Administrator

Administrator


     የባህር ዛፍ ተክልን ከእንጦጦ ተራራ ላይ በማስወገድ በሀገር በቀል ዛፎች ለመተካት እስከ 2012 ዓ.ም የሚቆይ እቅድ የተያዘ ሲሆን ዘንድሮም ከ130 ሺህ በላይ የሀገር በቀል ዛፍ ችግኞች ይተካላሉ ተብሏል፡፡
ከዚሁ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የኢትዮ ቴሌኮም እና የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ ሰራተኞች ከትናንት በስቲያ በተራራው ላይ 200 ያህል ሀገር በቀል ዛፎችን የተከሉ ሲሆን ይህን ተግባርም ላለፉት 4 ዓመታት ሲተገብሩት እንደቆዩ ተገልጿል፡፡ በ4 ዓመታት ከተከሉት መካከል 80 በመቶው መፅደቁም ተገልጿል፡፡
የእንጦጦ ተራራ በአብዛኛው በባህር ዛፍ ተክል ተሸፍኖ እንደነበር ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የጉለሌ ክፍለ ከተማ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ደጀኔ ሙሉጌታ፤ ከ9 ዓመት በፊት ይፋ በተደረገው ባህር ዛፍን በሀገር በቀል የመተካት እቅድ አብዛኛው የተራራው ክፍል ከባህር ዛፍ ነፃ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ እስከ 2012 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ተራራውን ከባህር ዛፍ ነፃ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የባህር ዛፍ ቅጠር ሲረግፍ በቶሎ ወደ አፈርነት የመቀየር ባህሪ የሌለው በመሆኑ፣ በብዝሃ ህይወት ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል በመረጋገጡ ነው እንዲወገድ የተፈለገው ተብሏል፡፡ በተራራው ላይ የተለያዩ ተቋማት ሀገር በቀል ችግኞችን የሚተክሉት ይሄን ዓላማ ለማሳካት ሲሆን ከተቋማቱ ውስጥም ዜድቲኢ ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ደጀኔ ተናግረዋል፡፡

 ፕራይም ኮምፒውተር የተባለውና ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ የሆነው ኩባንያ፤ ከደምበኞቹ የሚቀርቡለትን የተቀናጡ ምርቶች ጥያቄ  ለመመለስ በማቀድ ያመረተውን በ18 ካራት ወርቅ የተሰራ አዲስ አይነት ዴስክቶፕ ኮምፒውተር ባሳለፍነው ሳምንት በ1 ሚሊዮን ዶላር፣ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ለገበያ ማቅረቡ ተዘግቧል፡፡
ሰባት ኪሎ ግራም በሚመዝን ንጹህ ወርቅ የተሰራው ይህ በአይነቱ ልዩ የሆነ ኮምፒውተር፤አምስት ቴራ ባይት ሃርድ ድራይቭ እንዳለው የዘገበው አይፒቲኔት፣ በተለያዩ ኦፐሬቲንግ ሲስተሞች እንደሚሰራና ከአምስት አመት ዋስትና ጋር ለሽያጭ መቅረቡንም አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ፕራይም ጎልድ የሚል ስያሜ የሰጠውንና በተወሰነ መጠን አምርቶ ለገበያ ያቀረበውን ይህን ኮምፒውተር፤ በቀጣይም ባልተለመደ ሁኔታ አሻሽሎ ለማዘመን እቅድ መያዙን የጠቆመው ዘገባው፤ ከእነዚህ ማሻሻያዎች መካከልም የኮምፒውተሩን የማብሪያና ማጥፊያ ቁልፍ፣ እጅግ ውድ ዋጋ ባለው የከበረ ድንጋይ መስራት እንደሚገኝበት አስረድቷል፡፡
በዱባይ ከዚህ ቀደምም ከወርቅ የተሰሩ የአፕልና የብላክቤሪ ምርቶች ለገበያ ቀርበው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በጁሜራህ የሚገኘው እና በአገሪቱ እጅግ ዝነኛው እንደሆነ በሚነገርለት ቡርጂ አል አረብ ሆቴል፣ ደምበኞቹ በቆይታቸው የሚጠቀሙበትን ባለ24 ካራት ወርቅ አይፖድ፣ በነጻ እንደሚሰጥም አመልክቷል፡፡

   ታዋቂው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ጆርጅ ክሉኒ እና ባለቤቱ አማል ክሉኒ በሊባኖስ የሚገኙ 3ሺህ ሶርያውያን ሰደተኛ ህጻናትን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል የበጎ ምግባር ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊያደርጉ ነው ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ጆርጅ ክሉኒና ባለቤቱ በጋራ ባቋቋሙት ፋውንዴሽን፣ ከጎግል ኩባንያ ጋር በፈጸሙት የጋራ ስምምነት፣ ሶርያውያኑን ስደተኛ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት፣ ከ2.25 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ እቅዳቸውን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል፡፡ የስደተኞች ትምህርት ፕሮጀክቱ፣ ህጻናቱ በሰባት ትምህርት ቤቶች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል፡፡
በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአገሪቱ ስደተኛ ህጸናት ከትምህርት ገበታቸው ውጭ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በሊባኖስ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሶርያውያን ስደተኞች እንደሚኖሩና ከእነዚህም መካከል 500 ሺህ ያህሉ ህጻናት እንደሆኑም አመልክቷል፡፡

