Administrator

Administrator

  የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከ2.32 ቢሊዮን በላይ ደርሷል ከ35 ሺህ በላይ ቋሚ ሰራተኞች አሉት

     እ.ኤ.አ በ2004 በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ውስጥ በማርክ ዙከርበርግ የተጠነሰሰውና በተማሪዎች መካከል ትስስር ለመፍጠር ታስቦ እንደዋዛ የተጀመረው የአለማችን ቁጥር አንድ ማህበራዊ ድረ-ገጽ የሆነው ፌስቡክ የተመሰረተበትን 15ኛ አመት ባለፈው ሰኞ ያከበረ ሲሆን፣ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከ2.32 ቢሊዮን በላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
በ2004 ላይ በሰባት ሰራተኞች ብቻ ስራ የጀመረውና በስኬት ጎዳና ተጉዞ ከአለማችን ቀዳሚ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አንዱ ለመሆን የበቃው ፌስቡክ በአሁኑ ወቅት ከ35 ሺህ በላይ ቋሚ ሰራተኞች እንዳሉትም ኩባንያው አስታውቋል፡፡
በየቀኑ የሚጠቀሙት ደንበኞች ቁጥር 1.5 ቢሊዮን የደረሰለት ፌስቡክ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ 55 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እና 22 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን የዘገበው ሲኤንኤን፣ ያም ሆኖ ስኬቱ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ እንደነበር አስታውሷል፡፡
የ34 አመቱ ማርክ ዙከርበርግ የሚመራው ፌስቡክ ዋትሳፕንና ኢንስታግራምን በድምሩ 20 ቢሊዮን ዶላር በመግዛት የራሱ ካደረገ በኋላ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በተለየ ሁኔታ እንደጨመረም አመልክቷል፡፡
የሁለት ልጆች አባትና የሆነውና 119 ሚሊዮን የፌስቡክ ተከታዮች ያሉት የኩባንያው መስራች ማርክ ዙከርበርግ ከአለማችን ስመጥር ቢሊየነሮች አንዱ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ አጠቃላይ የተጣራ ሃብቱ 62.4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንም ገልጧል፡፡


    በሱዳን መንግስት ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካርቱም የሚያስተምሩ 300 ፕሮፌሰሮችና ከ200 በላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት ተቃውሞ፤ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በአፋጣኝ ስልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ አንጋፋው እንደሆነ በሚነገርለት የካርቱም ዩኒቨርሲቲ ቅጽር ግቢ ውስጥ ባለፈው ረቡዕ በተከናወነው ሰላማዊ ሰልፍ፤በፕሬዚዳንቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰሮችና መምህራን ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ ለሶስት አስርት አመታት አገሪቱን ያስተዳደሩትና ህዝቡን ለከፋ ኑሮ የዳረጉት ፕሬዚዳንት አልበሽር፣ በአፋጣኝ ስልጣን እንዲለቁና የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡
በሱዳን ፕሮፌሽናሎች ማህበር አስተባባሪነት የተካሄደው የተቃውሞ ትዕይንት፤እስካሁን ድረስ በአገሪቱ ከተደረጉት ተቃውሞዎች ሁሉ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅሙ ከፍ ያለ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ላለፉት ስድስት ሳምንታት ያህል ተቃውሞ በርትቶባቸው የቆዩትን አልበሽር፤ አደጋ ውስጥ ይጥላቸዋል ተብሎ መሰጋቱን አመልክቷል፡፡
በሱዳን ተባብሶ በቀጠለው ተቃውሞ እስካሁን ድረስ 40 ያህል ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን፣ አክቲቪስቶችንና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውንም ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ብሔራዊ የስለላና የደህንነት አገልግሎት ተቋም ባለፈው ማክሰኞ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ዜጎች በሙሉ እንዲፈቱ ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወሰው ዘገባው፤ የተፈቱ እስረኞች ስለመኖራቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም ብሏል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018፣ የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለመግባት ጉዞ ከሚያደርጉ ስደተኞች መካከል በየቀኑ በአማካይ ስድስቱ ለሞት እንደተዳረጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳለው፣ በ2018 ብቻ 2 ሺህ 275 የተለያዩ አገራት ስደተኞች ሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው በመጓዝ ላይ እያሉ ለሞት ተዳርገዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ ባለፈው ማክሰኞ በጅቡቲ የቀይ ባህር ዳርቻ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን አሳፍረው በመጓዝ ላይ የነበሩ ሁለት ጀልባዎች ሰጥመው 130 ያህል ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ስድስት አመት ሊሞላው የ3 ወራት እድሜ በቀረው የስልጣን ዘመናቸው በድምሩ ለ92 ጊዜያት ያህል ወደ ውጭ አገራት መጓዛቸው፣ በአገሪቱ ተቃዋሚዎች ዘንድ መተቸቱን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በሚያዝያ 2013 ወደ ስልጣን የመጡት ኡሁሩ፤ በስልጣን ዘመናቸው ወደ ውጭ አገራት ካደረጓቸው 92 ጉዞዎች መካከል አብዛኞቹ ያን ያህል ጥቅም የሌላቸው ናቸው በሚል የሚተቹ ቢኖሩም፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ፕሬዚዳንቱ ያደረጓቸው ጉዞዎች ዲፕሎማሲን በማጠናከርና አገሪቱ በአለማቀፍ መድረክ ያላትን ቦታ ከፍ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ናቸው ሲል አስተባብሏል፡፡  
አንዳንድ የአገሪቱ ተቃዋሚዎችና የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው፤በተለይ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የሚጓዙ ልዑካን በርካታ ቁጥር ያላቸው ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ አገሪቱን ላላስፈላጊ ወጭ ዳርጓታል በሚል ትችታቸውን እንደሰነዘሩ ዘገባው አስነብቧል፡፡ ኡሁሩ ኬንያታ ባለፉት ስድስት አመታት ውስጥ ወደ ውጭ አገራት ያደረጉት ጉዞ፣ ከቀድሞው የአገሪቱ መሪ ሙዋይ ኪባኪ በ3 እጥፍ ያህል እንደሚበልጥ የጠቆመው ዘገባው፤ ኪባኪ በ10 አመታት የስልጣን ዘመናቸው ወደ ውጭ አገራት የተጓዙት 33 ጊዜ ያህል ብቻ መሆኑን አስታውሷል፡፡
ኡሁሩ አብዛኛዎቹን ጉዞዎች ያደረጉት ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ቢሆንም፣ ወደ አውሮፓ ለ12፣ ወደ አሜሪካ ለ4፣ ወደ ቻይና ለ4፣ ወደ ህንድ ለ2 እንዲሁም ወደ ሌሎች የአለም አገራት አንድ አንድ ጊዜ ያህል መጓዛቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የ2018 የዓለም አገራት የሙስና ሁኔታ አመላካች ሪፖርት፤ ሶማሊያ በአመቱ እጅግ የከፋው ሙስና የተፈጸመባት አገር መሆኗን ያስታወቀ ሲሆን ኢትዮጵያ በሙስና ከ180 የአለማችን አገራት 140ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በ180 የአለማችን አገራትና አካባቢዎች ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ተቋሙ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ የሙስና ሪፖርት እንዳለው፤ ከሶማሊያ በመቀጠል የከፋ ሙስና የተፈጸመባት የአለማችን አገር ሶርያ ስትሆን ደቡብ ሱዳን በሶስተኛ ደረጃ ትከተላለች፡፡
በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ አነስተኛው ሙስና የተፈጸመባት አገር ዴንማርክ ስትሆን፣ ፊንላንድ፣ ሲንጋፖር፣ ስዊድንና ስዊዘርላንድ በቅደም ተከተላቸው መሰረት በአነስተኛ የሙስና መጠን እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት ሙስናን በመዋጋት ረገድ ውጤታማ አለመሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ባለፉት ሰባት አመታት ሙስናን ለመቆጣጠር ባከናወኗቸው ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ የቻሉት የአለማችን አገራት 20 ብቻ መሆናቸውንና ከእነዚህ አገራት መካከልም አርጀንቲናና አይቬሪኮስት እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
በአለማችን እጅግ ሙሰኛ መንግስታት ያሉበት አካባቢ ከሰሃራ በታች ያሉት የአፍሪካ አገራት ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤ የከፋ ሙስና ካለባቸው 10 አገራት መካከል አምስቱ ከሰሃራ በታች የሚገኙ መሆናቸውንና በእነዚህ አገራት ሙስናን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረትም ትርጉም ያለው ውጤት ሊያስመዘግብ አለመቻሉን ይገልጻል፡፡
