Administrator

Administrator

የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ለማገዝና ለዜጎች ይበልጥ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ፈጣን ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል፣ በዲጂታል የታገዘ የዳኝነት አገልግሎትን ተግባራዊ ያደርጋል የተባለ  ስምምነት፣ በኢትዮ ቴሌኮም እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል ተፈጸመ፡፡

በዛሬው ዕለት በተፈጸመው ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አስተማማኝና ደረጃውን የጠበቀ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት:- አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ የመጠባበቂያ ኔትወርክና የኔትወርክ ደህንነት ያለው ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል፣ የኔትዎርክ ኦፕሬሽን መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ የዋይድ ኤሪያና ሎካል ኤሪያ ኔትወርክ ግንባታ እንዲሁም የሶፍትዌር ደረጃ ዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ማስተዳደሪያ (SD-WAN) ዓለም አቀፍ ደረጃውንና ጥራቱን ጠብቆ በመገንባት ያስረክባል፡፡

ይህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢ-ኮርት ሲስተም አማካኝነት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የዳኝነት አገልግሎቶች ለተጠቃሚዎች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበሩትን የቴሌኮም አገልግሎቶች የትብብር ሥራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ተፈጻሚ ለማድረግ በተለይም በሁለቱ ተቋማት መካከል የአቅም ግንባታ፣ ሥልጠና፣ የእዉቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲከናወን  ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

የመሠረተ ልማቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ ባለድርሻ አካላት በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ጊዜና ገንዘብን ለመቆጠብ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ግልጸኝነትን  ለማስፈን እንዲሁም ዜጎች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

Saturday, 01 April 2023 20:45

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

 ለህሊናቸው “ምን ሥንሰራ ውለን መጣን” ብለው ይነግሩት ይሆን ?
                        ቴዎድርስ ተ/አረጋይ

       እያንዳንዳችን የብቻችን ሰዓት አለን። ማታ ቤት ገብተን በጀርባችን ተንጋለን ስለ ውሏችን፣ ድካማችን፣ ደስታችን፣ ሀዘናችን ለአፍታም ቢሆን የምናስብበት ቅጽበት አለን። በዚያች ቅጽበት መንፈሳዊነት ካለን ከአምላካችን፣ ኢ - አማኒም ከሆንን ከህሊናችን ጋር እንገናኛለን። ከራሳችን ጋር ጥያቄና መልስ እናደርጋለን። እነዚህ የስራ ጠባያቸው ቤት ማፍረስ የሆኑ ወንድሞቻችን፣ ማታ ደክሟቸው ቤታቸው ገብተው አረፍ ሲሉ ምን ያስቡ ይሆን? ለሚስታቸው ፣ለልጃቸው ወይም ለህሊናቸው “ምን ስንሰራ ውለን መጣን” ይሉ ይሆን? የንጹሀንን ቤት ስናፈርስ? ቤታቸውን የሚያፈርሱባቸውና ንብረታቸውን የሚያወድሙባቸውን ዜጎች ዓይን ሲያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን ? የሰውን ተስፋ የመስበርን ስሜት እንዴት ይቋቋሙት ይሆን ? ለአምላክም ለሰውም ይቅር፣ ለህሊናቸው ምን ብለው ነው የሚነግሩት? “ሥራ ነው” ነው የሚሉት? የሰዎችን ሀዘን ከማየት በላይ፣ የሀዘናቸው ምንጭ መሆን ምን ያህል መራር እጣ ፈንታ ነው ?


 በጥበብ አፍቃሪያኑና በጥበበኛው ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው ’The Big Art Sale’ ዓውደ ርዕይ በመጪው ሳምንት ለ18ኛ ጊዜ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ።
በዘንድሮው ታላቅ የሥዕል አውደ ርዕይ ላይ ከ5ሺ በላይ ጎብኚዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል ተብሏል።
 ’The Big Art Sale’ ተወዳጅ ከሆኑ የከተማችን የሥነጥበብ  ዝግጅቶች አንዱ መሆኑን የጠቀሰው አዘጋጁ “ዋትስ አውት አዲስ”፤ከሒልተን ሆቴል ጋር በመተባበር በዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ የጥበብ ዓውደ ርዕይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የዘንድሮው አውደ ርዕይ እንደተለመደው በሒልተን አዲስ በመጪው ቅዳሜ መጋቢት 30 እና እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚካሄድ ያስታወቀው አዘጋጁ፤በአውደ ርዕዩ ከ100 በላይ ሰዓሊያንና ቀራፂያን አዳዲስ ሥራዎቻቸውን ለጎብኚዎችና ለገዢዎች ያቀርባሉ ብሏል፡፡
ከጥበብ ስራዎች በተጨማሪ ጥበብ አፍቃሪያኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚዝናኑባቸው የመጠጥና የምግብ ኮርነሮች ሲኖሩ፤ለልጆች ልዩ የመጫወቻ ሥፍራም ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡ ይህ ልዩ ዓውደ ርዕይ ጠቢብያኑ ሥራቸውን እንዲሸጡ እድል የሚሰጣቸው ሲሆን ገቢውም  ለበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚውል ተጠቁሟል።  


