Saturday, 06 January 2018 12:59

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(11 votes)

 የገና ስጦታ
               
    ሰውየው ለመሞት ወሰነ፡፡ ገመድ ገዝቶ ራሱን ሰቀለ፡፡ አለመታደል ሆኖበት ..ገመዱ ተበጠሰና ህይወቱ ተረፈ፡፡ …ያሰበው  አልተሳካለትም!! …
ሰውየው ተቸግሯል፣ ጨለማ ውጦታል፣ በሮቹ ሁሉ ተዘግተውበት ግራ ገብቶታል፡፡ … አሰበ … አሰበና ትንፋሹን የሚያቆይበት አማራጭ በማጣቱ መታሰር ፈለገ፡፡ እስር ቤት መከርቸም፡፡ … ድንጋይ ይዞ ከመንገድ ዳር ቆመ፡፡ … ወታደሮች የጫነ የመንግሥት መኪና ሲመጣ ጠበቀና መስታወቱን አነከተው፡፡ … ግርግር ሆነ፣ መንገድ ተዘጋ፡፡ … ወታደሮቹ አጥፊውን ፍለጋ ሲሯሯጡ … “እኔ ነኝ የሰበርኩት! ሆን ብዬ ነው ያደረግሁት!” … እያለ ቢጮህም እሚሰማው አላገኘም፡፡ “አንተ ብትሆን ኖሮ እዚህ አትቆምም ነበር!” … ብለው ጥለውት ሄዱ፡፡ አሁንም ሳይሳካለት ቀረ፡፡
ተስፋ ቆርጦ መንገድ፣ … ለመንገድ ሲንቀዋለል … በሰልፍ የሚመጡ ብዙ ሰዎችን ተመለከተ። … ወደ አዲስ ወህኒ ቤት በመዛወር ላይ የነበሩ እስረኞች ናቸው፡፡ እንደ መንገደኛ ጠጋ ብሎ … “መታሰር ስለምፈልግ እባካችሁ ባንዳችሁ ቦታ ቀይሩኝ” እያለና … እየተከተለ ተማጠናቸው፡፡ … አሳቻ ቦታ ላይ አንደኛው እስረኛ፤  “ና … በኔ ቦታ ግባ” … አለውና ቀይሮት ተፈተለከ፡፡
በጉዞው ላይ የተቀየረው እስረኛ ምን አጥፍቶ እንደታሰረ የወህኒ ቤት ባልደረቦቹን ጠየቃቸው። አንድ እስረኛ ባልደረባው፤ ባልሰራው ወንጀል፣ በሃሰት ተመስክሮበት፣ ሞት የተፈረደበት መሆኑን ነገረው፡፡ “ጎሽ!” … አለ ሳያስበው፡፡ … ሰዎቹ በመገረም፤ “እንዴት ‹ጎሽ› ትላለህ? .. በሱ ቦታ’ኮ የምትሞተው አንተ ነህ?!” አሉት፡፡
… “እሱ ያለ ጥፋቱ ስለተፈረደበት … እግዜር እኔን ልኮ ነፃ አወጣው፣ ያስፈረዱበትና የፈረዱበት ደግሞ ኪሳራ ውስጥ እንዳይወድቁ እኔ በፍላጎቴ እሞትላቸዋለሁ…” አላቸው፡፡ እሱ ይሄን ያለው ከልቡ ነበር … እነሱ ግን የሚቀልድ መስሏቸው ተዝናኑ፡፡ ተዘባበቱበትም፡፡
አዲሱ ወህኒ ቤት እንደደረሱ፣ እስረኞቹ አንድ በአንድ እየተፈተሹ፣ ተቆጥረው እንዲገቡ ተደረገ፡፡ … ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያመለጠው እስረኛ ስም በድምፅ ማጉያ በተደጋጋሚ ተጠራ፡፡ … አጅሬም የራሱ ጉድ መሆኑን እንዳወቀ .. በመጀመሪያ “ተነቅቶብኝ ይሆን?” … በማለት ተጨነቀ፡፡ … ነገር ግን ለመሞት የቆረጠ በመሆኑ የመጣውን ለመቀበል፣ ወደ ተጠራበት ቀጥ ብሎ ሄደ፡፡
ከቢሮው እንደደረሰ የወህኒ ቤት ኃላፊው ከበራፉ ቆሞ ጠበቀው፡፡ የሞቀ ፈገግታ እያሳየው፤ … “ለምንድነው ስትጠራ በቶሎ የማትመጣው?” በማለት ጠየቀውና መልሱን ሳይጠብቅ፤ “እንኳን ደስ ያለህ! … ገድለኸዋል የተባለው ሰው በህይወት ስለተገኘ … ባስቸኳይ እንድትፈታ ትዕዛዝ ደርሶናል፤ ከአሁን በኋላ ነፃ ሰው ነህ”! አለው፡፡ … ኃላፊው፤ ሰውየው ፊት ላይ ምንም የመደሰት ምልክት ባለማየቱ፣ እንደውም ግር ያለው ነገር ስለመሰለው እየተገረመ … “በል ወንድሜ እንዳንወቀስ፣ ጨርቄን፣ ማቄን ሳትል ሂድልን!” ብሎ ከመገፍተር በማይተናነስ መንገድ ጊቢውን ለቆ እንዲወጣ አስደረገው፡፡ ሰውየው ለሶስተኛ ጊዜ አልተሳካለትም!!
