Sunday, 09 July 2023 17:18

‘ከመንበር ማውረድ!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እሱን እንኳን ተወው፣ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ እሱን እንኳን ተወው፡፡ ለራሳችሁ መሆን አቅቷችሁ የዓለም መዘባበቻ ሆናችሁ ጭራሽ ለእኔ ነው የምትቆሙት! ስማ ምስኪኑ ሀበሻ ትናንት እናንተ ስታዝኑላቸው የነበሩ፣ እንደው መቼ ይሆን ሰላም የሚያገኙት፣ መቼ ይሆን መከራቸው የሚቀልላቸው ስትሏቸው የነበሩ ሁሉ እኮ በተራቸው ስለእናንተ ግራ እየገባቸው ነው፡፡ ከርዕሴ አስወጣኸኝ እኮ!
       
       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ እኔ ነኝ እንዳትለኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እኔ ነኝ አንድዬ!
አንድዬ፡- በእርግጥ አንተ ያ የማውቀው ምስኪኑ ሀበሻ ነህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እኔው ነኝ፣ አንድዬ! ይህን ያህል ድምጼ ተለውጦብሀል እንዴ!
አንድዬ፡- እውነትም አንተው ነህ፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አልታወቀህም ይሆናል እንጂ ድምጽህማ  ከተለወጠ በጣም ከረመ እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ሙሉ ለሙሉ አለመጥፋቱም በአንተ ቸርነት ነው፡፡
አንድዬ፡- ይልቅ ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እየሰማሁ ነው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- የሚገርምህ ነገር መቼ ይሆን በጣም ላገኝህ ስለፈለግሁ የምትመጣው እያልኩ እየጠቅሁህ ነበር!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እኔኑ አንድዬ! እኔኑ!
አንድዬ፡- አዎ፣ አንተኑ... ምነው ይሄን ያህል ይገርማል እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- መግረም፣ ሰይሆን አንድዬ፣ መግረም ሳይሆን፣ እኔ ወደ አንተ የምመጣበትን ቀን ልናፍቅ እንጂ አንተ...
አንድዬ፡- እሱን ተወውና ይልቅ ስማኝ፡፡ እንደው እኮ ግርም የሚል ነገር ነው፡፡ እናንተ ሰዎች ምን አድርግ እያላችሁኝ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አ...አንድዬ አልገባኝም፡፡ ም...ምን አጠፋን!
አንድዬ፡- የተቆጣሁ አስመሰለብኝ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አ...አስደነገጥከኝ አንድዬ!
አንድዬ፡- እሺ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ስህተት ነው እታረማለሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ኸረ እንደሱ አትበል! እኛ እንደሱ እንበል አንጂ አንተ እንዴት ተሳሳትኩ ትላለህ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ ምን ላድርግ ብለህ ነው፡፡ እናንተ እንደሆነ እኮ መሀላችሁ አንድም የሚሳሳት፣ ወይም ተሳስቻለሁ የሚል ስለሌለ ቢያንስ በእናንተ ቦታ እኔ ልሳሳትላችሁ ብዬ ነው እኮ! አንድም እንደው አደናቅፎት እንኳን የሚሳሳት ሰው የሌለባት ሀገር እያሉ እንዳይዘባበቱባችሁ ላግዛችሁ ብዬ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ አንድዬ፣ እሱማ ተነግሮ አያልቅም፡፡
አንድዬ፡- ይልቅ ርዕስ የያዝኩትን አታስለውጠኝ፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እስቲ ሹክ በለኝ፤ እንደው ስለእኔ የሆነ ጭምጭምታ ሰምተህ ይሆን?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን አይነት ጭምጭምታ አንድዬ?
አንድዬ፡- እንደው ..ከመሀላችሁ አንዳንዶቻችሁ እኔን ከወንበሬ ለማንሳት...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ! እንደሱ ስትል እኮ ሁላችንን ነው የምታስደነግጠን!
አንድዬ፡- አስጨርሰኛ፣ ምስኪኑ ሀበሻ! ምድር ላይ ዴሞክራሲ መብት የምትሉት ለእኔ አይሠራም እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንደሱ ሳይሆን አንድዬ...
አንድዬ፡- አሁን ምን የሚያስደነግጥ ነገር ተናገርኩና ነው ታስደነግጠናለህ የምትለኝ! እንደው አሁን፣ አሁን እኔን በተመለከተ የአንዳንዶቻችሁ አያያዝ ምንም ስላላማረኝ ምን ቢያስቡ ነው ብዬ ነው እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አን...አንድዬ ምን መሰለህ...
አንድዬ፡- ቆየኝማ ምስኪኑ ሀበሻ... እንደው አሁን መሀላችሁ እኔን የሚቀናቀኑ፣ እኔን ከእናንተ ለመለየት መከራቸውን የሚያዩ የሉም ነው የምትለኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ መ...መአት አሉ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- እኮ እሱን አይደል የምልህ! በእኔ ስም ሀገሩን ሲያምሱ የሚውሉት እኮ ትንሽ ቆይተው በቃ ከመንበሩ አውርደነዋል ቢሉ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ኸረ እንደሱ አትበል! እኛ ልጆችህ የት ሄደን ነው እንዲህ አይነት ነገር የሚሞከረው!
