Administrator

Administrator

አይሲስ አሁንም ቀንደኛው የሽብር ቡድን ነው


    በመላው አለም ከሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት እየቀነሰ መምጣቱንና ባለፈው የፈረንጆች አመት በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰው በኢራቅና በሶርያ መሆኑን አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው ተቋም ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ የሽብርተኝነት ሁኔታ አመላካች ሪፖርት እንዳለው፣ በ2017 የፈረንጆች አመት በሽብር ጥቃቶች ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር በ27 በመቶ መቀነስ  አሳይቷል፡፡
በአመቱ በኢራቅና በሶርያ እንዲሁም በአውሮፓ አገራት ከሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ለመቀነሱ በምክንያትነት የተጠቀሰው አሸባሪው ቡድን አይሲስ በተወሰዱበት ወታደራዊ እርምጃዎች መሸነፉና መዳከሙ ነው፡፡
አይሲስ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ2017 የ52 በመቶ መቀነስ ማሳየቱ የተነገረ ሲሆን፣ ያም ሆኖ ግን የሽብር ቡድኑ ብዙዎችን ለሞትና ለመቁሰል አደጋ በመዳረግ አሁንም ቀንደኛው የአለማችን አሸባሪ ቡድን ሆኖ እንደቀጠለ ተገልጧል፡፡  
በ2017 በሽብር ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች በከፍተኛ መጠን የቀነሰው በአውሮፓ አገራት መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የመቀነሱ መጠን 75 በመቶ ያህል እንደሚደርስም አመልክቷል፡፡
ጥናቱ ከዳሰሳቸው 163 የአለማችን አገራት መካከል በ96ቱ በሽብር ጥቃቶች ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ማሳየቱን፤ በ46 አገራት ደግሞ መጨመር ማሳየቱን የዘገበው ሲኤንኤን፤ በአለማችን 67 አገራት ውስጥ በአመቱ ቢያንስ አንድ ሰው በሽብር ጥቃት ለሞት መዳረጉንም አክሎ ገልጧል።

 በአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የስማርት ፎን አምራች ኩባንያ የሆነው የቻይናው ሁዋዌ የፋይናንስ ዋና ሃላፊ ዋንዙ ሜንግ ባለፈው ረቡዕ በአሜሪካ ባለስልጣናት ጥያቄ በካናዳ መታሰራቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ሁለቱን አገራት ወደከፋ ነገር ሊያመራቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
የካናዳ መንግስት አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን የንግድ ማዕቀብ ጥሰዋል በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉትን ዋንዙ ሜንግ ለአሜሪካ አሳልፎ እንደሚሰጥ እየተገለጸሲሆን ጉዳዩ ከሰሞኑ የመርገብ አዝማሚያ የታየበትንና ለወራት የዘለቀውን የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት ዳግም ሊቀሰቅሰውና በአገራቱ መካከል የባሰ ፍጥጫን ሊያስከትል እንደሚችል መነገሩን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በካናዳ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ፣ የካናዳ መንግስት ግለሰቧን ማሰሩን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ሲል ያወገዘው ሲሆን ለአሜሪካ አሳልፎ የመስጠት ሃሳቡን በመሰረዝ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቅቃቸውም ጠይቋል፡፡
ለወራት በንግድ ጦርነት ውስጥ የዘለቁት አሜሪካና ቻይና ከሰሞኑ ግን በጉዳዩ ዙሪያ መክረው መግባባት ላይ እስከሚደርሱ ድረስ ለሶስት ወራት ያህል አንዳቸው በሌላኛቸው ምርቶች ላይ ቀረጥ ላለመጣል መስማማታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

