Administrator

Administrator

Saturday, 19 March 2016 11:12

የፀሐፍት ጥግ

- ረዥም ልብወለድ ስፅፍ እያንዳንዱ ቃል የራሴ
ነው፡፡ ከአርታኢዬ ሃሳቦች እቀበላለሁ፤ የመጨረሻ
ውሳኔዎቹ ግን የእኔ ናቸው፡፡
ሉዊስ ሳቻር
- ሁልጊዜ መፃፍ የምጀምረው በንፁህ ብጣሽ
ወረቀትና በቆሻሸ አዕምሮ ነው፡፡
ፓትሪክ ዴኒስ
- ፀሃፍት ሁለቴ ነው የሚኖሩት፡፡
ናታሊ ኮልድበርግ
- ለፃፍከው ነገር ጥብቅና መቆም በህይወት
ለመኖርህ ምልክት ነው፡፡
ዊሊያም ዚንሴር፣ ደብሊውዲ
- አንድ ሺህ መፃህፍትን አንብብ፤ ያኔ ቃላቶች እንደ
ወንዝ ይፈሱልሃል፡፡
ሊሳ ሲ
- ፀሃፊ የሰው ልጅ ነፍስ መሃንዲስ ነው፡፡
ጆሴፍ ስታሊን
- አርታኢ፤ ስንዴውን ከገለባ የሚለይና ከዚያም
ገለባውን የሚያትም ሰው ነው፡፡
አድላይ ኢ.ስቲቨንሰን
- አርታኢ ወይም ጋዜጠኛ መሆን ነበር የምፈልገው፤
ነጋዴ የመሆን ፍላጎት አልነበረኝም፤ ነገር ግን
መፅሄቴን በህትመት ለማቆየት ነጋዴ መሆን
እንዳለብኝ ተረዳሁ፡፡
ሪቻርድ ብራንሰን
- ፀሃፊ ወይም ካርቱኒስት በትክክል ምን
እንደሚሰማው ለማወቅ ከፈለግህ ሥራውን
ተመልከት፡፡ ያ በቂ ነው፡፡
ሼል ሲልቨርስቴይን
- ለምንድነው የምፅፈው? ሰዎች ጎበዝ እንዲሉኝ
ወይም ግ ሩም ፀ ሐፊ ስ ለሆንኩ አ ይደለም፡፡
የምፅፈው ብቸኝነቴን ለመግታት ስለምፈልግ
ነው፡፡
ጆናታን ሳፍራን ፎኧር
- ፃፊ ፃፊ እስኪለኝ ብጠብቅ ኖሮ፣ ከእነአካቴው
ምንም ነገር አልፅፍም ነበር፡፡
አኔ ታይለር

