Saturday, 24 May 2014 14:27

ከአንድ እንጀራ ለማያልፍ ከርስ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…ፀሀዩዋ እንኳን ፏ ብላ ከራሳችን በላይ ትንሽ ደበዘዝ ሲልብን ልንደነግጥ ነው! አሀ…ልክ ነዋ! እኛ ባቡሩን ወደሰማይ ለማቅረብ ብለን ድልድይ ብንሠራ… የአንበጣ መንጋ ወደመሬት ይቅረብብን!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የአዲስ አበባ የከርሞ ነገር አያሳስባችሁም! ልክ ነዋ…በዛ ሰሞን ጅቦች በጠራራ ፀሀይ መሀል ከተማ (ያውም አራት ኪሎን በጣም ተጠግተው!)  ነዋሪ አላስወጣ፣ አላስገባ ብለው ነበር፡፡
በቀደም ደግሞ የአንበጣ መንጋ በተለያዩ ቦታዎች (አሁንም አራት ኪሎን ጨምሮ) ከተማዋ ላይ ‘ተነሰነሰብን’ አይደል እንዴ! ኮሚክ እኮ ነው…“ዘመናዊነት አናቴ ላይ ወጣ!” “እድገቴ የእነ ኒው ዮርክና የእነ ፓሪስን ዓይን ባያቀላ ምን አለች በሉኝ!” ምናምን ለማለት ምንም የማይቀራት አዲስ አበባ፣ እንዲህ መጫወቻ ሆና ትቅር! ለአድባር ይሆናል ያሉት ዛፍ ምን ሆኖ ቀረ ነበር የተባለው! እኛ የአፍሪካ ሲንጋፖር እናደርጋታለን ብለን ‘ደፋ፣ ቀና’ ስንል…የአውሬና የነፍሳት መንሸራሸሪያ ስትሆን የማያበሳጨንሳ!
ለነገሩማ…እዚች ከተማ ውስጥ የሚታዩ አስገራሚ ነገሮችን ነገሬ ብሎ የሚሰበስብ ቢኖር አሪፍ ይሆን ነበር፡፡ እናላችሁ…ከጅብና ከአንበጣ ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ አንድዬ ይወቀው፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ብዙ ነገራችን ‘ነገ’ን የረሳን ያስመስለናል፡፡ ‘ለዛሬ’ ሲባል እነ ይሉኝታ፣ ታማኝነት፣ ወዳጅነት…አይነት ነገሮች እየተረሱ ነው፡፡ ያኔስ አንድ ይሁዳ ነበር ለሠላሳ ዲናር ማተቡን የበጠሰው፡፡ ዘንድሮ ‘ዛሬ’ን ብቻ በማየት ለሦስት…??? ዲናር ማተባችንን የምንበጥስ መአት ነን፡፡ ዘንድሮ ወዳጅን መካድ ከድርጊቶች ሁሉ የቀለለ ነው፡፡
እናላችሁ…እንዲህ ተቆሳስለን፣ እንዲህ ተበላልተን፣ እንዲህ ተማምተን፣ እንዲህ ተቦጫጭቀን፣ ከፊት ለፊት ስቀን ከጀርባ ተሳቀን…ያ ‘ነገ’ ሲመጣ፣ ያ ‘ሂሳብ ማወራረጃው’ ቀን ሲመጣ እንዴት ያደርገን እንደሆን ግርም አይላችሁም!
