Saturday, 24 June 2023 20:45

ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በራስ መተማመን አዳብሩ


         በማንኛውም ጉዳይ ስኬት ከመቀዳጃታችሁ በፊት በራሳችሁ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ያሰባችሁትንና ያለማችሁትን  እንደምታሳኩት ማመን አለባችሁ፡፡ የወጠናችሁት ግብ የቱንም ያህል ቢያደክማችሁና ዋጋ ቢያስከፍላችሁም፣ የማታ የማታ ስኬት የናንተ መሆኑን እመኑ፡፡ ያንን የማድረግም አቅም እንዳላችሁ በራሳችሁ ተማመኑ፡፡  በቀጣዩ ዓመት አስተማማኝ ገቢ በማግኘት የፋይናንሻል ነጻነታችሁን ማረጋገጥ የምትሹ ከሆነ፣ እንደምታሳኩት ከልባችሁ እመኑ፡፡ የስኬት ምስጢሩ ከሁሉም በፊት በራስ መተማመንን ማዳበር ነው፡፡ በራሳችሁ ማመን ያለባችሁ ደግሞ ስኬትና ድል ከተጎናጸፋችሁ በኋላ አይደለም፡፡ ገና ስትጀምሩ ነው፡፡ ስለዚህ በራስ መተማመንን በልምምድ አዳብሩት፡፡
ሚሊዬነር መሆን የሚያስደስታችሁ ከሆነ፣ ከሁሉ በፊት ሚሊዬነር የመሆን አቅምና ችሎታ እንዳላችሁ በራሳችሁ ማመን የግድ ነው፡፡ ይህንን በራስ መተማመን ከማዳበራችሁ በፊት ግን ማንኛውንም ስኬት መቀዳጀት በእጅጉ ያዳግታችኋል፡፡ እንኳንስ ትላልቅ የህይወት ህልሞችን አይደለም፣ ትናንሽ የሚመስሉ የዕለት ተዕለት ጉዳዮችንም ማሳካትና መፈጸም ፈተና ነው - እንደምናደርገው በራሳችን እምነት ከሌለን፡፡ ዕቅድ ነድፈን ግባችንን እውን ለማድረግ  ወደ ሥራ የምንገባው፣ በራሳችን እምነት ሲኖረን ነው፡፡ በራስ መተማመን ከሌለን ምናልባትም፣ መጀመሪያውኑ ትላልቅ ህልሞችን የማለም አቅምና ወኔ ሁሉ ላይኖረን ይችላል፡፡  
ውስጣችሁን አድምጡ
አንዳንዶች ህሊና ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ሌሎች  ውስጣዊ ማንነት ይሉታል፡፡ ስያሜው ምንም ቢሆን ለውጥ አያመጣም፡፡ ዋናው ቁምነገር ምን መሰላችሁ? ውስጣቸውን ማድመጥ የተማሩ ወይም የተለማመዱ ሰዎች በአብዛኛው ስኬት ይቀዳጃሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በጥናትና በበቂ መረጃ ተረጋግጧል፡፡ እስቲ እናንተም ህሊናችሁን ወይም  ውስጣችሁን ለማድመጥ ምቹ ጊዜና ቦታ ፍጠሩ፡፡ ጸጥ ያለ ሥፍራና  ጊዜ ፈጥራችሁ፣ የውስጣችሁን ድምጽ አድምጡት፡፡ ለምትሹት ስኬታማ ህይወት በእጅጉ ያግዛችኋል፡፡
ለአርምሞ ጊዜ ይኑራችሁ
በሳምንት ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻችሁን  የምታሳልፉበት ጊዜ ይኑራችሁ፡፡  በጸጥታ፡፡ የጸሎት ጊዜም  ሊሆን ይችላል፡፡ የሜዲቴሽን ሰዓት ልትሉትም ትችላላችሁ፡፡ ዋናው ጉዳይ በሁካታና ጥድፊያ ከተሞላው ዓለም ወጥታችሁ  በጸጥታ የምትቆዝሙበት ፋታ ማግኘታችሁ ነው - የአርምሞ ጊዜ! የግል ህይወታችሁንም ሆነ የቢዝነሳችሁን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ሂደት ለመገምገም ምቹና ትክክለኛ ቅጽበት ነው፡፡ በህይወታችሁ ለሚገጥሟችሁ ያልተጠበቁ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት የጥሞና ጊዜ ወሳኝ ነው፡፡ አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችንና አሰራሮችን ለማፍለቅም እንዲሁ የአርምሞ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ በነጻነት የምታስቡበትና ከራሳችሁ ጋር የምትመካከሩበት፡፡ ራሳችሁን ለመውቀስና ለማወደስም  ቢሆን፣ የብቻችሁ ጊዜ ቢኖራችሁ ይመረጣል፡፡ ከራሳችሁ ጋር ሰላም ለመፍጠርና ለመታረቅም  የአርምሞ ጊዜ ያስፈልጋችኋል፡፡ ሌሎችንም ሆነ ራሳችሁን ይቅር ለማለትም ይህን መሰሉ ቅጽበት ተመራጭ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡  እስቲ ሞክሩትና ውጤቱን  እዩት፡፡


Read 1366 times