Administrator

Administrator

     የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አቶ ነገሠ ተፈረደኝን፣ የብሔራዊ እርቅና መግባባት ጉዳዮች ኃላፊ አድርጐ ሾመ፡፡ ባለፈው ነሐሴ 14  የተሰበሰበው የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት፤ ያለፉትን ሁለት ወራትና በጠቅላላ የዓመቱን የሥራ ክንውን ሪፖርት ያዳመጠ ሲሆን የስራ አስፈፃሚውን አሠራር በግልና በቡድን ገምግሟል፡፡
ምክር ቤቱ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ የብሔራዊ እርቅና መግባባት ቋሚ ኮሚቴን ወቅታዊነትና አስፈላጊነት በመግለፅ፣ በመተዳደሪያ ደንብ 10/7 መሠረት ሲሰራ፣ አስፈፃሚ ውስጥ እንዲካተት ማፅደቁ ይታወሳል፡፡
በዚህ መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ነገሠ ተፈረደኝን በኃላፊነት መድበው፣ ለብሔራዊ ምክር ቤት በማቅረብ  ያፀደቁ ሲሆን ኃላፊነትና ተግባራቸውንም በዝርዝር አቅርበው አፀድቀዋል፡፡ ምክር ቤቱ የአቶ ነገሠን ሹመት በከፍተኛ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን እርሳቸውም የተሰጣቸውን ሃላፊነት በፅናት ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡
የብሔራዊ እርቅና መግባባት ጉዳዮች ኃላፊ፣ ከሚወጣቸው የሥራ  ሃላፊነቶች  መካከል፡- የድርድር ጥያቄዎች ሲመጡ በኃላፊነት ያስተባብራል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የድርድር ሀሳቦችን በማመንጨትና ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በማፀደቅ ለመንግስት፣ ለገዥው ወይም ለሌሎች ፓርቲዎችና ድርጅቶች ያቀርባል፣ የብሔራዊ እርቅ ተሞክሮ ያላቸውን ሀገሮች፣ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በማጥናት ለውይይት ያቀርባል፣ ብሔራዊ እርቅና መግባባትን  የተመለከቱ ትምህርትና ስልጠናዎች ያዘጋጃል፣ ለብሔራዊ እርቅ የሚረዱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የልምድ ልውውጦችን ያሳልጣል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ምክር ቤቱ ያካሄደው  የዘንድሮን  የመጨረሻ 5ኛ ዓመት፣ 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ሲሆን የቀጣዩን ዓመት ዕቅድ ለማፅደቅ፣ ለነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

በአደጋው 140 እንስሳት ሞተዋል፤በሰብልና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል
   በዘንድሮ ክረምት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመብረቃ አደጋ የ40 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን 149 እንስሳትም በዚሁ አደጋ መሞታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሰውና በእንስሳት ላይ ከደረሰው አደጋ በተጨማሪ በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይም  ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል - የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ደምሴ፡፡
አደጋዎቹ የደረሱት በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋርና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ የገጠር ወረዳዎች መሆኑ ታውቋል፡፡
በክረምቱ መጀመሪያ ሰኔ ወር ላይ፣ በሃዲያ ማሻ በመብረቅ፣ 1 ሰው ህይወቱ ሲያልፍ፤ በምዕራብ ሸዋ፣ በሚዳገንና በአሶሳ በድምሩ 44 ከብቶች ሞተዋል። በሐምሌ ወር ደግሞ በአማራ ክልል ስማዳ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ዋግ፣ ዳህኑ፣ ወልዲያ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል፡- ዶዶላና  ሄሪ እንዲሁም በትግራይና አፋር ክልሎች በተከሰተው የመብረቅ አደጋ፣ በጠቅላላው የ13 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ፣ 25 ከብቶችንም መግደሉ  ታውቋል፡፡
ከነሐሴ ወር ጀምሮ እስከ አሁን ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ደግሞ በሃረር፣ ወለጋ፣ መንዝ፣ ዋግህምራ፣ ወረባቡ፣ አልቡኮ፣ ጎንደር፣ አድዋ፣ አሶሳ፣ በከማሼና በአፋር በደረሰ የመብረቅ አደጋ 18 ሰዎች ሲሞቱ፣ 80 ከብቶችም እንደተገደሉ፣ ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን  ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ባለፈው ረቡዕ በሰሜን ሸዋ የደረሰ የመብረቅ አደጋ፣ በአረም የግብርና ስራ ላይ የነበሩ የ9 ዓመት ህፃንን ጨምሮ የ8 ሰዎች ህይወትን እንደቀጠፈም ታውቋል፡፡ በእንስሳትና በሰው ላይ ከደረሰው አደጋ በተጨማሪ በሃረር - ጃርሶ፣ አልቡኮ ወረዳዎች በድምሩ 12 ቤቶች ሲፈርሱ፣ 79ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብልም ጉዳት እንደደረሰበት ወ/ሮ አልማዝ አስታውቀዋል፡፡ የመብረቅ አደጋ ሊከሰት የሚችለው በዝናብ ወቅት ትላልቅ ዛፎች ስር በመጠለል መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ አልማዝ፤ ክረምቱ ቀጣይነት ያለው እንደመሆኑ፣ ሰዎች ዛፍ ስር መጠለል እንደሌለባቸው አሳስበዋል፡፡    