  የ7 አመቱ ህጻን በ12 ወራት 22 ሚ. ዶላር በማግኘት በዩቲዩብ ገቢ አለምን ይመራል


    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2018 የፈረንጆች አመት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ሙዚቀኞችን ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የአየርላንዱ የሙዚቃ ቡድን ዩቱ በ316 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ቀዳሚነቱን መያዙ ታውቋል፡፡
ኮልድፕሌይ የተባለው ታዋቂ የሙዚቃ ቡድን በ115.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ የ27 አመቱ ድምጻዊ ኤድ ሼራን በ110 ሚሊዮን ዶላር በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ታዋቂው ድምጻዊ ቡርኖ ማርስ በ100 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ የአራተኛነት ደረጃውን ሲይዝ፣ ኬቲ ፔሪ በ83 ሚሊዮን ዶላር አምስተኛ፣ ቴለር ስዊፍት በ80 ሚሊዮን ዶላር ስድስተኛ፣ ጄይ ዚ በ76.5 ሚሊዮን ዶላር ሰባተኛ፣ ጋንስ ኤን ሮዝስ በ71 ሚሊዮን ዶላር ስምንተኛ፣ ሮጀር ዋተርስ በ68 ሚሊዮን ዶላር ዘጠነኛ፣ ዲዲ በ64 ሚሊዮን ዶላር አስረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የአመቱ የፎርብስ ምርጥ አስር የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ሙዚቀኞች ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 886 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡
በተያያዘ ዜና በአመቱ በዩቲዩብ በለቀቋቸው የተለያዩ ቪዲዮዎች ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ሰዎች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ 22 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት በአንደኛነት ደረጃ ላይ የተቀመጠው የሰባት አመቱ አሜሪካዊ ብላቴና ራያን ነው፡፡ የህጻናት አሻንጉሊቶችን የተመለከቱ አዳዲስና አዝናኝ መረጃዎችን በዩቲዩብ የሚያሰራጨው ራያን፣ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ ሲሆን  የራያን የዩቲዩብ ገጽ 17 ሚሊዮን ያህል ተከታዮች እንዳሉት ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በዩቲዩብ ገቢ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው ጃክ ፖል የተባለ አሜሪካዊ ሲሆን፣ የሚለቃቸው የራፕ ሙዚቃዎችና የሽወዳ ትርኢቶች ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ጊዜ ታይተውለት፣ 21.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡
በዩቲዩብ በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙት ቀዳሚዎቹ አስር ግለሰቦችና ቡድኖች ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በድምሩ 180 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

የኖቤል ተሸላሚው የአለማችን የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን እ.ኤ.አ በ1954 የጻፈውና የፈጣሪ ደብዳቤ ተብሎ የሚታወቀው ዝነኛ ደብዳቤ ለጨረታ ቀርቦ 2.9 ሚ. ዶላር ተሸጧል፡፡
አንስታይን በፈጣሪና በሃይማኖት ዙሪያ ያለውን የግል አመለካከት በጥልቀት እንደገለጸበት የተነገረለትና በአወዛጋቢነቱ የሚታወቀው ይህ ደብዳቤ፣ ባለፈው ማክሰኞ በኒውዮርኩ አጫራች ኩባንያ ክርስቲ አማካይነት በተካሄደ ጨረታ ክብረወሰን ባስመዘገበ ዋጋ መሸጡን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አንስታይን ከመሞቱ አንድ አመት በፊት እንደጻፈው የተነገረለት ደብዳቤው፤ ከስድስት አመታት በፊት በ3 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ዋጋ ለጨረታ ቢቀርብም ሳይሸጥ መቅረቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ምዕራብ አውሮፓዊቷ ሉግዘምበርግ በአለማችን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በሙሉ ያለምንም ክፍያ ለዜጎቿ የምታቀርብ የመጀመሪያዋ አገር ልትሆን ነው ሲል ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መዲና ሉግዘምበርግ ሲቲ በመላው አለም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ከሚታይባቸው ከተሞች አንዷ ናት ያለው ዘገባው፣ ከጥቂት ወራት በኋላ ባቡርና አውቶብሶችን ጨምሮ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በሙሉ በነጻ ለተጠቃሚዎች ክፍት እንደሚደረጉም አመልክቷል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በተከናወነ በዓለ ሲመት የሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣቬር ቤቴል ዜጎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን በስፋት የመጠቀም ልምድ እንዲያዳብሩ በማድረግ ተሽከርካሪዎች የሚያወጡት በካይ ጭስ በአገሪቱ አየር ንብረት ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ በማሰብ፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በነጻ እንዲሰጥ ለማድረግ ማቀዳቸውን ዘገባው አመልክቷል።
የሉግዘምበርግ መንግስት ከ20 አመት ዕድሜ በታች ለሚገኙ ዜጎቹ በሙሉ የትራንስፖርት አገልግሎትን በነጻ እንደሚሰጥ የጠቆመው ዘገባው፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ ትምህርት ቤት ያለ ክፍያ የሚሄዱበት ትራንስፖርት እንደተመቻቸላቸው ገልጧል፡፡
በአገሪቱ መዲና ሉግዘምበርግ ሲቲ የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች በፈረንጆች አመት 2016 ብቻ በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ እያንዳንዳቸው 33 ሰዓታትን ያህል እንዳባከኑ አንድ ጥናት አስታውቆ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

የተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባስከተለው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ዜጎች የከፋ ኑሮን በሚገፉባት ቬንዙዌላ፤ የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በ286 ሺ % ጭማሪ ማሳየቱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
መላው የጠፋቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከሰሞኑ ለሰራተኞች በአመቱ ስድስተኛው የደመወዝ ጭማሪ የሆነውን የ150 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህን ተከትሎም ዜጎች ሸቀጦችን ለመግዛት ወረፋ ይዘው መዋል ማደር መጀመራቸውንና የዋጋ ግሽበትም በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ገንዘብ በገፍ እያተመ ማሰራጨቱ የዋጋ ግሽበቱን እየጨመረው እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፣ የደመወዝ ጭማሪው መደረጉን ተከትሎ በመዲናዋ ካራካስ የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን፣ የበርገር ዋጋም ባለፈው ሳምንት በ52 በመቶ ያህል መጨመሩን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ላይቤሪያ በአስከፊ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እጥረት ውስጥ መዘፈቋንና ለቀውሱ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች ዋነኛው አገሪቱ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥ 60 በመቶ ያህል በዜጎች የሚዘረፍ መሆኑ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በላይቤሪያ በየአመቱ ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥ 60 በመቶ ያህሉን ዜጎች ህገወጥ በሆነ መልኩ በስውር መስመር በመቀጠል ለቤታቸውና ለድርጅታቸው እያስገቡ በነጻ እንደሚጠቀሙበት የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ማስታወቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
አገሪቱ በህገወጥ መንገድ በዜጎች በምትዘረፈው ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል በየአመቱ 35 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣ ያስታወቀው ኮርፖሬሽኑ፣ በዚህ ህገወጥ ድርጊት ላይ የተሰማሩትን ዜጎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ብሄራዊ ግብረሃይል ተቋቁሞ ዘመቻ መጀመሩንም አመልክቷል፡፡

