Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62

በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 26 ተጨዋቾችን በመጥራት ዛሬ ዝግጅቱን ሊጀምር ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የተሳካ ለማድረግ የሚካሄዱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በጉዞና ገንዘብ አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴ ተሰጥቷል፡፡ ኮሚቴው ለብሄራዊ ቡድኑ የሚሆን እስከ 80 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን ገልጿል፡፡ በጉዞና ገንዘብ አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተ/ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው ፤ልዑል በእደማሪያም መኮንን፤ አምባሳደር ተወልደ ገብሩ፤ ኮ/ሃምሳሉ ገ/እግዚ፤አትሌት ኃይል ገ/ስላሴ፤ ኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬ፤ አቶ ሰለሞን አለምሰገድ፤አቶ አማረ ማሞ፤አቶ ሸዊት ወ/ሚካኤል፤አቶ አዋድ መሃመድ በመስራት ላይ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትያትር ኢንተርፕራይዞች ላለፉት 10 ዓመታት ለአንድ ሰው የሚከፈለው የትያትር ቤት መግቢያ 15 ብር መሆኑን በመግለፅ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መቶ ፐርሰንት የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ሲሆን የመንግሥት ትያትር ቤቶች ጭማሪውን ባለመቀበላቸው ውዝግብ እንደተፈጠረ ታውቋል፡፡ “ጭማሪው የተደረገው የአዳራሽ ኪራይ፣ የማስታወቂያና የፕሮዳክሽን እንዲሁም አልባሳትና ቁሳቁስ ዋጋ በመናሩ ነው” የሚሉት የግል ትያትር ኢንተርፕራይዞች፤ ጭማሪው የተመልካቹን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ብለዋል - “ተመልካች ለለስላሳና ለቀላል ምግቦች ከዚያ ያላነሰ ገንዘብ ያወጣል” በማለት፡፡ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት እና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ጭማሪውን እንደማይቀበሉት ለኢንተርፕራይዞቹ አስታውቀዋል፡፡ 

በአክሱም ፒክቸርስ እየተዘጋጀ ላለፉት አምስት ዓመታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ሲደመጥ የቆየው “ኢትዮፒካሊንክ”፣ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በዛሚ ኤፍ ኤም ዝግጅቶቹን እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ ውስጥ አዋቂን ጨምሮ ሁሉም ዝግጅቶች እንደሚኖሩና ሌሎች ተጨማሪ ፕሮግራሞችም ሊቀርቡ እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፕሮግራሙ ከሰኞ እስከ አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት፤ እንዲሁም ቅዳሜ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ለተማሪዎችና ለሠራተኞች በሚመች ሰአት እንደሚተላለፍ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ “ኢትየፒካሊንክ” በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ያቀርብ የነበረውን ፕሮግራም ባለፈው ነሐሴ ወር ከጣቢያው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ማቋረጡ ይታወሳል፡፡

በመሀመድ ዳውድ ተፅፎ ክብሮም አለም ያሰናዳው “ጊዜ ግዙን” የ90 ደቂቃ የፍቅር አስቂኝ ፊልም ነገ በአዲስ አበባ የግል ሲኒማ ቤቶች እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ በኬቢ ፊልም ስቱዲዮ በተሰራው ፊልም ላይ ካሌብ አርአያስላሴ፣ ሜሮን ጌትነት፣ ዘሪሁን ታደሰ፣ አንተነህ ታደሰ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡

ወርሃዊ የሥነ ፅሁፍ ዝግጅቱን የፊታችን ሰኞ ከምሽቱ 12 ሰአት ጀምሮ በራስ ሆቴል እንደሚያቀርብ ዩሴ የማስታወቂያ ድርጅት አስታወቀ፡፡ በዝግጅቱ ላይ አርቲስት አዳነች ወልደገብርኤል፣ ገጣሚ ባየልኝ አያሌው፣ ገጣሚት ትዕግስት ማሞ፣ ተዋናይና ወግ ፀሐፊ ፍቃዱ ከበደ፣ ድምፃዊት ጠረፍ ጥላሁን (ኪያ)፣ ገጣሚ ሰለሞን ሳህለ እና አርቲስት ሄኖክ በሪሁን የስነፅሁፍ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡
በተመሳሳይ ዜና፣ ግጥም እና ሙዚቃ ተዋዝተው የሚቀርቡበት “ግጥምን በጃዝ” 17ኛ ምሽት ዝግጅቱን የፊታችን ረቡዕ ምሽት በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ ያቀርባል፡፡