ሲሼልስ፣ ቦትሱዋና፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ሩዋንዳና ናሚቢያ እንደ ቅደም ተከተላቸው በአፍሪካ አህጉር አነስተኛ ሙስና የተፈጸመባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት መሆናቸው ተነግሯል፡፡

 አፕል በአይፎን ዋጋ ላይ ቅናሽ ሊያደርግ እንደሚችል ተነግሯል


     ላለፉት ተከታታይ አመታት በአለማቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የዘለቀው የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ፤ ያለፈውን የፈረንጆች አመት 2018 በቀዳሚነት ማጠናቀቁን ካናሊስ የተባለው የስማርት ፎን ገበያ የጥናት ተቋም አስታውቋል፡፡
ካናሊስ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፤ በ2018 የፈረንጆች አመት አለማቀፍ የስማርት ፎን ገበያ ውስጥ የ21.2 በመቶ ድርሻ የያዘው ሳምሰንግ በአመቱ 293.7 ሚሊዮን የተለያዩ ሞዴል ያላቸው የሞባይል ስልኮቹን ለመሸጥ ችሏል፡፡
ተፎካካሪው አፕል ኩባንያ በበኩሉ፤ በአመቱ 212.1 ሚሊዮን የአይፎን ስልክ ምርቶቹን በመሸጥና በአለማቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ውስጥ የ15.3 በመቶ ድርሻን በመያዝ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ያስታወቀው ተቋሙ፤ በአመቱ 206 ሚሊዮን የሞባይል ምርቶቹን ለመሸጥ የቻለው የቻይናው ሁዋዌለ፤ በ14.8 በመቶ የገበያ ድርሻ በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
ሳምሰንግ በገበያ ድርሻና በሽያጭ ከአፕል ቢበልጥም የሁለቱም ኩባንያዎች ሽያጭና አመታዊ እድገት ግን ከአምናው መቀነሱን  የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ሁዋዌ በበኩሉ በሽያጭና በአመታዊ እድገት ከአምናው ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጧል፡፡ በተያያዘ ዜናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገቢው በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰበት የመጣው አፕል ኩባንያ፤ በአንዳንድ አገራት ለገበያ ባቀረባቸው የአይፎን የስማርት ፎን ምርቶቹ ዋጋ ላይ ቅናሽ ሊያደርግ እንደሚችል ፍንጭ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አፕል ከአይፎን ሽያጭ የሚያገኘው ገቢ ባለፉት ሶስት ወራት በ15 በመቶ ያህል እንደቀነሰበት ያስታወሰው ዘገባው፣ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ ከሰሞኑ ባደረጉት ንግግር፣ በአንዳንድ አገራት የአይፎን መሸጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ ሊደረግ እንደሚችል መረጃ መስጠታቸውን ገልጧል፡፡
የአፕል አጠቃላይ ገቢ ባለፈው አመት ከነበረበት የ5 በመቶ ቅናሽ በማሳየት፣ 84.3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ ኩባንያው ለገቢው መቀነስ በምክንያትነት ከጠቀሳቸው ጉዳዮች መካከል በቻይና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ መፈጠሩ ይገኝበታል ብሏል፡፡


             “ሠላምና መረጋጋት ሳይፈጠር የሚደረግ ምርጫን እንቃወማለን”

    ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ አራት ወራትን ያስቆጠረው የ50 አመቱ የዕድሜ ባለፀጋ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፤ ራሱን በአዲስ መልክ እያደራጀ እንደሚገኝ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ መርሻ ዮሴፍ ይናገራሉ፡፡ ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም የሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተል ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ያብራሩት ሊቀመንበሩ፤ ባለፉት አራት ወራት ሲያከናውናቸው በነበሩ ሥራዎች፣ በመጪው ምርጫ፣ በአገሪቱ የለውጥ እርምጃ ወዘተ-- ዙሪያ የአፍታ ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ


    ኢህአፓ ወደ ሀገር ቤት ከገባ ከ4 ወራት በላይ አስቆጥሯል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን  አከናወነ?
