Administrator

Administrator

                      • አገሪቱ በታሪኳ ከባዱን ዘመን ያለፈችበት ጊዜ ነው
                      • ዕድገቱ የት ላይ እንደተስተዋለ ለማረጋገጥ አዳጋች ነው
                      • ያለፉት ሰባት ዓመታት “የክስረት ዓመታት” ናቸው


        ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ  ስልጣን ከመጡ እነሆ ድፍን  ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ፤ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሃላፊነት የተረከቡት። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ብዙ ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ብዙ ተግዳሮቶችና ተስፋን የሚያጨልሙ ክስተቶች ታልፈዋል፡፡ ቀላል የማይባሉ ስኬቶች የተመዘገቡትን ያህል፣ በእርስ በርስ ጦርነቶችና ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ህይወት አልፏል፡፡ ከፍተኛ ሃብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን የአገራዊ ለውጡ 7ኛ ዓመት በመንግሥትም በህዝብም ተከብሯል፤ በውይይትና በድጋፍ ሰልፍ፡፡ በተለይ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ  በተካሄዱ ውይይቶች፣ ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች እየተዘረዘሩ ተዘክረዋል፡፡  ሁሉም የመንግሥት አመራሮች በሁሉም ዘርፎች አስደማሚ ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው ሲገልጹ የሰነበቱት፡፡  ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ይሄን አይቀበሉም፡፡ ያለፉት ሰባት ዓመት ለእነሱ የስኬትና የዕድገት ጊዜያት ሳይሆኑ፤ የጦርነት፣ የግጭት፣ የችግርና የመከራ ወቅቶች ናቸው፡፡ 


የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ ያለፉትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር የሰባት ዓመት ጉዞ ፓርቲያቸው በጥልቀት እንደገመገመ ተናግረዋል። ይህን  የሰባት ዓመታት  ጉዞ፤ “ለኢትዮጵያ የመከራና ስቃይ ዓመታት ነበር” ይሉታል፡፡  “ምናልባትም አገሪቱ በታሪኳ ከባዱን ዘመን ያለፈችበት ጊዜ ነው” ሲሉም ያክላሉ፡፡
“ብልጽግና ፓርቲ አገሪቱ በዕድገት ጎዳና፣ በከፍታና በአብሮነት መንገድ ‘እየተጓዘች ነው’ ቢልም፣ አባባሉ ግን ከዕውነታ የራቀ ነው” የሚሉት መጋቢ ብሉይ፤ “የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ እየወደመ ነው፤  ለጦርነት በግብዓትነት እየዋለ ነው። ትልልቅ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶቿን ባዕዳን እየተቀራመቱት ነው። የአገሪቱ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት እየተደፈረ ነው” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡  
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ከአጼ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመን ጀምሮ የተለያዩ መንግሥታት ሲወጡና ሲወርዱ መቆየታቸውን አውስተው፣ “በ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ አስተዳደር ተሳታፊ የነበሩ አመራሮች፣ አሁን ላይ በተቃራኒው ያለፈውን አገዛዝ ይወቅሳሉ። እኛ እየተራብን ባለንበት ሁኔታ፣ ማርና ወተት የሚፈስባት አገር ነች እየተባለ ነው፤ ይሉናል” ሲሉም ይሳለቃሉ፡፡ እውነቱ ግን  በአገሪቱ ብዙ ረሃብተኞች መኖራቸው  ነው ባይ ናቸው፡፡


በአዲሱ  የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምም፣  በተጨባጭ በዜጎች ኑሮ ላይ የታየ ለውጥ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ እንደውም “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምንታወቅባቸው ደረጃዎች እየወረድን መጥተናል” ብለዋል፡፡ በመንግስት ባለሥልጣናት በአገሪቱ  ወደ 8 ነጥብ 4 በመቶ የሚጠጋ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳለ ይነገራል የሚሉት አቶ ሙላቱ፤ “ዕድገቱ የት ላይ እንደተስተዋለ ለማረጋገጥ አዳጋች ነው” ይላሉ፡፡ አያይዘውም፣ “የዕድገት አንዱ ማረጋገጫ ተደርጎ የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ነው። እኔ የኮሪደር ልማቱን አልቃወምም። ልማት መካሄድ አለበት። ነገር ግን ይህ ልማት የሚካሄደው የዜጎችን ጥያቄ፣ አጠቃላይ ሕግና ስርዓትን ባገናዘበ መልኩ ስለመሆኑ በደንብ የተፈተሸ አይመስለኝም።” ብለዋል፡፡  
“ያለፈው የኢሕአዴግ መንግስት ‘ልማታዊ መንግስት ነኝ’ ይላል። በልማት ምክንያት ያለአግባብ ቤቱ የፈረሰበት አንድ ዜጋ መብቱን መጠየቅ አይችልም ነበር። ፍርስራሹን ይዞ ነበር ወደሚሄድበት የሚሄደው። ምክንያቱም ልማታዊ መንግስት ዴሞክራሲን አያውቅም። የአሁኑ ግን ከኢሕአዴግም የባሰ ነው።” ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡  


መጋቢ ብሉይ አብርሃም፣ የአገሪቱ የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ባለፉት ሰባት ዓመታት ምን እንደሚመስል ሲናገሩ፤ “ኢትዮጵያ በታሪኳ በእርስ በርስ ግጭት የተወጠረችበት ጊዜ አልነበረም። አሁን ላይ ግን በመላ አገሪቱ ሰላም የለም። ብልጽግና ዜጎች ከቤታቸው በሰላም ወጥተው በሰላም  እንዳይመለሱ የሚያደርግ ፖሊሲ ይዟል። ከዚህም ባለፈ በአገራቸው የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸውና የዜግነት መብታቸው እንዳይከበር አድርጓል።” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
በዚህ ሃሳብ አቶ ሙላቱም ይስማማሉ።  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወታደሮች የሚሰለጥኑት ኢትዮጵያን ከባዕድ ወራሪ ሃይል ለመጠበቅ ሳይሆን የእርስ በርስ ጦርነትን ለመፋለም መሆኑን ጠቅሰው፣ “ዜጎች በጠራራ ጸሐይ ታግተው እየተሰወሩ ነው” ብለዋል። ለዚህ ጉዳይ በማስረጃነት ያቀረቡት፣ ከሳምንታት በፊት ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በአውቶቡስ ሲጓዙ የነበሩ ዜጎች በታጣቂዎች ታግተው የገቡበት እስካሁን ድረስ አለመታወቁን ነው።  “በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ላይ የሕግ የበላይነት የለም” የሚሉት አቶ ሙላቱ፤ “አገር የሚኖረው ሕገ መንግሥቱን አክብሮ የሚያስከብር መንግስት ሲኖር ነው፤ ይህ ከሌለ ግን ማንም ጉልበት ያለው ሃይል፣ አገሪቷ ላይ እየፈነጨባት ሊኖር ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የባይቶና ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ክብሮም በርሀ፣ ያለፉትን ሰባት የለውጥ ዓመታት  የገለጹት፣ “ጦርነት፣ ስደት፣ ድህነትና ሞት የበዛባቸው” በማለት ነው። አቶ ክብሮም የጠ/ሚኒስትሩን የአስተዳደር ዘመን  የገመገሙት ፓርቲያቸው ከሚንቀሳቀስበት ትግራይ ክልል አንጻር ሲሆን፣ “ያለፉትን ሰባት ዓመታት ትግራይ በጦርነት አሳልፋለች። ከጦርነት ፕሮፓጋንዳ የጦርነትን የጥፋት አዝመራ ወደ መሰብሰብ የተሸጋገርንበት ጊዜ ነበር” ይላሉ። በዚህም ምክንያት በትግራይ ክልል ትምህርት መቋረጡን፣ የሕክምና አገልግሎት መጥፋቱን፣ እንዲሁም የግብርና ስራ መቆሙን ይገልጻሉ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ሳቢያ፣ በርካታ የክልሉ ወጣቶች በሕገ ወጥ መንገድ በገፍ እየተሰደዱ መሆናቸውን የጠቆሙት  ሊቀ መንበሩ፤ በአጠቃላይ የጠ/ሚኒስትሩ ሰባት የአስተዳደር ዓመታት ለትግራይ ክልል ጥሩ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ 


