Saturday, 08 April 2023 19:48

“አቦ… ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንዳንድ ነገሮችን ስናይ ምን እንላለን መሰላችሁ...“ጫን ያለው መጣ!”  እናማ ዘንድሮ ብዙ ነገሮችን ስናይ... አለ አይደል... “ጫን ያለው መጣ፣” እንበል፣ ወይስ የድራማ ሰዎች እንደሚሉት፤ “ይሄ ‘ዘ ኦፕኒንግ አክት’ የሚሉት ብቻ ነው!” እንበል ያሰኛል፡፡ ኮሚክ እኮ ነው፣ ደግሞላችሁ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... አንዳንድ ነገሮች ሁልጊዜ ‘ኦፕኒንግ አክት’ ነገር እየመሰሉ ግራ ገብቷችሁ አያውቅም! እንደው ቀድሞ ከነበረበት ትንሽ እንኳን ፈቀቅ ማለት የለ!  እንደው ቀድሞ ከነበረበት ትንሽ እንኳን ከፍ ማለት የለ!
አንዲት ከዚህ ቀደም ያወራናት ቀልድ አለች፡፡ መድረክ ላይ የሮሚዮና ጁሊየት ድራማ እየታየ ነው፡፡ 
ጁሊየት፡- “ሮሚዮ፣ እባክህ ሳመኝና ቤቴ ልሂድ!”
ሮሚዮ፡- “አልችልም…”
ጁሊየት፡- “እባክህ ሮሚዮ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ሳመኝና ቤቴ እሄዳለሁ፡፡”
ሮሚዮ፡- “አዝናለሁ፣ ግን አልችልም፡፡”
ጁሊየት፡- “ሮሚዮ፤ የእኔ ፍቅር ሌላ ጊዜ አላስቸግርህም፣ አንዴ ሳመኝና ቤቴ ልሂድ!”
ይሄኔ ከተመልካች መሀል አንዱ የተበሳጨ ምን አለ፣ አሉ መሰላችሁ…
“አቦ… ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድ!” አለና አረፈው፡፡
እናላችሁ... ከመጀመሪያው ትዕይንት ፈቀቅ አልል ያሉ ነገሮች እየበዙ ሲሄዱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ልክ እኮ የሆነ መጽሐፍ በመቅድም ተጀምሮ ቀጥሎ ወላ አንደኛ ምዕራፍ የለ! ወላ ምናምነኛ ምዕራፍ የለ! ከዛ በኋላ፣ “ከዛ በኋላ ትዳር መስርተው፣ ልጆች ወልደው ለብዙ ዘመናት በደስታ ኖሩ ይባላል፣” ብሎ አንባቢ-ተኮር መዝጊያ የለ! (ቂ...ቂ...ቂ...) ዞሮ እዛው፣ ዞሮ እዛው፣ ዞሮ እዛው!፡፡ 
እሳቸው፣ ማለትም የድርጀቱ አለቅየው ዓመታዊ ሪፖርት እያቀረቡ ነው፡፡ ከተሾሙ አሥራ አንድ ወርም አሥራ አንድ ዓመትም ሊሆናቸው ይችላል፡፡ (እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... አንድ ሰሞን “የምን ስልጣን፣ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ እንቅልፍ ነው” የሚል ወይም የዚህ አይነት ቃና ያላት ነገር ነበረች መሰለኝ፡፡ እናማ... ምነው እሷ ነገር፣ በፈረንጅ አፍ እንደሚሉት ‘ፌድ’ እያደረገች፣ ‘ፌድ’ እያደረገች፣ ጭል ጭል የምትል ምልክት ቢጤ የማናይሳ! ነው... ወይስ የቅርንጫፎቹ ነገር “ወይ ፍንክች!” ሆኖ የዛፍ ላይ እንቅልፉ የተመቸን በዛን? እንደው ሲከነክነን ከሚሰነብትና ከሚከርም ለማለት ያህል ነው፡፡)
