Administrator

Administrator

    ያለፈው ዓመት ጥሩ የሚባሉ ስራዎችን የሰራሁበት ዓመት ነው፡፡ ሁለት ልጓሞቼን (ወርቅ በወርቅና፣ ሄሮሺማን) በቪሲዲ፣በዲቪዲ ለተመልካች ያቀረብኩበት ዓመት ነበር፡፡ የህዳሴውን ዋንጫም ይዘን ኢትዮጵያን የዞርኩበት ዓመት ነው፡፡ ዘመናዊ  ሲኒማ ቤትና የስፖርት ላውንጅ ግንባታም የጀመርኩበት ዓመት ነው፡፡ በብዙ መልኩ ለኔ ስኬታማ ዓመት ነበር፡፡
ቦሌ አካባቢ ያስገነባሁት ሲኒማ ቤት፣በአዲሱ ዓመት ሥራ ይጀምራል፡፡ መደበኛ ስራዎቹ እንደተጠበቁ ሆነው ሌላ አዲስ ፊልም የመስራት እቅድም አለኝ፡፡

   አንጋፋዋ ድምፃዊት አስቴር አወቀና ማዲንጎ አፈወርቅ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ዛሬ ምሽት  በጊዮን ሆቴል የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ፡፡ ከቀኑ 10፡30 ላይ የኮንሰርቱ መግቢያ በሮች እንደሚከፈቱ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ እዩኤል ልዑልሰገድ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤በኮንሰርቱ ላይ ድንገተኛ (surprise) እንግዳ የሚኖር ሲሆን እንግዳው 2 ወይም 3 ዘፈኖችን ያቀነቅናል፡፡ አስቴር በዋዜማው ኮንሰርት 25 ዘፈኖችን የምታቀርብ ሲሆን ማዲንጎ 8 ወይም 9 ዘፈኖችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡
የ2008 አዲስ ዓመትን ለመቀበል ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ የርችት ተኩስ ሥነስርዓት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ የVIP አቀማመጡ ከመድረኩ ፊት ለፊት መደረጉን የገለፁት አዘጋጆቹ፤ቲኬቶቹ ኤሌክትሮኒክ ስለሆኑ ግፍያ አይኖርም ብለዋል፡፡  

 የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከፖሊስ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመተባበር በነገው ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ልዩ የዓውዳመት የመዝናኛ ፕሮግራም ማዘጋጀቷን አስታውቋል፡፡ በእለቱ አጫጭር ድራማዎችን ጨምሮ ዘመናዊና ባህላዊ ዘፈኖች ከነውዝዋዜያቸው ይቀርባሉ፡፡ ፕሮግራሙን ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡30 በ30 ብር መግቢያ መታደም እንደሚቻል አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡

 “የአባባ ተስፋዬ ተረቶች የስዕል አውደ ርዕይ” ባለፈው ማክሰኞ በብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪ ተከፍቶ ለ4 ቀናት ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡ አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት አባባ ተስፋዬ፤በኔክስት ጄነሬሽን የበጎ አድራጎት ማህበር ህፃናትና ወጣቶች የተዘጋጀላቸው በሙካሽ የተጌጠ ካባ ተበርክቶላቸዋል፡፡ “በዓለም ላይ ብዙ አገራትን አይቻለሁ፤ሰርቶ ለመኖር እንደ ኢትዮጵያ የተመቸ አገር አላየሁም” ያሉት አባባ ተስፋዬ፤“አገራችሁንም ሥራንም ውደዱ፤እኔ አርቲስት ሆኜ እየሰራሁ  ሻሸመኔ ላይ በግብርና ሥራም ተሰማርቼ ነበር፡፡ ከግብርናው ባገኘሁት ትርፍም የራሴን ቤት ሰርቻለሁ፤መኪናም ገዝቻለሁ” በማለት የሥራን ጥቅም አስረድተዋል፡፡
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረገው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤“እኛ ዛሬ ላይ የደረስነው በቀደመው ትውልድ ታግዘንና ተረድተን ነው፡፡ ይህንን ውለታ ታሳቢ በማድረግ አባባ ተስፋዬን የሚዘክር መድረክ መሰናዳቱ መስፋፋትና መቀጠል አለበት” ብሏል፡፡
በአባባ ተስፋዬ ሳህሉ መኖሪያ ቤት ይዞታ ላይ ሊሰራ የታቀደው ቴአትር ቤትና የባህል ማዕከል ጋለሪ ህንጻ ዲዛይን በዕለቱ ቀርቦም ገለፃ ተሰጥቶበታል፡፡

