Saturday, 24 June 2023 20:38

ኳስ እና የቆዳ ቀለም!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


         እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...እስቲ ዛሬ ኮምጨጭ ብለን ስለ ኳስ እናውራማ፡፡ ስለ ስፖርቱ ሳይሆን በተለይ በአውሮፓ ሊጎችና በሌሎችም አካባቢዎች ስለተባባሰው፣ በአብዛኛው ጥቁር ተጫዋቾች ላይ እየደረሱ ስላሉ ጥቃቶች፡፡
ሊወራ የሚገባውን ያህል የተወራበት ስላልመሰለኝ ነው፡፡ (ለነገሩ የአሁኑን እንጃ እንጂ አንድ ሰሞን በራሳችን የእግር ኳስ ሜዳዎች ቅልጥ ያለ ዘረኝነት ነበር አይደል እንዴ!)  ምን መሰላችሁ-- ተጫዋቾቹ በተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን፣ በራሳቸው ደጋፊዎችም ነው ጥቃቱ የሚደርስባቸው፡፡
የበቀደሙን በማንቼስተር ሲቲና ኢንተር ሚላን መካከል የተካሄደውን የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ አይታችሁ እንደሁ፣ ማን ሲቲ አንድ ለባዶ እየመራ ሳለና ጨዋታው ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ሲመጣ፣ ኢንተር ሚላኖች እኩል የሚያደርጋቸውን እድል ያገኛሉ፡፡
 በረኛው የመለሳትን የሉካኩ (ረስቼው ካልሆነ) ሙከራ ተከትሎ፣ የግቡ አፋፍ ተርመስመስ ይላል፡፡
 ያቺን ኳስ ሌላኛው የኢንተር ሚላን ተጫዋች ዝቅ ብሎ በጭንቅላት ይመታትና ሙሉ ለሙሉ መረቡ ላይ ልታርፍ ትችል የነበረችው ኳስ፣ በትርምሱ ፊቱን ወደ መረቡ አድርጎ የነበረው ሉካኩ ተረከዝ ላይ ነጥራ ትመለሳለች፡፡
በማናቸውም አይነት ትንታኔ፣ በነበረው ፍጥነትና ትርምስ ሉካኩ በዛች ቅጽበት ያቺን ኳስ ሊያያት የሚችልበትን ሁኔታ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ማን ሲቲዎች ዋንጫውን ከወሰዱ በኋላ፣ ሉካኩ ላይ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የወረደበት የዘረኝነት ናዳ የጉድ ነበር፡፡
ምን መሰላችሁ... ሉካኩ አንድ ሰሞን እኮ በተከታታይ ግብ እያስቆጠረ ሚላኖችን ሲያስፈነጥዝ የነበረ ነው፡፡
የአጥቂ መስመራቸው ዋነኛ ፊትአውራሪ ሆኖ ሲጨፍሩለትና ሲያስጨፍራቸው የነበረ ነው፡፡ በዛች ትርምስ ውስጥ በተፈጠረች አጋጣሚ ግን አወረዱና ዘጭ አደረጉት፡፡
 እናላችሁ...እውነቱ ይህ ነው፡፡ አብዛኞቹ የአውሮፓ ሊጎች ውስጥ ማንኛውም በተለይ ጥቁር ተጫዋች፣ ግብ እስካስቆጠረና ውጤት እስካመጣ ድረስ ደጋፊዎች ስሙን ዘምረው አይበቃቸውም፡፡
ልክ ስህተት የፈጸመ እንደሆነ ግን እንትን የነካው እንጨት የሚሉትን አይነት ያደርጉታል፡፡ ወይም ዘረኞቹ ብዙ ጊዜ በሚጠቀሙበት ቋንቋ “ጦጣ” ሆኖ ያርፋል፡፡
ትዝ ይላችሁ እንደሁ ባለፈው የአውሮፓ ሀገራት ዋንጫ፣ እንግሊዞች በቅጣት ምት ተሸንፈው ከውድድሩ ውጭ የሆኑበት ጨዋታ ላይ፣ ሦስቱን የእንግሊዝ ቅጣት ምቶች የሳቱት ሦስት ጥቁር ተጫዋቾች ነበሩ...ራሽፎርድ፣ ሳንቾና ሳካ፡፡
 በዚህ ሰበብ ከእንግሊዛውያን የወረደባቸው የዘረኝነት ናዳ በአበሺኛ አነጋገር “እሪ የሚያሰኝ...” ነበር፡፡አንድ ጊዜ ካሜሩናዊው ሳሙኤል ኤቶ ለባርሳ ይጫወትበት በነበረበት ጊዜ በደረሰበት የዘረኝነት ስድብ ተበሳጭቶ ከሜዳ ሊወጣ በሚሞክርበት ጊዜ፣ እሱን አባብሎ ለመመለስ የተፈጠረው ሁኔታ አይረሳም፡፡