 አድማስ ዩኒቨርሲቲ በቢሾፍቱ ካምፓስ ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ከ500 በላይ ተማሪዎቹን ዛሬ በቢሾፍቱ ተዘራ ሲኒማ አዳራሽ ያስመርቃል፡፡
ከሚመረቁት መካከል 210 ተማሪዎች በድግሪ መርሀ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ቀሪዎቹ 300 ተማሪዎች ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ስልጠናቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን ዩኒቨርሲቲው በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች ናቸው ብሏል-ዩኒቨርሲቲው፡፡
አድማስ ዩኒቨርሲቲ በሶማሌላንድና በፑትላንድ የሚገኙትን ጨምሮ በ10 ካምፓሶች እንዲሁም ከ60 በላይ በሚሆኑ የርቀት ትምህርቱ ማዕከላት እስከዛሬ ድረስ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁን ገልጿል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በመካኒሳና በመቐለ አዳዲስ ካምፓሶችን ከፍቶ፣ የዲግሪና የቴክኒክና ሙያ መርሀ ግብሮች ስልጠና መጀመሩን ጠቁሞ፣ በቅርቡ በ4 የስልጠና ዘርፎች በማስተርስ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ ንጉሥ፤ በአንድ አገር ይኖር ነበረ፡፡ ንጉሡ አንድ ልጅ አለው፡፡ ይህ ልጅ ከዕውቀት ዕውቀት የሌለው፣ ከልምድ ልምድን ያላገኘ፣ በዕድሜውም ገና ለጋ ነበረ፡፡ ሆኖም የዕለት ሰርክ ምኞቱ፣ የአባቱን ዙፋን ወርሶ፣ በምቾት ተንደላቆ መኖር ነበር፡፡ ስለዚህ መኝታ ቤቱን ይዘጋና ነጋ ጠባ እንዲህ ሲል ይፀልያል፡-
“አምላኬ ሆይ፣ እስከ መቼ አልጋ - ወራሽ እየተባልኩ እቀመጣለሁ? ያረጀውን አባቴን ከዚህ ዓለም በቶሎ አሰናብትልኝ!”
ይሄን የሁልጊዜ ፀሎቱን እየደጋገመ ጮክ ብሎ ይፀልየዋል፡፡ አንድ ቀን በአጋጣሚ አባት የልጁን ፀሎት ሰማ፡፡
“ይህን ልጅ ከእንዲህ ያለ ቀቢፀ - ተስፋ ልገላግለው የምችለው እንዴት ነው?” እያለ ይጨነቅ ጀመር፡፡
ከብዙ ማውጣት ማውረድ በኋላ አንድ ዘዴ ታየው፡- አምላክን መስሎ፣ ፀሎቱን የሰማው አስመስሎ መልስ መስጠት፡፡
በዚህ መሠረት፣ አንድ ማታ ከልጁ መኝታ ጀርባ ተሸሽጎ እንዲህ አለው፡-
“ልጄ ሆይ! ፀሎትህን ሰምቻለሁ፡፡ ከእንግዲህ አባትህ ብዙ ዕድሜ አይኖረውም፤ ዙፋኑን ለመጨበጥ ተነሳ!”
ዕውነትም አባት ከዚያች ማታ ጀምሮ አልጋ ላይ ዋለ፡፡ ሆኖም አባት መታመሙን አገር ሁሉ ሰማ፡፡ የውስጥ ቦርቧሪዎች፣ የውጭ ወራሪዎች አገሪቱን አደጋ ላይ ጣሏት፡፡ ይንጧት ጀመር፡፡ ጊዜ ያመቻቸው የመሰላቸው ሁሉ ተረባረቡ፡፡ ልጅየው የሚያደርገው ጠፋው፡፡
ጭንቅ በጭንቅ ሆነ! ስለዚህ አምላክን ተማጠነ፡-
“አምላኬ ሆይ! በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠላት ተነሳብኝ፡፡ ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ፡፡ እባክህን መንገዱን ምራኝ?” አለ፡፡
ይህን ፀሎት የሰማው አባት፣ በአምላክ ተመስሎ፤ እንዲህ አለው፡-
“ፈጥነህ ወደ አባትህ ሂድ፡፡ ምክሩንም ጠይቀው፡፡ መዳኛህ የእርሱ ምክር ነው። እስትንፋሱ ሳያበቃ፣ የዕድሜ ፀጋውን አግኝ፡፡ በጭንቅ ሰዓት ምን ዓይነት ብልህነት ሊኖርህ እንደሚገባ ጠይቀውና የሚልህን በጥሞና አዳምጥ፡፡”  
ልጁ እየሮጠ ወደ አባቱ ሄደና፤ “አባቴ ሆይ፤ ምክርህን እሻለሁ፡፡” አለው፡፡
አባትየውም፤
“በመጨረሻ ወደ እኔ መጣህን? አሁንም አልረፈደም! አበክረህ አድምጠኝ” አለና ጀመረ፡፡ “በመጀመሪያ፤ በመከራህ ሰዓት የቅርብ ሰው እንደሚያስፈልግህ አስታውስ፡፡ ስለዚህ የቅርብህን ሰው አታርቅ! ለውርስ ብለህ የአባትህን ሞት ለማኝ አትሁን፡፡ ተጣጥረህ በግንባርህ ወዝ በልፅግ እንጂ የምኞት አቋራጭ መንገድ ለማግኘት አትፍጨርጨር!
አባትህ መመኪያህ ነው፡፡ አባትህ ማዕረግህ ነው፡፡ አባትህ ማስፈራሪያህ ነው፡፡ አባትህ የኋላ ታሪክ ያለው ስለሆነ፤ ባላንጣዎችህ ሁሉ በእሱ ዐይን ስለሚያዩህ፣ እሱ በመኖሩ እንደተከበርክ ትኖራለህ! ድንበርህን አይሻገሩም! አጥርህን አይነቀንቁም! አጋር - አልባ አድርገው አያዩህም! አባትህ ከአልጋ በዋለ ማግሥት፣ በአልጋው ዙሪያ የሚያሴሩትን የወዳጅ ጠላቶች አስተውል፡፡ ከሀሰተኛ ወዳጆች ይልቅ ዕውነተኛ ጠላቶች ያጠነክሩሃል። ቁርጥህን አውቀህ፣ አንጀትህን አስረህ እንድትጓዝ ያደርጉሃል፡፡ ህዝብህን አትናቅ፡፡ አዳምጥ፡፡ በራስህ ተማምነህ፣ በሁለት እግርህ ቆመህ፣ አገርህን በትክክል እንድትመራ፣ የህዝብ ፍቅር ያስፈልግሃል! የህዝብ ድጋፍ ያስፈልግሃል!!” አለው፡፡
ልጅየው ምክሩን ከሰማ በኋላ ወደ ፀሎት ቤቱ ገባና፤
“አምላኬ ሆይ! አባቴን አቆይልኝ! የህዝብን ፍቅርም እንዳገኝ እርዳኝ” ሲል ፀለየ!!
*      *     *
ያለ አበው ምክር፣ ያለ ህዝብ ድጋፍ የትም አይደረስም! የህዝብ ምሬት መጠራቀም የለበትም! “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚለውን ብሂል አለመርሳት ተገቢ ነው፡፡ በትንሽ በትልቁ አለመረበሽ፣ አለመሸበር ትልቅ ጥበብ ነው! ትዕግስት ማጣትና ፈጥኖ ወደ እርምጃ መሄድ አደገኛ ነው፡፡ “ችኩል ጅብ ቀንድ ይነክሳል” የሚለውን ተረት ከልብ ማስተዋል ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ማስፈራራት ቅኝቱን የለወጠ እለት፣ ለአንባ-ገነንነት ቦይ ይቀዳል። ዲሞክራሲን ያቀጭጫል፡፡ “ስለ ዲሞክራሲ ማዳነቅና ህዝቡን ፀጥ ማሰኘት ቧልታዊ ድራማ ነው፡፡ ስለ ሰብአዊነት እያወሩ ህዝቡን ግን መቃወም ሐሳዊነት ነው” ይለናል፤ ፖል ፍራየሬ የተባለው የፖለቲካ ፀሐፊ፡፡ የቀን ትጋትም ሆነ የሌሊት መልካም እንቅልፍ የሚገኘው አገር ሰላም ስትሆን ነው፡፡ አገርን ሰላም ለማግኘት ህዝባዊ ተሳትፎን ማጎልበት ግድ ነው፡፡ የአበው ምክርና የአዲስ ትውልድ ቅንጅትና ውህደት ከሌላ ወደመጣንበት እንመለስና፣ የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አታካች ሂደት መጫወቻ እንሆናለን! “መካር የሌላው ንጉሥ” የምንለውን ያህል፣ የተሳሳተ መካሪ እንደሚያቀልጠንም እናስብ! እርቅና መግባባት ከብዙ ጣጣ ያድናል፡፡ ሆድ ለሆድ ሳንቻቻል፣ አብረን እየተራመድን ነው ብንል፣ የለበጣ መንገድ ይሆናል፡፡ መንገዱ የአገራችንን ችግር ያህል ረጅም ነው!
አገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሙያዊ ብቃትን ትሻለች፡፡ ህንፃና መንገድ ብንሰራም የሰው ኃይላችን ያልሰለጠነ ከሆነ  ዋጋ የለንም፡፡ የሰው ኃይላችን አደረጃጀት የተሳካ እንዲሆን ለሰው ብቃት የምንሰጠው ክብር እጅግ ወሳኝ ነው! ቀና ውድድር እንጂ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ መቀናናት ውስጥ ከገባን፤ ውለን አድረን መናናቅና መደፋፈ ርጋ እንደርሳለን፡፡ መከቧርን፣ አለቃን ማክበርን፣ አመራርን ማክበርን፣ ሥርዓትን ማክበርን፤ አዋቂን ማክበርን፣ ለሚበልጡን ቅድሚያ መስጠትን እንተውና ትልቅና ትንሽ ይጠፋል፡፡ ሥርዓተ-አልበኝነት ይስፋፋል፡፡ የላቀውን ማኮሰስ፣ በስሜት ብቻ መነዳት፣ በጊዜያዊ ሞቅ ሞቅ ብቻ ዘራፍ ማለት ይከተላል፡፡ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ይኼው ነው፡፡




  “--አንድ የአሜሪካ ኩባንያ አንድ ጥቅም ለማግኘት፣ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ጉቦ በሚሰጥበት ጊዜ በአሜሪካ
በወንጀል ሲከሰስ፣ አትዮጵያዊው ባለሥልጣን በኢትዮጵያም ውስጥ ይጋለጣል ማለት ነው፡፡ የተቀበለውም ገንዘብ
አሜሪካ ከዘለቀና በኢትዮጵያ በኩል ጠያቂ ካለ፣ ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ይችላል፡፡---”
                 በዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም

     ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉቦ ወይም ሥልጣንን ተገን አደርጎ፣ አገርና ሕዝብን መበዝበዝ፣ በግዕዝ ቋንቋ ተሽሞንሙኖ፣ “ሙስና” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህ በስልጣን መባለግና የሕዝብ ወይም የግለሰብ ንብረት መዝረፍ - “ሙስና”፣ ትርጉም፣ ከእንግሊዝኛ አቻው- corruption ጋር ጨርሶ አይመጣጠንም። ምናልባት “ሙስና” የሚለውን ቃል እንደ እንግሊዝኛው በሚሰቀጥጥና ከመነሻው አጸያፊ በሆነ የአማርኛ ቃል መለወጥ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡  
በእንግሊዝኛ አንድ ሰው “ኮረፕት” (corrupt) ሆነ ሲባል፣ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ዘረፈ ከማለት በተጨማሪ በሰበሰ፣ ተበላሸ፣ ቆሸሸ የሚል አንድምታንም ይጨምራል፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው አገራዊ ብሂል የሚያመለክተው ጉቦ ባህል ሆኖ መኖሩን ቢሆንም  መጠኑ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከአንድ ሽንጥና ከጠርሙስ አረቄ ያልበለጠ ነበር፡፡ ዶላር ወይም ዩሮ በሚሊዮኖች ዘርፎ በተለያዩ አገራት ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን፣ የተንጣለሉ ቪላዎችን መግዛት፣ የውጭ ባንኮችን በማጠራቀሚያ ሂሳብ ማጣበብ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ተጸንሶ ተወልዶ፣ ለአካለ መጠን የደረሰ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡
የመንግሥት ባለስልጣናትም ሆኑ የሚተባበሩአቸው ነጋዴዎችና ደላሎች ንቅዘት፣ ከሥርዓቱ ጋር ቁርኝት እንዳለው አሌ አይባልም። ስለዚህም ሙሰኝነት ሊከስም የሚችለው ሥርዓቱ ተለውጦ፣ መንግስት ለህዝብ ተጠሪ ሆኖ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡  
በአንድ ፓርቲ አምባገነን ሥርዓት፣ በባለስልጣናቱ መሃከል የጋራ አስተሳሰብ፣ የጋራ እምነትና የጋራ ዓላማ ስላለ፣ አንዱ ሙሰኛ ባለስልጣን ሌላውን ባለስልጣን አያጋልጠውም፡፡ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግን የሕግ የበላይነት፣ የንግግርና የጽሁፍ ነፃነት በተረጋገጠበት ሁኔታ ሙስና ዋነኛ ችግር አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ፓርቲዎች ባለስልጣናት መካከል የሥልጣን ፉክክር ስለሚኖር፣ አንዱ ባለሥልጣን ሌላውን ሊያጋልጠውና በምርጫ እንዲወገድ ወይም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆን ጥረት ያደርጋል፡፡ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሥርዓት፣ ሕግ አውጪው የፓርቲው ተጠሪ ስለሆነ፣ ሙስናን ለመከላከል የሚያወጣው ሕግ ጥርስ ያለውና ጠበቅ ያለ አይሆንም፡፡ የሕጉ አፈጻጸም ላይ ደግሞ በቅርቡ በአገራችን እንደታየው፣ አንዳንድ አይነኬዎችን ዘልሎ፣ ትኩረቱ በትንንሽ ባለሥልጣናት ላይ ይሆናል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ጎሰኝነት ከማንኛውም የፖሊስ ግብዐት በልጦ ባለበት  ሁኔታ ሙሰኝነት ባይስፋፋ ይገርም ነበር፡፡
በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ውስጥ በምትገኘው አገራችን፣ የሥርዓት ለውጥ ሳይኖር፣ ጥቂት ሙሰኞችን (ያውም ዋና ዋናዎቹ ሳይሆኑ) በማሰር ሙሰኝነትን አጠፋለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ አንድ የጠገበ ሙሰኛ ሲታሰር ሌላ የራበው ብቅ ይላል። በድሮ ጊዜ ታላቋ ብሪታንያ፣ ኪስ አውላቂዎችን ሕዝብ በተሰበሰበበት በስቅላት ትቀጣ ነበር ይባላል። ታዲያ ኪስ አውላቂዎቹ ሲሰቀሉ፣ ሌሎች ኪስ አውላቂዎች ከተሰበሰበው ሕዝብ ኪስ ይመነትፉ ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው እውነተኛና ዘላቂ የሥርዓት ለውጥ በማድረግ እንጂ ጥቂት ግለሰቦችን  በመቅጣት ብቻ  ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል  ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ በአብዛኛው ልንተነትን የምንሻው፣ በአገር ውስጥ የሚፈጸመውንና በዚሁ በአገራችን ፎቅ የሚሠራበትን ወይም ፋብሪካ የሚቋቋምበትን ወይም የተንጣለለ ቪላ የሚሠራበትን ሙስና አይደለም፡፡ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ ግለሰቦች፣ ከግለሰብም ይሁን ከአገር ገንዘብ እየዘረፉ፣ ወደ ውጭ አገር የሚያሸሹትን፣ በእንግሊዝኛው Indigenous spoliation በሚባለው ላይ ሲሆን አገራትን ከእንዲህ ዓይነት የዘረፋ ወንጀል ለመከላከል የተደነገጉ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡  
በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድርጅት እንደገለጸው፤ ከአገር በሕገ ወጥ መንገድ የአገር ሃብት ተዘርፎ፣ ወደ ውጭ ከሚጓዝባቸው አሥር የአፍሪካ አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተአማኒነት ያተረፈው እውቁ ፎርብስ መጋዚን (Forbes magazine) ከኢትዮጵያ በ20 ዓመታት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የወጣው ገንዘብ መጠን፣ ሰላሳ ቢሊዮን (30,000,000,000) ዶላር መሆኑን ዘግቧል፡፡ ይህ ገንዘብ ለመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ በረሃብ የሚሰቃዩ ስምንት ሚሊዮኖችንም ጨምሮ ቢከፋፈል፣ እያንዳንዱ 7200 ብር ይደርሰዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች፣ ይህ ከአገር የወጣው ገንዘብ ውሀ በልቶታል፤ ወደ አገር የሚመለስበት ምንም መንገድ የለም፡፡ ገንዘቡ ያለበት አገር ሉዐላዊ እንደመሆኑ መጠን ገንዘቡ ወደ አገር እንዲመለስ የማድረግ ግዴታ የለበትም ይላሉ፡፡ ሆኖም ዛሬ የዓለም ሕግ በእጅጉ ተለውጦአል፣ በሉዐላዊነት ስም አንድ መንግሥት በአገሩም ውስጥ ቢሆን ያሻውን ማድረግ አይችልም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ሂትለር ብዙ ጀርመኖችን እየገደለ በነበረበት ወቅት ቸርቺል፤ “ግድያውን ማቆም አለበት” ሲል የሰማው ሂትለር፤ “ግማሹን የጀርመን ሕዝብ  ብገድል ቸርቺል ምን አገባው፣ ሉዐላዊ አገር መሆናችንን ዘነጋ ወይ” ሲል መለሰ። ዛሬ በሉዐላዊነት ስም ሕዝብን መጨፍጨፍ፣ የአንድን አገር ሕዝብ ገንዘብ ዘርፎ በዱባይ፣ በካናዳ፣ በአሜሪካ ወዘተ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ማነጽ፣ በሚስት ወይንም በልጅ ስም በተከፈተ ሂሳብ የሌላ አገር ባንክ አጣብቦ፣ ሕዝብን ለችጋር መዳረግ፣ የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በቸልታ የሚያየው ነገር አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በዴሴምበር 10 ቀን 2003 ዓ.ም ያጸደቀችው የተባበሩት መንግሥታት የጸረ ሙስና ስምምነት፤ ሙስና የአንድ አገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብን የሚመለከት ጉዳይ መሆኑን ደንግጓል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ንብረታቸውን በአንድ ማዕከል ውስጥ እንዲያስመዘግቡ ያሳስባል፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕግ አክብረው፣ ንብረታቸውን እንዳላስመዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ ይሄው የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት፣ በአንቀጽ 44፣ አንድ ባለሥልጣን ወይንም ግለሰብ በጉቦም ይሁን በሌላ መልክ ከአገሩ ገንዘብ ዘርፎ አገሩን ቢለቅ፣ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው፣ ዘራፊው እስከዘረፈው ገንዘብ ወደ አገሩ ተመልሶ፣ ለፍርድ ይቀርብ ዘንድ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት እንዲተባበሩ ተደንግጓል፡፡
ብዙ አገራት በተለምዶ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ፣ ኩባንያዎቻቸው በሌላ አገራት ገንዘባቸውን በሥራ ላይ በሚያውሉበት ጊዜ (invest) ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፣ ለአገራቱ ባለሥልጣናት ጉቦ መስጠት የተከለከለ ሲሆን ጉቦ በሰጡ ጊዜ ደግሞ በየአገራቸው በወንጀል እንደሚጠየቁ ሕጎቻቸው ይደነግጋሉ፡፡ የእነዚህ ሕግጋት ዋናው ዓላማ፣ በኩባንያዎቹ መሃከል ነፃ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ ቢሆንም ክሱ ግን ጉቦኞችን ማጋለጡ አይቀርም። አንድ የአሜሪካ ኩባንያ አንድ ጥቅም ለማግኘት ለአንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ጉቦ በሚሰጥበት ጊዜ በአሜሪካ በወንጀል ሲከሰስ፣ አትዮጵያዊው ባለሥልጣን በኢትዮጵያም ውስጥ ይጋለጣል ማለት ነው። የተቀበለውም ገንዘብ አሜሪካ ከዘለቀና በኢትዮጵያ በኩል ጠያቂ ካለ፣ ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕግ የደነገጉት በአብዛኛው ዴሞክራሲያዊ አገሮች ሲሆኑ ሌሎቹ እንዲያውም ገንዘብ ማሸሺያና መደበቂያ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል ቻይና እንዲህ ዓይነት ሕግ የላትም። ስለዚህ የቻይና ኩባንያዎች  ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ጉቦ እንዳሻቸው ሊሰጡ ይችላሉ፤ ከዚያም አልፎ ለባለሥልጣናት የሰጡት ጉቦ እንደ ወጪ ተቆጥሮላቸው፣ ለመንግሥት ከሚከፍሉት ቀረጥ ሳይቀነስላቸው ሁሉ አይቀርም፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት ሕግጋት በተጨማሪ የሕዝብን ገንዘብ ዘርፎ ወደ ሌላ አገር ማሻገርና ሕዝብን ችግር ውስጥ መጣል ከሁሉም የከፋ የሙስና ዓይነት ሲሆን ይህም ወንጀል በሰብአዊ ፍጡር ላይ ከሚሠሩ ወንጀሎች (crime against humanity) አንዱ ሆኖአል፡፡ በተለይ ስምምነቶችና ድንጋጌዎች እንደ ሰብአዊ መብት ጥሰትም ተወስደዋል፡፡
ሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት፣ የአንድን ዘር በከፊል ወይም በሙሉ ማጥፋት (genocide) በሰብአዊነት ላይ የሚሠራ ወንጀል (crime against humanity) የጦር ወንጀል (war crimes) ለመዳኘት ሥልጣን አለው፡፡ በሰብአዊነት ላይ የሚሠራ ወንጀል፣ ዓይነቱ ብዙ ሲሆን በየጊዜው የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እዚህ ውስጥ መካተታቸው አይቀርም። አሸባሪነትና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘብ ወደ ሌላ አገር ማሸጋገር (indigenous spoliation) በሰብአዊነት ላይ የሚሠራ ወንጀል ውስጥ እንደሚካተቱ ጥርጥር የለውም፡፡ በነገራችን ላይ በዓለም ዙርያ የሄጉ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን ሥልጣን አንቀበልም ካሉት አምባገነን መንግሥታት ጋር ኢትዮጵያ የተሰለፈች ሲሆን ፍርድ ቤቱን አምርረው ከሚያወግዙ ጥቂት መንግሥታት መካከል ኢሕአዴግ አንዱ ነው፡፡
በሙስና ከአገር ተዘርፎ የወጣ ገንዘብ መንግሥት በሚመሠረትበት ጊዜ የተዘረፈውን ገንዘብ ወደ አገር ማስመለስ ይቻል ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ተዘርፎ የወጣ ገንዘብን ክስ ከፍቶ ለማስመለስ እንዲቻል፣ ክሱ ለረጅም ጊዜ በይርጋ እንዲታገድ የተባበሩት መንግሥታት የጸረ ሙስና ስምምነት ይደነግጋል። እዚህ ላይ ግን አንድ ችግር አለ፡፡ የተዘረፈው ገንዘብ የተቀመጠው ለሰብአዊ መብት ደንታ በሌላቸው በሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮችና በቻይና ከሆነ ማስመለሱ እጅግ ሊከብድ ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም የተዘረፈ የሕዝብ ገንዘብን በማስመለስ በምሳሌነት ናይጄርያና ጋቦንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የናይጄርያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሳኒ ኦባቻ፣ ከዘረፈው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከፊሉ በናይጄሪያ መንግሥት ጠያቂነት ለናይጄሪያ ተመልሶአል። እንዲሁም የቀድሞ የጋቦን ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ፣ፓሪስ ውስጥ የገዛቸው ምርጥ ምርጥ ቪላዎች ተሸጠው ገንዘቡ ወደ አገሩ ተመልሶአል፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው ዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

