Administrator

Administrator

   መኖሪያቸውን ለንደን ባደረጉት ደራሲ ኤርሚያስ ሚካኤል (ሕርይቲ) የተፃፈው “የሚበርድ ፀሐይ” የተሰኘ የግጥም መድበል፤ ነገ ጠዋት ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ትንሷ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የተፃፉ 78 ግጥሞችን አካትቷል፡፡ በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን የግጥም ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ታዳሚያን በኮሜዲ ዝግጅቶች እንደሚዝናኑም የዝግጅቱ አስተባባሪ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንት የፕሬስ ስራዎች ድርጅት ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡

Saturday, 28 November 2015 14:11

የዘላለም ጥግ

(ስለ ጦርነት አስከፊነት)
• ኦ ሰላም! በስምሽ ስንት ጦርነቶች ታወጁብሽ።
አሌክሳንደር ፖፕ
• ጦርነት ጀብዱ አይደለም፡፡ በሽታ ነው፡፡ እንደ
ታይፈስ ዓይነት በሽታ፡፡
አንቶይኔ ሊ ሴይንት አክሱፔሪ
• ጦርነት እንደ ወንጀል መቆጠር አለበት፤
ቀስቃሾቹም እንደ ወንጀለኞች መቀጣት
አለባቸው፡፡
ቻርለስ ኢቫንስ ሁግስ
• ሰዎች አሁን ጦርነትን ማጥፋት ካልተሳካላቸው፤
ስልጣኔና የሰው ልጅ አከተመላቸው፡፡
ሉድዊግ ቮን ሚሴስ
• ጦርነት ለተሸናፊው ብቻ ሳይሆን ለአሸናፊውም
ጭምር ጐጂ ነው፡፡
ሉድዊግ ቮን ሚሴስ
• “እማዬ፤ ጦርነት ምንድን ነው?” ብሎ የሚጠይቅ
ህፃን ለመውለድ አልማለሁ፡፡
ኢቭ ሜሪያም
• አሜሪካ በ ሁሉም ነ ገር የ ዓለም መ ሪ መ ሆን
አለባት የሚለውን ሃሳብ ማስወገድ አለብን፡፡
ፍራንሲስ ጆን ማክኮኔል
• ጦርነቶችን የሚጀምሩት ወታደሮች አይደሉም፤
ፖለቲከኞች ናቸው፡፡
ጀነራል ዊሊያም ዌስትሞርላንድ
• ሰላም ከማስፈን ይልቅ ጦርነት መፍጠር በጣም
ቀላል ነው፡፡
ጆርጅስ ክሌሜንስዩ
• ጦርነት የፖሊሲ ክስረት ነው፡፡
ሃንስ ቫን ሲክት
• የታላላቅ መንግስታት ኃላፊነት ማገልገል እንጂ
ዓለም ላይ መግነን አይደለም፡፡
ሃሪ ኤስ. ትሩማን
• ለወታደራዊ ጀግንነት ትኩረት መስጠት
የፍልስፍና ድህነትን አመልካች ነው፡፡
ሄንክ ሚድልራድ
• በሰላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤
በጦርነት ዘመን አባቶች ልጆቻቸውን
ይቀብራሉ፡፡
ሔሮዱተስ

Saturday, 28 November 2015 14:09

የጸሐፍት ጥግ

(ስለ ፕሬስ)


