Administrator

Administrator

ከግብጽና ከአልጀሪያ ቀጥላ በአፍሪካ 3ኛ ናት

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ  አገራት ጠንካራ ወታደራዊ ሃይል በመገንባት የመጀመሪያውን ስፍራ እንደምትይዝ በ“ግሎባል ፋየር ፓወር” የተሰራ ጥናት አመለከተ፡፡
 “ግሎባል ፋየር ፓወር” 40 ያህል የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም የአገራትን ወታደራዊ አቅም ለመፈተሽ  የሰራው አዲስ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 182 ሺህ ያህል በስራ ላይ የሚገኙ ወታደሮች ያሏት ሲሆን  ከ24 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎቿም በውትድርና መስክ ለመሰማራት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡
ከ560 በላይ ታንኮችና ከ780 በላይ የወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ያሏት ኢትዮጵያ፣ በአህጉሩ ጠንካራ ከሚባሉ አየር ሃይሎች የአንዱ ባለቤት መሆኗን የሚጠቅሰው ጥናቱ፣ አየር ሃይሉ ከ81 በላይ የጦር አውሮፕላኖችና 8 ተዋጊ ሂሊኮፕተሮች እንዳሉትም ገልጿል፡፡
አገሪቱ ለመከላከያ የምትመድበው አመታዊ በጀት 340 ሚሊዮን  ዶላር መድረሱን የጠቆመው ጥናቱ፣ ኢትዮጵያ ከግብጽና ከአልጀሪያ ቀጥላ በአፍሪካ አህጉር ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ያላት ሶስተኛዋ አገር ናት ብሏል፡፡

የማስተር ፊልምና ኮሙኒኬሽን ማሰልጠኛ ተቋም የቀድሞ ተማሪዎች የፎቶግራፍ ስራዎች አውደ ርዕይ የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ በ10፡30 በብሔራዊ ትያትር አርት ጋላሪ ይከፈታል፡፡ በአውደ ርዕዩ በአስራ ሶስት የፎቶግራፍ ባለሞያዎች የተነሱ ፎቶግራፎች የሚቀርቡ ሲሆን አውደ ርዕዩ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ ድረስ ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ የማስተር ፊልምና ኮሙኒኬሽን ማሰልጠኛ ተቋም ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዜብ ከበደ ገልፀዋል፡፡

Monday, 07 April 2014 16:00

33ኛው “ግጥም በጃዝ”

ረቡዕ ይካሄዳል
33ኛው የ“ግጥም በጃዝ” ምሽት የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል አዳራሽ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ ግጥሞች፣ ወጎችና ዲስኩር በሚቀርብበት ዝግጅት፤ አርቲስት ግሩም ዘነበ፣ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ፣ ምንተስኖት ማሞ፣ በረከት በላይነህ እና ሚሊቲ ኪሮስ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ የመግቢያው ዋጋ በነፍስወከፍ 50 ብር ነው።

በፊልም ባለሙያዋ መቅደስ በቀለ (ማክዳ) ደራሲነትና ዳይሬክተርነት ተሰርቶ በኤራሶል ፊልም ፕሮዳክሽን የሚቀርበው “ሊነጋ ሲል” የተሰኘ አዲስ ፊልም በቅርቡ ለእይታ ሊበቃ ነው፡፡ የፊልሙ ዘውድ ፍቅር ድራማ ሲሆን በ “ባለታክሲው” ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የተወነው ሚኪያስ መሐመድ፣ ታዋቂዋ ተዋናይት ማህደር አሰፋ፣ ቃል ኪዳን አበራ፣ ቢንያም በቀለና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ተዋንያኖች ተውነውበታል፡፡ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 11 ወራት የፈጀ ሲሆን በሚያዝያ ወር በግል ሲኒማ ቤቶችና በብሔራዊ ትያትር እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችና የዩቶፒያ ክለብ አባላት፤ በቢዝነስና በስራ ፈጠራ መስክ ለስኬት በማነሳሳት የሚታወቁ ሰዎችን በመጋበዝ አነቃቂ ፕሮግራም አዘጋጁ፡፡ ለአርብ መጋቢት 28 ልዩ ዝግጅት የተመረጠው ቦታ የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች በተጨማሪ የ“ባለራዕይ ቶክሾው” ባለቤት ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል እና ዶ/ር ወረታው በዛብህ እንዲሁም የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በእንግድነት ተጋብዘዋል፡፡ ውጤታማው የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው እንዲሁም ታዋቂ አርቲስቶች ግሩም ኤርሚያስ እና ሰለሞን ቦጋለ እንደተጋበዙም አዘጋጆቹ ገልፀው፤ ተማሪዎችን ለቢዝነስና ለስራ ፈጠራ በማነሳሳት መልካም ስነ-ምግባርን የሚያላብስ ዝግጅት ነው ብለዋል፡፡

