Administrator

Administrator

እኛ ተርፈናል፤ እዛ ላሉት ድረሱላቸው
ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተገደው እየተደፈሩ ነው
እስር ቤት አንዲት ነፍሰ ጡር ሞታብናለች - የስደት ተመላሾች  

ሳኡዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ወደ አገሯ የገቡ ስደተኞችን በሃይል ማስወጣት ከጀመረች ሁለተኛ ሳምንቷን ያስቆጠረች ሲሆን ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደአገራቸው የመመለስ ዘመቻው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ዜጐችን ከሳኡዲ ለማምጣት ባለፈው ሳምንት በቀን ሰባት በረራዎች ይደረጉ እንደነበር ያስታወሱት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በዚህኛው ሳምንት በቀን 12 በረራዎች እየተደረጉ ዜጐችን ማምጣቱ እንደቀጠለና እስከትላንት ድረስ ከ19ሺ በላይ ዜጐች መመለሳቸውን ገልፀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በቦሌ አየር ማረፍያ ተገኝተው ተመላሾቹን ያነጋገሩ ሲሆን፤ ስደተኞቹን ለማቋቋም ከክልል መንግስታት ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ሁለት ሌሎች ቦታዎች ለስደተኞቹ በጊዜያዊ መጠለያነት እያገለገሉ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ከሶስት የሳኡዲ ተመላሾቹ ጋር ባደረገችው ቆይታ የስደት መከራቸውን እንደሚከተለው ነግረዋታል፡፡

“ኤምባሲያችን አይሰማም እንጂ ደጋግመን ነግረናል”
ራውዳ ጀማል ትባላለች፡፡ የሃያ ዓመት ወጣት ናት፡፡ ስለራስዋም ሆነ በሳኡዲ ስላሉ ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ሁኔታ ስታወራ እያለቀሰችና እየተወራጨች ነው፡፡ ለማነጋገር ስቀርባት “ወንድ ከሆናችሁ ጋዜጠኞች ነን፣ የህዝብ አፍ ነን ካላችሁ፤ እዚህ ተቀምጣችሁ፣ “ሁለት ሰው ሞተ” እያላችሁ ከምታቅራሩ ሳኡዲ ሂዱና በየቀኑ ሁለት ሶስት ሰው የሚሞትበትን እልቂት ተመልከቱ፣ “ሰዎቹን ምን እየሰራችሁ ነው?” ብላችሁም ጠይቁልን” አለችኝ። መቅረፀ ድምፄን ሶስት አራት ጊዜ ያስጠፋችኝ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ ሆነችልኝ፡፡
ስንት ዓመት ቆይተሽ መምጣትሽ ነው?
ከሁለት ዓመት በኋላ ነው የመጣሁት፡፡ እስከ አስረኛ ክፍል የተማርኩት አዲስ አበባ ቢሆንም፤  የኮምቦልቻ ልጅ ነኝ፡፡
እንዴት ነበር የሄድሽው?
በፓስፖርት… በኮንትራት ነበር የሄድኩት … ካላስ! የሰውየው ልጆች ግን “የማይሆን” ፊልም ተመልከቺ እያሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ሲመረኝ ጠፍቼ ወጣሁ፡፡ ከዚያም ከጓደኞቼ ጋር በነፃነት ቤት ተከራይተን እየኖርን፣ በ1800 ሪያል ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ቤተሰቤንም ገንዘብ እየላኩ እረዳ ነበር፡፡
ወደ አገርሽ እንዴት ተመለስሽ?
ውጡ ሲባል… ረብሻ ሲነሳ.. ጓደኞቻችን ሲሞቱ.. ሲደፈሩብን.. ‘ድሮም ስደተኛ ክብር የለውም’ ብዬ ተመልሼ መጣሁ..ከሚገሉኝ ከሚያበለሻሹኝ ብዬ እጄን ሰጠሁ፡፡ ብዙ ኢትዮጵውያኖች ችግር ላይ ናቸው.. እባካችሁ ድረሱላቸው፡፡ ብርዱም ፀሃዩም ሲፈራረቅባቸው.. ያሳዝናሉ፡፡ ብዙ ያልመጡ አሉ፤ መምጣት እየፈለጉ፡፡ ስቃይ ላይ ናቸው፡፡ እኔ አሁን አስራ ሶስት ቀን ታስሬ ነው የመጣሁት፡፡
እስቲ ስለ እስሩ ንገሪኝ …
ሁለት ቀን ያለ ምግብ ያለ ውሃ ነው የታሰርነው። ከዛ በኋላ ግን ጥሩ ምግብ ሰጥተውናል፣ ጥሩ መኝታም አግኝተናል፡፡ ብዙዎቹ ግን ከእኛ የባሰ ችግር ላይ ናቸው፡፡ መጠለያ ያላገኙ አሉ…ኤምባሲያችንም አይሰማም እንጂ ስንት ጊዜ ደውለን ተናግረናል መሰለሽ፡፡ ግን የሚሰማ የለም፡፡  
ከአገራችን ውጡ ካሉ በኋላ ትዕግስት ያጡና መልሰው ይዩዙናል፡፡ በዛን ጊዜ አበሻው፣ ሻንዛ/ጩቤ ይመዛል፡፡ ፖሊስ ራሱን ለማዳን ይተኩሳል። እኔ እንደውም ደህና ነኝ፤ እዛ ላሉት ድረሱላቸው። በምድረ ዱርዬ እየተደፈሩ ነው ያሉት /ለቅሶ/ ስንት ህፃናት አሉ የሚሞቱ፣ የሚታመሙ፡፡ ስንመጣ ደሞ፤ ሻንጣ  አትያዙ ተብለን ተመናጭቀን…በጥፊ ተመትተን..መከራችንን በልተናል፡፡
ወንዶችና ሴቶች ለብቻ ነበር የተቀመጣችሁት?
የተቀመጣችሁት አትበይ! የታሰራችሁት በይ፡፡ … የሴት እስር ቤት ለብቻው ነው በሴቶችና በህፃናት ለቅሶ የተሞላ ነው፡፡ እኔ ራሴ ስድስት ያበዱ ሴቶችን ይዤ መጥቻለሁ…/ለቅሶ/
አሁን ቤተሰብ እየጠበቅሽ ነው?
ነበረ ግን ሻንጣዬ ጠፋብኝ፡፡ በርግጥ ጤነኛ ሆኖ መምጣትም ቀላል አይደለም፡፡ እዛ ያሉትን ጥለናቸው ስንመጣ እያለቀስን ነው፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ አንድ እርጉዝ ሞታብናለች፡፡ እዛው እስር ቤት እያለን ምጥዋ መጣ፤ ግን የህክምና እርዳታ ባለማግኘትዋ ሞተች፡፡
እስር ቤት ያሉት ምን ያህል ይሆናሉ?
ሰማኒያ ክፍል አለ..በየክፍሉ ስልሳ አምስት ስልሳ አምስት ሰው ነው ያለው፡፡ መካሲመሺ እስር ቤት ይባላል፡፡ የወንድና የሴት እስር ቤት የተራራቀ ነው፡፡ በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ በመኪና እንጂ በእግር  አይሞከርም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማው ያለው እስር ቤት ሞልቶ የመዝናኛና የስብሰባ አዳራሹን ሁሉ እስር ቤት አድርገውታል፡፡ የተደፈሩት የሞቱት..ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዷን እርጉዝ ለሶስት ሲደፍሯት ሞታለች፡፡
የሌሎች አገር ስደተኞችም እየወጡ ነው ተብሏል…
አዎ፡፡ ኢትዮጵያዊው ከበደሉ ብዛት የተነሳ እየተናነቀው እኮ ነው ግጭቱ የሚከረው፡፡ ሚስቱንኧ እህቱን ከእጁ መንትፈው ሊወስዱበት ሲሉ ነው ጦርነት የሚነሳው፡፡ አበሻ ወንድ እየሞተ ያለው ‹‹ሴቶቻችንን አትንኩብን..›› ስለሚል እኮ ነው፡፡ ኤምባሲው ሊደርስላቸው ይገባል፡፡

“የሁለት ሰው መርዶ ይዤ መጥቻለሁ”
ስምሽ ማን ነው?
ፀጋ ኪዳኔ ገብረኪዳን
ምን እየጠበቅሽ ነው?
ዘመድ አለችኝ አዲስ አበባ የምትኖር፤ እስዋ እስክትመጣ እየጠበቅሁ ነው፡፡
ሳኡዲ ምን ያህል ጊዜ ቆየሽ?
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ነው ከሪያድ/ሞንፋ የመጣሁት፡፡ ከኢትዮጵያ ስሄድ በኮንትራት ቢሆንም በባህር ከሄዱት ስደተኞች የተለየ ክብር አላገኘሁም፡፡ ጭቅጭቅ፣ ስድብና ድብደባ  ሲበዛብኝ ከተቀጠርኩበት ቤት በስምንተኛ ወሬ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ የሄድኩት ለአንድ ስራ ብቻ ተዋውዬ ነበር። የምተኛው ግን ከሁለት ሰዓት አይበልጥም ነበር፡፡ ሥራ ብቻ ነው 24 ሰዓት!
እስቲ ስለደረሰብሽ ችግር በዝርዝር ንገሪኝ..
በ700 ሪያድ ተቀጥሬ ነበር ከዚህ የሄድኩት፡፡ አሰሪዬ ቤት አራት ትላልቅ ወንድ ልጆች አሉዋት። የእህትዋ ልጆችም እዚያው ነው የሚኖሩት፡፡ ‹‹ወሲብ ካልፈፀምን..›› ብለው ያስቸግራሉ፡፡ በጣም ተሰቃየሁ፡፡ ከአቅሜ በላይ … ለህይወቴ በጣም አስፈሪ….ሲሆንብኝ ወጣሁ፡፡
ከአቅሜ በላይ ስትይ …
ልጆቹ ወሲብ ካልፈፀምን ብለው አሻፈረኝ ስላቸው፣ “በቢላ እናርድሻለን” እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ እምነቴን እንድቀይር ሁሉ ይፈልጋሉ። አፈር ድሜ በላሁ፡፡ ሰርቼ ለፍቼ … በዚያ ላይ ነፃነት አልነበረኝም፡፡ ወገቤ፣ ዓይኔ ታመመ፡፡ እነሱ እኮ ሃያ አራት ሰዓት እየበሉ እየጠጡ ነው፡፡ በዚያ ላይ በእጅሽ ላይ ስልክ ማየት አይፈልጉም፡፡ ሁሉ ነገር ሲያንገፈግፈኝ ሁለት ወር የሰራሁበትን ገንዘብ ጥዬ ወጣሁ፡፡ ከዛ ኤጀንሲው ለሌላ ሰው ሸጠኝ፤ በአስር ሺህ ሪያድ፡፡ እዚያም ግን  አልተመቸኝም። ስራው ሃያ አራት ሰዓት ነበር፡፡ አምስት ሰው እንኳን የማይችለው ስራ ነበር፡፡ አንድ ኩንታል ሊጥ አብኩቼ፣ ለሱቅ የሚሸጡት ብስኩት ጠብሼ፣ ሰባት መቶ ሪያል ነበር የሚከፈለኝ፡፡ ሁለት ወር ሙሉ እንደምንም ድምጼን አጥፍቼ ሰራሁ… በእንቅልፍ እጦት ልወድቅ እየተንገታገትኩ፡፡ እፊታቸው ላይ ግን ደስተኛ እመስል ነበር፡፡ ሰውነቴ እየመነመነ መጣ፡፡ ይሄኔ ድጋሚ ለመጥፋት ተዘጋጀሁ፡፡
“ለሌላ ሰው ሸጠኝ” ያልሽው … ኢትዮጵያዊ ነው?
/እንባዋ እየፈሰሰ/አረብ ነው፡፡ ወደ ሳኡዲ ከላከኝ ኤጄንሲ ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ የረመዳን ጊዜ ደግሞ ሱቃቸው ወሰዱኝ፤ የአንድ ሰዓት መንገድ ተጉዞ ሌላ ቤት አላቸው፡፡ እዛ ይዘውኝ ሲሄዱ  ስራ ይቀልልኛል ብዬ ነበር፡፡ … ግን የባሰ ሆነብኝ፡፡ ለካ ጓደኞቻችን ወደው አይደለም ራሳቸውን የሚያጠፉት፤ አብደው ጨርቃቸውን ጥለው በየጎዳውና የወጡትና መንገዱ የወደቁት ... የወገብና የአእምሮ በሽተኞች የሆኑት? “ምነው እናቴ ስትወልጅኝ በመሃፀንሽ ውስጥ ደም ሆኜ በቀረሁ? እናቴ እባክሽ መልሰሽ ዋጪኝ” አልኩኝ፡፡ ራሴንና ቤተሰቤን ልረዳ ስንገታገት ከፊታቸው ድፍት ብል እኮ … እንደሰው ከቆጠሩኝ ... ሬሳዬን ለእናቴ ይልኩላት ይሆናል፡፡ ያለዚያ ግን የሀገራቸው መንግስት አውጥቶ ይቀብረኛል፡፡
ከዚያ ሁሉ በፊት ጠፍቼ መውጣት እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ አንድ ቀን ረመዳን ካፈጠሩ በኋላ ቤተሰቡ ተሰብስቦ ሊዝናኑ ወጡ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ቶሎ ብዬ የሴትየዋን ሙሉ ልብስ ለብሼ፣ ሽፍንፍን ብዬ ወጣሁ፡፡
ሻንጣ ምናምን ሳትይዢ?
ባዶ እጄን ነው የወጣሁት፡፡ የሰራሁበት ገንዘብ እንኳን በእጄ የለም፡፡ በቃ ዝም ብዬ ወጣሁ፡፡ ፓኪስታናዊ የታክሲ ሾፌር አገኘሁ፡፡ ‹‹ምን ሆንሽ?›› ብሎ ሲጠይቀኝ በዝርዝር ነገርኩት፤ አዘነ፡፡ ‹‹ሪያድ የሀበሻ ሃገር ነው፤ ብዙ ኢትዮጵያዊ አለ›› ብሎ እዛ (በነፃ) ወሰደኝ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን አገኘሁ፡፡
እዚያ መኖር ጀመርሽ ማለት ነው?
ሳያቸው በጣም ነው ያለቀስኩት፡፡ አገሬ የገባሁ ይመስል..መሬት ሁሉ ስሚያለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ በባህር (በህገወጥ መንገድ) የመጡ ሴቶች ነበሩ። ከእነሱ ጋር አንድ ቤት በስድስት መቶ ሪያድ ለስድስት ወር ተከራይተን አብረን እየኖርን እንሰራ ጀመር፡፡
ቤቱን ለስንት ተከራያችሁ?
አስር ነበርን፡፡ ሁለት ወር እንደሰራሁ ግን በአካባቢው ግጭት ተነሳ፡፡ እግሬ አውጪኝ ብለን በየፊናችን ተበታተንን፡፡
ምን ዓይነት ግጭት?
መንግስት የሌለበት አገር ይመስል ጐረምሶች በር እያንኳኩ በሽጉጥ፣ በካራ፣ ሰው መግደል ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ‹‹እጃችንን እንስጥ›› ብለን ተማከርን፡፡ ሌላው ችግር ፖሊስ፤ ትዳር መስርተው የሚኖሩትን የአበሻ ወንዶች እየወሰደ፣ ሴቶችን ለብቻቸው ይተዋቸው ነበር፡፡ በቤቱ ወንድ አለመኖሩን የተገነዘበ የአገሩ ዱርዬዎች (እንኳን ለአበሻው ለመንግስትም ልባቸው ያበጠ ነው) ሴትዋን ለአራትና ለአምስት እየሆኑ መድፈር ያዙ፡፡ ከእኛ ጎን የነበሩትን ሲያሰቃይዋቸው አይተናል፡፡ ወንዶቹን ፖሊስ ሲወስዳቸው ጎረምሶቹ ተከትለው ይገቡና ሴቶቹን መጫወቻ ያደርጓቸዋል/ለቅሶ/፡፡ አንድ ያየሁትን ልንገርሽ../ረጅም ትንፋሽ/እነዚህ ጐረምሶች…ሶስት ሴቶች ያሉበት ክፍል ውስጥ ገብተው ለሰባት ደፈሯቸው፡፡ /ማውራት አልቻለችም፤ ሳግና እንባዋ እያቋረጣት/..ከሶስቱ አንዷ የሰባት ወር ነፍሰጡር ነበረች፤ ሲገናኝዋት ሞተች፡፡ አንዷን ደግሞ ለሰባት ደፈሯትና ገድለው ጥለዋት ሊወጡ ሲሉ ሽርጣ/ፖሊስ መጣ፡፡ ከፖሊስ ጋር ተኩስ ገጥመው እርስ በርስ ተገዳደሉ፡፡ የሀበሻ ወንድ ከእህቱ ወይንም ከሚስቱ ሊለዩት ሲመጡ አልለይም ይልና ይገደላል፤ ይደበደባል … በቃ እልቂት ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ ብለሽ ካራ ቆሬ እንደምትይው..ሪያድ ብለሽ ሞንፋ የሚባል አካባቢ በርካታ አበሾች ይኖራሉ፡፡ እኔ እንኳን የማውቀው … ከአምስት በላይ ሴቶች እንደተገደሉ ነው፡፡  መላ አካላቸውን ቆራርጠው ነው የጣሏቸው፡፡ ግን ይሄ ሁሉ መከራ ምን አድርገን ነው?
አንቺ እንዴት መጣሽ ወደ አገርሽ?
እጄን ሰጠኋ፡፡ አሰሪዬ ‹‹የት ልትሄጂ ነው?›› ብላ ስትጠይቀኝ፡፡ ‹‹አንድ ጓደኛዬ ልትወልድ ነውና ልጠይቃት ..›› ብዬ የሰራሁበትንም ሳልቀበል ወጣሁ፡፡ ምክንያቱም ብትገለኝስ ብዬ ፈራሁ፡፡ አብዛኛው አበሻ ከስራ ወደቤቱ ሲሄድ እየተያዘ ነው የሚመጣው፡፡ የሰራበትን የለፋበትን ሳይዝ ባዶ እጁን፡፡ እና እኛም ነገሩ ስላስፈራን እጃችንን ሰጠን። በቃ እኔም ወደ እዚህ መጣሁ፡፡
ዛሬ ላይ ሆነሽ ስታስቢው ወደዛ በመሄድሽ ምን ይሰማሻል?
መጀመሪያ ከዚህ ስሄድ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፤ የራሴንና የቤተሰቤን ህይወት ላሻሽል እንደሆነ ተስፋ በማድረግ፡፡ ከዛ በኋላ ግን  ከስራው ብዛት የተነሳ ከጥቅም ውጪ ልሆን ነው ብዬ እጅግ አምርሬ አለቅስ ነበር፡፡ በጣም ስጋት ያዘኝ፡፡ ግን ከሞት ተርፌ ወደዚህ ስመጣ አምላኬን አመሰገንኩ፡፡
ቤተሰብሽ መምጣትሽን አውቀዋል?
አላወቁም፡፡ ምን እያሰቡ ይሆን? ይሄን ሁሉ ነገር እየሰሙ፡፡ እናቴ መንገድ መንገድ እያየች ይሆናል፡፡ ደሞ ከእኛ አካባቢ ልጆች ብዙ የሞቱ አሉ፡፡..አሁን እኔ ራሴ የሁለት ሰው መርዶ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ እናቴም ሰው ሲመጣ ‹‹ልጄን አይታችኋል?›› ትል ይሆናል፡፡ እኔስ መጣሁ..በረሃ ላይ ተደፍተው ለመምጣት ወረፋ እየተጠባበቁ ያሉ ህጻናትና ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ እዚህ የመጣነው እኮ ግማሽ አንሞላም፡፡ በሳኡዲ የኢትዮጵያውያን እንባ ያሳዝንሻል፡፡ ብዙዎቹ በሃዘን ላይ ናቸው፤ ድረሱላቸው፡፡