እናማ…‘ከአንድ እንጀራ ለማያልፍ ከርስ…’ አለ አይደል… ‘ነገ’ መኖሩንም ማወቅ አሪፍ ነው፡፡
ያ ‘ነገ’ መጥቶ… አለ አይደል… “የሰገሌ ዘመቻ ጊዜ የአርሴ ነበርክ የማንቼ…”  “የወልወል ግጭት ጊዜ ምን ትሠራ ነበር…” መባባል ሲመጣ የሚነገሩት ታሪኮች አይደለም ለ‘ብቸኛው’ ቲቪያችን፣ ለናይልሳት ጣቢያዎች በሙሉ የሚበቁ ታሪኮች የሚኖሩን ይመስለኛል፡፡
እናላችሁ…‘ነገ’ አይመጣ ይመስል፣ የ‘ዛሬዋ’ ቀን… አለ አይደል… ‘የፍርድ ቀን ዘመቻ ትመስል’… ሀቅ ተረግጦ፣ ይሉኝታ ጨለማ ቤት ተከርችሞበት… ከዛሬዋ ዕለት አርቀን ማሰብ ሲያቅተን ያሳዝናል፡፡
ስሙኝማ… ደግሞላችሁ አይነቃብኝም ብሎ የወዳጁን እንትናዬ የሚመነትፍ መአት ነው፡፡ እኔ የምለው…ይሄ ሁሉ ሰው የወዳጁን እንትናዬ የሚመነትፈው… የወዳጅ እንትናዬዎች ያልደረስንበት ‘ምስጢር’ አላቸው እንዴ! አሀ…እኛ አሁንም የምንከተለው የሦስተኛ ክፍልን የሰው አካል ልዩ፣ ልዩ ክፍሎች… ምናምን ነዋ! ልጄ…ዘንድሮ “እስኪ አምጣው የእንትኑን ሸማ…” እየተባለ በውድቅት ሌሊት የግቢ በር የተደበደበበት ‘ነገር’ በሞዲፈክ መሠራት ከጀመረ በኋላ የማንጠረጥርሳ!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ በቀደም እዚሁ የፈረደበት ኢንተርኔት ላይ በአንዱ ድረ ገጽ ምን የሚል አየሁ መሰላችሁ… አብዛኞቹ ወንዶች በ‘እነሆ በረከት’ ጊዜ ‘በደቂቃዎች የ‘መሰንበት ብቃታቸው’ ግፋ ቢል ሁለት ደቂቃ ነው ይላል፡፡ (ሁለት ደቂቃ!) እናላችሁ…ለሁለት ደቂቃ ብሎ የሀያ ሁለት ዓመት ወዳጅነት የሚያፈርስ መአት ነው፡፡ (‘ነጭ ላብ’ በግንባሩ እየተንቆረቆረ ሙሽሪት ሆዬ “ጨረስክ እንዴ!” የምትለው አባወራ አያሳዝንም! ራስጌ ላይ… “ሰበር የጥናት ውጤት፡ ሳይንቲስቶች እንደደረሱበት አብዛኞቹ ወንዶች ከሁለት ደቂቃ በላይ…” ምናምን የሚባል ማሳሰቢያ ይለጠፍማ!)
እናማ…በዛኛው ዘመን እንዲህ ፍጥጥ ብሎ ‘መነጣጠቅ’ (‘መቀባበል’ ማለትም ይቻላል) አልነበረም፡፡ እንደ ዘንድሮ… “ትንሽ አመሻሽቼ ነው የምመጣው፣ እራት ሠራተኛዋ ትስጥህና ብላ…” ብሎ ነገር ስላልነበረ አባወራ ‘ይከበር’ ነበር፡፡
ነድፌ፣ ነድፌ ባልጋ ከምሬያለሁ፣
የዛሬ ቀን ከብዷል ባል አለ ብያለሁ፡፡
ይባል ነበር፡፡
አንት የጓሮ ፍየል ብትስል ብታነጥስ፣
ዛሬ ባል ነውና ቅጠልም አልበጥስ፡፡
ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ… ወላ ሰምና ወርቅ የለ፣ ወላ በጥጥና በፍየል አሳቦ ‘በሾርኒ’ መናገር የለ፣ “ነገ ወሬው ሲሰማ አገርስ ምን ይለኛል!” ብሎ ጭንቀት የለ… ‘በረከተ መርገም’ የሆነ ዘመን!
አስቴር…
ነጠላ ለብሼ፣ ነጠላ ለብሰህ፣
አሁን ከምንጊዜው፣ ድርብ አማረህ፡፡
ነጠላ ነው ልብሴ፣ ሀገር ጠይቅብኝ፣
ይበርዳታል ብለህ፣ እንዳትደርብብኝ፡፡
ብላ የዘፈነችው ዘንድሮ ቢሆን ኖሮ… “እንዳትደርብብኝ ምናምን ብሎ ነገር ምንድነው! ግሎባላይዜሽን አይገባትም እንዴ?” ትባል ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ልጄ ዘንድሮ ‘ነጠላ’ የሚለው ቃል ከአፋችሁ እንደወጣ የሚቀርብላችሁ ጥያቄ ምን ይመስለኛል… “ማን ነው ሲንግል የለቀቀው?”