በአዲስ አበባና በኒውዴልሂ በ2000 ተማሪዎች መካከል በተካሄደ ውድድር ያሸነፉ ስድስት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የሚገኘውን ናሳ የጠፈር ምርምር ማዕከል ጎበኙ፡፡ ተማሪዎች ከሕዳር 16 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ቀናት በማዕከሉ ባደረጉት ጉብኝት የጠፈር መንኩራኩሮችን እና የናሳ ቤተመዘክርን እንደጐበኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለታሪክ አድቨርታይዚንግ ፕሮዲዩስ ያደረገው የቢኒያም ወርቁ “አራቱ” የቤተሰብ ኮሜዲ ትያትር ነገ እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ከቀኑ 8 ሰዓት እና ከምሽቱ 12 ሰዓት በሚመረቀው ትያትር ላይ ሳምሶን ታደሰ፣ ፍቃዱ ከበደ ማሞ፣ ቅድስት ገብረሥላሴ እና ራሄል ተሾመ ይተውናሉ፡!

Saturday, 08 December 2012 14:19

ቡናና ስዕል - በቶሞካ

በአዲስ አበባ ለ60 ዓመት ጠንካራና ልዩ ሱስ የሚያስይዝ ግሩም የማሽን ቡና ለደንበኞቹ በማቅረብ የሚታወቀው ቶሞካ፣ ሳር ቤት አካባቢ “ጋለሪያ ቶሞካ” የተባለ ቡናና ስዕል የሚቀርብበት የጥበብ እልፍኝ እንደከፈተ አስታወቀ፡፡
ከትላንት በስትየ በአስር ሰዓት በሁለት ሰዓሊያን የተሳሉ ሃምሳ አንድ ስዕሎችን ለተመልካች በማቅረብ ነው ጋለሪያ ቶሞካ በይፋ ስራ የጀመረው፡፡
በሰዓሊ መሪ ኮከብ ብርሃኑና በሰዓሊ ክብሮም ገ/መድህን የተሳሉት ስዕሎች ለሦስት ወር ለእይታ ክፍት ሆነው የሚቆዩ ሲሆን የስዕል ኤግዚቢሽኑ በየሶስት ወሩ ይቀየራል ተብሏል፡፡

የፊልም ባለሙያዋ ሊንድሴይ ሎሃን በዓል ባህርይዋ ሳቢያ ህይወቷ ሊቃወስ እንደሚችል ተገለፀ፡፡ የፊልም ተዋናይዋ በየቀኑ ሁለት ሊትር ቮድካ በመጠጣት መረን ለቃለች ያለው ቲኤምዜድ፤ ድረገፅ ወደ አዕምሮ ህክምና ተቋም መግባት እንደሚያስፈልጋት ገልጿል፡፡ ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ በሚገኝ የምሽት ክለብ ሰው ደብድባለች ተብላ በቁጥጥር ስር የዋለችው ሊንድሴይ፤ በዋስ ከተፈታች ከ24 ሰዓታት በኋላ በሌላ ክለብ ውስጥ እንደእብድ ሲያደርጋት እና አላግባብ ስትበጠብጥ መታየቷ ጉድ እንዳስባለ ተዘግቧል፡፡ በምሽት ክለብ ሰው በመደብደብ ክስ ቀርቦበት በአዲሱ የፈረንጅ ዓመት መግቢያ ፍርድ ቤት የምትቀርበው ሊንድሴይ ሎሃን፤ ዳኛዋ ከማንኛውም ሊያስከስስ የሚችል ብጥበጣ እንድትቆጠብ የጣሉትን ገደብ ጥሳለች፡፡

50 ሴንት “ስትሪት ኪንግ ዘ ኢሞርታል” የተባለ አዲስ አልበሙን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ኤምቲቪ ኒውስ ገለፀ፡፡ አልበሙ በ2003 ዓ.ም የወጣውን የመጀመርያ አልበሙን “ጌት ሪች ኦር ዳይ ትራይንግ” 10ኛ ዓመት ለማክበር ያዘጋጀው ነው፡፡ በዚህ አዲስ አልበም ስራው ላይ ራፐር ኤሚነም አስተያየት በመስጠት ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገለት፣ ለኤምቲቪ ኒውስ የተናገረው 50 ሴንት፤ በሚሰጠኝ ሃሳብ ሁሌ የምደሰትበት ሰው እሱ ነው ብሏል፡፡ 50 ሴንት ከራፐር ኤሚኔም ጋር በመጣመር ልዩ አልበም ለመስራት የረጅም ጊዜ ፍላጎት እንዳለው መግለፁንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል በሙሉ ስሙ ከርቲስ ጃክሰን ተብሎ የሚጠራው ራፐር ፊፍቲ ሴንት እድሜያቸው ከ40 በታች ከሆኑ ዝነኛ ስራ ፈጣሪዎች አንዱ መሆኑን ሂፕሆፕ ኒውስ አስታውቋል፡፡

Page 8 of 163