Administrator

Administrator

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያለ አንድ አስቸጋሪ ልጅ ነበረ፡፡ ይሄ ልጅ ነጋ ጠባ ማልቀስ ነው ሥራው፡፡ ሞገደኛ ነው፡፡
አባት፤ “አንተ ልጅ እረፍ፤ እምቢ ካልክ ዋ! ለጅቡ ነው የምሰጥህ” ይሉታል፡፡
ልጅ ለጥቂት ጊዜ ዝም ይላል፡፡ ሆኖም ብዙ ሳይቆይ እንደገና ማልቀስ ይጀምራል።
“አንተ ልጅ ዛሬ ምን ነክቶሃል ዋ! ለአያ ጅቦ ነው የምሰጥህ፤ አውጥቼ ነው የምወረውርህ” ይሉታል፡፡
አሁንም ልጁ የአያ ጆቦን ድምጽ ሲሰማ፣ ድንግጥ ይልና ድምፁን ያጠፋል፡፡ ሆኖም አመለኛ ልጅ ነውና ከጥቂት ቆይታ በኋላ ማላዘኑን ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ አባት ይናደድና ሁለት እጁንና ሁለት እግሩን ጥፍር አድርገው ያስሩታል፡፡ ቆጥ ላይ አውጥተው ያስቀምጡታል፡፡ ይሄኔ ልጁ ዝም ይላል፡፡
እናት መቼም እናት ናትና አንጀቷ ይባባና፤
“ግዴሎትም ይሄ ልጅ አሁን ፀባይ አሳምሯል፤ ልፍታው” ትላለች፡፡
አባት፡- እንደገና ቢያለቅስ ግን ውርድ ከራሴ፤ ልጃችን በጣም ሞገደኛ ሆኗል፡፡”
እናት፡- “ልጅ አይደል፤ በአንዴ አይታረም ቀስ በቀስ ያሻሽላል፡፡ እርሶም ብዙ አይጨክኑበት፡፡”
እውነትም እናት እንዳለችው ልጁ ፀጥ አለ፡፡
ለካ ይሄ ሁሉ ሲሆን አያ ጅቦ ጓሮ ሆኖ ያዳምጥ ኑሯል፡፡ ጥቂት ቆይቶ ድምፁ ሁሉ ፀጥ አለ፡፡ አሁን አሁን ልጁን ይወረውሩልኛል እያለ ይጠብቅ የነበረው አያ ጅቦ፣ ጆሮ ቢጥል ምንም ድምጽ ጠፋ፡፡ እናትና አባት ልጁን አስተኝተው የግል ወሬያቸውን ቀጥለዋል፡፡
“ያን ቦታ እንሸጠው ስልሽ… የመሬት ዋጋ አሽቆለቆለ”
እናት፡- “ግዴለም ላመት መጨመሩ አይቀርም፡፡ ዋናው መሬቱ በስማችን ያለ መሆኑ ነው፣ በዚያ ላይ ምንም አንገብጋቢ የኢኮኖሚ ችግር አለመኖሩ ነው፡፡ የመሬት ዋጋው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይመጣም፡፡”
አባት፡- “ነገሩ እውነትሽን ነው፡፡ የቦታ ሽያጭ በየጊዜው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ እኔ እንደው ጓጉቼ ነው የተጣደፍኩት”
ይሄንና ሌላም የቤታቸውን ነገር እየተወያዩ ቆይተው ለጥ ብለው ተኙ፡፡
“ይሄኔ አያ ጆቦ ወደ በራፉ ጠጋ ብሎ ኧረ የልጁን ነገር ቶሎ ወስኑልኝና ገላግሉኝ” አለ ይባላል፡፡
*   *   *
በሀገራችን ብዙ ያልተወሰኑና በይደር የቀሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንድም ቁርጠኛ ወሳኝ አካል ባለመኖሩ፣ አንድም ደግሞ ከስር መሰረት ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ በመሆናቸው፡፡ ወደ ተወሳሰበ ግጭት ያስገቡም በመሆናቸው ነው፡፡ ለያዥ ለገራዥ የማይመቹ በመሆን ደረጃ ላይ በመድረሳቸው፡፡ ይኸው የኢኮኖሚ ገጽታችን መልክ የሌለው ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፡፡