“ሰባት ያበዱ ሴቶችን አይቻለሁ”

ስምሽን ንገሪኝ..?
ሀያት አህመድ
እስቲ አካሄድሽን ንገሪኝ …
ከደሴ ነው በኤጀንሲ የሄድኩት፡፡ የምሰራው በጠለብ/በህጋዊ መንገድ ነበር፡፡ ሰዎቹ ሳይመቹኝ ሲቀሩ..ብዙ ጓደኞቻችን ችግር ሲደርስባቸው ሳይ፣ ስልካችንን ቀምተው ቤተሰቦቻችን በሃሳብ ሲያልቁ፣ እኔም ነገሩ ስላልተመቸኝ ጥዬ ጠፋሁ፡፡ ከዛም በሃጂና ኡምራ የሄድኩ አስመስዬ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡
በጠለብ ስንት ጊዜ ሰራሽ?
ሶስት ወር ነው የሰራሁት፡፡
አሰሪዎችስ ቤት የሚደርስብሽ ችግር ምን ነበር?
በቤት ውስጥ ያሉ ወንዶች ያስቸግሩኝ ነበር፤ አስገድዶ ለመድፈር ይተናነቁኛል፡፡ አሰሪዬ በስራዬ  አትደሰትም፣ ያጠብኩትን ነገር እንደገና እጠቢ ትለኛለች፡፡
“የኢትዮጵያ ሰራተኞች ሞያ የላቸውም፣ “ሞዴስ እንኳን በአግባቡ መጠቀም አይችሉም፣ በዚያ ላይ ወንዶቻችንን ያባልጋሉ” የሚል ክስ ከሳኡዲ ሴቶች ይሰማል፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?
በጭራሽ! እኛ ደልቶን ይሄን ልናስብ? አንገታችንን ቀና አድርገን እንኳን ለመሄድ እንቸገራለን እኮ፡፡ እዛ ቦታ ላይ እኛን ብታይ ኢትዮጵያዊነት ያስጠላሻል፡፡ አለባበሳችን ምንድን ነው፣ ሁኔታችንስ፣ ኑሮዋችንስ..እኛ የእነሱን ባል የምናባልግ ምን አምሮብን፣ እንዴት ሆነን ነው?  እኛን እኮ ይጠየፉናል፡፡ በምን አንገታችን ቀና ብለን ነው የእነሱን ወንዶች የምናባልገው? እኛ እኮ ለህይወታችን እየሰጋን ነው… እያንዳንዷን ቀን የምናሳልፈው፡፡ በርግጥ የገጠር ልጆችም ይሄዳሉ። እንግዲህ በንፅህና የሚታሙት እነሱ ናቸው፡፡ ግን ስንቱን አእምሮውን አሳጡት…. ወይኔ!!..አሁን ስንመጣ እንኳን ጅዳ ኤርፖርት ውስጥ ሰባት ያበዱ ልጆችን አይቻለሁ፡፡ ‹‹ይዛችኋቸው ሂዱ›› ሲሉን ነበር፤ እንዴት አድርገን እንይዛቸዋለን? ጥለናቸው ነው የመጣን፡፡ አይ ዜጎቻችን! እየቀወሱ፣ እየተደፈሩ፣ እየተደበደቡ፣ እየተጣሉ ነው ሜዳ ላይ ….ተመልካች አጥተው፡፡
ጣትሽ ላይ የጋብቻ ቀለበት አያለሁ … ባለትዳር ነሽ?
ፈትቻለሁ፡፡ የአስር ዓመትና የስምንት ዓመት ልጆች አሉኝ፡፡ እነሱን ላሳድግ ብዬ ነው በሰው አገር የተንገላታሁት፡፡ ገንዘብ እልክ ነበር፡፡ ሆኖም እኔም አልተለወጥኩም፤ ለልጆቼም አልሞላልኝም፡፡ አንድ ጊዜ ሆድ ብሶኝ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር፡፡ ታውቂያለሽ… ልጆቼ በዓይን በዓይኔ መጡብኝና … ከድርጊቴ ታቀብኩ፡፡
አይኔ እንቅልፍ ካጣ ስንት ጊዜው ሆነ መሰለሽ… አይኔ ስር ጥቁር ብሎ የምታይው፣ የበለዘ የሚመስለው እኮ በእንቅልፍ እጦት የተፈጠረብኝ ነው፡፡ ጀርባዬን ያመኛል፡፡ ብዙ ሰዓት የምቆምበት እግሬንም እጅግ ታምሚያለሁ፡፡ አሁን ለትንሽ ጊዜ  ማገገም አለብኝ፡፡
ጂዳ ኤርፖርት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚጠባበቁ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ ይባላል…?
በጣም ብዙ እንጂ! ‘ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገር ነቅሎ ነው እንዴ የወጣው ብዬ ተደንቄያለሁ፡፡ በጣም ያዘንኩት ግን ወደዚህ ስመጣ ኤርፖርት ሰባት ያበዱ ልጆች ስመለከት ነው፡፡ እዛ ያለው ኤምባሲያችን እንዴት  ወደ አገራቸው አይመልሳቸውም? ‹‹እህ›› ብሎ ችግራቸውን የሚያደምጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ እስቲ አስቢው…ሰባት ሴቶች አብደው አይቻለሁ፤ በአይኔ በብረቱ፡፡ አንዷ ልጅዋ ሞታባት (በረሃብ ነው) የቀወሰችው፡፡ ስድስቱ ደግሞ በስራ ቦታቸው ቀውሰው፣ አሰሪዎቻቸው ናቸው አምጥተው የጣልዋቸው፡፡ የምናየው ነገር ሁሉ ለዓይን ይዘገንናል፡፡
ከዕረፍት በኋላ ምን  ልትሰሪ አቀድሽ…?
አሁን ጤንነት አይሰማኝም፤ ካገገምኩ በኋላ እንግዲህ … እንጃ ምን እንደምሰራ፡፡ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ተቀምጬ ነው የመጣሁት፡፡ ከአስርና አስራ አምስት ዓመት በላይ የኖሩትም ‹‹ምንድነው የምንሰራው..›› የሚል ነው ጥያቄያቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ኖረው ቢመጡም ምንም የያዙት ነገር የላቸውም፡፡ በጣም ያሳሰበኝ እሱ ነው፡፡
ከአሁን በኋላ ወደ ሳኡዲ የመመለስ ሃሳብ አለሽ?
አላህ ያውቃል፡፡    