ምን መሰላችሁ...በእግር ኳስ የሚታየውን አስቀያሚ ዘረኝነት ይበልጥ ወደ አደባባይ ያወጣው ከጥቂት ቀናት በፊት በተካሄዱ ሁለት ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የተፈሩት ክስተቶች ናቸው፡፡
ዩሱፍ አብዱሪሳግ የተባለ የኳታር ተጫዋች ሚካኤል ቦክሶል በተባለው የኒውዚላንድ ተከላካይ ላይ የሆነ የዘረኝነት ነገር ይናገራል፡፡ ትንሽ ትርምስ ቢጤም ይፈጠርና የኒውዚላንድ አምበል፣ የመሀል ዳኛው እርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃል፡፡ ዳኛው ግን እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ መልበሻ ቤት የገቡት አብዛኞቹ ነጮች የሆኑት የኒውዚላንድ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ አልተመለሱም፡፡
 እዚህ ላይ ተሰዳቢው ተጫዋች የሳሞአ ተወላጅ ሲሆን፤ አስገራሚ የተባለው ተሳዳቢው የኳታር ተጫዋች ራሱ ጥቁር መሆኑ ነው፡፡ እንደውም ይህ በአጥቂ መስመር የሚጫወተው ጥቁር ተጫዋች፣ “እኔ ራሴ በጨዋታው ጊዜ የዘረኝነት ስድቦች ስሰደብ ነበር...” ነው አለ የተባለው፡፡
በሌላ በኩል እንዲሁ በአየርላንድና በኩዌት ከሀያ አንድ ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች መሀልም የተደረገ ጨዋታ ነበር፡፡ በዚህኛውም ጨዋታ ወቅት አንድ የኩዌት ተጫዋች፣ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረ የአየርላንድ ተጫዋች ላይ የዘረኝነት ስድብ በመሰንዘሩ አይሪሾቹ ወጣቶች ጨዋታውን አቋርጠዋል፡፡
በነገራችን ላይ ከአስር ዓመት በፊት እንዲሁ ጣልያን ውስጥ በወዳጅነት ግጥሚያ ወቅት የተፈጠረ አስቀያሚ የዘረኝነት ነገር ነበር፡፡ የተጋጣሚው ቡድን ደጋፊዎች የኤሲሚላን ተጫዋች የነበረው ኬቪን-ፕሪንስ ቦአቴንግ ላይ የዘረኝነት ስድቦችን ይወረውራሉ፡፡ የተበሳጨው ቦአቴንግም ጨዋታውን አቋርጦ ወደ መልበሻ ቤት ሲያመራ ሙሉ ቡድኑ ነው ተከትሎት የወጣው፡፡
በነገራችን ላይ የ2022 የዓለም ዋንጫን ተከትሎ፣ በማህበራዊ ሚዲያ በተጫዋቾች ላይ ይሰነዘሩ የነበሩ የዘረኝነት ስድቦችና የመሳሰሉት ላይ በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ድጋፍ ምርመራ ቢጤ ተደርጎ ነበር፡፡
በዚህም ሦስት መቶ ሰዎች ተለይተው ፊፋ ዝርዝራቸውን ለህግ አስከባሪ አካላት አስተላልፏል ነው የሚባለው፡፡
ነገሩ ተባብሶ የነበረው በተለይ በእንግሊዝና በፈረንሳይ መካከል ተደርጎ በነበረው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ወቅት ነበር፡፡
ሀያ ሚሊዮን የሚሆኑ ‘ፖስቶች’ እና አስተያየቶች ላይ በተደረገው ምርመራ፣ አሥራ ዘጠኝ ሺህ ገደማዎቹ ዘረኛ ነበሩ ተብሏል፡፡ ሠላሳ ስምንት ከመቶ የሚሆኑት ከአውሮፓ፣ ሠላሳ ስድስት ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከላቲን አሜሪካ ነበሩ፡፡
 በአሁኑ ወቅት ለለንደኑ ቶተንሀም ሆትስፐርስ የሚጫወተው ብራዚላዊው ረቻርሊሰን፣ በአንድ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ላይ ሙዝ ተወርውሮበታል፡፡  የብሬትፎርዱን ቶኒም በማህበራዊ ሚዲያ የዘረኝነት ስድብ ተሰድቦ ነበር፡፡
