ የሚገልጸው ወሬ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ “ይህ እጅግ አስቂኝ ነገር ነው፤ ኦፕራ ከኔ ጋር ልትፎካከር? አታደርገውም! የምታደርገው ከሆነ ግን፣ ግጥም አድርጌ ነው የማሸንፋት!” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ቻይና ቴሲጁ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የተሰኘው የቻይና የግንባታ ተቋራጭ ኩባንያ፣ ፉጂያን በተባለው የአገሪቱ ደቡባዊ አውራጃ የሚገኘውን የአንድ ግዙፍ የባቡር ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት፣በ9 ሰዓታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ አጠናቅቆ ማስረከቡን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
ናንሎንግ በተባለው ግዙፍ የባቡር ጣቢያ ፕሮጀክት የግንባታ ስራ ላይ 1 ሺህ 500 ቻይናውያን የግንባታ ሰራተኞች መሳተፋቸውንና ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በ9 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የተቻለው የተጠናና የተቀናጀ ስራ በማከናወናቸው መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሰራተኞቹ በሰባት ቡድኖች ተከፋፍለው እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን የሚያስችላቸውን ስልጠና አግኝተው ወደ ስራ መግባታቸውም ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በዚህ የሚገርም ፍጥነት እንዲያጠናቅቁ እንዳስቻላቸው ተነግሯል፡፡
ባለፈው አርብ በተከናወነው በዚህ እጅግ ፈጣን የግንባታ ስራ፣ ሰባት ባቡሮችንና 23 የቁፋሮ ማሽኖችን ጨምሮ የተለያዩ የግንባታ መሳሪያዎችን መጠቀሙን የጠቆመው ኩባንያው፣ በግንባታው ሶስት የባቡር ሃዲዶችን ወደ አንድ የማቀላቀል፣ የትራፊክ መብራቶችን የመግጠም፣ የተለያዩ የእንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን የመትከልና ሌሎች ስራዎች በሚገርም ፍጥነትና ጥራት መጠናቀቃቸውንም አመልክቷል፡፡


  ታዋቂው የአሜሪካ ኩባንያ ማይክሮሶፍት፣ ቶምሰን ሮይተርስ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው የዓመቱ የአለማችን ምርጥ 100 ታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ በመሪነት መቀመጡን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ትርፋማነትና ተቋማዊ ብቃት በመመዘን በየዓመቱ ይፋ በሚያደርገውና ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ፣ የኮምፒውተር መሳሪያዎችን በማምረት የሚታወቀው ኢንቴል የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ የኔትወርክ መሳሪያዎች አምራቹ ሲስኮ ሲስተምስ ኩባንያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ ከማይክሮሶፍት፣ ኢንቴልና ሲስኮ በተጨማሪ የአሜሪካዎቹ አፕል፣ አልፋቤት፣ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ማሺንስ ኮርፖሬሽንና ቴክሳስ ኢንስትሩመንት እስከ አስረኛ ባለው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አስከ አስረኛ ባለው ደረጃ ውስጥ የተካተቱት የሌሎች አገራት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ደግሞ የታይዋኑ ሰሚኮንዳክተር ማኑፋክቸሪንግ፣ የጀርመኑ ሳፕ እና ተቀማጭነቱ በደብሊን የሆነው አክሴንቸር መሆናቸውን ተቋሙ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በዘንድሮው የቶምሰን ሮይተርስ የዓለማችን ምርጥ 100 የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ታላላቅ ኩባንያዎች መካከልም አማዞንና ፌስቡክ ይገኙበታል፡፡ ከ100ዎቹ ምርጥ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መካከል 45 በመቶ ያህሉ መቀመጫቸውን በአሜሪካ፣ ጃፓንና ታይዋን  ያደረጉ መሆናቸው የጠቆመው ተቋሙ፤ ሰሜን አሜሪካ 47፣ እስያ 38፣ አውሮፓ 14 እና አውስትራሊያ 1 ኩባንያ በዝርዝሩ ውስጥ ማካተታቸውንም አመልክቷል፡፡