ጥንት አንድ አዋቂ ሰው ነበር ይባላል፡፡ በመጪው ዓመት ምን እንደሚከተል ያውቃል አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሡ የ አዋቂ መጥቶ መጪውን እንዲተነብይ ያስጠራውና ወደ ሸንጐ እየመጣ ሳለ፤ አንድ እባብ ያገኛል፡፡ “ንጉሡ ትንቢት ተናገር ብለውኛል፤ ምን ልበል?” አለና ጠየቀው፡፡ እባቡም፤
“መጪው ጊዜ ጦርነት ስለሆነ ፀልዩ! በላቸው” አለው፡፡
አዋቂው ሸንጐ ቀርቦ እባቡ እንዳለው፤ ለንጉሡ ተናገረ፡፡ “ያለው ዕውነት ነው” አሉና ንጉሡ ሸልመው ሸኙት፡፡ አዋቂው ወደቤቱ ሲመለስ ያን እባብ አገኘው፡፡ በጦሩ ወጋውና መንገዱን ቀጠለ፡፡
በሁለተኛው ዓመት እንደገና ንጉሡ አዋቂውን አስጠሩት፡፡ እዚያው ቦታ የቆሰለውን እባብ አገኘው፡፡
እባቡም፤ “ባለፈው ዓመት መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ጠይቀኸኝ፤ ነግሬህ፣ ወግተኸኝ ሄድክ፡፡ ሆኖም አሁንም እነግርሃለሁ፡፡ ይህ ዓመት የበሽታ ዓመት ነውና ፀልዩ በላቸው” አለው፡፡
አዋቂው ወደ ሸንጐ ሄደና የበሽታ ዓመት እንደሚሆን ተናገረ፡፡ ንጉሡም “ባለፈው ዓመት የተናገረው ዕውነት ስለሆነ ዘንድሮም የተናገረው ዕውነት መሆን አለበት፡፡ በሉ፤ ሸልሙና ሸኙት” አሉ፡፡
አዋቂው ሲመለስ ያንን እባብ አገኘው፡፡ በድንጋይ መትቶ ወግሮ ወግሮ መንገዱን ቀጠለ፡፡
በሶስተኛው ዓመት እንዲሁ አዋቂው ሸንጐ ተጠራና ሄደ፡፡ መንገዱ ላይ እዛው ቦታ እባቡን አገኘው፡፡
“ዘንድሮስ ምን ብል ይሻለኛል?” አለው፡፡
“ባለፈው ዓመት መክሬህ፣ ተናግረህ፣ ተሸልመህ ስትመለስ በድንጋይ መትተኸኛል፡፡ ሆኖም አልተቀየምኩህም፡፡ በዚህ ዓመት የእሳት ዘመን ነውና ፀልዩ በላቸው” አለው፡፡
ወደንጉሱ ሄዶ “ዘንድሮ የእሳት ዘመን ነው” አላቸው፡፡
ንጉሡም፤ “ባለፉት ሁለት ዓመታት የተናገረው ዕውነት ስለሆነ፤ ዘንድሮም ያለው ዕውነት መሆን አለበት፡፡ ሸልሙትና ይሂድ” አሉ፡፡
አዋቂው ሲመለስ እባቡን አገኘው፡፡ አሁን ግን መምታት ሳይሆን በእባብ ሊያቃጥለው ሞከረና መንገዱን ቀጠለ፡፡
በቀጣዩ ዓመት ለአራተኛ ጊዜ ንጉሡ አስጠራው፡፡ አዋቂው መንገዱ ላይ እባቡን አገኘው፤
“ዘንድሮስ ምን ልበል?” አለው፡፡
እባቡም፤ “ዘንድሮ የጥጋብ ዘመን ስለሆነ ፈንድቁ! በላቸው” አለው፡፡
ንጉሡ የጥጋብ ዘመን መሆኑን ሲሰሙ “እስከዛሬ የተናገረው ምንም መሬት ጠብ የሚል ነገር አልነበረውም፡፡ ዘንድሮም ዕውነት ስለሚሆን በርከት አድርጋችሁ ሸልሙልኝ” አሉ፡፡
አዋቂው ወደቤቱ ሲመለስ እባቡን አገኘው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን በሀር የተንቆጠቆጠ ካባ አለበሰው፡፡
እባቡም፤
“የመጀመሪያው ዓመት የፍልሚያ ዘመን ነበረና በጦር ወጋኸኝ፡፡
በሁለተኛው ዓመት የበሽታ ዘመን ነበረና በድንጋይ ወገርከኝ፡፡
በሦስተኛው ዓመት የእሳት ዘመን ነበረና በእሳት አቃጠልከኝ፡፡
በአራተኛው ዓመት ግን የጥጋብ ዘመን በመሆኑ ካባ አለበስከኝ፡፡ እነሆ ጥበቤን ሁሉ ሰጥቼሃለሁ፡፡ ያ ይበቃሃል፡፡ አሁን ካባህን መልሰህ ውሰድ፡፡ የሰጠሁህ ጥበብ ከምንም ነገር በላይ ነው፡፡ ጥበቤን ሁሉ ውሰድ፡፡ ራሴ የነገርኩህን የነገ ዕጣ - ፈንታ፤ ራሴውም መጋራት ስላለብኝ ነው ያልተበቀልኩህ! በምንም ቁሳቁስ ልትተካው አትሞክር”  
                                                        *   *   *
ዕጣ-ፈንታችንን አናመልጥም፡፡ የዕጣ-ፈንታችን አካል ነን፡፡ የምንለው፣ የምናቅደው፣ የምንራዕየው ሁሉ የእኛው አካል ነው፡፡ በተናገርነው እንነገርበታለን፡፡ በደነገግነው እንቀጣበታለን፡፡ በደሰኮርነው እናፍርበታለን ወይም እንኮራበታለን፡፡ በተለይ መንግስት ስንሆን ባወጣነው ህግ እከሌ ከእከሌ ሳንል፣ ወገናዊና ኢፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ መተዳደርና መቀጣት አለብን፡፡
የመንግሥትነታችን ትልቅ ቁም ነገር የህዝብን ደህንነትና የሀገርን ህልውና መታደግ ነው፡፡ ይህ ዋና ኃላፊነት ነው፡፡ ህዝብ እንዳይሸበር፣ እንዳይጠራጠር፣ ዕምነት እንዳያጣ ማድረግ፤ በአገሩ፣ በመንግሥቱና በኃላፊዎቹ ላይ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል፡፡  
“የመንግሥት መኖር ዓላማው የህብረተሰቡን የተለያዩ ፍላጐቶች ለማርካት፣ አገርን ለማጠንከር መሆን አለበት፡፡ መንግሥታዊ ህጐችና ተቋሞቹም ዘለዓለማዊ ሳይሆኑ ይህንኑ ማህበራዊ ፍላጐት ለማስገኘት ሲባል ከህብረተሰቡ ዕድገት ጋር አብረው የሚያድጉና የሚለወጡ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ድህነት፣ ሰብአዊ ጉስቁልና፣ ሀዘንና ሰላም - የለሽነት ይቆራኘውና ለውድቀት ይዳረጋል” ይለናል የጥንቱ፣ የታህሣሥ 1953ቱ ንቅናቄ ተዋናይ፤ ግርማሜ ነዋይ (የታህሣሡ ግርግርና መዘዙ)
የህዝብን ችግር ቸል አንበል፡፡ የኋላ ኋላ ጣጣው ይመለከተናልና!
ለትናንሽ የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ ሳንሰጥ ወደ ውስብስብና ግዙፍ ችግርነት እንዲያድጉ ከፈቀድንና ቸልታችን ከበዛ፤ ያለ ጥርጥር ወደ ፖለቲካዊ ችግርነት ማደጋቸው አይቀሬ ነው፡፡
የወሎ ረሃብ እንደተነናቀ ወደ አብታዊ ማዕበልነት ተለወጠ፡፡ የሚሊተሪ ዲክታተራዊ አገዛዝ መናጠጥ፣ የቢሮክራሲያዊ በደል ማጠጥ፣ የሥልጣን መባለግና ያላግባብ መበልፀግ የአማጽያንን መፈልፈልና የተቃዋሚን ቁርጠኝነት መውለዱን ወለደ፡፡
ዛሬም የህዝብን ኑሮና የሀገርን ውስብስብ ችግሮች በወቅቱ የመፍታት ቅን ልቦና ከሌለ ዕጣ- ፈንታ ወዳዘዘው ውድቀት ማምራት ግድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ የመንግሥት ዋንኛ ትኩረት የአንበሳውን ድርሻ ይውሰድ እንጂ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጐች ወዘተ የነገዋ አገራችን ዕጣ-ፈንታ ይመለከተናል ማለት ኤጭ የማይባል ነገር መሆኑን ልብ ማለት ደግ ነው!
“የህዝብ ችግር እየተባባሰ በሄደ ቁጥር፤ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እያወቀ እንዳላወቀ፣ እያየ እንዳላየ፣ በዝምታ መኖሩ ከባድ የህሊና ሸክምና ፈታኝ ጥያቄ ነው” ይላል ጄኔራል (መንግሥቱ ነዋይ፡፡)  
አቶ ብርሃኑ አስረስ “ማን ይናገር የነበረ…የታህሣሡ ግርግርና መዘዙ” በተባለው መጽሐፋቸው፤ ህዝብ ጭቆና ሲያንገፈግፈው ስለሚደርስበት ደረጃ ሲናገሩ፤
“የሕዝብን መነሳሳት ለማፍራት ብዙ ሙከራ ተደርጐ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ቀፎው ተነክቶበት የተሸበረ ንብና ተስፋውን ጨርሶ የተነሳ ሕዝብ ተመሳሳይ በመሆኑ፤ የተፈፀመው ሙከራ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ድሮው ተገዥነት ቦታው ለመመለስ አልቻለም…” ይሉናል፡፡
የአስተዳደር ብስለታችን፣ የዲፕሎማሲያችን ጥራት፣ ስለፓርቲና ስለ ሀገር ያለን ግንዛቤ፤ የምንመራውን ህዝብ አመኔታና ተቀባይነት የሚያስገኘው ቁልፍ ነገር መሆኑን መቼም ቢሆን መቼም እንወቅ፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ፣ የሀገር ወዳዶችንና ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደገዝጋዡ ሳይሆን እንደ አጋዡ በማየት ማግባባት፣ ማስማማት፣ ማደራደር ከመሪዎቻችን የሚጠበቅ የብልህ እርምጃ ነው፡፡ ያለድካ


በፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ከሌሎች ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ጋር በመጀመሪያ ተጠሪነት በሶስት መዝገቦች የተከሰሱት አቶ መላኩ ፈንታ ከሚኒስትርነታቸው ጋር ተያይዞ ለተነሣው ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ረቡዕ እለት የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ሲል ብይን ሠጥቷል፡፡
ቀደም ሲል ሠኞ ህዳር 9 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ አቶ መላኩ ፈንታ ባቀረቡት መከራከሪያ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን በማስረዳት ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊታይ እንደሚገባ የገለፁ ሲሆን አቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ በሠጠው አስተያየት፤ ተከሣሹ በእርግጥም በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ም/ቤት አባል መሆናቸውን ተቀብሎ፣ ነገር ግን የሚመሩት መስሪያ ቤት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለመሆኑ፣ ተጠቃሹ ያላቸው የሚኒስትር ማዕረግነት ለጥቅማ ጥቅም አላማ ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ አስረድቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለረቡዕ ህዳር 11 ቀን 2006 ቀጠሮ የሠጠ ሲሆን ረቡዕ እለት የዋለው ችሎትም መዝገቡ የተቀጠረው በፍርድ ቤቱ የቀረበውን ጉዳይ ከማየት ስልጣን ጋር ተያይዞ በተነሣው ጭብጥ ላይ ብይንና ትዕዛዝ ለመስጠት መሆኑን አስታውቆ ብይን ሠጥቷል፡፡
ፍ/ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት ነው የሚለው ሣይረጋገጥ ወደ ክርክር መግባት አይቻልም ካለ በኋላ፣ በተነሣው መከራከሪያ ጭብጥ መሠረት፣ አቶ መላኩ ሚኒስትር ናቸው ወይስ አይደሉም? ሚኒስትር ከሆኑስ ጉዳዩን አከራክሮ የመወሠን ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት ነው የሚለው የግድ እልባት ማግኘት አለበት ብሏል።
ፍ/ቤቱም አቶ መላኩ ፈንታ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ከግራ ቀኙ ክርክር እና ከተለያዩ ሠነዶች ማረጋገጡን በብያኔው አስታውቆ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ አዋጅ መሠረት፤ የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት (ሚኒስትሮች ጨምሮ) በስራ ሃላፊነታቸው ምክንያት ተጠያቂ በሚሆኑባቸው ሙስናን ጨምሮ ማናቸውም የወንጀል ጉዳዮች የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የስረ-ነገር ስልጣን የተሰጠው መሆኑ በግልፅ ስለ ደነገገ፣ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሁለት አዋጆች ሁለት ንኡስ አንቀፆች ህገ-መንግስታዊ ናቸው? አይደሉም? የሚለው ትርጉም የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ብሏል - ፍ/ቤቱ፡፡
በተለይ የአቶ መላኩ ጉዳይ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚታይ ከሆነ፣ በህገ መንግስቱ የተከበረላቸውን መሠረታዊ ጉዳያቸውን በይግባኝ እንዲታይ የማቅረብ መብት በግልፅ የሚጋፋ መሆኑን ያመላከተው የፍ/ቤቱ ብይን፤ አቶ መላኩ በዋና ወንጀል አድራጊነት ከሌሎች ሠዎች ጋር ተጣምሮ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው በመሆኑና የሁሉም ተከሣሾች ጉዳይ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቢታይ ሁሉም ተከሣሾች በህገ መንግስቱ የተከበረውን የይግባኝ ጉዳይ የማቅረብ መብት በግልፅ የሚጋፋ ከመሆኑም ሌላ የአቶ መላኩ ጉዳይ ብቻውን ተነጥሎ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እንዲሁም ከእሣቸው ጋር የተከሠሡት ሌሎች ተከሣሾች ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተነጥሎ ይታይ ቢባል ደግሞ ሁሉም ሠዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማናቸውም አይነት ልዩነት ሣይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል ከሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 25 መሠረታዊ መርህ ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ፍ/ቤቱ በብይኑ አትቷል፡፡ ይሄ ማለት፣ አቶ መላኩ በጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳያቸው ይታይ ቢባልና ሌሎች ተከሣሾች ተነጥለው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ጉዳያቸው ይታይ ቢባል፣ ሌሎች ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸው ሲከበርላቸው፣ አቶ መላኩ የይግባኝ መብት እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ይሆናል፡፡ የአቶ መላኩም ሆነ የሌሎች ተከሣሾች ሠብአዊ መብት በእኩል እንዲጠበቅ አከራካሪው ጉዳይ የህገ-መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ብሏል፡፡ በዚህ መሠረት የህገ መንግስታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሣኔ ሊያገኝ የሚገባ በመሆኑ፣ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፣ ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች የማጣራት ሃላፊነት የተጣለበት በመሆኑና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 20(6)፣ አንቀፅ 25፣ አንቀፅ 10 እና አንቀፅ 13(1) ይቃረናሉ ወይስ አይቃረኑም? እንዲሁም የስረ ነገሩ ስልጣን የየትኛው ፍ/ቤት ነው? የሚለውን እንዲመረምርና ትርጉም እንዲሠጠው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳዩ ሊመረመር እንደሚገባ በማመን፣ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ፍ/ቤቱ በይኗል፡፡
ፍ/ቤቱ በሠጠው ትዕዛዝም የብይኑ ትዕዛዝ ግልባጭ በመሸኛ ለፌደሬሽን ም/ቤት ፅ/ቤት እና የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ፅ/ቤት በእለቱ እንዲላክ በማለት ለታህሣስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በፍ/ቤቱ ብይንና ትዕዛዝ ዙሪያ የህግ ትንታኔ እንዲሠጡን ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ምሁራን፤ እንዲህ አይነቱ ብይን ከዚህ ቀደም በእነ አቶ ታምራት ላይኔ እና አቶ ስዬ አብርሃ ላይ ተግባራዊ ተደርጐ እንደነበር በመጠቆም፣ ፍ/ቤቱ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የሚላቸውን ጉዳዮች በራሱ ከመወሠኑ በፊት ለሚመለከተው አካል መምራቱ ተገቢ ነው ብለዋል።  

የአውሮፓ ህብረት 5.3 ቢሊዮን ብር የልማት እርዳታ ለኢትዮጵያ የሰጠ ሲሆን፤  የልማት እርዳታው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የትምህርት የጤናና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ግንባታና ጥበቃ፣ለድርቅ መከላከያና መቋቋሚያ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ማስፋፊያ የሚውል እንደሆነ ታውቋል፡፡
ከህብረቱ የኢትዮጵያ ልዑክ ፅ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከተሰጠው የ5.3 ቢሊዮን ብር የልማት እርዳታ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ሲውል፣ አንድ ቢሊዮን ብር ደግሞ ድርቅን ለመከላከልና ለመቋቋም ለሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡ የተቀረው ገንዘብ ደግሞ ለጤና፣ለትምህርትና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ግንባታና ጥበቃ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚውል ታውቋል፡፡ የልማት እርዳታው ስምምነት የአውሮፓ ኮሚሽን የልማት ኮሚሽነር አንድሪስ ፒባልግስና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ አህመድ ሽዴ መካከል የፊታችን ሰኞ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ግንባር ቀደም ከሆኑት የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች መካከል ዋነኛው ሲሆን የህብረቱና የኢትዮጵያ የልማት ትብብር ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ የልማት እንቅስቃሴ በገንዘብና በቴክኒክ ሲረዳ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ እምብርቱ ላይ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን ፊት ለፊት በ700 ሚሊዮን ብር የተሠራው ባለ 5 ኮከብ ዘመናዊ ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ዛሬ ይመረቃል፡፡
አቶ ገምሹ በየነ የተባሉ ባለሀብት ግዙፍ ኢንቨስትመንት የሆነው ባለ 10 ፎቅ መንትያ ሆቴል፤ 154 ክፍሎች ሲኖሩት የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራው መሳሪያ የተገጠሙለት መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ ሁለት ፕሬዚዴንሻል ክፍሎችና 16 ጁንየር ሱት፣ ስታንዳርድ፣ ኪንግ ሳይዝ፣ ደብል ትዊን፣ ፔንት ሃውስ ክፍሎች፣ አሉት፡፡ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሬስቶራንትና ባር፣ የሕፃናት መጫወቻ፣ የወጣቶች የኦሎምፒክ ደረጃ መዋኛ፣ ስፓና ጂምናዚየም…አለው፡፡
ሆቴሉ 10ኛ ፎቅ ፕሬዚዴንሻል ሱት ላይ ሆነው በሁሉም አቅጣጫ ከተማዋን እየቃኙ ለመዝናናት ያመቻል፡፡ ቀልብን የሚስቡት የመኝታ ክፍሎቹ፤ መታጠቢያ ገንዳና ሻወር፣ ብሮድ ባንድ ኢንተርኔት፣ 42 ኢንች ቴሌቪዥን ሳተላይት ቲቪና ስልክ፣…አላቸው፡፡
ኢሊሌ ሆቴል ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ዲፕሎማቶች፣ ኢንቨስተሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና፣ ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ዛሬ እኩለ ቀን ላይ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
ሆቴሉ፣ በአሁኑ ወቅት ለ300 ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር የሠራተኞቹ ቁጥር 450 እንደሚደርስ የሆቴሉ ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ ገልፀዋል፡፡

በተለያዩ ከተሞች በራሳቸው፣ በባለቤታቸውና በልጆቻቸው ስም 17 ቦታዎችንና ቤቶችን ይዘዋል ከሚለው ክስ ነፃ ሆነዋል፡፡
ከባለቤታቸው ጋር ምንጩ ያልታወቀ 490ሺ ብር በባንክ አንቀሳቅሰዋል ከሚለው ክስ ነፃ ናቸው ተብሏል

የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ያረጋል አይሸሹም፤ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ከቀረቡባቸው አምስት ክሶች መካከል በአንዱ ብቻ “ጥፋተኛ ናቸው” የተባሉ ሲሆን፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል በሚል ከቀረበባቸው ክሶች ነፃ ሆኑ፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ሃብታሙ ሂካ፣ ከሁለት የግል ድርጅት ሃላፊዎች ከአቶ ጌዲዮን ደመቀና ከቶ አሰፋ ገበየ ጋር “ጥፋተኛ ናቸው” የሚል ውሳኔ የተላለፈባቸው፤ ለሦስት የትምህርት ተቋማት ግንባታ ከወጣው ጨረታ ጋር በተያያዘ ክስ ነው፡፡ ህገወጥ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር  ለመምህራን ኮሌጅ፣ ለአዳሪ ት/ቤት እና ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የግንባታ ጨረታ ከመንግስት መመሪያ ውጪ እንዲከናወን አድርገዋል በሚለው ክስ 4ቱ ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው እንደተገኙ የከፍተኛው ፍ/ቤት ችሎት ሐሙስ እለት ገልጿል፡፡ 