 አንድ ጠና ያሉ አዛውንት የስጋ አምሮታቸውን ሊወጡ አንድ ስጋ ቤት ገብዋል። መቼም ስጋ መጀመሪያ በአይን ነውና የሚበላው፣ማተር ማተር አደረጉት የተሰቀለውን ስጋ።ሽንጡ ጮማ ነው። ከመቶ ሻማ አምፖል ስር ይቅለጠለጣል። ዳቢቱ ይገላምጣል። ሻኛው ያለተልታል። አዛውንቱ፤”አንድ ኪሎ ቆንጆ አድርገህ ለጥብስ!” አሉና ወደ ጓዳ ገቡ። ስጋ ቤቱን ያውቁታል። ስጋ ቤቱም ያውቃቸዋል። ባለፈው ሰሞን አሟቸው ስለነበር፣ ዛሬ ጥሬ ስጋ አልፈለጉም።
 “ኪሎ ጥብስ አዝዣለሁ” አሉ ገና ቦዩ “ምን ልታዘዝ” ሊል ሲመጣ። “ደረቅ ይበል ታዲያ!” አሉት፤ ቦዩ ፊቱን አዙሮ ሲሄድ። የሰማቸው አይመስልም።
ጥብሱ ቀረበላቸው። ሽንኩርትና ቃሪያ ሰንጠቅ ሰንጠቅ ተደርጎ ተጨምሮበታል። መልኩም ያምራል። ጭሱ ቁና ቁና ይተነፍሳል። በዘመድ የተጠበሰ ሳይሆን አይቀርም። ፈገግ አሉለት አዛውንቱ - ለጥብሱ። “ዌል ካም” እንደማለት።
“ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ” አሉና እጅጊያቸውን ሰብሰብ አደረጉ። ሊወርዱበት ነው እንግዲህ -የ78 አመቱ አዛውንት። በተለይ ጎድን ሲበሉ ነጭ አጥንቱ ከጥግ ጥግ  እስከሚታይ፣ እንደ እርሳስ ነው በጥርሳቸው የሚቀርፁት!
ቀና ብለው ሲመለከቱ ወጣት ወጣት ልጆች፣ ያዘዙት እስኪመጣላቸው እየጠበቁ ከፊት ለፊቱ ጠረጴዛ አግዳሚ ላይ ተኮልኩለዋል።
“ጎበዝ ኑ እንብላ እንጂ ታድያ” አሉ አዛውንቱ። ወጣቶቹ ጥቂት አመነቱ።
“ምን ሆናችኋል፤ ብቻዬን ይሄን ሁሉ ምን ላደርገው ነው? ኑ እንጂ ጎበዝ ነውር’ኮ ነው!”
ወጣቶቹ መጥተው ሽማግሌውን ከበቡና፣ ጥብሱን በነዚያ በመረመንጅ የጎረምሳ እጆቻቸው ይሻሙ ገቡ፡፡ በአንድ አፍታ ትሪዋ ወለልዋ ታየ፡፡ “Made in China” የሚለው ተነበበ፡፡ አይ ጉርምስና ደጉ፤ በሚል አስተያየት ልጆቹን አስተዋሉ፡፡ ወጣቶቹ ወደ ቦታቸው ተመለሱ፡፡ ሽማግሌውም ትንሿን ጉደር ወይን ጠጅ አዝዘው መጠጣት ጀመሩ፡፡
ጥቂት ቆይቶ ወጣቶቹ ያዘዙት ስጋ በትሪ ሙሉ መጣ፡፡ ወጣቶቹ ቀናም ብለው ወደ ሽማግሌው ሳያዩ፣ ያንን ትሪ ሙሉ ስጋ ተያያዙት፡፡ አዛውንቱም የወጣቶቹ ነገረ-ሥራ ገርሟቸው በትዝብት እያስተዋሉ ወይናቸውን ይጎነጫሉ፡፡
ወጣቶቹ ስጋውን አገባደው፣ ጉደር አዘዙና ዘና ብለው ተቀመጡ፡፡
ይሄኔ ሽማግሌው፤”ልጆች፣ ጎጂ ባህል ምንድነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
አንደኛው፤ “ግርዛት ነዋ!” አለ::
‹‹አይደለም›› አሉ አዛውንቱ፡፡
ሁለተኛው፤ ‹‹እንጥል ማስቆረጥ›› አለ፡፡
‹‹አይደለም›› አሉ፤ አዛውንቱ አሁንም፡፡
ሦስተኛው፤ ‹‹ጉሮሮ መባጠጥ…በወር አበባ ጊዜ  መገለል … እ …በአንዳንድ ጎሳ የሴቶችን አካል…››
‹‹ኧረ በጭራሽ!›› አሉ አዛውንቱ እየሳቁ፡፡
አንደኛው፤ ‹‹ካለ እድሜ ከማግባት የሚከሰት የማህፀን ብልሽት ፌስቱላ!››
‹‹መልሱ አጠገብም አልደረሳችሁ›› አሉ ሽማግሌው።
ሁለተኛው፤ ‹‹እንግዲህ በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን የሰማነውን ሁሉ ነገርንዎ፡፡ አሁን የእርሶን ንገሩን››
አዛውንቱም፤ ‹‹ልጆች፤ጎጂ ባህል ምን መሰላቹ?...‹‹ኑ እንብላ›› ማለት፡፡
XXX
ሀገራችን በጋራ የሚያስቡ ልጆች ያስፈልጓታል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ችግሮቻችን ብዛትና ስፋት በጥቂት ሰዎች፣ ድርጅቶች እና ፓርቲዎች አቅም ብቻ እንወጣው ከምንልበት ደረጃ ካለፈ ውሎ አድራል፡፡ በተለይ ዛሬ ይህ እውነታ ተፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እርዳ-ተራዳ የሚጠይቅም ሆኗል፡፡ አንድ የፖለቲካ ውጥረት ሲፈጠር፣ አንድ የኢኮኖሚ ጫና ሲመጣ ወይም አንድ ማህበራዊ ቀውስ ሲከሰት ብቻ እንተባበር፣ እንተጋገዝ ብለን ብንጮህ፣ ከእንግዲህ የቱንም ወንዝ የሚያሻግር መላ አናገኝም፡፡ ችግሮች ተባብሰው መጨረሻው ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ህዝብ እንዲነጋገርባቸው እድል መገኘት አለበት፡፡ ብሶቶች ከታመቁ የፈነዱ እለት የሚፈጥሩት ጎርፍ፣ በዋዛ የሚገደብ አለመሆኑን ብዙ ማህበራዊ ትእይንቶች አረጋግጠውልናል፡፡ ብሶቶች መተንፈሻ፣ ጥያቄዎች መልስ ይፈልጋሉ፡፡ ሁኔታዎች አንዴ ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ የፖለቲካ መተረማመስ፣ የኢኮኖሚ አደጋ እና የማህበራዊ ውጥንቅጥ መፍጠራቸው አይቀርምና በጊዜ መጠንቀቅ ያሻል፡፡
‹‹ዛር ልመና ሳይያዙ ገና
ከተያዙ ብዙ ነው መዘዙ›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በየዘመኑ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና አመፆች ተከስተዋል፡፡ ወደ ጦርነትም አድገዋል፡፡ የሁሉ መንስኤ፣ ብሶት (Discontent) ነው፡፡ በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ ያለ ብሶት፤በሥርአቱ ላይ ያለ ብሶት፣ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለ ብሶት፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ያለ ብሶት፣ በዜጎች ግድያና መፈናቀል ያለ ብሶት፣ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ ዙሪያ ያለ ብሶት፣ ከአቅም በላይ በሆነ የኑሮ ውድነት ላይ ያለ ብሶትና ምሬት ወዘተ በተጠራቀመ ጊዜ ለማህበራዊ እንቅስቃሴ ፍንዳታ ምቹ ማኮብኮቢያ ይሆናል፡፡ ኢንቨስተሮች ይሸሻሉ፤ ሌላውንምያሸሻሉ፡፡ ሥራ አጥነት ያጥጣል፡፡ ማህበራዊ ቀውስ ግራ ቀኙን ያቃውሳል፡፡ ወሮ በላው በረንዳ ያጣብባል፡፡ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራል! ዛሬ አገራችን የደረሰችበት ሁሉን- ዳሰስ ችግር የባለሙያዎችን፣ የምሁራኑን፣ የፖለቲካ አዋቂዎችን፣ የዳያስፖራውን፣ የልዩ ልዩ ማህበራትን እና ድርጅቶችን ሁሉ ልባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ለማሳካት ደግሞ ሆደ- ሰፊ የሆነ የፖለቲካ አመለካከትን ይጠይቃል፡፡
 ለመታረም ምክርን የሚያዳምጥ፣ ለግለ ሂስ ቀና መንፈስና ፅናት ያለው፣ ከኔ በላይ አዋቂ ለአፈር የማይል፣ ጉራ ሳይሆን ትህትና፣ ድንፋታ ሳይሆን የጥሞና ውይይትን፣ መቅጠፍን ሳይሆን በሀቅ ማሳመንን የሚያምን ሃላፊ ያስፈልጋል፡፡ ዊንስተን ቸርችል እንዳሉት፤ ‹‹ድል በተገኘ ሰአት ደግ መሆን መቻል ትልቅነት ነው፡፡ በውድቀትም ሰዓት ሽንፈትን መቀበል ብልህነት ነው››፡፡ ከጉልበት ይልቅ ብልሃትን መጠቀም ያዋቂ መሪዎች መገመቻ ነው፡፡ ትላንት የጀመርነው መንገድ የግድ መቀጠል አለበት ብሎ መታበይ አያዋጣም፡፡ ይልቁንም ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ የተሳትፎ መድረክ ለመፍጠር መትጋት  ያስፈልጋል፡፡
    ሆደ-ሰፊ የፖለቲካ አመለካከት ያለው፤ ከትምህክተኝነትም ሆነ ከጠባብነት አደጋ የመዳን እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ይህ አመለካከት ያለው የሥልጣንን ገበታ ብቻዬን ልያዘው አይልም፡፡ መቻቻልን ከጠረጴዛው የማይለየው አጀንዳ ያደርጋል፡፡ ልዩነትን በማጥበብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወደ ገበታው ይጋብዛል፡፡ ‹‹ኑ እንብላ›› ለማለት ይችላል፡፡ ለለውጥም በሩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡ አለማወቅን እንደ ውርደት ሳይቆጥር የማያውቀውን ይማራል፡፡ በዙሪያው በአጨብጫቢነት የተኮለኮሉ ግለሰቦችን በጥንቃቄ ያፀዳል፡፡ ምላሳቸው እረጃጅም የሆኑ መጣፍ ገላጮችን እና ቲኦሪ አንጋቾችን የፕሮፓጋንዳ አፎቶችን፣ የልሳን እና የብእር አንጋቾችን፣ በክፉ ሰአት ሁሉ ይመዝናል፡፡ በትላንት በሬ አያርስምና ለአዳዲስ የፖለቲካ ፈለግና ራእይ በሳል የሀገሪቱን ሰዎች ከእንቅስቃሴ መስክ አያርቅም፡፡ ዜጋ ሁሉ በሀገሩ በሚመለከተው ጉዳይ ‹‹ለምን?››  ብሎ የመጠየቅ መብት እንዳለው አበክሮ ይረዳል፡፡ ስለ ጎረቤት አገሮች ጉዳይ ከአገሬው ጋር ይመክራል፤ ይዘክራል፡፡ ኢንፎርሜሽን ይሰጣል፡፡
ፖለቲካን እንደ ጊዜያዊ ስራ (Part time job) የሚይዙ፣ ሁሌ ቤቴ የሆኑ፣ ለህዝቡ እንደ ጊዜያዊ ወዳጅ (part time lover) የሆኑ እና ‹‹ቱሪስት እና ፒስኮር የማይለዩ›› ካድሬዎችን እንዲሁም እምቡጣዎችን አበጥሮ ያወጣል፡፡ ጭፍን አምልኮ-ሰብ (cult) ለመፍጠር የሚሹትን እንደሚያንገዋልል ሁሉ ከመሀይም ምእመናንም በጊዜ ይገላገላል፡፡ ኩርፊያ ሳይሆን ውይይትን ያደንቃል፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ግን በሩን ለትችት ክፍት ያደርጋል፡፡ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት የሚችልበትን መንገድ ይጠርጋል፡፡ የአንገት በላይ ፍቅር አንገት ሲቆረጥ ወድቆ ይቀራል ይሏልና፣ ለህዝብ ያለው ፍቅር ልባዊ መሆን ይኖርበታል፡፡
እነዚህ ሁሉ ዲስፕሊኖችና ባህሪያት ከእውነተኛ ሰብአዊ መብት፣ ከእውነተኛ ነጻነት እና ዲሞክራሲ አብራክ የሚወለዱ ናቸውና ተዓማኒ እንጂ የይስሙላ እንዳይሆኑ ብርቱ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡
 ‹‹ዲሞክራሲ፣ ሰላም፣ ሰብአዊ መብት፣ እኩልነት፣ መቻቻል…›› ተደጋግሞ ቢጮሁ፣ የተግባርን ፀጋ ካልተጎናፀፉ አፋዊ አተታ ብቻ ናቸው፡፡ ሺ ጊዜ ቢንጡት የቁልቋል ወተት ቅቤ አይወጣውም እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ተግባር፣ ተግባር አሁንም ተግባር፤ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ኑ እንብላ›› ጎጂ ባህል የማይሆነው፣ ያኔና ያኔ ብቻ ነው፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት ዓለማቀፍ ተቋማት በቂ ምላሽ አልሰጡም ሲል ወቅሷል፡፡
       ባለፈው ዓመት በዓመት የጦር ወንጀል ከተፈፀመባቸው 20 አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት ብሏል፡፡
               አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአለም አገራትን የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚፈተሽበትን ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ድርጅቱ በዚሁ ሪፖርቱ ባለፈው የፈረንጅ ዓመት በዓለማችን ከተፈፀሙ ግጭቶች እጅግ አስከፊውና ገዳዩ የተፈፀመው በዩክሬን ሳይሆን በኢትዮጵያ ነው ብሏል። ይህ በአገሪቱ የተፈፀመው ዘግናኝ በደል የተፈፀመውም ከአለም የትኩረት  አቅጣጫ ውጪ ነው ሲልም አምነሲት ጠቁሟል። አመልክቷል።
ከትናንት በስቲያ ይፋ በተደረገው በዚሁ የድርጅቱ አመታዊ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ያለፈው የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎች የተፈፀሙበት ዝርፊያዎች፣ ፆታዊ ጥቃቶችና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀሙበት አመት ነበር። ድርጅቱ በተለይ በኢትዮጵያ ተፈፀሙ ያላቸውን የግፍ ግድያዎች ህገ-ወጥ እስሮችና መልከ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የዘረዘረ ሲሆን እነዚህ የጦር ወንጀሎችና የግፋ ግድያዎች በአለማችን እጅግ ከባድ ተብለው ከሚጠቀሱት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትም የከፋ ነው ብሏል። ባለፈው የፈረንጆች አመት እጅግ ገዳዩ ግጭት የተፈፀመው ዩክሬን ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብሏል ሪፖርቱ። በዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት አለማቀፍ ተቋማት ሰጡት ምላሽ በቂ አለመሆኑንም በሪፖርቱ አመልክቷል።
አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ይፋ ባደረገውና ባለፈው የአውሮፓውያን አመት በአለም ላይ በተከሰቱ ግጭቶችና ተቃውሞዎች ላይ ትኩረቱን ባደረገው በዚሁ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በተካሄደው ጦርነትና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ምክንያት በርካታ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል ብሏል።
ድርጅቱ ጥናት ካካሄደባቸው 156 አገራት መካከል በሃያዎቹ የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን ያመለከተው የድርጅቱ ሪፖርት በ79 አገራት ደግሞ ሃሳብን በነፃነት በሚገልፁ መብት ተሟጋቾችና አንቂዎች ላይ እስር ድብደባና በደል ተፈፅሞባቸዋል ብሏል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ አገራችን ክፍል የተካሄደውን ጦርነት በአለማችን ከተካሄዱ አውዳሚ ጦርነቶች መካከል አንዱ ነው ያለው የድርጅቱ አመታዊ ሪፖርት በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል። ጦርነቱ በተካሄደባቸው በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልል ውስጥ የሚኖሩ ከ8.35 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብሏል።
አለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ለግጭቱ የሰጡት ምላሽ በቂ አይደለም ሲልም ወቅሷል።አለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅት ይፋ ባደረገው በዚሁ አመታዊ የአለም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በከፍተኛ ሁኔታ መሸርሸሩንና ባለሞያዎች ታስረው እንደሚገኙ አመልክቷል።