       አሁን  አሁን ለዓመታት  ችላ ብለን የተውናቸው ኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነትና የአብሮነት ስሜቶች እያገገሙ ይመስላሉ፡፡ ዛሬ በጥቂቱ ስለ ሐገር ፍቅር ልናወጋ ነው፡፡ በርግጥ ስለ ሐገር ፍቅር ብዙ ተፅፏል፡፡ ብዙ ፊልም  ተሠርቷል፡፡ ብዙ ትያትር፣ ብዙ ትንግርት ተነግሯል፡፡ በዓለም ዙሪያ በርካታ ተፅእኖ ፈጣሪዎች፣ ለምሳሌ የአሜሪካው ጆን  ኤፍ ኬኒዲ፣ የእንግሊዙ ዊንስተን ቸርችል፣ የቬትናሙ ሆቺ- ሚን ተናገሩ ወይም አደረጉ የሚባሉት ነገሮች ከዘመን - ዘመን  እየተነገሩ አሁን ድረስ ዘልቀዋል፡፡ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት  ቀዩ ጦር ‹‹የአባት  ሐገርን  ማዳን››  ገድል  ተነግሮ  የሚያልቅ  አይደለም፡፡  ወደ ሐገራችን  ስንመለስ  የአፄ ቴዎድሮስ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ የኮሎኔል መንግሥቱ  ኃይለማርያም፣ አሁን  ደግሞ  የጠ/ሚኒስትር  ዐቢይ  አሕመድ  የሐገር  ፍቅር  ሞልቶ  እየፈሰሰ  ሁላችንንም  ሲያጥለቀልቀን  አይተናል፤ አሁንም  እያየን  ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ እኛ  ኢትዮጵያዊያን  የራሳችን  ስኬቶች  ሰለባ የሆንን  ሕዝብ  ነን፡፡  እንዲህ የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ቀደምት  ሥልጣኔያችንንና ታሪካችንን እያወሳንና  በግብዝነት እየተመጻደቅን፣ የጀመርነውን ማስቀጠል  አቅቶን፣ ዓለምን ረስተን፣ ዓለምም  እኛን ረስቶ መቀመጥ ከሚገባን ቦታ ተንሸራተን  በመውረድ፣  ከዝቅተኛው  እርከን  ላይ በመገኘታችን  ነው። እርግጥ  ነው - እኛ  ኢትዮጵያዊያን  እልኸኛና   ለነፃነታችን  ቀናዒ ህዝብ  ነን፡፡  የኢትዮጵያ   የቁርጥ  ቀን  ልጆች  በከፈሉት   መስዋእትነት፣ መላው  አፍሪካና  እስያ   በቅኝ  አገዛዝ  ለዘመናት  ሲማቅቁ፣  እኛ  ነፃነታችንን  አስከብረን  መዝለቃችን ብቻ ሳይሆን፤ ለነጻነት በሚደረገው ትግል አርአያና ተምሳሌት ሆነን ቆይተናል፡፡
በዚህች አጭር መጣጥፍ ስለ ሐገር ፍቅር  የማይጨበጥ ንድፈ-ሃሳባዊ ትንተና ለመስጠት  አይቃጣኝም፡፡ የመጣጥፏ  ዋና  ዓላማ  የአሁኑ  ዘመን  ኢትዮጵያዊያን የሐገር  ፍቅርን እንዴት  ይረዱታል?  እንዴትስ  ይተገብሩታል? የሚለውን  ጉዳይ በማንሳት ትንሽ  ሃሳቦችን   በማንሸራሸር  ውይይት ለመቀስቀስ  ነው፡፡  የሐገር  ፍቅር የማይጨበጥ ረቂቅ ነገር ሳይሆን፤ የሚታይ፣ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ፤ በአመለካከታችን፣ በአኗኗራችን፣ በዕለት-ተዕለት ምግባራችን ሁሉ  ሊገለፅ የሚችል ምሥጢራዊ  ኃይል ነው፡፡
በአንድ ወቅት “የኢትዮጵያዊያን የሐገር ፍቅር  በድመት ፍቅር ይመሰላል” የሚል ነገር ማንበቤን  አስታውሳለሁ፡፡ ድመት  ስለ ልጆቿ ያላት ፍቅር ቅጥ ከማጣቱ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ትበላቸዋለች። ድመት ልጅዋን የምትበላው ለሌላ ተቀናቃኝ ጥላ ላለመሄድ ወይም ከአደጋ ለመጠበቅ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አዎ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያንም  እንደ ድመቷ ሐገራችንን እየበላናት የሚያስመስሉ በርካታ ሁኔታዎችን መታዘብ ይቻላል፡፡ መጥኔ! ኢትዮጵያ ግን እያገላበጥን እየጋጥናትም አሁንም ድረስ አለች፡፡ ሐገራችንን እንደ ፍልፈል መቦርቦራችንን ከቀጠልን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፋት ሐገር አፅሟ የቀረ፣ በድህነት የተቆራመደችና ልጆቿ እርስ በእርስ የሚናከሱባት የመሆን ዕድሏ ከፍተኛ ነው። ይሄን የምለው ጨለምተኛ ሆኜ ሳይሆን እውነቱን መነጋገር ይጠቅመናል ብዬ ስለማምን ብቻ ነው፡፡
የሐገር ፍቅር ሲባል ወንዙን፣ ተራራውን ወይም ባሕላዊ ምግቡን መናፈቅ ብቻ አይደለም። በየጊዜው የተነሱና አሁንም ያሉ የኪነ-ጥበብ፣ የሥነ-ጽሁፍ፣ የሣይንስና ምርምር ሰዎቻችን፤ እንዲሁም አትሌቶቻችን፣ ዲፕሎማቶቻችንና ሌሎችም ያልጠቀስናችው የሐገር ፍቅር በተግባር ሲገለፅ ምን እንደሚመስል አሳይተውናል፡፡
እውነተኛ  የሐገር  ፍቅር ማለት፡-
የራስ  የሆነን ሁሉ  ከማጥላላትና  ማንቋሸሽ  መቆጠብ፤
በሐገር  ምርት  መኩራትና  መጠቀም፤
ከባሕል  ወረራ ራስን  መከላከልና ሐገራዊ እሴቶችን መንከባከብ፤
የመንግሥትና  የሕዝብ  ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረስ መቆጠብ፤
ተፈጥሮን ለመንከባከብ፣ የማህበረሰቡን የጋራ ጥቅምና  ደህንነትን  ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም ለከተማውና  ለሐገር  ውበትና  ገፅታ  ታስበው  የተዘረጉ/የተቋቋሙ መሠረተ  ልማቶችን፣ ተቋሞችን፣ ወ. ዘ. ተ በግዴለሽነት  ከማበላሸት  መታቀብ፤
“ለእኔ  ብቻ”>  የሚለውን  የግለኝነት  ስሜት ገታ አድርጐ  የጋራ ጥቅምን  ማስቀደም፤ እንዲሁም ወገኔ  የምንለውን  ሌላውን ኢትዮጵያዊ  ዜጋ  ማክበርና  መብትና  ጥቅሙን  አለመጋፋት፣ በስሜት  ስንታወር ታላቋንና በሩቅ  የምትታየውን  ኢትዮጵያን  ማሰብና  ማስቀደም፤
በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሳንለግም፣ ሳንሸቅብ፣ ሳናስመስል፣ አቅምና ችሎታችን በፈቀደ  መጠን ሃላፊነታችንን  መወጣት፤
በበጐ ፈቃድ በተለያዩ አካባቢያዊ፣ ማህበረሰባዊና ሐገራዊ  ጉዳዮች  ላይ በሃላፊነትና   በያገባኛል ስሜት መሳተፍ (የመሳተፊያ  ሜዳው ቢጠብም) ወ.ዘ.ተ ከብዙ  ጥቂቶቹ  ናቸው፡፡
እነዚህን ነገሮች በግለሰብ ደረጃም በቡድንም  የመተግበሩ ነገር ምን ያህል ተሳክቶልናል? ሁላችንም ይህን ጥያቄ ለራሳችን አቅርበን መመለስ  ይኖርብናል። ከዚህ አንፃር ጥቂት ማሳያዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል። (እዚህ ላይ ለማሳያ የምንጠቃቅሳቸው ጉዳዮች  ሁሉንም ሰው የሚመለከቱ እንዳልሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡) አሁንም  ድረስ በተሠማሩበት መስክ - ለዚያውም  ብዙ ባልተመቻቸ  ሁኔታ ሐገራቸውን  በቅንነትና በሃላፊነት  መንፈስ ለማገልገል ደፋ ቀና  የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በርካቶች ናቸው፡፡ ፈጣሪ የዚህ አይነቶቹን  ያብዛልን፡፡