አቶ ያረጋል እና አቶ ብርሃኑ ለተቋማቱ ግንባታ  የተመደበው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን እያወቁ በግልጽ ተወዳዳሪዎችን ጋብዘው ማጫረት ሲገባቸው፣ የሶስቱንም ፕሮጀክቶች የዲዛይን፣ የቁጥጥር እና የኮንትራት ጨረታ በህገወጥ መንገድ ለጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት በጥቅሉ በ250ሺህ ብር ሰጥተዋል ይላል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያቀረበው ክስ፡፡ አቶ ያረጋል ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ጨረታዎቹ  አቶ ሃብታሙ በሚመሩት የትምህርት ቢሮ በኩል እንዲከናወኑ አድርገዋል የሚለው የኮሚሽኑ ክስ፣ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ ስራው  በ “ውስን ጨረታ” እንዲከናወን በደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ብሏል፡፡  ለዚህ ወረታም አቶ ያረጋል ከ3ኛ ተከሳሽ ከአቶ ጌዲዮን ደመቀ፤ 50ሺህ ብር እንዲሁም አቶ ሃብታሙ 75ሺህ ብር እጅ መንሻ መቀበላቸው በክሱ ተገልጿል፡፡
“ጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት” ፕሮጀክቶቹን የመምራት አቅም እንደሌለው እያወቁ ውል የፈረሙት አቶ ጌዲዮንና ወኪላቸው አቶ አሰፋ ገበየሁ፤ ስራውን ለ5 ዓመታት በማጓተት መንግስትን ለ2.8 ሚ.ብር ተጨማሪ ወጪ ዳርገዋል ብሏል - የፀረ ሙስና ኮሚሽን፡፡

ፍ/ቤቱም በአራቱ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ባለስልጣናቱና ፕሮጀክቶቹን እንዲመራ የተደረገው አማካሪ ድርጅት፤ በህገወጥ የጥቅም ትስስር፣ የትምህርት ተቋማቱን ግንባታ ለሦስት ድርጅቶች ሰጥተዋል የሚለው ፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ የሚመሩት “ጋድ ኮንስትራክሽን” በ40 ሚ. ብር የአዳሪ ት/ቤትና በ18ሚ ብር የመምህራን ኮሌጅ እንዲገነባ፣ አቶ መክብብ የሚመሩት ንብረት ለሆነው “ኮለን ኮንስትራክሽን” ደግሞ በ17 ሚ. የቴክኒክና ሙያ ተቋም እንዲገነባ በመስጠት ስራው አጓትተዋል ብሏል፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም ከዚህ ክስ ነፃ መሆናቸውን ፍ/ቤቱ ገልፆ፣ የትምህርት ቢሮ ሃላፊና አራቱ የግል ድርጅት ሃላፊዎች ግን ጥፋተኛ ናቸው በማለት ወስኗል፡፡

ሌላኛው ክስ፣ አቶ ያረጋል፣ እንዲሁም የትምህርት ቢሮ ሃላፊውና ወንድማቸው ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል የሚል ነው፡፡
ርዕሠ መስተዳደር በነበሩበት ወቅት ደሞዛቸው 4500 ብር እንደነበረና ከዚያም  የፌደራል የህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲሠሩ 5670 ብር ደሞዝ ይከፈላቸው እንደነበረ የሚገልፀው የኮሚሽኑ ክስ፣ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ሃብት አካብተዋል በማለት ከሷቸዋል፡፡

አቶ ያረጋል በራሳቸው ስም በአዲስ አበባ በተለያዩ ከተሞች አራት ቦታዎችንና ቤት ይዘዋል የሚለው የክስ ዝርዝር፣ በባለቤታቸው ስም ደግሞ በ7 ሚሊየን ብር የሚገመት ሆቴልና ድርጅት እንዲሁም ስምንት ቦታ፣ የንግድ ሱቆችና ቤቶችን ቦታዎችን በተለያዩ ከተሞች ይዘዋል ይላል፡፡ በቤንሻንጉል ውስጥም በሁለት ልጆቻቸው ስምም 5 ቦታዎች ይዘዋል፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ቅርንጫፎች በራሣቸው እናበባለቤታቸው ስም ከ490 ሺ ብር በላይ አንቀሳቅሰዋል ብሏል - ፀረ ሙስና ኮሚሽን፡፡

የባለስልጣናት ሃብት ምዝገባ ሲከናወን ሃብታቸውን ሙሉ በሙሉ አላሣወቁም የተባሉት አቶ ያረጋል፤ “ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል” የሚለውን ክስ በበቂ ማስረጃ መከላከል በመቻላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡

የትምህርት ቢሮ ሃላፊውም እንዲሁ ከወንድማቸው ጋር ከተመሳሳይ ክስ ነፃ ሆነዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በሁሉም ክሶች ላይ ውሳኔ ያስተላለፈበትን ባለ 170 ገጽ ትንተና በንባብ ለማሰማት ሁለት ቀን ፈጅቶበታል፡፡
የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠባቸው ክሶች ላይ ከከሳሽ እና ከተከሳሽ የቅጣት አስተያየት ለመቀበል ለህዳር 26 ቀን ተቀጥሯል፡፡

በአስረስ አሰፋ ተፅፎ በድንቅስራው ደረጄ እና ያሬድ መንግስቴ የተዘጋጀው “የእኔ እውነት” የተሰኘ ትያትር ከህዳር 14 ጀምሮ በዓለም ሲኒማ ለተመልካች እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡ ትያትሩ ከአንድ አመት በላይ ተደክሞበታል ያሉት አዘጋጆቹ፤ ዘወትር ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት እንደሚታይም አስታውቀዋል፡፡ የትያትሩ ደራሲና ፕሮዱዩሰር አለም ሲኒማን የመረጡትን በመንግስት ትያትር ቤቶች ወረፋው አታካች በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ “ዓለም ሲኒማ ቀና ትብብር አድርገው ወዲያው ነው የፈቀዱልን፤ በቦሌ መንገድ ግንባታ ምክንያት ዘገየ እንጂ አምና ነበር የሚከፈተው” ሲሉም አክለዋል፡፡
በትያትሩ ላይ በ“ሰው ለሰው” የቴሌቪዥን ድራማ የምትሰራውን አርቲስት ምስራቅ ወርቁን ጨምሮ ተዘራ ለማ፣ ዳዊት ፍቅሬ፣ ጥሩዬ ተስፋዬ፣ ቢኒያም ፍቅሩ፣ አስረስ አሰፋ፣ ፍቅሩ ባርኮ እና እምነት ከፈለ ተውነውበታል፡፡

ግማሽ-መንገድ መሄድ ይቅር እንዝለቅ እስከጐሉ ጫፍ
ድጋፍ የለም በግማሽ-አፍ’ ከልባችን እንደግፍ!
የወረት ነው የሚመስል-ካሸናፊ ጋራ እፍ-እፍ
አኪሩ ሲዞር ማቀርቀር-ተሸናፊን ረግጦ ማለፍ!
መቼ በኳስ ብቻ ሆነ - ታይቷል በሌላም ምዕራፍ፡፡
ቋሚ እንሁን እንጽና’እንጂ ከእሳት ወደ በረዶ
መወንጨፍ ከጽንፍ ወደ ጽንፍ
ክñ አመል ነው ዥዋዥዌ-ዛሬ ጓዳ@ነገ ደጃፍ”
ስናገባ ብቻ ዘራፍ!
ስንሸነፍ ጉልበት ማቀፍ!
ሲሞቅ እንደ እንፋሎት መትነን@
ሲበርድ እንደግዑዝ ነገር’ፍፁም ዲዳ በድን መሆን
እሪ ስንል ጐል አግብተን’ያመት-ባል ገበያ መስለን@
በለስ ነስቶን ድል ባይቀናን
ሬሳ የወጣው ቤት መሆን@
ኧረ ጐበዝ! ቋሚ እንሁን !
ገብቶ መፋለም ቢያቅተን
መደገፍ እንዴት ይጥፋብን?!
ከፊልሙ እንዳልተዋደደ
ከግብሩ እንዳልተዋሃደ
ከትወናው ጋራ ሠምሮ’ወጥ ሆኖ አብሮ እንዳልሄደ
ከቦክስ ኋላ እንደሚመጣ’የቀሽም ፊልም አጃቢ ድምጽ
ከድርሰቱ እንደተፋታ’እንዳላማረ ኮሾ አንቀጽ
ሙሉ ጨዋታ መደገፍ’መጮሁ እንዴት ያቅተን?
በቴፕ አፍ የተፈጠረ’የዲጄ ነው እንዴ ድምፃችን?
ባገርም ጉዳይ ይሄው ነው፡-
ቅጥ-አንጣ በድላችን
ሲበልጡን ቆፈን አይያዘን-
መቼም መቼም የትም ቢሆን
ሙሉ ጊዜ ቋሚ እንሁን! እናግዝ ልጆቻችንን!
መቼም ኢትዮጵያዊነትን’የውጪ ባዕድ አልሰጠን
እኛው ውስጥ የበቀለ እንጂ’ “የዲጄ” አይደለም ድምፃችን
ብንሸነፍም እኛው’ብናሸንፍም እኛው ነን!
በወረት አንለዋወጥ’እንደግፍ ከልባችን!
እናግዝ አገራችንን!!
(ለኢትዮ-ናይጄሪያ የኳስ ፍልሚያና ለኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች) ኀዳር 2 ቀን 2006 ዓ.ም