• አንድ ሚሊዬነር 10 ጋዜጦች ስላሉት የፕሬስ
ነፃነት የተቀዳጀን ይመስለናል፡፡ 10 ሚሊዮን
ሰዎች ግ ን ም ንም ጋ ዜጦች የ ላቸውም - ይ ሄ
የፕሬስ ነፃነት አይደለም፡፡
አናስታስ ማኮያን
• በሌሎች አገራት ፕሬሱ፣ መፃህፍትና
ማናቸውም ዓይነት የሥነጽሑፍ ሥራዎች
ሳንሱር የሚደረጉ ከሆነ፣ እነሱን ነፃ ለማውጣት
ጥረታችንን እጥፍ ማድረግ አለብን፡፡
ፍራንክሊን ዲ. ሩስቬልት
• ሌላ ቦታ እንደተናገርኩት፤ ነፃ ፕሬስ አንድን
አገር ጠንካራና የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ
ያግዛል፤ እኛን መሪዎችንም የበለጠ ውጤታማ
ያደርገናል፤ ምክንያቱም ከፍተኛ ተጠያቂነትን
ይፈልጋል፡፡
ባራክ ኦባማ
• በእኔ አስተያየት፣ የዲሞክራሲ የማዕዘን ድንጋይ
ነፃ ፕሬስ ነው እሱ - ነው የማዕዘን ድንጋዩ፡፡
ሚሎስ ፎርማን
• ነፃ ፕሬስ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን
እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ግን
ያለ ነፃነት ፕሬሱ መጥፎ ከመሆን ውጭ ፈጽሞ
ሌላ አማራጭ የለውም፡፡
አልበርት ካሙ
• ነፃ ፕሬስ የተከበረ ፕሬስ መሆን አለበት፡፡
ቶም ስቶፓርድ
• የፕሬስ ነፃነት የተረጋገጠው የፕሬስ ውጤት
ባለቤት ለሆኑት ብቻ ነው፡፡
ኤ.ጄ ላይብሊንግ
• ፕሬሱን መገደብ ህዝብን መስደብ ነው፤
የተወሰኑ መፃሕፍት እንዳይነበቡ መከልከል
ነዋሪዎች ሞኞች ወይም ባሪያዎች ናቸው ብሎ
ማወጅ ነው፡፡
ክላውዴ አድሬይን ሄልቬቲየስ
• ጋዜጠኝነት የተደራጀ ሃሜት ነው፡፡
ኤድዋርድር ኤግልስቶን
• የዲሞክራሲ ጫጫታ ደስ ይለኛል፡፡
ጄምስ ቡቻናን
• ሚዲያ የባህላችን የነርቭ ሥርዓት ነው፡፡
ጌሪ ማልኪን