 በብሩክ ከድር የተዘጋጀው “የአረቦች ፀደይ” የተሰኘ መፅሃፍ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ፣ የፕሮፌሰር እሸቱ ጮሌ መታሰቢያ አዳራሽ ተመርቋል፡፡
መፅሀፉ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀው ንቅናቄ ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅልና ሁለንተናዊ ገፅታውን ይዳስሳል፡፡
በ253 ገፆች በተቀነበበው “የአረቦች ፀደይ” መፅሃፍ ላይ አጭር ውይይት እንደተካሄደም ታውቋል፡፡

በጀምስ ሬድፊልድ “The Celestine Prophecy” በሚል ርዕስ ተፅፎ በደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ተብሎ የተተረጐመው መጽሐፍ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በ11 ሰዓት በዋቢሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ ለደራሲው አምስተኛ የትርጉም ሥራው ሲሆን በምረቃው ሥነስርዓት ላይ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችና ጥበብ አፍቃሪያን እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡

    በዓመቱ እስካሁን ያሳለፍነው መልካም ነበር፡፡ በስራ ነው ያሳለፍነው፡፡ ከአመት ወደ አመት የስራ አፈፃፀማችን እየተሻሻለ ነው፡፡ ሠራተኞቻችን ጤናቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ፣ እንዲማሩ ማድረጋችን፣ ተማሪዎችን ማስመረቃችን እንደቀጠለ ነው፡፡ በሌላ በኩል በየቦታው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የመፍታት ብቃታችን ከእለት ወደ እለት እየተሻሻለ ነው፡፡ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ረገድ ጥሩ ክንውን ነበረን፡፡
በቀጣይ አመት ደግሞ የጀመርናቸው የ8 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ወደ ውጭ መላክ ብቻ አይደለም ትልቅ የሚያደርገን ብለን ስለምናምን፣ ሀገር ውስጥ ያለውን ተጠቃሚ ፍላጐት ማሟላት መቻል አለብን፡፡ የሀገር ውስጥ ተጠቃሚው እያደገ ነው፡፡ ይሄን ፍላጐት ለማሟላት በአዲሱ አመት ጠንክረን እንሠራለን፡፡

  የስልጣን ዘመናቸውን 100ኛ ቀን ባለፈው ሳምንት ያከበሩት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ፤ በባንክ ሂሳብ ደብተራቸው ውስጥ ያለው ገንዘብ 100 ሺህ ፓውንድ ብቻ መሆኑን በይፋ መግለጻቸውን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ከዚህ ገንዘብ ውጭ ያላቸው ንብረት በጭቃ የተሰሩትን ሁለት ቤቶቻቸውን ጨምሮ አምስት የመኖሪያ ቤቶችና 270 ከብቶች ያሉበት የእርሻ ቦታ ብቻ መሆኑን እንደገለጹ የጠቆመው ዘገባው፤ሰውዬው ያላቸው ሃብት ከተራው የናይጀሪያ ህዝብ እጅግ የበዛ ቢሆንም፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ዜጎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የግል ሃብታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ከዚህ ቀደም አገሪቱን ሲመሩ ከነበሩና የህዝቡን ሃብት ወደ ካዘናቸው በማስገባት ከሚታሙ እጅግ ባለጸጋ ፕሬዚዳንቶች የተለዩ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው ተብሏል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፤ከቡሃሪ ሃብት 9 እጥፍ የሚበልጥ የ900 ሺህ ፓውንድ ባለቤት መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ቡሃሪ ስልጣን በያዙ ማግስት ከመንግስት ካዘና 100 ቢሊዮን ዶላር መንትፈው የግል ሃብታቸው አድርገዋል በሚል የሚታሙትን ሙሰኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በ1980ዎቹ የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ቡሃሪ፤በስልጣን ዘመናቸው ከሙስና የጸዱ መልካም ሰው እንደነበሩ የጠቆመው ዘገባው፣ናይጀሪያን ለአምስት አመታት ያህል አንቀጥቅጠው የገዙት አምባገነኑ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳኒ አባቻ በአንጻሩ 3 ቢሊዬን ፓውንድ ሃብት እንደነበራቸውና አብዛኛውን ገንዘባቸውን በስዊዝ ባንክ እንዳስቀመጡት አስታውሷል፡፡