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ንጉሥ የሆነው አያ አንበሶ በጉልበት፣ በማን አለብኝና በገዢነት ስሜቱ መዋጡን ትቶ፣ ከሁሉም አራዊት ጋር አብሮ መኖርና ተጋግዞ በጋራ ፍሬ ማፍራትን በመፈለጉ፣ የዱሮው አያ አንበሶ መሆኑን ለመተው ማሰቡን ይፋ ለማድረግ አሻ፡፡
ስለሆነም ዋና መርሆው፡-
“ከሌሎች የዱር እንስሳት ጋር ተባብሮ መኖር ነው!” አለ
ይህንኑ በተግባር ለመተርጐም አያ ጅቦ ጋ ሄደና፤
“አያ ጅቦ የወትሮ ጠብና የገዢና ተገዢ ነገር ያብቃና በጋራ ተሳስበን እንኑር ብዬ አስቤያለሁ”፤
“መልካም ሀሳብ ነው፡፡ ደስ ብሎኛል” አለ፡፡
አያ አንበሶ ቀጥሎ ወደ አያ ነብሮ ሄደና፤
“አያ ነብሮ፤ የወትሮ ጠብና የገዢና ተገዢ ነገር ያብቃና በጋራ ተሳስበን የምንኖርበት ሥርዓት እንፍጠር” አለው፡፡
አያ ነብሮ፤
“እጅግ ቀና ሃሳብ ነው - ይህን የተቀደሰ ሃሳብ ማን እምቢ ይላል?” አለና መለሰ፡፡
ቀጥሎ ተኩላ ጋ ሄደ፡፡
ተባብሮ አብሮ የመሥራትን ሥርዓት ጉዳይ አነሳበት፡፡
ተኩላ፤
“ይሄማ እሰየው ነው፡፡ ምን ሆኜ እቃወመዋለሁ?” አለ፡፡
የሦስቱም መልስ እጅግ ያስደስተዋል፡፡
“እንግዲያው የተስማማንበትን በተግባር ማየት አለብን” አለ ተኩላ፡፡
ተስማሙና ታላቁ አደን ላይ ተሰማሩ፡፡
ሄደው ሄደው አርፍደው አንዳች የሚያህል ጐሽ ፊታቸው ድቅን አለ፤ ተረባረቡና ጐሹን መሬት ላይ ጣሉት፡፡ ከዚያ ተካፍለው ድርሻ ድርሻቸውን መውሰድ ነበረባቸው፡፡ አሁን ጉድ ፈላ
አንበሳ ዋና ደልዳይና አከፋፋይ ሆነ፡፡ አራቱም የምግብ አጠቃቀም ዘዬአቸው የተለያየ ነው። አብረው መብላት የማይታሰብ ነው፡፡
አያ አንበሶ፤ “መብላት አለብን፤ ተካፍለን እንመገብ” አለ፡፡
ሌሎቹ ልባቸው ባያምንበትም “በጄ” አሉ፡፡ አንበሳ የጐሹን ሥጋ አራት ላይ ከፈለው፡፡
የመጀመሪያውን የቅርጫ መደብ፤
“ይሄ መደብ የእኔ ነው፡፡ የአራዊት ንጉሥ በመሆኔ የማገኘው ድርሻዬ ነው”
ቀጠለና፤ “ሁለተኛወን መደብ የሚያገኘው
“አደኑ ላይ ትልቅ ሚና የተጫወተው ነው ያ ደግሞ እኔ ራሴ ነኝ፡፡”
“ሦስተኛው መደብ፤ እኔ ራሴ በአንበሳነቴ ልክ እንደናንተው ድርሻዬ ነው” አለ፡፡
አያ አንበሶ፤ አራተኛውን ቅርጫ ወደ ወለሉ ገፋና
“ይሄን የቅርጫ መደብ የሚነካ ወዮለት!” አለ፡፡
*   *   *
“የባህርይ ነገር አይለወጥም፡፡ በበጐ ፈቃድ አይሻርም፡፡ ጅብ ማንከሱን፣ አዞ ማልቀሱን፣ እባብ መላሱን በፍላጐታቸው ሊተውት አይቻላቸውም” ይባላል፡፡
የአንበሳውን ድርሻ አንበሳው ብቻውን እንደሚወስድ በሚታወቅበት አካባቢ፣ ዲሞክራሲያዊነት በዋዛ የሚገኝ ነገር አይሆንም፡፡ “ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ ይላል” እንደሚለው ተረት ዓይነት መሆኑ ነው፡፡
በራስ ወዳድነት ላይ ብቃት - አልባነት ሲጨመር ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ራዕይ ይደበዝዛል። የታቀደው ነገር ሁሉ የአፈፃፀም፣ ሰለባ ይሆናል፡፡ የበለጠ አሰቃቂው ነገር ደግሞ ስህተትን መድገም እንጂ ከስህተት መማር አይኖርም፡፡ ደጋግመን ስለአንድ ችግር የምናወራው ለዚህ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስና፣ ኢ - ፍትኃዊነት፣ የደላሎች ስርዓት፣ ኔትዎርክ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የአቋም መሸርሸር፣ የአፈፃፀም ችግር፣ የተቋማት አለመጠንከር፣ ብቁ አመራር አለመኖር ወዘተ … እነዚህን ሐረጋት ስንቴ ደገምናቸው? ወይ ማረም አሊያም በተሸናፊነት ከጨዋታው መውጣታችንን ማመን ነው፡፡ ለዚህም ቢሆን ውስጠ - ማንነታችንን መፈተሸ ይበጃል፡፡ ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ አብሮ መብላት ለማይችሉ ሰዎች፤ የትብብር ባህል ምን ያህል ዕሙናዊ ነው? ምን ያህልስ ረዥም መንገድ አብሮ መጓዝ ይቻላል? ራሳችንን በራሳችን እንድንሸረሽር የሚያደርጉ ኃይሎች ይኖሩ ይሆን? ለምንድን ነው ጉዟችን ውሃ ወቀጣ የሚመስለው? የመብራት … የውሃ ችግር ነጋ ጠባ የምናነሳው ለምንድነው? የህዝብ ብዛታችን በተለይ በዋና ከተሞች ጭንቅንቅ ደረጃ መድረሱን እያጤንን ነውን? ጥያቄዎች እየበዙ መልሶች እያነሱ መምጣታቸውን ልብ እንበል፡፡ የታክሲን ሰልፍ ርዝመት መጨመር እያስተዋል ነው? በአንድ አገር ላይ ዋና ለውጥ ሊያስከትል የሚችለው የአስተሳሰብ ለውጥ ወይስ የህንፃዎች ብዛትና የዓይነታቸው መበራከት ነው? የህንፃዎች መበራከት፣ የመንገዶች መሰራት በራሱ ይበል የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ይሄ ግን የብዙሃኑን ተገልጋይ ህዝብ ኑሮ ፈቀቅ የሚያደርግ መሆን አለበት። ህዝባዊ ኑሮ፣ ዕድገትም ሲታይ የዜጎች ተስፋ ይለመልማል፡፡ የበለጠ የህይወት ዕሳቤ ይመጣል፡፡ የሥነ-ልቡናና የአመለካከት ለውጥ ተጨባጭ ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ መደላደሉም አስተማማኝ ይሆናል፡፡
ግምገማዎች ከእከክልኝ ልከክልህ መውጣት አለባቸው፡፡ ይህ ችግር የሚወገደው ድክመቶች እየበዙና እየተሳሰሩ ሲመጡ አይደለም፡፡ የአንዱን ድክመት አንዱ የሚሸፍንለት ራሱን ማዳን ስላለበት ነው፡፡ የነግ - በኔ ሥጋትም ስላለበት ነው፡፡ አብረው የገቡበትን ሌብነት መደበቅ ግድ ስለሚሆን ነው፡፡ “ግምገማ ድሮ ቀረ” እያሉ በፀፀት የሚናገሩ ሰዎች አልጠፉም፡፡ ሆኖም አንድ እፍኝ ጨው ውቂያኖስን አያሰማ ሆኖባቸዋል፡፡ ከልብ ስለሀገር የማሰብና የመወያየት ነገር የተመናመነው ለዚህ ነው፡፡ በየስብሰባው ላይ ሲፋጠጡ ማየት አስገራሚ ነው፡፡ የልብ አውቃው፤ “መብላት ያስለመድከው ሲያይህ ያዛጋል” የሚለው ይሄኔ ነው!   