   · መንግሥት እንደ ጠላት፣ ጡረታዬን መከልከሉ ያሳዝነኛል
                      · የሶማሊያን ወራሪ ሃይል ድባቅ የመቱ ጀግኖች ታሪክ ተቀብሯል
                      · ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሚሰጠው ትርጉም ተዛብቷል
                      · ለሶማሊያ የምናደርገው ድጋፍና እርዳታ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል

     የዛሬ 40 ዓመት የዚያድ ባሬ አገር ሶማሊያ፤ እንደዛሬው የፀና መንግስት የሌላት፣ ደካማ ጎረቤታችን አልነበረችም። ከጦቢያ እገዛና ድጋፍ የምትሻ ምስኪን አገርም ፈፅሞ አልነበረችም፡፡ ይልቁንስ ኮሙኒስቷ ሶቭየት ህብረት እስከ አፍንጫዋ ድረስ በዘመኑ የጦር መሳሪያ ያስታጠቀቻት የፈረጠመች አገር ነበረች። የመሪዎቿም ዓላማ በዙሪያዋ ያሉትን ጨፍልቃ “ታላቂቱን ሶማሊያ” መፍጠር ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት ዚያድ ባሬ መሪነትና አዋጊነት ኢትዮጵያን በኃይል ለመውረር የተነሳችው፡፡
በአዲስ የመንግስት ምስረታ ሽግግር ላይ ለነበረችው ኢትዮጵያ ወቅቱ ፈታኝና አስቸጋሪ ነበር፡፡
ቢሆንም የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት  ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፤ ህዝቡ የአገሩን ዳርድንበርና ሉአላዊነት ከወራሪዋ ሶማሊያ እንዲከላከል ላደረጉት የእናት አገር ጥሪ ያገኙት ምላሽ፤ ፈጣንና በአገር ፍቅር ወኔ የተሞላ ነበር ይላሉ - በወቅቱ በጦርነቱ ላይ ከተሳተፉት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ የሆኑት መቶ አለቃ በቀለ በላይ፡፡ የያኔው ጎረምሳ፣ ለእናት አገር ጥሪው ምላሽ ሲሰጡ፣ ገና የ19 ዓመት ወጣት ነበሩ። ከ3 መቶ ሺ ሚሊሻዎች አንዱ የነበሩት መቶ አለቃ በቀለ፣ የሳቸው ክፍለ ጦር ተመርጦ በአየር ወለድ መሰልጠኑን ያወሳሉ፡፡ በዕብሪት አብጦ ኢትዮጵያን በኃይል የወረራትን የዚያድ ባሬ ሰራዊት፤ መክቶና ድባቅ መትቶ ለመመለስ፣ አያሌ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አልቀዋል፡፡
የዕድል ጉዳይ ሆኖ፤ በህይወት ተረፉ እንጂ መቶ አለቃ በቀለም ከሞት በመለስ ያልቀመሱት አበሳና ፍዳ የለም - ነፃነቷ የተጠበቀች አንዲት ኢትዮጵያን ለማቆየት፡፡ መቶ አለቃ በቀለ፣ ከሶማሊያ ጋር በነበረው አሰቃቂ ፍልሚያ፣ በሰሩት የጦርነት ጀብዱ፣ የአገሪቱን ብሔራዊ የጦር ሜዳሊያ ኒሻን፣ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እጅ ተሸልመዋል፡፡ በአገር ተከብረዋል ተወድሰዋልም፡፡
“የጀግናው ወሮታ” በሚል ርዕስ የህይወት ታሪካቸውን የሚዘክር ባዮግራፊ የተፃፈላቸው መቶ አለቃ በቀለ በጀግንነታቸው አገርና ትውልድ እንዳከበሯቸው ተገቢውን ወሮታ ከአገርም ሆነ ከመንግሥስት አግኝተው ለመኖር አለመታደላቸውን ይናገራሉ፡፡ የደርግ መንግስት ወድቆ፣ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ፣ ሰራዊቱ በጅምላ “የደርግ ሰራዊት” በሚል ተፈርጆ፣ ለእስር መዳረጉን በቁጭት ያስታውሳሉ፡፡ አገርንና ህዝብን ይቅርታ
ጠይቁ ተብለውም፣ “ምን በድዬ፤ ህዝብና አገር ሙትልኝ ሲሉኝ በመሞቴ?!” ብለው አሻፈረኝ በማለታቸው፣ ሌሎች ይቅርታ ጠይቀው ከእስር ሲለቀቁ፣ እሳቸው ከ2 ዓመት በላይ ታስረው መፈታታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በደሉ ግን በእስር ብቻ አላበቃም የሚሉት የጦር ሜዳው ጀግና፤ ለፈፀምኩት ጀብዱ ወሮታዬ እንደ ጠላት፣ ጡረታ መከልከልና ታሪካችንን ትውልድ እንዳያውቀው መደበቅና መቅበር ሆኗል ይላሉ፡፡ እኚህ የጦቢያ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ በአዛውንት ዕድሜያቸው፣ ጡረታም መጠለያም ታሪክም… ጭንር ተነፍገው፣ ህይወታቸውን በሰጧት አገር፣ እንደ አልባሌ ተጥለውና ተረስተው እየኖሩ መሆናቸውን በቁጭት ይናገራሉ፡፡ ሌላው ሁሉ ሳያንስ፣ ለሳቸውና መሰሎቻቸው ማስታወሻ ተብሎ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በር ላይ የተሰራው “ድላችን ሀውልት”፤ ስያሜው ተቀይሮ “የኢትዮ ኩባ” ወዳጅነት ሃውልት”  ሲባል መስማቴ ከምንም በላይ ያሳዝነኛል ብለዋል፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ከፈፀመች እነሆ 40 ዓመት ሞላት፡፡ እኚህ ጀግናስ አሁን የት ነው ያሉት? የጀግንነት ውሎአቸውን…፣ ከአገሪቱ የተከፈላቸውን ወሮታ፣… የዛሬውን ህይወታቸውን … በሀዘንና በቁጭት ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  እንዲህ አውግተውታል፡-  