ለማሳያነት ከተመረጡት መካከል የጐላ የሥነ-ምግባር ጉድለት ከሚስተዋልባቸውና የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ከሚመዘበርባቸው መስኮች  አንዱና ምናልባትም ዋንኛው የምህንድስናውና የኮንስትራክሽን  ዘርፍ ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱ የመንገድና የሕንፃ ግንባታ ሥራዎችን ማስተዋል በቂ ነው፡፡ መጀመር እንጂ መጨረስ የማይሳካልን እስኪመስል ድረስ መንገዶቻችን በተዘጋጀላቸው ዲዛይን መሠረት በአግባቡ ሳይጠናቀቁ ተዘረክርከው ማየት በጣም የተለመደ ነገር ነው፡፡ ተጠናቀቁ የሚባሉትም ቢሆኑ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ባለመሆኑ ተሠርተው ከመጠናቀቃቸው መፈራረስ ይጀምራሉ፡፡ የመንግሥት ሕንፃዎችን አጨራረስ ካስተዋልን ተመሳሳይ ሁኔታዎችን መታዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ሥራ ተቋራጮች ይህን ሲያደርጉ፣ አማካሪ መሐንዲሶችም ለእንደዚህ ዓይነት ሃላፊነት ለጐደለው አፈፃፀም የሐሰት ምሥክርነት በመስጠት ክፍያ እንዲፈፀም ሲያደርጉ ከተማቸው አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ትዝ ትላቸው ይሆን? ሠርተው መበልፀግ የቻሉት በድሃዋ ኢትዮጵያ መሆኑን ይገነዘቡ ይሆን? መሐንዲስና ምሕንድስና ከተማን፣ ሐገርን ይገነባል፤ እንዲሁም አሁን  እንደምናየው ሃገርንም  ይበላል፡፡
ፊታችንን ወደ ንግዱ ዘርፍ እናዙር፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያልተገባ ትርፍ ለማጋበስ በድሀው ዜጋ ላይ የሚረማመድ፣ ግብር  የሚደብቅ፣ እንዲያም ሲል በወገኖቹ ሕይወት ላይ ዘላቂ ጉዳት  ሊያስከትሉ የሚችሉ ባዕድ ነገሮችን እያቀላቀለ ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርብ ነጋዴስ ምን ሊባል ነው? ባለ ሐብት ልትሉት ትችላላችሁ፤ ግን  በእርግጠኝነት  ሐገር ወዳድ  ሊባል  አይችልም፡፡
ትውልድን የመቅረፅ  የተከበረ ሃላፊነት የተሸከመ መምህር፤ ሥራውን በብቃትና በሃላፊነት ስሜት ካላከናወነ፣ ሐኪሙ ጐስቋላ ታካሚዎቹን  ካንጓጠጠ ወይም ከሙያው ሥነ-ምግባር ውጪ የሆነ ነገር ከፈፀመ  የሁለቱም የሐገር ፍቅር  ጉዳይ ጥያቄ  ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ስንል በዋናነት ህዝብንና ወገንን ማለታችን ስለሆነ ነዋ፡፡
የመንግሥት ሠራተኛውስ  ቢሆን? የመንግሥትን  የሥራ ስዓት በየምክንያቱ ከሸራረፈ፣ ደሞዝ ለሚቆርጥለት ሕዝብ ቅንና ቀልጣፋ አገልግሎት  ካልሰጠ፣ እንዴት ሆኖ ሐገሬን እወዳለሁ ሊል  ይችላል? ባለሥልጣኑማ እንደውም የአንበሳውን  ድርሻ  ነው  መውሰድ  ያለበት፡፡ ያ ሳይሆን  ቀርቶ  ባለሥልጣኖቻችን የሕዝብን መብት የማያከብሩ፣ የሐገርን ብሔራዊ ጥቅም  ለድርድር የሚያቀርቡ ሆነው ሲገኙ ቋንቋው  ተቀይሮ  የሐገር ፍቅር  ሳይሆን የሐገር  ክህደት ይሆናል፡፡
አሽከርካሪውስ ቢሆን? ለሁላችንም  ደህንነት ሲባል የተቀመጡ  የመንገድ  ምልክቶችን ወይም  የከተማውን  ውበት  ለመጠበቅ የተዘጋጁ  ቁሳቁሶችን  በግዴለሽነት  የሚያወድሙ የመኪና አሽከርካሪዎች ቁጥር ጥቂት  አይደለም፡፡ መንገድ  የጋራ መገልገያ  መሆኑን ዘንግተው ብቻቸውን ሊቆጣጠሩት  የሚዳዳቸውም የዚያኑ ያህል በርካቶች ናቸው፡፡ አሁን አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ሕግ አክብሮ በመተሳሰብ መኪና ለማሽከርከር መሞከር እንደ ሞኝነት የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል፡፡ ይህ አዝማሚያ የአስተዳደግ ችግር ነው፣ ወይም ተራ የሥነ-ምግባር ጉድለት ነው ብለን የምናልፈው ሳይሆን ከፍተኛ የሞራል ዝቅተትን የሚያመለክት፣ በውጤቱም ሐገራዊ አንደምታ ያለው ነው፡፡ መነሻውም ዕብሪት፣ ደንታ-ቢስነትና ለሌላው ሰው፣ አንዳንድ ጊዜ ለራስ ሕይወትም  ጭምር ዋጋ አለመስጠት ነው። ጥሩ ዜጋ የሐገርን ሐብት ይጠብቃል፣ ሌላውን ወገኑን ያከብራል፣ ለራሱና ለወገኖቹ ሕይወት ዋጋ ይሰጣል፡፡
ጉዳይ ለማስፈፀም ወይም አገልግሎት ፈልገው ወደ አንድ መሥሪያ ቤት ሄደው፣ ወይም ነዳጅ ለመሙላት፣ ወይም ዳቦ ለመግዛት ወረፋ መጠበቅ ግድ ሆኖብዎት ያውቃል? ከፊታቸው የተሰለፈውን ሰው ረምርመው በማለፍ ለመገልገል የሚሽቀዳደሙ ሰዎችን  አላስተዋላችሁም? እነዚህ በአጠገባቸው ላለው ሰው ደንታ የሌላቸው፣ በራሳቸውና በራሳቸው ጥቅም ብቻ  የታወሩ  ናቸው፡፡ እናም ሐገር ወዳድ ፈጽሞ ሊባሉ አይችሉም፡፡
ጋዜጠኞችና ጦማሪዎችንም በተመሳሳይ መነፅር ማየት ይቻላል፡፡ በአጐብዳጅነት ሕዝብን በተዛባ መረጃ መደለል፣ ሌላኛውን ወገን ጥላሸት መቀባትና ስም ማጥፋት፣ በማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የጥላቻና የጠብ-አጫሪነት ንግግር መለጠፍና አመፅ ማነሳሳት ሀገርን ማፍቀር ሊሆን አይችልም።
የፖለቲካ አመራሩ ለውጡንና ተሃድሶውን የገፋበት ይመስላል፡፡ ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ገና ብዙ መሠራት  ያለበት  ነገር  ቢኖርም ጅምሩ የሚያበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን ለውጡና ሽግግሩ አድማሱ ሰፍቶ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሐገር  ደረጃ እውን ሆኖ መታየት አለበት፡፡
በእርግጥ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ማስፈለግ ብቻ ሣይሆን በፍጥነት መለወጥ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን የምንለውጠው የትኛውን ነው? እንዴትና መቼ ነው የምንለውጠው? የለውጡ ዋና ተዋናዮች እነማን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ፤ብርቅዬዎቹ ማህበራዊ እሴቶቻችን በደረሰባቸው ያላቋረጠ ጥቃት ተሸርሽረዋል፡፡ ችግሩ ወይ እነርሱን አላስቀጠልንም ወይም በሌሎች በተሻሉ እሴቶች አልተካናቸውም፡፡
እውነት ለመናገር፤ እርስ በርስ መከባበር እየራቀን ሄዷል፣ ጥራዝ - ነጠቅነት፣ ሁሉን ነገር በአቋራጭ የማግኘት ብልጣ-ብልጥነትና ግለኝነት ነግሰው፣ ወደ አጠቃላይ የሞራል ዝቅጠት እየወሰዱን ነው፡፡ ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣቱ ላይ ሀገራዊ መግባባት ከተፈጠረ ለውጡን እንዴትና በምን አግባብ እናስኪደው የሚለው ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ ነው። በአንድ ነገር ላይ መግባባት ይኖርብናል፤ ሁሉም ለውጦች በመንግሥት ብቻ ሊመጡ አይችሉም፤ ሁሉም የድርሻውን መወጣት  ይኖርበታል፡፡ የሐገር ፍቅር ማለትም ሌላ ሳይሆን ይሄ ይመስለኛል፡፡
 ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ ሜይል  አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

