Saturday, 09 April 2016 09:41

“እዚህ ላይ ታቆማለህ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(24 votes)

“ደገፍ ብሎ የሚያለቅስበት ትከሻ የሚያገኝ የታደለ ነው”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ሙዝ ነጋዴው ገበያ ቀዝቅዞበታል፡፡ እናላችሁ… በአጠገቡ ታልፍ የነበረች አንዲትን ሴትን “እንዴት ያለ ጣት የሚያስቆረጥም ሙዝ መሰለሽ!” እያለ ሊያባብላት ይሞክራል፡፡ እሷም ሙዝ የምትገዛበት ገንዘብ እንደሌላት ትነግረዋለች። እሱም “ግዴለም ቀስ ብለሽ ትከፍይኛለሽ፣” ይላታል። እሷ ብዙም ደስተኛ አልሆነችም፡፡ አንድ ሙዝ እንድትቀምስ ይሰጣታል፡፡ እሷም…
“አይ፣ አልበላም፣” ትለዋለች፡፡
“ለምን?”
“ጾም ላይ ነኝ፡፡”
“የጾም ወቅት መቼ ገባና ነው የምትጾሚው፣” ይላታል፡ እሷም ምን ትለዋለች…
“የስለት ገንዘብ በቃሌ መሰረት ስላላገባሁ ሀጢአቴ እንዳይበዛብኝ ብዬ ነው…” ትለዋለች፡፡  ሰውየውም የዘረጋውን ሙዝ መልሶ ቅርጫቱ ላይ ያስቀምጥና ምን ቢላት ጥሩ ነው…
“በይ ተዪው የእኔ እመቤት፣ የእግዚአብሔርን እዳ ገና ያልከፈልሽ የእኔን እንዴት አድርገሽ ትከፍያለሽ…” አለና ሙዙም ቀረ እላችኋለሁ፡፡
እኔ የምለው እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንድ ሰሞን የሆነ ሰው ወሬ ሲያበዛብን ወይም የማይሆን ነገር ሲያወራ…አለ አይደል… “እዚህ ላይ ታቆማለህ…” የምንላት ነገር ነበረች፡፡ እንዴት አሪፍ አባባል መሰለቻችሁ!
እናላችሁ…. ዘንድሮ
“እዚህ ላይ ታቆማለህ…”
“እዚህ ላይ ታቆማላችሁ…”
የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ኮሚክ እኮ ነው…በአገልግሎት ቅሽምናው የተገልጋዮችን  ጨጓሯ ወንፊት የሚያደርግ መሥሪያ ቤት ይኖራል፡፡ እናላችሁ… የሆነ ስብሰባ ላይ አለቅዬው ካሜራ ፊት ይቀርብና (የፈረደበት ቴሌቪዥን!) “የድርጀቱ ሠራተኞች ህዝቡን ለማገልገል በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው…” ምናምን ይልላችኋል፡፡ ይሄኔ ነው “እዚህ ላይ ታቆማለህ…” ማለት የሚያስፈልገው፡
ደግሞላችሁ…“ነዋሪዎቹ የመንደሩ መፍረስ ለልማት በመሆኑ ደስተኛነታቸውን ገልጸዋል” ሲባል… አለ አይደል… “እዚህ ላይ ታቆማለህ…” ማለት ያስፈልጋል፡፡
ባልበላነውና ባላየነው ነገር፣ “ጓዳቸው ሞልቷል፣ ደስተኞች ናቸው…” ምናምን ስንባል  “እዚህ ላይ ታቆማለህ…” ማለት ያስፈልጋል፡፡
የምር ግን… ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ይቺ አገር በዋናነት ያጣችው ተሰሚነት ያላቸው የእምነት አባቶች ናቸው፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ችግር ሲፈጠርና በሀሉም ወገን ስሜቶች ጣራ ሲነኩ… አለ አይደል… “ግዴለም፣ እስቲ እልሁ ይቆይና ረጋ ብላችሁ ምከሩ…” የሚሉ አባቶች እያጣን ይመስለኛል፡፡ አስታራቂዎች ማለት… “ከእናንተ ቃልማ አንወጣም…” የሚባሉ የአገር ዋርካዎች እየጠፉ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የምር ግን የእምነት አባቶችና ጠበቆች መንግሥተ ሰማያት የመግባት ዕድላቸው ትንሽ ነው የሚባለው እንዴት ነው! በቀልዱም በምኑም የምንሰማው ነዋ!