እስካሁን የተደረገው እርዳታ በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል

   ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ በድርቁ ለተጎዱ ዜጎች ተጨማሪ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲያደርጉ ለአለማቀፉ ማህበረሰብና ለለጋሽ ተቋማት ከትናንት በስቲያ ጥሪ ማቅረባቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ እስካሁን ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የተደረገው እርዳታ በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው በአብዛኛው ዘግይቶ ነው ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዩኒሴፍን የመሳሰሉ አለማቀፍ ተቋማት በአፋጣኝ ተጨማሪ እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውንም ገልጿል፡፡ በሌሎች የአለማችን አካባቢዎች የተከሰቱት ቀውሶች እንዳሉ ሆነው አለማቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ችላ ማለት የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፣ አገሪቱ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 750 ሺህ ያህል የጎረቤት አገራት ስደተኞችን እንደማስጠለሏ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ድጋፍ ሊያደርግላት ይገባል ብለዋል - ለአሶሼትድ ፕሬስ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ለጋሾች ከ10 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል መባሉንም አስረድቷል፡፡
ከፍተኛውን የእርዳታ ያደረገቺው አገር አሜሪካ መሆኗን የጠቀሰው ዘገባው፤ አሜሪካ ከጥቅምት ወር 2014 አንስቶ ለኢትዮጵያ ከ532 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሰብአዊ ቀውስ ድጋፍ እርዳታ መለገሷንና የኢትዮጵያ መንግስትም ችግሩን ለመቆጣጠር ከ380 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን አክሎ ገልጿል፡፡


- በዩኒቨርሲቲው ጀኔሬተር ፈንድቶ በተነሳ ቃጠሎ ትምህርት ተቋርጧል
- ህገወጥ ተብለው 250 ቤቶች ሲፈርሱ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተከስቷል

