Saturday, 23 January 2016 13:33

የእኛ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በዛ ሰሞን አንድዬ ለምስኪን ሀበሻ “ነገ ተነገ ወዲያ ብቅ በል…” ባለው መሠረት ምስኪን ሀበሻ ብቅ ብሏል፡፡ እስከዛው ድረስ ግን አንዳንድ ግራ የገቡን ነገሮች አሉ፡፡ ይሄ የ‘ፎርጀሪ’ ነገር የት ሊያደረሰን ነው! አለ አይደል…በቀደም ዕለት ‘ተመሳስለው የተሠሩ የትምህርት ማስረጃዎች’ መብዛት አሳሳቢ መሆኑ ሲወራ ነበር፡፡
በዛ ሰሞን ደግሞ ለሆነ ፈተና ከቀረቡ ዘጠኝ መቶ ምናምን መንጃ ፈቃዶች ሦስት መቶ ምናምኑ ‘ፎርጅድ’ ሆነው ተገኙ ነው ምናምን የሚል ነገር ሰምተን ነበር፡፡
እናላችሁ…በምርቱም፣ በሸቀጣ ሸቀጡም በሁሉም ነገር የ‘ፎርጀሪ’ መብዛት ሊያሳስብ የሚገባ ነገር አይመስላችሁም!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንዴት ከረምክልኝ
አንድዬ፡—  እንዴት ከረምክ!…ለአቤቱታና እኔን ለመጨቅጨቅ ሲሆን ሰዓት አታዛንፉም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ የአንተ ጉዳይ ሲሆን መቼም ቢሆን ሰዓት አናዛንፍም፡፡
አንድዬ፡— አሁን የሚቆፈር ተራራ አለ ብላችሁ ዶማና አካፋ ተሸክማችሁ በሰዓቱ ትመጣላችሁ!...የሚታረስ መሬት አለ ብላችሁ ሞፈርና ቀንበራችሁን ተሸክማችሁ በሰዓቱ ትመጣላችሁ!…
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዴታ አንድዬ! እንዴታ!
አንድዬ፡— የእናንተ አንዱን ችግር ልንገርህ አይደል…ሥራ አትወዱም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኧረ ልባችን እስኪጠፋ ነው የምንሠራው!
አንድዬ፡—  ይመስላችኋል፡፡ እናንተማ ይመስላችኋል፣ ብዙ ስለምታወሩ የሠራችሁ ይመስላችኋል፡፡ ብዙ ስለምትደሰኩሩ የሠራችሁ ይመስላችኋል፡፡ ቀን ከሌት ስለምትሰበሰቡ የሠራችሁ ይመስላችኋል፡፡ በትንሹም፣  በትልቁም “ሆ” ማለት ስለምትወዱ የሠራችሁ ይመስላችኋል፡፡ የበዓሉ ቀን አልበቃ ብሏችሁ ዋዜማውንና ማግስቱን ለጥ የምትሉ…ደግሞ ልባችን እስኪጠፋ እንሠራለን ትለኛለህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ…ይህን ያህል አትቆጣ! በቀደምም እኮ እስኪበቃን ነው የነገርከን፡፡
አንድዬ፡—  ምኑ ነው የሚበቃችሁ፡ እንደውም ሰማዩን ብራና ውቅያኖሱን ቀለም ባደርገው የእናንተ ነገር ተጽፎስ ያልቃል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አንተ እኮ አልተረዳህልንም…ችግር እኮ ነው እንዲህ የሚያደርገን!
አንድዬ፡—  ሥራ የማይሠራችሁ ችግር ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደ እሱ ማለት ሳይሆን መላ ቅጡን ያሳጣን ችግር ነው፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ እንደ እሱ ማለት ጥሩ፡፡ መላ ቅጡን ነው ያጣችሁት! ቆይ እስቲ፣ ግራ የሚገባኝ ነገር አለ…በሁሉ ነገር ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም ምናምነኛ የምትሉት ነገር…
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱንማ ከዚህ በፊት ብለኸኝ ነበር…
አንድዬ፡— ብልህም እደግመዋለሁ፡፡ በርዝመት ከአፍሪካ አንደኛ የሆነ ህንጻ ሠራችሁና ምን ይጠበስ! ንገረኛ ምን ይጠበስ! ይልቅ በስንዴ ምርት ከአፍሪካ አንደኛ አትሉም! በበቆሎ ምርት ከአፍሪካ አንደኛ አትሉም!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ረጅም ህንጻ መሥራታችን እኮ ቢያንስ፣ ቢያንስ ጊነስ ቡክ ምናምን ላይ እንወጣለን…ደግሞ ለቱሪዝም…
አንድዬ፡— (ከት ብሎ ይስቃል)  እውነት! እንዴት አይነት እውቀት ነች እባክህ… ከኒው ዮርክና በርሊን ነው የአንተን ከአፍሪካ አንደኛ ህንጻ ለማየት የሚመጣው፡፡ ራሳችሁን መካብ ስትወዱ እኮ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ታዲያ ራሳችንን ያልካብን…
አንድዬ፡— ትደርሱበት የለ…ለእሱም እኮ አንዳችሁ ራሳችሁን ስትክቡ አንዳችሁ ደግሞ አውርዳችሁ መጣል አይደል እንዴ ሥራችሁ! እርስ በእርስ እንኳን የማትግባቡ…ሌላው እንዴት እንዲያደንቃችሁ ትፈልጋላችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ዓለም ስለሚቀናብን ነዋ! መቼም ዓለም እንደሚቀናብን አንድዬም አንተም ታውቃለህ…
አንድዬ፡— አላውቅም፡፡ እኔ እንደሚቀኑባችሁ አላውቅም፡፡ እንደምውም የማውቀውን ልንገርህ አይደል… ብዙ የዓለም ህዝብ የት እንዳላችሁና እነማን እንደሆናችሁ አያውቅም…
ምስኪን ሀበሻ፡— እኮ ምን አልኩህ አንድዬ…ታዲያ ይሄ የቅናት ምልክት አይደለም!