እና እሳቸው የተለመደውን ሪፖርት፣ በተለመደው ጊዜ ያመጣቸው ቃላት፣ በተለመደው የጊዜ የቪ.አይ፣ፒ. ኩስተርና እያቀረቡ ነው፡፡ “ደርጅታችን ያለውን የሰው ሀይልና ድርጅታዊ አቅም በማሳለጥ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት፣ ምርቱን ምናምን መቶ በመቶ ለማሳደግ እቅድ ነድፎና አቅጣጫ አስቀምጦ፣ ርብርቡን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡”
“ኸረ በህግ አምላክ!...የዚህ ድርጅት አለቆች ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ ይህንን ስትሉ ከርማችኋል እኮ! “እስቲ ያለፈውን ዓመት ሪፖርት አውጥተህ ቀኑንና ዓመተ ምህረቱን ለዋውጠህ እንደገና በኮምፒዩተር አስመትተህ ለነገ አቅርብልኝ!” የሚል፣ ወይም የሚል ቃና ያለው ትእዛዝ ባይኖርም፣ ከምንሰማቸው ነገሮች ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ሲበዙብን ዘጠና ዘጠኝ ነገሮች ብንጠረጥር አይገርምም፡፡ ዘጠና ዘጠኝ ጊዜ ተሰላችትንም “አቦ… ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድ!” ብንል አይፈረድብንም፡፡
“ይሄን የፈረደበት የኳስ ወሬ ደግሞ አመጣብን!” አትበሉኝና...የእውነት ዛፍ ላይ እንቅልፍ ያለው በእንግሊዝ በፕሬሚየር ሊግ ነው፡፡ ልክ ነዋ...“ያለበት ሁኔታ ነው ያለው...” የሚለውን በ“አጠናክሮ ይቀጥላል...” በመተካት ብቻ የሚለወጥ  ነገር የለማ! እናላችሁ...ልብ ብላችሁልኝ እንደሁ አንድ አሰልጣኝ የሆነ ቡድንን ሲይዝ መአት ነገር ይወራል፡፡ እንዴት ቡድኑን እንደሚለውጠው፣ እንዴት በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ እንደሚያስፈነጥረው--ምናምን፡፡ ከዛላችሁማ...አይደለም የተወራው ሊፈጸም ቀርቶ ቡድኑን ሲረከበው የነበረውን ደካማ አቋም እንኳን ጠብቆ ማቆየት ይቸግረዋል፡፡ ከዛ ድንገትም የቡድኑ አለቆች አንገታቸው ምናምን ላይ ይደርስና “ቻዎ፣ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ...” ምናምን ብለው ያሰናብቱታል፡፡ የቅጥር ውሉን ሲፈጽም የገባውን ቃል አልፈጸመማ!
እናማ...አለቆች ሳሳ ካለች ወንበር ወፈር ወዳለው ወንበር ሲሸጋገሩ፣ ወይም ከአንደኛው ወፍራም ወንበር ወደ ሌላኛው ወፍራም ወንበር ሲሸጋገሩ ሊፈጽሙና ሊያስፈጽሙ ቃል የሚገቧቸው ነገሮች የሉም እንዴ! “ግራ ቢገባን ነው፡፡
ለምሳሌ እንበልና... የሆኑ ሰዎች ለገሚሶቻችን ‘በሚረባ’ ምክንያት፣ ለገሚሶቻችን ደግሞ  ‘በማይረባ’ ምክንያት ይጋጫሉ እንበል፡፡ እንደውም እኛ ዘመድ የመሆን ነገር በሚባልበት ዘመን ሆነና፣ ‘የሚረባ’ እና ‘የማይረባ’ ከሚባሉት ሌላ መአት ሀገር በቀል ‘መለኪያዎች’ ሳይኖሩን አይቀሩም፡፡ ልክ ነዋ ብዙዎቻችን የሚረባና የማይረባ ማለቱን ትተን ቀሺም ቦተሊካ፣ ወይም ቦተሊካ የሚመስል ቀሺም ነገር የፈጠረው ትርክት (‘ጭቅጭቅ’ ላለማለት የጨዋነት መንገድ ለመፈለግ የተደረገ ሙከራ!) ውስጥ ይገባላችኋል፡፡
“በመጀመሪያ ደረጃ በሁለቱ መሀል የተፈጠረውን ግጭት ታሪካዊ አመጣጡን መፈተሽ አለብን፡፡” ሰውዬ፣ አሁንም በህግ አምላክ! የምን ታሪካዊ ምናምናዊ ቅብጥርሶ ነው!