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አባት፣ ወንድ ልጁን ይዞ፣ አህያውን ለመሸጥ ወደገበያ እየሄደ ነበር፡፡ መንገድ ላይ የሆኑ ኮረዶች እየሳቁ እያላገጡ፣
“እንደነዚህ አባትና ልጅ ያሉት ጅሎች በዓለም ላይ ታይተው አይታወቁም፡፡ በዚህ አቧራማ ጎዳና አህያው ላይ ወጥተው እየጋለቡ መሄድ ሲችሉ፤ በእግራቸው ይኳትናሉ!” አሉ። አባትየው ኮረዶቹ ያሉት ልክ ነው ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ ልጁን አህያው ላይ አወጣውና እሱ በእግሩ መጓዝ ጀመረ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ የዱሮ ወዳጆቻቸው አዩዋቸው፡፡
እንዲህም አሉ፤
“ይሄን ልጅ በጣም አወማጠልከው፡፡ አንተን የሚያህል ሽማግሌ በእግሩ እየሄደ ይሄ ወጣት በአህያ መሄዱ ነውር ነገር ነው፡፡ “ኧረ በእግሩ ይሂድ፡፡ ወጣት ሮጠና አይደለም እንዴ?!”
አባት የዱሮ ወዳጆቹን ምክር ተቀበለ፡፡ ልጁን ና ውረድ ብሎ ሲያበቃ፣ በእሱ ቦታ ራሱ ፊጥ አለ፡፡ ብዙም ሳይሄድ እናቶችና ልጆቻቸው ብቅ አሉ፡፡ እነሱም፡-
“ምን ያለው ራስ - ወዳድ አባት ነው እባካችሁ! ራሱ ተዝናንቶ በምቾት እየጋለበ፣ ልጁን በእግሩ መከራ ያሳየዋል!” እያሉ ሲሳለቁ አባትየው ሰማ፡፡ ይሄንንም አመዛዘነና ትችቱን ተቀብሎ ልጁን ከጀርባው አፈናጠጠው፡፡
አሁንም ብዙም ሳይጓዙ መንገደኞች ያገኟቸዋል፡፡ እነሱም፤ “ለመሆኑ ይቺ አህያ የራስህ ንብረት ናት፤ ወይስ እንዲያው ከጫካ ያገኘሃት የዱር አውሬ ናት”
አባትየውም፤ “ኧረ የራሴ ናት! እንዲያውም እዚህ ታች ገበያ ልሸጣት አስቤ ነው የምሄደው”
“ኧረ የሰማያቱ ያለህ! እዚያ ስትደርስ‘ኮ አንደኛዋን ሞታ ነው የምትገኘው! ይልቁንም ተሸክማችሁ ብታደርሷት ነው የሚሻለው!
አባትየው - “ዕውነታችሁን ነው!” ብሎ ምክሩን ተቀብሎ ሁለቱም ወረዱና አህያዋን አሰሩዋትና በትልቅ እንጨት አንጠለጠሉ፡፡ ወደሚቀጥለው ከተማም ደረሱ፡፡
አባትና ልጅ አህያ ያንጠለጠሉበትን ትርዒት ያየ የከተማው ሰው ሁሉ፤ ግማሹ ዕብድ ናቸው አለ፡፡ ግማሹም በዱላ ይመቷቸው ጀመር፡፡ አህያውን ተሸክመው በወንዝ ላይ ወዳለው ድልድይ ሄዱ፡፡ አህያው የህዝቡ ጩኸት በእንግዳ ሆኖበት እየተንፈራገጠ፣ የታሰረበትን ገመድ በጠሰና ተስፈንጥሮ ወንዙ ላይ ወደቀ፡፡ በዚያው ሰምጦ ሞተ፡፡ ዕድለ ቢሱ አባት በመከራ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ሁሉንም ሰዎች አረካለሁ ብሎ አንዱንም ሰው ሳያረካ፤ አህያውንም አጥቶ ቀረ።
*           *            *
አማካሪን ሁሉ ከየአቅጣጫው እንዲያውም ተቃራኒውን ሀሳብ ጭምር፣ መስማትና መቀበል፣ ማታ ማንም ፍሬ ሳያፈራ እንዲቀር ያደርገዋል፡፡ በየጊዜው የሚለዋወጥ አቋም አንዱንም በወግ ለመያዝ ሳንችል እንድንቀር ያደርገናል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አንዱን በሥነ ስርዓት ለፍፃሜ ሳናበቃ ሜዳ ላይ እንድንወድቅ እንሆናለን፡፡ ዕቅደ ብዙ መሆን ብቻውን ከግብ አያደርስም፡፡ ይልቁንም ቅደም ተከተል አስይዘን፣ የከፋውን ችግር መጀመሪያ መፍታት፣ ምንም ይሁን ምን ችግርን አለመሸሸግ፣ በግልፅ ድክመትን ማመን፣ አለቃ እንዳይቆጣ ተብሎ እቅጩን አለመናገርን ማስወገድ፣ ሀገርን ከፓርቲ፣ ከቡድን ወይም ከግለሰብ ጥቅም ማስቀደም ወዘተ መልካም አካሄድ ነው፡፡ ከሁሉም ቁልፍ ነገር በዕውቀት ማመን ነው። በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የሀገር ግንባታ ርዕዩ ሩቅ ይሆናል፡፡ የተገነባው እንዳይፈርስ ባለቤት ሊኖረው እንደሚገባ አለመዘንጋት ነው፡፡ የተሰራው መንገድ፣ ባቡሩ፣ ግድቡ ወዘተ. በኃላፊነት የሚይዛቸው ከወራት የዘለለ ሀገር ወዳድነት ያለው አመራር ይሻሉ፡፡
ድርቁን እኛው በኛው እንመክተው ካልን ቁርጠኝነታችንን በውል መፈተሽ ደግ ነው፡፡ ምግብና ሌላ እርዳታ በአግባቡ መዳረሱን ለማየት ረዥም መንገድ ተጉዞ የደረሰው ባቡር “ላሜ ወለደች” ያሰኘን ቢሆንም፤ ቀጣዩ ተግባር ስኬታማ እንዲሆን ጠንቃቃ ትኩረት ይጠይቃል፡፡
የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ነገር ሁሌም አሳሳቢ እንደሆነ ነው፡፡ እንኳን ለአዘቦቱ ሰው፣ ለክቱ የኢኮኖሚክስ ባለሙያም አወዛጋቢና አነጋጋሪ ነው! ለኢኮኖሚው ዕድገት ችግር የሚሆነው የሰለጠነ የሰው ኃይል ማነስ ነው የሚሉ ያሉትን ያህል፣ የሰው ኃይል እጥረት አሳሳቢ አይደለም የሚሉም አሉ፡፡ መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉና ለጊዜው አያስፈልግም የሚሉም ይኖራሉ፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ሥርዓተ ኢኮኖሚ ስንሸጋገር፣ አይቀሬ ክስተት ይሆናል ሲባል የህዝብ ብዛት ፍንዳታ ምን መፍትሔ ይኖረው ይሆን ብሎ መጠየቅም ያባት ነው፡፡ የአገሪቱ የቅጥር ሁኔታም አሳሳቢ ስለመሆኑና ለውጥ ስለማስፈለጉ ብዙ እየተነገረ፣ “ቄሱም ዝም፤ ዳዊቱም ዝም” እንደሆነ አለ፡፡
አሁንም ከዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን አኳያ ቅደም  - ተከተል ማበጀት ወሳኝ ነው፡፡ ሳይታሰብ ቅድሚያ የተሰጠው፣ ግን ሊዘገይ ይችል የነበረ ጉዳይ ካለ፤ ቆም ብሎ መፈተሽ ተገቢ ነው። ባንድ ወቅት አሳሳቢ የመሰለን ችግር በሌላ ወቅት ቀላል ሆኖ ሊገኝ እንደሚችል ማስተዋል ያሻል፡፡ መሥሪያ ቤቶች “በጉዳይ - ገዳይ” እጅ ላይ እየተንሳፈፉ፣ ቀልጣፋ የሥራ አመራር አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ አገራችን “አንዱ ያለማ አንዱ ያደለማ” አጣብቂኝ ውስጥ ናት፡፡ በዚህ ዓይነት ወደፊት ፈቀቅ እያልን ነው ብንል የዋህነት ያለብን ያስመስላል፡፡ በየቢሮው የምናየውና በአደባባይ የምንሰማው መራራቅ የለበትም፡፡ አንዱ በታታሪነት ደፋ - ቀና ሲል ሌላው በዳተኝነት “ከልኩ አያልፍም” እያለ የምንጓዘው ጉዞ እየፃፉ እንደማጥፋት ነው፡፡ የሩቅ ዕቅዳችንንና የረዥም ጊዜ ራዕያችንን እያወደስን የቅርብ - የቅርብ ፍሬዎቻችንን በወጉ ሳንሰበስብ ከቀረን፣ ከአፍ እስከገደፉ የሞላውን ወሬ ነጋሪና ጉዳይ አስፈፃሚ በጊዜ ካልገደብን፤ “እሾክ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው” እንደሚባለው ነው የምንሆነው፡፡ ከልብ አገርን ማሳደግ የምንሻ ከሆነ፣ “ብዙ ከያዘ ነገረኛ፣ ትንሽ የያዘ ሀቀኛ ይስጥህ” የሚለውን ተረት ልብ እንበል!