በመሠረቱ ስራዬ ብሎና ይሁነኝ ብሎ የሚያጠና፣ የሚያቅድና የሚተገብር፤ የሚጨነቅና የሚጠበብ አካልና “አባከና” የሚል በሌለበት ንፍቀ ክበብ ውስጥ አገርን ለማልማትና ህዝብ የመታደግ ሂደትን ማጐልበት እጅግ አዳጋች ነው። ፖለቲካዊ ያገባኛል ባይነትና ኢኮኖሚያዊ ይገባኛል ባይነት ተሰናስለው በማይጓዙበት ሁኔታ ውስጥ ሥር የያዘ ለውጥን በአግባቡ ፈር አስይዞ መንቀሳቀስ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአህጉራችንም ካንሰር አከል አባዜ ነው፡፡ ዛሬም ስለ ሙያዊነት፣ ሥነ ምግባራዊነት ማውራት የምንገደደው ወደን አይደለም፡፡ ያልበለፀገ የሰው ኃይል፣ በሌብነት የፈነቀለ ጐደሎ ሥርዓት፣ ስለ ሀገርና ህዝብ ይሄ ነው የሚባል እውቀትም ሆነ ብቃት አሊያም በቂ ትምህርት በሌለው ትውልድ እጅ ላይ የወደቀ ህብረተሰብ ወደፊት እንዳይራመድ አያሌ አሽክላዎች እንደሚደቀኑበት ከቶም አጠያያቂ አይደለም፡፡
ከቀን ቀን እየተሸረሸረ ያለው ሞራል ቁልቁለቱ አሳሳቢ ነው፡፡ የሀገር ፍቅር እየተመናመነ መምጣቱ አስጊ ነው፡፡ እንስራ ሲባል “እንዝረፍ” የሚል አስተሳሰብ ያለው ትውልድ፤ እለት ሰርክ እየቀፈቀፍን፣ ቀቢፀ ተስፋን እንጂ ተስፋን ማለም ጤናማ ራዕይ አይደለም፡፡ ይህ ጥበብ  “decadence” ክፉ አባዜ ነው። ሳይታወቀን እየወረድንበት ያለውን አዘቅት መለስ ብለን የምናይበት አንገት የሚያሳጣ አስደንጋጭ ተዳፋት ነው፡፡
እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁላችንንም ተጠያቂ የሚያደርግ የመሽቆልቆል መርገምት ነው፡፡ “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” የሚያሰኝ ሶሽዮ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ አዝሎ የሚጓዝ ባለቤት አልባ የሚመስል ከባቢ አየር ውስጥ መሆናችን ኤጭ የማይባል ነገር ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ሠላምን ማረጋገጥ የመንግሥትም የህዝብም ግዴታ ነው። “እዚህ ቦታ ግጭት ተጀመረ…እዚህ ቦታ ሽብር ተቀሰቀሰ…” እያልን፣ በዜናና በዜማ የምናልፈው አይደለም፡፡ በድሮው መንግሥት ጊዜ መግለጫው ውስጥ “ዳሩ ሲነካ መሀከሉ ዳር ይሆናል” ይባል ነበር፡፡ ትልቅ እውነት ነው፡፡ በየዳር አገሩ የሚፈጠሩትን ግጭቶች ቸል ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ የምንመኘው ብልጽግናና እድገት እውን የሚሆነው ቅንነት፣ ታታሪነትና  የመነሳሳት መንፈስ ሲኖር ነው፡፡ ያ በሌለበት ሂደት ውስጥ ያለን ከሆነ ግን “ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” የሚለውን የአበው አባባል እንድናሰላስል እንገደዳለን፡፡በአሜሪካ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ፣ ከሞቀ ቤታቸው እየወጡ፣ ጎዳና አዳሪ የሚሆኑ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ምክንያቱ ደግሞ ከሥራቸው እየተባረሩ፣ ለቤት ኪራይ የሚከፍሉት ገንዘብ በማጣታቸው ነው ተብሏል፡፡