        ወደ ውትድርና መቼና እንዴት ገቡ?
በ1967 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ማጋጠሙን ተከትሎ፣ በተደረገ ወታደራዊ ምልመላ አማካኝነት ነው፡፡ በወቅቱ ሶማሊያን በመሳሪያ ያስታጠቀው የሶሻሊስት ሶቪየት ህብረት ሲሆን ኢትዮጵያ  ደግሞ ገና በለውጥ አብዮት ውስጥ ነበረች፡፡ ሶማሊያ ለረጅም ዘመን ወታደራዊ ኃይሏን ስታፈረጥም ነበር የቆየችው፤ በዚህም የተነሳ በመካከላችን ከፍተኛ የኃይል አለመመጣጠን ነበረ፡፡ በሶማሊያ ወረራ ሳቢያ ነው በ1969 ለውትድርና ከተለመለመሉ ወጣቶች አንዱ የሆንኩት፡፡ በወቅቱ እድሜዬ 19 አመት ነበር፡፡
ያኔ የሀገራቱ ወታደራዊ አወቃቀር ምን መልክና ቅርፅ ነበረው?
 ሰራዊቱ አራት ክፍለ ጦሮች ብቻ ነበሩት። የታጠቀው መሳሪያም ሶማሊያ ከነበራት አንፃር በእጅጉ የሚራራቅ ነው፡፡ 1ኛ ክፍለ ጦር በወቅቱ የአዲስ አበባ ዙሪያን ሲጠብቅ፣ 2ኛ ክፍለ ጦር ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያን፣ 3ኛ ክፍለ ጦር ሀረርጌን እንዲሁም 4ኛ ክፍለ ጦር የሶማሌ ጠረፍን ነበር የሚጠብቀው፡፡ ነገር ግን የዚህ ክፍለ ጦር ኃይል በእጅጉ አነስተኛ በመሆኑ ነበር የዚያድ ባሬ ጦር በቀላሉ አውድሞት ኢትዮጵያን የወረረው። በወቅቱም ጠንካራ መከላከል ያላጋጠመውና የሶማሊያ ጦር በአጭር ጊዜ የኦጋዴን ክልልን አቋርጦ እስከ ደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል የዘለቀው በዚያ የተነሳ ነው፡፡
በወቅቱ እንደገልፅኩት፤ ኢትዮጵያ በመንግስት ለውጥ ላይ በመሆኗ፣ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ “ተነስ ታጠቅ ሀገርህ በጠላት ተደፍራለች” የሚል ጥሪ ባደረጉበት ሰዓት፣ 3 መቶ ሺህ ሚሊሻ ነው በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ፣ የመከላከል እርምጃ የተወሰደው። ይህ ምልምል ኃይል ነው የሶማሊያ ወራሪን ከሃረርና ድሬደዋ እንዳያልፍ የተከላከለው፡፡
እርስዎ በየትኛው የጦር ክፍል ነው የተመደቡት?
እኛን ሲያሰለጥን የነበረው የኢትዮጵያ አየር ወለድ ነው፡፡ የተፈለግነውም ከአየር ወለዱ በተሻለ ከጠላት በስተጀርባ ተገኝተን የማጥቃት እርምጃ እንድንወስድ ነበር፡፡ ግን ለዚህ ግዳጅ የተፈለገውን ያህል ስልጠና ባለማግኘታችን ወደ መደበኛ ጦር ነው የገባነው፡፡ ስልጠናችንን አቋርጠን፣ ጥቅምት 1970 ነው፣ ወደ ጦር ግንባር የዘመትነው፡፡
የመጀመሪያ የጦር ሜዳ ተጋድሏችሁ ምን ይመስል ነበር?
የሶማሊያ ወራሪዎች የሃረር ሬድዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር፣ ከሀረር ከተማ 2 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የፈዲስ ተረተርና የሀረር ቢራ የሚያመርተው፣ ሶፊ የተሰየመበት የሶፊ ተራራ ላይ ሰፍሮ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ነው፣ እኛ የመጀመሪያ የጦር ሜዳ ግዳጅ የተወጣነው፡፡
በወቅቱ ሀረር ከተማን ወራሪው ኃይል ያለማቋረጥ ይደበድብ ነበር፡፡ የሀረር ህዝብ እኛ ስንደርስ ቤቱ አያድርም ነበር፡፡ ምሽግ ቆፍሮ በየምሽጉ ነበር የሚያድረው፡፡ ያገኘውን መሳሪያ ማለትም ቆንጨራ፣ ገጀራ በመያዝ ነበር ጠላትን ለመፋለም ይጠባበቅ የነበረው፡፡ ሁኔታው በእጅጉ ያሳዝን ነበር፡፡ ጠላት ከተማውን ያለ ርህራሄ በእሳት እያቃጠለ፣ ህዝቡን ያስጨንቅ ነበር፡፡
ሀረርን ከዚህ ጥቃት እንዴት ነው የታደጋችሁት?
 እኛ ማረፊያ አጥተን ያረፍነው የሃረር ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው ቦታ ሁሉ በጠላት አረሮች ይደበደብ ነበር፡፡ እዚያ ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ሆነን፣ ወደ ሶፊ ተራራ ስንመለከት፣ የጠላት አስተኳሽ፣ ተራራው አናት ላይ ቆሞ የተኩስ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ያለማቋረጥ ይጮሃል፤ “ልክ ነህ ዝቅ አድርግ … ከፍ አድርግ” እያለ ለተኳሾች ኢላማ ሲያመቻች በመገናኛ ሬዲዮ ይሰማል፡፡ ያለማቋረጥ በሶማሊያኛ ቋንቋ “ኦርያ ማ! መቀሌ ሰን! … ኦርያ ማ! መቀሌ ሰን!” እያለ አስተኳሹ ይጮሃል፡፡
በወቅቱ ሻለቃ፣ በኋላ ሌ/ኮሎኔል የሆኑት አዛዣችን ወኔ ቀስቃሽ ትዕዛዝ ነበር የሰጡን፡፡ “ይሄን አስተኳሽ … ሃረርን እያቃጠለ ያለን ጠላት … ከእነነፍሱ ይዛችሁልኝ ስትመጡ ብቻ ነው በእውነት የፓራ ኮማንዶ ሰልጣኝ መሆናችሁ የሚታወቀው … ለሀገራችሁ ያላችሁ ፍቅርም የሚለካው በዚህ ነው” አሉን፡፡ የጦራችን አባላት 140 ብቻ ነበርን። ትዝ ይለኛል፤ ሰዓቱ የጀንበር መጥለቂያ አካባቢ ነው፡፡ ወደ ተራራው ስንጠጋ፣ በሚደንቅ ሁኔታ ያ አስተኳሽ፣ በጠላት አንድ ሻለቃ ጦር ተከብቦ ነው የሚያስተኩሰው፡፡ እኛ እንግዲህ እዚህ የጠላት ጦር መሃል ነው የገባነው፡፡ ፍፁም ተመጣጣኝ አልነበረም ጦራችን፡፡ እነሱ ከ600 በላይ ናቸው፤ እኛ ደግሞ 140 ነን፡፡ በዚያ ላይ እኛ የነፍስ ወከፍ መሳያ ነው የያዝነው፤ እነሱ ዘመናዊ መሳሪያ ነው የታጠቁት። ይሄ ታሪክ ሲነገር ለብዙዎች የማይታመን ተረት ተረት ነው የሚመስለው፡፡ እዚህ ከ600 በላይ ጦር መሃል ገብተን ስንታኮስ፣ ጥይት አልቆብን በሳንጃ ነበር የተሞሻለቅነው፡፡ ውጊያችንን ሙሉ ለሙሉ በሳንጃ ነበር ያደረግነው፡፡ የኛ ኢላማ አስተኳሹ ነው፤ በፅናት ነበር የተዋጋነው፡፡ ያንን አስተኳሽ ከእነ መገናኛ ሬድዮው ይዘን፣ በቃላችን መሰረት ለአለቃችን አስረከብን፡፡ የሶማሌ ጦርም መፍረክረክ ጀመረ፡፡ ተራራውንም አስለቅቀን፣ ሃረርን ከመቃጠል ታደግናት፡፡ በጦነቱ ከተሳተፍነው 140 ጓዶች፣ 60ዎቹ ሲሞቱ፣ 80ዎቹ ነን በህይወት የተረፍነውና ግማሹም ቁስለኛ የሆነው፡፡
የሶማሊያ ወራሪ ኃይልን ድል ለማድረግ የተደረገው ፍልሚያ በበቂ ሁኔታ ተነግሮለታል፤ ተዘግቧል  ይላሉ?
በፍፁም፡፡ ታሪኩ አለመነገሩ በጣም ይቆጫል። በተለይ ያንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች፣ ታሪክ መቀበሩ ያሳዝናል ያስቆጫል፡፡ ወታደራዊ ጥበብ ራሱ ሳይንስ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ስለ እኛ መውደቅና መሸነፍ ነው በስፋት የሚነገረው፡፡ ለሀገር ዳር ድንበር ያበረከትነው አስተዋፅኦ መና ቀርቶ፣ በትውልዱ እንዳይታወቅ መደረጉ በእጅጉ ያስቆጫል፡፡
ከደርግ ጋር ተጨፍልቀን፣ እኛ በእናት ሀገር ፍቅር ልክፍት፣ ለዳር ድንበሯ ምትክ የሌለው መስዋዕትነት የከፈልን ሰዎች፣ ምንም እንዳልሰራን ተደርጎ በየቦታው መሳለቂያ ሆነናል፡፡ ይሄ አሳዛኝ የታሪካችን ምዕራፍ ነው፡፡ አለመታደል ነው፡፡ የዚያን ሰራዊት አወዳደቅና አፈራረስ ምክንያቶች፣ ነገ ከነገ ወዲያ ታሪክ የሚፋረደው ጉዳይ ነው፡፡ እንደ‘ኔ ግን በወቅቱ የደርግ ሰራዊት ተሸንፎ አይደለም የወደቀው፡፡ የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንደሚባለው፣ ሰራዊቱ ሳይሆን ስርአቱ ነው ተሸንፎ ሰራዊቱም አብሮ የተጨፈለቀው እንጂ ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ልክፍት የነበረው ሰራዊት ነበር፡፡
በመሰረቱ በኛ ሀገር የሰራዊት ሚና አረዳድ ችግር እስካሁንም አለ፡፡ ኢህአዴግ እኛን የኢትዮጵያ ሰራዊት ብሎ ሊቀበለን አልፈለገም፤ “የደርግ ሰራዊት” ነበር የሚለን፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በብዙዎች “የኢህአዴግ ሰራዊት” እየተባለ ይጠራል፡፡ ይሄ አንደኛው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚሰጠው ትርጉም ከጅምሩ መዛባቱንና አሁንም ድረስ መቀጠሉን አመላካች ነው። አንዱ መንግስት ሲፈርስ ሰራዊቱ መፍረሱ አሳዛኝ ነው። ንጉሱ በቁጭት ያቋቋሙት ባህር ኃይል እንዲፈርስ መደረጉ አሳዛኙ የታሪካችን አካል ነው፡፡
ለዚህ ተጋድሏችሁ የታሪክ ማስታወሻዎ የላችሁም?
ነበረን፤ ግን እንደ አለመታደል ሆኖ ዛሬ ስሙ ተቀይሮ፣ ታሪካችን እንዳይነሳ ሆኗል፡፡
ብዙዎች ላያውቁት ይችላሉ፡፡ የትኛው ነው ማስታወሻችሁ?
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ሃውልት “የድላችን ሃውልት” ነበር መጠሪያው፡፡ ሃውልቱ ላይ የተቀመጠው ምልክት፣ እኔና መሰሎቼ በጦር ሜዳ ለፈፀምነው ጀብዱ የተሰጠን ኒሻን አርማ ነው፡፡ ይሄን ብዙዎች አያውቁትም፡፡ አሁን “ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ሃውልት” ሲባል ስሰማ አዝናለሁ፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ታሪካችን፣ በትውልድ እንዳይዘከር ለማድረግ የታለመ ነው፡፡
ሃውልቱ ለምን ተግባር እንደቆመ የምታውቁ ሰዎች “ስያሜው ሊቀየር አይገባም” የሚል ተቃውሞ ለምን አላቀረባችሁም?
ለማን ነው የምናቀርበው? … የሚሰማ ሲኖር እኮ ነው። አሁንም ቢሆን ይሄ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እኛ እንዳንጠራበት መደረጉ ያሳዝናል ያሳፍራል፡፡ የነበረን ታሪክ እንዳልነበረ ለማድረግ ጥረት መደረጉ አሳዛኝ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኩባዎች ከኛ ጋር ተዋግተዋል፡፡ ግን መታሰቢያቸው በሌላ ሊሆን ይችላል እንጂ ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ የሀገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር የወደቁትን ጀግኖች መታሰቢያ ማሳጣት፣ በእውነት የታሪክም ተወቃሽ ያደርጋል፡፡ እኛ እናውቀዋለን፤ አዲሱ ትውልድ ግን የዚህን ሃውልት ምንነት እንዲያውቀው መንገድ አልተከፈተለትም። እኔ ደርግ ጥሩ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ግን ሰራዊቱ ለሀገር ዳር ድንበር የከፈለው መስዋዕትነት መና መቅረት የለበትም፡፡