ሆኖም የተሳዳቢው ማንነት ታውቆ የእንግሊዝ የእግር ኳስ ፌደሬሽን፣  ለሦስት ዓመታት በማንኛውም የእንግሊዝ ስታዲየም እንዳይገባ እግድ ተጥሎበታል፡፡  በነገራችን ላይ እንግሊዝ መዋቅራዊ ዘረኝነት ከሚካሄድባቸው ግንባር ቀደም ሀገራት አንዷ ነች እንደምትባል መጥቀሱ ግድ ይላል፡፡በአሜሪካና በሜክሲኮ መካከል ሲደረግ በነበረ ግጥሚያ ወቅት፣ በተለይ ግብረ ሰዶማውያን ላይ የጥላቻ ስደቦች ሰለበዙ ጨዋታው ተቋርጧል፡፡
የብራዚላዊው ቪንሲየስ ጁኒየር አማካሪ የሆነ ሰው፣ ስፔይን ውስጥ በአንድ የስቴዲየም ስነ ሥርአት አስከባሪ (ስቲዋርድ) የዘር ጥቃት ተሰነዝሮበታል ነው የሚሉት፡፡ ማለትም ሙዝ እየወዘወዘበት ነው አሉ የዘለፈው፡፡በነገራችን ላይ በአሁኑ ጊዜ በጣም ምርጥ ከሚባሉት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ቪንሲየስ፣ ከዘንድሮ የውድድር ዘመን ጀምሮ በስፔይን ስቴዲየሞች የዘር ጥላቻ ሲሰነዘርበት ነው የከረመው ይባላል፡፡ ለነገሩ ተጫዋቹ አንዴ ኳስ ይዞ መብረር ከጀመረ.... አለ አይደል...“የፖሊስ ያለህ አትሉም ወይ፣ የዳኛ ያለህ አትሉም ወይ...” የሚያስብል ነው ይባልለታል፡፡
የወራት የዘረኝነት ጥቃት አንገቱ ላይ የደረሰበት ቪንሲየስ፣ የዛሬ ወር ገደማ ግን ሲበቃ በቃ ነው አይነት ነገር ነው ያለው፡፡ በእኛ ግንቦት 13 ቡድኑ ሪል ማድሪድ በቫሌንስያ ሜዳ ጨዋታ ነበረው፡፡ በጨዋታው ወቅት የቫሌንስያ ደጋፊዎች በቃላትና በምልክት የዘረኝነት ስድቦች ሲሰድቡት እሱም ሳይበዛ በምልክት ምላሽ እየሰጣቸው ጨዋታው ቆሞ ነበር፡፡
“አንደኛም፣ ሁለተኛም፣ ሦስተኛም ጊዜ አይደለም...” ነው ያለው በትዊተር መልእክቱ፡፡
“ዘረኝነት በላ ሊጋ ኖርማል ነው፡፡ ወድድሩም እንደ ኖርማል ነው የሚያየው፣ ፌዴሬሽኑም እንደ ኖርማል ነው የሚያየው እና ተጋጣሚዎች ያበረታቱታል፡፡”
በነገራችን ላይ የቪንሲየስ ነገር በሜዳ ላይ ብቻ አልቀረም፡፡ የብራዚል መንግሥት በሀገሪቱ የሚገኙትን የስፔይን አምባሳደር እስከመጥራት ደርሶ ነበር፡፡ በተጨማሪም የብራዚላውያኑን ተቃውሞ ለመግለጽ በሪዮ የሚገኘውና በስፋት የሚታወቀው ‘ክራይስት ዘ ሪዲመር’ የሚባለው የክርስቶስ ቅርጽ ጨለማ ውስጥ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ከፔሌ ጀምሮ ጥቁር ብራዚላውያን በሀገራቸውም ሆነ በውጪ የዘረኝነት ጥቃቶች ሲደርሱባቸው ነው የኖሩት፡፡
እንደውም እኮ ቀደም ሲል ጥቁር ብራዚላውያን ተጫዋቾች ለፕሮፌሽናል ቡድኖችም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲጫወቱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡
ለምን እንደሁ እንጃ፣ ግን የእኛ ሀገር የስፖርት ሚዲያዎች ሁሉም ባይሆኑ በርከት ያሉት ከጨዋታ እንቅስቃሴና ውጤት፣ እንዲሁም የተጫዋቾች ግዢና ሽያጭና ባለፈ እጅግ ወሳኝ ለሆኑት የዘረኝነት ክስተቶች ትኩረት የሚሰጡ አይመስሉም፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት በተለይ ቀኝ አክራሪ የፖለቲካ ቡድኖችና አልፎ አልፎም ለጥቁሮች ያላቸውን ጥላቻ መደበቅ የማይችሉ ፖለቲከኞች ምርጫ እያሸነፉ ባለበት፣ የወደፊት አውሮፓ እግር ኳስ የዘረኝነት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው፡፡
እናላችሁ... እግር ኳስ ዘረኝነቱ እየበዛ ነው፡፡ ይህን ሳናውቅ በአርሴና ማንቼ እንካ ስላንትያ መወራወር ብቻ ሙሉ ስዕሉን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 905 times