      በአባይ ወንዝ አጠቃቀምና በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሳቢያ ለ5 ዓመት እየከረረና እየረገበ የዘለቀው የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት፤ ከሰሞኑ ትኩሳት አገርሽቶበታል፡፡
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲዘገይ ማድረግ እንችላለን በማለት እንደተናገሩ ሰኞ እለት የዘገቡ አልጀዚራና ምስር ጆርናል፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፤ “ግብፅ ኢትዮጵያን የመውረር አቅም የላትም” በማለት ምላሽ እንደሰጡ ፅፈዋል፡፡ ይህንን ሲዘግቡም፣ መረጃውን ያገኘነው ከአዲስ አድማስ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን፤ በየትኛው የአዲስ አድማስ እትም ዘገባው እንደወጣ ቀኑን አልጠቀሱም፡፡ በቅርብ ሳምንታት ካገረሸው ትኩሳት ጋር ተያይዞ፤ እንዲህ አይነት ዘገባ በአዲስ አድማስ ባይወጣም፤ የግብፅ መንግሥት፣ በግድብ ግንባታው ላይ ተቃውሞ ከማሰማት አልፎ ዛቻና ማስፈራሪያ እስከመሰንዘር እንደሚደርስ ግን በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቧል፡፡ የጦርነት ዛቻ ተቀባይነት እንደሌለውና እንደማያዋጣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ መግለፁም ይታወሳል፡፡ በተለይ አሁን፣ የግብፅ ትኩረት በኢኮኖሚ ፈተናዎችና በአሸባሪዎች ጥቃት ላይ መሆን ሲገባው፤ ወደ ጦርነት ዛቻ ማዘንበል እንደማያዋጣም ይገለፃል፡፡
በቅርቡ የህዳሴ ግድብ፣ በከፊል ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ውሃ የሚያጠራቅምበት ደረጃ ላይ መድረሱ የተዘገበ ሲሆን፤ የግብፅ መንግሥት በበኩሉ፤ የግድቡ ግንባታ ለ6 ወር እንዲቋረጥ ሊጠይቅ ይችላል የሚሉ መላምቶች ተሰንዝረዋል። ካሁን በፊትም በየጊዜው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ተሰንዝረው የነበረ ቢሆንም፤ የግድቡ ግንባታ ለአንድ ቀንም አይቋረጥም በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ 