 የዛሬውን ርዕሰ - አንቀፅ ለየት ከሚያደርጉት አንዱና መልኩንም ይሁን ገበሩን ልዩ የሚያደርገው ተረቱ በትርክት ዓይነት አለመቅረቡ ነው፡፡ ታዲያ በምን ሊቀርብልን ነው መባሉ አይቀርም፡፡ መልሱ በግጥም፣ የሚል ነው! በማን ግጥም? በፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ መንግሥቱ ለማ፡፡ የመንግሥቱ ለማ ግጥምን የመረጥነው ተራኪ በመሆኑ ነው፡፡ እንደሚመች አቅርበነዋል፡፡
የአንበርብር ጐሹ ሞት
እስቲ ላነሳሳው አንበርብር ጐሹን
በደራ አደባባይ የወደቀውን
እሱስ ሆኖ አይደለም ታሪከ - ቅዱስ
መጽደቋንም እንጃ ያች የአምበርብር ነብስ!
የሚያዘወትራት የአንበርብር ወዳጅ
ነበረችው አንዲት ጠይም ቆንጆ ልጅ፡፡
አንድ ቀን በምሽት፣ ደጃፉን ቢመታ
ወይ የሚለው አጣ፣ ገጠመው ዝምታ
ደጋግሞ ቢጥርም አሊያም ቢለምን
ሌላ ሰው ወስዶታል የሱን ቦታውን
በንጉሡ ብትለው ሥራዬን ልሥራበት
ለንጉሡ ተመኛት ለዚያን ቀን ሌሊት!
ይሄውም ሆነና ዋነኛ ጥፋቱ
አርባ ጅራፍ ሆነ ህገኛ ቅጣቱ!
እየተገረፈ እዚያው ግጥም አለ
ጅራፉም እድሜውም ሠላሳን ሳይሞላ!
ከተሰበሰቡት ከተመልካቾቹ
የልብ ድካም ነው አሉ ከፊሎቹ
ዓለም እንደዚህ ናት፤ አሉ ፈላስፎቹ፡፡
    ኧረ ስንቱ ስንቱ፣ ናቸው የሞቱቱ
    ለንጉሣቸው ክብር፣ ለባንዲራይቱ!!  
                (መንግሥቱ ለማ)