Monday, 18 November 2013 11:37

አስማተኞቹ እና ሚስጢራቸው

እኔ የተረዳሁትን ማንም ስላላወቀ እንጂ ሀሳቡ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ንግድ ማለት ቅይይር ማለት ነው፡፡ እንደ ልዋጭ። አንዱን እሴት ትቀበልና በእሱ ፋንታ ሌላውን ትሰጠዋለህ፡፡ ከልውውጡ የምታተርፈውን ነገር (እሴት) መሰብሰብ እና እንደገና በትርፍ ለመለወጥ መሞከር፡፡ ነጋዴ የመሆን ትርጉሙ በአጭሩ ይሄ ነው፡፡
የሚለወጠው ነገር የሚፈለግ መሆን አለበት፡፡ በዚህ በጨፈገገ ትውልድ ላይ እንደ ሳቅ የሚያስፈልግ ነገር የለም፡፡ ሳቅ ውስጡ የሌለው ማንም የለም፡፡ ሳቅን ፍለጋ ግን ገንዘቡን ከፍሎ “ኮሜዲ ሾ” ይገባል። ኮሜዲያን እንደ “አባ ገና” በትልቅ ስልቻ የሳቅ ገፀ በረከት ይዞ የሚዞር ይመስለዋል ታዳሚው፡፡ ግን ትልቅ ስልቻ ይቅርና ኪሱን የሚሞላ ሳቅ እንኳን ይዞ አይመጣም - እንዲያውም በተቃራኒው በኪሱ ያለው ለቅሶ ነው፡፡ እነሱ ታዳሚዎቹ በውስጣቸው ይዘው ያልመጡትን ሳቅ ኮሜዲያኑ ሊሰጣቸው አይችልም።
ኮሜዲያኑ አስማተኛ ነው፡፡ ማስመሰል ነው ስራው፡፡ ከተመልካቹ ሆድ ውስጥ ያወጣውን ሳቅ ከራሱ ሆድ ያፈለቀው አስመስሎ ማቅረብ፡፡ እኔ የገባኝ ሀሳብ ይሄ ነው፡፡ ሀሳቡን ተጠቅሜ የልዋጭ ሰራተኛ ሆንኩ፡፡ ከሰው ውስጥ የተደበቀውን ነገር ግልፅ አድርጌ መልሼ እሸጥለታለሁ፡፡ በሚስጥር፡፡
ሚስጥሩ፡- “If you don’t bring it here, you won’t find it here!” የሚል ቢሆንም፤ ሚስጥሩን ለታዳሚዬ ከገለፅኩለት አስማቴ ይነቃል፡፡ ሲነቃ፤ ጥበብ መሆኑ ይቀራል፡፡ ተራ የወሮበላ ማጭበርበር ይሆናል፡፡ መንገዱን ሳልገልፅ፤ መነሻውን እና መድረሻውን ብቻ ይፋ በማድረግ አስማቴን እሰራለሁ፡፡
መነሻው ይሄ ነው፡፡ መነሻው እንዲህ ነው። ሁሉም ሰው የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ አንዳንዱ መሳቅ ነው የሚፈልገው፤ ሌላው ማዘን፣ ሌላው ማፍቀር፣ ሌላው መክበር ወይንም መከበር … ሁሉም የሚፈልገው እና ሊያሟላው ያልቻለ አንድ ፍላጐት አለው፡፡ ያ ነው መነሻዬ፡፡ ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለው መንገድ የእኔ ሚስጢር ነው። መድረሻው ሁሉንም እንደየፍላጐታቸው መንካት መቻል ነው። መሳቅ የፈለገው ስቆ፣ ማልቀስ የፈለገው አልቅሶ፣ ማፍቀር የፈለገ ፍቅሩን አግኝቶ … ወደ ቤቱ እንዲሄድ ማድረግ፡፡ መነሻው ላይ ቃል እገባለሁ። ፍላጐቶች ሁሉ ስኬታቸውን እንደሚያገኙ፡፡ መድረሻው ላይ ብር እቀበላለሁ፡፡ ፍላጐታቸውን ከእነሱ ጋር ላገናኘሁበት፡፡
ጥበብ እና አስማተኝነት የደላላነትም ስራ ነው። ፈላጊ እና ፍላጐቱ የሚገናኙበት ምስጢር ግን ከእኔ ጋር ተደብቆ ይቆያል፡፡ የእኔ አስማተኝነት ያለው ሚስጢሩን እስከጠበቅሁ ድረስ ብቻ ነው። ከባድ የሚመስሉ ነገሮች ከብደው የሚቆዩት የክብደታቸው ምክንያት ሳይገለፅ እስከቆየበት ጊዜ ድረስ ነው። ሁሉም ሚስጢር ሲጋለጥ አስቀያሚ እና ተራ ይሆናል፡፡ የኔ ሚስጢር ደግሞ በጣም ቀላሉ ነው። መስታወት ፊት ፈላጊውን ማቆም ነው፡፡ ራሱን በመስታወቱ እየተመለከተ… ግን መመልከቱን እንዳያውቅ በእኔ አማካኝነት የራሱ ምስል ነፀብራቅ እንዲታየው አደርጋለሁ፡፡ መሳቅ የፈለገ ደንበኛዬ ራሱን በእኔ ትርጓሜ ውስጥ ያያል፡፡ ከራሱ የማንነት ምስል በላይ የሚያስቅ ነገር ምን አለ?
ማልቀስ ለፈለገውም ተመሳሳይ ነው፤ ከራስ ምስል በላይ የሚያስለቅስ ነገር ምን ይኖራል? … ግን ያጣውን ነገር ራሱ እንዳያገኝ፣ እኔ በእሱ እና የራሱ ምስል ነፀብራቅ መሀከል ቆሜ አስተረጉምለታለሁ። የራሱ ምስል በእኔ አማካኝነት ሲተረጐም ከማናደድ እስከ ማሳቅ፣ ከማሳቀቅ እስከ ማራቀቅ … ከተስፋ መቁረጥ እስከ ተስፋ ማግኘት ሊለዋወጥ ይችላል። አስማቴም ይኸው ነው፡፡ የጥበብ አስማት ሚስጢር።
ባለ ፍላጐቱ በራሱ አይን ነፀብራቁን ቢመለከት የሚያየው ፍላጐቱን እንጂ መድረሻውን አያይም። ራሱን በራሱ አይን ሲመለከት ጉድለት እንጂ ሙሉነት አይታየውም፡፡ ሁሉም ሰው ለራሱ እይታ ጉድለት ነው፡፡ እንደአጋጣሚ ሙሉ ቢሆን እንኳን ጉድለት ነው ለራሱ አይን የሚታየው፡፡ ስለዚህ አስማተኛ ያስፈልገዋል፡፡ ጉድለቱን ሞልቶ የሚነግረው። ሙሉነቱን ይዤ የምመጣው ከሌላ ቦታ አይደለም፡፡ ከራሱ ኪስ አውጥቼ ነው ወደ ፍላጐቱ የሚያደርሰውን ክፍያ የምሰጠው፡፡ ግን አስማት እንደመሆኑ፣ የሞላሁለትን ፍላጐቱን ይዞ ከትያትር ቤቱ ወጥቶ የወል ቤቱ ሲደርስ፣ ከአስማቱ በፊት ወደነበረው ማንነቱ ይመለስና ጐዶሎ ይሆናል፡፡
ሳንድሬላ በአስማተኛዋ አያቷ (አክስቷ) አማካኝነት ከአመዳም ገረድነት ወደ እፁብ ድንቅ ልዕልትነት ተቀየረች፡፡ አያቷ (አክስቷ) የከወነችው አስማት እኔ ያወራሁላችሁን ነው፡፡ ሳንድሬላን የቀየረቻት… ስለ ራሷ ያላትን አመለካከት በመቀየር ነው፡፡ ገረዲቱ በራሷ ፊት ስትቆም ይታያት የነበረውን ምስል ወደ ልዕልት ምስል ቀየረችው፡፡ ሳንድሬላ ውስጥ ቀድሞውኑ ልዕልት የመሆን ፍላጐት ወይንም ምኞት ባይኖር ኖሮ፣ በአስማተኛዋ አያቷ ሀይል ሆነ በጠንቋይ ድግምት ልትፈጠር፣ ልትለወጥ አትችልም ነበር፡፡ ፍላጐቷን እና መፍትሄዋን ከእራሷ ውስጥ አውጥታ አለበሰቻት፡፡ ከተቀዳደደ ልብሷ ውስጥ በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስ በአስማት አማካኝነት አለበሰቻት፡፡ ከራስ ምስሏ ጋር የተቆራኙትን አይጦች፣ በነጫጭ ፈረሶች ተካችላት፡፡ ዱባውን ደግሞ ወደ ሰረገላ፡፡
በአስማተኛ አያቷ የተለወጡ ማንነቷን ይዛ ልዑላኖቹ ጋር ተቀላቀለች፡፡ ህልሟን በጥበብ አስማት እውን አድርጋ ልዑል አፈቀረች፡፡ ስድስት ሰአት ከሌሊቱ ሲሆን … አስማቱ ወደ ቀድሞው ተፈጥሮው ተቀየረ፡፡ አይጥም አይጥ፣ ዱባውም ዱባ … ሳንድሬላም ተመልሶ ተራ አመዳም ገረድ ሆነች፡፡ አስማት እና ተአምር የሚለያዩት አንዱ ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ሌላኛው አስማት ሆኖ ይቀራል፡፡
ጥበብ የራስን ምስል ከጉድለት ወደ ሙሉነት የምትቀይር መስታወት ናት፡፡ በመስታወቷ የሚታየውን ምስል ወደ ታዳሚው ፍላጐት የሚቀይረው ሰው ጥበበኛ ይባላል፡፡ ራስን በራስ የሚቀይር ልዋጭ እንደማለት ነው፡፡ ራስን በራስ አማካኝነት የሚቀይረው ባለሞያ ጥበበኛ ተብሎ ሲጠራ መስማት የተለመደ ቢሆንም፣ ዋናው ስሙ ግን አስማተኛ ነው፡፡
የጥበብ ታዳሚው ራሱን ይዞ ወደ ትርዒቱ ስፍራ ይመጣል፡፡ በፍላጐት ተሞልቶ፡፡ የትርዒቱ ስፍራ የስዕል ሸራ፣ የመጽሐፍ ገፆች ወይንም የትያትር መድረክ ሊሆን ይችላል፡፡ ከራሱ ውስጥ ስሜቶቹን እንደ ክራር እየቃኘ … ፍላጐቱን፣ ምኞቱን ከጉድለት አውጥቶ ሙሉ ያደርገዋል - ባለ ሞያው ከተራ ቃላቶች ውስጥ ለእያንዳንዱ ታዳሚው የሚሆን መፍትሄ ያገኛል፡፡
ማልቀስ ለሚፈልገው ለቅሶ … መሳቅ ለሚፈልገው ሳቅ፡፡ የሚስቅ እና የሚያለቅሰው ታዳሚው ራሱ ቢሆንም …ሳቁና ለቅሶው ግን በራሱ ላይ ነው፡፡ በራሱ አማካኝነት ነው፡፡ በትክክል የሚገጣጥመው ጥበበኛ ካገኘ… ማንኛውም ሰው በውስጡ ሙሉነት አለ፡፡ ልዕልቷ ሳንድሬላን ትሆናለች፤ በአስማተኛው አማካኝነት፡፡ ሳንድሬላም ልዕልቷን፡፡
ግን አሁን አሁን፤ አስማተኛ የመሆን ሳይሆን አስማተኛን የማጋለጥ ፍላጐት እያደረብኝ ነው፡፡ የቆዩ የአስማት ሚስጢሮች ካልተጋለጡ አዳዲሶቹ አይፈጠሩም፡፡ ጠንከር ያሉ ወይንም ፍቻቸው ቶሎ የማይደረስበት መንገዶችን ለመፍጠር ቀላሎቹ የአስማት ሚስጢሮች “tricks” መጋለጥ አለባቸው። እውነተኛ አስማተኛ የሚለየው … ከፍላጐት ወደ ግኝቱ በሰው ስሜት መሰላል አማካኝነት ሲወጣጣ … የተወጣጣበትን መሰላል በመደበቁ አይደለም። መንገዱን እየገለፀም… ማንም መንገዱን ተከትሎ እሱ የከወነውን አስማት መስራት ሲያቅተው ነው፡፡ ሚስጢርን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን መግለፅም አዳዲስ አስማቶች እንዲፈጠሩ በይበልጥ ያግዛል፡፡
ሚስጢሩ ቢገለፅ እንኳን ማንም ማከናወን የሚችለውን አስማት እየሰሩ እውነተኛ ጥበበኛ መሆን አይቻልም፡፡ የወል የአስማት ትርዒት፣ ይትባህል እንጂ ጥበብ አይሆንም፡፡ ሚስጢሩ ቢገለጥም ማከናወን ከባድ የሆነ አስማት ሳንድሬላን አንዴ ልዕልት ካደረጋት በኋላ፣ ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ላይ ወደ አመዳም ገረድነት (ብቃት ባለው አስማተኛ በተሰራ ጥበብ ላይ) አትለወጥም፡፡ ልዕልት እንደሆነች ትቀራለች፡፡
መለወጧ ባይቀር እንኳን፤ በሰአታት ውስጥ ሳይሆን ብዙ ዘመናት ይፈጅባታል፡፡ ለምሳሌ ዶስትዮቪስኪ እንደዛ አይነት አስማተኛ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እኔ ደግሞ ኧ. ሄሚንግዌይ አስማቱን የሚሰራበት ሚስጢር ቢገለፅ እንኳን ማንም ሊያከናውነው የማይችል የአስማት አይነት ነው የሚሰራው ባይ ነኝ፡፡
የአስማታቸው ሚስጢር ሲጋለጥ፤ ሁሉም በየቤቱ ደብዳቤ ለመፃፍ የሚጫጭረውን ያህል ጥበብ ፈጥረው የተገኙም አሉ፡፡ ቀላሉን የአስማት ሚስጢር በማጋለጥ… ከባባዶቹ እንዲፈጠሩ መንገድ ማመቻቸት ነው… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመርኩት ስራ፡፡ እናም እላለሁ፤ አስማተኛ አስማቱን በከረጢት ይዞ አይዞርም፡፡ አስማቱን የሚፈጥረው ከታዳሚዎቹ ፍላጐት እና ነፀብራቅ በመነሳት ነው፡፡ ታዳሚዎቹ ሀዘን፣ ደስታ፣ ተስፋ እና አንዳች ፍላጐት በውስጣቸው ቀብረው ወደ አስማተኛው ባይመጡ አስማተኛው ብቻውን የሚከውነው አንዳች ነገር ባልኖረው ነበር፡፡ If you don’t bring it here you won’t find it here! ይላችኋል፤ ጥበበኛው ባዶ ከረጢቱን እያሳየ፡፡
የአስማተኛው ጥሬ እቃዎች እናንተ ናችሁ፡፡ ጥሬ እቃዎቹን ከተራ ወደ እፁብ ድንቅነት የሚቀይርበት መንገድ ነው ሚስጥሩ፡፡ ጥበበኛ ሚስጢረኛ ነው። ምርጥ ሚስጢረኛ ግን ሚስጢሩን የሚደብቅ ሳይሆን ለመግለፅ የሚሞክር ነው፡፡ ሚስጢረኛ የሆነበትን ሚስጢር ለመፍታት በሚያደርገው ሙከራ እና ሂደት …እናንተን ከፍላጐታችሁ ወደ ግባችሁ ያደርሳችኋል፡፡ ሚስጢሩን ለመፍታት በሚሞክርበት ጊዜ ነው አስማቱ የሚፈጠረው፡፡ ከከባድ ሚስጥሮች ፍቺ የሚገኝ አስማት ነው ልዕለ - ጥበብ፡፡ የልዕለ ጠቢብም አሻራ:- ሚስጥርን መግለፅ እንጂ መደበቅ አይደለም፡፡ በተገለፀ ቁጥር የሚደበቅ ሚስጥርን ለመፍታት ጠንካራ አስማተኞች ያስፈልጉናል፡፡ እውነተኛ አስማተኞች፡፡ ካርታን ደርድሮ “ቀዩዋን ያየ” እያሉ የሚያጭበረብሩት…እውነተኛም፣ ሚስጥረኛም አስተማኛም አይደሉም። ምናልባት “ወሮበላ” ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግልፁን ሚስጢር የሚያደርግ እና ሚስጢሩን ለመግለፅ በሚሞክር መሀል የሰማይ እና የምድር ያህል ርቀት አለ፡፡ አንደኛው ወሮ በላ ይባላል፡፡ ሌላኛው አስማተኛ ነው፡፡ አስማተኝነትን ከሌላ አስማተኛ በመማር ሚስጢሮችን እና አፈታታቸውን አጥንቶ፣ “የጥበቡ ጥሪ አለኝ” የሚል ሊጀምር ይችላል፡፡
አዲስ አስማት መፍጠር ካልቻለ … ወይንም ካልሞከረ ግን በስተመጨረሻ የሚገባው ወደ ማጭበርበሩ ነው፡፡ ቀላልን ሚስጢር ከባድ አስመስሎ ወደመደበቁ፡፡