መስዋዕትነታችን መና ቀርቷል ብለው ይቆጫሉ?
ለሀገር ዳር ድንበር የከፈልነው መስዋዕትነታችን አስታዋሽ ማጣቱ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ‘ኮ በ1983 ደርግ ሲወድቅ ታስሬያለሁ፡፡ ወሮታችን የተከፈለን በእስር ነው፡፡ በጦላይ ወታደር ማሰልጠኛ ውስጥ ለ2 ዓመት ተኩል ታስሬያለሁ፡፡ በወቅቱ ይቅርታ ጠይቁና ውጡም ተብለን ነበር፡፡ “ጥፋተኞች ነን፤ ሀገርንና የኢትዮጵያን ህዝብ በድለናል” ብላችሁ ይቅርታ ጠይቁ ተብለን ነበር፡፡ የጠየቁ አሉ፡፡ እኔ ግን፤ “ሀገሪቱንና ህዝቡን በድለሃል ነው እንዴ የምትሉኝ፤ … በፍፁም አልበደልኩም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያን ክብር! ሉአላዊነት! ነፃነትና ዳር-ድንበሯን ለመጠበቅ ስል፣ ከሞት በመለስ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍያለሁ” ነበር ያልኳቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ “ሂድና ሙትልኝ” ሲል ሞትኩለት እንጂ ምን የበደልኩት አለ? ይሄን ይቅርታ ካልጠየቅ ተብዬ በአቋሜ በመፅናቴ፣ 2 ዓመት ተኩል ታስሬ ሲሰለቻቸው ለቀውኛል፡፡
አሁን ሶማሊያ ከረጅም የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ መንግስት እየመሰረተች ነው፡፡ ይሄን ሲያዩ ምን ይሰማዎታል?
ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን የወረረችው፡፡ በ1956 ዓ.ም ጀነራል አማን አምዶም የቀለበሱት ወረራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በ1953 ዓ.ም የወረራ ሙከራ አድርገው ነበር፤ እሱም ከሽፏል። ሶማሊያ ነፃነቷን ከቅኝ ገዥዎቿ ከተቀዳጀች ጀምሮ ለኢትዮጵያ የተኛችበት ጊዜ የለም፡፡ ዛሬም ድረስ በሰንደቅ አላማዋ ላይ ባለ 5 ኮከብ አርማ ነው የምትጠቀመው፡፡ ዛሬም ድረስ ይሄ ህልሟ የተዳፈነ እንጂ ፈፅሞ የተቀበረ አይመስለኝም። የ5ቱ ኮከብ አላማ፡- ከሀገሪቱ ዜጎች ጭንቅላት እስካልወጣ ድረስ ለዳር ድንበራችን ትተኛለች ብዬ አላምንም፡፡ ይሄ ድጋፍና እርዳታችንም ውሎ አድሮ፣ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል የሚል ስጋትም አለኝ፡፡
የሀገሪቱ የጦር ሜዳይ ተሸላሚ ነዎት….
አዎ! የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀግና፣ የ2ኛ ደረጃ ሜዳይ ተሸላሚ ነኝ፡፡ በ1977 ነው ከደርጉ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም እጅ የተሸለምኩት፡፡ ይሄን እድል የሚያገኙት ደግሞ ጥቂቶች፣ የተለየ የጦር ሜዳ ጀብዱ የፈፀሙ ብቻ ናቸው፡፡
እርስዎን ለዚያ ያበቃዎት የተለየ የጦር ሜዳ ጀብዱ ምንድን ነው?
በእርግጥ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ በአንድ የጦር ሜዳ ውሎ ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ብዙ ውሎዎች ተደማምረው የሚገኝ ነው፡፡ ግን በዋናነት አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከወራሪው ሃይል ነፃ በወጡበት ጊዜ ደርግ “በምስራቅ የተገኘው ድል በሠሜን ይደገማል” በሚል ጦሩን ነቅሎ ወደ ሰሜን ሲወስድ፣ ጥቂት ብርጌዶችን ኦጋዴንን እንዲጠብቁ ያደርጋል፡፡ በወቅቱ የዚያድ ባሬ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ቢወጣም ጠረፉ ላይ ሰፍሮ ነበር፡፡ ደርግ ሰራዊቱን ወደ ሰሜን መውሰዱን ያወቀው ዚያድ ባሬ፤ ወረራ ለማድረግ ተንቀሳቀሠ፡፡ ያ ዳግም ወረራ ከተደረገባቸው አውራጃዎች መካከል ቀብሪ ዳሃር፣ ዋርዴር፣ ገላዲ፣ ቦህ፣ ሉድሞ፣ ሊምበል የመሣሠሉት ናቸው፡፡
እኔ የነበርኩበት ክፍል ጦር ዋና መቀመጫው ቀብሪ ዳሃር ነበር፡፡ በአንድ ሻምበል ጦር የተደራጀ ነበር፡፡ ወራሪው ሃይል ከሌላም አንድ ሻምበል ጦር ጋር እኛን በከበባ ውስጥ አስገባን፡፡ 6 ወር ሙሉ ከወገን ጦር ተቆርጠን ነው ውጊያ ያደረግነው። ስንቅና ትጥቅ የሚደርሠን ከአውሮፕላን ነበር፡፡ እኛ አንድ ሻለቃ ብርጌድ ብቻ ሆነን፣ የተከበብነወ በአምስት ክፍለ ጦሮች ነበር፡፡ የጠላት ጦር የሚመራው ደግሞ በራሱ በዚያድ ባሬ የመከላከያ ሚኒስትር ነበር፡፡ እኛ ምሽጋችንን ቆፈርን፣ 6 ወር ሙሉ እንቅልፍ የለ፣ እረፍት የለ፣ በመከላከል ላይ ቆየን፡፡ በዚህ መሃል ብዙ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡ በጠላት ጦርና በኛ መካከል የነበረው ርቀት 3 መቶ ሜትር እንኳን አያክልም ነበር፡፡ አፍንጫ ለአፍንጫ ተጋጥመን ነው 6 ወር የቆየነው፡፡
መጨረሻ ላይ ጠላት አንድ ብርጌድ የአየር መቃወሚያ፣ አንድ ሻለቃ መድፈኛ፣ አንድ ብርጌድ ታንከኛ፣ አንድ ብርጌድ ሜካናይዝድ ጦር አደራጅቶ፣ 4 መቶ የማንሞላውን ለመደምሰስ ግስጋሴ ጀመረ። እኛ የመከላከያ ምሽጋችን ውስጥ በተጠንቀቅ ነበር የተዘጋጀነው፡፡ በቅፅበት ሶስት ታንኮች ምሽጋችንን ሠብረው ገቡ፡፡ ከላይ የአየር ውጊያ፣ ከስር የታንክ ውጊያ ውርጅብኝ ይወርድብን ጀመር፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ እነዚያን ታንኮች ከምሽጉ ውስጥ እንዳሉ እየፈጯቸው፣ እያደቀቋቸው፣ የሰው ልጅ አካልና አፈር አብሮ እየተቦካ ብዙ ወገን ረገፈ። እነዚያ ታንኮችን የሚቋቋም መሣሪያ ማግኘት አልቻልንም። ወንድሞቻችን አይናችን እያየ፣ በታንክ ሠንሠለት ጎማ ተፈጩ፡፡ ይሄ ዛሬም ድረስ ከህሊናዬ የማይጠፋ ነው፡፡
በወቅቱ ሁኔታውን ለተመለከተ፣ የዘላለም የአዕምሮ እረፍት ነው የሚያጣው፡፡ እኔም ያ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም… ኢትዮጵያዊ ወኔዬ በእጅጉ ተቀሠቀሠ። ቦንቦቼን ታጥቄ፣ ብቻዬን ከምሽጌ ወጥቼ፣ ቀጥታ ወደ አንደኛው ታንክ ነው ያመራሁት፡፡ ታንክ ላይ መድፍ፣ መትረየስ፣ ፒኬቲ የሚባል መሣሪያ አለ፡፡ ታንክ እነዚህን ሁሉ የያዘ አውዳሚ መሳሪያ ነው፡፡ በደረቴ እየተሣብኩ ወደ ታንኩ ሄድኩና፣ በእጄ ያየዝኩትን ቦንብ በጭስ ማውጫው አጎረስኩት፡፡ ታንኩ እንዳልነበር ሆኖ ከእነ 8 ምድብተኛ ተኳሾቹ ዶግ አመድ ነው የሆነው። የወገኔን ደም ተበቅያለሁ፣ የሃገሬን ዳር ድንበር ህይወቴን አጋፍጬ ማስከበሬ ያኮራኛል፡፡
ዛሬ ህይወትን እንዴት እየመሩት ነው?
አምስት ልጆች አሉኝ፡፡ ስራ የለኝም፡፡ የሚያውቁኝ እየረዱኝ በሠው እጅ እየኖርኩ ነው። መንግስት ጡረታዬን እንኳ አይከፍለኝም፡፡ ዛሬ ሰውነቴን ብታዩት እንደ ድሪቶ የተሰፋፋ ነው፡፡ የቤት ኪራይ የሚከፍሉልኝ፣ ልጆቼን የሚቀልቡልኝ ታሪኬን የሚያውቁ ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ለሃገሬ ዳር ድንበር ያበረከትኩት አስተዋፅኦ ተዘንግቶ፣ እንደ ጠላት፣ ጡረታ እንኳ መከልከሌ ያሣዝነኛል፡፡ ለሃገሬ በከፈልኩት ዋጋ የምኩራራ ብሆንም፣ ለጀግንነቴ በተከፈለኝ ወሮታ ግን እያዘንኩ እኖራለሁ፡፡ መቼም የሰው እጅ እያዩ ከመኖርና ቤት አልባ ከመሆን የበለጠ ጉስቁልና የለም፡፡
ባለቤትዎስ …. አብራችሁ ነው የምትኖሩት?
የመጀመሪያዋ የትዳር አጋሬና የሁለት ልጆች እናት ባለቤቴ በ1996 ዓ.ም ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየችኝ፡፡ በዚያን ጊዜ እሷ ስትሞት ሁለቱም ወንዶች ልጆቼ አንዱ የ4 ዓመት፣ ሁለተኛው የ2 ዓመት ጨቅላ ህፃናት ነበሩ፤ እነዚህን ህፃናት ያለ እናት ብቻዬን ለማሳደግ፣ በጦር ሜዳ ከተፈተንኩት አውደ ውጊያዎች ሁሉ ህይወቴን የፈተነኝ ዘመን ነው፡፡ የልጆቼ እናት ከሞተችብኝ በኋላ ለ7 ዓመት በሀዘን አሳለፍኩ፡፡ ከዚያ የፈጣሪ ፍቃዱ ሆነና አሁን አብሬያት የምኖረው ባለቤቴ ጋር አዲስ ሕይወት መሰረትን፡፡ አበው ሲተርቱ፤ መከራው ያላለቀ በሬ ሲሞት፣ ቆዳው ለከበሮ ይወጠራል ይላሉ፡፡ አዲሱ የትዳር ጉልቻዬም እንደገና በፈተና ተሞላ፤ ይኸውም እኔን አዲሷ ባለቤቴ ወደንና ፈቅደን የድህነትን ተራራ አብረን ተጋፍጠን መኖር ስንጀምር፣ እሷም በአቅሟ ስራ ነበራት፡፡ እኔም ወጥቼ ወርጄ በማመጣው የዕለት ገቢ ተደጋግፈን ጎጆያችንን እየመራንና ልጆቻችን ማሳደግ ስንጀምር መጋቢት 14 ቀን 2006 ዓ.ም ሌላ የመከራ ድግስ ይዞልኝ መጣ፡- ይኸውም ውዷ ባለቤቴ የዕለት ስራዋን ለማከናወን ከምንኖርበት አየር ጤና ሰፈር ወደ ስራ ቦታዋ አብነት አካባቢ ለመሄድ ከካራ ቆሬ የተነሳ 66 ቁጥር አውቶቡስ ትሳፈራለች፡፡
ይህ ቀን ለውዷ ባለቤቴም አውቶብሷን ለተሳፈሩ ሁሉ አዝማም ቀን ነበር፡፡ 66 ቁጥር አውቶብስ አየር ጤናን አልፎ፣ ወደ አለርት ሆስፒታል ወይም ዘነበወርቅ ገደል እስከሚገባ ተሳፋሪው እየጮኸ እየተንገጫገጨ፣ ያን ሁሉ የጫነውን ሰው ይዞ ዘነበወርቅ ገደል ገባ፡-  በአደጋው የሞተ ሞተ፤ የተረፈው የሰው ልጅ እንደ ኮንቴነር መጫኛ በክሬን ነበር የወጣው፡፡ ባለቤቴም በአካሏ ላይ ከፍተኛ አደጋ ከአደረሰባት በኋላ በዚሁ መልክ በህይወት ተረፈች። የደቆነ ሳይቀድስ አይቀርም ይባል የለም ዛሬ ባለቤቴ አካሏ ጎደሎ ከሥራ ውጭ ሆነ እነሆ እስከ፣ አሁኗ ሰዐት ድረስ እሷኑ በማሳከም ላይ እገኛለሁ። በአሁኑ ሰዓት ያኔ ህይወት ለሀገሬ ለኢትዮጵያ በከፈልኩት መስዋዕትነት ልክ ሳይሆን ሀገርንና ወገንን እንደበደለ፣ ወንጀለኛ ለኢትዮጵያ በደሜ ፍሳሽ በአጥንቴ ክስካሽ፣ ስጋዬ እንደ ዲርቶ ልብስ በመርፌ ተሰፍቶ፣ የሀገሬን ዳር ድንበር ሉአላዊነት እና የታላቁን ህዝብ ክብር በአስከበርኩበት ምድር ላይ ለእግሬ መቆሚያ፣ ለአንገቴ ማስገቢያ አጥቼ፣ በዚህ ዘመን እንደ ሀገር ባለውለታ መጦርና ተከብሬ በክብር መኖር ሲገባኝ፣ ከአብራኬ የወጡ ልጆቼና ቤተሰቤ ሁሉ እንደ አንድ የጦር ሜዳ ጀግና ቤተሰብ ሳይሆን እንደ ወንጀለኛ ቤተሰብ ከእኔ ጋር ከቦታ ቦታ መጠለያ በማጣት የሰውን ኩሽና ስንጠርግ እንከራተታለን፡፡  