***
ለንጉሣቸው፣ ለባንዲራቸው፣ ለሀገራቸው፣ ለራሳቸውም የሞቱ እልፍ አዕላፋት ናቸው፡፡ ሆኖም ዕውቅና የሚሰጣቸው ቀርቶ የሚናገርላቸው፣ የሚዘምርላቸው የለም፡፡ አስከፊው ነገር ይህ በመሆኑ የሚሳቀቅም፣ የሚፀፀትም፣ የሚዘገንነውም የለም፡፡ በእኛ አገር ከቀደሰው ጋር ለመቀደስ፣ ማረስ ከጀመረው ጋር ለማረስ፣ ከተኮሰው ጋር ለመተኮስ ዝግጁ ያልሆነ ማንም የለም፡፡ ችግሩ ማን ይጀምርለት? ነው! “እድመቱ አንገት ላይ ማን የማትጊያውን ቃጭል ይሠር?” ነው፡፡
ለአንድ አገር፤
አንድ ቀዳሽ
አንድ አራሽ
አንድ ተኳሽ
ያስፈልጋል ይላሉ አበው፡፡ ጠቢቡ በሃይማኖትም በተሐድሶም ጠቃሚ ነው!! ቀዳሹ ውስጥ ምሁር አለ፡፡
አራሽ በምግብ ራሳችንን እንድንችል ዋስትና የሚሆነን አምራቻችን ነው!! የምርት ጀግና ነው፡፡
ተኳሹ፤ አገር ድንበር ጠባቂያችን፣ ጀግናችን ነው!
ያለነዚህ ሶስት አውታሮች በሰላም፣ በመረጋጋትና በልበ - ሙሉነት መጓዝ አዳጋች ነው፡፡
በሰላም ውስጥ ዕርቀ - ሰላም አለ፡፡ ብሔራዊ መግባባት አለ፡፡ በመግባባት ውስጥ ልማትና ዕድገት አለ፡፡ የጤና ልማት፣ የትምህርት ልማት፣ የፍትሕ ልማት፣ የዲሞክራሲ ልማት፣ የማህበራዊ ልማት ወዘተ የመግባባት ልጅ ልጆች ናቸው፡፡
ማናቸውም ዕድገትና እንቅስቃሴ የየራሱ እንቅፋት አለው፡፡
“…የጓሮ ጐመን ሲፈላ
አጥፊ ትሉን እንዲያፈላ!”
እንዳለው ነው ሎሬት ፀጋዬ፡፡ እንቅፋቶቹ፤ በጐሣ ግጭትም፣ በሙስናም ይምጡ፣ በመማር ማስተማርም ሆነ በነዳጅ እጥረት ወይም በሥርዓተ- አልበኝነት፤ መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ህብረተሰቡ ሊጋተራቸው ይገባል፡፡ ተጠያቂው መጠየቅ አለበት፡፡ አዋቂና በሳሉ መጠየቅ አለበት፡፡
“አዬ ያ አስተማሪ፣ ያለበት አባዜ
አስተዋይ ተማሪ በጠየቀው ጊዜ” የሚለው የጥንት ግጥም ትርጉምና ፋይዳ የሚኖረው እዚህ ላይ ነው!!