 የ34 ዓመቷ ሜሊሳ ኖርማን፣ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ከገጠማቸው አሜሪካውያን አንዷ ናት፡፡  ከምትኖርበት ሆስቴል ወጥታ በቶርኩዌይ ዴቮን አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ድንኳን ተክላ ለመኖር የተገደደችው፣ ለቤት ኪራይ የምትከፍለው ገንዘብ በማጣቷ ነው፡፡
ለአካባቢው አስተዳደር ጎዳና ልትወጣ መሆኑን ማሳወቋን የጠቆመችው ኖርማን፤ ሆኖም የጊዜያዊ መኖሪያ ቤት ፍላጐት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ሳቢያ፣ ከዓመት በፊት ቤት እንደማታገኝ እንደነገሯት ገልጻለች፡፡  
 “ወደ ሆስቴሉ የገባሁት አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ከመዘጋታቸው በፊት ነበር። ከዚያም በወረርሽኙ ሳቢያ የምሰራበት ማክዶናልድ መዘጋቱን ተከትሎ፣ ሥራዬን በማጣቴ፣ የሆስቴሉን ኪራይ እየከፈልኩ መቀጠል አልቻልኩም፡፡” ትላለች፤ ኖርማን።
በማከልም፤ “በድንኳን ውስጥ መኖር ከጀመርኩ ከሳምንት በላይ ሆኖኛል። አስተዳደሩ በተራ ጠባቂ ዝርዝር ውስጥ መሆኔን ነግሮኛል፤ ግን ቤት ለማግኘት እስከ አንድ ዓመት ድረስ ይወስዳል።; ብላለች፡፡
“ቅዝቃዜው እያየለ መጥቷል፤ እስካሁን የክረምት ድጋፍ አልተደረገልንም፡፡ ለወትሮው የመስክ መኝታ (ስሊፒንግ ባግ) እንደ ግላስቶንበሪ ከመሳሰሉ ፌስቲቫሎች እናገኝ ነበር፤ ዘንድሮ ግን ፌስቲቫሎች በመሰረዛቸው ምንም አላገኘንም፡፡"
"ከ16 ዓመቴ ጀምሮ ከሥራ አልተለየሁም፤ ያልከፈልኩት ግብርም የለም፡፡ ይሄ የሚያሳምም ነገር ነው" ስትልም ኖርማን ተናግራለች - እኒህን ሁሉ ዓመታት ሰርታ ጎዳና መውጣቷ እንደሚያበግናት በመግለጽ።
“ጎዳና ልትወጣ ስትል ለቶርባይ አስተዳደር የምትደውልበት ቁጥር አላቸው፤ ነገር ግን አንድ ሰው ጎዳና መውጣትህን እስኪያረጋግጥልህ ድረስ መደወሉ ለውጥ አያመጣም፤ እናም በዚህ መሃል ያ ሰው ጎዳና  ወጥቶ ያርፈዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ አይገኝም፡፡” በማለትም ታስረዳለች፤ ሜሊሳ ኖርማን፡፡  
የአስተዳደሩ ሃላፊ ክርስቲን ካርተር በበኩላቸው፤ “እንደ አብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በተባባሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ፣ በአማራጭ የመኖሪያ ቤቶች አገልግሎታችን ፍላጎት ረገድ፣ ከፍተኛ መጨመር እያየን ሲሆን ቡድናችን ጊዜያዊ ማረፊያዎችን ለሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ ለማቅረብ በርትቶ እየሰራ ነው::” ብለዋል::    
የኮቪድ 19 ጦስ ብዙ ነው፡፡ በቫይረሱ መያዝ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡ ከሥራ ገበታ ያፈናቅላል፡፡ ገቢ አሳጥቶም ተደጓሚ ያደርጋል፡፡ ከሞቀ መኖሪያ ቤት አስወጥቶ፣ ለጎዳና ኑሮም ይዳርጋል፡፡  አያድርስ ነው!