Saturday, 28 November 2015 08:56

የቀልድ ጥግ

(በፍቺና ጥርጣሬ ዙሪያ)
ሚስት የቤተሰቡ ጠበቃ ዘንድ ትደውልና
በአስቸኳይ እንደምትፈልገው ትነግረዋለች፡፡
ጠበቃውም ያለችበት ሥፍራ ከመቅጽበት
ይደርስና ለምን እንደፈለገችው ይጠይቃታል፡፡
“ምን ገጥሞሽ ነው እንዲህ በአስቸኳይ
የፈለግሽኝ?”
“ከባሌ ጋር መፋታት እፈልጋለሁ” አለች እሳት
ለብሳ እሳት ጐርሳ፡፡
“ምነው ደህና አልነበራችሁ እንዴ?”
“የመጨረሻ ልጃችን አባት እሱ አይደለም የሚል
ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ” ብላው እርፍ!!
* * *
አዳም ያለ አመሉ ለተወሰኑ ቀናት ውጭ እያመሸ
በመግባቱ፣ ሄዋን ጥርጣሬ ቢጤ አደረባት፡፡
“እንዳትዋሸኝ…ከሌላ ሴት ጋር መቅበጥ ጀምረሃል
አይደል!?” ስትል ታፋጥጠዋለች፡፡
“የምን ሌላ ሴት ነው የምታወሪው? አንቺው ነሽ
ሌላ ማን አለ!” አዳም ግራ በተጋባ ስሜት መለሰላት፡፡
የዚያኑ ዕለት ሌሊት አዳም ጥልቅ እንቅልፍ ላይ
ሳለ፣ ሄዋን ደረቱ አካባቢ በጣቷ ስትጫነው ባንኖ
ይነሳና፤ “ምን እያደረግሽ ነው?” ይጠይቃታል፡፡
“ጐድንህን እየቆጠርኩ” መለሰችለት፡፡
(አዳም ምን ብሎ ይሆን?