በናሚቢያ የሚገኙ ስደተኛ ዚምባቡዌያውያን ከሰሞኑ አገሪቱን የጎበኙትን አዲሱን ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋን በአካል በአይነስጋ ለማየት የሚችሉት 16 ዶላር ከከፈሉ ብቻ እንደሆነ ከኤምባሲያቸው በተላለፈላቸው መመሪያ ክፉኛ መቆጣታቸው ተዘግቧል፡፡
የበጀት እጥረት የገጠመው በናሚቢያ የሚገኘው የዚምባቡዌ ኤምባሲ፣ ሙጋቤን ተክተው ወደ ስልጣን የወጡትን የፕሬዚዳንት ምናንጋግዋን ጉብኝት እንደ አንድ የገቢ ማግኛ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በናሚቢያ የሚገኙ ዜጎቹንና ድሃ ናሚቢያውያንን ፕሬዚዳንቱን በቅርበት ለማየት 16 ዶላር ክፈሉ ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኤምባሲው በአንድ ሆቴል ውስጥ 300 ሰዎችን የሚይዝ አዳራሽ በመከራየት ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ በቦታው ተገኝተው ከፍለው ለሚገቡ ዚምባቡዌያውያን ንግግር ያደረጉበትን ፕሮግራም ያዘጋጀ ሲሆን፣ ከፍለው የታደሙ የመኖራቸውን ያህል እንዴት መሪያችንን እንደ ቱሪስት መስህብ ከፍለን እናያለን በሚል ቁጣቸውን የገለጹም ነበሩ ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን ደህና ገቢ ያላቸው ስደተኛ ዚምባቡዌያውያን ቀደም ብለው ትኬት ቆርጠው፣ መሪያቸውን ለማየት በሆቴሉ ቢታደሙም፣ ገና አዳራሹ ሳይሞላ የጥበቃ ሰራተኞች ከፍለው ለመግባት የተዘጋጁትንና ከውጭ ቆመው ይቃወሙ የነበሩትን ሰዎች ማባረራቸውንና ይህም ቁጣን መቀስቀሱን ዘገባው አስረድቷል፡፡

 ለኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት እውቅና በመስጠታቸው የደረሰባቸውን ዓለማቀፍ ውግዘት ተከትሎ፣ “ብዙ እየረዳኋት አታከብረኝም” በሚል ለፍልስጤም የሚሰጡትን እርዳታ እንደሚቀንሱ ሲዝቱ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉትም፣ ለፍልስጤም ስደተኞች ይሰጡት ከነበረው እርዳታ ላይ ከግማሽ በላይ መቀነሳቸው ተዘግቧል፡፡
አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ለፍልስጤም ስደተኞች ስትሰጠው ከነበረው 125 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ወይም 65 ሚሊዮን ዶላሩን መቀነሷን በይፋ ማስታወቋን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፤ ይህን ተከትሎም በዌስት ባንክ፣ ጋዛ ሰርጥ፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስና ሶርያ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ስደተኞች ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃሉ የሚል ስጋት መፈጠሩን አመልክቷል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ አገራቸው ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈቺው ማንንም ለመበቀልና ለማጥቃት በማሰብ ሳይሆን፣ ገንዘቡን ከመለገሳችን በፊት በተመድ ስር የሚገኘውን የእርዳታ ተቋም አጠቃላይ አሰራር በጥንቃቄ መፈተሽ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡ ተቋሙ ለፍልስጤም ታጣቂዎች ድጋፍ በማድረግና አድልኦአዊ አሰራር በመከተል በእስራኤል ተደጋጋሚ ትችት ሲሰነዘርበት እንደቆየ ያስታወሰው ዘገባው፤የትራምፕ አስተዳደር በተቋሙ አሰራር ላይ ፍተሻ ለማድረግ መወሰኑም ከዚህ ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል እየተነገረ ነው ብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ከሰሞኑ አፍሪካውያንን በአደባባይ ዘልፈዋል በሚል ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይቀር ከፍተኛ ውግዘት የገጠማቸውና በብዙዎች ዘንድ በአእምሮ ጤና ችግር ሲታሙ በቆዩት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ምርመራ ሲያደርጉ የቆዩት የዋይት ሃውሱ ሃኪም፣ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ ትራምፕ በአእምሮም ሆነ በአጠቃላይ ጤንነታቸው ቅንጣት ታህል ችግር የሌለባቸው ጤነኛ ሰው መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብለዋል፡፡
ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጊዜ አንስቶ በሚናገሯቸው አጉል ንግግሮችና በሚወስዷቸው አስደንጋጭ ውሳኔዎች አለም በወፈፌነት ሲጠረጥራቸው የቆዩት ትራምፕ፤ ሌሎች ምርመራዎችን ለሚያደርግላቸው ሃኪም “እባክህን የአእምሮዬንና የአስተሳሰብ ሁኔታዬንም አብረህ መርምረኝ” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤በዚህ መሰረት በተደረገው ምርመራ ሙሉ ጤናማ መሆናቸው መረጋገጡን ገልጧል፡፡ የአእምሮ ብቃታቸው አገር ለመምራት የሚያስችልና ትክክለኛው ደረጃ ላይ ነው የተባለላቸው ትራምፕ፣ አጠቃላይ ጤንነታቸው በጥሩ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ እንቅስቃሴ ማድረግና ከ10 እስከ 15 ፓውንድ ክብደት መቀነስ እንደሚገባቸው በሀኪማቸው መመከራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