  በአለማችን በሳምንቱ ከ2 ሚ. በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል

            በአለማችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛው ነው የተባለው ሳምንታዊ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ሳምንት መመዝገቡንና በሳምንቱ በመላው አለም ከ2 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በሳምንቱ በመላው አለም ከተመዘገቡት አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል ወደ ግማሽ የሚጠጉት በአውሮፓ አገራት እንደሚገኙ የዘገበው ቢቢሲ፤ በአውሮፓ አገራት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በየዕለቱ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በ40 በመቶ መጨመሩንም የአለም የጤና ድርጅትን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል።
በድርጅቱ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ማይክ ሪያን ባለፈው ሰኞ እንዳሉት፣ ቫይረሱ ከየትኛውም የአለም ክፍል በተለየ ሁኔታ በአውሮፓ አገራት እየተስፋፋ የሚገኝ ሲሆን አውሮፓ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በሞት ልትነጠቅ ትችላለች፤ የከፋውን ጥፋት ለመቀነስ አገራት ሙሉ ለሙሉ እስከ መዘጋት የሚደርስ ቁርጠኝነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመላው አውሮፓ የከፋና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመር ታይቷል ያሉት የአለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ዶ/ር ማርጋሬት ሃሪስ፤ ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በየቀኑ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ ሦስተኛ ሲጨምር፣ የሚመዘገበው የሞት መጠን በ40 በመቶ ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል።
በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት ሆስፒታሎች የሚገኙ የጽኑ ህሙማን የህክምና ክፍሎች በቫይረሱ ተጠቂዎች ከአፍ እስከ ገደፋቸው መሙላታቸውን መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ ባለፈው ሳምንት ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ያህል አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፤ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እስካለፈው ረቡዕ 1.74 ሚሊዮን መድረሱን፣ የሟቾች ቁጥር ወደ 42 ሺህ መጠጋቱን፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ1.42 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ጠቁሟል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በታደሙበት የእራት ግብዣ ላይ የተገኘ አንድ እንግዳ በኮሮና ቫይረስ መያዙ መረጋገጡን ተከትሎ፣ ራሳቸውን ማግለላቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

   ዶ/ር ደምስ ጫንያለው "ኢኮኖሚዉ፣ ፫ቱ ፖለቲከኞች እና ፖሊሲ"  በሚል ርዕስ ያሳተሙት አዲስ መጽሐፍ፤ ሕዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም በእለተ ሐሙስ፣ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል  ይመረቃል።  
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ከአዲሱ መጽሐፍ በተጨማሪ ዶ/ር ደምስ ቀደም ሲል በእንግሊዝኛ ያሳተሙት ‹‹The Quest for Change: Ethiopia’s Agriculture and Pastoral Policies, Strategies and Institutions; የተሰኘ መጽሐፋቸው ለሽያጭ እንደሚቀርብ ተጠቁሟል፡፡  
 ኢኮኖሚዉ፣ ፫ቱ ፖለቲከኞች እና ፖሊሲ፤ በ15 ምዕራፍ፣ መቅድሙን ጨምሮ 404 ገጽ  350 ብር፡፡ ሲሆን The Quest for Change: በ10 ምዕራፍ፣ መቅድሙን ጨምሮ 290 ገጽ 285 ብር ይቀርባል፡፡
ዛሬ ላይ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር፣ ስለ ሶስተኛው ፖለቲከኛ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘቱ፣ መገለጫውና ምንነቱ፣ እንዲሁም ይኸዉ ፖለቲከኛ በኢትዮጵያ ዉስጥ ስለሚጫወተው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሚና ማስገንዘቢያ እንዲሆን ከመጽሐፉ ምዕራፍ አምስት የተመረጡ አንቀፆችን በመንቀስ አባሪ ተደርጎ እንዲሰራጭ መደረጉንም ዶ/ር ደምስ ተናግረዋል፡፡  
