Monday, 14 August 2023 20:04

“በርታ!” “በርቺ!” መባባል 'ፎሪን ላንጉዌጅ' ሆነ?!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... እንደው በምኑም በምናምኑም “ምን ይሻለናል?” የሚያስብሉ ነገሮች በዙብንማ! ምነው አንዳችን የሌላኛችንን ደጋግና በጎ ነገሮች ማየቱ ይህን ያህል አስቸጋሪ ሆነብን! ምነው ያኛው ቢያጣው እኛ ዘንድ ለማይመጣ ነገር፣ ያኛው ስላላገኘው ብቻ እኛም ለማናገኘው ነገር፣ “እሰይ!” “እንኳን!” እያልን ምንም ባላደረገን ሰው ችግር፣ አጥራችን ባልነቀነቀ ሰው መከራ፤ ሲብስም ውድቀት መደሰትና ፌሽታ፣ ይህን ያህል ብዙዎቻችንን የተጠናወተን፣ ምን የሚሉት አይችሉት እርግማን ደርሶብን ነው! ያስብላላ! እንዴ፣ እንኳን ሊወዳጀውና ሊዛመደው ከእነመፈጠሩ የማያውቀው ሰው እንቅፋት ሲመታው፣ “እኔን ይድፋኝ!” ሲል የኖረ ህብረተሰብ፣ እንዴት ነው እዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው!
መቼም ሰዎች ነንና፣ መቼም ሥጋ ለባሾች ነንና በእርግጥ አንዳንዴ የሆነ የምናውቀው ሰው ላይ ችግር በደረሰ ጊዜ አፍ አውጥተን ባንነግረውም፣ በውስጣችን “የእጁን ነው ያገኘው!”፤ “ዋጋዋን ነው ያገኘችው!” ልንል እንችላለን፡፡ (“ልንል እንችላለን” የተባለው 'ጨዋ' የመምሰል ሙከራ ነው እንጂ “እንላለን” ብሎ በአራት ነጥብ መዝጋትም ይቻል ነበር!) እንበልና ቀደም ሲል እኮ... አለ አይደል... በህይወታችን የሆነ አጋጣሚ ላይ የሆነ ሰው በድሎናል እንበል፡፡ የተባለው ሰው ባመጣብን ችግርም ምናልባትም ለወራት ወይም ከዚያም በላይ ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሎብን 'አፈር እንቅማለን' እንበል፡፡ እናም ያው “ሁሉም ያልፋል፣” እንደሚባለው ሁሉም ያልፍና ከወደቅንበት ተነስተን፣ አቧራውን አራግፈን ቀና እንላለን። ይከርምና ያ ሰው የሆነ ድቅቅ የሚያደርግ ችግር እንደደረሰበት እንሰማለን፡፡ እናማ... እንደ እኛ አፈሩን መቃም ብቻ ሳይሆን ከእነ ምናምኑ ያለብሰዋል፡፡ ታዲያላችሁ... እመኑኝ በሆነ መንገድ 'ሰበር ዜናው' 'ሰበርነቱ' ከመቀዝቀዙ በፊት መጀመሪያ ይደርሳችኋል፡፡ የአንተ ነገርዬ እኮ ከተከሰተ ሁለትና ሦስት አስርት ዓመታት ያለፈው ሊሆን ይችላል፡፡
“ስማ ያ እንትና የሆነውን ሰማህ?”
“ምን ሆነ?”
“አንተ ቀድመህ ትነግረኛለህ ስል ጭራሽ እኔኑ ትጠይቀኛለህ!”
“ይልቅ የሆነውን ንገረኝ፡፡”
“ቤት ገዝቶ እንደነበር ሰምተሀል አይደል!” አዎ ሰምታችኋል፡፡ እንደውም ያንን የሰማችሁ ዕለት ያቺ አድፍጣ የቆየች ”አልሰራችሁ” ልትነሳ ቆንጠጥ፣ ቆንጠጥ ታደርጋችሁ ጀምራ ነው የተመለሰችው፡፡
“የሆነ ሰው የነገረኝ ይመስለኛል፡፡” (ልጄ ማን እጅ ይሰጣል! ደግሞ ሙሉ ለሙሉ “አዎ፣” ብላችሁ “ይሄ ሰውዬ የሚመክረው ዘመድ የለውም እንዴ! እስከዛሬ እሱን ሲከታተል ነው የኖረው!” ተብሎ ስማችሁ የሆነ የጤና ቡድን እንደሚያንገላታት ኳስ ይሁን!”
“ለካስ ቤቱን የገዛው ፌክ ሠርቶ ነው፡፡”
“አትለኝም!” (አሁን ወሬዋ መጣፈጥ፣ መጣፈጥ ጀመረች፡፡) “ምን ዶኪዩመንት ምናምን አጭበርብሮ ነው!”