በሳይቤሪያ በምትገኘው ኦይማይኮን የተባለች የገጠር መንደር ውስጥ በሳምንቱ መጀመሪያ ከዜሮ በታች ኔጌቴቭ 62 ዲግሪ ሴንትግሬድ የደረሰ ሃይለኛ ቅዝቃዜ የተመዘገበ ሲሆን ቅዝቃዜው በመንደሯ የነበረውን የሙቀት መለኪያ መሳሪያ በመስበር ከጥቅም ውጭ ማድረጉ ተነግሯል፡፡
እ.ኤ.አ በ1993 ከዜሮ በታች 67.7 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሃይለኛ ቅዝቃዜ የተመዘገበባት መንደሯ፤500 ያህል ቋሚ ነዋሪዎች እንደሚገኙባትና ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያላት መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ነዋሪዎች ቅዝቃዜውን ለመቋቋም ተቸግረው እንጨትና ከሰል በማቀጣጠል ህይወታቸውን ለማትረፍ ደፋ ቀና እያሉ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
በአለማችን ታሪክ ዝቅተኛው የሙቀት መጠን ሆኖ የተመዘገበው በምስራቃዊ አንታርክቲካ እ.ኤ.አ በ2013 የተከሰተው ከዜሮ በታች ኔጋቲቭ 94.7 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ቅዝቃዜ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡

   ሹዋን ቮኬሽናል ኮሌጅ  ኦፍ ካልቸር ኤንድ ኮሙኒኬሽን የተባለው የቻይና ኮሌጅ ተማሪዎች ሰሞኑን በወሰዱት የሴሚስቴር ማጠቃለያ ፈተና ላይ የመምህራቸውን ስም እንዲጽፉ የሚያዝዝ አንድ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡
ቤጂንግ ታይም እንደዘገበው፤ተማሪዎቹ የሰባት ሰዎችን ፎቶግራፍ የያዘ የጥያቄ ወረቀት የቀረበላቸው ሲሆን ከሰባቱ መካከል መምህራቸውን መርጠው ከስሩ ስሙን እንዲጽፉ ተጠይቀዋል። ጥያቄውን በትክክል የመለሱት ተጨማሪ ማርክ ባይሰጣቸውም፣ የተሳሳቱና መምህራቸውን ወይም ስሙን መለየት ያልቻሉት ግን ካገኙት ውጤት ላይ 41 ነጥቦች ተቀንሶባቸዋል፡፡
በኮሌጁ የሚያስተምሩት ሁ ቴንግ እንደሚሉት፤ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን ይህን ጥያቄ በፈተናው ውስጥ ማካተት ያስፈለገው፣ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ባሻገር በዙሪያቸው ላለው ነገር ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጡ ለመገምገም በሚል ነው፡፡ ይህ የኮሌጅ ፈተና ጥያቄ በቻይናውያን ማህበራዊ ድረገጾች መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ መሰንበቱን የጠቆመው ዘገባው፣ አንዳንዶች ክፉኛ ቢያብጠለጥሉትም የተወሰኑት ግን የመምህርን ስም ማወቅ ግዴታ ነው ሲሉ ድጋፋቸውን እንደሰጡት አመልክቷል፡፡

Saturday, 20 January 2018 12:31

የእግዜር ስላቅ

ነገ እኩለ-ቀን ላይ
ምሳ አብረን ልንበላ ተቃጥረን ነበረ
ጓዴን ዛሬ ማታ
ከቀጠሮው በፊት ሞት ቀድሞት አደረ
ይህ ገብቶት ነው ለካ
እኛ ስንቃጠር እግዜር ከላይ ሆኖ ሲስቅ የነበረ፡፡

ፈሪሃ እግዚአብሔር
‹እግዚአብሔርን ፍራ› እያለ ሲሰብከኝ በነጋ በጠባ    እግዜርን ፈርቼ
እግዜርን ሸሽቼ
ደብር መሄድ አቆምኩ ገነት እንድገባ፡፡

መልክኣ ሰብእ
አውቃለሁ ኃጢአቴን ብዙ በድያለሁ
ቃልህን ገድፌ ሺ ጊዜ ስቻለሁ፤
ቢሆንም ቢሆንም
ንስሀ ለመግባት ስለማይሆንልኝ
አቤቱ ጌታ ሆይ ና ተሰቀልልኝ!
(“አገሬን ሰቀሏት” ከተሰኘው የገጣሚ
ደሱ ፍቅር የግጥም መድበል የተወሰደ)

Saturday, 20 January 2018 12:18

የወቅቱ ጥቅስ

“ያልተደራጀ ኃይል፤ ኃይል አይደለም!”
     የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