መጋቢ ብሉይ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት አገሪቱ ለተጋፈጠቻቸው ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች፣ እሳቸው “ጠባብ ብሔረተኛነት” ሲሉ የጠሩት ፖለቲካዊ እሳቤ  መንሰራፋቱን በምክንያትነት  ይጠቅሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት የታዩ አዎንታዊ ለውጦችን ሲያስታውሱም፤ “መንግሥት በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችን ከእስር ፈትቷል፤ በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸው ቅጣት የተበየነባቸው ጋዜጠኞች ቅጣቱና ክሱ ተነስቶላቸው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል፤ በአገር ውስጥ እንዳይታዩ ክልከላ የተጣለባቸውና መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ ድረ ገጾችና መገናኛ ብዙኃን ዕግዱ ተነስቶላቸዋል። ይህንን እንቅስቃሴ የተመለከተው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) በወቅቱ ድጋፉን የገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን እንድታከብር ተመርጣ ነበር።” ይላሉ፡፡  “ይሁንና ብዙም ሳይዘልቅ  የፖለቲካ ምሕዳሩ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየተዘጋ ያለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ነጻ ጋዜጠኝነት የታፈነበትን ጊዜ ለማሳለፍ  ተገድደናል” ብለዋል፣ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንቱ።
አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ ከመጋቢ ብሉይ ሃሳብ ጋር የሚቀራረብ ዕይታቸውን ሲገልጹ፤ “ከሰባት ዓመታት በፊት ከነበረው የዴሞክራሲና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሁኔታ አንጻር፣ በአሁኑ ወቅት ምህዳሩ እየጠበበ መጥቷል” ይላሉ፡፡
መጋቢ ብሉይ፣ ያለፉትን ሰባት ዓመታት “የክስረት ዓመታት ናቸው” ሲሉ ይገልጹዋቸዋል፡፡ “አሁን ላይ የሰባት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያከብሩበት ሳይሆን፣ ራሳቸውን ፈትሸው ከስልጣን የሚወርዱበት ወቅት ነበር። ያንን በብልጽግና ፓርቲ አላየንም።” ብለዋል። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በአንድ የውይይት መድረክ ላይ “እኔ አሻግራችኋለሁ” በማለት ተናግረው ነበር፤ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋምና የአገሪቱን መጻዒ ዕድል የሚወስን ፍኖተ ካርታ እንዲቀረጽ ለሚጠይቁ ወገኖች ምላሽ ሲሰጡ። መጋቢ ብሉይ አብርሃም፣ ይህንን የጠ/ሚኒስትሩን ቃል ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ተዋናዮች ማመናቸው “ስሕተት” እንደነበር ይናገራሉ፡፡
“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘አሻግራችኋለሁ’ ሲሉ፣ ‘ያሻግሩናል’ ብለን የጠበቅነው ከጠባብ ብሔረተኝነት፣ አንድነታችንን ከማያስከበረው ሕገ መንግስት ነበር። እርሳቸው ግን ከጠባብ ብሔረተኛነት አላሻገሩንም፤ ሕገ መንግስቱ አልተሻሻለም። እንዲያውም  ህወሓት/ኢሕአዴግ ከፈጸማቸው ስሕተቶች፣ የባሱ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።” ሲሉ ተችተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በእጅጉ የከነከናቸው የሚመስሉት መጋቢ ብሉይ ነገሩ በስፋት ሲያብራሩት፤ “እኛ የፖለቲካ ሃይሎች ማድረግ ይገባን የነበረው በአጠቃላይ ለእነርሱ ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ አምነን መስጠት ሳይሆን፣ በጋራ ፍኖተ ካርታ መቅረጽና የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ከተፈለገ፣ ከእነርሱ ጋር ቁጭ ብለን መወያየት ነበር። ነገሮችን ግራና ቀኝ አልመረመርንም።” ሲሉ ራሳቸውን ጨምሮ የተቃዋሚውን ጎራ ወቅሰዋል፡፡ 


“ያጋጠመንን መልካም ዕድል በአግባቡ አልተጠቀምንበትም” የሚሉት ተቀዳሚ ፕሬዚዳንቱ፤ “አሁንም ቢሆን አልረፈደም። ቆም ብሎ ሁኔታዎችን ማጤን፣ ይህቺ አገር ከቀውስ የምትወጣበትን ዘዴ መፈለግ ከሁላችንም ይጠበቃል።” ሲሉ የመፍትሔ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የኦፌኮው አቶ ሙላቱ፣ እንደ አገር ከታሪክ ስሕተታችን መማር አልቻልንም ባይ ናቸው፡፡ “የአገራችን ችግር የኢኮኖሚ ችግር አይደለም። የማሕበራዊ ችግርም የለብንም። ያልተገራና ያልዘመነ ፖለቲካ ነው የእኛ ችግር። ፖለቲካችንን ካላዘመንነው፣ ችግራችን ቀጣይ ይሆናል።” ብለዋል፤ በማጠቃለያ አስተያየታቸው፡፡
አቶ ክብሮም በርሀ ደግሞ፣ በመጪዎቹ ጊዜያት በሰበብ አስባቡ የተጓተተው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ተደርጎ፣ የትግራይ ክልል ወደቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ፣ የፌደራል መንግሥቱን ጨምሮ  ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡


“ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች”


        እስራኤል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር አዲስ ፕሮጀክት ልትጀምር ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን የንግድ ትብብርና ግንኙነት የሚያጠናክረው እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶ/ አብርሃም ንጉሴ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት  ቃለ ምልልስ፣ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ  ከ122 በላይ የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በኢኮሲስተም እና የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ በመስራት ላይ እንደሚገኙ ያብራሩት አምባሳደሩ፤ እስራኤል የኢትዮጵያን ምርት በማስገባት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኗንም አመልክተዋል። “ጤፍን ወደ እስራኤል በማስገባት ቀዳሚነቱን  ይዘናል። ቡና እና ሰሊጥ፣ እንዲሁም ሌሎች  የጥራጥሬ እህሎችም  ወደ እስራኤል ይገባሉ” ብለዋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከእስራኤል የቴክኖሎጂ ምርቶችን እንደምታስገባ  የጠቆሙት አምባሳደር ዶ/ር አብርሃም፤ ከዚህም ባሻገር በሁለቱ አገራት መካከል የቴክኖሎጂ ተሞክሮ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
“በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ በኩል፣ በጣም ጥሩ የሆነ ግንኙነት አለ። ባለፈው ህዳር ወር የእስራኤል መንግስት አራት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤክስፐርቶችን በመላክ፣ ኢትዮጵያ አሁን የምታካሂደውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሲስተምና ኢኮሲስተም የበለጠ ለማጠናከር እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ በማሳለጥ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር አብርሃም፤ እስራኤል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር “ኤሮስፔስ” የተሰኘ ፕሮጀክት በቅርቡ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡ “የእስራኤል አውሮፕላን ኢንዱስትሪ፣ የኢትዮጵያን የመጓጓዣ አውሮፕላኖች ወደ ካርጎ የመለወጥ ፕሮጀክት ነው።” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሂደቶች የተጠናቀቁ መሆናቸውን አምባሳደሩ አመልክተዋል። “በሁለቱም አገሮች የንግድ ልውውጥ ሲደረግ፣ በአራት ሰዓት ውስጥ በሁለቱ አገራት መካከል የደርሶ መልስ ጉዞ ለማካሄድ ይቻላል። የበለጠ ለማጠናከር ደግሞ እየሰራን ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ዶክተር አብርሃም ንጉሴ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ባለፈው የፈረንጆቹ  ነሐሴ ወር 2024 ዓ.ም ነበር።



በአገር አቀፍ ደረጃ የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም መጠንን ለመቀነስ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት ይገባል ተብሏል። ከትምባሆ አጫሽነት ጋር የተገናኙ ጉዳቶች መጠን እየቀነሰ ስለመምጣቱ ተገልጿል።
ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በኤሊሊ ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ ላይ በ2016 ዓ.ም. የዓለም አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም ጥናት (GATS) ይፋ ተደርጓል። በዚህ መድረክ ላይ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ በሆናቸው አገር አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም (GATS 2024) ጥናት፣ ከፍተኛ የሆኑ ለውጦችን ስለመገኘቱ ተነግሯል። ይሁንና አሁንም ሰፋፊ ስራዎች እንደሚጠበቅ ተመላክቷል፡፡
አገር አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም የ2016 ጥናት፣ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር 5 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ዓመት ጥናት ደግሞ ወደ 4 ነጥብ 6 በመቶ “ቀንሷል” ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል፤ በGATS 2016 በተጠናው ጥናት፣ ሰዎች በሚሰሩባቸው የስራ ቦታዎች የነበረው ለትምባሆ ሁለተኛ ወገን አጫሽነት መጋለጥ (Second and smoker) 29 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2024 ጥናት ግን ወደ 19 ነጥብ 8 በመቶ ስለመቀነሱ ተጠቅሷል፡፡
ይህን በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተዛመተና በሰው ልጆች ጤና እና ማሕበራዊ ኑሮ፣ ብሎም ኢኮኖሚ ላይ ችግር እየፈጠረ ያለን ጉዳይ ለመግታት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ሰፋፊ ስራዎችን ሲሰራ እንደቆየ በዚህ መድረክ ላይ ተነግሯል። ከእነዚህም መካከል የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ ቁጥር 77/2013ን እና የትምባሆ ምርት አወጋገድ መመሪያ ቁጥር 1003/2016 TEA፣ ከዚህ በተጨማሪም አገር አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋምና የስምንት ዓመት አገር አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ስትራቴጅክ ዕቅድ በመንደፍ ስራዎች ሲሰሩ እንደቆዩ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነጻ ማድረግ፣ ሌሎችን ነጻ ለማድረግ “ይጠቅመናል” በሚል ዕሳቤ ባለፉት 5 ዓመታት አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ “ነጻ ማድረግ” የሚል ንቅናቄ ተቀርጾ መተግበሩ ከፍተኛ የሆነ ውጤት እንዳስገኘ ተገልጿል፡፡ በሌሎችም ክልሎች በተሰሩ ተከታታይ የትምባሆ ቁጥጥር ስራዎች ለውጥ መታየቱ በጥናት ጭምር “ተረጋግጧል” ተብሏል።
የተለያዩ መረጃዎችና ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለም በየዓመቱ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በትምባሆ ምክንያት ይሞታሉ። ከእነዚህም ውስጥ 12 ሚሊዮን ቀጥተኛ አጫሽ ሳይሆኑ ለጭሱ ብቻ ተጋላጭ በመሆን የሚጎዱ ናቸው፡፡
ከዚህም ባለፈ፣ ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የመጠቃት ዋነኛ ምክንያት የሆነውና ቁጥራቸው በማይናቅ ሁኔታ እየጨመረ ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ሲጋራ ማጨስና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም ጋር የተያያዘ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር ቆይቷል። ሲጋራ ማጨስና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም በሱስ ለማስያዝ፣ ለአደገኛ የሳንባ በሽታ ወይም ካንሰር፣ ለልብ በሽታ መዳረግ፣ ለጽንስ መጎዳት፣ በሚጨስበት አካባቢ በሚኖሩና በማያጨሱ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክና ሌሎችንም በሽታዎች እያስከተለ ይገኛል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ደጉማ፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዋን ለመደገፍ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) 28.5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አገኘች። የድጋፍ ስምምነቱ 25 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍና 3.5 ሚሊዮን ዩሮ የቴክኒክ ድጋፍን ያካትታል ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እንደገለጹት፤ ይህ ድጋፍ የኢትዮጵያን የመንግሥትና የግል ሽርክና፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ማሻሻያና የፋይናንስ ዘርፍ ተደራሽነትን ለማጠናከር ይረዳል። በተጨማሪም፤ ለውጤታማ ፖሊሲ ትግበራና ተቋማዊ አቅምን ለማሳደግ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።
የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ዳይሬክተር ሚስተር ሉዊስ-አንቶይን ሶሼት በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ለውጥ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ድጋፍ አስተዳደርን፣ ኢኮኖሚያዊ ዘላቂነትንና የመንግሥት ዘርፍ ቅልጥፍናን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ በ3.6 ሚሊዮን ዶላር የገዛትን አዲስ ዘመናዊ አውሮፕላን ሰሞኑን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተረክቧል፡፡ አውሮፕላኗ 14 ሰው የመያዝ አቅም ያላት ሲሆን፤ የተደራጀ የአውሮፕላን ማረፊያ በሌለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች በቀላሉ ማረፍ እንደምትችልም የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ትራንስ ኔሽንስ ኤር ዌይስ ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ አሚር አብዱልወሃብ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡
“ሴስና ካራቫን ኤክስ” የሚል ስያሜ ያላት አዲሷ አውሮፕላን፤ ሚድሮክ በማዕድንና በእርሻ ዘርፍ የሚሰራቸው ሥራዎችን ለማሳለጥ ተጨማሪ አቅም እንደምትፈጥርም ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም አውሮፕላኗ ለጎብኚዎችና ለአገልግሎት ፈላጊዎች የቻርተር አገልግሎት እንደምትሰጥም ተናግረዋል፡፡

በ5 ዓመት ውስጥ ለ300ሺ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል


የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሃይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ) ጋር ለአምስት ዓመታት የሚቆይ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር የስራ ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችልና ለአምስት አመት የሚቆይ መሆኑም ተመላክቷል።
በመድረኩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለፁት፤ በሃገር ደረጃ የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳዳግ በትኩረት እየተሰራ ነው። ይህ ስምምነትም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር፣ የአገልግሎት ዘርፉን ከማዘመን ባሻገር ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ስምምነቱ ሚኒስቴሩ በሚዘረጋው የስራ መስመር መሰረት በህጋዊ መንገድ ብዙ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎች ስራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ መውጣቱን ተናግረዋል።
የሃይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ) መስራችና ስራ አስፈፃሚ ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩላቸው፤ ኩባንያቸው የስራ እድል ለመፍጠርና ስራ የለም የሚባለው ነገር እንዲቆም በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። እስካሁን ለ120 ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ የገለፁት ስራ አስፈፃሚዋ፤ ይህ ስምምነትም በሚቀጥሉት አምስት አመታት 300ሺ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

 

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት መነኩሲት ጎኅ ሲቀድ  ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሄዱ ይነሳሉ፡፡ አንድ ዛፍ አጠገብ ሲደርሱ ተንበረከኩና ሁለት እጃቸውን በልመና መልክ ዘርግተው፤ ጸለዩ፡፡
“አምላኬ ሆይ! ድንገት ከወትሮው ፀሎቴ አሳንሼብህ ይሆናል፡፡ የከዋክብት ብዛቱን የውቂያኖስ  ስፋቱን፣ የሙሴ በትሩን፣ የገብርኤል ተዓምሩን፣ የእመቤታችን  አማላጅነቷን የምታውቅ፣ የምትሰጥ፤ የነገሩህን የማትረሳ፣ የለመኑህን የማትነሳ፣ ሰማይን ያለ ካስማ  ያቆምክ፣ የማያርሱ  የማይዘሩ ወፎችን  የእለት ጉሮሮ የምትዘጋ፣ ምንም የማይሳንህ አምላክ  ሆይ! ካንተ ልግስና  አንፃር እጅግ  ትንሽ ነገር ነው የምለምንህ፡፡ እባክህ ዕድሜዬን ጨምርልኝ?”
ለካ ይህን ፀሎታቸውን ሲያደርሱ፣ ሁሌ ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቆ የሚያዳምጣቸው አንድ ተንኮለኛ የቆሎ ተማሪ ኖሯል፡፡
በሚቀጥለው ማለዳ ጎኅ በቀደደ ሰዓት ያ የቆሎ ተማሪ፣ ቀደም ብሎ ዛፍ ላይ ወጥቶ ይጠብቃቸዋል፡፡ እሳቸው እንደልማዳቸው መጥተው ፀሎትና ልመናቸውን አሰሙ፡፡ በመጨረሻም፤ “ዕድሜዬን ጨምርልኝ፣ አደራ!” አሉ፡፡
ይሄኔ፤ ያ የቆሎ ተማሪ፤
“አንቺ መነኩሲት! ምን ያህል ዕድሜ ልጨምርልሽ?” አለ ድምፁን  ጎላ አድርጎ፡፡ መነኩሲቷ ደነገጡ፡፡  ፀሎታቸው ተሰማ! ሲያስቡት ሃያም ትንሽ ነው፡፡ አርባም ትንሽ  ነው፡፡ መቶም ትንሽ ዕድሜ ነው፡፡ በመጨረሻ እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “አምላኬ ሆይ! አንድ ድሃን  ከነጭራሹስ እዚሁ ብትተወኝ፣ ምን እጎዳሃለሁ!” አሉ፡፡
***
የዓለም ኢኮኖሚ ጉዳይ አንጋፋ ባለሙያ የሚባለው አዳም ስሚዝ፤ “የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን የለውም” ያለንን ከላይ ያየነው ተረት በአበሽኛ ሳይገልጥልን አልቀረም - Human wants are unlimited ማለት ይሄው ነው፡፡ ዛሬ መጠለያ ጠየቅን፡፡ ነገ ምግብ እንጠይቃለን፡፡ ከነገ ወዲያ መንቀሳቀሻ መኪና እንፈልጋለን፡፡ ከዚያ ታዲያ  ሰፋ ያለ ግቢ እንዲኖረን እንጠይቃለን፤ ወዘተረፈ--ችግሩ የሚመጣውና የሚስፋፋው መሰረታዊ ፍላጎታችን ከተሟላ በኋላ ነው፡፡ ወለሉ ግን መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን ከዚህ ወለል  በታች ከሆነስ? “እዚሁ ላይ ነው ችግሩ” እንዳለው ነው ሼክስፒር፡፡ ”መሆን ወይስ አለመሆን?” የሚባለው ጥያቄ፣ ማናቸውም ጉዳይ ለውሳኔ አሳሳቢ ደረጃ ሲደርስ የሚመጣ ነው፡፡ ውስጥን መፈተሽ አለመፈተሽ፣ እርምጃ መውሰድ አለመውሰድ? ነው ጉዱ! ምኞት ከአቅም በላይ  መሆን እንደሌለበት ማንም ጅል አይስተውም፡፡ የፍላጎት አቅማችን እየኮሰሰ፣ ምኞታችንን ሰያጫጨው፤ የተስፋ  መቁረጥ  ጉድባ ውስጥ  እንገባለን፡፡ ዜግነታችን ራሱ ያስጠላናል፡፡ የሀገር ፍቅራችን ይሟሽሻል፡፡ ሁሉን ነገር አሉታዊ እሳቤ ውስጥ እንከተዋለን፡፡ መንገድ ተሰራ ስንባል፣ የሚሄዱበት እነሱ እንላለን፡፡ ፎቅ ተሰራ፤ “የማን ነውና!” ዘር ተጋጨ፤  ማን አመጣውና! ዕውነትም ውሸትም አለው ነገሩ፡፡ ህይወታችን የምንግዴ ህይወት ይሆናል፡፡