በአንተነህ ግርማ ተፅፎ በኪሩቤል አስፋው ዳይሬክት የተደረገው ‹‹ፍቅር ሲመነዘር›› ፊልም ነገ በ11ሰዓት በሀርመኒ ሆቴል በቀይ ምንጣፍ ሥነ ሥርዓት ይመረቃል፡፡ የ1ሰዓት ከ42 ደቂቃ ርዝመት ያለው ‹‹ፍቅር ሲመነዘር››፤ ሮማንስ ኮሚዲ ፊልም ሲሆን፤ በነገው ዕለት በኤድናሞልና በሀርመኒ ሆቴል እንደሚመረቅ ካም ግሎባል ፒክቸርስ አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ‹‹አማላዩ››፣ ‹‹ስውሩ ሰይፍ››፣ ‹‹በራሪ ልቦች››፣ ‹‹ሼፉ››፣ ‹‹ወደ ገደለው›› እና ‹‹አማረኝ›› የተባሉ ፊልሞችን ሰርቶ ለእይታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

መርሴ ሐዘን ወ/ቂርቆስ “ትዝታዬ፤ ስለ ራሴ የማስታውሰው (1891-1923) በሚል ርዕስ የህይወት ታሪካቸውን የተረኩበት መጽሐፍ ላይ ነገ ውይይት ይካሄዳል፡፡ በብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ፣ ከቀኑ 8 ሰዓት አንባቢዎች እንዲገኙለት የግብዣ ጥሪውን ያስተላለፈው ሚዩዚክ ሜይዴይ፤ የውይይት መነሻ ሃሳብ በአቶ መኮንን ተገኝ እንደሚቀርብ ገልጿል፡፡”

በኤርትራዊው ሠዓሊ ሰለሞን ኣብርሓ የተዘጋጁ ሥዕሎች የሚቀርቡበት ያልታ የ“ዕይታ” የሥዕል አውደርዕይ ባለፈው ማክሰኞ በጣልያን የባህል ማዕከል የተከፈተ ሲሆን በነገው ዕለት እምደሚዘጋም ታውቋል፡፡ በኤርትራዊው ስደተኛ የተሳሉ በርካታ ሥእሎች የተካተቱበት አውደርዕይ ዓላማ “የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝቦችን በማቀራረብ ወደ አንድነት ለማምጣት የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማበርከት ነው” ብሏል፤ ሰዓሊው፡፡ሠዓሊው ካሁን ቀደም በኤርትራ የደቀመሃሪ መንደፍራ እና ሳዋ ከተሞች ሽልማት ባስገኙለት የሥዕል ትርኢቶች አውደርዕዮች ለይ መሳተፉን ለማወቅ  ተችሏል፡፡