በዕድሉ እየተማረረና እየተከዘ ወደ መኖሪያው ማዝገም ጀመረ፡፡ … የገና ዋዜማ መሆኑን ያስታወሰው፣ … የገና አባት ከመንገድ ዳር ቆሞ፣ ለአላፊ አግዳሚው ስጦታ ሲያድልና ሲያዝናና ሲመለከት ነበር፡፡ ዓይን ለዓይን ሲገጣጠሙ፣ መንፈስ የሚያናውጥ ስሜት ውስጡን አርገፈገፈው። … ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡ … የገና አባትም፤ “ስጦታዬን ጨርሻለሁ!” አለው፡፡ … ወደ እርሱ ቀረበናም በለሆሳስ፤ “ያንተን ስጦታ ቤትህ ከሰቀልከው አሮጌ ኮትህ ኪስ ውስጥ አስቀምጬልሃለሁ” አለው፡፡
መንፈሱ እስኪረጋጋለት ጠበቀና፣ እራሱን እየተቆጣጠረ፡-
“ምን አልከኝ? … ምንድነው ‘ምታወራው?” .. ሲል የገናን አባት ጠየቀ፡፡
የገና አባትም፤ “ለመሆኑ አውቀኸኛል?” በማለት መልሶ ጠየቀው፡፡
“ማነህ?”
“እግዜር ነኝ”
“እ…እግዜር…?”
“አዎን”
አጅሬው በቆመበት ማሰብ ጀመረ፡፡ አሰበ፣ አሰበና የደረሰበት እንግልት ሁሉ ከፊቱ ድቅን አለበት፡፡ ብስጭት በቃኘው ድምፅ፤ “ስማ አቶ እግዜር… መኖርን ብትከለክለኝ … እንዴት ሞትን ትነፍገኛለህ?” በማለት ጠየቀው፡፡
“ሞትን ልብህ ውስጥ አላየሁም” ሲል መለሰ የገና አባት፡፡
“እንዴ…? ስንት ጊዜ…?” በማለት ሰውየው ለመሞት ያደረገውን ሙከራ ሊያስረዳው ታተረ፡፡
“አውቃለሁ፡፡ ለኔ ልትነግረኝ ትፈልጋለህ!?”
“እና?” … አለ፤ ሰውየው እየተቆጣ፡፡
የገና አባትም በለሰለሰ አንደበቱ፤ “ልጄ ነገርኩ‘ኮ … ልብህ ውስጥ ተስፋን እንጂ ሞትን አላየሁም”
“አይ፣ አይ! … እንደዚህ ከምኖር መሞት ይሻለኛል!” … አለ አጅሬ፡፡
እግዜርም እንደ መገረም ብሎ፡- “እንደዛ ከፈለግህም … ችግር የለም፡፡ ሞትን እልክልሃለሁ” … አለው፡፡
“መቼ?”
