Saturday, 29 July 2023 12:28

ብራዚላዊቷ ወጣት ስልኳን ከሰረቃት ግለሰብ ፍቅር ይዟታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ብራዚል አስገራሚ የፍቅር ታሪክ ተሰምቷል።
ኢማኑኤላ የተባለችው እንስት ስልኳን ሞጭልፏት ካመለጠው ግለሰብ፣ ፍቅር ይዞኛል ማለቷን ኒውዮርክ ፖስት አስነብቧል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብም ስልኳን ከሰረቀ በኋላ የተሰማውን ስሜት አጋርቷል።  “በስልኳ ላይ የተነሳቻቸውን ምስሎች ስመለከት ልዩ ስሜት ተሰማኝ፤ ምን አይነት ውበት ነው ስል ተደነቅኩ፤ ለምን ሰረቅኳት ስልም ተጸጸትኩ” ሲልም ያስታውሳል።
የስልክ ስርቆት ያጣመራቸውን ጥንዶች በጋራ ቃለመጠይቅ ያደረገላቸው ጋዜጠኛም ጥያቄውን ያስከትላል፤ “ስልኳን ብቻ ሳይሆን ልቧንም ነዋ የሰረቅከው?” የሚል ጥያቄ፤ እሱም ጊዜ ሳይወስድ “በትክክል!” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ጥንዶቹ በስልክ የጀመሩት ንግግር ወደ ፍቅር ግንኙነት አድጎ ባለፉት ሁለት አመታት ደጋግመው ተገናኝተዋል።
የጥንዶቹ ቤተሰቦች ስለ ጉዳዩ መስማታቸው ባይታወቅም፣ በትዊተር መንደር ግን መነጋገሪያ ዜና ሆኗል።
አንድ አስተያየት ሰጪ፤ “ፍቅር የማይለውጠው ነገር የለም፤ የኢማኑኤላ ፍቅር ግለሰቡን ከስርቆት እንደሚገላግለው  እተማመናለሁ” የሚል ሃሳቡን አጋርቷል።
ሌላኛው ደግም፤ “ጉዳዩ ቀልድ ቢመስልም ዜናው የተሰማው ከብራዚል ነውና ሊሆን  የሚችልበት እድል ሰፊ ነው” ብሏል።
ባልተጠበቀ ሁኔታ የፍቅር ግንኙነት የሚጀምሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። የብራዚሉ ክስተትም ያልተለመደ ይምሰል እንጂ በተለያዩ ሀገራት መሰል ዜናዎች ተደምጠዋል ብሏል፤ ኒውዮርክ ፖስት በዘገባው።
(አል- ዓይን)



Read 1528 times