   በአለማችን 200 ጨቅላዎች፣ የመንታቸውን ጽንስ አርግዘው ተወልደዋል

      ነገሩ በሳይንስ ፊክሽን ፊልም አልያም በልቦለድ ካልሆነ በገሃዱ አለም የሚከሰት ነው ብሎ ለማመን ቢያዳግትም፤ የእንግሊዙ ሚረር ግን በእርግጥም የሆነ ነው ይለዋል - ከሰሞኑ በህንድ የተከሰተውን አስደንጋጭ ክስተት፡፡
ዘገባው እንዳለው፤ የመውለጃ ቀኗ ሲቃረብ ከፍተኛ የህመም ስሜት የተሰማትና ለቅድመ ወሊድ ምርመራ ወደ አንድ ሃኪም ቤት ያመራችው የ19 አመቷ ህንዳዊት፤ መንታ ወንድሙን ያረገዘ ጨቅላ በቀዶ ህክምና ተገላግላለች፡፡
ጨቅላው 7 ሴንቲ ሜትር ያለውና ሙሉ የራስ ቅል፣ እጆች እና እግሮች ያሉትን መንታ ወንድሙን አርግዞ መወለዱን የጠቆመው ዘገባው፤ በተደረገለት ቀዶ ህክምና ጽንሱ እንደወጣለትና እሱም ሆነ እናቱ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
በመላው አለም እስካሁን ድረስ 200 ያህል ተመሳሳይ ክስተቶች መፈጠራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህ ክስተት ከአምስት ሚሊዮን ወሊዶች በአንዱ ብቻ የመከሰት እድል እንዳለው ሃኪሞች መናገራቸውን አስረድቷል፡፡

     ፍርድ ቤቱ፣ በወህኒ ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ የተቋቋመ ነው

      ባለፈው አመት በተሞከረውና በከሸፈው የቱርክ መፈንቅለ መንግስት ሴራ፣ እጃቸው አለበት ተብለው የተከሰሱ 500 ያህል ቱርካውያን ባለፈው ማክሰኞ በአገሪቱ እጅግ ግዙፉ እንደሆነ በሚነገርለትና በወህኒ ቤት ውስጥ በተቋቋመው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተከሳሾቹ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶጋንን ለመግደልና የከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አካል የነበረውንና ከአንካራ አቅራቢያ ከሚገኝ የአየር ሃይል ጣቢያ የተነሱ የጦር ጀቶች የአገሪቱን ፓርላማ የደበደቡበትን ጥቃት በማስተባበርና በማቀናጀት ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከተከሳሾቹ መካከል የቀድሞው የአገሪቱ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ አኪን ኦዝቱክር እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ አገር በመክዳትና በሽብርተኝነት የተከሰሱት ግለሰቡ፣ የቀረቡባቸውን ክሶች ተቃውመው መከራከራቸውን ገልጧል፡፡
ከ1 ሺህ በላይ በሚሆኑ ወታደሮች ታጅቦ በጥብቅ ክትትል የተከናወነው ችሎት፣ ወደተከናወነበት ግዙፍ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተከሳሾች፣ የተከሰሱባቸው የወንጀል አይነቶች የተለያዩ ቢሆኑም፣ አብዛኞቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በእድሜ ልክ እስራት ሊቀጡ እንደሚችሉ መነገሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የተከሳሾቹን ጉዳይ በመመርመር ላይ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ፤ በአገሪቱ ግዙፉ እንደሆነና 1 ሺህ 558 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ሲኒካን ውስጥ በሚገኝ ትልቅ ወህኒ ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ፣ ከመፈንቅለ መንግስት ጋር የተያያዙ ክሶችን ለማስተናገድ ብቻ ታስቦ በቱርክ መንግስት መቋቋሙንም አስረድቷል፡፡
የጠይብ ኤርዶጋን መንግስት ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ለእስር የዳረጋቸው ዜጎቹ ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ እንደሚሆን የጠቆመው ዘገባው፤ የጅምላ እስር እና ከስራ የማባረር እርምጃው፣የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከበርካታ አካላት ተቃውሞ እንዳጋጠመውም አስታውሷል፡፡