ሰብአዊም ሆነ ቁሳዊ ዕሴት ያለን አይመስለንም፡፡ ይሄ የተስፋ ቆራጭነት ሁኔታ (desperado state) ለሀገርም፣ ለህዝብም አደገኛ ነው! አይበጅም! የኢኮኖሚ ችግር፤ የፖለቲካ ድንግዝግዝነትን (obscurantism) ብሎም ጠርዘኝነትንና ጽንፋዊ ጥላቻን ሲፈጥር፣ “የመጣው ይምጣ” አስተሳሰብ ይከሰታል፡፡ ማህበራዊ ቀውስ፣ ሥርዓተ-አልበኝነት፣  ዘራፊነት፣ እኔ ምንተዳዬነት ወዘተ ይነግሳሉ፡፡ አጠቃላይ ድቀት ይከተላል፡፡ ማንም ስለ ማንም መጨነቁን ይተዋል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!!
ዛሬ በሀገራችን የአሳሳች መረጃዎችና ሰነዶች መብዛት ከአቅም በላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አለ፡፡ የተጭበረበሩ ሰነዶች  ግን ከመፈጠር አላባሩም፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ በሀሰት የተፈበረከ (Forged) ፈቃድ---ለምሳሌ፡- የህንፃ ፈቃድ፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ የግንባታ ፈቃድ፣ የመንጃ  ፈቃድ፣ የንግድ ፈቃድ፤ አልፎ ተርፎም  የጋብቻ ሰርተፍኬት ሳይቀር  በሙስና አዋላጅነት፣  በሽበሽ ሆነዋል!  የቀረው የአመፅ ፈቃድ “በፎርጅድ” ማሰራት ብቻ ነው ተብሏል! እጅ ላይ ያለው ችግር በአግባቡ መፍትሄ ባለማግኘቱ፤ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዳችን ግድ ሆኗል፡፡ ብዙ ነገር ካንሰር- አከል በሽታ ሆኖብናል፡፡ አሰቃቂው ነገር፤ የጉዳዩ ተዋናዮች አለቃውም ምንዝሩም፣ ህግ አውጪውም፣ አስፈጻሚውም፣ መሆናቸው ነው! እርምጃ ማን ይውሰድ? አሰኝቶናል፡፡
ህገ-መንግስቱንም፣ ህዝቡንም የረሱ አያሌ  ሹማምንት ለመኖራቸው ዛሬ ብዙ አያጣራጥርም! ህገ ወጥነት ጣራው ጋ ሲደርስ ማጣፊያው ያጥራል! “የንጉሡን ፊት አይተህ ፈገግ በል” የሚለውን ተረት፣ በየደረጃው እንደ መሪ መፈክር የያዙ በርካታ ናቸው፡፡ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ለታ ግን  ሁሉን ጥፋት በክልል ከማላከክ አልፈን የራስ ተጠያቂነት አፍጦ ይመጣል፡፡ “ባሪያ ላግዝሽ ሲሏት መጁዋን  ትደብቃለች” የሚለው ተረትም በመንግሥትና በባለሙያ መካከል ይታያል፡፡
እያደር ዕውን የሆነና የሚሆን  ግጭት፣ ፍጭት፣ ወደ ዘረኝት  አቅጣጫ ለመሄድ እርሾው የሚታይና አብሲቱ የተጣለ የሚመስልበት ሁኔታ፣ ብዙው የፖለቲካ ጨዋታ ሲሟጠጥ እንደሚሆነው ሁሉ ወደ ጡንቻ የሚሄድ፣ የደም መፋሰስ ትርዒት ማየት፣ ስለ ብዙ ሰላም ለምታወራ አገር የሚያምር ቁም ነገር አይደለም፡፡ ያለመረጋጋት አስረጅ ይሆናልና፣ ከወዲሁ መገደብና ሰላማዊ መፍትሔ መሻት አስፈላጊ ነው፡፡ ቁጣን በቁጣ መመለስ አባዜው ብዙ ነው!
የተኙት ብዙዎች፣ የተናደዱትና  የነቁት ጥቂቶች ሲሆን፣  የበሰለ አመራር በስሜታዊነት ይዋጣል፡፡ ቁጣ ቦታ የሚያገኘው  ይሄኔ ነው፡፡ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ሆድ ሰፊ መንግስት  an eye for an eye (ዐይን ያወጣ ዐይኑ ይውጣ)  ከሚል ጥንታዊ ህግ የተላቀቀ  ሊሆን ይገባዋል፡፡ የሠለጠነ ህግ አለውና፡፡ ህግ እንዳለ ከረሳን ግን የአልዛይመር  ምርመራ ማድረግ ነው፡፡
አሁንም የውስጥ ምርመራ ያስፈልጋል፡፡ ከአንገት በላይ ምርመራው ብቻ በቂ አይሆንምና፡፡ ትንሽ ቁስል ሰፍታ ሰፍታ የአገር ህመም የምትሆን ከሆነ፣ ጠቅላላ ምርመራ የግድ ነው፡፡ ክፍሎቻችን ሁሉ በቅጡ ይመርመሩ!!
የሚጠራቀሙ ጥቃቅን ብሶቶች፤ ልክ ጠብ ጠብ እንደሚሉ የውሃ ጠብታዎች ናቸው፡፡ ሲጠራቀሙና አቅም ሲያገኙ ጎርፍ ይሆናሉ፤ ይላሉ የጥንቱ የቻይናው ማዖ  ዜዱንግ፣ ትግላቸውን ነብሱን ይማረውና፡፡ ጫማ ልክ አልሆን ሲል እግር የመቁረጥ ፖለቲካም  አይሠራም ይላሉ፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ችግሮች፣ ያለ አራሚ አንድሚያድጉ አረሞች ናው፡፡ እያደር ዙሪያ ገባውን ዳዋ እንዲውጠው  ያደርጋሉና፡፡ ከዚያ “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ነው ተከታዩ፡፡ ሀገራችን ከዚህ “ውጣ እምቢ፣ ግባ እምቢ” አጣብቂኝ የሚያወጣት መላ መምታት አለባት፡፡ ቅርቃ ውስጥ ናት፤ በሰላም  ማጣት ራስ ምታት መካከል፡፡ ቅርቃሩ ጊዜያዊ ነው ወይስ አይደለም? መመርመር ነው!!  አሁንም ጠብታዎች ጎርፍ፣ ጎርፎች ዥረቶች፣ ዥረቶች ወንዞች እንዳይሆኑ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ማየት ደግ ነው፡፡ ላቲኖች፤ “ጎርፍም ያለ እርከን፣ ምራቅም ያለ ከንፈር አይቆምም፡፡” ያሉትን ልብ ማለት ይጠቅመናል፡፡