በጥበብ አፍቃሪያኑና በጥበበኛው ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው ’The Big Art Sale’ ዓውደ ርዕይ በመጪው ሳምንት ለ18ኛ ጊዜ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ።
በዘንድሮው ታላቅ የሥዕል አውደ ርዕይ ላይ ከ5ሺ በላይ ጎብኚዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል ተብሏል።
 ’The Big Art Sale’ ተወዳጅ ከሆኑ የከተማችን የሥነጥበብ  ዝግጅቶች አንዱ መሆኑን የጠቀሰው አዘጋጁ "ዋትስ አውት አዲስ"፤ከሒልተን ሆቴል ጋር በመተባበር በዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ የጥበብ ዓውደ ርዕይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የዘንድሮው አውደ ርዕይ እንደተለመደው በሒልተን አዲስ በመጪው ቅዳሜ መጋቢት 30 እና እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚካሄድ ያስታወቀው አዘጋጁ፤በአውደ ርዕዩ ከ100 በላይ ሰዓሊያንና ቀራፂያን አዳዲስ ሥራዎቻቸውን ለጎብኚዎችና ለገዢዎች ያቀርባሉ ብሏል፡፡
ከጥበብ ስራዎች በተጨማሪ ጥበብ አፍቃሪያኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚዝናኑባቸው የመጠጥና የምግብ ኮርነሮች ሲኖሩ፤ለልጆች ልዩ የመጫወቻ ሥፍራም ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡
 ይህ ልዩ ዓውደ ርዕይ ጠቢብያኑ ሥራቸውን እንዲሸጡ እድል የሚሰጣቸው ሲሆን፤ ገቢውም  ለበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚውል ተጠቁሟል።

እማሆይ ጽጌ ማርያም በኢትዮጵያ ቀዳሚዋ የቫዮሊን እና ፒያኖ አቀናባሪ እንደነበሩ ይነገራል።
እማሆይ ፅጌማርያም ከአባታቸው ከአቶ ገብሩ ደስታ እና እናታቸው ወይዘሮ ካሣዬ የለምቱ በ1916 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ ነው የተወለዱት።
በልጅነታቸው ለትምህርት በሄዱባት ስዊዘርላንድ ፒያኖን በደንብ ተምረዋል።
ከትምህርት መልስም በ19 አመታቸው ነበር ወደ ወሎ ግሸን ማርያም ገዳም በመሄድ በ21 አመታቸው ምንኩስናን የተቀበሉት።
ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም የውብዳር ሲሆን በወጣትነታቸው ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ መጠሪያቸው ወደ እማሆይ ጽጌ ማርያም ተቀይሯል።
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ "ቅድስቲቷ ከተማ" ተብላ በምትጠራው ኢየሩሳሌም አድርገዋል።
አባታቸው ገብሩ ደስታ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩ ሲሆን በአፄ ሃይለ ሥላሴ ዘመንም የፓርላማ አፈ ጉባኤ በመሆን ማገልገላቸውን የቤተሰባቸው ታሪክ ያስረዳል።

ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
አንድ የጫማ ዕደሳ ሥራ ላይ የተሠማራ ጫማ ሰፊ፣ ገበያ አልመጣ ብሎት ይቸገራል፡፡ ስለዚህ ጫማ የማደስ ሥራውን ይተውና;፤.”.መድኃኒት አዋቂ ነኝ.. “ ብሎ የህክምና ሥራ ላይ ይሠማራል፡፡
“..ከማናቸውም በመርዝ ከሚመጡ በሽታዎች መከላከያ የሚሆኑ ልዩ  መድኃኒቶች በቅናሽ ዋጋ የሚሰጥ ምርጥ መድኃኒተኛ..” የሚል ጽሁፍ ይለጥፋል፡፡ (በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል ከእሱ ይሆን የመጣው?)
ሰው እንደ ጉድ ይጎርፍለት ጀመር፡፡ እሱም በየዓይነቱ ቅጠላ ቅጠል እያመጣ እየቀመመ፤
“..አንተ ይሄንን ከኑግ ጋር በማንኪያ ጠዋትና ማታ ውሰድ..” ይላል፡፡ ታማሚው ይከፍላል፡፡ አመስግኖ ይሄዳል፡፡
ሌላዋ:- ትመጣለች
“..አንቺ ይሄንን ከሱፍ ጋር አድርገሽ በየሶስት ቀን ውሰጂ.”. ይላታል፡፡ አመስግና ከፍላ ትሄዳለች፡፡
እንዲህ እያለ  ያ ጫማ ሰፊ፣ ዋና መድኃኒት አዋቂ ተብሎ ዝናው እየገነነ፣ እንደ ወጥ-ሠሪ “..እጁ አይለወጥም፣ እጁ መድኃኒት ነው፣ እሱ የዳበሰው ሰው ወዲያው ብድግ ነው!..” እየተባለ ጥሩ አድርጎ ራሱን ሸጠ፡፡ አንደበተ-ርቱዕ ስለሆነም አፉ ይጣፍጣል - ሰው ያለውን ሁሉ ይሰማዋል፡፡ ባንድ ጊዜ ዝና አገኘ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በጣም ታመመና፣ እቤት አልጋ ላይ ዋለ፡፡ የአገሩ ንጉሥም፤ ባለሟሎቹን  ጠርቶ፤
“..የዚህን መድኃኒተኛ ዕውነተኛ ችሎታ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ሂዱና ያንን እሱ የመርዝ መከላከያ እያለ የሚሰጠውን መድኃኒት ተቀብላችሁ ከመርዝ ጋር ቀላቅለን ልናጠጣህ ነው ብላችሁ ንገሩትና ውሃ ብቻ ጨምራችሁ ጠጣ በሉት፡፡ ከዚያ ምን እንደሚያደርግ መጥታችሁ ንገሩኝ..” አላቸው፡፡
ባለሟሎቹም በንጉሡ በታዘዙት መሠረት፣ ከመድኃኒቱ ጋር መርዝ ሊያጠጡት እንደመጡ ነገሩት፡፡
መድኃኒተኛው በጣም ደነገጠ፡፡ መርዝ ሊያጠጡት መሆኑን በማሰብም ክፉኛ ተጨነቀ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ሲል ዕውነቱን በመናገር ተናዘዘ፤
“..ጌቶቼ፤ እኔ ምንም ዓይነት የመድኃኒተኝነት ችሎታ የለኝም፡፡ የጫማ ዕደሳ ገበያዬ ሲቀዘቅዝብኝና የኑሮ መላው ሲጠፋብኝ በልቼ የማድርበት አንድ ዘዴ ለመፍጠር ተገደድኩ፡፡ መድኃኒተኛ ሆንኩ፡፡ ህዝቡ ተቀበለኝ፡፡ ቀጠልኩበት.. “ አለ፡፡
ባለሟሎቹ መድኃኒተኛው ያለውን ወስደው ለንጉሡ ተናገሩ፡፡ ንጉሡ አገሬውን ሰብስቦ፤
“..የአገሬው ሰዎች ሆይ! ከእናንተ በላይ ስህተት ላይ የወደቀ ማን አለ? ለዚህ ጫማ ሰፊ አንዳችሁም ጫማችሁን እንዲያድስ አልሰጣችሁም፡፡ የመርዝ ማርከሻ አድርግልን ብላችሁ ግን ነብሳችሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፡፡ ከእንግዲህ ግን ባለሙያ ለዩ፡፡ በስሜት እየተገፋችሁ በወረት አትነዱ..” ብሎ አጥብቆ አሳሰባቸው፡፡
 ***
አላዋቂ እጅ መውደቅ እርግማን ነው፡፡ ነብሴ በእጅህ ናት ብሎ የአላዋቂ ተገዢ መሆን የከፋ መርገምት ነው፡፡ አንዱ ስላደረገው ብቻ ሌላው የሚከተልበት፣ እንደ መንጋ ተከታትሎ ከሚነዱበት ሥርዓት (Herdism) ይሰውር፡፡ ቆም ብሎ የምሄድበት መንገድ ትክክል ነወይ? ከተለመደው መንገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አጥቼ ነወይ? አኪሜስ በእርግጥ መርዙን እያረከሰልኝ ነወይ? ጠንቋይ ለራሱ አያውቅ እንደሚባለው ቢሆንስ? ጫማ ሰፊው ሙያ ወይ ሥራውን ለውጦ አኪም ነኝ ያለው መደበኛ ሙያው አንሶት ነውን? ያገሬው ህዝብ ሙያውን ስላላወቀለት ነውን? ጫማ የሚያሳድስበት ገንዘብ ስላጣ ነውን? አሮጌ ማሳደስ በቃኝ ብሎ ነው?
ለመንገኝነት አስተሳሰብ ወይም ለወረተኝነት አካሄድ ወይም እንደ አዲስ ፕሮጀክት፣  ዕቅድ፣ መመሪያ፣ ሲወጣ እንደ ፋሽን መከተልና ሳይመረምሩ መቀበል፣ ከተለመደ ቆይቷል፡፡ ይህ የሚከሰተው ከአለማወቅ ወይም ግንዛቤ ከማጣት ሊሆን ይችላል፡፡                                 
“ጌታዬ  ያሉት ሁሉ ልክ ነው”  ከሚል የሎሌያዊነት አመለካከት (Servitude) ሊሆን ይችላል፡፡ ጎረቤቴ ካደረገው ልክ ቢሆን ነው ብሎ ከማሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ ሆነ ብሎ ስህተትም ቢሆን ልከተለውና ገደል ሲገባ ልየው ከሚል እኩይ ሀሳብም ሊሆን ይችላል፡፡
እነዚህ አስተሳሰቦች በአገርም፣ በአህጉርም፣ በሉልም ደረጃ የሚሠሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ግን በዚህ በመጠቀም ዝናን የሚያካብቱ፣ ከአገሬው በላይ ያሉ ንጉሦች፣ መሪዎች፣ ኃላፊዎችና አለቆች ይኖራሉ፡፡ የአገሬው መራብ፣ መቸገር፣ በኑሮ መማቀቅ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ዝና ወዳዴ የሚባሉ ሰዎች ህልማቸው ሁሉ በዝና የተሞላ ነው፡፡ ሮማዊውን ሴናተር ሲሴሮን ጠቅሶ ሞንታኝ የተባለ ፀሐፊ እንደጻፈ፤
“..ዝናን የሚቃወሙ ሰዎች እንኳን ቢሆኑ፣ ስለ አቋማቸው በሚጽፉት መጽሐፍ ላይ ስማቸው እንዲኖር ይፈልጋሉ - ዝናን የሚቃወሙ ዝነኞች ይሆናሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው የገበያ ጉዳይ ነው፡፡ ዋና ዋና ኤኮኖሚያዊ ጥቅሙን ለማንም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ዝናን ግን ቢሞቱ አያጋሩም፡፡.”.
ከዓለም ጋር የምንሟገተው፣ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አቋም የምንወስደው፣ ጐረቤት አገር የምንረዳው፣ ለዝና ሳይሆን ለሀገራችን ጥቅም መሆን አለበት፡፡ አገራችን በዝነኝነቱ ስትታወቅ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ዕድገቷና የህዝቧ አኗኗር ግን ከዚያ ጋር አልሄደላትም፡፡ አለመታደል ነው፡፡ አንድ ወጣት ቻይናዊ፤ ምዕራባውያን አንድን መንግሥት ስለመደገፍ የሚሰብኩትን ስብከት እንዲህ ሲል ይሞግታል፤
“..ሱዳን ውስጥ ያለ አምባገነን የምንደግፈው ነዳጁን ለማግኘት እንዲቻል ነው ትሉናላችሁ፤ የሜዲቫል ንጉሣዊ ሥርዓት ያለውን የሳውዲ አረቢያ መንግሥትስ የምትደግፉት ስለምን ነው?..”
ዛሬ ብቅ ብቅ እያሉ የመጡት የእስያና የላቲን አገሮች፣ ምዕራቡ ዓለም ውስጥ ይግቡ እንጂ በራሳቸው መንገድ ሥርዓቱን እየቃኙ ነው፡፡ የራስ መተማመን መልዕክቱም ለኛም ነው፡፡
“..እኛ አሜሪካኖች፤ ሌሎችን ለውጥን አትፍሩ፤ ከእኛ ተማሩ ስንል ቆይተን. . . አሁን ስናከብራቸው የነበርናቸውን ነጻ ገበያን፣ ንግድን፣ ካገር አገር መንቀሳቀስን ነፃነት እና ቴክኖሎጂያዊ ለውጥን መፍራትና መጠራጠር ጀመርን  እያሉ ነው” (ፋሪድ ዘካርያ)
.. አለም እየተከፈተ አሜሪካን እየተዘጋች ነው - በራሷ ጨዋታ፡፡ ከሀገራችን ጋር በአንድ ይቆጠሩ የነበሩት የእስያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ዛሬ የት ናቸው? እኛ የት ነን? የኋላ ቀርነትና የድህነትን መርዝ ማርከሻ ስንፈልግ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በጫማ ሰፊ አሮጌ እደሳና በመድኃኒት አዋቂ ቤተ-ሙከራ መሃል ሆነን ብዙ ዳክረናል፡፡ መፈክር በማስነገር በፖለቲካ መር አካሄድ ብዙ ፎክረናል፡፡ እጃችን አፈር ጨብጦ ዕድገት ለማምጣት ግን ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ሙስናችን ዛሬም ለከት አጥቷል፡፡ ንግዳችን በራሳችን ሻጥርም በሌሎች ሸርም ውሉ በማይታወቅና ግቡ በማይተነበይ ኤኮኖሚያዊ ዘመቻ ውስጥ ይዳክራል፡፡ በስታቲስቲካዊ አሀዝና በስትራቴጂ ብዛት መልካም ዝና አለን፡፡ ዝና ግን፤
 አንድ ያልታወቀ ገጣሚ፤ .”.ዝና..” ን እንዲህ ጽፎታል፤
..ዝናኮ እንደ ንብ ነው
ዜማ አለው
መውጊያ አለው
ቀን የጨለመ እለት
በሮ እሚጠፋበት
ጉድ ነው! ክንፍም አለው!!..
ቀሪው አገር ነው፡፡ አገሬው ነው፡፡ ዝና አላፊ ጠፊ ነው እንደማለት ነው፡፡
ገበያ ካጣ ጫማ ሰፊና አለሙያው ከሚያክመን አዋቂ ይሰውረን እንጂ፣ አንድ ቀን ራስን መቻል አይቀርም፡፡ ራስን በራስ ማከምን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ራስ ከመግዛት የተሻለ ነገር የለም፡፡
በጥንቶቹ ቀናት የእንግሊዝ የመጨረሻው ጌታ ለታላቁ የህንድ መሪ ለማህተመ ጋንዲ፤ “..እኛ ህንድን ለቀን ትተናችሁ ከወጣን ቀውስ ይፈጠራል..” ይለዋል፡፡ ጋንዲም፤ “..አዎ ቀውስ ይኖራል፤ ግን የራሳችን ቀውስ ነው..” አለው፡፡
በሌሎች እጅ ወድቆ ነጻ ናችሁ ከመባል፣ የራስን ቀውስ ማስታመም ይሻላል እንደ ማለት ነው፡፡ የዚህን ትክክለኛ ትርጉም ከእኛ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ የሚያውቀው የለም፤በተለይ ባለፉት ሁለት የጦርነት ዓመታት ክፉኛ ተፈትነንበታል፡፡ ድህነታችን ለኃያላኑ እጅ ጥምዘዛ ተጋላጭ አድርጎናል፡፡ በተለይ ለአንድ ዓመት ያህል፣ የሉላችን የኢኮኖሚ ጡንቸኞች በአንድ አብረው፣መፈናፈኛ መላወሻ  አሳጥተውን ነበር፡፡ ያለ ይሉኝታ አፍጠውና አግጠው፤ “ወይ እኛ የምንለውን አድርጉ፤ወይ ደግሞ መዘዙን ቻሉት ብለውናል፤በምስጢር ሳይሆን በዓለም ፊት፡፡ በኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ማዕቀቦች መከራችንን ሊያበሉን እንደሚችሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀውናል፡፡ በተግባርም የብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ድጋፍ በመያዝ፣ ፈትነውናል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ም/ቤት፣ ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ለ13 ጊዜ ያህል የውይይት አጀንዳ ሆና መቅረቧን ታሪክ መቼም አይዘነጋውም፡፡ የዓለማችን ቁጥር አንድ የደህንነት ስጋት የሆነችውና ቁጣዋን ኒውክለር በማስወንጨፍ መግለጽ የሚቀናት ሰሜን ኮሪያ ራሷ፣ በጸጥታው ም/ቤት፣ እንደ ኢትዮጵያ፣ የውይይት አጀንዳ ሆና አታውቅም፡፡
ኃያላኑ አገራት፤ “.እኛ እርዳታ ካቆምንባችሁ ቀውስ ይፈጠራል..” ያሉን ጊዜ ልክ እንደ ጋንዲ፤”..አዎ ቀውስ ይኖራል፤ ግን የራሳችን ቀውስ ነው..” ማለት መቻል አለብን፡፡  ይህን በልቦናችን ያኑርልን፡፡