 አሸናፊዎች ለዓለማቀፍ ውድድር እንዲመረጡ ዕድል ይሰጣል - ሁአዌ

    በዓለም በሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ግዙፉና ታዋቂው የቻይና የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁአዌይ፤ በሰሜን አፍሪካና በተቀረው የዓለም አገሮች መካከል የሚካሄድ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ውድድር በመጪዎቹ ወራት እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
ሁአዌይ፣ ከቻይና ኤምባሲና ከትምህርት ሚ/ር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሦስተኛው የአይሲቲ ውድድር መጀመሩን ለማስታወቅ ባለፈው ማክሰኞ በትምህርት ሚ/ር የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው ሥነ-ሥርዓት፤ በኢትዮጵያ የሁአዌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚ/ር ቲበር ዞሁ፤ ለሦስተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር፣ በኢትዮጵያ የአይሲቲ ትምህርት ከሚሰጡ 20 ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 4000 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ገልፀዋል፡፡
የውድድሩ ዓላማ የኢትዮጵያን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማሳደግና ለማስፋፋት መሆኑን የጠቀሱት ሚ/ር ቲበር ዞሁ፤ይህ ከመንግሥት፣ ከትምህርትና ከኢንዱስትሪ የተዋቀረ ሐሳብ፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች እውነተኛ የሕይወት ልምድ እንዲያገኙ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር (ልውውጥ) ለማካሄድ፣ የተሻለ ሥርዓተ ትምህርት ለመቅረጽና ተማሪዎችን ለወደፊት የቅጥር ዕድሎች ለማዘጋጀት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ልዩ ውድድር ለተማሪዎች የተለየ የትምህርት ልምድ ከመስጠቱም ባሻገር፣ በአገራቸው ተወዳድረው፣ ለዓለም አቀፍ ውድድር እንዲመረጡ ዕድል ይሰጣል ያሉት ሚ/ር ዞሁ፤ መጀመሪያ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 4000 ተማሪዎች ይወዳደራሉ፡፡ እያንዳንዱ የትምህርት ተቋም የአይሲቲ ፈተናዎችን በማካሄድ፣ 20 ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ይመርጣል፡፡
እነዚህ የተመረጡ አሸናፊዎች የሁአዌይ ተወካዮች በተገኙበት ይፈተኑና ብልጫ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተመርጠው፣ ለመጨረሻው አገር አቀፍ ውድድር ያልፋሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 3 አሸናፊዎች በፈተና ተመርጠው ይሸለማሉ ብለዋል፡፡
ሁአዌይ ለአሸናፊ ተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለትምህርት ተቋማት ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን 1ኛ እና 2ኛ የወጡት ተማሪዎች የሁአዌይ ሜት 10 ሞዴል ተንቀሳቃሽ ስልክና ሰርቲፊኬት፣ 3ኛ ለሚወጣው ደግሞ የሁአዌይ ዋይ 7 ሞዴል ተንቀሳቃሽ ስልክና ሰርቲፊኬት ይሸለማሉ፡፡
ከተሸላሚዎቹ መካከል ሦስት ተማሪዎችና አንድ መምህር ተመርጠው በአፍሪካ አህጉር ውድድር ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ተማሪ፤ በቻይና ሸንዘን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር የመሳተፍ ዕድል ያገኛል ተብሏል፡፡

 በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰዋና 6.3 ሚሊዮን ያህል ዜጎቿ የተሰደዱባት ሶርያ፤በአለማችን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች አገራቸውን ጥለው የተሰደዱባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ዩኤስኤ ቱዴይ ዘግቧል፡፡በሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት እ.ኤ.አ ከ2011 አንስቶ 6.3 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ከእነዚህም መካከል 3.3 ሚሊዮን ያህሉ በቱርክ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡ ከአለማችን አገራት በርካታ ዜጎችን በማሰደድ የሁለተኛ ደረጃን የያዘቺው አፍጋኒስታን ናት ያለው ዘገባው፣ 2.6 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች መሰደዳቸውንና ከእነዚህም መካከል 1.4 ሚሊዮን ወይም 74 በመቶ ያህሉ በጎረቤት አገር ፓኪስታን የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ነጻነቷን ያወጀቺውና እንደ አገር መቆም ተስኗት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ የኖረቺዋ ደቡብ ሱዳን፤ በ2.4 ሚሊዮን ስደተኞች የሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ዘገባው አመልክቷል።
ሌላዋ አፍሪካዊት አገር ሶማሊያ፤ በ806 ሺህ ያህል ስደተኞች የአራተኛ ደረጃን ይዛለች ያለው ዘገባው፤ 723 ሺህ ያህል የሮሂንጋ ሙስሊሞች ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዴሽ የተሰደዱባት ማይንማር፣ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡

Page 1 of 409