  ማላዊን ለአራት አመታት ያስተዳደሩት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ተመዝብሮበታል በተባለ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ሲሆን በአሜሪካ የሚገኙት ባንዳ ግን “ወንጀሉን አልፈጸምኩም፣ ወደ አገሬ ተመልሼ ንጽህናዬን አረጋግጣለሁ” ብለዋል፡፡
በእሳቸው የስልጣን ዘመን ተሰራ ከተባለው ሙስና ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንቷን ጨምሮ 70 የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎችና የመንግስት ሰራተኞች መከሰሳቸውን የዘገበው አልጀዚራ፤ በ2014 በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ወደ አሜሪካ በማቅናት፣ በአንድ የልማት ተቋም ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ጆይስ ባንዳ ግን፤ በስልጣን ዘመኔ እንዲህ ያለ አስጸያፊ ተግባር አልፈጸምኩም ሲሉ ውንጀላውን ማጣጣላቸውን አመልክቷል፡፡
በአሁነ ወቅት ለስራ ጉዳይ ባመሩበት ደቡብ አፍሪካ የሚገኙት ጆይስ ባንዳ፤ የአገሪቱ ፖሊስ የእስር ማዘዣ እንዳወጣባቸው መስማታቸውን ተከትሎ፣ ለሮይተርስ በስልክ በሰጡት መግለጫ፣ በስልጣን ዘመናቸው ሙስናን በትጋት የታገሉና የመጀመሪያውን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ያቋቋሙ፣ የመጀመሪያዋ የአገሪቱ መሪ እሳቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ወደ አገሬ ተመልሼ የሚመጣውን ሁሉ ለመጋፈጥ ዝግጁ ነኝ፤ ምንም የሚያስጠይቀኝ ነገር ስላልሰራሁ የሚያስፈራኝ ነገር የለም ብለዋል፡፡
የቀድሞዋ የማላዊ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ፣ በደቡብ አፍሪካ እያከናወኑት የሚገኙትን የበጎ ምግባር ተልዕኮ እንዳጠናቀቁ፣ ወደ አገራቸው በመመለስ፣ የፍርድ ቤት ምርመራ ሂደቱን እንደሚከታተሉ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

 አዲሱ አሰራር የህጋዊ ስደተኞችን ቁጥር በግማሽ ይቀንሳል ተብሏል

      ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባለፈው ረቡዕ በይፋ ድጋፋቸውን የሰጡት አዲሱ የአገሪቱ የህጋዊ ስደተኞች አቀባበል ስርዓት ረቂቅ አዋጅ፣ የሴኔት ድጋፍ አግኝቶ የሚጸድቅ ከሆነ፣ አሜሪካ የዲቪ ሎተሪ ዕድለኞችን ከመላ አለም መሰብሰቧን ትታ፣ በተለያዩ መስፈርቶች የላቀ ውጤትና ችሎታ እንዳላቸው የተረጋገጡ፣ የተመረጡ ስደተኞችን ብቻ በመቀበል የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት እንደምትጀምር ተዘግቧል፡፡
ኤንቢሲኒውስ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ ዕድልን ሳይሆን ችሎታን መሰረት ያደረገ የስደተኞች አቀባበልን ተግባራዊ ለማደረግ ታስቦ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ፤ በየአመቱ በህጋዊነት ወደ አሜሪካ የሚገቡ የተለያዩ የአለማችን አገራት ስደተኞችን ቁጥር በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ በግማሽ ሊቀንስ ይችላል ተብሏል፡፡
አዲሱ አዋጅ በሴኔት ጽድቆ እንደ ህግ በስራ ላይ የሚውል ከሆነ፣ ስደተኞችን የምትቀበለውና የመኖሪያ ፍቃድ የምትሰጠው በዕጣ እና በኮታ ወይም በዘመድ አዝማድ መጠራራት ሳይሆን የተለያዩ መስፈርቶች ተጠቅማ እየገመገመች ነው ያለው ዘገባው፤ከእነዚህ መስፈርቶች መካከልም የስደተኞቹ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ፣ የትምህርት ደረጃና ዕድሜ እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በቅጡ መደገፍ የሚያስችላቸውን አካላዊ ብቃት መያዝና፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ክህሎት ባለቤት መሆንም፣ በህጋዊነት ወደ አሜሪካ የሚገቡ የተለያዩ አገራት ስደተኞች፣ ከሚገመገሙባቸውና የመኖሪያ ፈቃድ ከሚያገኙባቸው ሌሎች መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሲኤንኤን በበኩሉ፤ ስደተኞችን ለመቀበልና የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠት መስፈርት የሚደረጉ መመዘኛዎችን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዝርዝር ዘገባ፣ ዕድሜው ከ26 እስከ 30 የሆነ፣ የሌሎች አገራት የመጀመሪያ ወይም የዶክትሬት ዲግሪ ያለው እና የእንግሊዝኛ ችሎታው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ስደተኛ፣ ወደ አሜሪካ የመግባትና የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት እድሉ እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
የኦሎምፒክ ሜዳይ ባለቤቶች ወይም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዎች የሆኑ የሌሎች አገራት ስደተኞችም፣ ከሌሎች በተለየ ወደ አሜሪካ የመግባትና የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት እድላቸው ከፍ ያለ እንደሚሆንም ዘገባው ገልጧል፡፡
በየአመቱ የመኖሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸውን ስደተኞች ቁጥር 50 ሺህ ለማድረስ ያለመውና ባለፈው የካቲት ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰምቶ ሲያወዛግብ የነበረው ረቂቅ አዋጁ፤ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በእጅጉ እንደሚደግፉትና ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ በይፋ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ እንደገና የውዝግብና የውይይት አጀንዳ መሆን መጀመሩንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ናሽናል ኢሚግሬሽን ፎረም የተባለው የአገሪቱ ቡድን በበኩሉ፤ በመጪዎቹ 3 አመታት ጊዜ ውስጥ የ7.5 ሚሊዮን ሰራተኞች ዕጥረት እንደሚገጥማት በተነገረላት አሜሪካ፤ከፍተኛ የሰራተኛ የሰው ሃይል ምንጭ የሆነውን የህጋዊ ስደተኞች ፍሰት የሚገታውን ይህን አዋጅ ማጽደቅ፣የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ የሚጎዳ አደገኛ እርምጃ ነው ማለቱን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ረቂቅ አዋጁ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኞች ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ነው ያለው ዘገባው፤ ረቂቅ አዋጁ እንደታሰበው በምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ የመዋል ዕድሉ እጅግ ጠባብ ነው እየተባለ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡

   ከፈረንሳይኛና ከሌሎች ቋንቋዎች ወደ አማርኛ የተመለሱ ከ20 በላይ አጫጭር ልቦለድ ታሪኮችን ያካተተው “የልብ ሽበትና ሌሎችም” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በተርጓሚና ደራሲ ሀይላይ ገብረ እግዚአብሔር የተተረጎመው ይሄው መፅሐፍ ያካተታቸው ታሪኮች ከዚህ ቀደም በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በተለያዩ መፅሄቶች ላይ የወጡና አዳዲስ ታሪኮችም ተጨምረውበት ለንባብ የበቃ መሆኑን ተርጓሚው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ በ2015 ገፆች የተመጠነው መፅሐፉ፤ በ68 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 የገጣሚ ሰለሞን ሞገስ (ፋሲል) አራተኛ ስራ የሆነው “የተገለጡ አይኖች” የግጥም መፅሐፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡ ከ75 በላይ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ግጥሞችን ያካተተው የግጥም መፅሐፉ፤ እጥር ምጥን ብሎ በ90 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ40 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡መፅሀፉ በ3ኛው “ንባብ ለህይወት” የመፃህፍት አውደርዕይ ላይ ለምረቃ ከበቁ 28 መፃህፍት መካከል አንዱ ነበር፡፡ ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ከዚህ ቀደም “እውነትን ሰቀሏት”፣ “ከፀሀይ በታች” እና “ፅሞናና ጩኸት” የተሰኙ የግጥም መድበሎች ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

   ‹‹የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች” የተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርትና የፓናል ውይይት ሊካሄድ ነው፡፡ የሙዚቃ ኮንሰርቱንና የፓናል ውይይቱን የሚያዘጋጀው “ሰለብሪቲ ኤቨንትስ” ባለፈው ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሁለቱን አገራት ህዝቦች የቀደመ ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ያግዛል ያለውን የሙዚቃ ድግስና የፓናል ውይይት የሚያካሂደው በቀጣዩ ዓመት ህዳር ወር ላይ ሲሆን በሙዚቃ ኮንሰርቱ ታዋቂና ዝነኛ የሁለቱ አገራት ድምፃውያን ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የታሪክ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የማህበረሰብ ሰራተኞች የመንግስትና የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በአጠቃላይ 800 ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን በሁለቱ አገር ህዝቦች የወደፊት ግንኙነት ላይ ይመካከራሉ ተብሏል፡፡ የኮንሰርቱና የፓናል ውይይቱ አላማ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ድንበርና ጥበቃ ሳይገድባቸው በችግር ጊዜ አብሮ የመቆምና የመደጋገፍ ባህልን እንዲያዳብሩ፣ እንዲሁም የቀደመ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር ያለመ መሆኑን የሰለብሪቲ ኤቨንትስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብቶም ገ/ስላሴ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የፓናል ውይይቱ በመጪው ህዳር 17 የሚካሄድ ሲሆን ኮንሰርቱ ህዳር 30 በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ በሙዚቃ ኮንሰርቱ ላይ በኢትዮጵያ በአራቱ መጠለያዎች የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችም ይታደማሉ ተብሏል፡፡