22ሚ. ብር የሚፈጅ “የብዕር አምባ” ግንባታ ይጀመራል
አዲሱ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ መላው የአገሪቱ ደራሲያንና የድርሰት ወዳጆች ከስነ ጽሑፍ እድገት ጐን እንዲቆሙ ጠየቀ፡፡
በቅርቡ የተመረጠው የደራስያን ማህበር አመራር፤ ትላንት በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ ማህበሩ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያካበተውን ልምድና ያከናወናቸውን ተግባራት መሠረት በማድረግ፣ ከዘመን ዘመን ማህበሩን ሲፈታተኑ የቆዩ ማነቆዎችንና ተግዳሮቶችን በማስወገድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ አዳዲስ የአስተሳሰብና የአሠራር አቅጣጫዎችን ቀይሶ፣ አባላቱን ከዳር እስከዳር በማንቀሳቀስ ማህበሩን ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ ለማድረስ ቆርጦ መነሣቱንም ገልጿል፡፡
የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ቀዳሚ የትኩረት እንቅስቃሴ አቅጣጫዎቼ ናቸው በማለት ከዘረዘራቸው መካከል፤ ከ22 ሚ. ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው “የብዕር አምባ” ግንባታ እንዲጀመር ማድረግ፣ የማህበሩን ገቢ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማስፋትና የማህበሩን የህትመት ውጤቶች በብዛትም በጥራትም መጨመር የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በየክልሎቹ ያሉትን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሠራና ብዕርተኞች የሚዘከሩባቸውን የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያካሂድ የገለፀው ማህበሩ፤ የመጽሐፍት ማከፋፈያና መሸጫ መደብሮች፣ በአዲስ አበባ ማዕከላዊ ቦታዎች ላይ ለመክፈት እጥራለሁ ብሏል፡፡ የማህበሩን ጥረት ለማገዝም የድርሰት ወዳጆች ከጐኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