 ፋውንዴሽኑ ከ200 ሚ. ብር በላይ የተመደበለት ፕሮጀክት ከመንግሥት ተቋማት ጋር ተፈራርሟል


      ባለፉት ዓመታት ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸው እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎች ላይ አተኩሮ ሲሰራ የቆየው “ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን”፤ ለ3 ዓመታት እንደሚዘልቅ የተነገረለትን “ውባንቺ ፕሮጀክት” ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በስካይ ላይት ሆቴል በይፋ አስጀምሯል።
ፋውንዴሽኑ፤ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር ጠቅላላ ባጀቱ ከ200 ሚ. ብር በላይ የሆነ የሦስት ዓመታት ፕሮጀክት መፈራረሙ ታውቋል፡፡
 ፕሮጀክቱ፤ በልጅነቷ ከክፍለ ሃገር ወደ አዲስ አበባ መጥታ፣ ከ11-15 ዓመት ዕድሜዋ ድረስ በህፃናት ማሳደጊያ ተቋም ውስጥ ባደገችውና በ17 ዓመት ዕድሜዋ ሊደፍራት በሞከረ አንድ ሰካራም በተገደለችው ውባንቺ ስም ነው የተሰየመው፤ታዳጊዋን ለመዘከር፡፡
“ውባንቺ ፕሮጀክት”፤ ሌሎች ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች፣ የውባንቺ ዓይነት ዕጣፈንታ እንዳይገጥማቸው ለመታደግና የተሻለ እንክብካቤና ደህንነት አግኝተው እንዲያድጉ ታልሞ የተቀረጸ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከትላንት በስቲያ ፕሮጀክቱን ለማስተዋወቅ በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሜሮን አራጋው-  ባደረጉት ንግግር፤ “ሁሉም ህጻናት በዕድሜያቸው መጀመሪያ ላይ የተሻለ እንክብካቤና ክትትል ያገኙ ዘንድ ያገኙ ዘንድ እንደ “ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን” ያሉ የግል ተቋማትን ሰፊ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ጠቁመው፤ ፋውንዴሽኑ በዚህ ረገድ መንግሥትን እያገዘና የመንግሥትን ሃላፊነት እየተወጣ በመሆኑ ምስጋና ሊቸረው  ይገባዋል ብለዋል፡፡
እስካሁንም ቢሮአቸው ከፋውንዴሽኑ ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ሃላፊዋ፤ ወደፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ ተቋሙ ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸው ታዳጊዎች ላይ አተኩሮ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ድጋፍና እገዛ  ለማድረግ  ቃል ገብተዋል፡፡  
በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ “ህጻናቶቻችንን በጤናማና በምቹ ሁኔታ ማሳደግ ሃላፊነታችን ቢሆንም፣ይህንን ሳያገኙ የውባንቺ ዓይነት ዕጣፈንታ የሚገጥማቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እንደሆኑ በመጠቆም፤ከዚህ አንጻር ፋውንዴሽኑ እያከናወናቸው ያሉትን ሥራዎች አመስግነዋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤታቸው፤ ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ ጋር በአንድነትና በትብብር ለመሥራት ፍላጎትና ፍቃደኝነት እንዳለውም ሚኒስትሯ  አስታውቀዋል፡፡
“ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን” ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል፣ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸውን እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎች ከማህበረሰቡ ነጥሎ ከማሳደግ ይልቅ የቤተሰብ ይዘት ያላቸውን (ፋሚሊ ሃውስ) ከፍቶ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ማኖር፣ማሳደግና ማስተዳደር በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ተቋሙ በተጨማሪም፣ በመንግሥት ሥር በሚተዳደሩ ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ለሚኖሩ በርካታ ቁጥር ላላቸው ታዳጊዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ከማመቻቸትና ወጪ ከመሸፈን ባሻገር ሙሉ የህክምና የአልባሳትና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ ድጋፎችን እንደሚሰጥ እንዲሁም የትምህርት- ጥናት አገልግሎትና የሥነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚያደርግም ጠቁሟል፡፡
በዚህ መልኩ አጠቃላይ ድጋፍ በማድረግም፣ ዕድሜያቸው የደረሰ ታዳጊና ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ከተቋሙ እንዲወጡና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ፋውንዴሽኑ ይገልጻል፡፡

Saturday, 18 March 2023 20:22

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

 “መሃይምነትና ድንቁርና ይለያያሉ”


     “...በነገራችን ላይ መሃይምነትና ድንቁርና ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። መሃይም የሚባለው የትምህርት እድል ያላገኘ ነው። ድንቁርና ግን የትምህርት እድልም አግኝቶ በመሃይምነት ግርሻ የተጠቃው ነው። ፈረንጆች ምን ይላሉ --- arrogance (እብሪተኝነት) Ignorance (አለማወቅን) ያመጣል።  arrogance እና  Ignorance ይመጋገባሉ። መሃይምነት ሲያገረሽብህ እብሪተኛ ትሆናለህ፤ እብሪተኛ ስትሆን ደግሞ የበለጠ መሃይምነት ያገረሽብሃል። እናም ብዙዎቻችን በዲግሪያችን ጀርባ በድንቁርና ነው የምንኖረው። ሰውም እንዳይመክረን ዲግሪ አላቸው ይባላል። በእድርም ስትሄድ ዶክተር ይናገር ነው የሚባለው። ግን ሰውየው መሃይምነት ውስጥ ነው ያለው።.... እና ምንድነው እየሆነ ያለው ብላችሁ ያያችሁት እንደሆነ... መደማመጥ የሌለው፣ መነጋገር የሌለበት፣ የማንተማመነው፣ ለችግሮቻችን መፍትሔ የማናገኘው የምሁር ቁጥር እንጂ የአዋቂ ቁጥር ስለሌለ ነው። ለምን ያላችሁ እንደሆነ፤ አብዛኞቻችን በመሃይምነት ግርሻ ውስጥ ስላለን ነው። የዲግሪ ፎቶ በየቤቱ ስትሄዱ ግድግዳ ላይ ታያላችሁ። በትክክል ያ የሚያሳየው ሰውዬው በመሃይምነት መኖሩን ነው። ምክንያቱም ማረጋገጫው ያ ብቻ ነው። ሌላ ምን ያሳያል? ምን እናሳያለን ሌላ?....”
 (ዶ/ር አለማየሁ አረዳ፣ በአማራ
ቴሌቪዥን ከተናገሩት)
____________________________________