    አዳማ (ናዝሬት) ከተማ ላይ፣ የስጋት መንፈስ ሲያንዣብብባት ሰንብቷል፤ የዩኒቨርስቲ ትምህርት ተቋርጦ በርካቶች ወደየትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡ በከተማዋ አንድ ዳርቻ ህገወጥ ናቸው የተባሉ ቤቶች ለማፍረስ በተጀመረ ዘመቻም ግጭት ተፈጥሮ ጉዳት ደርሷል፡፡
በከተማዋ በተፈጠረው አለመረጋጋት ስጋት እንዳደረባቸው የገለፁልን ነዋሪዎች፤ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በርካታ አመታት ሲያገለግል የነበረ ጀኔሬተር ፈንድቶ የእሳት ቃጠሎ እንደተነሳና በተለያዩ ክፍሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ተደናግጠው አለመረጋጋት በመፈጠሩ ትምህርት እንደተቋረጠ ምንጮች ጠቅሰው፣ አንዳንዶቹ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወደየመጡበት አካባቢ መሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ኩሽነን እና ቀበሌ 03 በተሰኙ ቦታዎች፣ ህገወጥ ናቸው የተባሉ የጨረቃ ቤቶችን ለማፍረስ በተጀመረ ዘመቻ፣ ከነዋሪዎች ጋር ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ከ250 በላይ ቤቶች እንደፈረሱ ምንጮች የገለፁ ሲሆን፤ ነዋሪዎች ከፖሊስና ከአፍራሽ ግብረ ሃይል አባላት ጋር ተጋጭተው ጉዳት የደረሰ መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ ክስተቶች ሳቢያ አለመረጋጋትና ስጋት ቢፈጠርም፣ ከዚሁ ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኘው 10 ቀበሌ ተጨማሪ ህገ ወጥ ቤቶችን ለማፍረስ ተወስኗል ብለዋል ምንጮቹ፡፡ በሰባት ቀናት ውስጥ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የተናገሩ ነዋሪዎች፤ በሰባተኛው ቀን አፍራሽ ግብረ ሃይል መጥቶ ቤቶችን እንደሚያፈርስ ተነግሮናል ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅና ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ  ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ 

ግንባታው ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ለርሃብ አጋልጧል ብሏል
   አለማቀፉ የመብት ተሟጋች ተቋም “ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል” የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በገነባው የግልገል ጊቤ 3 የሃይል ማመንጫ ግድብ ሳቢያ በኢትዮጵያና በኬንያ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህልውና ለከፋ አደጋ አጋልጧል በሚል የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ለተባለው ተቋም መክሰሱን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው በገነባው በዚህ ግድብ ሳቢያ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለርሃብ አደጋ ተጋልጠዋል ያለው ተቋሙ፤ በኢትዮጵያና በኬንያ ለሚኖሩ መቶ ሺህ ያህል ሰዎች የህልውና መሰረት የሆነውን የኦሞ ወንዝ ነባር ፍሰት አቅጣጫ ማስቀየሩ፣ በሰዎቹ ህልውና ላይ በቀጣይ ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራል ሲል ተቋሙን ከስሷል፡፡
ሳሊኒ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችን ይሁንታ ሳያገኝ ግድቡን ገንብቷል ያለው ተቋሙ፣ ምንም እንኳን በግንባታው ሳቢያ በነዋሪዎቹ  ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ካሳ ለመስጠት ቃል ቢገባም፣ የገባውን ቃል አላከበረም ሲል አቤቱታውን አሰምቷል፡፡
የ “ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል” ዳይሬክተር ስቴፈን ኮሪ፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የግድቡ ግንባታ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በተመለከተ የቀረበለትን ማስረጃ ችላ ብሏል፤ የገባውን ቃል አላከበረም፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መብት ጥሷል ብለዋል፡፡

    በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተከሰተው ግጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለከተው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት መንግስት ሃገራዊ የውይይት መድረክ በአስቸኳይ እንዲያዘጋጅ ጠየቀ፡፡
ፓርቲው በሁለት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና ግጭት መንግስት እያስተናገደበት ያለው አግባብ ትክክል አለመሆኑንና ችግሩ የመልካም አስተዳደር እጦት ውጤት ብቻ ነው በማለት አቅልሎ ከመመልከት ይልቅ የችግሩን ትክለኛ መነሻ እንዲመረምር አሳስቧል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሚታዩት ወቅታዊ ግጭቶችና ጥያቄዎች በዋናነት ብሄረሰባዊ ማንነትን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ መሆናቸውን የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት በመግለጫው ጠቅሶ፤ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ካልቻለ የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ብሏል፡፡
መንግስት ችግሩን ለመፍታት የኃይል እርምጃ ከመጠቀም እንዲቆጠብ ያሳሰበው ፓርቲው፣ የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ፤ የታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ፤ በአስቸኳይ በግልፅ ፍ/ቤት እንዲዳኙ እና በጠበቆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኙ ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በፓርላማ ቀርበው፣ “ለችግሩ ዋነኛ ተጠያቂዎቹ እኛ ነን” ማለታቸውን ፓርቲው አድንቆ፤ ተጠያቂ ነን ካሉ ተጠያቂዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡
በኦሮሚያ ጉዳይ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ችግሩ የተፈታ በማስመሰል አድበስብሰው መዘገባቸውን የተቃወመው የፓርቲው መግለጫ፤ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችም ግጭቱን ከሚያባብሱ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል በሀገሪቱ የተከሰተው የድርቅ ችግር፣ የሰው ህይወት መቅጠፍ ከመጀመሩ በፊት ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ህዝቡ ከምንጊዜውም በበለጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግስት ጥሪ እንዲያቀርብና ድርቁን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም የሚሞክሩ ኃይሎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ፓርቲው ጠይቋል፡፡


      በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ “ለታማሚ ልጃቸው ማሳከሚያ” በሚል ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንዳሉ የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ ከእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ግማሽ ሚሊዮን ብር በርዳታ እንዲሰጣቸው መወሰኑን የተቃወሙት የገዳሙ ሒሳብ ሹም ከሥራና ከደመወዝ መታገዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ ሕመምተኛ ልጃቸውን በውጭ ሀገር ለማሳከም ይችሉ ዘንድ፣ ከሀገረ ስብከቱ የገዳማትና አድባራት ሓላፊዎች ተውጣጥተው በክፍላተ ከተማ በተዋቀሩ ኮሚቴዎች ከ2 ሚ. ብር ያላነሰ ገንዘብ መሰብሰቡን የጠቀሱት ምንጮች፤ አገልጋዮች በየግላቸው የገንዘብ ርዳታ እንዲያበረክቱ ከመጠየቅ ውጭ የአብያተ ክርስቲያናቱ ገንዘብ ለድጋፉ ወጪ መደረጉ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ “ድጋፉ በሥራ አስኪያጁ ዕውቅና የሚደረግ ከመኾኑ አንጻር ባለው ተጨባጭ ኹኔታ ከተጽዕኖ የጸዳና በበጎ ፈቃድ ብቻ የሚደረግ ነው ለማለት እንቸገራለን” ያሉት ምንጮቹ፣ በጉዳዩ ላይ ተቃውሞን ማሰማት፣ ከሥራ አላግባብ መታገድንና መዛወርን ጨምሮ በተለያዩ ሰበቦች ሽፋን ለጉዳት ሊዳርገን ይችላል ብለው እንደሚሰጉ ያስረዳሉ፡፡
ለዚህም፣ በእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሒሳብ ሹም ላይ ባለፈው ሰኞ የተወሰደውን ከሥራና ከደመወዝ የማገድ ርምጃ የጠቀሱት ምንጮች፤ ውሳኔውም በሌላ ሰበብ ሽፋን መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡
ሒሳብ ሹሟ እማሆይ ዐጸደ ማርያም ማሞ፣ ቀድሞ ከሚሠሩበት ቤቴል ቅዱስ ሚካኤል ወደ ገዳሙ ተዘዋውረው የመጡት፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ባለፈው ኅዳር ወር ከደርዘን በሚልቁ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሠራተኞች ላይ የሥራ ዝውውር ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ ገዳሙ፣ “ሕገ ደንባችን አይፈቅድም” በሚል ምደባቸውን ቢቃወምም ይህንኑ ቅሬታ በውስጡ እንደያዘ ተቀብሏቸው እንደነበር ይገልጻል፡፡ እማሆይ ዐጸደም ላለፉት አራት ወራት የገዳሙ ሒሳብ ሹም ኾነው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከመጋቢት 5 ቀን ጀምሮ ግን ከሥራና ከደመወዝ መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ባለፈው ሰኞ ከገዳሙ ጽ/ቤት ደርሷቸዋል፡፡
ገዳሙ የሒሳብ ሹሟን ምደባ የተቀበለው፣ “ከበላይ መሥሪያ ቤት ላለመጋጨትና ትእዛዝ ለማክበር ሲባል” እንደነበር አስታውሶ፣ ይህም የገዳሙን ማኅበር ዕረፍትና ሰላም ነስቶ ቁጣን እንደቀሰቀሰ የገለፀ ሲሆን፤ እገዳው፥ “የገዳሙን ሕገ ደንብና ሥርዓት ለመጠበቅና ለማስከበር ሲባል” የተላለፈ መኾኑን ከማመልከት በቀር በጽ/ቤቱ የተጠቀሰ አዲስ ምክንያት የለም፡፡ የምደባው ጉዳይ ጽ/ቤቱ በሽፋንነት የተጠቀመበት መኾኑን የሚናገሩት ምንጮቹ፤ ለወራት ሥራቸውን ሲያከናወኑ በቆዩት ሒሳብ ሹሟ ላይ የተላለፈው እገዳ ተገቢነት የሌለውና የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ የካቲት 25 ቀን ባካሔደው ስብሰባ ካሳለፈው ውሳኔ ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደኾነ ያረጋግጣሉ፡፡
በተጠቀሰው ቀን የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ በዋና አስተዳዳሪው ሰብሳቢነት ባካሔደው ስብሰባ፤ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ለልጃቸው ማሳከሚያ ገንዘብ ለማሳባሰብ በተዋቀሩ ኮሚቴዎች የቀረበው የድጋፍ ጥያቄ፣ ተገቢነት ያለውና ገዳሙ ከሌሎች ገዳማትና አድባራት ሳይለይና ብዙ ሳይዘገይ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አስታውቋል፡፡  “ጥያቄው ሰብአዊ ፍጡርን የማዳን ወሳኝ ጉዳይ መኾኑ ታምኖበት፣ ከገዳሙ ገቢ ላይ ብር 500‚000 ወጪ ኾኖ እንዲመደብ፣ ከዚህ ውስጥ 300‚000 ብር በገዳሙ ስም፤ 200‚000 ብር በገዳሙ ሠራተኞች ስም ተሠይሞ በገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ አማካይነት ለክብር ሥራ አስኪያጁ  እንዲደርሳቸው” በሚልም ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የገዳሙ ጽ/ቤት፣ ውሳኔው እንዲፈጸምና ሒሳቡ እንዲወራረድ የካቲት 30 ቀን ለሒሳብ ክፍሉ በጻፈው መሸኛ ትእዛዝ ቢሰጥም፣ ሒሳብ ሹሟ ክፍያውን እንደማይፈጽሙ በመግለጽ ውሳኔውን ተቃውመዋል፤ ይህንኑም ተከትሎ ባለፈው ሰኞ ከሥራና ከደመወዝ መታገዳቸው ታውቋል፡፡ ሒሳብ ሹሟ እገዳውን በመቃወም ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አቤቱታ ማቅረባቸው የተጠቆመ ሲኾን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም ጉዳዩን እንዲያውቀው መደረጉ ተገልጿል፡፡