“ዛሬውኑ! … ለሊት ጎረቤትህን መስሎ ይመጣል .. በርህን ሲያንኳኳ ወዲያውኑ እንድትከፍትለት”
“በጣም ጥሩ! … እጠብቀዋለሁ!” … አለ ሰውየው፤ … በልበ ሙሉነት፡፡
የገና አባት ፊቱን አዙሮ መሄድ ጀመረ፡፡ የሆነ ነገር ለማለት የፈለገ ይመስል…ድንገት መለስ አለ። ሰውየው ወደሚሄድበት አቅጣጫ ተመለከተና ተመልሶ መንገዱን ቀጠለ፡፡
አጅሬው ከራሱ ጋር እያወራ፣ ምሽት ላይ ከመኖሪያው ደረሰ፡፡ የቤቱን መብራት አብርቶ በሩን ቆለፈ፡፡ ደክሞት ነበረና ወደ ውስጥ ተራምዶ ከወንበሩ ላይ ዘፍ አለ፡፡… ዘወትር እንደሚያደርገው፣ ትንሷን ሬዲዮን ከፍቶ ማዳመጥ ጀመረ፡፡… የዕለቱን ዜና ለመስማት እየጠበቀ ሳለ፣ ዓይኖቹ ግድግዳው ላይ ከተሰቀለው አሮጌ ኮቱ ላይ አረፈ፡፡ የገና አባት የነገረው ትዝ አለውና ብድግ አለ፡፡ ኪሶቹን በደንብ በረበራቸው፡፡ ጠፍታበት ከነበረ የሎቶሪ ቲኬት በስተቀር ምንም ነገር አላገኘም፡፡ እየደጋገመ ፈተሻቸው፤ ያው ነው፡፡
መጠራጠር ጀመረ፡፡ “የቅድሙ የገና አባት በርግጥ እግዜር ነበር? ወይስ አእምሮዬ የፈጠረው ቅዠት ነው?” እያለ… የተለያዩ ነገሮችን በዓይነህሊናው እያመላለሰ አሰበ፡፡… የዕለቱ ዜና ሲጀምር ሃሳቡን ወደ ሬዲዮው ሰበሰበ፡፡ … ዜናውን ተከትሎ የገና ሎተሪ መውጣቱ ተገለፀ፡፡ ዕድለኛ የሆኑት አሸናፊ ቁጥሮች ሲዘረዘሩ፣ ሰውየው ጆሮውንና ዓይኑን ማመን አልቻለም፡፡ … በጁ የያዛት ሎተሪ ቁጥርና በሬዲዮ የሰማው ቁጥር አንድ ዓይነት ሆኑበት፡፡
የሰማው ነገር ዕውነት መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥ፣ የሚቀጥለው የዜና ሰዓት እስከሚደርስ ብዕርና ወረቀት አዘጋጅቶ መጠባበቅ ጀመረ፡፡ የጊዜው መርዘም የአንድ ሚሊዮን ዓመታት ያህል መስሎ ተሰማው፡፡ ድንገት ደግሞ በሌላኛው የአእምሮው ጎን ይመጣል የተባለው እንግዳ፣ በከፍተኛ ፍጥነት ወደርሱ እየገሠገሠ መሆኑ ደወለበት፡፡
ህይወትና ሞት የወለዱት ዕውነት፤ አንደኛው እግሩ ልቡ ውስጥ፣ ሌላኛው ደግሞ አናቱ ውስጥ ተተክለው ዥዋዥዌ እያጫወቱት ነው፡፡… በልጅነቱ ያልገባው “ቲዎሪ ኦቭ ሪላቲቪቲ” ደግሞ ከተደበቀበት ብቅ ብሎ “አወቅኸኝ… እኔ‘ኮ ነኝ” እያለ ከሌላው የአዕምሮው ጥግ እጆቹን አወዛወዘለት፡፡…ሰዓቱ እየገፋ መጣ፡፡… ሃሳቡን እንደ ምንም ሰብስቦ ሬዲዮኑ ላይ አፈጠጠ፡፡.. የሚሰማው ድምፅ ግን የእንግዳው ኮቴ መሰለው፡፡
ከዜናው በሁዋላ አሸናፊዎቹ ቁጥሮች መጠራት ሲጀምሩና በሩ ሲንኳኳ አንድ ሆነ፡-
“8…4 …ጓ!…ጓ!…ጓ!…6”
..3…2 …ጓ!…ጓ!…ጓ!…ጓ! ክፈት!... እገሌ ነኝ!”
የሚፅፋቸው ቁጥሮች ከሬዲዮው የሚሰማቸው ሳይሆን… እዛው አእምሮው ሰሌዳ ላይ ቦግ ድርግም እያሉ ድብብቆሽ የሚጫወቱ ሆኑበት፡፡
“…ጓ!…ጓ!…ጓ! ኧረ ክፈት!”
እጁ እየተንቀጠቀጠ… የፃፈውን ቁጥር እንደ ምንም ከሎተሪው ቁጥር ጋር አመሳከረ፡፡ የበለዘ ዓይኖቹን እያሻሸ እንደገና አስተያያቸው፡፡.. አንድ ዓይነት መሆናቸውን እንዳወቀ ራሱን ሳተ!!
It is Christmas!
Christmas is here,
after all
let happiness be
everywhere and for all.
Yes it is Christmas,
In hospital beds
And prison cells,
It is still Christmas.
To forget hatred-among
the human race.
Yes, it is Christmas to hope!!
ሰውየውን ያነቃው ሳይዘጋ ካደረው ሬዲዮ የሚወጣው መዝሙር ነበር፡፡ እንዴት ነው --- ሰውየው አሁንም አልተሣካለትም? ወይስ…?
መልካም የገና በዓል ይሁንልን!!
ሠላም!!
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው የጸሃፊው የእንግሊዝኛ ግጥም፣ በ1995 ዓ.ም በገጣሚ ነቢይ መኮንን ወደ አማርኛ ተተርጎሞ፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ነበር፡፡

Read 4588 times