አንድዬ፡— ደግሞ እኮ …የሌላውን አገርና ህዝብ ነገር ስትተነትኑ…እንደው ግርም ይለኛል፡ ሰዎቹ ራሳቸው እኮ ያንን ያህል ስለ ራሳቸው አያውቁም፡፡ (ከት ብሎ ይስቃል)
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ልታበረታታን ይገባል እንጂ ለምንድነው ግርም የሚልህ!
አንድዬ፡— ላበረታታችሁ!…የጓዳችሁን ችላ ብላችሁ ሌሎች ሳሎን ውስጥ ዘው ብላችሁ ስትገቡ ላበረታታችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— እኛ እኮ በክፋት ሳይሆን…ከሌሎች ለመማር ነው፡፡
አንድዬ፡— ነው…ራሳችሁ “መርፌ የራሷን ቀዳዳ ሳትመለከት የሰው ትጠቅማለች” ትሉ የለ እንዴ! እንደውም ትዝ አለኝ…ተረቶቻችሁን ሳይ እኮ አንዳንዴ የእኔን ቃል ሊሸፍን ምንም አይቀረው፡፡ ምን ያደርጋል… አንዱንም አትፈጽሙትም እንጂ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ የቅኔ አገር ስለሆንን ነው እኮ፡፡
አንድዬ፡— ሌላ ደግሞ ለምንድነው ትዳራችሁን አክብራችሁ ቤታችሁ የማትሰበስቡት! ምንድነው እሱ ከትንሽ እስከ ትልቅ አጥር የሚያዘልላችሁ፣ እዚህ እዚያ የሚያቅበዘብዛችሁ! እናንተ ሰዎች ምን አይነት በሽታ ነው የሰፈረባችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እሱም እኮ አለ አይደል…የተስፋ መቁረጥ…
አንድዬ፡— እሱን እንኳን ተወው… መጀመሪያ ነገር እኔ አንድ ለአምስት፣ አንድ ለአራት እንድትሆኑ ብፈልግ አንድ ለአንድ እል ነበር!
ምስኪን ሀበሻ፡— ጊዜው እኮ…
አንድዬ፡— ጊዜው፣ ጊዜው አትበለኝ፡ እኔ እኮ በትዳራችሁ ላይ መወስለታችሁ ብቻ አይደለም…የሌላ ሰው ሚስት ላይ የሚያንጠላጥላችሁ ምንድነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ያን ያህል እንኳን አልደረስንም…
አንድዬ፡— አልደረስክም!…እናንተው አይደላችሁም እንዴ እናንተ ብትደብቁት እኔ ገልጬ እንደማይ የምትናገሩት!
ምስኪን ሀበሻ፡— ሁሉንም ነገር ለአንተ ስለሰጠን ነዋ!
አንድዬ፡— እኔን የምትፈልጉት ሲቸግራችሁ…ወይ ገንዘብ ስታጡ፣ ወይ ስትታመሙ፣ እንደው በደህና ቀን ትዝ ብያችሁ አውቃለሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ሁልጊዜ እንጂ አንድዬ፣ ሁልጊዜ…
አንድዬ፡— ጸሎት ብላችሁ ስላነበነባችሁ እኔን አስታወሳችሁ ማለት አይደለም፣ ቤተክርስትያን ስለተሳለማችሁ እኔን አስታወሳችሁ ማለት አይደለም፡፡ እውነቱን ልንገርህ የእናንተ ነገር በጣም፣ እጅግ በጣም…ምንድነው የምትሉት…አንገቴ ነው የደረሰው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ተው ይህን ያህል እንኳን አትጥላን…
አንድዬ፡— መጥላት ሳይሆን…እስቲ ደግሞ አቤቱታችሁን ተዉና፣ እጃችሁን አጣምራችሁ “እሱ ያውቃል…” የምትሉትን ተዉና፣ እኔ እጄን ባልከተትኩበት ነገር “ከእግዜሐር ጋር…” እያላችሁ አባሪ ተባባሪ ማድረጋችሁን ተዉና… ራሳችሁ ባበላሻችሁት እኔን “ምን አደረግንህ…” እያላችሁ ማሳጣቱን ተዉና…ያኔ፣ ምናልባት ያኔ የእናተን ጉዳይ በቁም ነገር አየው ይሆናል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ከእንግዲህ በቃ አትድረሱብኝ እያልከን ነው!
አንድዬ፡— (ያመነታል) እስቲ አንኳኩና ከመሰለኝ እከፍትላችኋሁ፣ ካልመሰለኝም አልመሰለኝም፡፡ ደህና ሁን…
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ! አሜን!
እናማ…የእኛ ነገር ለምድሩም፣ ለሰማዩም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 5095 times