ታዲያላችሁ…እሷና እሱ ለመጋባት ወደ ማዘጋጃ ቤት ሲሄዱ አደጋ ይደርስባቸውና ሁለቱም ህይወታቸው ያልፋል፡፡ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ቅድሚያ ፈቃድ ያገኛሉ፡፡ እዛም ሆነው ተራቸው እስኪደርስ ይጠብቃሉ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም ሲመጣም መንግሥተ ሰማያት ውስጥ መጋባት እንደሚፈልጉ ይነግሩታል። እሱም “ይሄ ነገር ከዚህ በፊት ተደርጎ አያውቅም፡፡ እስቲ ምን ማድረግ እንደሚቻል ላጠያይቅ፣” ይልና ይሄዳል፡፡
ቢጠብቁ፣ ቢጠብቁ አይመጣም፡፡ ለወራት ይጠብቃሉ፡፡ እግረ መንገዳቸውን “ከተጋባን በኋላ መሀላችን የሆነ የሚያለያይ ነገር ቢፈጠርስ!” ምናምን እያሉ ያወራሉ፡፡ የተወሰኑ ወራት ቆይቶ ቅዱስ ጴጥሮስ ይመጣል፡፡
“ጥሩ፣ ጥያቄያችሁ ተቀባይነት አግኝቷል። መንግሥተ ሰማያት መግባት ትችላላችሁ፣” ይላቸዋል፡፡ እነሱም ካመሰገኑ በኋላ ምን ይሉታል…
“ድንገት በመሀላችን አለመግባባት ቢፈጠር መንግሥተ ሰማያት መፋታት እንችላለን?” ይሉታል።
ቅዱስ ጴጥሮስም ይዞት የነበረውን መዝገብ በንዴት መሬት ላይ ይወረውረዋል፡፡ እነሱም በፍርሀት ተውጠው…
“ምነው፣ ምን አጠፋን?” ይሉታል፡፡ ምን ቢላቸው ጥሩ ነው…
“የሚያጋባችሁ መንግሥተ ሰማያት የገባ ቄስ ለማግኘት ሦስት ወር ፈጅቶብኛል፡፡ የሚያፋታችሁ ጠበቃ ለማግኘት ምን ያህል እንደሚወስድብኝ አታውቁም!” ብሏቸው አረፈ፡፡
እናላችሁ…እንደ ልባችን እየተናገርን ወይም እየሠራን… “እዚህ ላይ ታቆማለህ…” የሚባለው ነገር የሚመጣው ‘ነገር አብራጅ’ እየጠፋ ነው፡፡ አለ አይደል…የሆነ ነገር ቀዩን መስመር ከማለፉና እዚህ ላይ ታቆማለህ…ተብሎ ነገር ከመካረሩ በፊት… ከእኛ ቃል ከወጣችሁማ…” የሚሉ ከአንገት በላይ ሳይሆን ከልብ የሚያቀራርቡ አባቶች አንሰውናል፡፡
እናማ የሚያቀራርቡን ሳይሆን…የሚያራርቁን ነገሮች እየበዙ በሄዱበት በዚህ ጊዜ “ልጆቼ…እስቲ ረጋ በሉና ልባችሁን አዳምጡ…” ምናምን ብለው የደፈረሰው ይበልጡኑ እንዳይደፈርስ የሚያደርጉ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሰዎቹ ጎረቤታሞችና የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች ናቸው፡፡ አንደኛው ሰውዬ ከተወለደች ጀምሮ ተንከባክበው ያሳደጓት ፍየል አለቻቸው፡፡  እናላችሁ…ጎረቤቶቹ “ሽጥልን” ይሏቸዋል፡፡ እሳቸውም ገንዘብ አስፈልጓቸው ኖሮ እያዘኑም ቢሆን ይሸጡላቸዋል፡፡ ሰዎቹም ወዲያውኑ ፍየሏን ያርዱና እየበሉ እያለ የሸጡት ሰው ይመጣሉ፡፡ ታዲያላችሁ…እንደተቀመጡም ከቁርጡ ብድግ አድርገው መብላት ይጀምራሉ፡፡ ሰዎቹ ይደነግጣሉ፡፡
“ምነው?” ይሏቸዋል፡፡
እሳቸውም “ምነው?” ይላሉ፡፡
“የእኛና የአንተ እምነት አንድ አይደለም፡፡ እኛ ያረድናትን ፍየል ስጋ እንዴት ትበላለህ?” ይሏቸዋል። ሰውየው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ከውልደቷ ጀምሮ ያሳደግኋት እኔ፡፡ እናንተ ዘንድ አንድ ሰዓት ያህል ሳትቆይ ተለወጠች እንዴ?”
እናላችሁ…የእኛ ‘በሆነ ባልሆነው’ መለያየት አንሶ ፍየሏንም ሊያስገቧት! ቂ…ቂ…ቂ…
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሆነ ትንሽ ልጅ ጉልበተኛ ሲሰድበው፣ ወይ የሆነ ነገር ሲነጥቀው ሄዶ አባቱ ትከሻ ላይ ያለቅሳል፡፡ አባትም…
“ምን ሆንክ?” ይለዋል፡፡ ልጅም…
“ይሄ ጩኒ መታኝ፣” ይላል፡፡ አባትም የልጁን ራስ እያሻሸ..
“አታልቅስ አይዞህ፣ እኔ የማደርገውን አውቃለሁ፣” ይለዋል፡፡ ልጅም ደገፍ ብሎ ‘የሚያለቅስበት ትከሻ’ና የሚሰማው አባት በማግኘቱ ደስ ይለዋል፡፡
እናላችሁ…ዘንድሮ የቸገረን ዋና ነገር ደገፍ ብለን የምናለቅስበት ትከሻ ማጣታችን ነው፡፡
የእውነትም…ደገፍ ብሎ የሚያለቅስበት ትከሻ የሚያገኝ ልጅ ዕድለኛ ነው፡፡
ብንበደል እንኳ ደገፍ ብለን የምናለቅስበት የአባቶች ትከሻ አንሶብን ተቸግረናል፡፡
ታዲያላችሁ… እዚህ ላይ ታቆማለሀ…” ምናምን እየተባለ ያበጠው እንዳይለይለት… አለ አይደል… “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል…” የሚሉ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡    
እናማ… “እዚህ ላይ ታቆማለህ…” መባባል የሚመጣው መስመር ሲታለፍ ነው፡፡ መስመር ከታለፈ በኋላ ደግሞ መመለሱ አስቸጋሪ ስለሆነ…ለሁሉም ነገር እስቲ መጀመሪያ ረጋ በሉና ልባችሁን አዳምጡ የሚሉ ‘የእውነትም ለነፍሳቸው ያደሩ’ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6026 times