“አዎ! ለካስ መአት ሰነድ በፌክ አሰርቶልህ፣ ገንዘቡን እዚህ እዛ ረጭቶልህ፣ ለአንድ ምስኪን ሴትዮ ይገባ የነበረውን ቤት ነው የወሰደው፡፡”
“እና አሁን ምን ሆነ ነው የምትለኝ?” (አቦ ሰስፔንሱን ተውና የታሪኩን መጨረሻ!)
“የሴትየዋ ነገር የከነከናቸው ጠበቆች ናቸው አሉ፡፡ መረጃቸውን ሰብስበው ይከሱታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሰነዱን ያይልህና ምን ቢወስን ጥሩ ነው...ቤቱ በአስቸኳይ ለሴትየዋ እንዲመለስ፤  እሱ ደግሞ በሰነድ ማጭበርበር አስር ዓመት ነው እዛው ገደማ ዘብጥያ እንዲወርድ፡፡”
“ጽኑ እስራት ነው?” በመከራ የደበቅነው፣ ሊገነፍል ባለ ቁጥር በሆነ መንገድ እያፈንን ያቆየነው ፍላጎትና ምኞት ሳይታሰብ ፈንቅሎ ሲወጣ... አለ አይደል... ዘንድሮ በተለመደና በብዙ ቦታ እንደ ጆከር እያገለገለ ባለው  «መፋቅ፣” በሚሉት ቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ 'መገሽለጥ' ብትሉት ስህተት አይሆንም፡፡
«እስራቱ እንኳን ጽኑ አይደለም፡፡ ግን ከዛ በተጨማሪ የካሳና የቅጣት ሰባት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር እንዲከፍል ተፈርዶበታል፡፡” ('አለሀ! አንተ የላይኛው ጌታ አለሀ!') አንዳንዱ ቀን እንዴት ነው እንዲህ ሳይታሰብ ደስ፣ ደሳስ የሚለው! ስሙኝማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ምንም እንኳን ጥናት ይቅረብ ብንባል ግራ ገብቶን ልንቁለጨለጭ ብንችልም፣ የፈለገ ቀደም ሲል የሆነ በደል የተፈጸመበት “ጉድ ሳማሪታን፣” የፈለገ ኮቱን አውልቆ ለታረዘ ወገኑ የሚሰጥ ርህሩህ እንዲህ አይነት 'ብሬኪንግ ኒውስ፣' ደስ አይለውም ማለት አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ በአሁኗ ጦቢያችን!
ታዲያላችሁ...ዘንድሮ የሆነ ሰው ችግር ሲገጥመው “እሰይ! እሰይ!” ማለት፤ የሆነ ሰው ደግ በጎና ነገር ሲገጥመው ማናናቅና ማጣጣል በሽ ነው፡፡ በዛ ሰሞን ግማሽ ሚሊዮን ነው እንደዛ ገደማ ተማሪዎች ተመርቀው የለ...እናማ የሆነች በብዙ ችግርና መከራ ጥርሷን ነክሳ ስትማር የኖረች በዝቅተኛ የኤኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቤተሰብ ልጅ፣ በሆነ የትምህርት ዘርፍ ማስተርሱዋን ትይዛለች አሉ፡፡ በርከት ያሉት ጓደኞቿና ወዳጆቿ ከአንጀታቸው ደስታዋን አብረዋት ሲካፈሉ፣ በጣም የቅርብ የሚባሉት የተወሰኑ ጓደኞቿ ናቸው አሉ፣ “አሁን እሷ ነች ማስተርስ የምታገኘው!” “አናውቃትምና ነው! አንድ ሙሉ የእንግሊዝኛ ዓረፍተ ነገር እኮ ያለ ስህተት መጻፍ አትችልም!” ምናምን ሲሏት ነበሩ አሉ፡፡ እንደ አነሱ አባባል ልጅቱ በስነ ስርአት ትምህርቷን ተከታትላ እዚህ ደረጃ የደረሰች ሳይሆን ሴትነቷን ተጠቅማ፣ ነው ባይ ናቸው፡፡ ልጅቱ ግን ከታችኛው ደረጃ ጀምራ በአብዛኛው ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች የመጣች ነች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያዋን በከፍተኛ ውጤት እንዳለፈች፣ እነኚሁ የቅርብ ጓደኞች የተባሉት የሚያውቁት ነው አሉ፡፡ እናላችሁ ምንም ያላደረገቻቸው፣ እንደውም ታከብራቸውና ትወዳቸው የነበረ፣ እንኳን በደል ልታደርስባቸው ለአንዲት ሰከንድም አስቀይማቸው የማታውቃቸው፣  ያውም የቅርብ ወዳጆቿ ናቸው የሚባሉት እንዲህ ሲሆኑ በዘመን ይሁን በማን እንደምንፈርድ ግራ ይገባናል፡፡