Monday, 07 April 2014 15:56

ህልመኛው ክንፈኛ

ከትከሻዬ ጫፍ ግራና ቀኝ ካለው፣
ጉቶ የመሳሰለ ብቅ ያለ መሰለኝ፣
ይኸ እንግዳ ነገር እጅጉን ገረመኝ፡፡
የህልም ነገር ሆኖ መች አድሮ መች ውሎ፣
አየሁታ ወዲያው ጉቶው ክንፍ አብቅሎ፡፡
ወደፊት ወድሬ ሁለቱን እጆቼ፣
እግሬን ወደ መሬት ወደታች ዘርግቼ፣
በእነዚህ ረጃጅም ሰፋፊ ክንፎቼ፣
ከፍ ከፍ ወደ ላይ፣
ወዲያ ወደ ሰማይ!
አየሩን ቀዝፌ፣
ሄድሁ ተንሳፍፌ፡፡
ዕድሜዬን በሙሉ መሬት ተጣብቄ፣
አንድ ሜትር እንኳ ከፍ ያላልሁ ርቄ፣
ይኸው አየሩ ላይ ቀጨሁት ዓለምን፣
ያከራርመውና ዕድሜ ይስጥልኝ ህልሜን፡፡
እያደር ግን ኋላ ስካነው መብረሩን፣
ልክ እንደ ጭልፊቷ ሽው እልም ማለቱን፣
ጅው ብዬ ወርጄ ልክ እንደ የሎሱ፣
ወይ እንደ ድራጎን ያየር ላይ ንጉሱ(ሡ)፣
ይመስለኛል ያሰብሁ ልመካ በክንፌ፣
ያሻኝኝ ለመውሰድ ከመሬት ጠልፌ፡፡
አንዳንዱን ክፉ ሰው ላጥ አደርገውና፣
አንጠልጥዬ ወደ ላይ ርቄ እወስደውና፣
እንደ ሥራው መጠን ከድንጋይ ዓለቱ፣
ከጥልቅ ውቅያኖስ አልያም ከጅረቱ፣
ለቅቄ ስተወው ላይመለስ ከቶ፣
እረካለሁ መሰል ሳየው ሲቀር ሞቶ፡፡
ደግሞም ሆዳሙን ሰው ብድግ አደርግና፣
ፊቱን ወደ መሬት ዘቅዝቄ አይና፣
እጥለው መስሎኛል ጭው ካለው መሬት፣
አራዊት አምባ ምድር ሰው ከማይኖርበት፡፡
ይኸ ባለጌውን አለብላቢት ምላስ፣
የባጡን የቆጡን ቀባጥሮ የሚላላስ፣
ሳያስበው ድንገት ሁለት እጁን ይዤ፣
ከሰዎች መካከል ይህን ሰው መዝዤ፣
ወደ ላይ ወስጄው እዚያ ላይ አምጥቄ፣
ያዝ ለቀቅ አድርጌው ነፍሱን አስጨንቄ፣
ለቅቄ ስተወው ከላይ ደመናው ጥግ፣
ወደ ታች ወረደ ሄደ ሲምዘገዘግ፡፡
የሞተ መሰለኝ ምላሱን ጎልጉሎ፣
ብረት ምሰሶ ላይ በልቡ ተተክሎ፡፡
ሃይ የሚል የሌለው ከልካይም ተቆጪ፣
እኔው ራሴ ሆኜ ፈራጅ ዳኛ ቀጪ፣
ክንፎቼ እንዳይረግፉ እየለመንሁ ዕድሜ፣
እየቀጣሁ አለሁ ባለጌውን በህልሜ፡፡
ደግሞስ ማን ደርሶብኝ እንዴት ተነክቼ፣
ሽው ነው ወደ ላይ እብስ በክንፎቼ፡፡
ይህን ህልም እያየሁ ሳልነሳ ካልጋ፣
ሌቱ በረዘመ ጨርሶ ባልነጋ፡፡
ምን እንደ ህልም አለ፣ ከቶ ሌላ የለም፤
ህልመኛው ክንፈኛ አድራጊ ፈጣሪ …
        የሆነበት ዓለም፡፡
ይዘቱም መጠኑም የተስተካከለ፣
እንደዚህ እንደኔው ያለመ ሰው ካለ፣
ወደኔ ብቅ በሉ ሰማችሁኝ ሰዎች?
በጉዳዩ እናውራ የሌት አላሚዎች፡፡
በዝርዝር እንንገር ይህንን ሁኔታ፣
ምስጢሩን ገላልጦ ህልም ለሚፈታ፡፡
    ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
የካቲት 2006 ዓ.ም

Monday, 07 April 2014 15:55

የፍቺ ነገር!

በአሜሪካ
በፍቺ የሚጠናቀቁ ጋብቻዎች የሚቆዩበት አማካይ ጊዜ 8 ዓመት ነው፡፡
ሰዎች ፍቺ ከፈፀሙ በኋላ እንደገና ለማግባት በአማካይ ለሶስት ዓመት ይጠብቃሉ፡፡
ጥንዶች የመጀመሪያ ፍቺያቸውን የሚፈጽሙበት አማካይ ዕድሜ 30 ዓመት ነው፡፡
ወላጆቻችሁ ስኬታማ ትዳር የነበራቸው ከሆነ ለፍቺ የመጋለጥ ዕድላችሁ በ14 በመቶ ይቀንሳል
ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር የፍቺን ዕድል 40 በመቶ ይጨምራል፡፡
ኮሌጅ የተማራችሁ ከሆናችሁ፣ ለፍቺ የመጋለጥ ዕድላችሁ 13 በመቶ ይቀንሳል፡፡
ከአሜሪካ ህፃናት ገሚሱ የወላጆቻቸው ትዳር ሲፈርስ ይመለከታሉ፡፡ ከእነዚሁ ህፃናት ግማሽ ያህሉ የወላጆቻቸው ሁለተኛ ጋብቻ ሲፈርስም ያያሉ፡፡
ኦክላሆማ ከፍተኛ ፍቺ የሚፈፀምባት ግዛት ስትሆን ከግዛቷ ያገቡ አዋቂዎች መካከል 32 በመቶው ፍቺ ፈጽመዋል፡፡
ዛሬ በአሜሪካ ካሉ ህፃናት ውስጥ 43 በመቶው ያለአባት ነው የሚያድጉት፡፡