ደራሲው ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫ፤ "በምረቃው ዕለት መጥተዉ መጽሐፉን ይግዙ። በምዕራፍ አምስት ከተገለፀው በተጨማሪ በፖሊሲም ሆነ በተለያዩ ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ልማት ጉዳዮች በርካታ ትምህርታዊ ማስረጃዎችና ማብራሪያዎችን ያገኙበታል፡፡" ሲሉ የግብዣ ጥሪ አድርገዋል፡፡  

በየአመቱ ግማሽ ቢሊዮን ህጻናት በተበከለ አየር ሳቢያ ይሞታሉ

             በመላው አለም ከሚገኙት አጠቃላይ ህጻናት 16 በመቶው ወይም 356 ሚሊዮን ያህሉ በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የእኒህን ህጻናትን ቁጥር በእጅጉ ይጨምረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነገረ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ቁጥር እስከ 2017 በነበሩት አራት አመታት፣ በ29 ሚሊዮን ያህል የቀነሰ ቢሆንም፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ግን ችግሩን በከፋ ሁኔታ ያባብሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም በተበከለ አየር ሳቢያ በየአመቱ ግማሽ ቢሊዮን ያህል ህጻናት በተወለዱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሞት እንደሚዳረጉ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገውን የ2020 አለማቀፍ የአየር ሁኔታ ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት (2019) በአለማችን ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ህጻናት በተበከለ አየር ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከነዚህም መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የእንጨትና ኩበት ጭስን ጨምሮ በቤት ውስጥ በሚፈጠሩ የአየር ብክለቶች ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡ በ2019 የፈረንጆች አመት በመላው አለም በድምሩ ከ6.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተበከለ አየር ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ የተበከለ አየር በአሁኑ ወቅት በአለማችን በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ለሞት በመዳረግ በአራተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

 የሰው ልጅ እስከ መጪዎቹ አምስት አመታት ድረስ ለረጅም ዘመናት ሲያከናውናቸው ከኖራቸው የስራ አይነቶች መካከል ግማሽ ያህሉን የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባፈራቸው ማሽነሪዎችና ሮቦቶች ይነጠቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ከሰሞኑ ባወጣው አለማቀፍ መረጃ እንዳለው፣ አለምን እያጥለቀለቀ ያለው የ“ሮቦቶች አብዮት”፤ የሰውን ልጅ ከስራ ገበታው በማፈናቀል ረገድ ተጽዕኖው እየተባባሰ እንደሚሄድና እ.ኤ.አ እስከ 2025 ወደ 85 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ለስራ አጥነት ይዳርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመላው አለም በሚገኙና እስከ 8 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰራተኞች ባላቸው 300 ታላላቅ ኩባንያዎች የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ተቋሙ እንዳለው፣ አብዛኞቹ ኩባንያዎች ሰዎችን በሮቦቶች ለመተካት ማቀዳቸውን የተናገሩ ሲሆን ሮቦቶች የሰዎችን ስራ በከፍተኛ መጠን ይነጥቋቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ የስራ መስኮች መካከልም የአስተዳደርና የመረጃ ማጠናከር መስኮች ይገኙበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላው አለም ከሚገኙት የስራ መስኮች መካከል ከ33 በመቶ በላይ የሚሆኑት በማሽኖችና ሮቦቶች ተይዘው እንደሚገኙ የጠቆመው ተቋሙ፣ በመጪዎቹ አምስት አመታት ግን ሮቦቶች በርካታ ስራዎችን ከሰዎች ይነጥቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡


 ታዋቂው የሞባይል ስልኮች አምራችና የኔትወርክ ዝርጋታ ኩባንያ ኖኪያ፤ ከሁለት አመታት በኋላ ጨረቃ ላይ የመጀመሪያውን የሞባይል ኔትወርክ ሊዘረጋ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ እ.ኤ.አ እስከ 2024 ሰዎችን ወደ ጨረቃ ለመላክና ለተራዘመ ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ የያዘው አርቴሚስ ፕሮግራም አካል የሆነውን ይህን የሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታ ለማከናወን በርካታ ኩባንያዎች ቢወዳደሩም፣ ኖኪያ በአሸናፊነት መመረጡ ባለፈው ሰኞ ይፋ መደረጉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኖኪያ በአለማችን ታሪክ የመጀመሪያው የሆነውን የጠፈር የሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታ እ.ኤ.አ እስከ 2022 መጨረሻ ድረስ ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ኔትወርኩ 4ጂ/ኤልቲኢ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርና በሂደት ወደ 5ጂ እንደሚያድግም ገልጧል፡፡