   የ22 ሺህ የአይሲስ ታጣቂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ማንነት በዝርዝር ያሳያል
     በአይሲስ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ለአመታት ሲከናወኑ በነበሩ የጸረ-ሽብር እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደ አንድ ትልቅ ስኬት የሚቆጠርና የቡድኑን ህልውና የከፋ አደጋ ውስጥ ይጥላል የተባለ፣ የ22 ሺህ የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎችንና የቤተሰቦቻቸውን ማንነት የሚገልጽ ሚስጥራዊ ዝርዝር መረጃ አፈትልኮ መውጣቱ ተዘገበ፡፡
ዴይሊ ሜይል ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ አፈትልኮ የወጣው መረጃ በሶርያና በኢራቅ የሚገኙ 22 ሺህ የቡድኑ ታጣቂዎችን ስም፣ ዜግነት፣ አድራሻ፣ የስልክ ቁጥር፣ ቤተሰቦች፣ የትውልድ ቦታና ዘመን፣ የቀድሞ የስራ ልምድ፣ የውትድርና ተሞክሮና የመሳሰሉ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ ሲሆን በቡድኑ የሽብር እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን ተልዕኮም ያሳያል፡፡
ታጣቂዎች ቡድኑን በአባልነት በሚቀላቀሉበት ወቅት በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ የተሰበሰበውና ሶርያ ውስጥ በምትገኘው ራቃ ከተማ ተቀምጦ እንደነበር በተገመተው በዚህ ዝርዝር መረጃ ውስጥ ከተካተቱትና ዜግነታቸውን ከገለጹት የቡድኑ ታጣቂዎች መካከል፣ 480 የሳኡዲ አረቢያ፣ 375 የቱኒዝያ፣ 140 የሞሮኮ፣ 101 የግብጽ፣ 35 የፈረንሳይ፣ 18 የጀርመን፣ 16 የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ዝርዝር መረጃ ውስጥ የ51 የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው የቡድኑ ምልምል ታጣቂዎች ዝርዝር ማንነት መካተቱን የጠቆመው ዘገባው፣ መረጃው አፈትልኮ መውጣቱ ቡድኑ በቀጣይ ያቀዳቸውን የሽብር ጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማክሸፍና የሽብር መረቡን ተከታትሎ ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል መባሉንም አስረድቷል፡፡ በአይሲስ ውስጥ አዋቂዎች ኤስ ኤስ ተብሎ በሚጠራው የቡድኑ የውስጥ ደህንነት ፖሊስ ሃላፊ እጅ ውስጥ የነበረው መረጃው፣ አቡ ሃሚድ በተባለ የቡድኑ አባል በሜሞሪ ካርድ ተሰርቆ መውጣቱንና ስካይ ኒውስ ለተባለው የዜና ተቋም መድረሱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜና በኢራቅ የአይሲስ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ቀንደኛ ተመራማሪ የሆነው ሰልማን ዳኡድ አል አፋሪ የተባለ ቁልፍ ሰው ከሳምንታት በፊት በአሜሪካ ልዩ የጸረ ሽብር ግብረ ሃይል በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

 በዓለማችን ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ አደጋዎችና ያንዣበቡ ስጋቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸውንና መንግስታት በአለማቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ማስታወቁን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም በቅርቡ ባወጣው ትንበያ፣ የአመቱ የአለማችን የኢኮኖሚ እድገት እንደሚቀንስ መግለጹን ያስታወሰው ዘገባው፣ የተቋሙ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዴቪድ ሊፕተን ባለፈው ማክሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የአለማችን ኢኮኖሚ ፈተናዎች ከመባባሳቸው በተጨማሪ አዳዲስ ስጋቶች መፈጠራቸውንና መንግስታት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው መናገራቸውን ገልጧል፡፡
ተቋሙ የአመቱ የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.4 በመቶ ይሆናል የሚል ትንበያ ባለፈው ጥር ወር ማውጣቱን ያስታወሱት ዴቪድ ሊፕተን፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች የተወሰነ መሻሻል ቢታይም በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ አደጋዎች እየተባባሱ መምጣታቸውን ገልጠዋል፡፡
ሊፕተን መንግስታት በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የገንዘብ፣ የፊዚካል ፖሊሲና የተቋማዊ ለውጥ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይገባቸዋል ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ቻይና ሰሞኑን ባወጣችው መግለጫ ባለፈው ወር የወጪ ንግዷ በ25 በመቶ መቀነሱን አስታውሶ፣ ይህም በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ ከተጋረጡ አሳሳቢ ስጋቶች አንዱ ነው ብሏል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት በደቡብ አሜሪካ አገራት የተከሰተውና ነፍሰ ጡር ሴቶችን በማጥቃት የሚታወቀው የዚካ ቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና በመጪዎቹ ወራት በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቀ፡፡
ቫይረሱ ከትንኞች በተጨማሪ በወሲባዊ ግንኙነት እንደሚተላለፍ መረጋገጡን የጠቆሙት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ማርጋሬት ቻን፣ ቫይረሱ የተሰራጨባቸው አገራት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ወቅቱ የዝናብ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቫይረሱ ስርጭት ይስፋፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጠዋል፡፡
ቫይረሱ በተስፋፋባቸው አገራት የሚገኙና ወደ አገራቱ የሚጓዙ ነፍሰጡር ሴቶች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ቫይረሱን ለመዋጋት እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም የአለማቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ተቋም በደቡብ አሜሪካና በካረቢያን አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ የሚያስችል ተጨማሪ የ2.3 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል፡፡