እስካሁን ሁለገብ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ ዋናው ስራችን የምንለው ኢህአፓን እንደገና የማደራጀት ስራ ነው፡፡ ኢህአፓ እንደሚታወቀው፣ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የመጀመሪያው ነው፤ በ1964 ዓ.ም ነው የተመሠረተው፡፡ ባለፉት ዘመናት ብዙ ታግሎ ያታገለ ፓርቲ ነው፡፡ 17 አመት በደርግ፣ 27 አመት በወያኔ ስር ህገ ወጥ ሆኖ፣ ከሀገር የተባረረ ድርጅት ነው፡፡ ሀገር ውስጥ ይታገድ እንጂ  በውጪ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በህቡዕ ሲንቀሳቀስ ነበረ፡፡ ከመጣን በኋላ በተለይ ከቀድሞ አባላት ውስጥ በህይወት ያሉትን እያገኘን እያሰባሰብን ነው፡፡ ጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ አድርገን፣ የአዲስ አበባ የኢህአፓ ኮሚቴን በይፋ አቋቁመናል፡፡ ዘጠኝ የአመራር አባላት ተመርጠዋል፡፡ በዚያኑ እለት ጐንደር ላይ የኢህአፓ ኮሚቴ ተመስርቷል፡፡ ከዚያ በፊት ደሴ ላይ፣ ባህርዳር፣ አርባምንጭ፣ ባሌ ጐባ፣ ሃዋሣ---አባላት እንደገና እየተደራጁና ኮሚቴም እያቋቋሙ ነው ያሉት፡፡ ይህን የፖለቲካ ማደራጀት ስራ እየሠራን ጐን ለጐን፣ ከህብረ ብሄራዊ  የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት፣ የጀመርናቸው  የትብብር ውይይቶች አሉ፡፡
ከእነማን ጋር ነው የትብብር ውይይት እያደረጋችሁ ያላችሁት?
እሱ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ቢገለጽ ይሻላል። ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር ግን ንግግር እያደረግን ነው፡፡ ከቀሩት የብሔር ድርጅቶች ጋር ግን ሰፋ ያለ ግንኙነት አድርገን ሀገራዊ የፖለቲካ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበትን ተሞክሮ እያጋራን ነው፡፡ በጠ/ሚኒስትሩ አነሳሽነት በተጀመረው የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ውይይት መድረክ ላይም ተሳታፊ ነን፡፡ በሌላ በኩል፤ ይህቺ ሀገር ሠላምና መረጋጋት እንዴት ነው የምታገኘው? ህዝቡ በመረጠው ቦታ ያለ ምንም መሳቀቅ መኖር የሚችለው እንዴት ነው? የሚለው በጣም ስለሚያስጨንቀን፣ የሠላምና መረጋጋት ጉዳይ ቅድሚያ እንዲያገኝ፣ በሁሉም መድረኮች እየወተወትን ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንገብጋቢ ጉዳይ፣ ምርጫ ሳይሆን ሠላምና መረጋጋት ነው፡፡ ሀገሪቱ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት እስከሌለ ድረስ ሮጦ ምርጫ ውስጥ መግባት ምንም ጥቅም አያመጣም፡፡ ስለዚህ ሠላምና መረጋጋት ሳይመጣ፣ ሁሉም ዜጋ ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ሳይፈጠር፣ ወደ ምርጫ መሄድ የበለጠ ቀውስን መጋበዝ ነው፡፡
በዚህ ሰዓት ወደ ምርጫ ሂደቱ መግባት፣ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ በምርጫው ላይ ስለሚያደርግ  አንፃራዊ ሠላም ያስገኛል የሚሉ ወገኖች አሉ -----፡፡
እንደውም በምርጫ ወቅት ሁሉም ከሌላው በልጦ የራሱን ሃሳብ ለማስበለጥ በሚፍጨረጨርበት ወቅት የበለጠ ለግጭት በር ይከፍታል ባይ ነን፡፡ ለምን ከተባለ? አሁንም በማህበረሰባችን ውስጥ መረጋጋትና ነገሮችን በሠከነ መንገድ የማየት ልማድ ገና አልዳበረም። አንዳንድ ቦታ እኮ አሁንም “አትግቡብን፤ ይሄ የእናንተ ቦታ አይደለም፤ የኛ ብቻ ነው” እየተባለ ነው፡፡ ይሄ የክልል ፖለቲካ የፈጠረው መከፋፈል፣ መጠራጠርና እርስ በእርስ የመቧደን ነገር እልባት ሳያገኝ ወደ ምርጫ መግባቱ የበለጠ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡
በበርካታ አካባቢዎች አባላትን እያደራጀን ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሂደት የገጠሟችሁ ተግዳሮቶች አሉ?