የተለያዩ የአየር ንብረቶችን ተቋቁሞ የጠፈር ተመራማሪዎች፣ በድምጽና በምስል ግንኙነት እንዲያደርጉ ያስችላል ለተባለው ታሪካዊ የሞባይል ኔትወርክ ግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶችን፣ ወደ ጨረቃ የማጓጓዙን ስራ የሚያከናውነው፣ ተቀማጭነቱ በቴክሳስ የሆነው ኢንቲዩቲቭ ማሽንስ የተሰኘ የግል ኩባንያ መሆኑንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 በዓለማችን በቀን 10 ቢሊዮን ሰዓታት በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ይባክናል


              ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚ መሆኑንና ማህበራዊ ድረገጾችን በቋሚነት የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር 4.14 ቢሊዮን ያህል መድረሱን ከሰሞኑ የወጣ አንድ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ሆትሱት እና ዊአርሶሻል የተባሉት የጥናት ተቋማት ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉት የሩብ አመት አለማቀፍ ዲጂታል ሪፖርት እንደሚለው፤ 7.81 ቢሊዮን ከሚገመተው የአለም ህዝብ ውስጥ 60 በመቶው ወይም 4.66 ቢሊዮን ያህሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥም 4.14 ቢሊዮኑ ማህበራዊ ድረገጾችን በቋሚነት የሚጠቀሙ ናቸው፡፡
ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በአለማችን የተለያዩ አገራት ከ450 ሺህ በላይ አዳዲስ የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚ ደንበኞች መመዝገባቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህም በአመቱ በአማካይ በየአንዳንዱ ሰከንድ 14 ሰዎች ማህበራዊ ድረገጽ መጠቀም መጀመራቸውን ያሳያል ብሏል፡፡
ከሃምሌ እስከ መስከረም በነበሩት 3 ወራት በመላው አለም፣ የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚዎች ቁጥር፣ በአማካይ በየዕለቱ በ2 ሚሊዮን መጨመሩን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሰው ዋናው ጉዳይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ ሰዎች እንቅስቃሴያቸው ተገትቶ በቤት መቆየታቸውን ነው፡፡
ባለፈው ሩብ አመት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች፣ በየዕለቱ በአማካይ 6 ሠዓት ከ55 ደቂቃ ያህል ጊዜ ኢንተርኔት በመጠቀም አሳልፈዋል ያለው ሪፖርቱ፤ 2 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ያህሉን ያጠፉት ደግሞ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ መሆኑን አክሎ ገልጧል፡፡
የአለማችን የማህበራዊ ድረገጽ ደንበኞች በቀን በድምሩ 10 ቢሊዮን ሰዓታትን ኢንተርኔት ሲጎረጉሩ ያጠፋሉ ማለት ነው፤ በሪፖርቱ ስሌት ሲታሰብ፡፡

  ከዕለታት አንድ ቀን ከታዋቂው መምህርናa ደራሲው ባለቅኔአችን ከከበደ ሚካኤል ጋር አንድ የሀገራችን ገጣሚ ተገናኝቶ ሲወያይ :-
“እስከዛሬ ከፃፉልን ግጥሞች የትኛውን በጣም ይወዱታል ብሎ ጠየቃቸው”
አቶ ከበደም፤ ልጅን ማመረጥ አይቻልም፡፡
“ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆዩ ሲባል አልሰማህም” ይሉታል፡፡
ገጣሚውም፤ “እርግጥ ነው አቶ ከበደ ያሉት እውነት ነው” ነገር ግን አንድን ፈጠራችንን አብዝተን እንወዳለን ማለት ሌላውን እንጠላለን ማለት አይደለም። “እንዲያው በጣም የሚያስታውሱትን ግጥም ይንገሩኝ፤ ብዬ ነው፡፡” ይላቸዋል በትህትና።
አቶ ከበደም በቃላቸው የሚከተለውን ግጥም ይሉለታል፡፡
አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
ያው ከወንዙ ዳር እያለ ጐርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ ድምፁን አሳምሮ
“ምነው አቶ አዝማሪ ምን ትሠራለህ?” ብሎ ቢጠይቀው
ምን ሁን ትላለህ?
አላሻግር ቢለኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ”
“አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
ነገሩ ባልከፋ ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ?
እስኪ ተመልከተው ይሄ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ
ተግሳጽም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ!” አሉት፡፡
*   *   *
የሀገራችን ገጣሚያን በተለይ የጥንቶቹ ከልባቸው መካሪ፣ ከአንጀታቸው አስተማሪ ናቸው፡፡ ልጅነታችንን ያነፁ፣ አዋቂነታችንን የቀረፁ፡፡ ሃዋሪያት ነበሩ፡፡ ዛሬም ናቸው፡፡ ነገም ለልጆቻችን በእኛ ውስጥ ይኖራሉ!