 1. በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ50 በላይ የመንግስት ባለሥልጣናት በሙስና ተጠርጥረው ታስረው፣የ8 ባለሃብት ኩባንያዎችና ድርጅቶች በፍርድ ቤት
ታግደው፣ከ200 በላይ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ገና ሊያዙ እንደሚችሉ ተስፋ ተሰጥቶት፣ህዝቡ ግን አሁንም ዋናዎቹ መች ተያዙና እያለ ነው፡፡ ጨርሶ የልቡ
አልደረሰለትም፡፡ ግን እርስዎስ ምን አሉ?
ሀ) እኔም ከህዝቡ የተለየ ሃሳብ የለኝም!
ለ) ህዝብ መንግስትን ቢጠራጠር አይፈረድበትም!
ሐ) ሁሉም ከታሰሩማ ማን ይመራናል !? (ባይሆን ተራ በተራ)
ሠ) የኮንዶሚኒየምና የስቴዲየም ግንባታ፣ የጸረ- ሙስና ዘመቻ መቼ ነው?!
2. የመንግስት ባለሥልጣናት የሃብት ቆጠራ ተከናውኖ፣ የእያንዳንዱን ሹመኛ ሃብትና ጥሪት ይፋ እናደርጋለን ተብሎ አልነበር እንዴ? ቀርቶ ነው ወይስ ዘግይቶ?
ሀ) ሃብታቸው ተቆጥሮ አላልቅ ብሎ ይሆናል?!
ለ) ”ይሄማ ለህዝብ ፊት መስጠት ነው” በሚል፣ውድቅ ተደርጎስ ቢሆን?
ሐ) ለነገሩ ሃብት ተቆጠረ ማለት ሙስና ላለመብላት ግዝት ነገር አይደለም!
መ) መንግስት ድሮም ያመጣው፣የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት፣የባለሥልጣናትን ሃብት እንዲቆጥሩ ስለሚጠይቅ ሳይሆን አይቀርም
ሠ) አሁንማ በደንብ ተበርብሮ መቆጠር አለበት ( ስንት መ ቶ ሺ ነው፣”ለአስቤዛ” በሚል ቤት ውስጥ የተገኘው?)
3. ሰሞኑን የሶማሊያ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ትምህርትና ተሞክሮ ሲቀስሙ መሰንበታቸውን ከኢቢሲ ሰምተናል፡፡ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ፣ትግራይና አማራ ክልል ነው፣ የፌዴራሊዝም ልምድና ተሞክሮን ሲጋሩ የሰነበቱት፡፡ እውነት ግን ለጎረቤት ተሞክሮ የሚበቃ፣አስተማማኝ
የፌደራሊዝም ሥርዓት መሥርተናል እንዴ?
ሀ) አዲሲቱን ሶማሊያ ጉድ እንዳንሰራት!?
ለ) ከኢትዮጵያዊነት ጋር አኳርፎናል የተባለ መስሎኝ?!
ሐ) ተሞክሮው ለኛው ይሆን እንዴ (እምዬ ኢትዮጵያ ለምንለው!)
መ) ምናልባት የተሻለ ሌላ ሥርዓት ካለም፣ ክፍት ብንሆን ይበጀናል?!
ሠ) እኔ የሰለቸኝ እንዲህ ዓይነቱ የኢህአዴግ ድራማ ነው!
4. የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 5ኛ ሙት ዓመትን ምክንያት በማድረግ፣ ኢቢሲ፣ከጠ/ሚኒስትሩ ንግግር
እየቀነጫጨበ ሲያሰማ ሰንብቷል፡ ፡ በተለይ ስለ ዲሞክራሲ፣ስለ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት የተናገሩት፣የኢህአዴግ አይመስልም፡፡ አንዳንድ ሰዎችማ ማመን
እስኪያቅታቸው ድረስ በሰሞኑ የጠ/ ሚኒስትሩ ንግግር ተደምመዋል አሉ፡፡ እርስዎስ ምን ተሰማዎት?
ሀ) ሰው ካልሄደና ካልሞተ አይመሰገንም!
ለ) እኔ ወሬ ሰልችቶኛል፤በተግባር ማየት ነ ው የ ምፈልገው
ሐ) ኢህአዴጎች የገባቸው አይመስለኝም፤ ደጋግመው ይስሙት
መ) ኢህአዴግ አሁንም ሌላ ተናጋሪ አልተካም እኮ
ሠ) የአሁኑ ኢህአዴግና የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ኣራምባና ቆቦ ነው
• ውድ አንባቢያን፤ መልሶቻችሁ ከምርጫዎቹ ውስጥ ከሌሉ፣ረ) ብላችሁ የራሳችሁን አማራጭ መጻፍ ህገ መንግስታዊ መብታችሁ ነው፡፡