ስሙኝማ... ዘንድሮ እንደሁ አየሩ ሁሉ ልንገምታቸው ከምንችላቸው በላይ በሆኑ ትርክቶች ተሞልቶ የቱን አምነን የቱን እንደምንተው ግራ የገባን ዘመን ላይ ነን። ለዚህም ነው ስለ መከዳዳት፣ አንዱ የቅርብ ጓደኛው ላይ ለይቅርታ የማይመች በደል ስለመፈጸሙ፣ ቤተሰቡ መሀል የተወሰኑ ልጆች ለሀብትና ለንብረት ሲሉ ተንከባክበው ባሳደጉ ወላጆች ላይ ስለመዶለታቸው፣ ወንድም እህቱ በሕይወት የሌሉ ወላጆችን ንብረት እንዳትካፈል ለማድረግ እያሳደደ ስለመሆኑ የመሳሰሉ መአት ትርክቶች ስንሰማ ወዲያውኑ እውነት ነው ብለን ለመቀበልም፣ የፈጠራ ወሬ ነው ብለን ችላ ለማለትም እየተቸገርን ነው ያለነው። ግን ደግሞ በየመንደራችን፣ በየቀዬአችን፣ በየፍትህ መጠየቂያ ስፍራዎች ሁሉ በርካታ መሰል ታሪኮችን ስናይና ስንሰማ፣ ዓይናችን እያየ የፈለገው ዓለምን በአፍጢሟ የሚደፋ ማዕበል አይነቀንቃቸውም የተባሉ ቤተሰቦች፣ ግንኙነቶች፣ ወዳጅነቶች፣ ጉርብትናዎች ሲፈረካከሱና ሲበታተኑ፣ ችግራችን ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል... የሰውን መልካም ሥራ የማናናቅ፣ የማጣጣል ነገርማ...ምን አለፋችሁ... ይሄ በኤሌትሪክ ሀይል ሊቆጣጠሩብን ነው እየተባለ ያለ፣ ዲ.ኤን.ኤ. የሚሉት ነገራችን ውስጥ የተቀበረ ነው የሚመስለው፡፡
“ስማ እንትና የሾርት ስቶሪ መጽሐፍ ማውጣቱን ሰማህ!”
“የእነማንን ሾርት ስቶሪ?”
“የራሱን ነዋ! የእነማንን ሊያወጣልህ ነበር!”
“ምን! ማለት ራሱ ጽፎ አወጣ ነው የምትልኝ?”
“እራሱ ጽፎ፡፡ የሚገርምሀ እኔ ይህን ሁሉ ዘመን ሳውቀው እንዲህ አይነት የስነጽሑፍ ታለንት ያለው አይመስለኝም ነበር፡፡”
“ኸረ ሌላ ነገር አውራ! እኔ እኮ እሱን አብጠርጥሬ ነው የማውቀው፡፡ አይደለም ሾርት ስቶሪ፣ የቀበሌ ማመልከቻ እንኳን መጻፍ የማይችል ነው፡፡”
“እና እሱ አልጻፈውም እያልከኝ ነው!”
“ስማ፣ ይሄኔ ለሰው ገንዘብ ሰጥቶ ከሰው ላይ ገዝቶት ነው፡፡”
“አንተም አበዛኸው፡፡ እሱ ለራሱ የለየት ቺስታ፡፡ ከየት አምጥቶ ነው በገንዘብ የሚገዛው?”
“ይኸው መጽሐፉን አሳተመ አይደል!”
“የመጽሐፍ ነጋዴዎች ናቸዋ ያሳተሙለት!”
“ነገርኩህ... እሱ እንደገና ተጠፍጥፎ ቢሠራ እንኳን አይደለም ሾርት ስቶሪ፣ ነፍስ ያለው ደብዳቤ መጸፍ አይችልም፡፡”
ስሙኝማ፣ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ስነ ጽሑፍ አካባቢ ያላችሁ፣ ለምንድነው እዛ ሰፈር መናናቅ የበዛው! እንደው መደጋገፍ እንኳን ቢያቅት ሁሉም የሁሉንም ሥራ እያጣጣለ እስከ መቼ ልንዘልቅ ነው! አሁን  ማበረታታት ምን ክፋት አለው!
እኔ የምለው... በ'ጥሁፍ' ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ዘርፎች “በርታ!” “በርቺ!” መባባል 'ፎሪን ላንጉዌጅ' ሆነ ማለት ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1130 times