“እያንዳንዱ ደራሲ አንድ ሌላ መንግስት ነው!” የሚለው የቶልስቶይ አባባል እውነትነቱ፤ ደራሲ የህዝብ አይን በመሆኑ ላይ ነው፡፡ ሌላ መንግሥት ነው የሚለን፤ የነገ ህልውናችንን ጠቋሚና አመላካች በመሆኑ ነው! ነጋችን የዛሬ ጥንስሳችን በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የዛሬ እቅድ የሁሉም ወደፊት መሠረት  ማለት ነው፡፡ “አንድ ፀሐፊ Plagiarize the future” እንዳለው ነው ጉዳዩ፡፡  
የኢትዮጵያ ስልጣን “አልሰሜን ግባ በለው” የሚባል አይነት ነው፡፡ ጨከን ብለን ካሰብንበትም “የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው!” መባሉ እውነት አለው፡፡
“ሥልጣንንም የህዝብ ማገልገያ እንጂ የግል መጠቀሚያ እንዳናደርግ አንድም ህሊናችን፣ አንድም ህግ ሊያስገድደን ይገባል፡፡”ይሉናል ጠበብት፡፡
“Absolute Tower corrupts absolutely” ይላሉ፡፡ “ፍፁም ስልጣን ፍፁም ሌባ ያደርጋል” እንደማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ህግን መሠረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ግለሰቦች ወደ ግለሰባዊ ጥቅማቸው እንዳያተኩሩ መቆጣጠሪያው ህግ ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ግን  “ተቆጣጣሪዎቹን ማን ይቆጣጠራቸው?” የሚለውን በጥብቅ ማስተዋል ይገባል ማለት ነው፡፡ በተለይ እንደኛ ሀገር የበቃ የሰው ሃይል በበቂ ደረጃ በሌለበት፣ በቂ ማቴሪያልና አመቺ ሁኔታ ባልጠረቃበት ሁኔታ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” ይባል እንደነበረው ዛሬ ፣ሁሉም ነገር ወደ ልማት መባሉ አግባብነት አለው፡፡ “ጉዞችን ረጅም ትግላችን መራራ መባሉን እንደ አርቆ አስተዋይ አሳቢ ሁነኛ መርህ ነው እንደ እኛ አገር ባለ ኋላቀር ኢኮኖሚያዊ አቅም መሠረታዊና የማያወላዳ ለውጥን ለማምጣት፤ በሂደት ቀስ በቀስ መበልፀግ እንጂ በዕመርታ ማደግ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ ምኞትና ትጋት በቀላሉ አይጣጣሙም፡፡ ልማትን ልማት የማያደርጉ አያሌ ሳንካዎች አሉ፡፡ “የግድቡ ሙሌት የልባችን ሙሌት ነው”፡፡ ለማለት ብዙ የጥርጣሬ ጐርፍ ካናወጠን በኋላ የመጣ ነው፡፡ ተመስገን ነው! ከግል ስጋታችን ባሻገር የጐረቤቶቻችን አይን መቅላት፣ የሌሎች ሀገሮች የሩቅ ባላንጣነት ተጨማምሮ፣ ለብዙ አሉታዊ መላምት መዳረጉ ፀሐይ የመታው እውነት ነው፡፡
መቼም በደሀ ሀገር፣ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደሉምና፣ አልፎ አልፎ የሚያገረሹ የጐሣ ግጭቶች፣ የአልፀዱ ብሔር ብሔረሰቦች ፣የነገር ፈሪ ሴራዎች፣ ካልተባ አዕምሮ የሚመነጩ ስህተቶች ወዘተ ለለጋ እድገታችን ማነቆ መሆናቸው የሚታበል አይደለም ስለሆነም፤ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የሚችሉ ምሁራንን በበለጠ አሳምኖ በመጋበዝ፣ ከፍዝ ተመልካችነትና ከምንግዴ ዜግነት ወደ ንቁ ተሳታፊነት ማሸጋገር ዋና ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ ካላመጣን የየአቅጣጫውን ዘራፌነትና ምዝበራ ማስቆም ዘበት ይሆናል፡፡ የምሁራን አይነተኛ ሚና ጠቃሚ መሣሪያ የሚሆነውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ከሁሉ በፊት “የአባት ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚለውን አስተሳሰብ እንዲዋጉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የምንለው ለዚህ ነው፡፡   

Page 1 of 499