Saturday, 20 January 2018 12:26

ማራኪ አንቀፅ

 አንድ የአሜሪካን ባህር ኃይል አባል ታሪክ ትውስ አለው፡፡ አንድ ጦር መርከብ ከአንድ ወደብ ተነስቶ ወደ ሌላ ግዳጅ በሚሰማራበት ወቅት የእያንዳንዱ ክፍል ኃላፊ ያለውን የሰው ኃይልና የተመደበበትን ክፍል ምን ያህል ዝግጁ ሆኖ እንደሚሰለፍ ለካፒቴኑ እየመጣ ተራ በተራ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ በአንደኛው ግዳጅ ላይ ቀዘፋው ተጀምሮ አንዱ መርከበኛ የደረሰበት ጠፋ፡፡ የመርከቧ ጓዳ ጎድጓዳ ሁሉ ተፈለገ፡፡ አልተገኘም፡፡ ይህንን አሳዛኝ ዜና ለባህር ኃይል መደብ ሪፖርት አድርገው ወደ ፊት ቀዘፋቸውን አቀኑ፡፡
ይህ ልጅ በጠፋበት አካባቢ አንድ ሰማያዊ ዓሣ ነባሪ በዓሣ አጥማጆች ተሰገረ፡፡ ዓሣ ነባሪውን ያሰገረችው መርከብ፣ የራሷ ቄራ ነበራትና ዓሣ ነባሪውን ጎትታ ወደ ቄራው እገባችው፡፡ በላቾቹ በፍጥነት የዓሣ ነባሪውን ሆድቃ አንዳች በሚያክለው ቢላቸው ሲበረግዱ፤ አንዱ ጥግ ላይ ያ ከመርከብ ላይ ጠፋ የተባለ መርበኛ እጥፍጥፍ ብሎ እንቅልፉን እየለጠጠ ነበር፡፡ በላቾቹ ተደናግጠው ሲቀሰቅሱት፤ “ምነው የዘብ ሰዓት ደረሰ እንዴ?” ብሎ መጠየቁ ይወራለታል፡፡
ይህ መርከበኛ ከመርከቧ ላይ እንደወደቀ ዓሣ ነባሪው ዋጥ አድርጎታል፤ ሳያውቀው ወደ ሞቱ እያዘገመ ነበር፡፡ ዛሬ ዕድሜ ለዓሣ አስጋሪዎች በሕይወት ተረፈ፡፡ ይሁን እንጂ ሕይወቱን በሙሉ ለምጣም ሆኖ ኖረ፡፡
“የእኛስ ምን ይሆን ዕጣችን?...” አውጠነጠነ፡፡ ምላሽ የለውም፡፡ መፍጠን አለበት፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሻርክ ራት ሆነው የቀሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን፣ ጀርመናውያንና እንግሊዛውያን መርከበኞች ታሰቡትና አሁን ሲሆን ያየ ይመስል ዘግንኖት አይኖቹን ጨፈነ። ደገመና “የእኛስ መጨረሻ ምን ይሆን?” ሲል በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ዓለም ውስጥ ሲኖር መግቢያው ብቻ ሳይሆን መውጫውንም ማውጠንጠን የግድ ነው፡፡
ጀርባዋ ላይ በእርዳታ የታደለ ቦክራ የዱቄት ወተት አለ፡፡ ብዙዎቹ መርከበኞች በጥብጦ የመጠጣት ልምድ የላቸውም፡፡ ያሬድ ሐጎስ ባህር ኃይል በልክ ሰፍሮ የሚሰጠው ምግብ ከአንጀቱ ጠብ ስለማይል ቦክራውን በጥብጦ በመጠጣት የምግብ ፍላጎቱን ያሟላል፡፡ ከተማ ወጥቶ ተዝናንቶ እስኪመለስ የበጠበጠውን የቦክራ ወተት ፍሪጅ ውስጥ አስቀምጦ ይሄዳል። ምሽቱ ሲጋመስ በደንብ ቀዝቅዞ ስለሚጠብቀው አንጀት አርስ እንደሚሆንለት ዕምነቱ ነው፡፡ ይህንን አልሞ በጥብጦ የማስቀመጥ ባህሉን ቢያዳብርም፣ በቅርቡ ግን ማንነቱን ያላወቀው መርከበኛ እየሰረቀ ጠጥቶበት በተደጋጋሚ ባዶ ጆግ ፍሪጅ ውስጥ አጋጥሞታል፡፡ ይህን ቀበኛውን ለማጥመድ ዛሬ ቦክራው ውስጥ “ፈንጂ” አጥምዶበት ነው ፍሪጁ ውስጥ ያኖረው፡፡
(ከደራሲ ዘነበ ወላ “መልህቅ”
የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ላይ የተቀነጨበ)