•    ኮንሶዎች በኮሪደር ልማቱ አሻራቸውን እያስቀመጡ ነው


የተፈጥሮ ሃብት ልማትን ለመጠበቅ ፈታኝ የሆነውን መልከዓ ምድር በእርከን ስራ  ለእርሻ  ያዋሉትና ተፈጥሮን  ተንከባክበው በትውልድ ቅብብሎሽ  ያቆዩት የድንቅ ባህል ባለፀጋዎች ናቸው፤ የኮንሶ ማህበረሰቦች፡፡
ህይወታቸው በእጅጉ ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘው የኮንሶ ማህበረሰቦች፤ ተፈጥሮን በመጠበቅና በመንከባከብ ይታወቃሉ፡፡ ኮንሶዎች ከተፈጥሮ ጋር ባደረጉት የረጅም አመታት ትግል የአካባቢውን መልክዓ-ምድር በባህላዊ የእርከን ሥራ በፈለጉት መንገድ ለመቀየርና ለመጠቀም የቻሉ ሲሆን፤ በዚህም ከሀገራቸው አልፈው ዓለምን በማስደመም የራሳቸውን  ታሪክ ሠርተዋል።
ኤ.አ.አ. በ2011 ዓ.ም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶ ማራኪ መልክዓ-ምድር፤ 23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡ መልክዓ- ምድሩ፣ በውስጡ በተለያዩ ባህላዊ ዘዴዎች  የተሰሩ እርከኖችና ካቦች የታጠሩ መንደሮች እንዲሁም ጥብቅ ደኖችን ጭምር ያካተተ ነው፡፡ የኮንሶ የድንጋይ እርከኖች በዓይነታቸውም ሆነ በአሰራራቸው ውበትን የሚያጎናፅፉና የአካባቢውን መልከዓ-ምድር የሚጠብቁ ናቸው፡፡
ለኮንሶዎች ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ኩራት የሆነው ባህላዊ የእርከን አሰራር በኮንሶ ብቻ  ሳይገደብ፣ 24 ሰዓት ሳታንቀላፋ ለእድገት በምትታትረው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባም እየተተገበረም  ይገኛል፡፡ ኮንሶዎች  የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ባደረገባቸው  የእንጦጦና  ሌሎች የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የእርከን ሥራ ጥበባቸውን መተግበር  ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በዚህ ሥራቸውም  በመዲናዋ  ላይ  አሻራቸውን እያሳረፉ  ይገኛሉ።
በኮሪደር ልማቱ የአፈር መሸርሸር እንዳይከሰት የእርከን ስራዎችን ሲያከናውኑ ያገኘናቸው ከኮንሶ ማህበረሰብ የመጡት የእርከን ሥራ  ባለሙያ አቶ አማኑዔል አክመል፣ተወልደው ያደጉት በደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ዞን ከአራት ከተማ ሲሆን፤ በደንና መሬት ጥበቃ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን   ይናገራሉ፡፡
“እኔ ከመጣሁ ጀምሮ እስከ አሁን እየሰራን ያለነው በወንዞች ዳርቻ ሲሆን፤  የኮሪደር ልማት ስራዎቹ በጣም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ  መሆናቸውን አይተናል። የኮንሶ ልጆችም እርከኑን በመስራት አሻራቸውን እያስቀመጡ ናቸው፡፡ በእኔ በኩልም ቱሪስቶች ሊጎበኙት የሚችል፣ውብና ጥራት ያለው  ስራ ሰርተን ከተማችን ላይ አሻራችንን ማስቀመጥ እንፈልጋለን፡፡ አሁንም ከመንግሥት ጋር በኮሪደር ልማት ዙሪያ ጠንካራ ሥራዎችን  እየሰራን እንገኛለን፡፡” ብለዋል፤ አቶ አማኑዔል፡፡
በኮሪደር ልማቱ ስለተፈጠረላቸው የሥራ እድልም ሲናገሩ፤ “ለበርካታ ኮንሶ ወጣቶች የስራ እድል ከመፈጠሩ ባሻገር ከምናገኘው ገቢ በመቆጠብ ቤተሰቦቻችንን ለመርዳት እንዲሁም ወደፊት ለመነገድም ሆነ በተለያየ ሙያ ለመሰማራትና ኑሮአችንን ለማሻሻል የምንችልበት አጋጣሚ ተፈጥሮልናል፡፡” ይላሉ፡፡


የኮንሶ የእርከን አሰራር ከቅድመ አያቶቻችን  ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ነው የሚሉት አቶ አማኑዔል፤ ይህ ጥንታዊ የሆነ  የእርከን ሥራ ኮንሶን በዩኔስኮ እንድትመዘገብ ያደረገ ጥበብ  መሆኑን  ያወሳሉ፡፡ እኛም አባቶቻችን ያስረከቡንን ጥበብ  ይዘን በዚህ የልማት ስራ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ጭምር አሻራችንን እያኖርን ነው፤ብለዋል፡፡
“በተለያየ ምክንያት ወደ መዲናዋ የሚመጡ የኮንሶ ልጆች በእኛ እጅ የተሰሩ ስራዎችን ሲያዩ፣ እነሱም የራሳቸውን  ታሪክና አሻራ ለማኖር መነቃቃት  ይፈጥርላቸዋል።” ሲሉም አክለዋል፡፡
የእርከን ስራዎች ዋና ዓላማ መሬት በጎርፍ እንዳይሸረሸር መከላከልና አካባቢን ማስዋብ  መሆኑን የገለጹት አቶ አማኑኤል፤ እኛም በአካባቢያችን ለእርሻ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን በማስተካከልና እርከን በመስራት ነው የምንጠቀመው፤ ብለዋል፡፡ ከልምድና ተሞክሮአችን ተነስተን ከኮንሶ በተሻለ ሥራውን በማስፋትና በማጠናከር እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡


የእርከን ሥራ በህብረትና በአንድነት መሥራትን ይፈልጋል ይላሉ፤ አቶ አማኑኤል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፤ “የእርከን ሥራ  የተለያዩ አሰራሮችን በየደረጃው የሚፈልግ ነው፡፡ አንዱ መሰረት ሲጥል ሌላው ድንጋይ ይጠርባል፤ የተጠረበውን ድንጋይ ሌላው ሲደረድር  አፈር የሚሞላም አለ፤ ስራው የሰው ኃይል ስለሚፈልግ እነዚህን ተግባራት  በሙሉ አቅም ለመፈፀም በህብረት መስራት ያስፈልጋል፡፡” ብለዋል፡፡
“በህብረት በመስራታችን ደግሞ ህብረ-ብሄራዊነትን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን እያሳየን ነው፡፡ ይህ ለወደፊቱ የብልፅግና ጉዞ መሰረት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላው የእርከን ሥራ  ባለሙያ ደግሞ አቶ ያቤና ያኬሳ ይባላሉ፡፡ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከኮንሶ ዞን ከነአ ወረዳ ነው የመጡት፡፡ እዚህ አዲስ አበባ የመጡት ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅ/ቤት በተደረገላቸው ጥሪ፣ በከተማዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ ለመሳተፍ መሆኑን   ይናገራሉ፡፡
በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የወንዝ ዳርቻ ልማት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፤ “እጅግ በጣም የሚያኮራ የልማት ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ለማየት ችለናል፡፡ እኛም በልማቱ  እየተሳተፍን በመሆናችን  በጣም ደስተኞች ነን፡፡” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተፈጠረላቸውን የሥራ እድል አስመልክቶ ሲናገሩም፤ ለኮንሶ ልጆች ትልቅ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው፣ እዚህ  በቀን የሚያገኙት ዕለታዊ ገቢ በኮንሶ ከሚያገኙት ጋር  ጨርሶ የሚነጻጸር እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡    
“እኛ ጥቅምት ላይ በመጀመሪያ ዙር የመጣን ነን፤ስድስተኛ  ወራችንን ይዘናል፡፡ በኮንሶ እለታዊ ገቢያችን ዝቅተኛ ነበር፡፡ እዚህ ምግብና ልብስን ሳይጨምር በቀን 650 ብር እናገኛለን፤ በወር ከ19 ሺ ብር በላይ ይደርሰናል፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ አርሶ አደር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡
በዚህ ገቢም የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ እየቀየሩበት፣ ልጆቻቸውን እያስተማሩበትና የተቸገሩ ዘመዶቻቸውን እየረዱበት መሆኑን  ያስረዳሉ፡፡ ሥራው በጣም አድካሚ ቢሆንም፣ የዚያኑ ያህል ተጠቃሚ መሆናቸውን አልሸሸጉም፡፡
  መጀመሪያ ላይ በዚህ ሥራ ላይ  ከኮንሶ የመጡ 50 ባለሙያዎች ብቻ ተሰማርተው   እንደነበር ያስታወሱት አቶ ያቤና፤ አሁን ላይ ከ400 ያላነሱ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡  
የኮንሶ ባህላዊ የእርከን ሥራ ታሪካዊ ዳራን በተመለከተ ሲያብራሩም፤ “የኮንሶ ማህበረሰብ በተፈጥሮው ታታሪ ህዝብ ነው፡፡ መልክዓ ምድሩም ሲታይ አብዛኛው ተራራማ፣ አሸዋማና ዝናብ አጠር   ነው፡፡
ይሄ  አካባቢ ታዲያ በምን አይነት ዘዴ ነው ለረጅም አመታት የኖረው ቢባል በአፈርና ውሃ ጥበቃ ዘዴ ነው፡፡ ይህም ከጥንት ጀምሮ አፈር በጎርፍ ተጠርጎ እንዳይሄድ ሲሰራበት የኖረና እንደ ባህል የተወሰደ ልምድ በመሆኑ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ እኛ ዘንድ ደርሷል፡፡ እኛም እዚህ ተገኝተን ልምዳችንንና አሻራችንን እያኖርን ነው፡፡” ብለዋል፡፡


  ከደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ዞን  የመጡት አቶ ከድረው ገበየሁ እንዲሁ በመዲናዋ እየተከናወነ በሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ የተለያዩ የእርከን ካብ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ከእንጦጦ ተራራ ወደ ከተማው የሚፈሰው ወንዝ አፈሩን እንዳይሸረሽር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዳይከሰትና የተክሎቹ ስር እንዳይነቃቀል እንዲሁም የወንዝ ዳርቻዎችን ውበት ለማስጠበቅ የእርከን ስራ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሥራውን የለመድነው ከአያቶቻችን በማየት ነው የሚሉት አቶ ከድረው፤ የአዲስ አበባ  ወጣቶችም  ከእኛ ልምድ ቢቀስሙና ከተማቸውን ቢያለሙ ተጠቃሚ ይሆናሉ ባይ ናቸው፡፡
“እኛ በአሁኑ ወቅት እየሰራን በምናገኘው ገንዘብ ህይወታችንን እየቀየርን ነው፤በዚህም በጣም ደስተኞች ነን፤ሥራችን አልቆ ጥርት ያለ ውሃ በወንዝ ሲፈስ ስናይ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ደስተኞች እንሆናለን፡፡” ሲሉም ስሜታቸውን  ገልጸዋል፡፡
ከኮንሶ ምድር መጥተው በኮሪደር ልማቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉና ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች በሙሉ  ይህንን መልካም የሥራ ዕድል ለፈጠሩላቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤና ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይሄ ከኮንሶ ምድር አልፎ በመዲናዋ የኮሪደር ልማት ላይ እየተተገበረ የሚገኝ የኮንሶ ባህላዊ የእርከን ሥራ በክልሎችም ቢዳረስ ጠቀሜታው የትየለሌ ነው ብለን እናምናለን፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ፣ የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክቷል። ኮሚቴው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አሳስቧል።
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ሁለተኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን፤ በገንዘብ ፖሊሲው ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር አቅርቧል። ኮሚቴው የዋጋ ግሽበትን፣ የፊስካል ፖሊሲ ትግበራን፣ የውጭ ኢኮኖሚን፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን፣ እንዲሁም  በአገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ከፍተኛ አንድምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በግምገማ ቃኝቷል።
ካለፈው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ወዲህ፣ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በመምጣት በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ፣ 15.0 በመቶ መድረሱን ኮሚቴው ገልጿል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት የዋጋ ግሽበት በተከታታይ እየረገበ የመጣው፣ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተሉ፣ የግብርና ምርት በመሻሻሉና በአስተዳደራዊ ዋጋዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ማሻሻያ ቀስ በቀስ በመተግበሩ ምክንያት እንደሆነ ኮሚቴው አመልክቷል፡፡
 ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ 14.6 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ይህም ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 3 በመቶ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያነሰ ነው ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ፣ ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ቀንሶ 15.6 በመቶ የደረሰ ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ወራት የማንሰራራት አዝማሚያ ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡
በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች የታየው ምቹ የመኸር ዝናብ ወራትና በግብርናው ዘርፍ እየተወሰዱ ያሉ የአቅርቦት ማሻሻያ ውጥኖች በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ የሰብል ምርት እንደሚኖር ማሳያ መሆናቸውን ኮሚቴው አንስቷል፡፡ በሌሎች ዘርፎችም፣ በተለይም በኢንዱስትሪ፣ በሸቀጦች ወጪ ንግድ (በተለይም በቡናና በወርቅ)፣ እንዲሁም በአገልግሎት ወጪ ንግድ (በተለይም በአየር ትራንስፖርትና በቱሪዝም) ዘርፎች የተጠናከረ ዕድገት እንደሚኖር ኮሚቴው ግምቱን አስፍሯል፡፡
ካለፈው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ወዲህ የገንዘብ ዝውውር እድገት መጠነኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፤ ይህም ሊሆን የቻለው የብድር፣ የፊስካልና የውጭ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላላ በመደረጋቸው ነው ተብሏል። እስከ ጥር ወር 2017 ድረስ በኢኮኖሚው  ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) የ22.8 በመቶ፣ መሰረታዊ ገንዘብ (base money) 42.0 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ሲያሳዩ፤ የሀገር ውስጥ ብድር በ19.8 በመቶ መጨመሩ ተመላክቷል፡፡ መሰረታዊ ገንዘብ ፈጣን ዕድገት ሊያሳይ የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በመያዙና ተመጣጣኝ የአገር ውስጥ ገንዘብ ወደ ባንክ ስርዓት እንዲገባ በመደረጉ ነው፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ እስካሁን የታየው የዋጋ ግሽበትን የመቀነስ ጥረት አበረታች መሆኑን በመጥቀስ፣ የዋጋ ግሽበት አሁንም ቢሆን ከተጠበቀው በላይና በመካከለኛው ጊዜ ከሚደረስበት ከነጠላ አሃዝ ግብ ከፍ ያለ እንደሆነ አስታውቋል። በመሆኑም የዋጋ ግሽበት ትርጉም ባለው መልኩ እስኪቀንስ ድረስ አሁን ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ተገቢ በመሆኑ ሊቀጥል እንደሚገባ መስማማቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የገንዘብ መጠን በገንዘብ ፖሊሲው ላይ ያልተፈለገ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር መጠንቀቅ እንደሚያሻ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከፍ ብሎ “ይታያል“ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስና በውጭ ምንዛሪ ተመን ረገድ የሚታዩ ግምታዊ አስተሳሰቦችን (expectations) ለመቆጣጠር ሲባል የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Rate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይና በወለድ ተመን ላይ ወደ ተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደር ስርዓት የሚደረገው ሽግግር ገና በመሆኑ በባንኮች የብድር ዕድገት ላይ የተቀመጠው 18 በመቶ ገደብ እንዲቀጥል መወሰኑን  ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ሰሞኑን  ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውንና የመንግሥት ሠራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ የወር ደሞዝ ላይ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድደውን  የአደጋ ስጋት ፈንድ ረቂቅ አዋጅ እንደሚቃወም ገለጸ፡፡ ፓርቲው  የመንግሥት ሰራተኞች ለመንግሥት ታጣቂ ሃይሎች የገንዘብ መዋጮ እንዲያዋጡ እየተገደዱ ነው ሲል ነቅፏል፡፡  
ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከትላንት በስቲያ  ሐሙስ መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በረቂቅ ዓዋጅነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን የአደጋ ስጋት ክፍያን የተቃወመ ሲሆን፣ የቀረበው ረቂቅ ዓዋጅ የመንግሥትና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሰራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ የወር ደመወዝ ላይ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ድንጋጌ  ማካተቱ፣ “በኑሮ ውድነት የሚፈተነውን ሕዝብ ለሌላ ዙር ችግር የሚጋብዝ ነው፡፡” ሲል ተችቶታል፡፡ ፓርቲው አክሎም፤ “በሥርዓት ሰራሽ ጦርነትና የኑሮ ውድነት እየተፈተነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ተጨማሪ ዕዳ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ሥርዓታዊ ክፋትን ያረጋግጣል” ብሏል፡፡
“አሁን ያለው የሰራተኛ አጠቃላይ ወጪና ገቢ ሲታይ፣ አገዛዙ የዚህ አገር ዜጎች በአገራቸው ነፍሳቸውን ለማቆየት በሚያስችል ደረጃም ቢሆን በልተው እንዳይኖሩ እየፈለገ መሆኑን የሚያሳይ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል” ያለው ፓርቲው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረትን የሚከታተሉ የተለያዩ የምርምር ተቋሞች በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት ደረጃ ከ60 በመቶ እንዳለፈ መጠቆማቸውን አመልክቷል፡፡ “የኑሮ ውድነቱ በዚህ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ እያለ፣ ሠራተኛው ከወር ወር አላደርስ ያለውን ገቢ በሃይል በመቀነስ፣ በየክልሉ የሚያካሂደውን ጦርነት ለመደጎም እየተጠቀመበት ይገኛል” ሲልም ባልደራስ መንግሥትን ወንጅሏል፡፡
የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ  ረቂቅ ዓዋጅ፣ የመንግስትና የግል ሰራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ የወር ደመወዝ ላይ ክፍያ እንዲፈጽሙ ግዴታ የሚጥል ሲሆን፤ ባንኮች፣ አነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ድርጅቶች ከሚሰጡት የብድር መጠን ላይ፣ እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚዎች ከሚከፍሉት  የአገልግሎት ክፍያ እንደሚሰበሰብ ይደነግጋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የመንግሥት ሰራተኞች ለመንግሥት ታጣቂዎች የገንዘብ መዋጮ እንዲያዋጡ እንደሚገደዱ የጠቆመው ፓርቲው፤ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ለመንግሥት ታጣቂዎች ዕርዳታ ከደመወዛቸው ሰባት በመቶውን በግዴታ እንዲያዋጡ መፈረማቸውን አመልክቷል፡፡
 “አገዛዙ እየፈፀመ ያለውን አውዳሚ ጦርነትና በሕዝብ ላይ እየተገበረ ያለውን አግባብ ያልሆነ ምዝበራ እንዲያቆም እንጠይቃለን” ያለው ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘላቂ ደህንነቱ መከበር ሰላማዊ ትግልን በመከተል “እንዲታገል ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል፣ በመግለጫው።

Page 3 of 763