   በ12 ወራት 26 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች

       በርካታ ታላላቅ ሽልማቶችን ባገኘው ላላ ላንድ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የሰራቺው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይት ኢማ ስቶን፣ ባለፉት 12 ወራት በድምሩ 26 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት የአመቱ የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ የፊልም ተዋናይት ሆናለች፡፡
ፎርብስ መጽሄት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ እንዳለው፣ የ28 አመቷ የፊልም ተዋናይት ኢማ ስቶን ገቢ አምና ከነበረው 10 ሚሊዮን ዶላር የ160 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 26 ሚሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ለገቢዋ መጨመር ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረገላት አመቱን በስኬት እየገፋ ያለው ላላ ላንድ ፊልም ነው።
ታዋቂዋ የሂልም ተዋናይት ጀኔፈር አኒስተን በ25.5 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን፣ አምና በአንደኛነት ተቀምጣ የነበረቺው ጄኔፈር ሎውረንስ ዘንድሮ በ24 ሚሊዮን ዶላር የሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ፎርብስ መጽሄት አስታውቋል፡፡
ሜሊሳ ማካርቲኒ በ18 ሚሊዮን ዶላር፣ ሚላ ኩኒስ በ15.5 ሚሊዮን ዶላር የአራተኛና የአምስተኛ ደረጃን እንደያዙ የጠቆመው ፎርብስ፣ የዘንድሮዎቹ ምርጥ 10 ከፍተኛ ተከፋይ ሴት የፊልም ተዋንያን፣ ባለፉት 12 ወራት በድምሩ 172.5 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡

 ባለፈው አመት 1 ሚሊዮን ኮፒ አልበም ተሸጦለታል

       ታዋቂው የሙዚቃ አቀንቃኝ ኤልቪስ ፕሪስሊ፤ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ባለፈው ረቡዕ 40 አመት እንደሞላው ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ድምጻዊው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ 27 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘቱንና በአመቱ አንድ ሚሊዮን ያህል አልበሞች እንደተሸጡለት ዘግቧል፡፡
በተወለደ በ42 አመቱ እ.ኤ.አ በ1977 በልብ ድካም ከዚህ አለም በሞት የተለየው ኤልቪስ ፕሪስሊ፤ ዛሬም ድረስ ዝናው የማይቀዘቅዝ ዘመን አይሽሬ ድምጻዊ ነው ሲል የዘገበው ሎሳንጀለስ ታይምስ በበኩሉ፣ የሙዚቃ ስራዎቹም በዩቲዩብ ድረገጽ፣ ከ2.8 ቢሊዮን ጊዚያት በላይ እንደታዩለት አስታውቋል፡፡ ወደ ሙዚቃው አለም ከገባበት ጊዜ አንስቶ በድምሩ 197 ያህል የጎልድ፣ የፕላቲኒየምና የዲያመንድ ሽልማቶችን ያገኘው ኤልቪስ፣ በፖፕ የሙዚቃ ታሪክ ይህን ያህል ሽልማት በማግኘት ዛሬም ድረስ የሚስተካከለው ድምጻዊ እንደሌለም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በስሙ የተለያዩ ተቋማትና የመዝናኛ ስፍራዎች እንደተቋቋሙለትና በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያንቀሳቀሱ የጠቆመው የቢቢሲ ዘገባ በበኩሉ፣ ከእነዚህም መካከል በአሜሪካ ሜምፊስ የሚገኘውና በአመት ግማሽ ሚሊዮን ያህል ጎብኝዎችን በማስተናገድ ለኢኮኖሚው 150 ሚሊዮን ዶላር ያህል የሚያበረክተው ግሬስላንድ የተባለው መዝናኛ ስፍራ እንደሚጠቀስ አመልክቷል፡፡ የኤልቪስ አድናቂዎች ማስታወሻዎቹንና በስሙ የሚመረቱ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሸጥ ዳጎስ ያለ ገቢ እያገኙ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ የኤልቪስ ጌጣጌጦች፣ መጽሄቶች፣ መጽሃፍት፣ ቲሸርቶችና መነጽሮች በአለማቀፍና አገር አቀፍ ጨረታዎች በከፍተኛ ዋጋ እንደሚሸጡም አመልክቷል፡፡
ታዋቂው አለማቀፍ አጫራች ተቋም ኤቤይ፣ ደምበኞቹ ከኤልቪስ ፕሪስሊ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቁሳቁሶችና ማስታወሻዎች ለመግዛት ያላቸው ፍላጎት ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያስታወቀ ሲሆን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በእያንዳንዱ ሰዓት 12 ያህል ከኤልቪስ ጋር ግንኙነት ያላቸው እቃዎችን መሸጡን አስታውቋል። ኤቤይ በአሁኑ ወቅት 70 ሺህ ያህል የኢልቪስ ማስታወሻዎችንና ከእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለገዢዎች ማቅረቡንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

  የእውቁ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ “ያልተቀበልናቸው” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሐፉ ከ20 በላይ መጣጥፎችን፣ ወጎችን እና “የካሳ ፈረሶች” የተሰኘ ታሪካዊ የተውኔት ድርሰትን ያካተተ ሲሆን የዚህ መፅሐፍ አብይ ትኩረትም ባልህ፣ ታሪክ ሚዲያና ፖለቲካ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል “ያልተቀበልናቸው” መፅሐፍ ከተጠቀሱት ታሪኮች በተጨማሪ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ የተወለዱ ግለሰቦች በዚህ ዘመን ስለሚደርስባቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጫና፣ በህክምና ሰበብ ስለሚፈጠሩ ሳንካዎች፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በኢትዮጵያ ስለገጠመውና እየገጠመው ስላለው ተግዳሮት የሚያትት ነው ተብሏል፡፡
መፅሐፉ በ260 ገፆች ተቀንብቦ በ75 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “እምቢታ” ፣ ማዕቀብ፣ ኬርሻዶ፣ በዓሉ ግርማ ህይወቱና ስራዎቹ፣ ዛጎል፣ ደርሶመልስ የተሰኙ መፅሐፎች ለንባብ ያበቃ ሲሆን ከጥቁር ሰማይ ስር፣ የመኝታ ቤት ምስጢሮች እና ፅላሎት በተሰኘ አጫጭር ትረካዎቹ ይታወቃል፡፡