                 “እንደ ብልህ አብረን መኖር ካልቻልን፣ እንደ ሞኝ አብረን እንጠፋለን”
                      ዘላለም ጥላሁን


       ያለፈውን ዘመን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ” እንዳለው ሎሬቱ፣ የኢትዮጵያ ልጆች ያልሞከሩት የእርስ በርስ ትግል የለም። ከወረቀት እስከ ጥይት፣ ከሐሳብ እስከ ሒሳብ፣ ከመንደር እስከ ሀገር፣ ከዘር እስከ ስናይፐር፣ ከረሃብ እስከ ጥጋብ፣ ከሰፈር ንትርክ እስከ ሀገር ታሪክ፣ ከገጀራ እስከ ሚሳኤል ሁሉንም አብሮ የመጥፊያ መንገዶችን ሞክረዋል።
ረጅሙ የንትርክ ታሪካችን፣ አድዋ፣ ማይጨውንና ካራማራን በመሰሉ አጭር የአብሮነት ታሪኮች ባይገመድ ኖሮ፣ ይኸኔ  ተበትነን ነበር። “እንደ ብልህ አብረን መኖር ካልቻልን፣ እንደ ሞኝ አብረን እንጠፋለን” እንዲሉ፣ መፍትሔው አብሮና አብ’ሮ መኖር ነው።
አብሮ ለመኖር “ትናንትን በይቅርታ እያለፉ፣ የዛሬን ቀዳዳ እየሰፉ፣ ነገን በተስፋ መንደፉ” ያልሞከርነው መንገድ ነው። ከሞከርነው ያልሞከርነው ብዙ ነው።
አብረን ከመጥፋት ይልቅ አብረን ለመኖር የምትመች ሀገር ለመፍጠር ህሊናዊ አስተውሎትና ብስለት ከመሪ እስከ ተመሪ ተነፈግን። ሁሉም ነገር የጅብ እርሻ ሆነ-እየጎለጎሉ ማረስ፣ እየገነቡ ማፍረስ።  ህሊናችን በጥላቻ ቆሸሸ፣ በመጠላለፍ ሟሸሸ። ተስፋችንና ህልማችን ሁሉ እንደ አመዳይ ወየበ። ስጋትና ብሶት የየቀን ቀለባችን ሆነ። ሁላችንም ከቃላችን ከህሊናችን ሸሸን።
ለአንድ ህይወታችሁ፣ ለአንድ ሆዳችሁ፣ ለአንድ የስልጣን ምኞታችሁ፤ ሀገርንና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ተንኮል ውስጥ የገባችሁ አደብ/ቀልብ ብትገዙ ምን አለበት? ቆም ብላችሁ ህሊናችሁን ጠይቁ፣ እራሳችሁ ለራሳችሁ ጥያቄ አርቅቁ (ህዝብማ መች ትሰሙና?)።
ሀገሪቱን  ሌላ ሴራ፣ ሌላ መከራ፣ ሌላ ኪሳራ ውስጥ  አትክተቷት። ቢያንስ ቢያንስ መጀመሪያ ከራሳችሁ ከህሊናችሁ ታረቁ። ከዚያ መንገዱ ቀላል ይሆናል.... ያልተሞከረውን ሞክሩ፣ ያልተሄደበትን መንገድ አሳብሩ..... .መጀመሪያ ከህሊናችሁ ታረቁ፣ ነፃ ውጡ። ነፃ ያልወጣ ህሊና፣ እንኳን ህዝብን ግለሰቡን ነፃ አያወጣም። አሊያ “እንደ ብልህ አብረን መኖር ካልቻልን፣ እንደ ሞኝ አብረን እንጠፋለን”፡፡
________________________________________

                      አጠቃላይ ቅኝት "እስከ መቼ በአጼዎቹ እያሳበብን እንሳነፋለን?"