“ምንድነው የምትለው! ሌላ መስሎህ ከሆነ፣ እኛ እኮ እያወራን ያለነው በእንትናና እንትና መሀል በሁለት ሺህ ብሩ ብደር የተፈጠረውን አለመግባባት ነው፡፡
“ኖ! እናንተ አይገባችሁም፡፡ ይሄ ዝም ብሎ አለመግባባት አይደለም፡፡ ከጀርባው ታሪካዊ መነሻ ያለውና ሆነ ተብሎ አንዱን ወገን ለመጉዳት የሚደረግ ነው፡፡” ‘ሰውየዋ የየትኛውን ሀገር ካቴ ገልብጣ ነው እንዲህ ቀብጠርጠር የሚያደርጋት!’  ‘ካቴ’ም የለች፣ የብርጭቆው ግማሽ ፈሳሽ የልብስ ሳሙና የፈጠረው በሚመስል አረፋ የተሞላ ድራፍትም የለ... እናማ፣ እኛን ባያገባንም እንዲሁ የሆነች ነገር ወርወር ለማድረግ፣ ሰውየዋን የሚያስቀባጥራት ነጩ ካቴ ሳይሆን ቀለሙ ለይቶለት ያልለየው የዘመኑ የቦተሊካ ካቴ ነው፡፡ ታዲያማ በሚያገባቸው፣ የሚያገባቸው በሚመስሉና እንደማያገባቸው ቢታወቅም፣ በ“ምን የቆረጠው ነው ቀና ብሎ የሚያየኝ!” በሚል አይነት ‘ማስተር ኦፍ ሴርሞኒ’ አይነት በሚያደርጋቸው (ቂ...ቂ...ቂ...) መሰል የፊትና የኋላ መብራቶቻቸው የማይለዩ፣ ፍሬቻ የሚባል ነገር የማያውቁ ነገሮችነ በተደጋጋሚ ስንሰማ  “አቦ ሳማትና... አይነት ስሜት ቢያድርብን አይገርምም፡፡
ታዲያላችሁ...ሁለት ሰዎች ሲጋጩ ዘንድሮ...
“ቆይማ ረጋ በሉ፡፡ ጥል ለማንም አያዋጣም፡፡”
“መጀመሪያ እስቲ ቁጭ ብላችሁ ተነጋገሩ፡፡”
“ሦስተኛ ሰው ሳታስገቡ ራሳችሁ ለመጨረስ ሞክሩ፣” ምናምን ከማለት ይልቅ በሁለቱም ወገን “ሃይ! ዘራፍ!...” ባይ መአት ነው፡፡ በአንደኛው በኩል...
“እሱ ነው እኮ ፊት እያሳየ እዚህ ያደረሰው፡፡ አንድ ጊዜ መንጋጭላውን ብሎ አያነጥፈውም! ያኔ እያንዳንዷን ሳንቲም ቁጭ ያደርጋት ነበር!” የሚል ‘ያገባኛል ባይ፣’ ይፈጠራል ብቻ ሳይሆን ይፈለፈላል፡፡ በዛኛው ወገን ደግሞ...
“እኔ እኮ የምለው “እንዴት ቢደፍርህ ነው! እዚህ ደረጃ ሲደርስ ዝም ብሎ ተመለከተ፡፡ እንዴት ቢደፍረው ነው ያልሰጠውን ገንዘብ መልስልኝ የሚለው! ወይ ነዶ!” ባዮች ከባለጉዳዩ በላይ ባለጉዳይ ይሆናሉ፡፡ እናማ እንኳን አባባሾች ኖረው ቀርቶ፣ እንዲሁ አየሩ ራሱ ‘ነገር፣ ነገር’ የሚያሰኛችሁ፣ ለትርጉም የሚያስቸግር ዘመን ነው፡፡
እናላችሁ... ነገርዬው ይባባስና ሌላ፣ ሌላ ደረጃ ይከተላል፡፡ ይሄኔ ነው የነገር አባባሾች ‘ሲዝን ሁለት’ ታሪኩ ሙሉ ለሙሉ ይለወጥና ይቀጥላል፡፡ አንደኛው ወገን...
“እነሱ ራሳቸው ተነጋግረው አይፈቱትም ነበር እንዴ!”
“ጭራሽ ጎረምሳ ይመስል ይዛዛታሉ እንዴ!”
 እነኛው አባባሾቹ፣ እነኛው ነገሩ ሲያጦዙት የከረሙት፣ እነኛው ባለጉዳይ ሳይሆኑ ባለጉዳይ የሆኑት ሰዎች፣ ዋነኞቹ ሰላም ፈላጊዎች፣ ዋነኞቹ በግብረ ገብ የተሞሉ ሰዎች ሆነው ቁጭ! (“ዳዝ ዛት ሳውንድ ፌሚሊየር?” የሚለውን ሀረግ የት ነው የሰማሁት?) እናላችሁ... መሰል ጨዋታዎችን በማህበራዊ ኑሮም፣ በቦተሊካውም ደጋግመን ስለምናይና ስለምንሰማ፤ “አቦ… ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድ!” አይነት ነገር ቢሰማን አያስገርምም ለማለት ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1321 times