እናማ…‘ከአንድ እንጀራ ለማያልፍ ከርስ…’ አለ አይደል… ‘ነገ’ መኖሩንም ማወቅ አሪፍ ነው፡፡  
ስሙኝማ…‘ቦተሊከኞች’ን ነገሬ ብላችሁ እንደሆነ… አለ አይደል… ‘ነገ’ የሌለ ይመስል…‘ማልያ በገለበጡ’ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ልውጥውጥ ይላሉ…‘ነገ’ የማይመጣ ይመስል! እናላችሁ…‘ማልያ በገለበጠ’ በሦስተኛው ቀን…“የአንተን የፖለቲካ አመላካከት እኮ ድሮም ጀምሮ እጠራጠረው ነበር…” አይነት የወዳጅነት ዲስኩር ያመጣባችኋል፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…አይደለም ድሮ፣ ከዓመት ከሁለት ዓመት በፊት ከረሜላ ምናምን እያዞሩ የሚሸጡትን ህጻናት… “ፖለቲካ የሚባል ማስቲካ አለህ?…” ምናምን ለማለት ምንም የማይቀረው ከመጥበሻ ወደ ገበር ምጣድ ቢገለባብጡት የማይበስል ነው እኮ!
እናማ…የማይመጣ የሚመስለው ‘ነገ’ ሲመጣና መጋረጃው ሊገለጥ፣ ያደፈጠ ሁሉ ሰነዱን ሲመዝ ነገሩ ሁሉ አደባባይ ሊወጣ…አለ አይደል…ዛሬን ብቻ ማሰብ አሪፍ አይደለም፡፡ ዘንድሮ በአገራችን ላይ በላይ እየተደራራቡ የምናያቸው ነገሮች አብዛኞቹ ትናንትና…‘ነገ’ የሚባል ቀን መኖሩን በረሱ ሰዎች ሰበብ ይመስለኛል— ‘ነገ’ን የረሱ ግለሰቦች፣ ‘ነገ’ን የረሱ ቡድኖች፣ ‘ነገ’ን የረሱ የቡድንና የቡድን አባቶች፣ ‘ነገ’ን የረሱ የሚዲያና ሌሎች ተቋማት በሠሯቸው ሥራዎች ነው፡፡
እናላችሁ…ከእናንተ ጋር ትናንት እነ እትናን ሲረግም የነበረ ሰው፣ ዛሬ ዛሬ አወዳሽ የሚሆነው የእምነት መለወጥ ሳይሆን ነገ የሌለ ስለሚመስለው ነው፡፡ “ጥርግ ባሉልን፣ አበሳችንን አበሉን እኮ…” ምናምን ሲል የነበረው ሰው ዛሬ እንትን የነካው እንጨት ሲያስመስላቸው ከነበሩት ከእነዛው እነእንትና ጋር ታዩታላችሁ፡፡ ‘ነገ’ ሲመጣ ደግሞ…“እኔ እኮ ውስጣቸውን ልሰልል ብዬ እንጂ…” ማለት ይመጣል፡፡ እናማ…ዘንድሮ  ‘ነገ’ን ረስተን “ውድቀትም ሆነ እርገት ዛሬና ዛሬ ብቻ ነው!” የምንልና ጳጳሳቱን ‘በቅድስና የምናስከነዳ’ ሰዎች መዝገብ እያጣበብን ነው፡፡
እናማ… ያላሰብነውን ነገር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማወቁ አሪፍ ነው፡፡ አዲስ አበባ በጠራራ ፀሀይ በአንበጣ ትሸፈናለች ብሎ ማን አስቦ ያውቃል!...የመሀል አዲስ አበባ መንደሮች በጠራራ ፀሐይ በጅብ መንጋ ይተራመሳሉ ብሎ ማን አስቦ ያውቃል!….‘ፈረንጅ’ በጤፍ ፍቅር ይወድቃል ብሎ ማን አስቦ ያውቃል! (ቂ…ቂ…ቂ…)
‘ከአንድ እንጀራ ለማያልፍ ከርስ…’ አለ አይደል… ‘ነገ’ መኖሩንም ማወቅ አሪፍ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4363 times