         ሰሞኑን በመጠኑ የቃኘነዉ ኪታብ /ኢንቲሻር…/ ‹‹ታሪካችን በወጉ አልታጻፈም ወይም ሆነ ተብሎ ተዘሏል፤ ጠልሽቷል ወዘተ›› በሚለዉ በኃይማኖትና በዘዉግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ዘንድ በተለመደ ሙሾ የተወጠነ ነዉ፡፡ በኪታቡ መግቢያ (ተምሂድ) ለዚህ ሙሾ ይሁንታ ተችሮ ለዚሁ አገልግሎት በአማርኛ የተጻፈች አንዲት አርቲክል እንደወረደች ወደ ዐረብኛ ተተርጉማ ነግሳበታለች፡፡
ጥንትም ሆነ በቅርቡ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጻፍ ብዕር ያነሱ ጸሀፍት፤ Selection, Omission, Demonization, Interpretation or misinterpretation የተሰኙ አራት ዘዴዎችን በመጠቀም  ታሪክ እንዳዛነፉ አርቲክሏ ታትታለች፡፡ ሌሎች ወንድሞችም አርቲክሏን የመጽሀፍ መግቢያ ሲያደርጓት ታዝቤያለሁ፡፡
በወጉ ያልተመዘገበ የታሪክ ክፍል ሊኖር ስለመቻሉ አልከራከርም፡፡ ሆኖም ታሪክ ላለመዘገቡ እንደ ምክንያት ሊመዘዙ ከሚችሉ በርካታ ሰበዞች መካከል ሴራን ለይቶ ሁሉንም ችግር በርሱ ላይ መደፍደፍ  የ‹‹conspiracy mentality›› አባዜ ነዉ፡፡ ለታሪክ ዘገባዎች ያልተሟሉ መሆን ሊጠቀሱ ከሚችሉ ሰበቦች መሀል፡-
1.  የጽሁፍ ባህል አለመዳበርን ማንሳት ይቻላል፡፡ በአሀዝ ረገድ በርከት የሚሉ የሀገራችን ጎሳዎችና ነገዶች ሳይቀር የጽሁፍ ባህል ሳያዳብሩ ለዘመናት በመኖራቸዉ ታሪካቸዉን በአፈታሪክ መልክ ከትዉልድ ትዉልድ ከማስተላለፍ በስተቀር በጽሁፍ መዝግበዉ ማሻገር አልቻሉም፡፡ በጽሁፍ ያልተሰነደ ነገር ደግሞ በጊዜ ሂደት መጥፋቱ፣ መበረዙና መከለሱ፣ መጨመሩና መቀነሱ አይቀርም። የጽሁፍ ባህል በአንጻራዊነት የዳበረባቸዉ አካባቢዎች ጸሀፍት የሚጽፉት በዙሪያቸዉ ስላለዉና ስለሚያዉቁት ህዝብ፣ ሀይማኖትና ባህል፣ በተለይም ደግሞ ስለ ነገስታቱ ገድል እንደሆነ ዕሙን ነዉ፡፡ ወንዝ ተሻግረዉ የሌላዉን ለመጻፍ የቦታ ርቀት፣ የቋንቋ አለማወቅ፣ የባህል ወዘተ ዉስንነቶች እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ አንዳች አጋጣሚ ሲፈጠር የሌላዉን አካባቢ ከመጻፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ አባ በሕሪይ የተባሉ የጋሞ መነኩሴ፣ በ16ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበረዉን የኦሮሞ ታሪክ ክፍል በዓይን ምስክርነት አሳምረዉ ከትበዉታል፡፡ ይህ የመነኩሴዉ  ሥራ፣ የዚያ ዘመን ታሪክ አብይ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ ‹‹የአባ ባሕሪይ ድርሰቶች…›› በሚለዉ ድንቅ መጽሀፋቸዉ፤ ግዕዙን ወደ አማርኛ በመመለስ ከሌሎች የታሪክ ምንጮች ጋር እያሰናሰሉ ጠቃሚ ዳሰሳ አድርገዉለታል፡፡ አሁናዊ ሁኔታዎችን ሳይቀር በወጉ ለመረዳት በእጅጉ ስለሚጠቅም ብታነቡት ታተርፉበታላችሁ፡፡
2.  በሙስሊሙ ወገን የጽሁፍና የምርምር ባህል ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የሀገራችን ሊቃዉንት የአትኩሮት ማዕከል ሀይማኖታዊ መጽሐፍትን ማዘጋጀትና መተንተን፣ እንዲሁም የነብዩ ሙሀመድ ዉዳሴ (መድህ) በመሆኑ፣ የሀገር ቤቱ የእስልምና ታሪክ በነርሱ ተገቢዉ ትኩረት አልተቸረዉም፡፡ ሊቃዉንቶቻችን ለሀይማኖታዊ ትምህርት አገልግሎት የሚዉሉ ኪታቦችን በአስደናቂ ብቃት መጻፋቸዉና ማብራሪያ (ሸርህ) መስራታቸዉ የሚታወቅ ነዉ፡፡ የነብዩ ዉዳሴ (መድህ) ድርሳኖቻቸዉም መሳጭና ዘመን ተሻጋሪ ናቸዉ፡፡ ዓለማቀፍ ዕዉቅናን ከተጎናጸፉ ጸሀፊዎቻችን መካከል በ662 ሂጅሪያ የሞቱት የሀዲስ ጥናት አዋቂ ጀማሉዲ ዐብደላህ እብን ዩሱፍ፤ ‹‹ነስቡራያ ፊተኽሪጂ አሀዲሲል ሂዳያ›› የተባለ መጽሐፍ አዘጋጅተዉ ለዓለም አሰራጭተዋል፡፡ በ643 ሂጅሪ የሞቱት የሀነፊ መዝሀቡ ሊቅ ፈኽሩዲን ዑስማን እብን ዐሊ ‹‹ተብይነል ሀቃኢቅ ፊሸርህ ከንዘ ደቃኢቅ››፣ ‹‹ሸርህ ጃሚዑል ከቢር›› የተሰኙና ሌሎችንም ለሀነፍይ መዝሀብ በዓለማቀፍ ደረጃ ‹‹ሪፈረንስ›› የሆኑ ዕዉቅ ኪታቦችን አዘጋጅተዋል፡፡
በ1230 ሂጅሪይ የሞቱት ጀማንጉስ፣ በ1240 የሞቱት ተማሪያቸዉ ሸኽ ሰይድ እብን ፈቂህ ዙበይር፣የራያዉ ጀማሉዲን አልዐኒ ወዘተ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ከሠሩ ሊቃዉንቶቻችን መካከል ናቸዉ፡፡ በዚህ ረገድ የሀገራችን ዑለሞች አስተዋጽኦ በ‹‹ኢንቲሻር…›› ኪታብ ዉስጥ በሚያምር ሁኔታ ተጽፏል። በነብዩ ዉዳሴ (መድህ) ቅኔዎች ረገድም እነ ሸኽ ጫሌ የመሳሰሉ ማዲሆች በዐረብኛም በአማርኛም እጅግ መሳጭ ሥራዎችን ለሀገር አበርክተዋል፡፡ አበልቃሲም የሊቃዉንቶቻችንን ብቃት ሲመሰክሩ፡-
‹‹በዚህ ዘመን በሙስሊሙም ሆነ በዐረቡ ዓለም ከሚገኙ ዑለሞች ዉስጥ የፊቅህና የነህዉ ረቂቅ ሚስጥራትን በመረዳቱ ረገድ የሀበሻ ዑለሞችን የሚገዳደር እንደሌለ ነዉ የማምነዉ። ይህም የሆነዉ የመማር ማስተማር ሂደታቸዉ የተበጠረና የነጠረ በመሆኑ ነዉ፡፡›› (አዕላም 159)
ሆኖም ይህን ያህል ብቃት ላላቸዉ ሊቃዉንቶቻችን ታሪክን መዝግቦ ለትዉልድ ማስተላለፍ የትኩረት ማዕከላቸዉ አልነበረም። አስበዉበት ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያችንን ታሪክ የተሟላ የሚያደርጉ ግሩም ጥናቶችን እናገኝ ነበር፡፡
ስለዚህ ታሪክን መዝግቦ የማስተላለፍ፣ ቅርስን ጠብቆ ለትዉልድ የማስቀረት ወዘተ ባህል በሊቃዉንቶቻችን ዘንድ እምብዛም አለመኖሩ ለታሪካችን በወጉ አለመጻፍ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህም ስለሆነ አብዛኞቹ የሊቃዉንቶቻችን (መሻኢኾቻችን) ገድሎች የተላለፉት በጽሁፍ ሳይሆን በአንደበት (በቂሷ) ነዉ፡፡ ታሪክን በጽሁፍ ያስተላለፉ በጣት የሚቆጠሩ ሊቃዉንት ቢኖሩንም የሚጽፉት በዐረብኛ በመሆኑና መኖሩም ስለማይታወቅ ለሀገራችን ታሪክ ጸሀፊዎች እንደ ምንጭ አላገለገለም፡፡ ከነዚህ የዐረብኛ ሥራዎች መካከል የህትመት ብርሀን ያገኙት ኢምንት ናቸዉ፡፡ አሁን አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል የተወሰኑ ኪታቦች ለሁለተኛና ለሶስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናት እየተሠራባቸዉ መሆኑ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ ከሚፈለገዉና ከሚጠበቀዉ አኳያ የተሠራ ነገር አለ ለማለት ይቸግራል፡፡
በጥቅሉ በሙስሊሙ ወገን የተከወነዉን የኢትዮጵያ ታሪክ ክፍል፣ እንዲሁም ቅርሶቻችንን እምብዛም ጠብቀን ማቆየት አልቻልንም። ይህ መሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ያልተሟላ እንዳደረገዉ የታሪክ ጸሀፊዎች ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሀይሌ በአባ ባህሪ ድርሰቶች ቅኝታቸዉ ዉስጥ ይህን መሰል ነጥብ አንስተዉ ‹‹ያልተሟላዉን ስለማሟላት›› ሀሳብ አጭረዋል፡፡ እናም በራስ በኩል የተፈጠረን ክፍተት ‹‹ከአጼዎቹ›› ወይም ከ‹‹ጭቆና›› እያገናኙ መነጫነጭ ፍትሀዊ አይደለም ብቻ ሳይሆን፤ ችግሩ በትክክል ታዉቆ መፍትሄ እንዳይበጅለት እንቅፋት ይሆናል፡፡