እስካሁን የገጠመን የከፋ ችግር የለም፡፡ ላለፉት 27 አመታት ህወሓት ህዝቡን ለብጥብጥ የማዘጋጀቱን ያህል ችግር እያጋጠመ አይደለም። ወጣቱ ትውልድ፣ በየቦታው፣ በዘርና በጐሣ ስለተከፋፈለ፣ በፖለቲካው ላይ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደ ድሮው አይነት ጠንካራና ዘላቂ የፖለቲካ ተሣትፎ በወጣቱ በኩል አላየንም፡፡ ይሄ በተወሰነ የማደራጀት ስራ የሚለወጥ ይመስለናል፡፡
ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመዋሃድ አላሳባችሁም?
ውህደት የሚፈጠረው የአላማ አንድነት ሲኖር ነው፡፡ የሚስማማንን ካገኘን እንዋሃዳለን፤ አሁን ግን ጥድፊያ ውስጥ አንገባም፡፡ በመጀመሪያ ድርጅቱ በሁለት እግሩ ቆሞ፣ የራሱን አባላት አሰባስቦ፣ የራሱን የፖለቲካ ማንነቱን አሳውቆ፣ ተጠናክሮ ከወጣ በኋላ፣ ከሌሎቹ ጋር የመዋሃድ ጉዳይ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህ እስኪሆን ግን ውህደት አይፈጠርም፡፡
በመጪው አገራዊ  ምርጫ ትወዳደራላችሁ?
በሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ተፈጥሮ፣ ምርጫ ከተካሄደ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሳተፍ እንችላለን፡፡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት ሳይኖር ምርጫ የሚደረግ ከሆነ አንሳተፍም፡፡ ሠላምና መረጋጋት ሳይፈጠር የሚደረግን ምርጫም በግልጽ እንቃወማለን፡፡ እኛን የሚያሳስበን በምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን መያዝ ሳይሆን በዋናነት የሀገሪቱና የህዝቦቿ ሠላምና መረጋጋት ነው። ምርጫ ምርጫ የሚሆነው፣ ህዝቡ በነፃነት፣ ከስጋት በፀዳ፣ ፍፁም ሠላማዊነት እየተሠማው ሲሳተፍ ነው፡፡ ተቋማት እንደገና ነፃ ሆነው መደራጀት አለባቸው፡፡ በተቋማት ነፃነት ላይ ፍፁም መተማመን መፈጠር አለበት፡፡ ይሄ ነው ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራት የሚገባው፡፡ እንጂ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ አድርጐ ስልጣን መቀራመት አይደለም ቁም ነገሩ፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስትን የለውጥ እርምጃዎች እንዴት ታዩታላችሁ?  
እኛ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ የለውጥ (ሪፎርም) መንግስት ተግባራትን በሙሉ እናደንቃለን፡፡ ጥሩ እቅድና ጥሩ ጅምር ነገሮች አሉት፡፡ ሁሉም ጥሩ እቅዶች በተግባር መሟላት አለባቸው፡፡ ምናልባት መሰናክሎቹ በዝተውባቸው ሁሉንም አቅዶች አልተገበሩ ይሆናል፡፡ እኛም ሁሉንም ነገር በአንዴ አንጠብቅም፡፡ እስካሁን ድረስ አካታች የሆኑ የእርቅና የሠላም ስራዎች ግን በበቂ እየተሠሩ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለን የምናስበው፡፡
ፓርቲያችሁ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቧል?
ኢህአፓን ህጋዊ ለማድረግ እንድንችል የድጋፍ ፊርማ እያሰባሰብን ነው፡፡ እኛ መጠነ ሠፊ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ ካሟላን በኋላ እንመዘገባለን፡፡ አሁን በስፋት ወጣቶችን ጭምር ወደ ፓርቲው እያሰባሰብን ነው፡፡ ፓርቲውን፣ መሠረቱን በሀገር ውስጥ የማጠናከር ሥራ እየሠራን ነው፡፡
የምትከተሉት ርዕዮት  ዓለም ምንድን ነው?
ሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምን ነው የምንከተለው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ በጣም አስፈላጊ ነው ብለን የምናምንበት ርዕዮት ዓለም ነው፡፡ ተሣክቶልን ይሄን ርዕዮት ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ካመጣነው ትምህርት በነፃ፣ ህክምና በነፃ፣ በዋናነት የማህበራዊ ዋስትና ጉዳይ ላይ ብዙ እንሠራበታለን፡፡ የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል ታሣቢ ያደረገ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ በብዙ ሀገሮች ተፈትኖ ያለፈ ርዕዮት ስለሆነ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ርዕዮተ ዓለም ስር  ወጣቶችን በስፋት እናሳትፋለን፡፡




 ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ጅብ በረት እየገባ ጊደር እየበላ፣ ጥጃ ነክሶ እየወሰደ፣ ሰፈር እያመሰ፤ እጅግ አድርጎ ያስቸግራል፡፡
አባትና ልጅ ይህን ጅብ የሚገድሉበትን ጊዜ ለመወሰን ይወያያሉ፡፡
አባት፤
“ለምን አንድ ሌሊት አድፍጠን ሲመጣ አናቱን በጥይት ብለን አንገድለውም?”
ልጅ፤
“አባዬ እንደሱ አይሆንም፡፡ ድንገት ከሳትነው ጦሱ ለእኛም ይተርፋል፡፡ በዛ ላይ በየትኛው ሌሊት እንደሚመጣ አናውቅም”
አባት፤
“ታዲያ ሌላ ምን መላ አለ ብለህ ነው?”
ልጅ፤
“ለምን አናጠምደውም?”
አባት፤
“ጅብ እንዴት ይጠመዳል ልጄ?”
ልጅ፤
“ጅብ መቼም ሥጋ ይወዳል፡፡ ስለዚህ አንድ ሙዳ ሥጋ በገመድ አስረን ጠመንጃችን አፈ- ሙዝ ላይ አድርገን፣ የገመዱን ጫፍ ቃታው ላይ እናስረዋለን፡፡ ጅቡ ሥጋውን ሊበላ ሲጎትት፣ ቃታውን ይስበውና ይገላገላል!”
አባት፤
“በጣም ቆንጆ ዘዴ ዘየድክ”
 በተስማሙበት መሰረት፤ ስጋውን አፈ-ሙዙ ላይ ገጠሙና ገመዱን ቃታ ላይ አስረው፤ ጅቡ ይመጣበታል ብለው በሚጠረጥሩት አቅጣጫ አስቀመጡት፡፡
አባት፤
“በል እንግዲህ ልጄ ጅቡን ጠብቅና፣ የምስራቹን መጥተህ አሰማኝ፡፡ እኔ አረፍ ልበል።” ብሎ ሄደ፡፡
ልጅ ሲጠብቅ ቆየ፡፡ ጅቡ መጣና በመጨረሻ ሲሮጥ፣ አባቱ ወዳለበት ቤት መጣና፤
“አባዬ፤ አባዬ፤ ጉድ ሆነናል፡፡”
አባት፤
“እንዴት? ምን ተፈጠረ?”
ልጅ፤
“ጅቡ፤ ጠመንጃችንን በኋላ በኩል ነክሶ እየጎተተ ይዞት ሄደ!”
አባት፤
“ኧረ ልጄ! እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው!” አለ፡፡
*   *   *
ያጠመድነው ሁሉ ይሳካል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው! ያቀድነው ሁሉ ምን ተግዳሮት ወይም ተገዳዳሪ እንቅፋት እንዳለበት አለማመዛዘንም አጉል ገርነት ነው፡፡ ባላንጣዎቼ ይተኙልኛል ብሎ ማንቀላፋትም አጉል ሞኝነት ነው፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “እንቅልፍ ነው የሚያስወስድህ” በሚለው ግጥሙ፤
“ትቻቸዋለሁ፤ ይተዉኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተውኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
የተወጋ በቅቶት ቢተኛ የወጋ መች እንቅልፍ አለው?