አንድዬ፡- እሱን እንኳን ተወው፣ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ እሱን እንኳን ተወው፡፡ ለራሳችሁ መሆን አቅቷችሁ የዓለም መዘባበቻ ሆናችሁ ጭራሽ ለእኔ ነው የምትቆሙት! ስማ ምስኪኑ ሀበሻ ትናንት እናንተ ስታዝኑላቸው የነበሩ፣ እንደው መቼ ይሆን ሰላም የሚያገኙት፣ መቼ ይሆን መከራቸው የሚቀልላቸው ስትሏቸው የነበሩ ሁሉ እኮ በተራቸው ስለእናንተ ግራ እየገባቸው ነው፡፡ ከርዕሴ አስወጣኸኝ እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በእርግጥ...አንድዬ...
አንድዬ፡- ስማኝ፣ አሁንማ ጭራሽ አንዳንዶቹ እርስ በርስ ተጣልተን የተለያየን ይመስል የሉሲፈር መንታ ሊያደርጉን ምንም አልቀራቸው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በስመአብ! በስመአብ! አንድዬ ዛሬ ደግሞ እንዴት፣ እንዴት አይነት ከባድ ነገር እያልከኝ ነው!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ እኔም ይህን ሁሉ እያየሁ እንዲህ እንደ እናንተ የማማትበት ቢኖር ምንኛ ዕድለኛ በሆንኩ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...እኛ እኮ ሁልጊዜ የምናማትበው፣ ቀን ከሌት የምንጸልየው መከራችንን አይተህልን ይቅር እንድትለን፣ እንድታድነን ነው፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ጎሽ! አንተ ስለሆንክ እንጂ ሌሎቹ፣ ማለቴ እነኚህ ስልጣኔን አንድ በአንድ ሊነጥቁኝ እየሞከሩ ያሉት፣ እኛ ነን እሱን ይቅር የምንለው ይሉ ነበር፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የትም አይደርሱ አንድዬ፣ የትም አይደርሱ!
አንድዬ፡- የእናንተ የዋህነት እኮ ግርም ነው የሚለኝ፡፡ ስንትና ስንት የትም አይደርሱም የተባሉ ተንኮሎች ነገር ከተበላሸ በኋላ እኮ ነው የሚታወቁት!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ ልክ ነው አንድዬ!
አንድዬ፡- ደግሞ እኮ የማይሳካላቸውም ቢሆኑ የትም አለመድረሳቸውን እስኪያውቁ ድረስ ማመሳቸው ይቀራል! ስማኝ...እኔ ለራሴ ዛሬ  ምን ጉድ ይዛችሁ ትመጡብኝ ይሆን ብዬ ቁልጭ እንዳልኩኝ ጭራሽ እኔኑ አድነን ትሉኛላችሁ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ወደ አንተ ካልሆነ ሌላ ወደ ማን እንዞራለን አንድዬ?
አንድዬ፡- ካልተቀየማችሁኝ ሀሳብ ላቅርብና ወደ አሜሪካ መዞሩ ሳይሻላችሁ አይቀርም፡፡ የማላውቅ ይመስላችኋል እንጂ አሜሪካን በአንደኛ ደረጃ አስቀምጣችሁ እኔን እኮ ሁለተኛ ደረጃ አውርዳችሁኛል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ደግሞ ለእነሱ ጠበቃ ሁን አሉ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንደሱ ሳይሆን እንዴት ብለን ነው አንተን ያውም የሀጢአት መፈልፈያ ከሆነችው አሜሪካ ጋር የምናመሳስለው!
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ...ቤተ መቅደስ አንፃችሁ አልጸለይችሁላትም እንጂ የው በአንቺ መጀን እያላችኋት አይደለም እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ማምለክ ሳይሆን ያው  ሀያል ስለሆነች...
አንድዬ፡- ቆይ፣ ቆይማ... ሀያል ሳይሆን ጡንቸኛ ስለሆነች ብትሉ ይሻላችኋል፡፡ እኔ ዘንድ ሀያልነት የጡንቻ ሳይሆን የአስተሳሰብና የባህሪይ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!...
አንድዬ፡- አንተ... የፖለቲካ ቅስቀሳ መሰለብኝ እንዴ! ይሄን ነገር ደግሞ ሄደህ ንገራቸውና “እሱ እንዳለው” እያሉ የንግግር ማሳመሪያ ያድርጉኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኔ ትንፍሽ አልልለም!
አንድዬ፡- ግዴለሀም ምስኪኑ ሀበሻ የሆነ ቦታ ላይ አውቀህም ይሁን ሳታውቅ ትንፍሽ ሳይሆን እንዳለ ነው የምትዘረግፈው፡፡ ይልቅ ምን ታደርግልኛለህ  መሰለህ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ላድርግልህ አንድዬ!
አንድዬ፡- የሚቀጥለው ጊዜ ስትመጣ አጣርተህ ና! ከመንበሬ ሊያነሱኝ እንደሁ ከተረጋጋጠ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ከመንበሬ ሊያነሱኝ እንደሁ ከተረጋገጠ ምን አደርጋለሁ፣ ያው ጸጥታው ምክር ቤት ወደምትሉት...ስቀልድ ነው ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ እንዲህማ ፊትህን ጭፍግግ አታድርግ! ሰላም ግባ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1545 times