ጥንት ይቅርና አሁንም በዕዉቀት፣በተለይም በታሪክ ዕዉቀት ምርትና ልማት ዘርፍ ሁነኛ ሚና አለን ብዬ አላምንም፡፡ ይህ የሆነዉ ‹‹አጼዎቹ›› ስለከለከሉን ወይም ‹‹ስለጨቆኑን››፣ ወይም ደግሞ ‹‹ደብተራዎች›› ስላሴሩብንና ‹‹ኦርቶ-አማራ›› ስላቀበን ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ ለትምህርትና ለዕዉቀት ልማት ያለን ግንዛቤ እጅግ አናሳ በመሆኑ ነዉ፡፡ ምን ያህል የፊሎሎጂ፣ የታሪክ ወይም የአንትሮፖሎጂ ወዘተ ተማሪዎች አሉን? ካሉት ተማሪዎቻችን መሀል ምን ያህሎቹ ትምህርታቸዉን በወጉ ያጠናቅቃሉ? ስንቶቹስ በተማሩበት መስክ ይሠራሉ? ስንቶቹ ወደ ላይ በትምህርት ይገፋሉ? ከነርሱ መካከል ብቁ ተመራማሪዎች ምን ያህል ናቸዉ? የትኞቹስ በሙስሊሞች ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን ይሠራሉ? ለመሥራት ቢያስቡስ ምርምር የሚጠይቀዉን የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ሊሰጥ የሚችል የማህበረሰብ ክፍል ወይም ተቋም አለን? የቅርስ ጥበቃ ባህላችን ምን ይመስላል? ለነዚህና መሰል ጥያቄዎች የምንሰጠዉ መልስ ተጨባጫችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገዉ ወጣት የፊሎሎጂ ዶክተርና ተመራማሪ ሁኔታዎች ስላልተመቹት ዕድሜ ልኩን የለፋበትን ትምህርትና ምርምር እርግፍ አድርጎ ትቶ ልብስ እንደሚቸረችር አዉቃለሁ፡፡ አንድ ጉምቱ የታሪክ ፕሮፌሰር -ልክ እንደ ሀዲስ ሊቁ ሀጅ ራፊዕ- በደሳሳ የቀበሌ ጎጆ ዉስጥ ኖሮ አልፏል፡፡ ዕዉነታዉ ይህ ሆኖ እያለ ‹‹እገሌ ታሪኬን አልጻፈልኝም›› እያሉ አሁንም ድረስ ማላዘን፣ አጼዎችን መዉቀስ፣ የታሪክ ሰናጆቻችንን ‹‹በሙስሊም ጠልነት›› መክሰስና ሥራዎቻቸዉን ማራከስ ተገቢነቱ አይታየኝም፤ ጠቀሜታም የለዉም፤ ለችግራችንም መፍትሄ አይሆንም፤እንዲያዉም ራሳችንን በወጉ ፈትሸን ችግራችንን እንዳንረዳና ወደትክክለኛዉ አቅጣጫ ጉዞ እንዳንጀምር ማሳነፊያ ይመስለኛል፡፡ ችግርን ወደ ሌሎች ማላከክ ቅንጣት መፍትሄ አይሆንም፡፡ እስከ መቼ በአጼዎቹ እያሳበብን እንሳነፋለን?
3.  የሀገራችን ታሪክ ጸሀፊዎች ታሪክን በጎሳና በሀይማኖት ሸንሽነዉ የመጻፍ ልምድ እምብዛም አላቸዉ ብዬ አላምንም፡፡ በነርሱ አዕምሮ ዉስጥ የነበሩት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን እንጂ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ … አይደሉም። ስለአጤ ዮሀንስ ሲጽፉ ትግሬነታቸዉ፣ ስለአጤ ቴዎድሮስ ሲጽፉ አማራነታቸዉ፣ ስለጎበና ዳጬ ወይም ስለጅማ አባጅፋር ሲጽፉ ኦሮሞነታቸዉ ከጸሀፊዎቻችን ስሌት ዉስጥ እምብዛም አልገባም፡፡ ቢበዛ ከሸዋ፣ ከጎንደር፣ ከሀረር ወዘተ እያሉ አካባቢ ሊጠቅሱ ይችላሉ እንጅ ዘዉግ ዋነኛ ጉዳያቸዉ አልነበረም፡፡ ክስተቶችን (ለምሳሌ ዶጋሊን፣ የአምባላጌን፣ የጉደትና ጉራን ወይም የአድዋን ፍልሚያዎች) ሲዘግቡ የሚያተኩሩት በሂደቱና ‹‹በራስ እገሌ የተመራ ጦር እንዲህ አደረገ›› በሚሉት ጉዳዮች ላይ እንጅ በጎሳና ነገድ ሽንሸና ላይ አይደለም፡፡ የዘዉግ/ብሄር ነገር መላቅጡን እያጣ የመጣዉና የፖለቲካ መቧደኛ በመሆን ሀገር ሊያፈርስ የደረሰዉ ከ1960ዎቹ ወዲህ ነዉ፡፡ ስለዚህ ከዚያ በፊት ታሪክ የመዘገቡ ወገኖችን ከዚያ ወዲህ በመጣ እኩይ አስተሳሰብና ዝንባሌ መመዘን ተገቢ አይደለም፡፡
ባይሆን ለክስተቶች ሀይማኖታዊና መንፈሳዊ ትርጓሜ (interpretation) መስጠት የዚያ ዘመን አጻጻፍ ባህሪ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ጸሀፊዉ የርሱ ወገን ሲያሸንፍ ‹‹መላእክት ረድተዉት፣ ፈረሰኛዉ ጊዮርጊስ አብሮት ተዋግቶ፣ታቦቱ ተከትሎት…›› የሚል ምክንያት ይሰጥና ሲሸነፍ መሸነፉን ዘግቦ፣ ግና ከመንፈሳዊነት ጋር ሊያይዘዉ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሰይጣን ከጠላቶቹ ጎን ስለሆነ ወይም ጾም ጸሎት ስለተዘናጋ ወይም የማርያምን ቤተ ክርስቲያን ስላላሠራ፣ ስለቷን ስላላስገባ፣ በባዕል ቀን ስራ ስለሰራ ወዘተ›› እያለ ለሽንፈቱ መንፈሳዊ ምክንያት ይደረድር ይሆናል። ይህ ዓይነቱ አጻጻፍ በየትኛዉም ሀይማኖት ታሪክ ጸሀፊዎች ዘንድ የተለመደ ነዉ፡፡ ‹‹ፉቱሀል ሀበሽ››ን ለናሙና በማየት ይህን ማጤን ይቻላል፡፡ ዐረብ ፈቂህ የኢማሙን እንቅስቃሴዎች፣ ዉጊያዎች ማፈግፈጎች፣ ድሎችና ስኬቶች በአንድ በኩል፣ የተቃራኒያቸዉን ሁለንተናዊ ድርጊቶችና እንቅስቃሴዎች፣ በሌላ በኩል የሚገልጹበትና የሚተረጉሙበት መንገድ ከመንፈሳዊና ሀይማኖታዊ ቃናና ዝንባሌ ዉጭ አይደለም፡፡ የጥንት ዘመን የታሪክ አጻጻፍ መንገድ እንደዚሁ ስለሆነ ገለልተኛ ተመራማሪ ከሁለቱም ወገን መንፈሳዊ ትርጉሞችን፣ የተጋነኑ ገለጻዎችንና የዉገና ዝንባሌዎችን አበጥሮ በመለየትና ወደ ጎን በመተዉ ክስተቶችን ብቻ ወስዶ በሳይንሳዊ መንገድ ያጣራል፣ ያቀናጃል፣ ይተነትናል። የዘመናዊ የታሪክ አጻጻፍ ጅማሮ የሆኑት ተክለጻድቅ መኩሪያ ‹‹የግራኝ አህመድ ወረራ›› መጽሀፋቸዉ ዉስጥ በ‹‹ፉቱሀል ሀበሺ››ም በግእዙም የታሪክ ድርሳናት ወገን የሚገኙ ተመሳሳይ ገለጻዎችንና ግነቶችን እየተከታተሉ በመመርመር ሲሀይሱ በብዛት ይስተዋላል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሄር ጭቆና ነበር›› የሚለዉ ስሁት ተረክ፤ ሀሰቶች ተደርተዉበትና አለቅጥ ተጋኖ አየሩን በማጨናነቁ፣ ብዙ ጸሀፍት የዚህ ተረክ ሰለባ ሲሆኑና ከርሱ ባሻገር ለማየት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ ይህ የጭቆና ተረክ ባለፉት 700 ዓመታት የጊዜ ሂደት ዉስጥ ተፈጽመዋል ‹‹የሚባሉ›› ‹‹ክፉ ነገሮች›› ሁሉ ለአማራ የሚያሸክም አይዲዮሎጂ ሆኖ ይህን መከረኛ ህዝብ ላለፉት 30 ዓመታት ሲያስጨፈጭፈዉ ኖሯል፡፡ አሁንም እያስጨፈጨፈዉና በሚሊዮኖች እያፈናቀለዉ ይገኛል፡፡ ‹‹ኢንቲሻሩል ኢስላም…›› መጽሐፍ ከዚሁ ‹‹የብሄር ጭቆና›› ዝንባሌ ረገድ የደረሰበት ተጽእኖ ይኖር ይሆን? በምን ያህል መጠን? የሚሉ ጉዳዮችን በሌላ ጊዜ ከሌሎች መጽሐፍት ጋር በማሰናሰል እንመለስባቸዉ ይሆናል፡፡
እስልምና ለዘለዓለም ጭቆና የሚዳርግ ‹‹ንጥረ-ነገር›› በዉስጡ የያዘ፣ መጨቆን የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሁልጊዜ ‹ቀደር›› እስኪመስል ድረስ የሃይማኖት ጭቆና አቀንቃኞች ይህን የ‹‹ተጨቁነን ኖረናል›› ተረክ አብዝተዉ ሲያራግቡት ይስተዋላል፡፡ ለቅሶን ለፖለቲካ ዓላማ የሚጠቀሙ ወገኖችም እጅግ አጋነዉና አግዝፈዉ፣ ወይም የተሳሳተ የትንተና ስልትን ተጠቅመዉ በዚሁ ሙሾ የተቃኙ ድርሳን ማዘጋጀታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ተረክ በ‹‹ኢንቲሻር…›› ኪታብ ላይ ጥላዉን በምን ያህል መጠን እንዳጠላ ተገቢዉን ፍተሻ ማድረግ አስፈላጊነቱ እንዳለ ሆኖ ተረኩ የፈጠረዉን ጭጋግ የሚገፍና በኢትዮጵያ የሙስሊሞችን የድልና የስኬት ክንዋኔዎች ጨምሮ ነባራዊዉን ሁኔታ ሳያጋንንና ሳያቀጭጭ እንዳለ የሚያቀርብ መጽሐፍ በባለሞያዎች የመሠራቱ አስፈላጊነት አሁን ጊዜዉ ይመስላል፡፡
የያዝነዉን መጽሀፍ ቅኝት ለጊዜዉ እዚህ ላይ ልግታ፡፡ የቀሩ ነጥቦች እንዳሉ ዕሙን ነዉ። ሆኖም ለፌስቡክ አቅም እስካሁን የቀረቡት ሀሳቦች ከበቂ በላይ ናቸዉ፡፡ ቀሪዎቹ ሰፋ ባለ ሌላ ‹‹ፕላትፎርም›› ይቀርቡ ይሆናል። ከመጽሀፉ ዉስጥ ለናሙና ያየናቸዉና ሌሎችም የ‹‹ፋክት››፣ የቅኝትና የትንታኔ እንከኖች እንደተጠበቁ ሆኖ መጽሐፉ በዉስጡ ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ በመሆኑ ማንበቡ አትራፊ ያደርጋል፡፡
በመጨረሻም ደራሲዉ ዓመታትን ፈጅተዉ አድካሚዉን የምርምር ሥራ በማከናወን ለሀገራችን የታሪክ ምርምር ግብአት የሚሆን ድርሳን ስላበረከቱልን ሊመሰገኑ ይገባል። አሁን ያላቸዉን ጥሩ የምርምርና የመጻፍ ክህሎት የበለጠ አዳብረዉ ሌሎች ጠቃሚ የጥናት ዉጤቶችን እንደሚያስነብቡን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በወርሀ ረመዳን ሁኔታዎች ከተመቻቹ ከወሩ መንፈሳዊ ድባብ ጋር የሚሄዱ ጽሁፎችን አጋራ ይሆናል፡፡ የመጽሀፍት ዳሰሳዎችና ሌሎች አጀንዳዎችን ግን ከረመዳን ማግስት እመለስባቸዋለሁ፡፡
መልካም የዒባዳ ጊዜ!!!

Page 10 of 646