12 ሄኮፕተሮችንና 4 ተዋጊ ጀቶችን ለመግዛት የተመደበ ገንዘብ በልተዋል ተብለዋል
    የቀድሞው የናይጀሪያ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሳምቦ ዳሱኪ የአገሪቱን አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሃራም ለመታገል ለተጀመረው ብሄራዊ ወታደራዊ ዘመቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት የተመደበውን 2 ቢሊዮን ዶላር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል የእስር ትዕዛዝ እንደተላለፈባቸው ቢቢሲ ዘገበ፡፡ግለሰቡ 12 ሄኮፕተሮችን፣ አራት ተዋጊ ጀቶችንና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ለመግዛት በተደረገው ድርድር በነበራቸው ተሳትፎ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ቢባሉም፣ እሳቸው ግን ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግለሰቡ እንዲታሰሩ ትዕዛዝ የሰጡት ሰሞኑን ቢሆንም፣ ግለሰቡ ግን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ይዘው በመገኘት ወንጀል ተከሰው በቁም እስር ላይ እንደነበሩና ጉዳያቸውን የያዘው ፍርድ ቤትም ፓስፖርታቸው ተመልሶላቸው ህክምናቸውን በእንግሊዝ እንዲከታተሉ ቢፈቅድላቸውም መንግስት ከአገር እንዳይወጡ እንደከለከላቸው ዘገባው ገልጧል፡፡
የፕሬዚዳንት ቡሃሪ ቃል አቀባይ፣ ግለሰቡ የሰሩት የሙስና ወንጀል በሺህዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች በአሸባሪው ቦኮ ሃራም ለሞት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል ማለታቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡ግለሰቡ በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ህጋዊ ስራ ሲሰሩ እንደነበር ገልጸው፣ ይሄን ያህል ገንዘብ በሙስና ለግል ጥቅማቸው አውለዋል፤የተጠቀሱት የጦር መሳሪያዎችም በአግባቡ ተገዝተው ለመንግስት አልደረሱም የሚለው ውንጀላ እንዳሳቃቸው ተናግረዋል፡፡

   አንድ ኪ. ሜትር ያሽከረከረ፣ 25 ሳንቲም ይሸለማል
    ማሳሮሳ የተባለችው የጣሊያን ከተማ ወደ ስራ ገበታቸው ሲጓዙ ከመኪና ይልቅ ብስክሌት የሚጠቀሙ ነዋሪዎቿን በወር እስከ 50 ዩሮ የሚደርስ ሽልማት እንደምትሰጥ ማስታወቋን ቢቢሲ ዘገበ፡፡የከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት፤ ብስክሌት ለሚጠቀም ነዋሪ በአንድ ኪሎ ሜትር 25 ሳንቲም ሂሳብ እየተሰላ ሽልማት እንዲሰጠው መወሰኑን የጠቆመው ዘገባው፣ አንደመነሻም ለ50 ሰራተኞች የአንድ አመት ሽልማት ለመስጠት ማሰቡንና በቀጣይም ሽልማቱን ለማስፋፋት ማሰቡን ገልጧል፡፡
በሽልማት መልክ የሚሰጠው ገንዘብ፣ ከትራፊክ ክፍያ ትኬት ከሚሰበሰበው የከተማዋ ገቢ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ የከተማዋ አስተዳደር ሽልማቱን ለመስጠት ያሰበው ብስክሌት መጠቀም የትራፊክ መጨናነቅን ያስቀራል፣ የጤና ጠቀሜታም አለው በሚል መነሻ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ባለፈው አመት በፈረንሳይ ተመሳሳይ የማበረታቻ ሽልማት መሰጠት ተጀምሮ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም የብስክሌት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከፍ አድርጎት እንደነበር አክሎ ገልጧል፡፡

አሜሪካ በ3 ወር ውስጥ ከ26 ሺህ 500 በላይ ተጠቃሚዎቼን መረጃ ጠይቃኛለች
     ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ፣ የተጠቃሚዎቹን የግል መረጃዎች አሳልፎ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁት መንግስታት ቁጥር እያደገ መሆኑን ማስታወቁን ሲኤንቢ ኒውስ ዘገበ፡፡
መሰል መረጃዎችን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከመንግስታት የሚቀርቡለት ጥያቄዎች ቁጥር በ2015 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ18 በመቶ ማደጉን የገለጸው ፌስቡክ፣ ባለፉት የጥር፣ የካቲትና መጋቢት ወራት ብቻ ከተለያዩ የአለም አገራት መንግስታት 41 ሺህ 214 ጥያቄ እንደቀረበለት አስታውቋል፡፡
የተጠቃሚዎቹን የግል መረጃ እንዲሰጡት ከጠየቁት መንግስታት መካከል የአሜሪካ መንግስት ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ የጠቆመው ፌስቡክ፣ የአሜሪካ መንግስት በሶስቱ ወራት ከ26ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፌ እንድሰጠው 17 ሺህ 577 ጥያቄዎችን አቅርቦልኛል ሲል ገልጧል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ህንድ 5 ሺህ 115፣ እንግሊዝ 3 ሺህ 384፣ ፈረንሳይ 2 ሺህ 520፣ ጀርመን 2 ሺህ 344 መሰል ጥያቄዎችን እንዳቀረቡለት ያስታወቀው ፌስቡክ፣ የምመራበት ፖሊሲ የተጠቃሚዎቼን የግል መረጃ አሳልፌ እንድሰጥ ስለማይፈቅድልኝ ጥያቄያቸውን አላስተናገድኩም ብሏል፡፡

 አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በፓሪስ ስድስት የተለያዩ አካባቢዎች የሰነዘረው የሽብር ጥቃት፣ 136 ያህል ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል፡፡ የመቁሰል አደጋ ከደረሰባቸው 352 ሰዎች መካከልም ከ100 በላይ የሚሆኑት ክፉኛ በመጎዳታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡የፈረንሳይ መንግስት፣ የአርቡን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በሽብር ድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የማፈላለግ ዘመቻ ጀምሯል፡፡ እስካሁንም አራት ያህል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሌሎች የሽብር ጥቃቶች ሊሰነዘሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረበት የፈረንሳይ መንግስት፣ የጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ይችላሉ ባላቸው የተለዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጨማሪ 1 ሺህ 500 ያህል ወታደሮችን አሰማርቶ፣ ጥብቅ ጥበቃ እያደረገ ይገኛል፡፡ በድንበር አካባቢዎችም የተለየና የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ ነው፡፡
የሽብር ጥቃቱ ካደረሰው ሰብአዊ ጥፋት በተጨማሪ በስደተኞችና በአገሪቱ የቱሪዝም መስክ ላይ የራሱ የሆነ ጉልህ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ  ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡
የስደተኞች ጉዳይ
የፓሪሱ ጥቃት ከፈረንሳይ አልፎ የመላ አውሮፓ ብሎም የሌሎች አገራት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ተጽዕኖውም ድንበር መሻገር ይዟል፡፡ ጥቃቱ የአውሮፓ አገራት የድንበር ላይ ቁጥጥርን ለማቆም ያሳለፉትን ውሳኔ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡ ይሄው ውሳኔ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በብዙዎቹ የአውሮፓ አገራት ተጥሷል፡፡ የጥቃቱ ዋነኛ ሰለባ ፈረንሳይ የድንበር ላይ ቁጥጥሯን እንደገና የጀመረች ሲሆን፤ ስዊድን፣ ጀርመንና ስሎቫኒያም የድንበር ላይ ቁጥጥራቸውን ከጥቃቱ አስቀድመው ዳግም አጠናክረው ጀምረዋል፡
የአውሮፓ አገራት በመካከላቸው ያለውን ድንበር ብቻም ሳይሆን፣ የአህጉሪቱን ድንበሮች ለሶርያና ለሌሎች አገራት ስደተኞች ወደ መዝጋት ተሸጋግረዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ፣አይሲስ ለሽብር የመለመላቸውን አባላቱን ከስደተኞች ጋር ወደ አውሮፓ አገራት እያስገባ ነው የሚል ነው፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ እንዳለው፤የፓሪሱ ጥቃት አውሮፓ በስደተኞች ላይ ያላትን አቋም እንድትቀይርና ትኩረቷን ስደተኞችን ከማቋቋም ወደ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንድትለውጥ እያስገደዳት ነው፡፡ በፓሪሱ ጥቃት ከተሳተፉት አሸባሪዎች አንዱ ወደ ፈረንሳይ የገባው በሶርያ ፓስፖርት መሆኑን የሚያሳይ መረጃ መገኘቱ በስፋት መነገሩን ተከትሎ፣ የአውሮፓ አገራት መሪዎች ድንበራቸውን አልፈው ወደ ግዛቶቻቸው የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ ክፉኛ እያስጨነቃቸው ነው ይላል ዘገባው፡፡
ሲቢኤስ ኒውስ በበኩሉ፤ የፓሪሱ ጥቃት በስደተኞች ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ከአውሮፓ አልፎ አሜሪካ መግባቱን ዘግቧል፡፡ ግማሽ ያህሉ የአሜሪካ ግዛቶች፣ የሶርያን ስደተኞች ወደ ግዛቶቻቸው ከመግባት የሚያግድ ውሳኔ ለማሳለፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ፖላንድ ከአውሮፓ ህብረት የደህንነት ዋስትና እስካልተሰጣት ድረስ፣ ከአሁን በኋላ ስደተኞች ወደ ግዛቷ እንዲገቡ እንደማትፈቅድ መግለጧን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ፓሪስ የቱሪስቶች መናኸሪያ ሆና ትቀጥል ይሆን?
ከአለማችን የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ፓሪስ፣ በዚህ አመት ብቻ ሁለት አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶችን አስተናግዳለች፡፡ ይህም የከተማዋን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ከመላ አለም ወደ ከተማዋ ለመጓዝ ያሰቡ በርካታ ቱሪስቶችንና የንግድ ጉዞ ለማድረግ ቀጠሮ የያዙ ኩባንያዎችን በድንጋጤ ክው አድርጓል፡፡
ፎክስ ኒውስ እንደዘገበው፤ ከአጠቃላዩ የአገር ውስጥ ምርቷ 7.4 በመቶ ያህሉን በቱሪዝም የምታገኘው ፈረንሳይ፣ በተሰነዘሩባት የሽብር ጥቃቶች ሳቢያ የቱሪዝም መስክ ገቢዋ እንደሚቀንስ እየተነገረ ነው፡፡የሰሞኑ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ወደ ፈረንሳይ ለመሄድ ተመዝግበው የነበሩ የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች ጉዟቸውን ሰርዘዋል፤ ፓሪስ ውስጥ የነበሩ ቱሪስቶችም በድንገተኛው ጥፋት ተደናግጠው ባፋጣኝ ከተማዋን ለቅቀው ወጥተዋል፡፡ ከጥቃቱ በኋላ ታዋቂውን ኤፍል ታወር ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ዋነኛ የቱሪስት መስህቦች እስከ አራት ቀናት ያህል ለጎብኝ ዝግ እንዲደረጉ መወሰኑ በአገሪቱ ቱሪዝም ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ ፕሬዚዳንት ሆላንዴ የአገሪቱ ድንበሮች እንዲዘጉ ማዘዛቸውም፣ ፈረንሳይ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ክፉኛ እንደሚጎዳውና ጥቃቱ በቀጣይም በአገሪቱ ቱሪዝም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ እንደማይቀር እየተነገረ ነው፡፡
ዘ ጋርዲያን ባለፈው ሰኞ ያወጣው ዘገባ ግን፣ የፓሪሱ ጥቃት የከተማዋንና የአገሪቱን ብቻ ሳይሆን የመላ አውሮፓን የጉዞና የሆቴል ዘርፍ ኢንቨስትመንት ክፉኛ እንደሚጎዳ ይገልጻል፡፡
የፓሪሱ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በነበሩት ሶስት ቀናት ብቻ፣ ጥቃቱ በመላው የአውሮፓ አገራት ቱሪዝምና በተጠቃሚዎች ላይ  ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት በኢንቨስተሮች ላይ በመፈጠሩ፣ የአህጉሪቱ የጉዞና የሆቴል ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከ2 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ አጥቷል ይላል ዘገባው፡፡
ሌሎች የሽብር ጥቃቶች ሊሰነዘሩ ይችላሉ የሚለው ስጋት እንዲሁም በድንበር ላይ ያለው ጥብቅ ቁጥጥር የመንገደኞችንና የንግዱን ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ሊያስተጓጉለው ይችላል ከሚለው ግምት ጋር ተዳምሮ፣ ኤር ፍራንስ - ኬኤልኤምን የመሳሰሉ አየር መንገዶች እንዲሁም ቶማስ ኩክን የመሳሰሉ ታላላቅ የጉዞ ወኪል ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጎታል ብሏል ዘገባው፡፡