     ፖሊስ በአይፎን ተጠቃሚ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ጀምሯል
             ማይክሮሶፍትም የወንጀል ተጠርጣሪን ኢሜል ባለመስጠቱ ተከሷል
   የአሜሪካ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከአደንዛዥ ዕጽ እና ከጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ ለምናደርገው ምርመራ የሚጠቅሙ የጽሁፍ መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠን አልፈቀደም ያሉት ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፤ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት የሚጣልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው መንግስትን መጠየቃቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የኤፍቢአይ እና የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ አፕል በሚያመርተው አይፎን አማካይነት ከሰዎች ወደ ሰዎች የተዘዋወሩ አጭር የጽሁፍ መልክቶችን ለወንጀል ምርመራ አሳልፎ አልሰጥም ብሎ በእምቢተኝነት በመጽናቱ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት ሲሉ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥያቄ ማቅረባቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ወንጀል መርማሪዎች የአፕል ምርት የሆነውን አይፎን በሚጠቀሙ የአደንዛዥ ዕጽ እና የጦር መሳሪያ ወንጀል ድርጊቶች ተጠርጣሪዎች ዙሪያ ለሚያደርጉት ምርመራ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው መናገራቸውም ተጠቁሟል፡፡
አፕል ከዚህ ቀደም ከፖሊስ ለቀረበለት ጥያቄ፣ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ የተላለፉበት አይሜሴጅ የተሰኘ የመልዕክት መላላኪያ ሲስተሙ ነባር መረጃዎችን የሚያጠራቅምበት ቋት የሌለው በመሆኑ የተጠየቀውን መረጃ ስለማያገኝ አሳልፎ መስጠት እንደማይችል ማስታወቁን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በተጠረጠረ አንድ ግለሰብ ዙሪያ ለሚደረግ የወንጀል ምርመራ ጠቃሚ የሆኑ የኢሜይል መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠው ባለመፍቀዱ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር የፍርድ ቤት ክርክር እያደረገ እንደሚገኝም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

አሜሪካዊው ታዋቂ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን፤ያለ ፈቃዴ ዝናዬን ተጠቅሞ ሃብት አፍርቷል ባለው አንድ ኩባንያ ላይ ለመሰረተው ክስ በካሳ መልክ እንዲከፈለው በፍርድ ቤት የተወሰነለትን 8.9 ሚሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሊለግስ እንደሆነ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የ52 አመቱ ጆርዳን፤ሴፍዌይ የተባለው የአሜሪካ የምግብ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ፣ ሳያስፈቅደኝ ምስሌን ለምርቶቹ ማስታወቂያ ተጠቅሟል፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል በሚል የመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት፤ 8.9 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ወስኗል፡፡
ቺካጎ ውስጥ የተሰየመው ችሎት፤ውሳኔውን ማሳለፉን ተከትሎ ጆርዳን ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፤ጉዳዩ ክብርን የማስጠበቅ እንጂ በካሳ ገንዘብ የማግኘት አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ኩባንያው የሚሰጠውን 8.9 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚያውለው አስታውቋል፡፡ ነዋሪነቷ በኒውዮርክ ኢስት ሀምፕተን የሆነው አሜሪካዊቷ ሚሊየነር ሌስሊ አን ማንዴል በበኩሏ፤4 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣው እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ለምታረባቸው 32 ወፎች፣ 100 ሚሊየን ዶላር ማውረሷን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሚሊየነሯ በፈረመችበት ህጋዊ የውርስ ሰነድ ላይ፣ ወፎቼ ጎጇቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ እየተጸዳላቸውና ከሱፐርማርኬት ደረጃቸውን የጠበቁ ጣፋጭ ኬኮች፣ ካሮትና ፈንድሻ እንዲሁም የተጣራ ውሃ እየተገዛላቸው በአግባቡ እየተመገቡ እንዲኖሩ እፈልጋለሁ ብላለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 ሊዎና ሄልምስሌ የተባለች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማረች አሜሪካዊት ሚሊየነር ለአንድ ውሻዋ 12 ሚሊየን ዶላር ማውረሷንም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