የጅምሩን ካልጨረሰው…”
ማለቱን ልብ እንበል፡፡
ለሥራም፣ ለእርምጃም፣ ለለውጥም እንንቃ፣ እንፍጠን፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ለምንም ነገር አይረፍድም፡፡ የጥንቶቹ ሚሲዮናዊያን የታሪክ ፀሐፍት፤ “Ethiopia slept a hundred years, forgetful of the world by whom it was forgotten” ይሉናል። (ኢትዮጵያ የረሳትን ዓለም ረስታ ለመቶዎች ዓመታት ተኝታ ነበር፤ እንደማለት ነው፡፡) ማንቀላፋታችን ዕውነት ነው፡፡ አሥራ ሰባት ዓመት፣ ሃያ ሰባት ዓመት እየተባባልን ዛሬም ጊዜ እየፈጀን እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ተለወጠ የምንለውን ሥርዓት በማወደስም ሌላ ጠፊ- ጊዜ አለማባከን ደግ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡ ዋናው የዳበረ ዕውቀትና የበለፀገ ዕውነት ሊኖረን ተገቢ መሆኑ በጭራሽ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ባለሙያዎቻችን፣ ሹመኞቻችን፣ መሪዎቻችን፣ የጊዜ አጠቃቀማቸውን በጥሞና ማወቅና በጠንቃቃ መልኩ መገልገል ይገባቸዋል፡፡ “ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” ይላል ሎሬት፡፡
“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድም ጊዜ ታክሲ አይደለም
አይጠብቅም ቆሞ” ----- የሚባለውም ለዚሁ ነው!


    በ1987 የኢፌዴሪ ህገመንግስት ሲረቀቅ ወሳኝ ሚና የነበራቸው የመጀመሪያው የኢህአዴግ ዘመን መንግስት አፈጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ስነሥርዓት ዛሬ ይፈፀማል፡፡
ሃገራቸውን በአፈ ጉባኤነትና አምባሳደርነት ያገለገሉት ዳዊት ዮሐንስ፤ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ሐምሌ 17 ቀን 1983 ዓ.ም ሲመሠረት በህግ ቋሚ ኮሚቴና በህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1987 እስከ 1998 ድረስም በሁለት ዙር የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ በመሆን ለአስር አመታት በም/ቤቱ ቆይተዋል፡፡ አምባሳደር ዳዊት ዮሐንስ የቀድሞ ብአዴን የማዕከላዊ ኮሚቴና አስፈፃሚ አባል በመሆንም ሀገሪቱን በከፍተኛ የስልጣን እርከን ከመሩ ባለስልጣናት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ የተወለዱት አምባሳደር ዳዊት ዮሐንስ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን እንዲሁም ሁለተኛ ድግሪያቸውን ከአምስተርዳም ዩኒቨርስቲ በህግ አግኝተዋል፡፡  በ63 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት አምባሳደር ዳዊት ዮሐንስ፤ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የነበሩ በህክምና ሲረዱ በቆዩበት አሜሪካን ሀገር ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ሻምበል ለገሠ አስፋው የቀብር ስነሥርዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
በ76 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ሻምበል ለገሠ አስፋው፤ በአለም ገና መስከረም 21 ቀን 1935 የተወለዱ ሲሆን፤ ሀገራቸውን በውትድርና በመንግስት አመራር አገልግለዋል፡፡ ሻምበል ለገሠ አስፋው የ4 ሴት ልጆችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆኑ አራት የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡

 አፍሪኤዥያ ባንክ፣ የ2018 የአፍሪካ ቀዳሚ አስር ሃብታም ከተሞችን ዝርዝር በቅርቡ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሃብቷ 276 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው የደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ተቋሙ በአፍሪካ 23 ከተሞች የሃብት መጠን ላይ ያደረገውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባወጣው ሪፖርት መሰረት፣ ሌላኛዋ የደቡብ አፍሪካ ከተማ ኬፕታውን፣ በ155 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሃብት፣ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘች ሲሆን የግብጽ መዲና ካይሮ በበኩሏ፣ በ140 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሃብት፣ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
የናይጀሪያዋ ሌጎስ በ108 ሚሊዮን ዶላር፣ የደቡብ አፍሪካዋ ደርባን በ55 ቢሊዮን ዶላር፣ የኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በ54 ቢሊዮን ዶላር፣ ሉዋንዳ በ49 ቢሊዮን ዶላር፣ ፕሪቶሪያ በ48 ሚሊዮን ዶላር፣ ካዛብላንካ በ42 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የጋና ዋና ከተማ አክራ በ38 ቢሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን የሃብት ደረጃ መያዛቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የተቋሙ ጥናት ደግሞ፣ በአፍሪካ አህጉር የግለሰቦች ሃብት አጠቃላይ ድምር በአመቱ 2.3 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህ የሃብት መጠን በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ የ34 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 3.1 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመልክቷል፡፡